Administrator

Administrator

በአለማችን የተለያዩ አገራት በድምሩ 150.8 ሚሊዮን ያህል ህጻናት በተመጣጠነ ምግብ እጥረት ሳቢያ የሚከሰት የመቀንጨር ችግር ተጠቂዎች መሆናቸውንና ተጨማሪ 50.5 ሚሊዮን ህጻናትም የሰውነት ክብደታቸው ከሚገባው በታች መሆኑን አንድ አለማቀፍ ሪፖርት አስታውቋል፡፡ከትናንት በስቲያ የወጣው አለማቀፍ የስነምግብ ሪፖርትን ጠቅሶ አልጀዚራ እንደዘገበው፤ የህጻናት መቀንጨር በሁሉም የአለማችን አገራት የሚታይ ችግር ቢሆንም ከአለማችን አገራት በርካታ ቁጥር ያላቸው ህጻናት የችግሩ ሰለባ የሆኑባት ቀዳሚዋ አገር ህንድ ናት፡፡
የመቀንጨር ችግር ሰለባ ከሆኑት የአለማችን ህጻናት ከ35 በመቶ በላይ የሚሆኑት በህንድ እንደሚገኙ የጠቆመው ሪፖርቱ፤ በአገሪቱ 46.6 ሚሊዮን ህጻናት የመቀንጨር ችግር ሰለቦች መሆናቸውንና ተጨማሪ 25.5 ሚሊዮን ህጻናትም ከቁመታቸው አንጻር ተገቢው የሰውነት ክብደት እንደሌላቸው አመልክቷል፡፡በ140 የአለማችን አገራት ላይ የተሰራውን ጥናት መሰረት አድርጎ ይፋ የተደረገው ሪፖርቱ፣ የመቀንጨር ችግር ድሃ አገራትን ብቻ ሳይሆን ያደጉ አገራትንም ጭምር እያጠቃ እንደሚገኝና አለማችን በመቀንጨር ችግር ሳቢያ በየአመቱ 3.5 ትሪሊዮን ዶላር ያህል እንደምታጣም አክሎ ገልጧል፡፡

 የህዝብ ብዛት ፈተና በሆነባትና ኢኮኖሚያዋ በማያወላዳው ሌሴቶ፤ ከፍተኛ ተከፋይ ከሆኑ ዜጎች መካከል የሚጠቀሱት የአገሪቱ የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባላት፣ደመወዛቸው በእጥፍ እንዲጨመርላቸው ጥያቄ ማቅረባቸውን አጃንስ ፍራንስ ፕሬስ ዘግቧል፡፡የስራ አጥነት ችግር 39 በመቶ ያህል በደረሰባት ሌሴቶ፣የፓርላማ አባላቱ የደመወዝ ጭማሬ እንዲደረግላቸው ጥያቄ ማቅረባቸውን ተከትሎ፣ የአገሪቱ ጠቅላይ ሚኒስትር ቶማስ ታባኔ፣ ለፋይናንስ ሚኒስትሩ፣ የደመወዝ ማስተካከያ ዕቅድ እንዲያወጡና እንዲያቀርቡ ትዕዛዝ መስጠታቸውንም ዘገባው አመልክቷል።
የፓርላማ አባላቱ ያቀረቡት እጥፍ የደመወዝ ጭማሪ ተቀባይነት የሚያገኝ ከሆነ፣ አንድ የሌሴቶ ፓርላማ አባል በወር 5 ሺህ 344 ዶላር ያህል ደመወዝ እንደሚበላ የጠቆመው ሪፖርቱ፤ በአገሪቱ መደበኛ የመንግስት ሰራተኞች የሚያገኙት ወርሃዊ ደመወዝ በአማካይ 144 ዶላር ብቻ እንደሆነም ገልጧል፡፡
