Administrator

Administrator

Monday, 08 July 2024 20:03

ሳልሸኝህ

ሁሌ  ሳስብህ: በምናቤ: ስምል: ስገዘት: ላገኝህ
ካንተ: ወግ: እኔ: ልቋደስ: ሙጭርጭሬን: ላስነብብህ
ሙጭርጭሬን: ላነብልህ
ፈገግ: ስትል: ሲታየኝ: የ “በርታ” አይነት: ድብቅ: ደስታ
ስታይ: ፈለግህን: ስከተል: ‘ቤቱን: ቢመታም: ባይመታ’፣

መች: አውቄ: አንተ: እንዳለህ: ዝንፍ: የማይል: ቀጠሮ
እትብትህ: እንደጎተተህ: ሳይበጠስ: ከርሮ: ከርሮ
ከናትህ: ጐን: ልታሸልብ: ዳግም: ከቅፏ: ልትገባ
ናፍቆትዋን: ትወጣብህ: ዘንድ: እንዳትሰጋ: እንዳትባባ፣

ፍቅር: ሆነ: ያውም: የናት: የመጨረሻው: ስንኝህ
“ከናቴ: ዘንድ: ማርያም: ደብር” ያንተ: ኑዛዜ: ቃል: ምርጫህ፣

ግሩም: አንተ: ባለቅኔ: ጭር: አረከን: ስታሸልብ
ይኖራል: ብለህ: ነው: እዛ: ግጥም: እና: መነባንብ?

ያንተና: የመሰሎችህ: ይገርመኛል: አሁን: ሳስብ
ጠብ-ጠብ: እንደሻማ: ሰም: እንደተወርዋሪ: ኮከብ
የጥበብ: ዛር: በናንት: ሰፍሮ: ክረምት: ሳይል: ወይንም: በጋ
አይተናችሁ: ሳንጠግባችሁ: አብርታችሁ: ሌት: ሳይነጋ
መጥፋታችሁ: ላንተያይ: ላትገኙ: በፍለጋ፣

እንቆቅልሽ: ነው: ወዳጄ: ያካሄዳችሁ: አይነቱ
ቅኔ: ሆኗል: “ስውር: ስፌት”: “ጎሕ” ካልቀደደ: ሌሊቱ
ካልነጋልን: የማይገባን: ድብቅ: ሚስጥር: ብልሀቱ፣

እናም: ነባ…..

አልታደልኩም: ይመስለኛል: ካንተ : ርቄ: በመጥፋቴ
ልክ: እንዳልሆንኩ: አእምሮዬ: ቢነግረኝም: ሰውነቴ
‘ግዴለም: ይደርሳል: ነገ’ : አያስቸኩልም:  ማለቴ፣

ውዱ: ነብይ: ቃል: ልግባልህ: የማይታጠፍ: መሃላ
ሙጭርጭሬ: ጥራዝ: ሆኖ: ምናልባት: ቢቀናኝ: ኋላ
ስንብት: ልቋጥርልህ: ላሳለፍነው: ዝክር: ደስታ
ባልሸኝህም: እንዳሳቤ: ላትመለስ: የሄድክ: ለታ።

WT, Kampala, July 2024
ከወሰን ታዬ - ለውድ: ወዳጄ: ገጣሚ: ነቢይ: መኮንን: መታሰቢያ

ባለፈው ሳምንት ነቢይ መኮንን በአዲስ አድማስ ጋዜጣ ላይ በርካታ የውጭ አገር ጸሃፍት ሥራዎችን ወደ አማርኛ በመመለስ በተከታታይ ለአንባቢያን ማቅረቡ ተወስቷል፡፡ ከእነዚህም መካከል፡- “ዘ ዳቪንቺ ኮድ”፣ “ዉመን አት ፖይንት ዜሮ”፣ “ቱስዴይ ዊዝ ሞሪስ”፣ “ኤ ሾርት ሂስትሪ ኦቭ ትራክተርስ ኢን ዩክሬኒያን” ወዘተ ተጠቃሽ ናቸው፡፡ ይህንን ጉዳይ ዳግም ማንሳቴ አለምክንያት አይደለም፡፡ ከእነዚህና መሰል መጻሕፍት አብዛኞቹን ከባህር ማዶ ታመጣልን የነበረች አንዲት የጋራ ጓደኛችንና የአዲስ አድማስ ወዳጅ ትዝ ብላኝ ነው፡፡

ጸጋ ብርሃኑ ትባላለች፡፡ የአንጋፋው ደራሲ፣ ጸሃፌ ተውኔትና  ጋዜጠኛ ብርሃኑ ዘሪሁን ልጅ ናት፡፡ ጸጋ በአሜሪካ አገር የተማረችና የኖረች የሥነጽሁፍ አፍቃሪ ናት፡፡ ከአሜሪካ እንደመጣች ከአዲስ አድማሱ መሥራች አሰፋ ጎሳዬ ጋር በሥራ ጉዳይ ተዋውቃ፣ በዚያው ጓደኛችን ሆና የቀረች ይመስለኛል፡፡ (እንዴት ጓደኛችን እንደሆነች እንኳን በቅጡ አላስታውስም)፡፡ ለረዥም ዓመታት ጓደኛችን እንደነበረች ነው  የማውቀው፡፡ በየጊዜው የአዲስ አድማስ የሥርጭት መጠን ስንት እንደደረሰም ትጠይቀን እንደነበር ትዝ ይለኛል፡፡ ለአዲስ አድማስ ከኛ እኩል ነበር የምትጨነቀው፡፡  

አዲስ አድማስ ላይ ተተርጉመው ከወጡት መጻሕፍት አብዛኞቹን እርሷ ያመጣችልን ቢሆንም፣ አንድም ቀን ግን የእርሷን ስም በምስጋና ወይም ዕውቅና በመስጠት አንስተነው የምናውቅ አይመስለኝም፡፡ በዚህ አጋጣሚ ጸጋን በአዲስ አድማስ ዝግጅት ክፍል ስም ላመሰግናት እወዳለሁ፡፡ አይረሴ የወዳጅነት ዘመን ማሳለፋችንንም ላስታውሳት እፈልጋለሁ፡፡

(ኢ.ካ)

አዲስ አበባ ለኮሪደር ልማት ስትፈርስ፣ ቼ ባር ወይም በአካል ባር እንዳልሆነ መሆን ወይም ፒያሳ እንደ ኢራቅ የቴምር ዛፎች ስትገነደስ፣ ዶሮ ማነቂያ እንደ ካርቴጅ ስርወ መንግስት ስትገረሰስ አልታመምኩም፡፡

የጆሊ ባር እንዳልነበረ መሆንም ይሁን እንደ ጃፓኗ ከተማ እንደ ዋጂማ እንደ ትናንት ታይታ ዛሬ የወደመችው አዋሬ መጥፋት፣ የወይዘሮ ደኸብ ሬሲፒም ይሁን የገብረ ትንሣኤ ኬክ ቤቶች refurbish መደረግ አላስደነገጠኝም፡፡

ናይጄሪያዋን አቡጃን ሌጎስ፣ ኤሚሬቶች Old dubai ን በኒው ዱባይ፣ ግብፆች ጥንታዊ ካይሮ በአዲሱ ካይሮ፣ ህንዶች ጥንታዊውን ደልሂ በአዲሱ ዴልሂ እንደቀየሩ እኛም አዲስ አበባን ትተን አዲስ ከተማ ቢፈጠር የሚል ክርክርም አይመስጠኝም፡፡

የኔ ትዝታ እንደ ታይታኒክ ልትሰምጥ ያለችው ጋዜጦች ይነበቡበት የነበረ ቦታ ነው፤ ነቢይ ልጅነቴን ከጥበብ የሰፋበት ቦታ፤ እዚያ ነው የኔ ትዝታ።

እኔ ግን የነቢይ መኮንን አዲስ አድማስ ነው የሚያስደግጠኝ፤ ያ ቀይ ዳማ፣ ያ ብሩህ ኢትዮጵያ ለብቻው የመዘገበችለት ሪከርድ ነበረው። በምን በሉኝ ? ስሞትላችሁ

ወንጌላዊው ዮሐንስ እና ነቢይ መኮንን፡፡

ነቢይ እስረኛ ነበር፤ ወንጌላዊው ዮሐንስ ኢየሱስን በታማኝነትና በተለይ በትህትና እስከ መስቀሉ ተከትሎት ስለነበር ኢየሱስ ለዮሐንስ ምስጢር  ገለጠለት፤ በሮማው ንጉስ ዶሚሽያን ፍጥሞ ደሴት ታስሮ ሳለ ራዕይን ፃፈ ፤ በጌታና በባርያዎቹ መሀል ብራና ተወ፡፡

ነቢይ ያው ነው፤ ለኢህአፓነቱ ፈፅሞ ታዛዥ ሆነ፤ ደርግ ለአመታት አሰረው፤ ታስሮ ግን ተስፋ ነበረዉ፤ ትሁት ነውና አያሌ መጻሕፍትን አነበበ፤ እገደላለሁ የሚለውን ስሜት ትቶ Gone with the wind ይተረጉም፣ ግጥም ደግሞ የሲጃራ ወረቀት ላይ ይፅፍ ነበር፤ደርግ ነቢን አልገደለውም፤ እግዜር ይስጠው!!

ከእስር ወጣና እንደ ዮሐንስ በጥበብ ጌቶች (መጻሕፍት እና ፀሐፍያን ) እና ባርያዎች መሀል ተወዳዳሪ አልባ ድልድይ ሆነ፤ ነባ እጅግ ምጡቅ ነበር ፤ በሀርቫርድና ኦክስፎርድ መሀል መዋለል እየቻለ በኢትዮጵያዊ ሀሳብ መሀል ተጋ፤ ለIVy league ተወልዶ በካዛንቺስ ነሆለለ፡፡

በውጭ ሀገር First class መኪና፣ First class ቤትና ኑሮ ተመቻችቶለት ለአዲስ አድማስ ጋዜጣ ተሰዋ፤ ቅዱስ ዮሐንስ እነኋት እናትህ ተብሎ የጌታ እናት ተሰጠችው፤ ነቢይ ጥበብ እነኋት እናትህ ብላ የሰጠችውን አደራ ተወጣ።

ሳይቀና፣ ሳይሰደድ፣ ሳይማረር ገንዘብ ማጣትን ተቋቁሞ ትውልድ አፈራ፤ በኢትዮጵያ ታሪክ የነቢይ ብቻ የሆነ፣ ያ የአዳማ ጀንትል ማን የፈጠረው ቀመር አለ።

የአዲስ አድማስ ርዕሰ አንቀፅ

በ9ዐዎቹ  እና በ2000 መጀመሪያ የነበርን፣ ጋዜጣ የመግዣ ገንዘብ ያለውም ሆነ የሌለው፣ ምሁርም ይሁን ያልተማረ፣ አዲስ ነገርን፣ አዲስ ጉዳይን፣ ጦቢያን ያነበብን ሁላችን መጀመሪያ የምንመርጠው የነቢይን ርዕሰ አንቀፅ ማንበብ ነበር። የነቢይ ርዕሰ አንቀፅ ዝም ብሎ ርዕሰ አንቀፅ አይደለም፡፡
* ማንም ከያኒ
* ማንም ሀያሲ
* ማንም አዘጋጅ እርሱን ሊሆን አልቻለም።
እርሱ Simplicity ነው።

ማርክ ትዌይንን አቅልሎ እንዴት እንደሰጠን፤ በርናንድ ሾውን እንዴት እንዳፍታታልን? ኒዛር ቃባኒን እንዴት መሬት እንዳወረደው? ነባ አንድን ርዕሰ ጉዳይ ሲያፍታታ ሲፈልግ Leonardo -  Simplicity is the ultimate sophistication  እንዳለው ያደርጋል፤ ወይም ደግሞ Albert Einstein - If you can't explain it simply, you don't understand it well enough እንዳለው፡፡

ትልቁን concept በተረት ፣ በምሳሌ በገጠመኝ እያዋዛ በርዕሰ አንቀፁ ያጫውትሀል፤ አንድ ደራሲ ወዳጄን  ስለ አዲስ አድማስ ጋዜጣ ጠይቄው እንዲህ ብሎኝ ነበር :- "ርዕሰ አንቀፁን አንብቤ ሌላውን እተወዋለሁ"

ምነው ስለው፤ " ነብይ ነዋ" አለኝ። እውነት ነው፤ የራዕየ ዮሀንስ መጠቅለያ " ከዚህ መፅሐፍ የጨመረና የቀነስ " ይላል ፤ የኢትዮጵያ ፖለቲካም ይሁን ወቅታዊ ሁኔታ መጠቅለያ የአዲስ አድማስ ርዕሰ አንቀፅ ውስጥ ነበረ።

ነቢይ እና ፍጥሞ ደሴት

ደርግ እግዜር ይስጠው አልገደለውም ፤ ኢህአዴግ እግዜር ይስጠው ጋዜጣውን አልዘጋበትም፤

ለምን ?

ኢትዮጵያዊው ዮሐንስ እጅግ ጥበበኛ ነበር፤ ብሶታችንን የሚተነፍሱልን ጋዜጦች ሲዘጉ ነባ ነበር። ህመማችንን የሚያስተጋቡልን መፅሄቶች ጥለውን ሲሄዱ መፅናኛችን ህይወት ፖለቲካ ብቻ አይደለም የምትለን አዲስ አድማስ በነቢይ ብልጠት ቀጠለች፡፡

የግሪኳ ፍጥሞ ደሴት በኦቶማን ቱርክ በተያዘች ጊዜ ኦቶማኖች ፍጥሞን አላጠፉም፤ ታሪክ ነውና አስቀሩት ፤ የነባ ርዕሰ አንቀፅ ሊጠፋ ነበር፤ ኢህአዴግ አዲስ አድማስን ተወልን።

ነቢይ depth ሰጠን ፤ በሩቅ ምስራቅ ፍልስፍና  እያሰከረ፣ በምስራቃውያን ሀሳብ እያጠመቀን አበራን።

* የፀጋዬ ገብረመድህንን ሀሳብ አቅልሎ መሬት አወረደልን፤ ተደመምን፤ የሼክስፒርን ድርሰት "ሼክስፒር በፀጋዬ ብዕር እንዳለው" እያለ አስገረመን።

* ጌታቸው ቦሎድያን ስለሚባል ባዮኬሚስት ነግሮን የማናውቀውን ሠው በልባችን ሀውልት እስክንሰራለት አሰገደን።

* ምሁራን ከአደባባይ ጀርባ ስላለው ውሎአቸውና እውነት የሀገራቸውን ችግር ተረድተዋል ወይ የሚል ቃል ሲያወጣ ? በሱ ዘመን የፈኩ በምሁራን መካከል ስላለው አለመግባባት ሲያጠይቅ ፣ መቀናናታቸው ላይ ክስ ሲያነሳ የኢትዮጵያን ችግር ላይ ላዩን ሳይሆን ከስር ከመሰረቱ ሲያሳየን እውነትም ይህ ሰው ከአዳማ ሳይሆን ከፍጥሞ ደሴት ነው ያስብላል።

ነባ didn't give us Knowledge, but he taught us how to manage knowledge.

በመጨረሻ መፅናኛ አንድ፡-

ከመሞቱ በፊት መንግስት ቤት ሰጥቶታል ፤
ሀገሪቷን ሳይረግም በመሞቱ
Thank you ብልፅግና!

መፅናኛ ሁለት

እግዜር በሰማይ የገብረክርስቶስ ጭዌ ፣ የተስፋዬ ገሠሠ ጨዋታ ፣ የሰለሞን ደሬሣ ግጥም ፣ የበዓሉ ግርማ ወግ ሠለቸው፤

እንደ ህፃን መሣቅ ፣ መፈንደቅ ፣ በፈጠረው ፍጡር መገረም እና መኩራት አማረው ፤ ወግ እና የጣፈጠ ወሬ አማረው ፤ እርጋታ አማረው፤

ወሰደው ፤

መፅናኛ ሶስት

የነባን የጥበብ ጠብታ ለመወጋት

* ከስኮላ በስተደቡብ ወይም የኤጂያን ባህር ማቋረጥ አይጠበቅብህም።

* ሚዲትራኒያንን ማቋረጥ አልያም ትኬት ቆርጠህ  ግሪክ አትሄድም፤

* ራዕየ ዮሐንስ  " ኦሂ ስቶ 666 " የሚል አደናጋሪ ፅሁፍ ድንጋይ ላይ ተፅፎ ማግኘት አይጠበቅብህም፤

በፍጥሞ ደሴት ቁርጥራጭ ወርቆች ፣ የከበሩ ድንጋዮች እና ቁርጥራጭ የማርቆስ ወንጌል አለ።

የኢትዮጵያዊውን ዮሐንስ ቁርጥራጭ ጥበብ መቀጠል የፈለገ ሩቅ እንዳይሄድ

አዲስ አድማስ ርዕሰ አንቀፅን ይመልከት።

(ናትናኤል ከበደ)

ባለፈው  የፈረንጆቹ  መስከረም ወር 2023 ዓ.ም  ጡረታ መውጣታቸውን ያስታወቁት  የ92 ዓመቱ  የሚዲያ ቱጃር  ሩፐርት ሙርዶክ፤ ያለፉትን ሰባት አስርት ዓመታት ያሳለፉት ዓለም አቀፍ የሚዲያ ኢምፓየር በመገንባት ሲሆን፤ በዚህም ሂደት  በጋዜጠኝነት፣ በፖለቲካና በፖፕ ባህል ላይ ተፅእኖ ማሳደር ችለዋል፡፡  
በ1931 ዓ.ም በአውስትራሊያ ሜልቦርን የተወለዱት ሙድሮክ፤ ወደ ሚዲያው ዓለም የገቡት በወጣትነት ዕድሜያቸው  ነበር፡፡ ዛሬ በመቶዎች የሚቆጠሩ ጋዜጦች ባለቤት የሆኑት  ሩፐርት ሙርዶክ፤ በ19.1 ቢሊዮን ዶላር የተጣራ ሃብት በአሜሪካ 31ኛው፣ በዓለም ደግሞ 71ኛው ባለጸጋ መሆናቸውን የፎርብስ መጽሄት መረጃ ይጠቁማል::
የሩፐርት ሙርዶክ የሚዲያ አመራር ዘመን ቅሌት አልባ አልነበረም፤ በብሪታንያ ከሚገኙት የሚዲያ  ንብረቶቻቸው አንዱ፣ በ2011 ዓ.ም፣ ከስልክ ጠለፋ ምርመራ በኋላ የታጠፈ ሲሆን፤ ባለፈው ዓመት ፎክስ ኒውስ፣ ስለ 2020 የአሜሪካ ፕሬዚዳንታዊ ምርጫ የሃሰት  ወሬ ማሰራጨቱን በይፋ አምነዋል። የሆነስ ሆነና፣ ሩፐርት ሙርዶክ የሚዲያ ኢምፓየራቸውን እንዴት ገነቡ? እንዴትስ ለስኬት በቁ?
 ሙርዶክ የሚዲያ ግዛታቸውን እንዴት እንደገነቡ እነሆ፡-
1950ዎቹ
ትውልደ- አውስትራሊያዊው ተጽዕኖ ፈጣሪ ባለጸጋ፣ለመጀመሪያ ጊዜ ወደ ሚዲያ ሥራ  የገቡት፣ በ1952 ዓ.ም አባታቸው ኪት ሙርዶክ ከዚህ ዓለም በሞት ተለይተው፣ የቤተሰቡን ቢዝነስ ከወረሱ በኋላ ነበር፡፡  የ21 ዓመቱ የኦክስፎርድ ወጣት ተማሪ፤ በደቡባዊ አውስትራሊያ ይታተም የነበረውን ዘ ኒውስ ኦቭ አድላይድ የተሰኘ የአባቱን  ጋዜጣ፣ በባለቤትነት የመምራትና የማስተዳደር ዕጣ ፈንታ    ወደቀበት፡፡
1960ዎቹ
ሚስተር ሙርዶክ፣ በ1960ዎቹ በአውስትራልያ ውስጥ የሚታተሙትን  ዘ ሰንዴይ ታይምስ  እና ዴይሊ ሚረርን ጨምሮ  በርካታ የሀገር ውስጥ ጋዜጦችን ገዙ፡፡ በ1964 ዓ.ም ዘ አውስትራልያን የተሰኘውን የመጀመሪያውን የአውስትራልያ ብሔራዊ ጋዜጣ የጀመሩት ሙርዶክ፤ በመቀጠልም የሚዲያ ቢዝነሳቸውን ወደ ዩናይትድ ኪንግደም አስፋፉ፡፡ በ1969 ዓ.ም ዘ ኒውስ ኦቭ ዘ ወርልድ እና ዘ ሰንን በመግዛት ወደ ብሪቲሽ የሚዲያ ገበያ ሰተት ብለው ገቡ።
1970ዎቹ
ሩፐርት  ሙርዶክ፣ በሚዲያ ኩባንያቸው  በኒውስ ኮርፖሬሽን አማካኝነት፣ በ1973 ዓ.ም፣ ወደ አሜሪካ የሚዲያ ገበያ  የገቡት፣ አሁን በእጃቸው ላይ የሌሉትን ዘ ሳን አንቶኒዮ ኤክስፕረስ እና ዘ ሳን አንቶኒዮ ኒውስን በመግዛት ነበር፡፡ ከሦስት ዓመት በኋላ በ1976 ዓ.ም፣ ዘ ኒውዮርክ ፖስት ጋዜጣን ገዙ፡፡ ይህን ጋዜጣ  በ1988 ዓ.ም ከሸጡት በኋላ፣ በ1993 ዓ.ም  መልሰው የራሳቸው ንብረት አድርገውታል፡፡   
1980ዎቹ
 ሙርዶክ፣ በ1981 ዓ.ም፣ የብሪታንያ ጋዜጦች  የሆኑትን  ዘ ታይምስ እና ዘ ሰንዴይ ታይምስን የገዙ ሲሆን፤ በዚህም  የብሪታንያ የሚዲያ ገበያን ትልቁን ክፍል ተቆጣጠሩ፡፡ በ1985 ዓ.ም 20th Century Fox የፊልም ስቱዲዮን ገዙ። በ1986 ዓ.ም፣ ፎክስ  የብሮድካስት ኔትወርክን በመጀመር የቴሌቪዥን ቢዝነሳቸውን ማስፋፋት ያዙ፡፡
በ1986 ዓ.ም፣ ሙርዶክ፣ የብሪታንያ ጋዜጦቻቸውን ቢሮዎች፣ ህትመቱ፣ በትንሽ ጉልበት በቴክኖሎጂ  ወደሚከናወንበት ሥፍራ  በድንገት ያዛወሩ ሲሆን፤ ይህን ተከትሎም፣ የሥራ ማቆም አድማ የጠሩ ከ5,000 በላይ የህትመትና ፕሮዳክሽን ሠራተኞች ከሥራ ተባረሩ።
በ1987 ዓ.ም፣ ኒውስ ኮርፖሬሽን፣ Harper & Row የተሰኘውን አሳታሚ ድርጅት የገዛ ሲሆን፤ በ1990 ዓ.ም ከሌላው አሳታሚ ድርጅት ዊሊያም ኮሊንስ ጋር ከተቀላቀለ በኋላ፣ HarperCollins የሚል ስያሜ ተሰጥቶታል፡፡
በ1988 ዓ.ም፣ ሩፐርት ሙርዶክ፣ ስካይ ቴሌቪዥንን በብሪታንያ የመሰረቱ ሲሆን፤ በቀጣዩ ዓመት ኔትወርኩ ስካይ ኒውስ የተባለውን የኬብል ቲቪ የዜና ጣቢያ ጀመረ።
1990ዎቹ
በ1995 ዓ.ም፣ ኒውስ ኮርፖሬሽን፣ በአውስትራሊያ ውስጥ Foxtel የተባለ የብሮድካስት ኩባንያን ያቋቋመ ሲሆን፤ በዓመቱ  ስካይ ኒውስ አውስትራሊያን ጀመረ።
በ1996 ዓ.ም፣ ሚ/ር ሙርዶክ፣ ከቀድሞው የፕሬዚዳንት ሪቻርድ ኤም.ኒክሰን እና የጆርጅ ኤች. ደብሊው. ቡሽ የሚዲያ አማካሪ ሮጀር ኢ.አይልስ ጋር በመሆን፣ የፎክስ ኒውስ የኬብል ቻናልን ጀመሩ፡፡    ፎክስ ኒውስ፤ እንደ ቢል ኦ’ሬይሊ፣ ግሌን ቤክ፣ ታከር ካርልሰንና ሜጊን ኬሊ ያሉ ጋዜጠኞችን ሙያ በማጠናከር፣ ለወግ አጥባቂ የቴሌቪዥን  አስተያየት መለያ ምልክት ሆነ።
2000ዎቹ
 ሙርዶክ፤ የማይስፔስ ባለቤት የሆነውን ኢንተርሚክስ ሚዲያን በ2005 ዓ.ም በ580 ሚሊዮን ዶላር ገዙ። ከሌሎች የማህበራዊ ሚዲያ ተፎካካሪዎች ጋር ለመራመድ ተግዳሮት የገጠመው  ማይስፔስ፤ ከስድስት ዓመታት በኋላ በ35 ሚሊዮን ዶላር ተሸጠ።
 በ2007 ዓ.ም ሚ/ር ሙርዶክ፣ የዎል ስትሪት ጆርናል ባለቤት የሆነውን ዶው ጆንስ በ5 ቢሊዮን ዶላር ገዙ፡፡ ከግዢው በኋላ ብዙም ሳይቆይ፣ በጆርናል ኤዲቶሪያል ሰራተኞች ዘንድ  የአመራር ሽግሽግ የተደረገ ሲሆን፤ አዲሱ ባለቤቱ ጋዜጣው የበለጠ የፖለቲካ  ሽፋን እንዲኖረው ግፊት አደረጉ፡፡
2010ዎቹ
ከሚ/ር ሙርዶክ ልጆች አንዱ የሆነው ጄምስ ሙርዶክ፣ በ2011 ዓ.ም፣ የኒውስ ኮርፖሬሽን ምክትል ዋና ኦፕሬሽን ኦፊሰር ተብሎ ተሾመ። በዚያው አመት ለNews of the World መዘጋት ምክንያት በሆነው የስልክ ጠለፋ ቅሌት ተወጠረ።
 በ2012 ዓ.ም፣ ሩፐርት ሙርዶክ፣ የጋዜጣ ቢዝነሱንና  የመዝናኛ ቢዝነሱን በሁለት የተለያዩ አካላት ከፈሏቸው፤ በኒውስ ኮርፕ እና 20th Century Fox። ሙርዶክ፤ እነዚህን ሁለት ዘርፎች ዳግም  ለማዋሃድ አስበው ነበር፤ ነገር ግን እነዚያ እቅዶች ባለፈው ዓመት እንዲቀሩ ተደርገዋል፡፡
 በ2018 ዓ.ም፣ የሚ/ር ሙርዶክ የመጀመሪያ  ልጅ የሆነው  ላክላን ሙርዶክ፣ የሚዲያ ግዛቱ የቴሌቪዥን ክንፍ፣ የፎክስ ኮርፖሬሽን፣ ዋና ሥራ አስፈፃሚ በመሆን ተሾመ፡፡
የዋልት ዲስኒ ኩባንያ፣ የ21st Century Fox ንብረቶችን በ2019 ዓ.ም፣ በ71.3 ቢሊዮን ዶላር በመግዛት፣ የሩፐርት  ሙርዶክ የመዝናኛ ቢዝነስን የተቆጣጠረ ሲሆን፤  የቀረው የብሮድካስት ቢዝነስ አሁን Fox Corp. በተባለ አዲስ አካል ሥር ይመራል፡፡  
2020ዎቹ
ጄምስ ሙርዶክ በ2020 ዓ.ም፣ “በኩባንያው የዜና ማሰራጫዎች በሚታተሙ አንዳንድ የኤዲቶሪያል  ይዘቶችና በተወሰኑ ሌሎች ስልታዊ ውሳኔዎች ላይ በተፈጠሩ አለመግባባቶች” ሳቢያ ከኒውስ ኮርፖሬሽን ኃላፊነቱ  ለቀቀ፡፡
በሴፕቴምበር 2023 ዓ.ም፣ ሚስተር ሙርዶክ፣ የፎክስ እና የኒውስ  ኮርፖሬሽን አመራርን ለላክላን ሙርዶክ ያስረከቡ ሲሆን፤ አዛውንቱ ሙርዶክ የሁለቱ ኩባንያዎች የክብር  ሊቀ መንበር ሆነው ቀጥለዋል።

ዘመናዊነት የተለያዩ ሀሳቦችን ከምንም ነገር ጋር ሳያገናኙ፣ እንደያዙት ትርጉም ክብደት ማስተናገድ ነው። ይህ ማለት የትኛውንም ሀሳብ ያለምንም አጥር መመርመር ማለት ነው። ነገር ግን በተለይ በሀገራችን ከቅርብ ጊዜ ወዲህ እየተስተዋለ ያለው የዘመናዊነት ብሂል ከዚህ በጣም ይለያል። በደንብ መመርመር የሚገባቸውን ሀሳቦች ወቅታዊ እርግብግቢታቸውን እያዩ አብሮ የማራገብ፣ መንጋነት ይነበባል። ከነዚህ እርግብግቢቶች አንዱም ፌሚኒዝም ነው።
እ.ኤ.አ በ1848 እንደተጀመረ የሚታወቀው የፌሚኒዝም እንቅስቃሴ፣ አሁን ላይ 4ኛው ምዕራፍ ላይ እንደደረሰ ይነገርለታል። ይህ አብዮት ቀላል የማይባሉ ማህበረሰባዊ በደሎችን የተከላከለ ቢሆንም፣ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ግን ምህዋሩን እየሳተ ይገኛል።
እንደ ፌሚኒዝም ያሉ ለተጎጂ ማህበረሰብ ድምፅ ለመሆን የተጠነሰሱ እንቅስቃሴዎች አንዳንዴ ግባቸውን ከመምታት አልፈው ተፈጥሯዊ ምህዋራቸውን ሊስቱ ይችላሉ። ይህም የሚሆነው ይዘውት ከተነሱት ዓላማ ዘመም ማለት ሲጀምሩ ነው። ፌሚኒዝም ወንዶች በሴቶች ላይ ያደርሱት የነበረው ጭቆና የወለደው ብሶት ለበስ እንቅስቃሴ ነው። ጭቆናዎቹም በህግ፣ ሴቶችን እንደ ሁለተኛ ደረጃ ዜጋ የመቁጠር፣ እንደ ሰውም ዝቅ አድርጎ የማየት ነበሩ። በአሁኑ ጊዜ በተለይ 'በኋላቀር' አካባቢዎች ግቡን መምታት ባይችልም፣ እንቅስቃሴዎቹ በተካሄደባቸው ቦታዎች ግን ከታሰበለትም ርቀት በላይ በመጓዝ፣እንደውም ጭቆናውን ያደርስ የነበረውን 'ወንድ' በቁጥጥሩ ስር ማዋል ችሏል። የአሁኑ ምዕራፍ እንቅስቃሴ ግን፣ጉዞውን እንዳይቀጥል በራሱ  የአስተሳሰብ ገመድ ተጠፍሮ ይገኛል። ጠፍሮቹም፦ እኩልነት፣ፋሽንና ታሪክ አጥላይነት ናቸው።
የበፊቶቹ ፌሚኒዝም ምዕራፎች፦ እንዲመርጡ አይፈቀድላቸው የነበሩ ሴቶችን የመምረጥ መብት ማጎናጸፍ፤የትምህርት ዕድል አያገኙ የነበሩትን ማመቻቸት፤ጾታዊ ጥቃት ይደርስባቸው የነበሩትን መከላከልና የመሳሰሉትን ጭቆናዎች ማስቀረት መነሻቸው ነበር። ያሁኑ ምዕራፍስ? የአሁኑ፣ከላይ እንደተገለጸው ጭቆናዎቹ በአመዛኙ የተቀረፉ በመሆናችው፣እላይ ታች የሚባትልበት አላማ 'እኩልነትን'፣ከተቻለም የበላይነትን ማረጋገጥ ነው።
እኩልነት ከፖለቲካዊ አውድ ዉጪ ያለቦታው ሲገባ ከተፈጥሮ ጋር ይጣረሳል። ምክንያቱም፦ ተፈጥሮ ፍጥረቷን እኩል አድርጋ ስለማታውቅና፤እኩል የማድረግ አባዜም፣ ሀሳብም ኖሯት ስለማያውቅ! እኩልነት የሰው ልጅ ‘ኢጎ’ ቋንቋ ነውና!
'“ከጥላቻ በስተጀርባ ፍቅር አለ” እንዳለው ሲግማን ፍሮይድ፣ከእኩልነት በስተጀርባም የፉክክር ስሜት አለ። ፍጥረታት እኩልነት ለምን ያሻቸዋል? ሁሉም ለየቅሉ እስከተፈጠሩ ድረስ! ተፈጥሮ ውሻን ውሻ አደረገችው፣ በግንም በግ፣ ሰውንም ወንድ እና ሴት። ከዚህ ያለፈ አላማ ለፍጥረቶቿ አልሰጠችም። ነገር ግን የሰው ‘ኢጎ’ ሁሌም አርፎ ስለማይተኛ:- መጀመሪያ የሰው ልጅ የበላይ ፍጥረት ነው ብሎ አወጀ፣ ከዚያም ወንድ በሴት ላይ የበላይ ነው ብሎ ቀጠለ፣ ከዚያም ነጭ ከጥቁር ይበልጣል ብሎ አከለ፤ አሁን ደግሞ ሀብታምን ከድሃ በካፒታሊዝሙ እያበላለጠ፣ ‘ቆንጆን፣ ከአስቀያሚ በሞዴሊንጉ እየመነጠረ መኖሩን ቀጥሎበታል። ይሄ ሁሉ ከላይ የተጠቀሰችው፣ የበላይነት ስሜትን ካልተቀዳጀች ተረጋግታ መኖር የሚያቅታት ጭንቅላቱ ውስጥ ያለችው የፍርሃት ስሜቷ ንግስት ‘የኢጎ’ ስራ ውጤት ነው።
ተፈጥሮ ሴትን ሴት፣ ወንድን ወንድ ስታደርግ፣ ጾታቸውን ብቻ አለያይታ አይደለም፣ ግብራቸውንም እንጂ። ተወደደም ተጠላም ወንድ በወንዳወንድነቱ (masculine)፣ ሴት በሴታሴትነቷ (feminine) ተለያይቶ የተሰጣቸው ገጸባህሪ አለ። ይህ ልዩነት ከጾታ ባሻገር ኢኮኖሚያዊ፣ማህበራዊና ፖለቲካዊ ተሳትፏቸው ላይ ይንጸባረቃል ማለት ነው። ወቅታዊው ፌሚኒዝም ግን ይህን ልዩነት ጆሮ ዳባ በማልበስ፣ ሴትን እንደ ወንድ በማኖር እኩልነትን ለማስፈን እየጣረ ይገኛል።
በእስያ ይን እና ያንግ የሚባል ጽንሰ ሃሳብ አለ። አንዱ ጠንካራ፣ ፈጣንና ብሩህ ሲሆን፣ አንደኛው ደግሞ የሱ ተቃራኒ ነው። አንዱ በአንዱ ውስጥ ያለና፣ ልዩነታቸውንም አስጠብቀው የሚኖሩ ናቸው። አንደኛው ከአንደኛው አይበልጥምም አያንስምም። እንደው በአንጻር ይኖራሉ እንጂ። ታዲያ ይህን ሃሳብ ለብዙ ነገር ሲጠቀሙበት፣ወንድና ሴትንም የሚገልጹት በዚህ መንገድ ነው።
ሌላው ፌሚኒዝም በዚህ ወቅት እንደ ፋሽን የመያዙ ጉዳይ አሳሳቢነት ነው። ፅንሰ-ሃሳቦች እንደ ፋሽን የመያዛቸውን ጉዳይ አሳሳቢ የሚያደርገው፣ፋሽን በባህሪው፣አንድን ነገር ወቅታዊ ሽፋን በማልበስ፣የማይመረምሩ(shallow) ተከታይ መንጋዎችን የማፍራት ጉልበት ስላለው ነው። የፋሽን ታሪክ እንደሚያሳየው፣ነገሮች 'የሆይሆይታ'(hype) ጊዜያቸውን ጨርሰው የሚከስሙ ሲሆን፤ ፌሚኒዝምም ከፋሽናዊ ብርድልብስ ራሱን ገፎ ወደ ምክንያታዊነት እስካልመጣ ድረስ የመክሰሙ ነገር፣ የጊዜ ጉዳይ ነው።
ሌላው በወቅታዊው ፌሚኒዝም ላይ በከባዱ የሚታየው ጥራዝ ነጠቅነት፦ የኋላውን ታሪክ የበደል ጥላሸት እየቀቡ ኢ-ፍትሃዊ ጥላ የመፍጠር ነው። አባቶቻችን እናቶቻችንን ይጨቁኑ እንደነበርና፣ የኋለኛው ዘመን ታሪክ ለሴቶች የግዞት እንደነበር በማተት፣ የተጠቂነት ስሜትን (victim mentality) በመጫር አሁን ላይ የነፃነት ፍንጣቂ እንደታየ መወትወት ይስተዋላል። ይሄ ሃሳብ ስህተት መሆኑን ለማሳየት ምን ያህል ሴት ነገስታት ሃገራቸውን አንቀጥቅጠው ይገዙ እንደነበር ማሰብ በቂ ነው። እንደውስ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ አይደል እንዴ እንደ መስቀል ወፍ ብቅ የሚሉትን ሴት መሪዎች ማየት ብርቅ ያደረግነው? በሃገራችን እነ ምንትዋብ፣ ሳባ፣ ህንደኬ...፤ በአፍሪካ እነ ሞረሚ፣ ናንዲ፣ አሳንቴዋ፣ ናፈርቲቲ...፤በዓለም እንደ ሁቺ፣ ኢዛቤላ፣ ኤልሳቤጥ ወዘተ...። የማይካደው ሃቅ፣ በብዙ የዓለም ቦታዎች፣ ለሴቶች ንግስናና አስተዳደር፣ የተፈቀደና አልጋ ባልጋ የነበረ አለመሆኑ  ነው። ነገር ግን አሁን ለመሳል እንደሚሞከረው፣ወንድና ሴት የሰውና የእንስሳ ያህል መናናቅ ከነበራቸው፣እንዴት በሚንቃት መመራት አስቻለው? እሷስ መምራት የሚለው ሃሳብ እንዴት ውል አለባት?
ይልቅስ የድሮዎቹ ሰዎች ሴቶቹም ሴትነታቸውን፣ ወንዶቹም ወንድነታቸውን አምነውና ተቀብለው፣ ወንዱም ቤተሰቡን ማስተዳደሩ ላይ በመትጋት፣ ሴቷም ቤቷን በመምራት  ድርሻቸውን የተወጡ ናቸው። ይህ ሲባል ጥፋት ያልነበረባቸው አድርጎ መውሰድ  አይገባም። ነገር ግን የሚና ክፍፍላቸውን እንደ በጎ ነገር አድርጎ በመውሰድ፣እነሱንም ከጊዜያቸው አንጻር በመዳኘት፣ትሩፋታቸውንም ከአሁኑ ጊዜ ጋር በመስፋት መሄድ ያሻል።
መግቢያው ላይ እንደተገለጸው ፌሚኒዝም ጭቆናን ታግሏል። ወንድ ጡንቻውን እየተጠቀመ ይረግጣቸው የነበሩ ሴቶችን አስተንፍሷል። አሁን ላይ ላሉ ‘ስኬታማ’ ሴቶች ህልማቸውን ይኖሩ ዘንድም በር ከፍቷል። ሆኖም ግን ጭቆናን ሰበብ አድርጎ፣ ድሮም ለየቅል የነበሩትን ሰዎች፣ እኩል አደርጋለሁ ብሎ፣ ተፈጥሯቸውን እየጨቆነ ነውና ይመርመር! ይፈተሽ!

Saturday, 06 July 2024 20:49

የወቅቱ ጥቅስ

“ጠመንጃችሁን አስቀምጡ። ማሽንገናችሁን እጠፉ። መድፎቻችሁን ፊታቸውን መልሱ። በመቻቻል፣ በመሸማገል፣ በሰላም እመኑ… ሀገር በታሪክ ውስጥ የምታድገው በጦር ሜዳ በጀግንነት በሚዋደቅላት ሰራዊት ብቻ አይደለም። ፊቷን ወደ ፍትህና ወደ መብት መልሳ፣ ስለእነሱ ጠቀሜታ ስትቆም እንጂ፡፡”
(አሪስቲድ ብሪያንድ፤ የፈረንሳይ መሪ)

የሚቀጥለው ታሪክ ዛሬ እንደ ተረት ይወራል እንጂ ዱሮ እውነት  ነበር።
በአንድ የሀገራችን አሰቃቂ ዘመን፣ የአንድ ከፍተኛ፣ ሊቀመንበር  ነበር። ክፉ ነው ይሉታል - ልጆቻቸውን ከጉያቸው ነጥቆ ያሰረባቸው እናቶች። ክፉ አረመኔ ነው ይሉታል - ልጆቻቸው በእስር ቤት ተሰቃይተው የተገደሉባቸው አባቶች። ነብሰ-በላ ነው ይሉታል- ጓደኞቻቸው የሞቱባቸው ወጣት ባልንጀሮቹ።
ይህ ሰው ድንገት በከፍተኛው ውስጥ ያልታሰረ ወጣት ካየ፤ ስራውን በሚገባ ሳይሰራ እንደኖረና “አብዮታዊ ግዴታውን እንዳልተወጣ” አድርጎ ይቆጥረዋል ይባላል። ስለዚህም፤ ወጣቱን ያስጠራውና፤
“እስከዛሬ የታባክ ተደብቀህ ከርመህ ነው፣ ገና አሁን ብቅ ያልከው?” ይላል።
ወጣቱ ግራ በመጋባትና በድንጋጤ፤
“ኧረ በጭራሽ ተደብቄ አይደለም ጓድ!” ይላል።
“ጉድጓድ ግባና ጓድ አትበለኝ! በእንዳንተ ያለ ጸረ- አብዮተኛ ‘ጓድ’ አልባልም!”
“ኧረ ጸረ አብዮተኛ አይደለሁም ጓድ!”
“ጓድ አትበለኝ!- ጓድነቴን ታረክስብኛለህ ነው የምለው! ይልቅ ና ቅደም!” ብሎ እስር ቤት አስገባው።
አንድ ቀን ደግሞ ለእስረኞች ንቃት ለመስጠት እንደተለመደው ንግግር ሲያደርግ፤ አብዮት ጥበቃው ከጎኑ ነበር። “ጓድ፤ እነዚህ የምታስተምራቸው እስረኞች እኮ ማታ ይወጣሉ (ይገደላሉ)፤ ምን አለፋህ?” ይለዋል።
ሊቀመንበሩ፤ “ቢሆንም፤ ነቅተው ይሙቱ” አለ፤ ይባል።
ጊዜው አለፈና ይህ ሊቀ መንበር ዩኒቨርሲቲ ገባ- ህግ ሊያጠና። ታዲያ እንደ ሱው ህግ ት/ቤት በዚያው ወቅት የገቡ አንድ ተረበኛ ሽማግሌ አሉ። ከሱ ጋር የአንድ ሀገር ልጆች ናቸው። እኚህ ሽማግሌ ለረዥም ጊዜ ዳኛ ሆነው የሰሩ ናቸው።”
“ለምን ህግ ይማራሉ?” ሲሏቸው፤” “ምናባቴ ላድርግ፤ ‘ያለወረቀት አይሆንም’ የሚባልበት ዘመን መጣ’ኮ! እኛ ‘የልምድ አዋላጅ’ የሚል ስም ተሰጥቶናል!” እያሉ ሰውን ያስቁታል። ታዲያ አንድ ቀን እኚህ ጨዋ አዋቂ ሽማግሌ፣ ያን ከፍተኛ ሊቀመንበር እዚያው ዩኒቨርሲቲ ግቢ ውስጥ ያገኙትና፤
“ኦ እንዴት ነው ያገሬ ልጅ!” ብለው ሰላምታ ያቀርቡለታል።
“እንደምን ነዎ? በአገር አሉ እንዴ እርስዎ?” ይላል ሊቀመንበሩ።
“በዚያ አንተ ሞቅ ባለህ ዘመን ‘አለሁ’ አልልም ነበር እንጅ፣ መኖርስ አለሁ፤ ከአገሬ ወዴት እሄዳለሁ?” ይሉና ይመልሱለታል።
“እርስዎ ይሄን ተረብ ዛሬም አልተውትም እንዴ?”
“‘ተራቢ ቢሞት ተረብ አይሞትም’ ልበላ፤ በአንተው የትግል ቋንቋ!”
“እንደው አሁን ጊዜው አለፈ እንጂ፣ እርስዎን ነበር እዚያ እስር ቤት አስገብቶ እየገረፉ ማስለፍለፍ?”
“በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ! ምነው ምን አደረኩህ ያገሬ ልጅ! እኔን! የገዛ ወገንህን! በአገር አማን ትጎመዠኝ!?...እሱ ይቅር ይበልህ…”
አሉና ወሬውን ለመቀየር “ለመሆኑ ወደ ግቢ ምን እግር ጣለህ?” ብለው ይጠይቁታል።
“ኦ አልነገርኩዎትም ለካ! እዚህ ዩኒቨርሲቲ ህግ እየተማርኩ‘ኮ ነው። ሁለተኛ አመቴ ነው” አላቸው ሞቅ አድርጎ።
ይሄኔ ሽማግሌው በድንጋጤ አናታቸውን ይዘው፤
“እንዴ!! ፈርደህ ጨርሰህ?!”
***
ፍትህና ርትዕ የጎደለው ስርዓት ውስጥ መኖር ክፉ መርገምት ነው። የአሜሪካ ሰብአዊ መብት ተሟጋቹ ማርቲን ሉተር ኪንግ ጁኒየር፤ “የትም ቦታ የሚፈጠር ኢ-ፍትሃዊነት፤ በማንኛውም ቦታ ያለውን ፍትሃዊነት አደጋ ላይ ይጥለዋል” እንዳለው የፍትህ መጓደል እዚህ ድንበሩ፤ እዚህ ክልሉ የሚባል አይደለም። ግፍ በተፈጸመበት ቦታ ሁሉ ስለእውነት የሚጮሁ ድምጾች  ይጮሃሉ-ህያዋን ቢጠፉም ከመቃብር የሚመጡ አሉ ይባላል።
በታሪክ ያየነው ኢ-ፍትሃዊ ሁኔታ እንዳይደገም፣ የአሁን ዘመን ዜጎች ስለ መብትና ስለ ፍትህ መቆም፣ ስለ ሰላም ስንል መንገዶችን ሁሉ ማጽዳት ይገባል። ፍትህን የሚያጎድሉ፣ ዳኝነትን የሚያዛንፉ ሰዎች ድርጊታቸው አይታወቃቸውም። ስለሆነም የተበዳዮች ቁጥር ይበረክትባቸዋል። ያም ሆኖ ራሳቸውን አይጠብቁም። ታሪክ ይጠይቀናል አይሉም። የእነሱ ሚዛን፣ የእነሱ ፍርድ ሁሌ ልክ፣ ሁሌ ፍጹም ይመስላቸዋልና ህሊናቸውን አይቆረቁራቸውም።
ፒዩ ባሮዣ የተባለ ታዋቂ ጸሃፊ፤ “እንደ እኔ ጉዳዩ ውስጥ የሌለ ማንም ተራ ሰው፤ ጅብን፣ ሸረሪትንና ዛፍን በማየት በቀላሉ መኖር እንዳለባቸው ይረዳል። የፍትህ አስተሳሰብ አለኝ የሚል እቡይ ሰው ግን ጅብን ሲገድል፣ ሸረሪትን በእግሩ ሲድጣትና ከዛፍ ጥላ ስር ሲቀመጥ፣ ደግ ስራ የሰራ ይመስለዋል” ሲል ግራሞቱን የጻፈው በተመሳሳይ አንፃር ነው። ሰውም እንደ ሀዲስ አለማየሁ ስንኝ፤ “ዳሩ ዳኛ የለም ልተወው ግዴለም” ይላል እስከ ጊዜው።
የህዝብን ምሬትና ብሶት እህ ብሎ ማስተናገድ፣ የማንኛውም መሪ፣ ሃላፊና ሹም ግዴታ ነው። ህዝብን ባልሆነ ተስፋ መሸንገልም ሆነ መዋሸት ኗሪ ትዝብት ማትረፍ ነው። አንዴ ሊሸነገል ቢችል፣ ሌላ ጊዜ በጄ አይልምና።
ኦሉፍ ፓርም የተባሉ ስዊድናዊ መሪ፤ “ስለ ማህበራዊ ፍትህ የሚጠየቁ ጥያቄዎችን በሃይልና በወታደራዊ ጉልበት ምላሽ ለመስጠት መሞከር ከንቱ ቅዠት ነው። ከቶም ህዝቦች አይተውት የማያውቁትን ነጻነት እከለከልላችኋለሁ በማለት የህዝቦችን እምነት ለማግኘት መሞከር ከንቱ ድካም ነው” ያሉት እንዲህ ያለውን ሁኔታ አይተው ሳይሆን አይቀርም። በየትኛውም የስልጣን እርከን ላይ ብንሆን የሰራነው ክፉ ስራ እንደ ጥላ ይከተለናል። ፍትሃዊ ያልሆነ እርምጃና ጠያቂ የለንም በሚል የጉልበት ስሜት የሚመነጭ መብት-ረገጣ፤ በታሪክ የሚያስከፍለው ዋጋ ቀላል እንዳልሆነ የአያሌ አገራት ታሪክ ይመሰክርልናል።
አሪስቲድ ብሪያንድ የተባሉ የፈረንሳይ መሪ፤
“ጠመንጃችሁን አስቀምጡ። ማሽንገናችሁን እጠፉ። መድፎቻችሁን ፊታቸውን መልሱ። በመቻቻል፣ በመሸማገል፣ በሰላም እመኑ… ሀገር በታሪክ ውስጥ የምታድገው በጦር ሜዳ በጀግንነት በሚዋደቁላት ሰራዊት ብቻ አይደለም። ፊቷን ወደ ፍትህና ወደ መብት መልሳ ስለእነሱ ጠቀሜታ ስትቆም እንጂ” ብለው ነበር።
ሚዛናዊ ያልሆነ የአእምሮ ፍርድ፣ ስሜታዊ የሆነ ኢ-ዲፕሎማሲያዊ አካሄድ፣ የማይፈጸም ባዶ-ተስፋና ሰበካ፤ ፍትህን ሊያጨልም የሚችል የማንአለብኝ አቅጣጫ… በታሪክ አስወቃሽ እንደሚሆኑ አንድና ሁለት የለውም። በጊዜ መታረም ያለባቸውን ነገሮች፣ በግትርነት አሻፈረኝ የሚል፣ የማታ ማታ እጣፋንታው፣ “እኔስ ሮጬ አመልጣለሁ፤ ታሪኬ ወዴት ያመልጣል?” ያለው ሰው አይነት እንዳይሆን፣ ከወዲሁ ማሰብ የአባት ነው።

በአዲስ አበባ ከተማ የ2016 ዓ.ም. የአረንጓዴ አሻራ የማስጀመሪያ መርሃ ግብር መካሄዱ ተገልጿል። የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ከንቲባ ክብርት አዳነች አቤቤ፣ ምክትል ከንቲባ አቶ ጃንጥራር አባይ፣ የአዲስ አበባ ከተማ የብልጽግና ጽሕፈት ቤት ሃላፊ አቶ ሞገስ ባልቻን ጨምሮ የተለያዩ የመንግስት ሃላፊዎች፣ የሃይማኖት አባቶች፣ አምባሳደሮች፣ የተፎካካሪ ፓርቲ አመራሮች፣ እንዲሁም ጥሪ የተደረገላቸው የሕብረተሰብ ክፍሎች በመርሃ ግብሩ ላይ ተገኝተዋል።

መርሃ ግብሩን በንግግር ያስጀመሩት ክብርት ከንቲባ አዳነች አቤቤ "የምንተክለው ዛሬን አይደለም። ለነገም ጭምር ነው" ያሉ ሲሆን፣ የአረንጓዴ አሻራ እንቅስቃሴ መተባበርን እና በጋራ መስራትን በይፋ ያሳየ ስራ ስለመሆኑም ገልጸዋል።

አክለውም፣ በአረንጓዴ አሻራ እንቅስቃሴ የከተማዋ የደን ሽፋን ማደጉን በማውሳት፣ "ከባለፈው ዓመት በላቀ መጠን የመተከል እና የመከታተል ስራ መስራት አለብን" ብለዋል። እንዲሁም ችግኝ የመትከሉን ስራ ከማጠናከር ባሻገር የመንከባከብ ሂደት መከወን እንዳለበትም በአጽንዖት አመልክተዋል።

ባለፈው ዓመት 17 ነጥብ 5 ሚሊዮን ችግኞች በከተማ አቀፍ ደረጃ እንደተተከሉ ያስረዱት ክብርት ከንቲባ አዳነች፣ በዘንድሮው የታቀደው 20 ሚሊዮን ስለመሆኑ ጠቅሰዋል። በተጨማሪም፣ "የችግኝ ተከላ ስራው በዓለም አቀፍ ስታንዳርድ ደረጃ ለማሳደግ በጋራ መስራት ይገባል" ሲሉ ነው የተናገሩት።

"በጋራ ስንተክል የምንተክለው ችግኝን ብቻ ሳይሆን መተባበር እና አብሮ የመስራትን አሻራ ጭምር ነው።" በማለት መልዕክታቸውን አስተላልፈዋል።

የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ውበት እና አረንጓዴ ልማት ቢሮ ሃላፊ ወይዘሮ ይመኙሻል ታደሰ በበኩላቸው፣ የአረንጓዴ ልማት ከሌሎች መሰረተ ልማት ስራዎች ጋር አብሮ የሚሰራ መሆኑን በመጥቀስ፣ "ባለፉት አምስት ዓመታት ዜጎች ያለልዩነት አገር በቀል እጽዋት፣ የውበት እጽዋት፣ የአትክልት እና ፍራፍሬ እጽዋት ተክለዋል" ብለዋል።

በእነዚሁ ዓመታት በከተማ አስተዳደሩ አማካይነት ከ58 ነጥብ 2 ሚሊዮን በላይ ችግኞች እንደተተከሉ የገለጹት የቢሮ ሃላፊዋ፣ የእነዚህ ችግኞች 89 በመቶ የጽድቀት መጠን ማስመዝገባቸውን አብራርተዋል።

ወደፊት በአምስት ኮሪደሮች ተለይቶ የሚሰራ ስራ እንደሚኖር የገለጹ ሲሆን፣ "የተገኙ ድሎች ላይ ሳንኮራ ሌሎች ስራዎችን መስራት ያስፈልጋል" ነው ያሉት።

"ለችግኞች ተገቢውን እንክብካቤ ካላደረግን ወልዶ እንደመጣል ይቆጠራል" ሲሉ የተተከሉ ችግኞችን መንከባከብ እንደሚያስፈልግ በአንክሮ ተናግረዋል። እስከዛሬ ለተገኙ ስኬቶች ባለድርሻ አካላትን፣ በተለይም ክብርት ከንቲባ እና አስተባባሪ ኮሚቴውን አመስግነዋቸዋል።

የአዲስ አበባ ከተማ የደን ሽፋን በ2010 ዓ.ም. ከነበረበት 2 ነጥብ 8 በመቶ ወደ 17 በመቶ ከፍ እንዳለ በማስጀመሪያ መርሃ ግብሩ ላይ ተገልጿል።

በዚሁ መርሃ ግብር ላይ ከፍተኛ የመንግስት አመራሮችን ጨምሮ የተለያዩ የሕብረተሰብ ክፍሎች የችግኝ ተከላ ስነ ስርዓት አከናውነዋል።

"የምትተክል አገር፣ የሚያጸና ትውልድ" በሚል መሪ ቃል የተጀመረው ሁለተኛ ምዕራፍ፣ ሁለተኛው ዙር የአረንጓዴ አሻራ መርሃ ግብር በተለያዩ ክፍለ ከተሞች ተጠናክሮ እንደሚቀጥል ለማወቅ ተችሏል።

ተረጂነት እንደ አዙሪት ነው። ከዓመት ዓመት የእርዳታ እጅ ይጠብቃሉ። ጥገኛ ይሆናሉ። የረጂዎች ታዛዥና ተጎታች የመሆን ፈተና ላይ ይወድቃሉ። ክብራቸውን ያጣሉ። እንዲህ ዐይነት ውርደት፣ በጭራሽ ለኢትዮጵያ አይመጥንም። ለየትኛውም አገር ቢሆን፣ የእርዳታ አዙሪት ጥሩ አይደለም። ለኢትዮጵያ ግን በጭራሽ መታሰብ አልነበረበትም።   
ኢትዮጵያ ትልቅ አገር ናት። የረዥም ዘመን ታሪክ ባለቤት ናት። በዓለም ታሪክ ሕልውናቸውን አስጠብቀው በነጻነት መዝለቅ የቻሉ አገራት ቢበዛ ከአምስት አይበልጡም። ኢትዮጵያ ከእነዚህ ውስጥ የምትጠቀስ ናት። ለአፍሪካ የነጻነት ፋና ለመሆን የበቃች አገር ናት። በሕዝብ ብዛት ከዓለም 10ኛ ናት። የተረጂነት አዙሪት በፍጹም ለኢትዮጵያ አይመጥንም።
ከተረጂነት ጋር አብሮ የሚመጣ የታዛዥነትና የተጎታችነት ውርደት ለኢትዮጵያ ባህል “አለርጂክ” ነው። ባለፉት ወራት በመላ አገሪቱ በተካሄዱ ውይይቶች ላይ፣ ከሕዝብ የቀረቡ ሐሳቦች ይህን መንፈስ አጉልተው አሳይተዋል ይላሉ - የአዲስ አበባ አስተዳደር የሕዝብ አደረጃጀት ም.ኀላፊ ዘውዱ ከበደ።
ለነገሩ፣ “ውርደት ከኢትዮጵያ ባህል ጋር አይሄድም” የሚል የቁጭት ስሜት በሕዝብ ዘንድ መፈጠሩ አይገርምም።
የሕዳሴ ግድብን ለማስተጓጎልና ለማስቆም ብዙ ዘመቻ ተካሂዶብናል። በኢትዮጵያ ላይ እየተደራረበ የመጣባትን የውጭ ጫና እንዲሁ እንደዘበት የምንረሳው አይደለም። ኢትዮጵያውያንን ምንኛ እንዳስቆጣቸው እናስታውሳለን። እንዴት አናስታውስም? በኛው ዘመን በኛ ትውልድ ላይ የተካሄደ ዘመቻ ነው። የራሳችን ታሪክ፣ የእያንዳንዳችን ትዝታ ነው። ያኔ ክፉኛ አንገብግቦናል። አንገሽግሾናል። ዛሬም ይከነክነናል።
“የሕዳሴ ግድብ ግንባታን አቋርጡ፤ አለበለዚያ እርዳታ እንከለክላለን!” የሚል ማስፈራሪያ ሊዋጥልን ይቅርና መታሰቡ ራሱ ይተናነቀናል።
በተረጂነት ሰበብ የሚመጣ የውጭ ጫና እንዲህ ነው ለካ! አገራዊ ጸጋዎቻችንን እንዳናለማ፣ ሠርተንና ገንብተን እንዳናድግ አስሮ የሚይዘን ከሆነ ዘላለም “ተረጂ” ሆኖከመቅረት ውጭ ምን አማራጭ ይኖረናል? ተረጂነት ተረጂነትን ይወልዳል የሚባለውም ለዚህ ነው። “ተረጂነት ይብቃ” ብለው በጥሰው ሰብረው ካልተላቀቁ፣ እውነትም “አዙሪት ነው” ያስብላል።
በእርዳታ ሰበብ የውጭ ጫናዎችን አሜን ብለን ከተቀበልንማ፣ ከነአካቴው ተስፋችንን ከማጨለም አይመለስም። አገራችን ታዛዥና ተጎታች እንድትሆን ከተገደደች፣ እንዴትስ “አገር አለን” ብለን በሙሉ ልብ እንናገራለን?
የተረጂነት ጣጣ ብዙ ነው። ሁሉንም ነገር ይነካል ይላሉ አቶ ዘውዱ። የሕልውና ፈተና ይሆናል። በኑሮ የመሻሻል ተስፋን ያጨልማል። የኢኮኖሚ እድገትንና የአገር ብልጽግናን አሰናክሎ ያስቀራል። የአገር ሉዓላዊነትን ያሳጣል። የአገርና የሕዝብ ክብርን ያዋርዳል። በተረጂነት ሳቢያ የሚመጡ አደጋዎች ኢኮኖሚን፣ ፖለቲካን፣ ባሕልን ሁሉ የሚያበላሹ ናቸው።
ተረጂነት ያስጠቃል፤ ያስደፍራል፤ ያዋርዳል። ከተረጂነት የመላቀቅ ጉዳይ ትልቅ አገራዊ አጀንዳችን መሆን ያለበትም በእነዚህ ምክንያቶች ነው። ተስፋችን መጨለም የለበትም። ለልጆቻችን ተረጂነትንና የዕዳ ሸክም ማውረስ የለብንም። የአገራችንና የሕዝባችን ክብር መታደስ አለበት። አገራችን ከተረጂነት በመላቀቅ ወደ ብልጽግና መጓዝ አለባት። ደግሞም ትችላለች። እንደምትችልም ከራሳችን ልምድና ከራሳችን የስኬት ጅምሮች መማር እንደማይከብደን አቶ ዘውዱ ይገልጻሉ።
ፈተናዎችን በራሳችን ዐቅም ተቋቁመን መሻገር እንደምንችል በኮቪድ ወረርሽ ወቅት አይተናል። ያኔ የዓለም ኢኮኖሚ እንደተናጋ ሁላችንም እናውቃለን። የብዙ አገራት ኢኮኖሚ አሽቆልቁሏል። በኢትዮጵያ ግን፣ ወረርሽኙን ከመከላከልና ከመቋቋም ጎን ለጎን፣ ኢኮኖሚያችንም እንዲያድግ በጥበብና በትጋት ስለጣርን ተሳክቶልናል።
በኮቪድ ምክንያት የዓለም አየር መንገዶች ከፍተኛ ኪሳራ ላይ ሲወድቁ፣ የኢትዮጵያ አየር መንገድ ግን በርካታ የመፍትሔ አማራጮችን በመጠቀም ውጤታማ ሆኗል። ይህም ብቻ አይደለም። ወረርሽኙን ከመከላከል ባሻገር ለዘለቄታው የሚጠቅም መንገድ የጤና ተቋማትን ዐቅም ለማሳደግ ተችሏል።
ኢትዮጵያ ችግሮችን በራሷ ዐቅም ተቋቁማ ወደ ተሻለ ከፍታ ማደግ አያቅታትም።   
የሕዳሴ ግድብ ግንባታን በሚመለከት በኢትዮጵያ ላይ የደረሰባት ከባድ የውጭ ጫናም ሁለት ነገሮችን ያስተምረናል ብለው እንደሚያምኑ አቶ ዘውዱ ይገልጻሉ።
በአንድ በኩል፣ በዓለም ታሪክ ታይቶ የማይታወቅ ከባድ የውጭ ጫናዎችን ተቋቁመን፣ በዓለም የዲፕሎማሲ መድረክ ላይ ተከራክረን የማሸነፍ ዐቅም እንዳለን አሳይተናል።
በሌላ በኩል ደግሞ፣ በተረጂነት ሳቢያ የሚመጣ የውጭ ጫና የቱን ያህል አደገኛና የቱን ያህል ቅስም ሰባሪ ሊሆን እንደሚችል በዚሁ አጋጣሚ አይተናል። የሕዳሴ ግድብን ለማስቆም የተካሄደ ዘመቻ፣ የኢትዮጵያን ቅስም ለመስበር የተደረገ ሙከራ ነው ማለት ይቻላል።
ለዚያውምኮ የሕዳሴ ግድብ ግንባታ በብድር ወይም በእርዳታ የሚካሄድ አይደለም። እንደዚያ ቢሆንማ፣ ከመነሻውም እርዳታና ብድሩ አይገኝም። በሆነ ተዓምር እርዳታ ተገኝቶ የግድብ ግንባታ ቢጀመርም፣ የትም አይደርስም ነበር። እርዳታው ተቋርጦ፣ የግድብ ግንባታው ምኞት ብቻ ሆኖ ይቀር ነበር።
ኢትዮጵያ በራሷ ዐቅም የምትገነባው ስለሆነ ነው፣ “የአገር ምኞት” በተግባር “የአገር እውነት” ወደመሆን እየተሸጋገረ የመጣው።
እንዲያም ሆኖ፣ ከብዙ ፈተና አላመለጠም። በውጭ እርዳታ የሚካሄድ ፕሮጀክት ባይሆንም፣ ከውጭ ጫና አልዳነም። ለምን? ኢትዮጵያ ተረጂ አገር ስለሆነች በውጭ ተጽዕኖ እጇን መጠምዘዝ እንችላለን ብለው ስላሰቡ ነው። “በደካማ ጎኗ እንግባባት” ብለው ነው የተረባረቡባት። “ለግድብ ግንባታ ባይሆንም ለሌላ ለሌላ ነገር እርዳታ ትፈልጋለች። እርዳታ እንቀንሳለን፤ ከፈለግንም እናቋርጣለን” ብለው የማስፈራራት ቀዳዳ አግኝተዋል።
እንዳሰቡት ቢሳካ ኖሮ፣ በኢትዮጵያ ታሪክ ውስጥ ለዘመናት ይቅር የማንለው ከባድ የታሪክ ቁስል ይሆንብን ነበር። ትልቅ የታሪክ ስብራት በደረሰብን ነበር። ፊት ለፊት የመጡ ወረራዎች ሳይበግሯት አሸንፋ መልሳለች። ወረራው እጅግ ሲከፋም “አሻፈረኝ” ብላ፣ እጅ ሳትሰጥና በባርነት ሳትንበረከክ ነጻነቷን አስከብራለች። ዛሬ፣ “ያለ ጦርነት እንድትንበረከክ መጠበቃቸው” ቢያንገበግበን አይገርምም። ነገር ግን አንድ እውነት እንድንገነዘብም ያስገድደናል። ተረጂነት ያስደፍራል፤ ያስጠቃል፤ ለውርደት ያጋልጣል።
ታዲያ ምን እስኪመጣብን፣ ምን እስክንሆን ነው የምንጠብቀው? እስከ መቼስ ነው የእርዳታ እጅ የምናየው? ለምንስ ነው ከትውልድ ወደ ትውልድ የምናስተላልፈው?
በእርግጥ “ተረጂነት ውርደትን ያመጣል” ሲባል፣ በአደጋ ጊዜ ያገዙንን ሰዎች ለማጣጣል አይደለም። እንዲያውም በችግር ጊዜ የደረሱልንን ለማመስገን አናመነታንም። ኢትዮጵያ ታመሰግናለች። አቶ ዘውዱ እንደሚሉት፣ የኢትዮጵያ መንግሥትም ከማመስገን ወደ ኋላ አይለም። ክብር የሚያውቅ አገር ውለታ ቢስ አይሆንም። ኢትዮጵያ ደግሞ ክብር ታውቃለች። ታሪኳ ነው። ባለውለታዎቿን ታመሰግናለች።
ነገር ግን “ተረጂ” ሆና ለመቅረት አይደለም። በጭራሽ! አዎ ተከባብሮ መተጋገዝ መተባበር መልካም ነው። ኢትዮጵያም በተለያዩ ጊዜያት የራሷን ድጋፍ እንዳበረከተች አቶ ዘውዱ ይናገራሉ። በቅርቡ የሩዋንዳው መሪ ፖል ካጋሜ ለጠቅላይ ሚኒስትራችን ለዶ/ር ዐቢይ አህመድ ያበረከቱትን የምስጋና ሽልማት በምሳሌን እንደሚጠቀስም ገልጸዋል።
በበርካታ የአፍሪካ አገራት የኢትዮጵያ ሰላም አስከባሪ ኃይል ተሰማርተዋል። ኢትዮጵያዊ ጨዋነትን የተላበሱና የአፍሪካዊ ወዳጅነትን የሚያስፋፋ አገልግሎት ሰጥተዋል።
አሜሪካ የሽብር ጥቃት በደረሰባት  ጊዜ ኢትዮጵያ አጋርነቷን አሳይታለች። ኢትዮጵያውያን ደቡብ ኮሪያ ድረስ ሄደው መስዋዕት ከፍለዋል። ወደ ኮንጎም ተሰማርተዋል ። በርካታ የአፍሪካ አገራት ከቅኝ ግዛት እንዲላቀቁ በስልጠና ረድታለች። በዓለም መድረክ ዋና አለኝታ ሆናላቸዋለች።
እንዲህ ዐይነት የመደጋገፍ ተግባር መልካም ነው። ከመከባበር ጋርም ይሄዳል።
አንዱ አገር የሁልጊዜ ረጂ፣ ሌላኛው አገር የሁልጊዜ ተረጂ ከሆነ ግን መከባበርን ያጠፋል።
“ተረጂነት? በጊዜ ካልተገታ፣ “ጌታና አሽከር” ለመፍጠር ይጠቀሙበታል። በወዳጅነት ምትክ የበላይነትና የበታችነት ስሜትን ያቀነቅኑበታል።
“ቁጭ ብድግ በሉልኝ” የሚል ይመጣል።
“ማን ነው አጎንብሶ ያልሰገደልኝ? ማን ነው ተንበርክኮ ያልተለማመጠኝ?” ብሎ ማስፈራራት ይጀምራል።
ኢትዮጵያ እንዲህ ዐይነቱን ውርደት እንደማትቀበል በተደጋጋሚ አሳይታለች።
ሁነኛውና አስተማማኙ መፍትሔ ግን፣ ችግሮችን በራሷ ዐቅም ተቋቁማ በመሻገር  የሚገኝ መፍትሔ ነው። ከተረጂነት በመውጣት ነው የውጭ ጫናዎችን ሙሉ ለሙሉ ማምከን የሚቻለው።
እንዲያውም ከረጂነት ውጥታ ወደ ብልጽግና ስትሸጋገር፣ ለወዳጅነት የሚፈልጓት፣ የሚያከብሯትና ከጎኗ የሚቆሙ ይበረክታሉ። በጠላትነት ስሜት ክፉ የሚያስቡባት ደግሞ ሐሳባቸውን ይለውጣሉ። ወይም ለክፉ ያሰቡትን ዋጥ አድርገው ያስቀሩታል። ለጥቃት ሊሰነዘሩ የነበሩ እጆችም ይሰበሰባሉ።
ከተረጂነት የመላቀቅ ሐሳብ ዙሪያ በመንግሥትና በሕዝብ መካከል እንዲህ ዐይነት መሠረታዊ መግባባትና የጋራ ጽኑ ዓላማ በውይይት እንደተፈጠረና በውይይት እየዳበረ መሄድ እንዳለበት የገለጹት አቶ ዘውዱ፣ ከተረጂነት መላቀቅ ለኢትዮጵያ የሉዓላዊነትና የአገር ክብር ጉዳይ ነው በሚለው የጋራ አቋም ላይ ሙሉ እምነት እንዳላቸው ይገልጻሉ።
የውጭ ኃይሎች የሚደፍሩት ሳይሆን የሚያከብሩት አገር፣ የሚያከብሩት ሕዝብ እንሆናለን - ለጠላትነት የሚያስቡት ሳይሆን ለወዳጅነት የሚፈልጉት።
ደካማ ጎን አይተው ጥቃት የሚሰነዝሩበት ሳይሆን፣ “ጠንካራ ነው፤ ለምንም አይበገርም፤ የሚቃጡበትን ያሳፍራል” ብለው ይጠነቀቃሉ። “ኢትዮጵያ የሚያከብራትን ታከብራለች” ብለው የሚተማመኑባት ጠንካራ አገር ትሆናለች። ክብሯም ይታደሳል። በኛ ዘመን የኢትዮጵያን ክብር ማዋረድ የለብንም።
“ከተረጂነት ወደ ምርታማነት፣ ከዕዳ ወደ ምንዳ” እንዲሉ ነው። ከተስፋ ብርሃን ወደ ተጨባጭ ብርሃን መሸጋገር ይቻላል። ይህም ብቻ አይደለም። ካወቅንበትና ከሠራንበት፣ አገራችን ዕምቅ ጸጋ የበዛላት አገር ናት። በአገራችን በየአካባቢያችን የሚገኙ ጸጋዎችን ወደ ብልጽግና ልንቀይራቸው እንችላለን። በአፍሪካ የብልጽግና ተምሳሌት የምንሆንበት ጊዜም ሩቅ አይሆንም።
ያኔ፣ የተረጂነት ታሪክ የድሮ ትዝታ ይሆናል። በችግር ጊዜ በቀና ልቦና የረዱንን የምናመሰግንበት ትክክለኛው መንገድም፣ ከተረጂነት በመውጣትና ራሳችንን በመቻል ነው። ከራሳችን አልፈን ወደ ብልጽግና ስንጓዝና ሌሎችን የመርዳት ዐቅም ሲኖረንም ነው “ውለታ ከፋይ” የምንሆነው ይላሉ - አቶ ዘውዱ ከበደ።


“ነቢይን የሚያውቅ ሁሉ ሳቁን ይጋራል”
‹‹እምቢልታ ማስነፋት ነበር አመላችን
ነጋሪት ማስመታት ነበር አመላችን
ሰው መሆን አይቀርም ደረሰ ተራችን››
ብለው ነበር አሉ፣ በአንድ ቀን አዳር፣ ከንግሥትነት ወደ ወይዘሮነት የተቀየሩት እመቤት፡፡
ይህ አባባል ዛሬ ነበር ሊባል ለተገደድነው ለነቢይ ይሁን ለሕያዋን እንደሚሠራ በደንብ ማሰብ ይፈልጋል፡፡ ነቢይ መቶ ወዳጆች ካሉት ከሁሉም ጋር የተለያየ ትዝታ፣ የተለያየ ወግ፣ የተለየ ሣቅ፣ የተለየ ትረካ ያስቀመጠ ሰው ነው፡፡ (እንዲያውም ቢያንስ አንድ ሰው ጋ መቶ የተለያየ ታሪክ አስቀምጧል፡፡) ነቢይን የሚያውቅ ሰው ሁሉ የሚጋራው አንድ ነገር ሣቁን ነው፡፡ ሮንግ ተርን ፊልም ኮሚዲ አድርጎ እንደመተረክ ያለ፣ በሕመም ጭምር ፈገግ ብሎ ማውራት የነቢይ ወዳጆች የጋራ ትዝታ ነው፡፡
ነቢይ በራሡ አባባል ‹‹ቀለሜዋ›› የሳይንስ ተማሪ መኾኑና ኬሚስትሪን ደህና አድርጎ ማጥናቱ ጠቅሞት ይመስላል፣ ፔሬዲክ ቴብሉን ገልብጦ፣ ወደ ጥበብ አምጥቶት ተርጓሚ፣ ደራሲ፣ ጸሐፌ-ተውኔት፣ ተዋናይ፣ ሰዓሊ፣ ተራኪ፣ ገጣሚ፣ ጋዜጠኛ… በሁሉም መስክ ልክ በልጅነቱና በወጣትነቱ ትምህርት ቤት ውስጥ አስተማሪዎቹ እንደሚሠጡት ውጤት 100 ከ 100 በሚያሰጥ ብቃት ተወጥቶታል፡፡ ችግሩ ግን ነቢይ ይህ ሁሉ ማዕረግ ይጠብበዋል፡፡ ነቢይ ራሡ ማዕረግ ነው፡፡
ነቢይ መኮንንን ወደፊት ለሚመጣ ትውልድ ለማስረዳት ቀላሉ መንገድ፣ (ይህም ቢኾን ያንሰዋል) ነቢይ ‹‹ጉግል›› ነው ማለት ነው፡፡ ስለ ቅጠል ሆነ ስለ ሰው አንድ ቃል ብቻ ሲጠራለት ‹‹ኦ እሱኮ አሪፍ ነው፡፡›› ብሎ ይጀምራል፡፡ በቃ ከዚያ ተከትሎ የሚናገራቸው ነገሮች… ራሱ የኮምፒውተሩ ጉግልም የሚያውቃቸው አይመስለኝም፡፡ ደግሞ የሚያወራው መረጃ አይደለም - መረጃማ ሁሉም ሰው ያውቃል፡፡ ነቢይ ግን ራሱ ሰውዬው ቢጠየቅ ስለራሱ የማይናገረውን ሁሉ ያስረዳል፡፡ ነቢይ እንደዚያ ነው፡፡
ነቢይን አግኝቶ ያናገረም ያላናገረም፣ ‹‹ይህን ጉዳይ አንስቼ ሳላወራው…›› ብለው መጸጸት አይቀርላቸውም፡፡ ምክንያቱም ነቢይን አግኝተው ለሚያወሩት ሁሉ ቅርብ ሆኖ የማናገሩን ያህል ዛሬ ሙሉ ቀን ቢያወሩት፣ ቀኑን ሙሉ የሚያወራው ነገር ካለመሰልቸቱም በላይ ያልነገረኝ የቀረ አለ ማለት ነው ያስብላል እንጂ፣ በፍጹም አናግሬዋለሁ ብሎ እፎይ አያስብልም፡፡
ነቢይ መሞቱ እጦት የሚኾነው ለቤተሰብ፣ ወዳጅ ዘመድ፣ ለሚያውቁት ለሚያውቃቸው አንድ ትልቅ ወዳጅ መንጠቁ እንዳለ ኾኖ፣ እንደ ሰው ግን የሞተው አንድ ሰው ብቻ አይደለም፡፡ የዚህን ሰው አምሳያዎች ለማግኘት ምናልባትም ዘመናትን መጠበቅ ግድ ይላልና፣ እርሱ ለገብረክርስቶስ ደስታ የተጠቀመውን አገላለጽ ጠቅሰው፣ ወዳጁ በኃይሉ ገብረመድኀን አንተም ያው ነህ እንዳሉት፤
‹‹ነቢይን ዓይነት ሰብል ለማግኘት ሥንት ዘመን ማረስ ያስፈልጋል?››
አንድ ወዳጁ ነቢይን ሲገልጸው ምን አለ?
‹‹ነቢይን ግጥም አንብብልኝ፣ ድርሰት ተርክልኝ ማለት ሳይሆን፣ ጠዋት ሲነሳ ጀምሮ በሄደበት እየተከተለ የሚቀርጽ ካሜራ አሰናድቶ ከአካሄዱ፣ አቀማመጡ ጀምሮ ጫማ ጠራጊዎችን፣ የረዥም ዘመናት ወዳጆቹን፣ ዛሬ ያገኙት አድናቂዎቹን፣ ምግብ የሚበላበት ውኃ የሚጠጣበት ቦታ ከአስተናጋጅ፣ ከጥበቃዎች ጋር ሁሉ ሲያወራ መቅረጽ ነው የሚሻለው፡፡›› ግን እንደዚያስ ቢኾን ነቢይ ያልቅ ይሆን?
ደህና ሁን ናዝራዊው ነቢይ፡፡
ደህና ሁን የአድማሱ ሰው፡፡
ደህና ሁን ነቢይ መኮንን፡፡
ሰው ስለሆንህ አመሠግንሃለሁ፡፡
(ዮሴፍ ዳሪዮስ ሞዲ)
በሰቀቀን የፈራነው፣ ሰንሸሸው የከረምነው
እውነት ደረሰ
የቃል ኃይል፣ የኪነት ጉልበት፣ መቅኒው
ተሰብሮ ፈሰሰ፤
ትውልድን የሚያገናኘው፣ የግጥም የቅኔው
ድልድይ፣
ይኸው ዛሬ ፈረሰ፣
ዛሬን ለቀሪው ትቶ፣ ወደ ትላንት ፈለሰ
እንደ ነፋስ ሲነፍሰን ክርሞ፣ እንደ ውሃ ፈሰሰ፤
የብዙ ተጠየቅ መላሽ፣ የመንፈቅ የዓመቱ
ስንክሳር፤
በወግ ያልተነበበው፣ የየአሳራችን አሳር፤
ከአትሮኑሱ ላይ ወረደ፤
ገድሉን ሰምተን ሳንጨርስ፣ ሰቀቀናችን ላይ
ረፈደ፤
የሁለት ትውልድ መስካሪው፣
መሲህ ነህ ያልነው ነቢይ፣  ላይመጣ ሄደ
ነጎደ፤
ይብላኝልን፣
ያለ ምሥክር ለቀረን።
በሰላም እረፍ ጋሽ ነቢይ !!!!
(ገጣሚ አበባው መላኩ)

Page 3 of 714