Administrator

Administrator

ከዕለታት አንድ ቀን አንድ በገጠር የሚኖር የናጠጠ ሀብታም ልጅ፤ የንጉሡን ልጅ ለማግባት ፈልጎ፤ ወደ ንጉሡ ከተማ ሽማግሌዎች ይልካል፡፡ የፋሲካ ማግሥት ነው ዕለቱ፡፡ ሽማግሌዎቹ ተፈቅዶላቸው ግቢ ይገባሉ፡፡
ንጉሡን ጨምሮ ልዑላኑና መኳንንቱ ተቀምጠዋል፡፡
ሽማግሌዎቹ ገብተው ከፊት ለፊት ቆሙ፡፡
‹‹ተቀመጡ እንጂ›› አሉ ንጉሡ፡፡
‹‹የለም፡፡ ጥያቄ አለንና፣ ጥያቄያችን ሳይመለስልን አንቀመጥም›› አሉ
‹‹መልካም፤ ጥያቄያችሁን እንስማ!›› አሉ ንጉሡ፡፡
ከሽማግሌዎቹ ጠና ያሉት ተነሱና፤
‹‹የመጣነው ልጃችሁን ለልጃችን ለጋብቻ ለመጠየቅ ነው፡፡ ፈቃዳችሁ እንደሚሆን ተስፋ እናደርጋለን፡፡››
‹‹ከየት ነው የመጣችሁት ከማንስ ቤተሰብ ነው የመጣችሁት?››
ሽማግሌው፤
‹‹ቤተሰባችን ጨዋ፣ የደራ የኮራ፣ ልጃችን የታረመ የተቀጣ፣ ምሁር ነው፡፡ የቤተክህነት ትምህርት  ጠንቅቆ ያቃል፡፡  የደጃች እከሌ ቤተሰብ ነን፡፡ ከሩቅ ገጠር ከለማው ቀዬ ነው የመጣነው፡፡ በማናቸውም መንገድ ከእናንተ ቤተሰብ ምንም ዓይነት ዝምድና እንደሌለ አጥርተን አውቀናል››
ንጉሡ፤
መልካም፡፡ ከሩቅ አገር መምጣታችሁን ገምተናል፡፡ ስለዚህ ብዙ አናመላልሳችሁም፡፡ እዚህ አካባቢ ቆየት ብላችሁ ተመለሱ፡፡ ልጃችንን እናናግራት፡፡ ዘመድ አዝማዱንም እናማክርና ጥያቄም ካለ ይቀርብላችኋል፡፡ እንደሚታወቀው ልጃችን ጠቢብ ናትና የምትጠይቀው አታጣም›› አሉ፡፡
ሽማግሌዎቹ እጅ ነስተው ወጡ፡፡ ከሰዓት በኋላ ተቀጥረዋል፡፡ ሽማግሌዎቹ በየዘመድ አዝማድ ዘንድ እህል ውሃ ሲሉ ቆይተው፣ በተቀጠረው ሰዓት ተመልሰው መጡ፡፡ አሁን ጠርቀም ያለው የቤተሰብ ዘርፍ እልፍኝ ተሰባስቧል፡፡
ንጉሱ፤
‹‹አገር ሽማግሌዎች አጣደፋችሁንኮ፡፡ ዋናው ጉዳይ የእኛ ፈቃደኝነት ብቻ ሳይሆን የልጃችንም መቀበል ነው፡፡ ልጃችን ጥያቄ አቅርባለች፡፡ ጥያቄዋም፡- ‹እኔ ላገባው የምችለው ወንድ፣ ለእኔ ያለው ፍቅር፤
1ኛ/ እንደ እናቴ መቀነት
2ኛ/ እንደ አባቴ ጥይት
3ኛ/ እንደነብስ አባቴ ማተብ
ከሆነ ነው፡፡  የዚህን ፍቅር ፍቺ በወጉ ከተረዳ እሺ ብላለች በሉት” ብላናለች፡፡
እንግዲህ የዚህን ፍቺ በሁለት ቀን ውስጥ ከላከና የገባው ከሆነ ታገባዋለች” አሉ ንጉሡ፡፡
ሽማግሌዎቹ፤ “በሁለት ቀን መልስ ይዘን እዚሁ እንገኛለን” ብለው ሄዱ፡፡
በሁለተኛው ቀን ቤተ - መንግስት ቀረቡ፡፡
ንጉሡ፤
 “እህስ ሁነኛ መልስ ይዛችሁልን መጣችሁ?”
ሽማግሌ፤
“አዎን፤ ንጉሥ ሆይ!”
ንጉሥ፤
“በሏ እንስማችሁ?”
ሽማግሌው ተነስተው፤
“ልጃችን ለአንደኛው ጥያቄ ያለው መልስ፡- የእናቴ መቀነት ማለቷ - የእናት መቀነት ተፈትሎ፣ ተከሮ፣ ተሸምኖ ነውና መቀነት የሚሆን ሥራ ወዳድ መሆኑን ፈልጋለች፡፡
አንድም ደግሞ እናት ሁሉን ዋጋ ያለው ነገር የምታኖረው መቀነቷ ውስጥ በመሆኑ ገንዘብና ንብረት ያዥና ቆጣቢ መሆን ያለብኝ መሆኔን ማመላከቷ ነው፤ ብሏል፡፡
ሁለተኛው ጥያቄዋ አዳኝ መሆኔን፣ ተኳሽ መሆኔን፣ ጀግና መሆኔን እንደምትወድ ስትገልፅልኝ ነው፡፡
ሶስተኛው ጥያቄዋ፤ ለትዳራችን ሁለታችንና ሁለታችን ብቻ ወሳኝ መሆናችንንና አንዳችን የአንዳችንን ምስጢር እንደነብስ አባት መጠበቅ እንዳለብን መንገሯ ነው፡፡
እኔ ደግሞ ሶስቱንም አክባሪ ነኝ” ብሏል አሉ፡፡
ንጉሡ ደስ አላቸው፡፡
“በቃ ልጃችንን ለልጃችሁ ፈቅደናል፡፡ ወደ ገበታው እንቅረብና የምስራቹን፣ ቤት ያፈራውን እንቅመስ!” አሉ፡፡
 ፋሲካው ደመቀ፡፡
***
በየትም ጊዜ፣ በየትም አገር ከውጣ - ውረድ ነፃ የሆነ ነገር የለም፡፡ ያለ ሥራ፣ ያለ ቁጠባ፣ አስፈላጊ ከሆነ ደግሞ ያለ አላሚ - ተኳሽና ጀግና፣ ቤቱን አስከባሪ፣ ድንበሩን አክብሮ - አስከባሪ፤ በመጨረሻም የአገሩን ምሥጢር አክባሪ መሆን፤ ትዳርን በሀገር ለመተርጎም ለቻለ ሁሉ ወሳኝ ነው! እንደ ምን ቢሉ - የሀገር ምሳሌ ቤተሰብ ነውና!
ቤተሰብ በፍቃደኝነት ላይ ተመስርቶ ይጀመርና እንደ ባህሉ በህግ ይታሰራል፡፡ እንደ ባህሉ ተከባብሮ፣ አንተ ትብስ አንቺ ትብሽ ተባብሎ፣ ግጭት ቢፈጠር ተወያይቶ፣ ችግርን ፈቶ፣ በእኩልነት የመተዳደርን ባህል አዳብሮ በፍቅር ይዘልቃል፡፡ ልጆች ቢወለዱም በዳበረው ልማድና ባህል ውስጥ መተዳደሪያቸው ተቀምሮላቸው፣ በግብረ-ገብነት ታንፀው እንዲያድጉ ይደረጋል፡፡ ለአቅመ-አዳም ወይም ለአቅመ - ሄዋን ሲደርሱ ከቤተሰብ ወጥተው  ቤተሰብ ይመሰርታሉ፡፡ የራሳቸውን ደምብና ሥርዓት አበጅተው ህይወትን ይቀጥላሉ:: የመተዳደሪያ ደምብ፣ የኢኮኖሚ ይዞታ፣ የልጅ አስተዳደግና ሥነ ምግባር ደምብ፣ የኢኮኖሚ ይዞታ፣ የልጅ አስተዳደግና ሥነ ምግባር፣ ከጎረቤት ጋር ያለ ባህላዊ ግንኙነት፣ የጤናና የትምህርት ሁኔታ፤ ወዘተ-- በቤተሰብ ውስጥ የምናያቸው ሥርዓተ-አኗኗሮች ሁሉ የአንድ አገር መንግሥት መዋቅር መሰረት ናቸው፡፡ በተለይ የኢኮኖሚ ሁኔታው እጅግ ወሳኝ ነው፡፡ ኢኮኖሚውን በቅርብ ተከታትሎ መሰረቱ እንዳይናድ፣ እንዳይመዘበር፣ ሥርዓት እንዳያጣ ተጠንቅቆ መምራት የአስተዳደሩ ቁልፍ ጉዳይ ነው፡፡ አስተዳደሩ የፖለቲካው ዋና መዘውር ነው፡፡ ፖለቲካ የኢኮኖሚው አቅም ጥርቅም ገፅታ ነው (politics is the concentrated form of the economy) እንዲሉ ፈረንጆቹ:: ቀለል አድርገን ብናየው “የሆድ ነገር ሆድ ይቆርጣል” እንደምንለው ይሆናል፡፡ ኢኮኖሚው ሲበላሽ ፖለቲካው መናጋቱ፣ ህዝብ ጥያቄ ማንሳቱ፣ አመራሩ ሁነኛ መልስ ካልሰጠ አጣብቂኝ ውስጥ መግባቱ፣ የመሰረታዊ ለውጥ አስፈላጊነት (Radical change) እየጎላ መምጣቱ አይቀሬ እየሆነ ይሄዳል፡፡ በታሪክ እንደታየው ማንኛውም አመራር አካል በቸገረው ሰዓት፤ ሰዎችን ከመዋቅር መዋቅር ለመለወጥ ይሞክራል፡፡ ያ ካልተሳካ የመዋቅሩን ደም-ሥር እንዲመረምር ይገደዳል፡፡ ፍትሐዊ ሂደት መኖር አለመኖሩን ያጣራል፡፡ ዲሞክራሲያዊ አካሄድ መኖር አለመኖሩን ይፈትሻል፡፡ መልካም አስተዳደር ሰንሰለታዊ ባህሪ አለው- hain Reaction እንዲል መጽሐፍ፡፡ ለምሳሌ የመልካም አስተዳደርን ጉዳይ ብቻ ነጥለን እንመታለን ብሎ ማሰብ፣ ከደን ውስጥ አንድ ዛፍ መፈለግ ዓይነት ነው፡፡ ፍትሕ፣ ዲሞክራሲ፣ የሰው ኃይል አደረጃጀት፣ ተቋማዊ ብቃት፣ ባህላዊና ልማዳዊ አካሄድ፣ የአገር ሉአላዊነት፣ የአዕምሮ ውጤቶች አያያዝ፣ ማህበራዊና ሥነ ምግባራዊ ዕድገት ወዘተ ሁሉ በስፋትና በጥልቀት ሲኬድባቸውና ሲታዩ የመልካም አስተዳደር መጋቢ መንገዶች ናቸው፡፡ ድርና ማግ ናቸው፡፡ አንዱ ያለ አንዱ ፍሬ አያፈሩም፡፡ ወንዝ አያሻግሩም፡፡ እነዚህን ሁሉ በወግና በሥነ ሥርዓት ቀንብቦ ለመያዝ በህግ የበላይነት አምኖና ተማምኖ መመራት ያስፈልጋል፡፡ “በህግ አምላክ” የማይባልበት አገር ዜጋ ተከባብሮና ሥርዓት ይዞ ለመኖር ያዳግተዋል፡፡ ሰላሙን በቀላሉ አያገኝም፡፡ የህግ የበላይነት የእኩልነት መቀነቻ ነው፡፡ የተገነባው እንዳይጠቃ፣ ዘራፍ - ባይ ቆራጭ ፈላጭ እንዳይፈጠር፣ ቀና ብለን የምናየው የህግ የበላይነት መኖር አለበት፡፡
መኖሩን የሚያሳይ ተግባርም መታየት አለበት፡፡ የህግ የበላይነት በሥራ ተተርጉሞ ካልታየ ባዶ ነው፡፡
ከላይ ያነሳናቸው ፍሬ - ጉዳዮች እየተሟሉ ሲሄዱ የአገር ተስፋ ይለመልማል፡፡ ሆኖም ልምላሜው የሚገኘው በወርቅ አልጋ በእርግብ ላባ ላይ ተተኝቶ አይደለም፡፡ መንገዱ አልጋ በአልጋ አይደለም፡፡ ውጣ ውረድ፣ አቀበት ቁልቁለት የበዛበት እሾሃማ መንገድ ነው፡፡ አንዴ ልምራው ተብሎ ከተገባ እሾኩን እየነቀሉ፣ አበባውን እየጠበቁ መጓዝን ይጠይቃል፡፡ የነብርን ዥራት ከያዙ አይለቁም ነው ነገሩ፡፡
በመሰረቱ ለዘመናት በችግር የተተበተበችን አገር ውስብስብ ህልውና፤ በአንድ ጀንበር ማቅናት አይቻልም፡፡  ስኬታማነት ሊኖር ይችላል፡፡ ግን መሰናክሎችም አብረውት አሉ፡፡
“ችግር አለ፡፡ ችግሩንም ለመናገር ችግር አለ” በሚባልበት አገር፣ ስኬት ብቻ ነው የሚታየኝ ማለት ወይ ሆነ ብሎ ዐይንን መጨፈን ነው፡፡ አሊያም “የፋሲካ ዕለት የተወለደች ሁል ጊዜ ፋሲካ ይመስላታል” የሚለውን ተረት ውስጠ - ነገር አለመገንዘብ ነው፡፡ ከችግሩ ሁሉ ወጥተን ትንሳኤ እናገኝ ዘንድ እንመኛለን፡፡
ከአዘጋጁ፡- ውድ አንባቢያን፤ እነሆ አዲስ አድማስ ተመሥርታ ለአንባቢያን መድረስ ከጀመረች ድፍን 20 ዓመት ሊሞላት ጥቂት ወራት ነው የቀራት፡፡ በመጪው ዓመት ታህሳስ 29 ቀን 2012 ዓ.ም የምስረታ  በዓሏን በተለያዩ ኪነጥበባዊ ዝግጅቶች ታከብራለች፡፡ ይሄን ምክንያት በማድረግም፣ ባለፉት ዓመታት ከታተሙ የጋዜጣው ጽሁፎች እየመረጥን፣ ለትውስታ ያህል እናቀርባለን፡፡ ከላይ የተነበበው  ርዕሰ አንቀጽም በዚህ መንፈስ ካለፈው ዕትም የተመረጠ ነው፤ አፕሪል 21, 2012  በአዲስ አድማስ ድረ ገጽ ላይ ፖስት ተደርጓል፡፡

 ለ2019 የሠላም የኖቤል ሽልማት ታጭተዋል

              ታይም መፅሔት ጠቅላይ ሚኒስትር ዶ/ር ዐቢይ አህመድን ከ100 ተፅእኖ ፈጣሪ መሪዎች መካከል አንዱ አድርጎ መረጣቸው፡፡ ጠቅላይ ሚንስትሩ በዚህ ዝርዝር ውስጥ የተካተቱት በአገራቸው ፈጣን ለውጥ ባመጡ መሪዎች ዘርፍ ነው፡፡  እሳቸው በተካተቱበት ዘርፍ ውስጥ የአሜሪካ ኮንግረስ አፈጉባኤ ናንሱ ፔሎሲ፣ ፕሬዚዳንት ዶናልድ ትራምፕ፣ ፖፕ ፍራንሲስ፣ የኒውዝላንድ ም/ሚኒስትር ጆሲንዳ አርደን መካተታቸውም ታውቋል፡፡
ከጠቅላይ ሚኒስትር ዶ/ር ዐቢይ ጋር ከአፍሪካ በዚህ ዘርፍ የተካተቱት የደቡብ አፍሪካው ፕሬዚዳንት ሳይረል ራማፎሳ ናቸው:: በዚህ ዝርዝር ከተካተቱት ተጨማሪ መሪዎች መካከል የእስራኤሉ ጠ/ሚኒስትር ቤኒያሚን ኔትኒያሁ የተባበሩት ኤምሬት ልኡል መሃመድ ቢን ዛይድ እና የፓኪስታኑ ጠ/ሚር ኢምራን ካሃን ተጠቃሽ ሆነዋል፡፡
ጠቅላይ ሚኒስትሩ ወደ ስልጣን ከመጡበት መጋቢት 24 ቀን 2010 ዓ.ም ጀምሮ ባከናወኗቸው የፖለቲካ እና ማህበራዊ ሪፎርሞች በተለያዩ አካላት ሙገሳ ከማግኘታቸው ባሻገር እውቅና እና ሽልማቶችን አግኝተዋል፡፡ ይህም ከኢትዮጵያ መሪዎች በአንድ ዓመት ጊዜ ውስጥ በርካታ በጎ እውቅናዎችን ያገኙ ብቸኛው መሪ እንደሚያደርጋቸው መረጃዎች ያመላክታሉ፡፡
ወደ ስልጣን ከመጡ በ3ኛ ወራቸው በኡጋንዳ ብሔራዊ በአል ላይ የተገኙት ጠ/ሚኒስትሩ በስ ስርአቱ ላይም ለአፍሪካውያን በመላ ተስፋን የሰነቀ የለውጥ እንቅስቃሴ ለመፍጠር እና ሃገራቸውን ከአደጋ በመታደግ የሃጊቱን ከፍተኛ የጀግና አርበኞች ሜዳሊያ ተሸልመዋል፡፡
ደፋር የዲፕሎማሲ እርምጃ ወስደውበታል ተብሎ ስማቸው በበጎ በሚነሳበት የኢትዮጵያ እና የኤርትራ ግንኙነት ዳግም እውን እንዲሆን ላበረከቱት አስተዋፅኦም ከተባበሩት አረብ ኤምሬትስ እና ከሳውዲ አረቢያ መንግስታት የክብር ሜዳሊያ እና ኒን ሽልማቶችን አግኝተዋል፡
ከክብር ሽልማቶቹ ባሻገር ጠቅላይ ሚኒስትሩ በሃገራቸው የፖለቲካ ሪፎርም ማካሄዳቸው በጎ እውቅናን አስገኝቶላቸው የአፍሪካን ሜጋዚን የአፍሪካ የዓመቱ ምርጥ ሰው አሸናፊም ለመሆን በቅተዋል፡፡
ጠ/ሚኒስትር ዶ/ር ዐቢይ አህመድ አሁንም በሌላ ተጨማሪ ከፍተኛ እውቅና እና ሽልማት እየተጠበቁ ነው፡፡ ለታላቁ የኖቤል ሽልማት ታጭተዋል፡፡ የታጩበት ዘርፍም የሰላም ሽልማት ዘርፍ መሆኑ ታውቋል፡፡
ለ2019 የሰላም ኖቤል ሽልማት ዶ/ር ዐቢይን ጨምሮ 223 ግለሰቦች እና 78 ተቋማት በእጩነት የተጠቆሙ ሲሆን በቀጣዩ ዓመት ህዳር 17 ቀን 2012 ዓ.ም በኖርዌይ ኦስሎ የሽልማት ስነ ስርአቱ ይከናወናል፡፡

 ስካይትራክስ የተባለው አለማቀፍ የአቪየሽን ዘርፍ ተቋም፣ የ2019 የፈረንጆች አመት የአለማችን ምርጥ የአውሮፕላን ማረፊያ ጣቢያዎችን ዝርዝር ከሰሞኑ ይፋ ያደረገ ሲሆን፣ ላለፉት ስድስት ተከታታይ አመታት በአንደኛ ደረጃ ላይ ሆኖ የዘለቀው የሲንጋፖሩ ቻንጊ ዘንድሮም በቀዳሚነት ተቀምጧል፡፡ ተቋሙ በአለማችን በሚገኙ ከ550 በላይ አውሮፕላን ማረፊያዎች ላይ የሰራውን ጥናት መሰረት አድርጎ ባወጣው የዘንድሮው የምርጥ አውሮፕላን ማረፊያዎች ዝርዝር የሁለተኛነት ደረጃን የያዘው ቶክዮ አለማቀፍ አውሮፕላን ማረፊያ ሲሆን፣ የደቡብ ኮርያው ሌንቼን ሶስተኛ ደረጃ ላይ መቀመጡን ሲኤንኤን ዘግቧል፡፡
ተቀማጭነቱ በለንደን የሆነው ስካይትራክስ ባወጣው የአመቱ የአለማችን ምርጥ አውሮፕላን ማረፊያ ጣቢያዎች ዝርዝር ውስጥ እንደ ቅደም ተከተላቸው ከአራተኛ እስከ አስረኛ ያለውን ደረጃ የያዙት ደግሞ የኳታሩ ሃማድ፣ የጃፓኑ ሴንትራል ጃፓን፣ የጀርመኑ ሙኒክ፣ የእንግሊዙ ለንደን ሄትሮው፣ የጃፓኑ ናሪታ እና የስዊዘርላንዱ ዙሪክ አለማቀፍ አውሮፕላን ማረፊያ ጣቢያዎች ናቸው፡፡
በዘንድሮው የአመቱ ምርጥ አውሮፕላን ማረፊያዎች ዝርዝር እስከ አስራ አምስተኛ ባለው ደረጃ ውስጥ አንድም የአሜሪካ፣ የአውስትራሊያና የአፍሪካ አውሮፕላን ማረፊያ ጣቢያ አለመካተቱንም ዘገባው አመልክቷል፡፡
ስካይትራክስ ከ100 በላይ በሚሆኑ የአለማችን አገራት ውስጥ የሚገኙ ከ550 በላይ የአውሮፕላን ማረፊያዎችን ለማወዳደር ከ39 በላይ የአገልግሎት አሰጣጥ ጥራት መስፈርቶችን ከመጠቀም ባለፈ የደንበኞችን የአገልግሎት እርካታም ለመለኪያነት እንደሚጠቀምም ዘገባው አክሎ ገልጧል፡፡

 ባለፈው የፈረንጆች አመት 2018 ብቻ ቻይናን ሳይጨምር በአለማችን 20 አገራት ውስጥ የሞት ፍርድ የተፈረደባቸው 690 ያህል ሰዎች መገደላቸውን አምነስቲ ኢንተርናሽናል የተባለው የሰብዓዊ መብቶች ተሟጋች ተቋም ባወጣው ሪፖርት አስታውቋል፡፡
በ2017 በአለማቀፍ ደረጃ የሞት ፍርድ ቅጣት ተጥሎባቸው የተገደሉ ሰዎች ቁጥር 993 እንደነበር ያስታወሰው ሪፖርቱ፣ በ2018 ይህ ቁጥር የ31 በመቶ መቀነስ ማሳየቱን አመልክቷል::
ቻይና በሞት የቀጣቻቸውን ዜጎች ቁጥር በመደበቋ በሪፖርቱ ውስጥ ሊያካትተው አለመቻሉን የጠቆመው አምነስቲ ኢንተርናሽናል፣ አገሪቱ ከአለማችን አገራት መካከል ከፍተኛ ቁጥር ያላቸው ሰዎችን በሞት ልትቀጣ እንደምትችል ግምቱን አስቀምጧል፡፡
በ2018 ከአለማችን አገራት መካከል ከፍተኛ ቁጥር ያላቸው ሰዎች በሞት የተቀጡባቸው ቀዳሚዎቹ  አገራት ኢራን፣ ሳኡዲ አረቢያ፣ ቬትናምና ኢራቅ እንደሆኑ የጠቀሰው ሪፖርቱ፤ በአመቱ በአለማችን በሞት ከተጠቁት 690 ያህል ሰዎች መካከል 77 በመቶ ያህሉ በእነዚህ አራት አገራት እንደተገደሉም አመልክቷል፡፡
በ2018 የሞት ፍርድ ተፈጻሚ የተደረገባቸው ሰዎች ቁጥር ኢራን፣ ኢራቅ፣ ፓኪስታንና ሶማሊያን በመሳሰሉ አገራት መቀነስ ማሳየቱን የጠቆመው ሪፖርቱ፤ ከፍተኛው መቀነስ በተመዘገበባት ኢራን በ2017 ላይ 507 የነበረው ይህ ቁጥር በ2018 ወደ 253 ዝቅ ማለቱን አመልክቷል፡፡ በሞት የተቀጡ ሰዎች ቁጥር በእነዚህ አገራት መቀነስ  ቢያሳይም በአንጻሩ ደግሞ አሜሪካ፣ ጃፓን፣ ሲንጋፖር፣ ደቡብ ሱዳንና ቤላሩስን በመሳሰሉ አገራት መጨመር  ማሳየቱንም ሪፖርቱ አስታውቋል፡፡
ማንኛውም አይነት ወንጀል ቢሰሩ ሰዎች በሞት እንዳይቀጡ የከለከሉ የአለማችን አገራት ቁጥር ባለፈው የፈረንጆች አመት መጨረሻ ላይ 106 መድረሱን ያስታወሰው ሪፖርቱ፤ አግደውት የነበረውን የሞት ፍርድ እንደገና ተግባራዊ ማድረግ የጀመሩ ታይላንድን የመሳሰሉ አገራት መኖራቸውንም አክሎ ገልጧል፡፡


 አድርገውት ከሆነ በእድሜ ልክ እስራት ሊቀጡ ይችላሉ

             የቀድሞው የደቡብ አፍሪካ ፕሬዚዳንት ጃኮብ ዙማ፣ ከሟቹ የሊቢያው አቻቸው ሙአመር ጋዳፊ 30 ሚሊዮን ዶላር  ተቀብለዋል በሚል ከሰሞኑ የወጣውን ዘገባ ፍጹም ውሸት ነው ሲሉ በትዊተር ገጻቸው ማስተባበላቸው ተዘግቧል፡፡
ሰንደይ ታይምስ ሰሞኑን ባወጣው ዘገባው፤ ጃኮብ ዙማ ከጋዳፊ ብዙ ገንዘብ ተቀብለዋል፤ በህገወጥ መንገድ በሚሊዮኖች የሚቆጠር ዶላር ከሊቢያ ወደ ደቡብ አፍሪካ አሸሽተዋል ማለቱን ተከትሎ፣ ጉዳዩ መነጋገሪያ ሆኖ መሰንበቱን የገለጸው ቢዝነስ ኢንሳይደር፣ በእርግጥም አድርገውት ከሆነ በእድሜ ልክ እስራት ሊቀጡ እንደሚችሉ መነገሩን ጠቁሟል፡፡
ጃኩብ ዙማ ከስምንት አመታት በፊት የሞቱትን ጋዳፊን በህይወት እያሉ ለመጨረሻ ጊዜ በአካል ያገኙ መሪ እንደነበሩ ያስታወሰው ዘገባው፤ በወቅቱም ከፍተኛ መጠን ያለው ገንዘብ ከሊቢያ ወደ ደቡብ አፍሪካ ለማሸሽ ሳያሴሩና ተግባራዊ ሳያደርጉት እንዳልቀሩ መነገሩን አመልክቷል፡፡
የደቡብ አፍሪካ የደህንነት ባለሙያዎች ጃኩብ ዙማ ከጋዳፊ 30 ሚሊዮን ዶላር መቀበላቸውን የሚያመለክት መረጃ እንዳገኙ ለአገሪቱ ፕሬዚዳንት ራሞፋሳ ጥቆማ መስጠታቸውንና በጉዳዩ ዙሪያ ምርመራ ሳይጀመር እንዳልቀረም ሰንደይ ታይምስ ባወጣው ዘገባ ገልጧል፡፡

ታዋቂው ማህበራዊ ድረገጽ ፌስቡክ ከዚህ አለም በሞት የተለዩ የፌስቡክ ተጠቃሚዎችን አካውንት የሚዘጋበት አዲስ አሰራር እየቀየሰ መሆኑን ከሰሞኑ ባወጣው መረጃ አስታውቋል፡፡
በሞት የተለዩዋቸውን ዘመድ ወዳጅ እንዲሁም ጓደኞቻቸውን በተመለከተ በሚደርሷቸው የተለያዩ የፌስቡክ ኖቲፊኬሽኖች ወይም መልዕክቶች ሀዘናቸው ዳግም እየተቀሰቀሰባቸው መማረራቸውን የሚገልጹለት የፌስቡክ ተጠቃሚ ደንበኞቹ ቁጥር በከፍተኛ ሁኔታ ማደጉን ተከትሎ፣ ኩባንያው ችግሩን ለመፍታት ሲል የሟች ደንበኞቹን አካውንት የሚዘጋበት አዲስ አሰራር መቀየሱን ገልጧል፡፡
አንድ የፌስቡክ ተጠቃሚ በሞት ከተለየ በኋላ የፌስቡክ አካውንቱ እንደማይዘጋና፣ ለሌሎች የፌስቡክ ወዳጆቹም ሆነ ለሌላ ተጠቃሚ እንደሚታይ ያስታወሰው ኩባንያው፣ ከዚህ በኋላ ግን ጥቆማዎችን በመቀበልና አርቴፌሻል ኢንተለጀንስን በመጠቀም የሟቾችን አካውንት እያጣራ እንደሚዘጋ አመልክቷል፡፡

ታዋቂው ማህበራዊ ድረገጽ ፌስቡክ ከዚህ አለም በሞት የተለዩ የፌስቡክ ተጠቃሚዎችን አካውንት የሚዘጋበት አዲስ አሰራር እየቀየሰ መሆኑን ከሰሞኑ ባወጣው መረጃ አስታውቋል፡፡
በሞት የተለዩዋቸውን ዘመድ ወዳጅ እንዲሁም ጓደኞቻቸውን በተመለከተ በሚደርሷቸው የተለያዩ የፌስቡክ ኖቲፊኬሽኖች ወይም መልዕክቶች ሀዘናቸው ዳግም እየተቀሰቀሰባቸው መማረራቸውን የሚገልጹለት የፌስቡክ ተጠቃሚ ደንበኞቹ ቁጥር በከፍተኛ ሁኔታ ማደጉን ተከትሎ፣ ኩባንያው ችግሩን ለመፍታት ሲል የሟች ደንበኞቹን አካውንት የሚዘጋበት አዲስ አሰራር መቀየሱን ገልጧል፡፡
አንድ የፌስቡክ ተጠቃሚ በሞት ከተለየ በኋላ የፌስቡክ አካውንቱ እንደማይዘጋና፣ ለሌሎች የፌስቡክ ወዳጆቹም ሆነ ለሌላ ተጠቃሚ እንደሚታይ ያስታወሰው ኩባንያው፣ ከዚህ በኋላ ግን ጥቆማዎችን በመቀበልና አርቴፌሻል ኢንተለጀንስን በመጠቀም የሟቾችን አካውንት እያጣራ እንደሚዘጋ አመልክቷል፡፡


                  ከ42 ሺህ በላይ ሆላንዳውያን ወጣቶች፣ በአገሪቱ ገንዘብ ከፍለው ከሴተኛ አዳሪዎች ጋር የሚተኙ ቅጣት እንዲጣልባቸው የሚጠይቅ ፊርማ በማሰባሰብ ለፓርላማ ማቅረባቸውን ቢቢሲ ዘግቧል፡፡
ሴተኛ አዳሪዎችን የሚጎበኙ ዜጎችን በህግ የማስጠየቅ አላማ ባነገበውና የአገሪቱ ወጣቶች በማህበራዊ ድረገጾች በከፈቱት ዘመቻ ከ42 ሺህ በላይ ሆላንዳውያን ሃሳቡን ደግፈው ፊርማቸውን ማስፈራቸውን የጠቆመው ዘገባው፣ በአንጻሩ ደግሞ የእንጀራ ገመዳችንን የሚበጥስ ነው በማለት ዘመቻውን የተቃወሙት ሴተኛ አዳሪዎች መኖራቸውን አመልክቷል፡፡