75 በመቶ ያህሉ ህዝቧ በገጠር እንደሚኖርና ኑሮውን በግብርና ላይ መሰረት ያደረገ እንደሆነ የገለጸው ዘገባው፤ ግማሽ ያህሉ የአገሪቱ ቤተሰብ ኑሮውን የሚመራውም፣ በደቡብ አፍሪካ፣ የስደት ኑሮን የሚገፋ ወዳጅ ዘመዱ በሚልክለት የድጎማ ገንዘብ እንደሆነ አክሎ አስረድቷል፡፡


 ግዙፉ የአለማችን የኤሌክትሮኒክስ አምራች ኩባንያ የደቡብ ኮርያው ሳምሰንግ፤ “የጋላክሲ ስማርት ሞባይል ስልኮቼን የማመርትበትን ቴክኖሎጂ በህገወጥ መንገድ መንትፈው፣ ለቻይና ኩባንያዎች በመሸጥ፣ 13.8 ሚሊዮን ዶላር ያህል ገንዘብ አግኝተዋል” በሚል በ8 ሰራተኞቹና ፈጠራዎቹን ገዝተዋል በተባሉት ሁለት የቻይና ኩባንያዎች ላይ ክስ መስርቷል፡፡
ኩባንያው ያወጣውን መግለጫ ጠቅሶ ብሉምበርግ እንደዘገበው፤ ሳምሰንግ በ8ቱ ሰራተኞቹ ላይ ክስ የመሰረተው፣ የጋላክሲ የሞባይል ስልኮቹን ስክሪን የሚሰራበትንና 1333.5 ሚሊዮን ዶላር ያህል ወጪ ያደረገበትን ኦርጋኒክ ላይት ኢሚቲንግ ዳዮድ የተሰኘውን የቴክኖሎጂ ፈጠራውን መንትፈው፣ ለሁለት የቻይና ኩባንያዎች ሸጠውብኛል በሚል ነው፡፡
በአለማችን የስማርት ፎን ገበያ ቀዳሚነቱን የያዘው የደቡብ ኮርያው ሳምሰንግ፤ “የቻይና ኩባንያዎች በራሳቸው ፈጠራ በገበያ ላይ መወዳደር ሲያቅታቸው፣የቴክኖሎጂ ፈጠራዎቼን መዝረፍ ጀምረዋል” በሚል በኩባንያዎቹ ላይም ክስ መመስረቱን ዘገባው አመልክቷል፡፡
የቻይና ኩባንያዎች በአገሪቱ መንግስት የተደገፈ የቴክኖሎጂ ፈጠራዎች ምንተፋ ላይ በስፋት ተሰማርተዋል በሚል አሜሪካም በተደጋጋሚ ቻይናን ስትወነጅል እንደቆየች ያስታወሰው ዘገባው፤ የተለያዩ የአሜሪካ ኩባንያዎችም የፈጠራ መብቶች ጥሰት ፈጽመዋል በሚል በተለያዩ የቻይና ኩባንያዎችና በሃላፊዎቻቸው ላይ ክስ መመስረታቸውንም አክሎ ገልጧል፡፡


    የተባበሩት መንግስታት ድርጅት የትምህርት፣ የሳይንስና የባህል ተቋም ዩኔስኮ፤ የሬጌ ሙዚቃን በአለማቀፍ መድረክ በተለያዩ ጉዳዮች ዙሪያ ውይይት ለመፍጠር ባበረከተው አስተዋጽኦ በአለም ቅርስነት መዝግቦታል፡፡
ሬጌ ኢፍትሃዊነትንና ጭቆናን የመሳሰሉ ጉዳዮችን ለመቃወምና ለውጥን ለማቀጣጠል ጥቅም ላይ ሲውል የኖረ ተወዳጅ የሙዚቃ ስልት መሆኑን ከግምት ውስጥ በማስገባት፣ በአለም ቅርስነት እንደመዘገበው ተቋሙ ከትናንት በስቲያ ባወጣው መግለጫ አስታውቋል፡፡
ፍቅርና አንድነት፣ ፍትህና እኩልነት ሲዘመርበት የኖረውና ከጃማይካ ምድር የፈለቀው የሬጌ የሙዚቃ ስልት፤ “በቀጣይ ዘመናትም የሁሉንም ብሶት የሚያሰማ ድምጽ ሆኖ ይቀጥላል” ሲልም ተቋሙ በመግለጫው አመልክቷል፡፡
የጃማይካ መንግስት የሙዚቃ ስልቱ በዩኔስኮ ቅርስነት እንዲመዘገብ ከፍተኛ ጥረት ሲያደርግ እንደነበር የዘገበው ሮይተርስ፤ እ.ኤ.አ በ1960ዎቹ መጨረሻ በጃማይካ እንደተፈጠረ የሚነገረው ሬጌ፣ በመላው አለም ድንበር ሳያግደው የሚቀነቀን ተወዳጅ የሙዚቃ ስልት እንደሆነም ገልጧል፡፡
የሬጌውን ንጉስ ቦብ ማርሌይንና ፒተር ቶሽን ጨምሮ በርካታ ታዋቂ ድምጻውያን፣ ሬጌን በመላው አለም እንዲወደድ እንዳደረጉትም ዘገባው አክሎ ገልጧል፡፡

ከዕለታት አንድ ቀን አንድ ልዑል በአንድ ጫካ ውስጥ አደን ሲያድን ውሎ እየተመለሰ ሳለ አንድ ባላገር ያገኛል፡፡ ባላገሩ የልዑሉን ማንነት አያውቅም፡፡ ስለዚህም እንዲሁ በአዘቦት ሰላምታ፡-
“እንዴት ዋልክ ወዳጄ?” አለ
ልዑሉም፤
“ደህና እግዚአብሔር ይመስገን፡፡ አንተስ ደህና ውለሃል?”
“ደህና፡፡ ከየት እየመጣህ ነው?”
“ከአደን”
“ቀናህ?”
“ዛሬ እንኳን እንደትላንትና አደለም”
ልዑሉ፤ ባላገሩ እንዳላወቀው ገብቶታልና፤
“ለመሆኑ ንጉሥ ማለት ምን ማለት ነው? ታውቃለህ?”
“አላውቅም”
“አየህ፤ ንጉሥ ማለት በፈረስ ሲሄድ ሰዎች ሁሉ ቆመው የሚያሳልፉት፣ እጅ የሚነሱት፣ አንዳንዴም ያለፈበትን መሬት ሳይቀር የሚስሙለት ሰው ነው፡፡ አሁን ና ፈረሴ ላይ ተፈናጠጥና ወደ ከተማ አብረን እንዝለቅ” አለው፡፡ ባላገሩ ተፈናጠጠና አብረው መጓዝ ቀጠሉ፡፡ ወደ ከተማ እየተጠጉ ሲመጡ፣ ሰው ሁሉ በያለበት ይቆም ጀመር፡፡ ግማሹ እጅ ይነሳል፡፡ ግማሹ ይንበረከካል፡፡ ዕልል የሚሉ ሴቶች ሁሉ ታዩ፡፡
ልዑሉ፤
“እሺ ወዳጄ፣ አሁን ንጉሡ ማን እንደሆነ ገባህ?”
“አዎን”
“ማን ይመስልሃል?”
“እንግዲህ ወይ እኔ ወይ አንተ ነን ማለት ነዋ!”
***
ሰዎች የሚያስቡት በገባቸው መጠን ነው፡፡ በቀናነት የሚያስቡ ሰዎች ልክ አላቸው፡፡ ንፅህና አላቸው፡፡ የአዕምሮ ልኬት አላቸው፡፡ ሁሌ ካፍንጫችን ስር ብቻ ማሰብ፣ እንደ መንጋ መነዳትን ያስከትላል፡፡ ስለ ሜቴክ ሲነግሩን፣ እሱን ብቻ ልናስብ ከሆነ፣ በዚያው ታቅበን እንቀራለን፡፡ አገራችን ኢትዮጵያ የወንጀል ደሀ ሆና አታውቅም፡፡ የምላስም ደሀ አይደለችም። የሥራ እንጂ!
