Administrator

Administrator

“--የኢትዮጵያ ሴቶች የሚገባቸውን ያህል ዋጋ አልተሰጣቸውም ብዬ አምናለሁ፡፡ በኢትዮጵያ ሴቶች አካላዊ ውበት ላይ የማተኮር አዝማሚያ ይታያል፤ የኢትዮጵያ ሴቶች መለያ ግን አካላዊ ውበታቸው ብቻ ነው ብዬ አላምንም፡፡ አስደናቂ ጥንካሬና ብርታታቸውም መለያቸው ነው፡፡--”

             በልጅነቴ ሬዲዮ ላይ እሰራለሁ የሚል ሀሳብ ሽው ብሎብኝም አያውቅም ነበር፡፡ ክፍል ውስጥ ከኋላ እንጂ ከፊት መሆንን የማልደፍር፤ በፅሑፍም ሆነ በትወና ችሎታዬ እርግጠኛ ያልሆንኩ ተማሪ ነበርኩ፡፡ በአጋጣሚ በሬዲዮ ድራማ ላይ አንዴ የመስራት ዕድል አገኘሁና የምወደውን ሙያ እንዳገኘሁ አወቅሁ፡፡ ለመስራት ወደምሻው ሙያ የሚያቀርበኝን ስራ ሳፈላልግ ግን ከአስር ዓመት በላይ ፈጀብኝ፡፡ በ1987 ዓ.ም በኢትዮጵያ ሬዲዮ 97.1 ኤፍኤም ላይ ጨዋታ ፕሮግራምን በጋራ የማዘጋጀት እድል አገኘሁ፡፡ በ1999 ዓ.ም ደግሞ ከባለቤቱ አበበ ባልቻ እና ከረዥም ጊዜ ጓደኛዬና የሥራ ባልደረባዬ ተፈሪ አለሙ ጋር ሸገር ኤፍኤምን አቋቋምን፡፡ የምወደውን ሙያ የመስራት እድል የከፈቱልኝ እነዚህ አጋጣሚዎች ነበሩ፡፡
የተወለድኩት በ1950 ዓ.ም አዲስ አበባ ውስጥ ነው፡፡ ወላጆቼ የሐረር ሰዎች ሲሆኑ፤ እስከ 9 ዓመቴ ድረስ በምዕራብ ሐረርጌ በምትገኘው ትንሿ የሂርና ከተማ ነበር ያደግሁት፡፡ ሂርና በሚገርም ሁኔታ የተለያዩ ህዝቦችን በአንድ ላይ ያስተሳሰረች ከተማ ነበረች፡፡ ጎረቤቶቼ የመናውያን፣ ኦሮሞዎች፣ ሐረሪዎችና ሶማሌዎች ነበሩ፡፡ የእነዚህን ሁሉ ህዝቦች የበለፀገ የባህል መስተጋብር እያጣጣምኩ አደግሁ፡፡
ወላጆቹ ነጋዴዎች ነበሩ፡፡ አባቴ ቡናና ሌሎች ምርቶችን ወደ ውጭ በመላክ የተዋጣለት ነጋዴ ሲሆን እናቴ ደግሞ የአነስተኛ ግሮሰሪ ባለቤት ነበረች:: ባለፀጋ ቤተሰብ ነበርን፡፡ አንብቦ የማይጠግበው አባቴ፤ ብዙ መጻሕፍትና ጋዜጦችን ወደ ቤት ይዞ ይመጣ ነበር፡፡ ጋዜጦችን እንዳነብ ከማበረታታትም ባሻገር የእጅ ጽሑፌ እንዲሻሻል ከጋዜጣው ላይ በእጄ እንድገለብጥ ያደርግ ነበር፡፡ ሁሌም በእኔ ላይ ትልቅ ተስፋ እንዳለው ይነግረኝና ያበረታታኝ ነበር፡፡ አባቴ የሁለተኛ ደረጃ ተማሪ ሳለሁ ቢሞትም፣ በራሴ ላይ እምነት ሳጣ እንኳን፣ እሱ በእኔ ላይ የነበረው እምነት ብርታት ይሰጠኛል፡፡
የ9 ዓመት ልጅ ሳለሁ ወላጆቼ አዲስ አበባ ባለው የቅድስት ማርያም አዳሪ ት/ቤት አስገቡኝ፡፡ ሴቶች ብቻ በሚማሩበት በዚህ የካቶሊክ አዳሪ ት/ቤት፤ መነኮሳቱ የትምህርት ቤቱ አስተዳዳሪዎች ወለም ዘለም አያውቁም ነበር፡፡ በሥነ ሥርዓት ጉዳይ ላይ ፈፅሞ የሚደራደሩም አልነበሩም፡፡ ለመጀመሪያዎቹ ሁለት ሳምንታት ማታ ማታ ስራዬ ማልቀስ ብቻ ነበር:: ቀስ በቀስ ግን የአዲስ አበባ ኑሮን ተላመድኩት፤ የሳምንቱን የእረፍት ቀናት አክስቴ ቤት ማሳለፌም አረጋጋኝ፡፡ ንባብ ብቸኝነቴን የማመልጥበት መደበኛ ባልንጀራዬም ሆነ፡፡ ያኔ ልጃገረዶች ወጣ ወጣ ማለት አይፈቀድላቸውም ነበርና በየሳምንቱ መጨረሻ አክስቴ ቤት ስሄድ፣ ሁለትና ሶስት መጻሕፍትን እየያዝኩ ነበር፡፡ ለዚያን ዘመን ልጃገረዶች ያልተለመደ ቢሆንም፣ “አዲስ ዘመን” እና “የዛሬይቱ ኢትዮጵያ” ጋዜጦችንም ማንበብ እወድ ነበር፡፡
የ10ኛ ክፍል ተማሪ ሳለሁ በደርግ ወታደራዊ መንግስት የእድገት በሕብረት ዘመቻ፣ በሰሜን ትግራይ ወደምትገኘው ውቅሮ የተባለች የገጠር መንደር ተላኩ፡፡ ለእኔ ነፃ የወጣሁበት ጊዜ ይሄ ነበር ማለት እችላለሁ፡፡ ትክክለኛ ኃላፊነት ምን እንደሚመስል የተገነዘብኩበት የመጀመሪያ አጋጣሚዬም ነበር፡፡ ገበሬዎችን የሕብረት ሥራ ማህበራት እንዲመሰርቱ ለማገዝ ከዩኒቨርሲቲ ተማሪዎች ጋር እልም ወዳለ ገጠር ነበር የተላኩት:: ከስድስት ወራት አገልግሎት በኋላም ወደ አዲስ አበባ ተመለስኩ፡፡ ከዚያም ቅድስት ማሪያም ት/ቤት ተመልሼ በመግባት ያቋረጥኩትን ትምህርት የቀጠልኩ ሲሆን በ1970 ዓ.ም የሁለተኛ ደረጃ ትምህርቴን አጠናቀቅሁ፡፡ ይህ ጊዜ የደርግ መንግስት አስከፊውን የቀይ ሽብር ዘመቻ ያጧጧፈበት ወቅት ስለነበር፤ በተለይ ለተማሪዎች አስፈሪ ነበር:: አዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ብገባም የእለት የእለቷን ከመኖር ውጭ ለወደፊት ህይወቴ ምንም ዓይነት ህልም አልነበረኝም፡፡ የተመደብኩበትን የሥነ ልሳን ትምህርት ባልወደውም፣ አብረው ለሚሰጡት የሥነ ጽሑፍ ትምህርቶች ስል ገፋሁበት፡፡
የመጨረሻ ዓመት ተማሪ ሳለሁ በአጋጣሚ በሬዲዮ ድራማ ላይ የመተወን እድል አገኘሁ፡፡ ነገሩ እንዲህ ነው፡- አንድ ቀን የትያትር ጥበባት የትምህርት ክፍል ተማሪዎች የነበሩት አስታጥቃቸው ይሁን እና ተፈሪ አለሙ፤ የተማሪዎች መኖሪያ ደባል ጓደኛዬን መንበረ ታደሰን ፍለጋ ወደ ክፍላችን ይመጣሉ፤ መንበረን የፈለጓት አስታጥቄ በፃፈው የሬዲዮ ድራማ ላይ ለመቀረፅ አብራቸው እንድትሄድ ነበር:: እሷ እንደሌለች ስነግራቸው በእሷ ምትክ ካልሰራሽ ብለው ወጥረው ያዙኝ፡፡ መጀመርያ ላይ አሻፈረኝ ብያቸው ነበር፡፡ በኋላ ግን ተስማምቼ፣ በያኔው የታደሰ ሙሉነህ ‹እሁድ ፕሮግራም› የተሰኘ ተወዳጅ የሬዲዮ ፕሮግራም ላይ ድራማ ለመቅረፅ አብሬያቸው ሄድኩ፡፡ ያኔ ‹የእሁድ ፕሮግራም› በኢትዮጵያ ሬዲዮ ከወታደራዊው አገዛዝ አብዮታዊ ፕሮፓጋንዳ የተለየ መዝናኛ የሚያቀርብ ብቸኛ ዝግጅት ነበር:: በቀረፃው ወቅት ታደሰ ሙሉነህ አገር ውስጥ አልነበረም:: እንደተመለሰ ግን “ለሬዲዮ ጥሩ ድምፅ አላችሁ” በሚል እንድናነጋግረው ጠየቀን፡፡ በሬዲዮ ላይ መስራት የጀመርኩት በዚህ መልኩ ነበር፡፡ ታደሰ ሙሉነህ ለሁላችንም የሙያ አባታችን ነበር፡፡ ምንም ልምድ ባልነበረን ጊዜ ተቀብሎ በማሰልጠንና በሬዲዮ እንድንሰራ እድሉን በመስጠት አግዞናል፡፡
ከዩኒቨርሲቲ ከተመረቅሁኝ በኋላ መንግሥት፤ ባህልና ስፖርት ሚኒስቴር መደበኝ፡፡ ያኔ የሚዲያ ዋና ስራው የፖለቲካ ፕሮፓጋንዳ ማሰራጨት ስለነበረ፣ ሚዲያ ውስጥ የመስራት ጉጉት አልነበረኝም:: መጀመርያ ላይ የሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ የፕሬስ መምሪያ ኃላፊ፣ አብሬው እንድሰራ አልፈለገም ነበር:: ለነገሩ በእሱም አይፈረድም፤ ቀድሞ የነበረችው ሰራተኛ የወሊድ ፈቃድ እየወሰደች በቅጡ ስለማትሰራ እኔም እንደሷ እንዳልሆን ሰግቶ ነው:: ከስድስት ወራት የሥራ ጊዜ በኋላ ግን አቅሜንና ችሎታዬን በማረጋገጡ፣ የመርሃ ስፖርት ጋዜጣ፣ የስፖርት ዘጋቢ እንድሆን ተመደብኩ፡፡ እውነቱን ለመናገር የስፖርት ፍላጎት አልነበረኝም፤ ነገር ግን የክልል ውድድሮችን ለመዘገብ ወደተለያዩ የአገሪቱ ክፍሎች ስለምጓዝ፣ በአጋጣሚው ያገኘሁትን ኢትዮጵያን ተዘዋውሮ የማየት እድል ወድጄው ነበር፡፡ በኋላ ላይ ወደ ባህል ሚኒስቴር ዓለም አቀፍ ግንኙነት ክፍል ተዛወርኩ፡፡ ጎን ለጎን ግን በኢትዮጵያ ሬዲዮ እሁድ ፕሮግራም ላይ በግል መስራቴን ቀጠልኩ፡፡ በባህል ሚኒስቴር ሥራዬ እርካታ ባይኖረኝም፣ አስደሳች ተመክሮ መቅሰምና ለጋዜጠኝነት የሚቀርብ ሥራ ማፈላለጌን ገፋሁበት:: ከዚያም በኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ ተቀጥሬ የባንኩ ወርሃዊ መፅሄት ብሪቱ ዋና አዘጋጅ በመሆን፣ የፋይናንስ ዜናዎችንና አጭር ልብወለዶችን መፃፍ ጀመርኩ፡፡ በመቀጠልም አዲሱ የኢትዮጵያ የሽግግር መንግስት፣ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር የፕሬስና መረጃ ዋና ዳይሬክተር እንድሆን ጠየቀኝ፡፡ ለቀጣዮቹ አራት ዓመታት፣ በዚህ መ/ቤት ውስጥ ያገለገልኩ ቢሆንም፣ በመጨረሻ ለስራው እንደማልሆን ተገነዘብኩ:: በሬዲዮ ሥራዬ የሚያውቁኝ አንዳንድ ሰዎች ለቢሮክራሲያዊ ስራ እንደማልሆን ይነግሩኝ ነበር፤ እኔም ትክክል እንደሆኑ አውቅ ነበር፡፡ ለስምንት ዓመታት በግሌ በሬዲዮ ላይ ሰርቻለሁ፡፡ በእነዚህ ጊዜያትም በሬዲዮ ድራማዎቼ፣ ጭውውቶቼና ጥናታዊ ስራዎቼ ታዋቂነትን አትርፌአለሁ፡፡  
ሦስተኛ ልጄን እርጉዝ ሳለሁ ነበር ከውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር የለቀቅሁት፡፡ ለጥቂት ጊዜያት ምን መስራት እንዳለብኝ እያሰላሰልኩ ቆየሁ፡፡ ለትንሽ ጊዜ በፕሬስ አደራጅነት የሰራሁ ሲሆን የሕዝብ ግንኙነት ስራዎችን የሚያከናውን ድርጅትም ከፍቼ ነበር፡፡ በዚህ መሃል ግን የኢትዮጵያ ሬዲዮ ሥራ አስኪያጅ የነበረው ፈቃዱ የምሩ፣ ባለቤቴን በኤፍ ኤም 97.1 የአየር ሰዓት ወስዶ፣ የራሱን ፕሮግራም እንዲያዘጋጅ ጠየቀው፡፡ ባለቤቴ አዘጋጅ ሆኖ፣ እኔና ተፈሪ አለሙ ቅዳሜ ከሰዓት በኋላ የሚቀርበውን “ጨዋታ” የተሰኘ ፕሮግራም ማዘጋጀት ጀመርን፡፡ በኋላም ጌታቸው ማንጉዳይ፣ ብርሃኑ ድጋፌ፣ ግሩም ዘነበና ደረጀ ኃይሌ ተቀላቀሉን፡፡ “ጨዋታ” ለስምንት ዓመት ገደማ በአየር ላይ ውሏል፡፡ ፕሮግራሙ የመፅሄት ይዞታ የነበረው ሲሆን የታሪክ ትረካዎች፣ ድራማዎች፣ ቃለ ምልልሶችና ሌሎችንም ያካተተ ነበር፡፡
ከዚያም መንግስት ለሁለት የግል ሬዲዮ ጣቢያዎች ፈቃድ እንደሚሰጥ ይፋ ሲያደርግ ባለቤቴ ማመልከት አለብን አለ፡፡ መጀመርያ ላይ ወደ ኋላ ብዬ ነበር፡፡ ሳልፈልግ ቀርቼ ሳይሆን ገንዘቡም ዝግጅቱም ሳይኖረን፣ ምኑን ከምኑ እናደርገዋለን የሚል ፍራቻ ይዞኝ ነው፡፡ ባለቤቴ ግን ይህን እድል በድጋሚ ላናገኘው እንችላለን ብሎ ተሟገተኝ፡፡ በመጨረሻም የእሱ ሃሳብ አሸነፈና ከተፈሪ አለሙ ጋር አመለከትን:: ረዥም ጊዜ ከፈጀ ሂደት በኋላም የሸገር ኤፍኤምን ፈቃድ በእጃችን አስገባን፡፡ ይኼኔ በፍርሃት ራድኩኝ:: “አሁን ምንድነው የምናደርገው?” ብዬ ግራ ገባኝ:: የምንመዘነው የ90 ዓመት እድሜ ካስቆጠረው ግዙፉ የኢትዮጵያ ሬዲዮ ድርጅት ጋር ነው፡፡ ሸገር ከዜሮ መጀመር ነበረበት፡፡ ነገሩ በከፍታና በዝቅታ የተሞላ አጓጊ፣ አነቃቂና እልህ አስጨራሽ ነበር:: አንዳንዴ “ለምንድነው እዚህ ውስጥ የገባሁት?” እያልኩ ራሴን እጠይቅ ነበር፡፡ የእኔ ጥንካሬ በሬዲዮ ፕሮግራሞችና ይዘቶች ዝግጅት ላይ እንጂ በቴክኒክ፣ በአስተዳደራዊ ወይም በንግድ ጉዳዮች ላይ አልነበረም፡፡ እንደመታደል ሆኖ ግን ከአሜሪካዊው አማካሪዬ ከዴኒስ እስራኤል ጋር ዕድል አገናኘኝ:: እሱ የሬዲዮ ጣቢያ ለማቋቋም አስፈላጊ የሆኑ ቴክኒካዊ ጉዳዮችን ሁሉ ቁጭ አድርጎ አማከረኝ፡፡ በንግዱ በኩል ደግሞ በኢትዮጵያ ሬዲዮ ከደጓሚዎች ጋር የመስራት መጠነኛ ልምድ ነበረን፡፡ ባለቤቴም በማስተዋወቅና የንግድ ትልሙን በመንደፍ አገዘን:: በመጨረሻም የግል ሬዲዮ ሥርጭት መስፋፋትን በሚደግፉ በርካታ ባለሙያዎች እገዛ፣ ሸገር 102.1 መስከረም 25 ቀን 1997 ዓ.ም አየር ላይ ዋለ፡፡
ሸገር በኢትዮጵያ ውስጥ ካሉ ሌሎች የሬዲዮ ጣቢያዎች ለየት የሚያደርገው የራሱ ልዩ ድምፅና ድባብ እንዲኖረው እንፈልግ ነበር፡፡ ከኢትዮጵያ ሬዲዮ ውጭ ከነበሩ ሁለት አማራጮች አንደኛው ስለነበርን፣ መጀመርያ ላይ ይሄን ማድረግ ከባድ አልነበረም፡፡ ዛሬ ግን ሌሎች ሬዲዮ ጣቢያዎች የአቀራረብ ስልታችንን ያለ ፈቃድ ስለሚወስዱብን፣ ሁልጊዜም አዲስ ነገር መፍጠር ይጠበቅብናል:: በእርግጥ ይሄ ያኮራናል እንጂ አያስቆጨንም:: በየሳምንቱ ቅዳሜ የሚተላለፈውን ‹የጨዋታ እንግዳ› እና የእሁድ ጠዋቱን ‹ሸገር ካፌ› ፕሮግራሞች በመቅረፅ የማሳልፋቸው አራት ሰዓታት ለእኔ ተወዳጅና ተናፋቂዎች ናቸው፡፡
ወደፊት ሸገር ኤፍ.ኤም ወደ ሸገር ሬዲዮና ቴሌቪዥን፣ ቀስ በቀስም ወደ ሸገር ሲኒማ አድጎና ሰፍቶ ማየት እፈልጋለሁ፡፡ ሸገር ኤፍኤም ህብረተሰቡ ሰምቶት የማያውቀውንና የሚማርበትን፣ የሚያዝናናውንና የሚያስቀውን ነገር እንዲያቀርብ እንሻለን፡፡ ሸገር አድማጮቹ ሃሳባቸውን የሚያንሸራሽሩበት ትክክለኛ መድረክና ድምፅ አልባ ለሆኑትም ድምፃቸው ነው፡፡
በኢትዮጵያ ውስጥ ሴት ሆኖ መኖር ተጨማሪ ፈተና አለው፡፡ በስፖርት ኮሚሽን ሳለሁ ሥራዬን የማከናወን ብቃት እንዳለኝ ለአለቃዬ ለማሳየት የበለጠ መትጋት ነበረብኝ፡፡ አሁንም ሳይቀር በሥራዬ ላይ አንዲትም ክፍተት እንዳይገኝብኝ በከፍተኛ ጥንቃቄ እዘጋጃለሁ፡፡ በቀላሉ ደግሞ ተስፋ አልቆርጥም፡፡ በመንገዴ ላይ መሰናክል ከገጠመኝ መውጪያ መንገድ የምፈልገው በመሰናክሉ ዙሪያ ነው፡፡ በምሰራው ሁሉ መቶ በመቶ እርግጠኝነት ተሰምቶኝ አያውቅም፡፡ አሁንም ወደ ቃለ መጠይቅ ስሄድ፣ ሁሉን ነገር እንደማላውቅ ስለማውቅ መረበሼ አይቀርም፡፡ ግን ደግሞ ሁሉን ነገር አለማወቃችን ነው ህይወትን የሚያጣፍጣት፡፡ ያልተገመቱ ነገሮች እንዲከሰቱም እድል ይሰጣል፡፡
የኢትዮጵያ ሴቶች የሚገባቸውን ያህል ዋጋ አልተሰጣቸውም ብዬ አምናለሁ፡፡ በኢትዮጵያ ሴቶች አካላዊ ውበት ላይ የማተኮር አዝማሚያ ይታያል፤ የኢትዮጵያ ሴቶች መለያ ግን አካላዊ  ውበታቸው ብቻ ነው ብዬ አላምንም፡፡ አስደናቂ ጥንካሬና ብርታታቸውም መለያቸው ነው፡፡ ራሳቸው የኢትዮጵያ ሴቶችም ሆኑ ቀሪው ዓለም ይሄን ጥንካሬያቸውን የሚገነዘቡላቸው ጊዜ እንደሚመጣ ተስፋ አደርጋለሁ፡፡
በትምህርት ቤት ወይም በራሳቸው ንባብ አሊያም ደግሞ እርስ በእርስ በመማማር ሴቶች ራሳቸውን እንዲያስተምሩ እመክራለሁ፡፡ በባል፣ በልማድ፣ በሃይማኖት ወይም በአጠቃላይ በህብረተሰቡ የተቀመጡ መለኪያዎችን ወይም ገደቦችን መቀበል የለባቸውም፡፡ ራሳቸውም ቢሆኑ በራሳቸው ላይ ገደብ ከማስቀመጥ መታቀብ አለባቸው፡፡ ሁሉ ነገር ወዲያውኑ አይሳካምና የሚፈልጉት ነገር ጊዜ ሊወስድ እንደሚችል መረዳት፤ እንዲሁም ውስጣቸውን ማድመጥ አለባቸው፡፡  
ምንጭ፡- (ተምሳሌት፤ ዕጹብ ድንቅ ኢትዮጵያውያን ሴቶች፤2007)   


            ሚዩዚክ ሜይዴይ ከኢትዮጵስ ኮሌጅ ጋር በመተባበር ነገ ከቀኑ 8፡00 ጀምሮ “Born a crime” በተሰኘውና በጥላሁን ግርማ “የአመፃ ልጅ” በሚል ወደ አማርኛ በተመለሰው መፅሀፍ ላይ በብሔራዊ ቤተ መዛግብትና ቤተ መፃህፍት ኤጀንሲ አዳራሽ ውይይት ይካሄዳል፡፡
በዕለቱ ለውይይቱ የመነሻ ሀሳብ የሚያቀርቡት በወልቂጤ ዩኒቨርሲቲ የገቨርናንስና ዴቨሎፕመንት ትምህርት ክፍል መምህር የሆኑት መኮንን መንገሻ ሲሆኑ የመፅሀፉ ተርጓሚ ጥላሁን ግርማ በዕለቱ ተገኝተው በውይይቱ ላይ እንደሚካፈሉና የውይይቱ መድረክ በሰለሞን ተሰማ ጂ. እንደሚመራ የገለፀው ሚዩዚክ ሜይ ዴይ ፍላጎት ያለው በውይይቱ ላይ እንዲሳተፍ ጋብዟል፡፡

 ደራሲ ገጣሚ ተርጓሚና ፀሐፌ ተውኔት ጋዜጠኛ ነቢይ መኮንን ለማህበረሰቡ ላበረከተው አስተዋጽኦ፣ ለመራው መንገድና ላጋራው እውቀት፤ ምስጋናና አክብሮት ለመስጠት የተዘጋጀው “ነብይ ባገሩ እንዲህ ይከበራል” የምስጋናና የኪነጥበብ ምሽት ትላንት በአዲስ አበባ ቲያትርና ባህል አዳራሽ በድምቀት ተካሄደ፡፡ ገጣሚ ፍሬዘር አድማሱና የመሶብ ባህላዊ ባንድ መስራችና ዋሽንት ተጫዋች ጣሰው ወንድም ሃሳብ አፍላቂነት በተዘጋጀው በዚህ የምስጋና ምሽት፤ ገጣሚያን ሰዓሊያንና ሙዚቀኞች የተሳተፉ ሲሆን፤ ገጣሚና ጋዜጠኛ ተፈሪ አለሙ፣ አርቲስት አበባ ባልቻና አዋቂው በሃይሉ ገ/መድህን ስለታላቁ የጥበብ ሰው ነቢይ መኮንን የሚያውቁትን ለታዳሚ ገልፀዋል፡፡
ሰዓሊያን በበኩላቸው ነቢይን እንደ ገጣሚ፣ እንደ ተርጓሚ፣ እንደ ጋዜጠኛና ፀሐፌ ተውኔት ምን ሊመስል ይችላል በሚል በገባቸው መጠን በመድረኩ ላይ በስዕል ገልፀውታል፡፡ በተጨማሪም ገጣሚያኑ ጌትነት እንየው፣ ኤፍሬም ስዩም፣ ተስፋሁን ፀጋዬ፣ አበባው መላኩ ደምሰው መርሻ፣ ሰለሞን ሳህለ፣ ፍሬዘር አድማሱ፣ ምልዕቲ ኪሮስ፣ ምስራቅ ተረፈና ረድኤት ተረፈ የግጥም ስራዎቻቸውን ያቀረቡ ሲሆን፤ ተፈሪ አለሙና በሃይሉ ገ/መድህን ወግ አቅርበዋል፡፡
“አንድ ሰው በርካታ ስራዎችን ሰርቶ ምንም እንዳልሰራ ሊቆጠር ይችላል፤ ነገር ግን የሰራውን ያበረከተውን መስዋዕትነቱንና አስተማሪነቱን በተዘዋዋሪ መንገድ ለራሱ ለመንገርና ከፍታውን ለማሳየት፣ ከዛም ራሱን መቃኘት እንዲችል እንዲህ አይነት መድረኮች ወሳኝ ናቸው” ያለው ገጣሚ ፍሬዘር አድማሱ፣ ነቢይ መኮንንም በዚህ መድረክ ሲመሰገንና አክብሮት ሲቸረው ራሱንም ይቃኝበታል በሚል የምስጋና መድረኩ መዘጋጀቱን ለአዲስ አድማስ ገልጿል፡፡ ገጣሚ ነቢይ መኮንን፤ የአዲስ አድማስ መስራችና ዋና አዘጋጅ መሆኑ ይታወቃል፡፡

 ዓለም አቀፉ ማህበረሰብ የተፈጸመውን ግድያ አውግዟል

             የሱዳን ህዝባዊ ተቃውሞ  ተባብሶ መቀጠሉንና የወታደራዊ የሽግግር ምክር ቤት ወታደሮች በወሰዱት የሃይል እርምጃ ባለፉት ጥቂት ቀናት አንድ መቶ ያህል ተቃዋሚዎች መገደላቸውን ተከትሎ፣ የአፍሪካ ህብረት የሰላምና ጸጥታ ምክር ቤት፣ ሱዳንን ከህብረቱ አባልነት ማገዱን ከትናንት በስቲያ አስታውቋል፡፡
የሰላምና ጸጥታ ምክር ቤቱ በሱዳን ወቅታዊ ሁኔታ ዙሪያ በአዲስ አበባ ያካሄደውን አስቸኳይ ስብሰባ ሲያጠናቅቅ ባወጣው መግለጫ እንዳስታወቀው፣ ሱዳንን በማስተዳደር ላይ የሚገኘው ወታደራዊ የሽግግር ምክር ቤት ስልጣኑን በሲቪል ለሚመራ የሽግግር መንግስት እስከሚያስረክብ ድረስ ሱዳን በየትኛውም የህብረቱ እንቅስቃሴ ውስጥ እንዳትሳተፍ እገዳ ተጥሎባታል፡፡
በተቃውሞ እየተናጠችና ወደ እርስ በእርስ ግጭት እያመራች የምትገኘዋን ሱዳን ከቀውስ ለመታገድ የሚቻለው በሲቪል አስተዳደር የሚመራ የሽግግር መንግስት ማቋቋም ሲቻል ነው ያለው የህብረቱ የሰላምና የጸጥታ ምክር ቤት፤ ወታደራዊው ምክር ