Administrator

Administrator

አማራ ባንክ የተገልጋዩን  የክፍያ ሥርዓት አካች፣ ዘመናዊና ቀላል እንዲሁም ከካሽ ነጻ ለማድረግ ከሚያከናውናቸው መጠነ ሰፊ ሥራዎች ጋር በተያያዘ፣ ከሳንቲም ፔይ ፋይናንሻል ድርጅት ጋር በጋራ ለመሥራት የሚያስችለውን የስምምነት ሰነድ ተፈራረመ፡፡

አማራ ባንክና ሳንቲም ፔይ የስምምነት ሰነዱን የተፈራረሙት፣ ዛሬ ረፋድ ላይ በባንኩ ዋና መሥሪያቤት ነው፡፡

በዚህ ስምምነት መሰረት፣ አማራ ባንክ ከበርካታ የንግድ አካላት ጋር የሥራ ግንኙነት በመፍጠር ደንበኞች ለሚፈጽሙት ግብይት፣ በንግድ ተቋማት ውስጥ የሚገኘውን ኪው አር ኮድ፣ በተንቀሳቃሽ የእጅ ስልካቸው አማካኝነት በማንበብ፣ በቀላሉ እንዲከፍሉ ከማስቻሉም ባሻገር፣ ደንበኞች ልዩ ልዩ ክፍያዎችን መፈጸም የሚችሉበት ይሆናል ተብሏል፡፡

ደንበኞች በጤና ተቋማት፣ በአልባሳት መደብሮች፣ በግንባታ ዕቃ መሸጫዎች፣ በኤሌክትሮኒክስ ሱቆች፣ በሆቴሎች፣ በካፌዎችና በሌሎችም ለተጠቀሙት አገልግሎትና ለፈጸሙት ግዢ፣ በተንቀሳቃሽ የእጅ ስልካቸው ብቻ ክፍያ መፈጸም እንደሚችሉ ታውቋል፡፡

”ደንበኞች ካርድ መጠቀም ሳያስፈልጋቸው በስልካቸው ብቻ ክፍያዎችን መፈጸም የሚችሉ ሲሆን፤ የንግድ አካላት ደግሞ ምንም ዓይነት ተጨማሪ መሳሪያ ሳያስገጥሙ፣ ሳንቲም ፔይ በአማራ ባንክ ሂሳባቸው አማካኝነት የሚያዘጋጅላቸውን ኪው አር ኮድ ብቻ ለደንበኞች ዕይታ ምቹ በማድረግ ክፍያዎችን ይቀበላሉ፡፡” ብሏል፤ ባንኩ ባወጣው መግለጫ፡፡

በዚህ የክፍያ ማሳለጫ ነጋዴዎች ከደንበኞች ጋር ግብይት ለመፈጸም፣ ከአማራ ባንክ የክፍያ ልዩ ሂሳብና ከሳንቲም ፔይ አጋርነት ስምምነት እንዲኖራቸው የሚጠበቅ ሲሆን፤ በዚህም ደንበኞች በቀጥታ ወደ ነጋዴው የአማራ ባንክ ሂሳብ በስልካቸው ብቻ በቀላሉ ክፍያ ይፈጽማሉ ተብሏል፡፡

ይህ የክፍያ ማሳለጫ ለነጋዴዎችና ለደንበኞች ምቾትን የሚያጎናጽፍ ከመሆኑም ባሻገር ደንበኞች ካሉበት ሆነው የተለያዩ ክፍያዎችን መፈጸም እንደሚያስችላቸው ነው የተገለጸው፡፡

ሳንቲም ፔይ ፋይናንሻል ሶሉሽን አክስዮን ማህበር፣ በኢትዮጵያ የክፍያ ሥርዓት ኦፕሬተር ሆኖ እንዲያገለግል በብሔራዊ ባንክ የክፍያ ሥርዓት አዋጅ ቁጥር 718/2011፣ ሃምሌ 2014 ዓ.ም የተቋቋመ ድርጅት ነው፡፡

        ሰኔ 2 አሸናፊዎች በስካይላይት ሆቴል ይሸለማሉ


      ባለፈው ዓመት (በ2014) በአገራችን ውስጥ ለመጀመሪያ ጊዜ ለእይታ ከቀረቡ ፊልሞች መካከል 22ቱ ለውድድር መቅረባቸው ታውቋል፡፡ሰሞኑን የሽልማት ድርጅቱ ባወጣው መግለጫ፤ ከጉማ ጅማሮ አንስቶ በተለያዩ ሙያተኞች ሲጠየቅ የነበረው ”የተከታታይ ፊልም” ምድብ እና ”የዘጋቢ ፊልም” ምድብ ዘንድሮ እንዲካተቱ ተደርጓል፡፡በዚህ ዓመት የውድድር ዘርፎቹ ወደ 29 ያደጉ ሲሆን፤ የጉማ “የህይወት ዘመን ተሸላሚ” ዘርፍ እና ”የጉማ የሄርሜላ የሴቶች ሽልማት”፤ እንዲሁም ”የጉማ  በጎ ስራ ተሸላሚ” ያለ ውድድር፣ በኮሚቴው ጥናትና ምርጫ ይወሰናሉ ተብሏል፡፡
ለተከታታይ ሰባት ዓመታት የጉማ ፊልም ሽልማትን በብቸኝነት ስፖንሰር በማድረግ የሚታወቀው በደሌ ስፔሻል፤ የዘንድሮውንም 8ኛ ዙር የጉማ ፊልም ሽልማት ስፖንሰር ማድረጉ ተገልጿል፡፡
“ይህ በየዓመቱ የሚካሄድ የፊልም ውድድር ሽልማት መርሃ ግብር፣ በዘንድሮው ውድድር በ28 ዘርፎች ተወዳድረው ላሸነፉት እውቅና ይሰጣል፡፡ ሂይንከን ኢትዮጵያ ከበደሌ ስፔሻል የጉማ ፊልም ሽልማት በተጨማሪ በሃገሪቱ የሚካሄዱ የተለያዩ ጥበባዊ ዝግጅቶችን በሌሎች ምርቶችም ድጋፍ እያደረገ ይገኛል፡፡” ብሏል፤ሂይንከን በመግለጫው፡፡ 8ኛው የጉማ ፊልም ሽልማት ሥነስርዓት የፊታችን አርብ ሰኔ 2 ቀን 2015 ዓ.ም በስካይላይት ሆቴል እንደሚከናወን ታውቋል፡፡
የጉማ ሽልማት እጩዎች በከፊል
1. ምርጥ ፊልም
የሱፍ አበባ/ለገሰ ገነቱ
ረመጥ/የከፍታ ዘመን ትሬዲንግ
አጨብጭቡለት/ወንድወሰን ሞላ
ክሱት/አድዋ ፊልምስ
ጥላዬ/ ንጉስ ፊልም ፕሮዳክሽን
2. ምርጥ ቅንብር
ሐረግ/ምትኩ በቀለ
የሱፍ አበባ/ እስክንድር ተፈራ
እንደልቤ/ ኤፍሬም ምስጋናው እና ናትናኤል ወርቁ
ክሱት/የአብ በቀለ
ረመጥ/ፅገአብ ተስፋዬ
3. ምርጥ ዋና ወንድ ተዋናይ
አጨብጭቡለት/ ታሪኩ ብርሃኑ
የሱፍ አበባ/ ግሩም ኤርሚያስ
ረመጥ/ሄኖክ ብርሀኑ
ክሱት/አማኑኤል የሺወንድ
ጥላዬ/ቸርነት ፍቃዱ
4. ምርጥ ረዳት ሴት ተዋናይት
እንደልቤ/ማህሌት ሰለሞን
የማር ውሃ/ መስከረም ነጋ
ጥላዬ/ባዩሽ ከበደ
የአዳም ቃል/ቲና ገ/አምላክ
ሐረግ/ቤተልሔም ኢሳያስ
5. የበደሌ ስፔሻል ምርጥ የህዝብ ፊልም
የሰኔ ግርግር/ዩሴፍ ካሳ
ጥላዬ/ንጉስ ፊልም ፕሮዳክሽን
የአዳም ቃል/ይሄነው ቴዎድሮስ እና ዘላለም አለማየሁ
አጨብጭቡለት/ ወንድወሰን ሞላ
የሱፍ አበባ/ለገሰ ገነቱ
6. ምርጥ ዳይሬክተር
ጥላዬ/አልዓዛር ደሳለኝ
ረመጥ/ዳንኤል በየነ
የሱፍ አበባ/ግሩም ኤርሚያስ
ክሱት/የአብ በቀለ
አጨብጭቡለት/ወንድወሰን ሞላ
7. ምርጥ የፊልም ፅሁፍ
ረመጥ/ዳንኤል በየነ
የሱፍ አበባ/ዳዊት ተስፋዬ
ክሱት/የአብ በቀለ
ጥላዬ/ቸርነት ፍቃዱ
የአዳም ቃል/ዘላለም አለማየሁ              
8. ምርጥ ዋና ሴት ተዋናይት
ክሱት/ጠረፍ ካሳሁን
ረመጥ/ዮአዳን ኤፍሬም
የሱፍ አበባ/መስከረም አበራ
ቅዳሜ ገበያ/ትዕግስት ያረጋል
ሐረግ/ራህማ ሰይድ
9. ምርጥ ውርስ ተከታታይ የቴሌቪዥን ድራማ
ሁለት ጉልቻ
ደራሽ
አደይ
የባስሊቆስ እንባ
የተገፉት
10. ምርጥ የፊልም ሙዚቃ
ጥላዬ/ ኤልያስ ተሾመ እና
አዲስ ሙላት ግጥም/ እሱባለው ይታየው
 ዜማ/ እሱባለው ይታየው
እንደልቤ/ ኤልያስ ተሾመ
ግጥም/ የወሰን ልጅ ሸዊ
ዜማ/ መሳይ ተፈራ
ፊናፍ/መርጊቱ ወርቅነህ ግጥም/ ለሊሳ እንድሪስ ዜማ/ ሌንጮ ገመቹ
አጨብጭቡለት/አህመድ ሁሴን
ግጥም እና ዜማ እሱባለው ይታየው
5  አበባ/ መዓዛ /ሙሉዓለም ታከለ/
ግጥም/ ብሩክ ሞላ/ግሩም ኤርሚያስ
 ዜማ/ ብሩክ ሞላ/ሙሳ ማቲ/ሙሉዓለም ታከለ
11. ምርጥ ሲኒማቶግራፊ
ሐረግ/ዮናስ ወርቁ
የሱፍ አበባ/ዋለልኝ አደገ
ረመጥ/ጆሴፍ ኢቦንጎ
የአዳም ቃል/አልዓዛር አበበ
ክሱት/ዳዊት ጸጋዬ እና የአብ በቀለ

 አንድ የህንዶች ተረት አለ፡፡
አንድ ሽማግሌ አባት የመሞቻቸው ጊዜ ሲቃረብ፣ አምስት ልጆቹን ይጠራል፡፡ “ስሙ ልጆቼ፤ የመሞቻዬ ጊዜ እንደተቃረበ ይሰማኛል፡፡ ስለዚህ በህይወታችሁ ሳላችሁ በጭራሽ ባታደርጓቸው ደስ የሚሉኝን ልንገራችሁ፡፡”
ሁሉም በፀጥታና በሃዘን ድባብ ውስጥ ሆነው ያዳምጣሉ፡፡
በተቻለ መጠን ሃገር ከድታችሁ ወደ ውጭ ለመሄድ አታስቡ፡፡
ከሄዳችሁም ያለ በቂ ምክንያት አትመለሱ፡፡
ካልተመለሳችሁም እዛው ጠንክሩ እንጂ፣ ባልጠና አካልና ባልጠና ልቦና፣ ጊዜያችሁን በዋልጌነት አትጫወቱበት፡፡
ከተሳካላችሁ በኋላ ግን በጭራሽ አገራችሁን አትርሱ፡፡
ይህን ካለ በኋላ ለአንዴም ለሁሌም ፀጥ አለ፡፡
ከጊዜ በኋላ ከአምስቱ አራቱ ልጆች ወደ ውጭ ሀገር ሄዱ፤ አንዱ አገር ውስጥ ቀረ፡፡
አገር ውስጥ የቀረው የአባቱን ቤት ሸጦ እየመነዘረ መኖር ጀመረ፡፡
ውጭ ከሄዱት አንደኛው ደግሞ ጨርሶ ዋልጌ ሆነ፤ገንዘብ መዝራት፣ መስከር፣ መጨፈር ሆነ ስራው፡፡ ግን ገንዘብ አፈራ፡፡
ሌላኛው እጅግ ሀብታም ሆኖ መቼ ሀገሬ ተመልሼ በገንዘቤ ተምነሽንሼበት ይል ጀመር፤ ሶስተኛው ግን በቶሎ ወደ ሀገሩ ተመለሰና የራሱን ኑሮ ይኖር ጀመር፡፡
አራተኛውና የመጨረሻው ትንሹ ልጅ ግን ውጭ ሀገር ሆኖ፣ የአባቱን ቤት መልሶ ለመግዛት የሚችልበትን መንገድ ሲፈልግና ጊዜ ሲጠብቅ ቆየ፡፡
በመጨረሻም ሁሉም ሀገራቸው ተገናኙ፡፡ ስለ ትላንትና ውሏቸው መወያየት ጀመሩ። የመጨረሻው ልጅ አንድ ጥያቄ ያነሳል፡፡ “ለመሆኑ ከመካከላችን የአባቱን ቃል ያከበረ ማን ነው?” በተራ በተራ ይመልሱለት ጀመር፡፡
በመጀመሪያ አገር ውስጥ የቀረው መለሰ፡- “የአባቴን ቃል ያከበርኩ እኔ ነኝ፤ አባቴ አገራችሁን አትክዱ በሎ ነበር፤ እሱን ፈፅሜያለሁ ዛሬም ለአባቴ ቃል ታማኝ ነኝ፡፡”
ሁለተኛው የመለሰው ወደ አገሩ ቶሎ የተመለሰው ነበር፡፡ “የአባቴን ቃል ያከበርኩ እኔ ነኝ፡፡ በሁኔታዎች ተገድጄ ከሀገር ብወጣም ተመልሻለሁ” አለ፡፡
ሶስተኛው፡- “እኔ በበኩሌ ውጭ ከኖራችሁ ጊዜያችሁን በዋልጌነት አታሳልፉ ያለንን ቃል ለማክበር ሞክሬያለሁ፡፡ ነገር ግን ውጭ ሀገር አባባ እንዳሰበው አደለም፤ ገንዘብ ለማግኘት ገንዘብ መመንዘር ግድ ነበር፡፡ ያንን አድርጌ ገንዘብ አፍርቼ መጣሁ”
አራተኛው፡- “እኔም አገር እንደከዳሁ አይቆጠርም፤ ምክንያቱም የናጠጥኩ ሀብታም ሆኜ ተመልሻለሁ፤ ጊዜዬን በከንቱ አላሳለፍኩም” አለ፡፡
አምስተኛው፡- “በበኩሌ የአባቴን ቃል ያከበርኩ እኔ ነኝ እላለሁ፤ ምክንያቱም አባታችን በታቻለ መጠን አገር ከድታችሁ አትሂዱ ሲል ከቻላችሁ ማለቱ ነው፡፡  ከመሬት ተነስታችሁ ውጪ እንሂድ አትበሉ ማለቱ ነው፤ ከሄዳችሁ ያለ በቂ ምክንያት አትመለሱ ሲልም፣ በመጀመሪያ ከሀገር ያስወጣችሁ ጥያቄ ተመልሶልኛል ወይ? በሉ ማለቱ ነው፡፡
 ጊዜያችሁን አትጫወቱበት ሲልም አካልና መንፈሳችሁን ለውጭ ሀገር አሸሼ ገዳሜ አታስገዙ፣ ሰብእናችሁን አትሽጡ ማለቱ ነው፣ በንዋይ አትደለሉ ማለቱ ነው፡፡”
የቀሩት ወንድሞቹም በጥሞና አዳመጡት፡፡ ግን ልባቸው አልተቀበለውምና በአፋቸው ተቃወሙት፡፡ ተከራከሩት፡፡ ክርክሩ እጅግ ተጋጋለና አንደኛው በስለት ሊወጋው ተነሳ፡፡
 ሆኖም አንድ ድምፅ በድንገት በቤት ውስጥ ተሰማ፡፡
“ልጆች” አለ፤ የአባታቸው የሙት መንፈስ ነው፡፡
ሁሉም ፀጥ አሉ፡፡ “በህይወት እያለሁ ትጨቃጨቁ ነበር፤ ዛሬም እየተጨቃጨቃችሁ ነው፡፡ ሁላችሁም እራሳችሁን ከጥፋተኝነት ነፃ ለማድረግ እየሞከራችሁ መሆኑ ገብቶኛል፡፡ ይህን ትታችሁ የሁላችንም አስተዋፅኦ ቢደማመር ምን ይፈጥራል ብላችሁ ጠይቁ፡፡ እኔን አያድነኝም-አይመልሰኝም፡፡
 ሆኖም ቀሪው ትውልድ መዳን አለበት፤ መኖር አለበት፡፡ የሚያድናችሁ ስለ ነገ ማሰብ ብቻ ነው፡፡ እኔም ሞትኩ፤ እናንተ ከእንግዲህ ዳኑ፡፡ መዳን የምትችሉት ዛሬ ላይ ቆማችሁ ስለ ነገ በማሰብ ብቻ ነው፡፡ ስለዚህም አእምሮአችሁን ከትላንት ነፃ አድርጋችሁ ጀምሩ፡፡” ድምፁ ተሰወረ፡፡ ልጆቹም ከድንጋጤያቸው ሲነቁ አባታቸው ያለውን ፈፅመው ለመዳን ወሰኑ፡፡
***
አዕምሮን ከትላንት የፀዳ ማድረግ መታደል ነው፡፡ በደልና ግፍ እንደ ጥቁር ጥላ በተከተለን ቁጥር ከመሳቀቅ ንስሃ ገብቶ ወደ ፊት መራመድ ይመረጣል፡፡
በአገራችን አያሌ የፖለቲካ ድርጅቶች በቅለዋል፡፡ ጥቂቶቹ ገና በችግርና በቡቃያ ደረጃ ተቀጭተዋል፡፡
ከፊሎቹም ግማሽ መንገድ ተጉዘው ጠውልገዋል፡፡ ከፊሎቹ በስልጣን ላይ ያለውን ፓርቲ ጨምሮ አሁንም አሉ፡፡ ገና ጉዞ ላይ ናቸው፡፡
በየዘመኑ ከመጡ መንግስቶች ጋር ያበሩ ነበሩ፡፡
ገና የሚያብሩም አሉ፡፡ ሁሉም የየበኩላቸውን የህሊና ፅዳት ፍለጋ እጃቸውን መታጠቡን ተያይዘዋል፡፡
 ሆኖም ዛሬም ከየራሳቸው የፖለቲካ ንፍቀ-ክበብ ባለመውጣታቸው ከትልቁ የአገር ስእል፣ ከህዝቡ ጥቅም አንፃር ጉዳዩን ያዩት አይመስለኝም፡፡
ስለ ነገ በቅጡ የማሰብን ነገር ፕሮግራማቸውም ሆነ የኢላማ መነፅራቸው ከልብ አላስተናገደም፡፡
አንዳንዶቹ “መጫኑንስ ጫኑ ግን ገብስ ይሁንልኝ” እንዳለችው አህያ፣ ለእነሱ የሚቀላቸውን ሸክም በመሸከም ብቻ ሊገላገሉት ይሻሉ፡፡
አንዳንዶቹ ደግሞ “ሞት አለና ድንገት ለስንቃችሁ ደግ ስሩ” ቢባሉም እኔ ያልኩት ምን ሆነና ብለው በግትርነት ጎዳና ላይ ናቸው፡፡ ሌሎቹ “የእንጨት ምንቸት እራሱ አይድን ሰው አያድን” አይነት ብቻ ሆነዋል፡፡ ዋናው ጉዳይ ግን የምንጓዘው የት ድረስ ነው፣ ግባችን ምንድን ነው፣ ህዝባችን የት ላይ ይጠቀማል? የሚለው ነው፡፡
ስብሰባዎች ቢደጋገሙ፣ ኮንፈረንሶች ቢሟሟቁ፣ ዱለታዎች በየማታው ቢጋጋሉ በመካያው “ማረፊያችን ለሀገራችን መሻሻል ምን ያህል ፍሬ ይሆናል?” ካላሉ በየራስ አጥር ታጥሮ፣ እኔ ነኝ አንደኛ ከማለት ያለፈ ድል አይሆንም፡፡
ዛሬ በአገራችን የምንመኘውን ለውጥ ለማምጣት ”የት ቦታ ቆመን?” ማለት ተገቢ ነው፡፡
 አርኪሜደስ የተባለ ሳይንቲስት “give me a lever and fulcrum and a place to stand and I can move the earth” ብሎ ነበር፡፡  
(“ሺብልቁን እና የምቆምበትን ቦታ ብትሰጡኝ አለምን አጎናት-አጦዛት ነበር” እንደማለት ነው፡፡) በ13 ዓመት እድሜያችን ውስጥ የት ጋር ቆመን ያለፉትን እንነቅፋለን? የት ጋር ቆመን የሌሎችን ፖለቲካዊ አካለ-ጎዶለነት እናያለን? በምን የሞራል-እሴት ትላንትንና ሌሎችን ተወቃሽ፣ እራሳችንን አወዳሽ ለማድረግ ይቻለናል? ይሄ ገብቷት ነው መሰል የአገራችን ዥንጀሮ እንደ አርኪሜደስ መሆን ሲያምራት፤ “መሬቱ ቢገለበጥ ኩንቲ እጠግብ ነበር፤ ግን የት ላይ ሆኜ?” አለች አሉ፡፡
ሁሉም ድርጅቶች ሊያስቡበት ይገባል፡፡ የልጆቹ አባት እንዳሉት፤ “የሁላችንም አስተዋፅኦ ቢደማመርስ  ምን ይፈጠራል?” ብለው መጠየቅ ይኖርባቸዋል፡፡


     ኢትዮ ቴሌኮም  ከአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ጋር የኮኔክቲቪቲና ዲጂታል አገልግሎቶች ለማቅረብ የሚያስችል ስትራቴጂያዊ የአጋርነት ስምምነት ከትላንት በስቲያ  አድርጓል፡፡
  ስምምነቱ፤ 18 ካምፓሶችን ከፍተኛ ፍጥነት ባለው የኢንተርኔት አገልግሎት ማገናኘት፣ ስማርት ክፍሎችን መገንባት፣ የተለያዩ የዲጂታል አገልግሎቶችን ማቅረብ፣ ከፍተኛ ባንድዊድዝ ያለው የብሮድባንድ ኢንተርኔት አገልግሎት አቅርቦት ከ24 ሰዓት ክትትልና የጥገና ዋስትና ጋር የሚያካትት ነው ተብሏል፡፡ ይህም ለዩኒቨርሲቲው ማህበረሰብ ዲቫይሶችና ተርሚናሎችን በረጅም ጊዜ ክፍያ ለማቅረብ፣ የእውቀት ሽግግርና የልምድ ልውውጥ ለማድረግ እንዲሁም የምርምርና ፈጠራ ስራዎችን የሚያግዙ ቴክኖሎጂዎችንና የመሰረተ ልማት ግንባታዎችን ለማከናወን የሚያስችል እንደሚሆን ተጠቁሟል፡፡ በተጨማሪም፤ የቴሌብር የዲጂታል የክፍያ ሥርዓትን በመጠቀም ነባር ወይም አዲስ ተመዝጋቢ ተማሪዎች የምዝገባ፣ የፈተና፣ የማመልከቻ፣ የሰነድ ማረጋገጫ፣ የትምህርት ክፍያዎች፣ የትምህርት ማስረጃዎች፣ የአልሙኒና መሰል የአገልግሎት ክፍያዎችን ካሉበት ሆነው በመፈጸም አገልግሎት ለማግኘት የሚያባክኑትን ጊዜና ገንዘብ ለመቆጠብ እንዲሁም ዩኒቨርሲቲው የአገልግሎት አሰጣጡን ለማዘመን፣ የተቀላጠፈ አገልግሎት ለመስጠትና አስተዳደራዊ ወጪዎች ለመቀነስ ትልቅ ፋይዳ እንደሚኖረው ኩባንያው አመልክቷል፡፡
 በሌላ በኩል፤ኢትዮ ቴሌኮም  ከዚህ ቀደም ከአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ጋር በመተባበር፣ በቴሌኮሙኒኬሽን ኔትወርክ ኢንጂነሪንግና የቴሌኮሙኒኬሽን ኢንፎርሜሽን ሲስተም የሙያ መስኮች የጋራ ካሪኩለም በመቅረጽ፣ በድህረ-ምረቃ ፕሮግራም፣ ባለፉት ሦስት ተከታታይ ዙሮች፣ 152 የኩባንያው ባለሙያዎች በመስኩ ሰልጥነው በመመረቅ  ወደ ሥራ ገበታቸው ተመልሰው የተሻለ ሙያዊ አገልግሎት እየሰጡ ሲሆን፣ በ2023 የትምህርት ዘመንም ለ4ኛ ጊዜ 53 ተማሪዎችን በቴሌኮሙኒኬሽን ኔትወርክ ኢንጂነሪንግና ኢንፎርሜሽን ሲስተም የትምህርት ዘርፎች ተቀብሎ ለማስተማር የሚያስችል ስምምነት ተደርጓል፡፡
ኩባንያው፤ ከአዲስ አባባ ዩኒቨርስቲ ጋር በርካታ ስትራቴጂያዊ ስራዎችን በአጋርነት በመከወን ላይ የሚገኝ ሲሆን፣ በቀጣይም  የዩኒቨርሲቲውን የአሰራር ስርዓት ለማዘመንና የትምህርት ጥራትን ለማሻሻል በሚደረገው ጥረት የሚያደርገውን የቴክኖሎጂና መሰል ድጋፎችን አጠናክሮ እንደሚቀጥል አስታውቋል፡፡

 ራሚስ ባንክ፤ አስፈላጊውን የባንክ አደረጃጀትና መስፈርት አሟልቶና ከብሄራዊ ባንክ ፈቃድ አግኝቶ የተመሰረተ ሲሆን ፤የፊታችን እሁድ ግንቦት 27 ቀን 2015 ዓ.ም በዋና መሥሪያቤቱ   በይፋ ተመርቆ ስራ ይጀምራል።
 ባንኩ ከዛሬ ግንቦት 24 በኢሊሊ ሆቴል በሰጠው ጋዜጣዊ መግለጫ ነው፣ ይህን ያስታወቀው። ከመላው የሃገሪቱ ክፍሎት በተሰባሰቡ ከ8 ሺህ በላይ ባለአክሲዮኖች የተመሰረተው ባንኩ፤ በተፈረመ ከ2.1 ቢሊዮን ብር በላይና በተከፈለ ከ636 ሚሊዮን በላይ አጠቃላይ አደረጃጀቱን አጠናቅቆ፣ እሁድ ቦሌ መንገድ ፍላሚንጎ፣ ኦሮሚያ ፕሬዚዳንት ቢሮ ፊትለፊት በሚገኘውና ለዋና መስሪያ ቤትነት በገዛው ባለ ዘጠኝ ወለል ራሚስ ታወር ህንጻ ተመርቆ ስራ እንደሚጀምር ነው በመግለጫው የተነገረው፡፡
ባንኩ የስራውን ጅማሮ በአዲስ አበባ ዋናው መስሪያ ቤት አድርጎ፣በጥቂት ወራት ውስጥ የቅርንጫፎቹን ብዛት 50 ለማድረስ እየሰራ መሆኑም ተጠቁሟል፡፡
ሙሉ ለሙሉ ከወለድ ነፃ አገልግሎት ለመስጠት የተደራጀው ባንኩ፤ በተለይም ለዚሁ አገልግሎት የሚያበቃውን አጠቃላይ ሂደት ጨርሶ ስራ ለመጀመር መቃረቡን የተናገሩት ሐላፊዎቹ፤ በምስራቅ አፍሪካ ከሚገኙና ከወለድ ነፃ  የባንክ አገልግሎት  ከሚሰጡ ባንኮች አንዱና ቀዳሚው የመሆን ራዕይ ሰንቆ እየንቀሳቀሰ መሆኑም በጋዜጣዊ መግለጫው ተነግሯል።
ራሚስ ባንክ አክሲዮን ማህበር፣  ዘመኑን የሚዋጅና ቀልጣፋ አገልግሎት ለመስጠት  የሚያስችለውን የኮር ባንኪንግ ሲስተም በማደራጀት ከሸሪአና  ፋይናንሺያል ደረጃ አደራጅቶ ስራ እንደሚጀምር አስታውቋል።በባንኩ የምርቃት ሰነስርዓት ላይ የብሄራዊ ባንክ ተወካዮች፣የተለያዩ የግል ባንክ ፕሬዚደንቶች ፣ከፍተኛ የመንግስት ሐላፊዎች፣  ጥሪ  የተረገላቸው እንግዶችና  ታዋቂ ሰዎች ይታደማሉ ተብሎ እንደሚጠበቅ የባንኩ ሐላፊዎች ተናግረዋል።

    የ10ኛ ዓመት በዓሉን በኢንተርኮንቴኔንታል አክብሯል
         በጥር 2005 ዓ.ም በ20 መሥራች አባላትና በ9ሺ ብር ካፒታል ተቋቁሞ፣ ዛሬ ከ5500 በላይ አባላትና ከ1ቢሊዮን ብር በላይ ሃብት ማፍራት የቻለው አሚጎስ ቁጠባና ብድር ኃ.የተ.ህብረት ሥራ ማህበር፤ ባለፈው  ሰኞ ግንቦት 21 ቀን 2015 ዓ.ም፣ በኢንተርሌግዠሪ ኢንተርኮንቲኔንታል ሆቴል የተመሰረተበትን የ10ኛ ዓመት በዓሉን አክብሯል፡፡የአሚጎስ ቁጠባና ብድር ዋና ሥራ አስኪያጅ አቶ ፍጼም አብርሃ ባስተላለፉት መልዕክት፤ ”ማህበራችን በ10 ዓመታት ውስጥ ያገኘው ክብር በአጠቃላይ ሠራተኞቻችን ከላይ እስከ ታች ያሉ የአመራር አካላት በመቀናጀት በአንድነት በመሥራታቸው የመጣ  ነው፡፡ ወደፊትም በአደራ የተሰጠንን እምነት ለመጠበቅና የአገልግሎታችንን ጥራት በቀጣይነት ለማሻሻል መሥራታችንን እንቀጥላለን፡፡” ብለዋል፡፡
ማህበሩ፤ በአሁኑ ጊዜ ከ5500 አባላት በላይ ሲኖሩት፣ ለ2750 የማህበሩ አባላት ከ2.5 ቢሊዮን ብር በላይ ብድር የሰጠ ሲሆን ብዙዎችን አባላት የግል ሥራ እንዲጀምሩ፣ የቤት ባለቤት እንዲሆኑ፣ የስራ መኪና እንዲገዙ እንዲሁም በተለያየ የሥራ ዘርፍ እንዲሰማሩ እያገዘ እንደሚገኝ ተጠቁሟል፡፡
አሚጎስ ከሚሰጣቸው የብድር ዓይነቶች መካከል የግል ብድር፣ የቢዝነስ ብድር፣ የመኪና ብድር፣ የትምህርት ብድርና የቤት ብድር ይገኙበታል፡፡
የማህበሩ አባልና የአገልግሎቱ ተጠቃሚ የሆኑት አቶ ኤርሚያስ፣ በአምራች ዘርፍ ላይ የተሰማሩ ሲሆን፣ ከማህበሩ ከፍተኛውን ብድር፣  7ሚ.500ሺ ብር  በመውሰድ፣ ለሥራቸው ማስፋፊያ ተጠቅመዋል፡፡ የአሚጎስ ብድርም ሆነ የአገልግሎት ፍጥነት እሳቸው ከሚሰሟቸውና ከሚያውቋቸው የፋይናንስ አገልግሎት ሰጪዎች በእጅጉ እንደሚሻል ባለሃብቱ ምስክርነታቸውን ሰጥተዋል፡፡
አሚጎስ፤ በቀጣይ አምስት ዓመታት፣ ሃብቱን ከ5 ቢሊዮን ብር በላይ ለማሳደግና የራሱ የሆነ ህንጻ ለመገንባት ወጥኖ በመንቀሳቀስ ላይ እንደሚገኝም ታውቋል፡፡


    አርቲስት ሰለሞን ቦጋለ፣ ከትላንት በስቲያ ሐሙስ፣ የፀደይ ባንክ ብራንድ አምባሳደር ሆኖ ተሾመ። አርቲስቱ ይህን ሹመት ያገኘው ባለፈው ሐሙስ ግንቦት 25 ቀን 2015 ዓ.ም   በስካይ ላይት ሆቴል በተካሄደ  ሥነስርዓት ነው።
አርቲስት ሰለሞን ለፀደይ ባንክ ብራንድ አምባሳደርነት የተመረጠበት ዋና ምክንያት፣ በኪነጥበቡ ዓለም በሙያው በፈጠረው ተወዳጅነትና በበጎ አድራጊነቱ እንዲሁም  በመልካም ሥነምግባሩ እንደሆነ፣  የፀደይ ባንክ ከፍተኛ አመራሮች በስነስርዓቱ ላይ ገልፀዋል።
ከ3 ሚሊዮን ብር የገንዘብ ቁጠባና ብድር ተቋምነት ተነስቶ፣ በ50 ቢሊዮን ብር አጠቃላይ ሐብት ወደ ፀደይ ባንክነት ያደገው ተቋሙ፣ አርቲስቱን የባንኩ ብራንድ አምባሳደር አድርጎ በመሾሙ ታላቅ ኩራት እንደሚሰማው የባንኩ ዋና ሥራ አስፈፃሚ አቶ መኮንን የለውም ወሰን ተናግረዋል።ፀደይ ባንክ በወርሃ መስከረም አጋማሽ፣ በፀደይ ወቅት፣ አማራ የገንዘብ ቁጠባና ብድር ተቋምን ተክቶ፣ ባንክ ለመሆን የበቃ  ሲሆን ዝቅተኛ የኑሮ ደረጃ  ያላቸውን የህብረተሰብ ክፍሎች ለማገልገል የተቋቋመ ከመሆኑ አንጻር፣ በአሁን ሰዓት በመላ ሃገሪቱ በተለይም በገጠሩ አካባቢ 600 ቅርጫፎችን ከፍቶ አገልግሎት እየሰጠ እንደሚገኝ ተነግሯል፡፡  አርቲስት ሰለሞን ቦጋለ፣ በኢትዮጵያ የፊልምና ቴአትር ኢንዱስትሪ፣ እጅግ ተፅዕኖ ፈጣሪ፣ ድንቅ የትወና ብቃት ያለውና  አዛኝና ሩህሩህ  ባህሪን የተላበሰ በጎ አድራጊ በመሆኑ፣ በብራንድ አምባሳደርነት እንዳስመረጠው የተገለፀ ሲሆን፤ እስከዛሬ ከ60 በላይ ፊልሞች ላይ በአብዛኛው በመሪ ተዋናይነት፣ ከ16  በላይ የመድረክ ቴአትሮች፣ ከ6 በላይ ተከታታይ የቴሌቪዥን ድራማዎች እንዲሁም  በርካታ የሬዲዮ ድራማዎች ላይ በመሥራት አስደማሚ የትወና  ብቃቱን አስመስክሯል፡፡ ከሐገር ውስጥና ከውጪ ጉማንና ኢትዮ ፊልም ፌስቲቫል ሽልማቶችን ጨምሮ በርካታ ሸልማቶችን ማግኘት ችሏል፡፡ አርቲስቱ የዛሬ 8 ዓመት ባቋቋመው “ሕብረት ለበጎ የኢትዮጵያ በጎ አድራጎት ድርጅት” አማካኝነት፣ በገንዘብ እጦት ህክምና ማግኘት ያልቻሉ ወገኖችን የማሳከም ህልሙን እውን ለማድረግ ፣ በለገጣፎ ለገዳዲ 4 ሺህ ካሬ ሜትር ቦታ ወስዶ፣  የሪፈራል ሆስፒታል ግንባታ እያካሄደ ይገኛል።አርቲስት ሰለሞን የፀደይ ባንክ አምባሳደርነትን የተቀበለበትን ምክንያት ሲናገር፤ አንደኛ የባንኩ መሪ ቃል የሆነውን፣ “የሁሉም ባንክ” የሚለውን በመውደዱ፣ እንዲሁም  በአርቲስትነቱ እርሱም  የሁሉም አገልጋይ በመሆኑ፣ ከትንሽ ተነስቶ  ትልቅ  ደረጃ በመድረሱ፣ በገንዘብ እጦት የተቸገሩትን ሲረዳ በመቆየቱና ይህም እርሱ ከሚሰራው የበጎ አድራጎት ጋር በመመሳሰሉ እንደሆነ አስረድቷል፡፡
 ፀደይ ባንክ፣የቁጠባና ብድር ተቋም ሆኖ ከተመሰረተበት ጊዜ አንስቶ፣”አፍሪካ ባንከርስ አዋርድ”ን ጨምሮ 6 ዓለም አቀፍ ሽልማቶችን ማግኘቱም ታውቋል፡፡ ባንኩ ስራ የጀመረው በ7.75 ቢሊዮን ብር ሲሆን፤ አሁን በአጠቃላይ  13.3 ቢሊዮን ብር  ካፒታል  እንዳፈራ  የገለፁት ዋና ስራ አስፈፃሚው፤ 13 ሚሊዮን የሚደርሱ ገንዘብ አስቀማጭ ደንበኞች እንዳሉትም ጠቁመው፣ይህም  ቁጥር ከንግድ ባንክ ውጪ በግል ባንክ ደረጃ ያልተደረሰ መሆኑን ጠቁመዋል፡፡

  ቴክኖ ሞባይል ዓለማችን የደረሰበት ሞባይል የቴክኖሎጂ ደረጃ ያሳያል የተባለለትን የፋንተም ቪፎልድ (Phantum V told) ሞባይሉን ለኢትዮጵያ ገበያ አስተዋወቀ፡፡በአዲስ አበባ ሳይንስ ሙዚየም በተዘጋጀው ስነስርዓት ላይ የቴክኖ ሞባይ ብራንድ ማኔጀር አቶ ኤሊክ እንደተናገሩት ኩባንያው እጅግ ዘመናዊውን የፋንተም ቪ ፎልድ ሞባይል ለገበያ ከሚያቀርብባቸው ውስን ሀገራት መካከል አንዷ ኢትዮጵያ መሆኗ ይህም በአፍሪካ የሞባይል ኢንዱስትሪ ትልቅ ቦታ የሚሰጠው ነው ብለዋል::ይህ የሚታጠፍ የሞባይል ስልክ ቴክኖሎጂ በመያዝ የተመረተው ፋንታሞ ቪ ቮልድ ሲዘረጋ ባለ 7.85 ኢንች ሰፊ ስክሪን ያለውና በባለ 5 ሌንስ ሲስተም የሚተገበር ካሜራን በመጠቀም ከፍተኛ ጥራት ያላቸው ምስሎችን የማንሳት አቅም ያለው ነው ተብሏል፡፡ባለ 256 ጂቢ ሚሞሪ እና 12 ጂቢ ራም ያለው ይኸው ዘመናዊ ስልክ የሞባይል ስልክን በመጠቀም የተለያዩ ስራዎችን ለሚሰሩ ባለሙያዎች ተመራጭ እንደሆነ ተገልጿል፡፡በአዲስ አበባ ከተማ ጎሮ አካባቢ የሚገኘው የኢትዮ አይሲቲ ፓርክ ውስጥ ያስገነባውን ለአገራችን የመጀመሪያ የሆነውን ዘመናዊ ፋብሪካ በመጠቀም ቴክኖ ሞባይል ላለፉት ዓመታ የተለያዩ አይነትና አገልግሎት ያላቸውን የስልክ ምርቶች በመገጣጠም ለገበያ ሲያቀርብ የቆየ መሆኑ ይታወቃል፡፡


*  ጂኤፍአር ሬት (GFR rate) የኩላሊት ጤንነት የሚታወቅበት መለኪያ ነው። የጂኤፍአር መጠን የኩላሊታችንን ጤነንት ይናገራል።

* ደረጃ 1 – የጂ.ኤፍ.አር መጠናችን ጤነኛ ነው። ቢሆንም ግን የኩላሊት በሽታ እንዳለ ታውቋል።
* ደረጃ 2 – የጂ.ኤፍ.አር መጠናችን ከ90 ሚሊ ሊትር በታች ሲሆን፤ ኩላሊታችን ውስጥ በሽታ እንዳለ ያሳውቃል፡፡
* ደረጃ3 – የጂ.ኤፍ.አር መጠናችን ከ60 ሚሊ ሊትር በታች ነው።
* ደረጃ 4 – የጂ.ኤፍ.አር መጠናችን ከ30 ሚሊ ሊትር በታች ነው።
*  ደረጃ 5 – የጂ.ኤፍ.አር መጠናችን ከ15 ሚሊ ሊትር በታች ነው። የኩላሊት ማቆም ያጋጥማል፡፡

* አብዛኛው የኩላሊት በሽታ ታካሚ በሽታው ከስቴጅ 2 አያልፍበትም። ነገር ግን ህመሙ እንዳይባባስ ህክምና በማድረግ የኩላሊትን ጉዳት መከላከል ተገቢ ነው።

* ስኳር በሽታ ያላቸው ሰዎች ዓመታዊ ህክምና ማድረግ አለባቸው። ሽንታቸው ውስጥ ያለውን የፕሮቲን መጠን በመለካት ኩላሊታቸው አለመታመሙን ማረጋገጥ አለባቸው።

ህክምና

  የተለያዩ ህክምናዎች በሽታውን ለመቆጣጠር አገልግሎት ላይ ይውላሉ። ከባድ ኩላሊት በሽታ ያላቸው ሰዎች ብዙ መድሃኒቶችን መውሰድ ይገባቸዋል።
* የደም ማነስ ህክምና
* የደም ግፊትን ማከም
* ዳያሊሲስ
* ኩላሊት ንቅለ-ተከላ
* የአመጋገብ ለውጥ

መንስኤዎች

*  የስኳር ህመም
* ከፍተኛ የደም ግፊት –
* ሽንት መቋጠር
*  ሌላ የኩላሊት በሽታ
*  በእርግዝና ወቅት የሚፈጠር የኩላሊት እድገት ችግር
* አንዳንድ መድሃኒቶች – እንደ አስፕሪንና አይቡ ፕሮፊን የመሳሰሉ  
*  ኩላሊት ላይ የሚደርስ ጉዳት
 
 ምልክቶች

* ብዙ ጊዜ ህመሙ አሳሳቢ ደረጃ እስኪደርስ እንደታመምን ላናውቅ እንችላለን
* የደም ማነስ
* ደም የተቀላቀለበት ሽንት
* የጠቆረ ሽንት
* ንቁ አለመሆን
* የሽንት መጠን መቀነስ
* የእግር፣ የእጅና የቁርጭምጭሚት ማበጥ
* የድካም ስሜት
* የደም ግፊት
*  እንቅልፍ እጦት
* የቆዳ ማከክ
 * የምግብ ፍላጎት መጥፋት
* ወንዶች ላይ የብልት መነሳት ችግር
* በሌሊት ቶሎ ቶሎ ለሽንት መመላለስ
* የትንፋሽ እጥረት
* ሽንት ላይ ፕሮቲን መገኘት
*  በፍጥነት የሚቀያየር የሰውነት ክብደት
* ራስ ምታት

Page 1 of 647