ጥንት በነበረው የትግል ሂደት ውስጥ…
“ከማዕበል በፊት የባህር እርጋታ
ከንግግር በፊት የአርምሞ ፀጥታ
ዛሬም ያገሬ ሰው ጊዜያዊ ዝምታ
 ነገ ግን ይነቃል መታገሉ አይቀርም
ታግሎም ያሸንፋል አንጠራጠርም”
… እንል ነበር፡፡
ብለናል ግን የሀገራችን ሰው ከዝምታው ሳይነቃ ዘመን አልፏል፡፡ ጊዜው አልደረሰም ማለት ነው፡፡ አሁን መሆን ያለበት፣ አግባብ ያላቸውን ጥያቄዎች በአግባቡ መጠየቅ ነው። ከጥያቄዎቹ አንዱና ዋነኛው “አንድ ምርጫ ብቻ ነው ማሰብ ያለብን?” የሚለው ነው፡፡ የ1966 አብዮት ወደ 1969 ሲያድግ በጠባቡ “ያለምንም ደም ኢትዮጵያ ትቅደም” ብለን የጀመርነውን፤ “ደም በደም ነው የሚጠራው” ብለን ደመደምነው፡፡ ዋጋ ከፈልንበት፡፡ የ1993 የምርጫ ሂደት አንድ ዙር ልናልፈው ስንችል፤ “ዕውር ነገ አይንህ ይበራልሃል” ሲባል፣ “ዛሬን እንዴት አድሬ?” አለ የተባለው ሆነና፣ በስድስት ወር አገር እንለውጣለን ብለን ሁሉንም አፋረሰነውና ዋጋ ከፈልን። አሁንም የያዝነው ለውጥም ሆነ መጪው ምርጫ የመጨረሻው ነው ብለን አናስብ። ከምርጫው በኋላ ሌላ ምርጫ ይኖራል ብለን እናስብ፡፡ እንዘጋጅ፡፡ ይኖራል ያልነው ላይኖር፣ አይኖርም ያልነው ሊኖር ሁኔታዎች ሊያስገድዱት፤ የተፈጥሮም፣ የሶሻልም፣ ምናልባትም የሶሻል ሳይንስ ህግ ነው! ምክንያቱም ለመኖር አለመኖርን መቃወም ተፈጥሯዊ ነውና -Living is resisting death ይባላልና በፈረንጅ አፍ!  
ዞሮ ዞሮ ያለንን አዎንታዊ መንፈስ ለማጠንከር፣ በቅን ልቦና ለውጥን ማመን ያስፈልገናል። ስለ ምንም ስለ ማንም ብለን ሳይሆን፣ የሀገርና የህዝብ ነገር ስለሚቆረቁረን ነው፡፡ “ከተስማማን ዘጠኝ ቂጣ ለባልና ሚስት ይበቃል” ስንል፤ ከተስማሙ ላይ አስምረን ነው፡፡ አለዚያማ ቂጣው ለጎረቤትስ ይበቃ አልነበር? ጥናቱን ይስጠን!

Monday, 03 December 2018 00:00

የፓርቲዎች የውህደት ጉዞ

ሰባት የፖለቲካ ድርጅቶች ለመዋሃድ ተስማሙ

ኢራፓን ጨምሮ በሃገር ውስጥና በውጪ ሲንቀሳቀሱ የነበሩ 7 የፖለቲካ ድርጅቶች ለመዋሃድ መስማማታቸው ታውቋል፡፡ ሰሞኑን ተፎካካሪ ፓርቲዎች ከጠ/ሚኒስትር ዶ/ር ዐቢይ አህመድ ጋር በተወያዩበት ወቅት፤ በውይይቱ ላይ 70 ፓርቲዎች መገኘታቸውን የጠቀሱት ዶ/ር ዐቢይ፤ በሃሳብ ተሰባስበው 4 ወይም 5 እንዲሆኑ ምክረ ሃሳብ ማቅረባቸው ይታወሳል፡፡
 ሰሞኑን ውህደት ለመፈፀም የመግባቢያ ስምምነት የተፈራረሙት በሀገር ውስጥ ሲንቀሳቀሱ የነበሩት የኢትዮጵያ ራዕይ ፓርቲ (ኢራፓ)፣ የኦሞ ህዝቦች ዲሞክራሲያዊ ህብረት እና በቅርቡ ወደ አገር ቤት የተመለሱ  አምስት የፖለቲካ ድርጅቶች ናቸው፡፡
በወ/ሮ ጽጌረዳ ሙሉጌታና በፕ/ር አቻሜለህ ዲባባ የሚመራው “የኢትዮጵያ መድህን ዲሞክራሲያዊ ፓርቲ (መድህን)”፣ በአቶ ስለሺ ጥላሁን የሚመራው “የኢትዮጵያ ብሔራዊ የሽግግር ም/ቤት (ሽግግር)”፣ በዶ/ር አክሎግ ቢራራ የሚመራው “ብሩህ ኢትዮጵያ ዲሞክራሲያዊ ንቅናቄ (ብሩህ)”፣ በአቶ በርገና ባሣ የሚመራው “ቱሣ የኢትዮጵያ ትንሣኤ ዲሞክራሲያዊ ድርጅቱ (ቱሣ)” እና በአቶ ነሲቡ ስብሃት የሚመራው “ኢትዮጵያችን ንቅናቄ” የውህደቱ አካል ናቸው ተብሏል፡፡
ድርጅቶቹ ለመዋሃድ የተስማሙት ላለፉት 6 ወራት ሠፊ የመጠናናት ውይይት ካደረጉ በኋላ መሆኑን ለአዲስ አድማስ የገለፁት የኢራፓ ፕሬዚዳንት አቶ ተሻለ ሰብሮ፤ ህዳር 15 ቀን 2011 ለመዋሃድ የመግባቢያ ሰነድ ተፈራርመው፣ ቀሪ የአፈፃፀም ጉዳዮች እየተከናወኑ ነው ብለዋል፡፡
ፓርቲዎቹ በሀገሪቱ የተጀመረውን ሪፎርም ተከትሎ፣ ከጠቅላይ ሚኒስትሩና ከህዝባቸው እየቀረበ ያለውን ጥሪ በመቀበል፣ ወደ ውህደት ማምራታቸውን አቶ ተሻለ አስታውቀዋል፡፡
በተመሳሳይ ሰሞኑን በአንጋፋዎቹ የኦሮሞ ነፃነት ግንባር መስራቾችና በኋላም የኦሮሞ ዲሞክራሲያዊ ግንባርን በመመስረት በውጭ ሀገር የፖለቲካ ትግል ሲያደርጉ የቆዩት አቶ ሌንጨ ለታ፣ ዶ/ር ዲማ ነገዎ፣ አቶ ሌንጮ ባቲን ጨምሮ በርካታ አንጋፋ ፖለቲከኞች ያሉበት ፓርቲ ከኦሮሚያ ክልል ገዥ ፓርቲ የኦሮሞ ዲሞክራሲያዊ ፓርቲ ጋር ውህደት ፈጽመዋል፡፡
በተመሳሳይ የአማራ ገዥ ፓርቲ የአማራ ዲሞክራሲያዊ ፓርቲ እና በትጥቅ ሲንቀሳቀስ የነበረው የአማራ ዲሞክራሲያዊ ንቅናቄ ከሶስት ሣምንታት በፊት ውህደት መፈፀማቸው ይታወሳል፡፡

“ሂውማን ራይትስዎች” እና “አርቲክል 19”ኝን ጨምሮ 12 ዓለማቀፍ የሰብአዊ መብት ተሟጋች ድርጅቶች አዲሱን የበጐ አድራጐት እና ሲቪክ ተቋማት ረቂቅ አዋጅ አስመልክቶ ለጠቅላይ ሚኒስትር ዶ/ር አብይ አህመድ ደብዳቤ ፃፉ፡፡
ተቋማቱ በሀገሪቱ የማህበራትንና መንግስታዊ ያልሆኑ ድርጅቶችን ነፃነት ለማስጠበቅ እየተደረገ ያለውን ጥረት አድንቀው፣ አዲስ የተረቀቀው አዋጅ አለማቀፍ የሠብአዊ መብት አጠባበቅ ህግጋትን ጠንቅቆ ያሟላ እንዲሆን ጠይቀዋል፡፡
“አዲስ የተረቀቀው አዋጅ በዋናነት መንግስታዊ ያልሆኑ ድርጅቶችና ሲቪል ማህበራት ስለሚኖራቸው የፋይናንስ ምንጭ፣ ያለ ውጣ ውረድ በቀላሉ ምዝገባ ስለማያከናውኑበት ሁኔታ አብዝቶ የተጨነቀ ነው” ያሉት ተቋማቱ፤ “ለሰብአዊ መብት ተከራካሪ ቡድኖች ምቹ ሁኔታን የሚፈጥር አይደለም የሚል ስጋት አለን” ብለዋል፡፡
አዲሱ ረቂቅ አዋጅ በተለይ የአፍሪካ ህብረት የሰብአዊ መብት አጠባበቅ በነፃነት የመሰብሰብና ማህበር የመመስረት መብቶችን በተመለከተ የደነገጋቸውን ማሟላቱን የሚኒስትሮች ም/ቤት እንዲያረጋግጥ ተቋማቱ ለጠቅላይ ሚኒስትሩ በፃፉት ደብዳቤ ጠይቀዋል፡፡
“ረቂቅ ህጉ፤ ሁሉ ማህበራትና ተቋማት እንደ አዲስ ሊመዘገቡ ይገባል ማለቱም ተገቢ አይደለም” ያለው ደብዳቤው በተለይ የሰብአዊ መብት ተቋማትን እንቅስቃሴ የሚገድብ ድንጋጌ በመሆኑ ሊሻር ይገባዋል ብሏል፡፡ አዲስ እየተረቀቀ ያለው አዋጅ፤ ሃገሪቱ የጀመረችውን የለውጥ እንቅስቃሴ ሙሉ የሚያደርግና በእጅጉ ለሰብአዊ መብት ጥሰቶች መቀረፍ አስተዋጽኦ የሚያበረክት ሆኖ እንዲዘጋጅም ጠይቀዋል፡፡
በተጨማሪም በሀገር ውስጥ ያሉም አለማቀፍ የሰብአዊ መብት ተሟጋች ድርጅቶች በሀገሪቱ ያለምንም ገደብ ተንቀሳቅሰው የሚሠሩበትን ምቹ ሁኔታ የሚፈጥር አዋጅ መሆኑን ጠቅላይ ሚኒስትሩ እንዲያረጋግጡ በደብዳቤው ተጠይቋል፡፡
ደብዳቤውን የፃፉት12 ድርጅቶች፡- አርቲክል 19፣ በኢትዮጵያ የሰብአዊ መብት ተሟጋቾች ማህበር፣ ሲቪክስ፣ የሲቪል መብት ተሟጋቾች፣ የኢትዮጵያ መብት ድርጅቶች ቡድን፣ ሂዩማን ራይትስዎች፣ ኬኔዲ ሂውማን ራይትስ፣ ዎርልድ ኦርጋናይዜሽን አጌኒስት ቶርቸር እና ዲፌንድ ዲፌንደርስ የተሰኙ አለማቀፍ የሰብአዊ መብት ተሟጋች ድርጅቶች ናቸው፡፡ 


221 ሺህ 772 ናይጀሪያውያን ቫይረሱ በደማቸው ውስጥ ይገኛል

በናይጀሪያ በየአመቱ ከ9 ሚሊዮን በላይ ነፍሰጡር ሴቶች እንደሚኖሩና ከእነዚህም መካከል የኤች አይ ቪ ምርመራ የሚያደርጉት 2.4 ሚሊዮን ያህሉ ብቻ መሆናቸውን የአገሪቱ መንግስት አስታውቋል፡፡
የናይጀሪያ የጤና ሚኒስቴር ይፋ ያደረገው መረጃ እንደሚያሳየው በአገሪቱ የቅድመ ወሊድ የህክምና አገልግሎት አቅርቦት የሚያገኙት 3.6 ሚሊዮን ያህል ነፍሰጡሮች ብቻ ሲሆኑ፣ ከእነዚህም መካከል የኤች አይ ቪ ምርመራ የሚያደርጉት 2.4 ሚሊዮን ያህሉ ብቻ ናቸው፡፡
በየአመቱ የኤች አይ ቪ ምርመራ ከሚያደርጉት 2.4 ሚሊዮን ያህል የአገሪቱ ሴቶች መካከል በትንሹ 64 ሺህ የሚሆኑት በደማቸው ውስጥ የኤች አይ ቪ ቫይረስ እንደሚገኝባቸው ሚኒስቴሩ ባወጣው መግለጫ አስታውቋል፡፡
ኤች አይ ቪ ቫይረስ በደማቸው ውስጥ ከሚገን 64 ሺህ ያህል ነፍሰጡሮች መካከል የጸረ ኤች አይቪ ኤድስ መድሃኒት ተጠቃሚ የሚሆኑት 74 በመቶ ያህሉ ብቻ እንደሆኑ የጠቆመው ሚኒስቴሩ፣ በናይጀሪያ 221 ሺህ 772 ህጻናት ቫይረሱ በደማቸው ውስጥ እንደሚገኝ ከእነዚህ መካከልም ህምክና የሚያገኙት 54 ሺህ ያህሉ ብቻ እንደሆኑ አመልክቷል፡፡እጅግ ፈጣን ነው የተባለለት አዲሱ የ5ጂ ወይም አምስተኛ ትውልድ የሞባይል ኔትወርክ ቴክኖሎጂ አለምን አስደንቆ ሳይጨርስ፣ ከሰሞኑ ደግሞ ቻይና ከዚህም እጅግ የላቀውን የ6ጂ ኔትወርክ ለመጀመር በዝግጅት ላይ እንደምትገኝ ይፋ ማድረጓ ተነግሯል፡፡የቻይና ተመራማሪዎች ከ5 ጂ ገመድ አልባ ኔትወርክ በአስር እጥፍ ያህል የሚበልጥ ፍጥነት እንዳለው የተነገረለትን የ6 ጂ ኔትወርክ በስራ ላይ ለማዋል የሚያስችል ምርምር በሁለት አመት ጊዜ ውስጥ እንደሚጀምሩ ብሉምበርግ ዘግቧል፡፡ እጅግ ፈጣኑን የ6ጂ ኔትወርክ ቀድማ ለአለማችን ለማስተዋወቅ ጉዞ የጀመረቺው ቻይና፣ የ5 ጂ ኔትወርክ ቴክኖሎጂ በማስፋፋት ረገድም ከአሜሪካና ከሌሎች ያደጉ አገራት ጋር ከፍተኛ ፉክክር ውስጥ እንደምትገኝና ለዚህም እጅግ ከፍተኛ በጀት መድባ እየሰራች እንደምትገኝ ዘገባው አመልክቷል፡፡  በኮንጎ ኢቦላ 177 ሰዎችን፣ ኮሌራ 857 ሰዎችን ገድሏል
በአለማችን የስኳር በሽተኞች ቁጥር ቁጥር ባለፉት ሶስት አስርት አመታት በከፍተኛ ሁኔታ ማደጉንና በአሁኑ ወቅት የስኳር በሽተኞች ቁጥር 420 ሚሊዮን ያህል መድረሱንና የስኳር በሽታ በየአመቱ 1.6 ሚሊዮን ያህል ሰዎች ለህልፈተ ህይወት እንዲዳረጉ ምክንያት ይሆናል ተብሎ እንደሚገመት የአለም የጤና ድርጅት አስታወቀ፡፡
የስኳር በሽታ ለአይነ ስውርነት፣ ለኩላሊት ከጥቅም ውጭ መሆንና ለልብ ድካም በሽታ በማጋለጥ ረገድ ቀዳሚነቱን እንደሚይዝ  ድርጅቱ ከትናንት በስቲያ ባወጣው አለማቀፍ ሪፖርት የጠቆመው ድርጅቱ፣ ሰዎች የስኳር በሽታን ለመከላከል ጤናማ አመጋገብ እንዲከተሉ፣ የሰውነት እንቅስቃሴ እንዲያደርጉና ከመጠን በላይ የክብደት መጨመር እንዳይከሰትባቸው መጠንቀቅ እንዳለባቸውም መክሯል፡፡
በሌላ በኩል ደግሞ በዲሞክራቲክ ሪፐብሊክ ኮንጎ ባለፈው ሃምሌ የተቀሰቀሰው የኢቦላ ወረርሽኝ 303 የአገሪቱ ዜጎችን ማጥቃቱንና በቫይረሱ ለሞት የተዳረጉ ሰዎች 177 መድረሱን ቢቢሲ ዘግቧል፡፡
የአገሪቱ የጤና ሚኒስቴር ያወጣውን መረጃ ጠቅሶ ዘገባው እንዳለው፣ በአገሪቱ የተቀሰቀሰው የኦቦላ ቫይረስ የከፋ ጥፋት እንዳያደርስ ለመከላከል ጥረት እየተደረገ ሲሆን፣ ከ30 ሺህ በላይ ሰዎች የጸረ-ኢቦላ ቫይረስ ክትባት እንዲወስዱ ተደርጓል፡፡
በተያያዘ ዜናም የኮሌራ ወረርሺኝ በዚህ አመት ብቻ በዲሞክራቲክ ሪፐብሊክ ኮንጎ 857 በናይጀሪያ ደግሞ 1 ሺህ 110 ሰዎችን ለህልፈተ ህይወት መዳረጉ ተዘግቧል፡፡
በዲሞክራቲክ ሪፐብሊክ ኮንጎ በ2018 የፈረንጆች አመት የተቀሰቀሰው የኮሌራ ወረርሽኝ 25 ሺህ 170 ያህል የአገሪቱ ዜጎችን ማጥቃቱንና ከእነዚህም መካከል 857 ሰዎች ለህልፈተ ህይወት መዳረጋቸውን የዘገበው አናዶሉ ኒውስ ኤጀንሲ፣ ባለፈው አመት በአገሪቱ የተከሰተው የኮሌራ ወረርሽኝ 55 ሺህ ሰዎችን ማጥቃቱንና 190 ያህሉ ለሞት መዳረጋቸውንም አስታውሷል፡፡
በዘንድሮው አመት ከ36ቱ የናይጀሪያ ግዛቶች በ29 ያህሉ ውስጥ የተቀሰቀሰውና 1 ሺህ 110 ሰዎችን የገደለው ኮሌራ ለህልፈተ ህይወት የዳረጋቸው ሰዎች ቁጥር ከአንድ አመት በፊት ከነበረው የ84 ሰዎች ሞት በእጅጉ ጭማሪ ማሳየቱንም ዘገባው አመልክቷል፡፡
ኮሌራ በመላው አለም በየአመቱ 2.8 ሚሊዮን ያህል ሰዎችን እንደሚያጠቃና 91 ሺህ ያህል ሰዎችም ከኮሌራ ጋር በተያያዘ ለሞት እንደሚዳረጉም ዘገባው ገልጧል፡፡

Page 10 of 417