ጉዳዩ በማህበራዊ ድረገጾች የመነጋገሪያ ርዕስ መሆኑን ተከትሎ አምስተርዳም ውስጥ ወደሚገኝና ሴተኛ አዳሪዎች በብዛት ወደሚገኙበት ሞቅ ያለ ሰፈር በማቅናት የሴተኛ አዳሪዎችን ስሜት ለመገምገም እንደሞከረ የጠቆመው የቢቢሲው ዘጋቢ፣ በርካታ ቁጥር ያላቸው ሴተኛ አዳሪዎች “ምርጫችን ከሆነ መብታችን ነው” በማለት ተቃውሟቸውን እንደገለጹለት አትቷል፡፡  
ከሴተኛ አዳሪነት ጋር በተያያዘ ላላ ያለ ህግ ካለባቸው አገራት አንዷ እንደሆነች በሚነገርላት ሆላንድ፣ እድሜያቸው ለወሲብ የደረሰ እስከሆኑና እስከተስማሙ ድረስ ገንዘብ ከፍሎ ወሲብ መፈጸም ህጋዊ እንደሆነም ዘገባው አመልክቷል፡፡
ስዊድን፣ ኖርዌይና ፈረንሳይን በመሳሰሉ አገራት በአንጻሩ፣ ገንዘብ ከፍሎ ወሲብ የሚፈጽም በህግ እንደሚቀጣና ይህም በመሆኑ በአገራቱ ገንዘብ ከፍለው ወሲብ የሚፈጽሙ ሰዎችና በሴተኛ አዳሪነት የሚበዘበዙ ዜጎች ቁጥር አነስተኛ መሆኑን ዘገባው አክሎ ገልጧል፡፡


         ከዕለታት አንድ ቀን፣ አንድ ገጠር ሀብታም፣ በአንድ ትንሽ ከተማ ይኖር ነበረ፡፡ ይህ ሀብታም ሶስት ልጆች ነበሩት፡፡ አንደኛው መስማት የማይችልና ጆሮው የደነቆረ ልጅ ነው፡፡ ሁለተኛው፤ መናገር የተሳነው ዲዳ ነው፡፡ ሶስተኛው ደግሞ ማየት የተሳነው ዓይነ ስውር ነው፡፡ አባትየው ተጨንቆ ተጠቦና አውጥቶ አውርዶ፤ ከአንድ ጠቢብ ጋር ሊማከር ወደ ሩቅ ሃገር ሄደ፡፡ ለጠቢቡም፤
“ሶስት ልጆች አሉኝ፡፡ ነገር ግን ሶስቱም አንድ አንድ ችግር አለባቸው፡፡
አንደኛው - አይሰማም፡፡
ሁለተኛው - አይናገርም
ሶስተኛው - አያይም፡፡
ምን ባደርግ ይሻለኝ ይመስልሃል?”
ጠቢቡም እንዲህ ሲል መለሰለት፤
“ለማይሰማው ጽሑፍ አስተምረው፡፡
ለማያየው የዳሰሳ ሰሌዳ (ብሬል) አስተምረው፡፡
ለማይናገረው የምልክት ቋንቋ አስተምረው፡፡”
ሀብታሙ ሰውም ጠቢቡ የመከረውን ለማድረግ የፅሁፍ አስተማሪ፣ የብሬል አስተማሪና ብሬል፣ የምልከት ቋንቋ አዋቂ መቅጠር ነበረበት፡፡ ይህን የሚያስደርግ በቂ ገንዘብ ግን አልነበረውም፡፡ ስለዚህ ሰው ቤት ተቀጠረ፡፡ “ጎሽ ለልጇ ስትል ተወጋች” እንዲሉ፣ ቀጣሪው ሰው እጅግ ክፉ ነበረና ሱሪ ባንገት የሚያስወልቀው ዓይነት ሆነ፡፡
“እንደምን አደርክ?” ይለዋል፡፡
“ይመስገነው፡፡ በጣም ጥሩ እንቅልፍ ነበረኝ፡፡”
“አንተማ ምን ታረግ? የሥራውን ጭንቀት ለእኛ ጥለህ ለጥ ብለህ ትተኛለህ”
“ምን ማድረግ ነበረብኝ ጌታዬ?”
“አለመተኛት፡፡ ከእኔ ጋር መጨነቅ፡፡”
“እሱንማ አልችልም”
“ያ እኮ ነው ችግሩ፡፡ ለልጆችህ ገንዘብ ለማጠራቀም ጊዜ ግን ትችላለህ”
“ያዘዙኝን ሁሉ‘ኮ እየፈፀምኩ ነው ጌታዬ”
“አትተኛ ስልህ ‹እሺ ጌታዬ› ብለህ አለመተኛት ነው፡፡ ትዕዛዝ መፈፀም እንጂ አንድ ቤት ውስጥ ጌታው እንቅልፍ እያጣ፣ ሌላው እንቅልፉን እየለጠጠ የሚያድሩበት ሁኔታ መለወጥ አለበት፡፡”
“እንዴት ሊለወጥ እንደሚችል ያውቃሉ ጌታዬ?”
“አላውቅም”
“እንድነግርዎት ይፈቅዳሉ?”
“አሳምሬ!”
“ማድረግ ያለብዎት አንድ ነገር ብቻ ነው”
“ምን ማድረግ ነው ያለብኝ እሺ? ንገረኝ”
“በእኔ ቦታ እርሶ፣ በእርሶ ቦታ እኔ ሆነን እንድንሰራ ያድርጉ!”
***
“The right man at the right place” የዋዛ አነጋገር አይደለም፡፡ ትክክለኛውን ሰው በትክክለኛው ቦታ ማስቀመጥ ይገባል፤ እንደ ማለት ነው፡፡ ካልሆነ ስራ አይሰራም፡፡ ስነምግባሩም ይበላሻል፡፡ ሙያተኝነትና ስነ ምግባር ከቶም የሚነጣጠሉ አይደሉም፡፡ ምሉዕነት ያ ነው፡፡
“Uneasy lies the head that wears the crown” ይላል ሼክስፒር፡፡ ዘውድ የጫነን አናት ጭንቀት አይለየውም እንደማለት ነው፡፡ ቦታውን መያዝ፣ መሾም - መሸለም ብቻ የቢሮክራሲውን ስራ ውጤታማ አያደርገውም፡፡ ሰው መለዋወጥም ጉልቻ ቢቀያር ወጥ አያጣፍጥምን እንድንረሳ ማድረግ የለበትም፡፡ ዋናው የተለወጡት ሰዎች ማንነት፣ ቀናነት፣ ታታሪነት፣ ፅኑነትና ቆራጥነት ነው፡፡
ሎሬት ፀጋዬ ገ/መድህን በፃፈው “እሳት ወይ አበባ” ላይ፤ “እንቅልፍ ነው የሚያስወስድህ” የሚል ግጥም አለው፡-
“.. ትቻቸዋለሁ ይተዉኝ
አልነካቸውም አይንኩኝ
ብለህ ተገልለህ ርቀህ
ዕውነት ይተዉናል ብለህ
እንዴት ተስፋ ታደርጋለህ?
የተወጋ በቅቶት ቢ‘ኛ፣ የወጋ መች እንቅልፍ አለው
የጅምሩን ካልጨረሰው
እና በእኔ ይሁንብህ
እንቅልፍ ነው የሚያስወስድህ”
“ታንዛንያ፣ ዳርኤ ሰላም በሌተር ቦምብ ለተገደለው ለአልፍሬድ ሞንድ ላንድ - የፍሬሊሞው ታጋይ)
ዋናው ነገር፤ እኛ በቃን ብለን ብንተኛም ጠላቶቻችን አይተኙልንም ነው፡፡ ያ ማለት ጠላቶቻችን ሁሌም ይፈሩናል፡፡ ስለዚህም መቼም አይተኙልንም፡፡ ጠላት ያለው ሰው የሰላም እንቅልፍ እንደማይኖረው ሳይታለም የተፈታ ነው፡፡ መልካም ጎረቤት እንዲኖረን የምናደርገው እኛው ራሳችን ነን፡፡ ዲፕሎማሲን እንደዋዛ ማየት በራስ እንደመቀለድ ነው፡፡ “ሲግል በማንኪያ ሲበርድ በጣት” የተለመደ አካሄድ ቢሆንም አስቦ፣ ቀምሮ፤ ወጪ ገቢውን አስቦ መጓዝ ያባት ነው፡፡ አገርና ህዝብ መቼም አሉ፤ ይኖራሉም፡፡ ታሪክ ሰሪው ሰፊው ህዝብ ነው፡፡ መሪዎች ይለዋወጣሉ፡፡ ቀና መሪዎች ይቆያሉ፡፡ ከፊተኛው የኋለኛው ትምህርት ማግኘቱ ግድ ነው፡፡ አለበለዚያ ውድቀቱን ማፋጠኑ አይቀሬ ነው፡፡ ወቅት ምንጊዜም መሪዎችን መፈታተን አይሰንፍም፡፡ ስለሆነም መሪዎቻችን ወቅትን ማሸነፍ አለባቸው፡፡ ሥልጣን ከእርግብ ላባ ከወርቅ የተሰራ አልጋ አይደለምና ነቅቶ ማየት ብልህነት ነው፡፡ አዋቂ የሚናገረውን ማዳመት የመሪ ኃላፊነት ነው፡፡
“… አሁን የት ይገኛል ቢፈልጉ ዞሮ
መስማት ከማይፈልግ የባሰ ደንቆሮ”
የሚለው ግጥም የሚያፀኸየው ይሄንኑ ነው፡፡   

 የአሜሪካው ፕሬዚዳንት ዶናልድ ትራምፕ ልጅናየዋይት ሃውስ አማካሪዋ ኢቫንካ ትራምፕ ከሳምንታት በኋላ ኢትዮጵያንና አይቬሪኮስትን እንደምትጎበኝ መነገሩን ቢቢሲ ዘግቧል፡፡
ዋይት ሃውስ ባለፈው ረቡዕ ባወጣው መግለጫ እንዳለው፤ በሁለቱ አገራት የአራት ቀናት ቆይታ የምታደርገው ኢቫንካ ትራምፕ፤ በአይቬሪኮስት በሚካሄደው የሴቶች ኢኮኖሚያዊ አቅም ማጎልበት ጉባኤ ላይ የምትሳተፍ ሲሆን፣ በአገራቱ ከፖለቲካ መሪዎችና ከሴት ስራ ፈጣሪዎች ጋር ውይይት ታደርጋለች፡፡
ባለፈው የካቲት ወር ላይ የተጀመረውና በኢቫንካ ትራምፕ የሚመራው ውሜንስ ግሎባል ዲቨሎፕመንት ኤንድ ፕሮስፐሪቲ ኢኒሽየቲቭ እስከ 2025 የፈረንጆች አመት ድረስ ባላደጉ አገራት ውስጥ የሚገኙ 50 ሚሊዮን ሴቶችን ኢኮኖሚያዊ አቅም የመገንባት ግብ ማስቀመጡንና የኢቫንካ ጉብኝትም የዚህ ፕሮግራም አካል መሆኑን ዘገባው አስረድቷል፡፡

Page 5 of 428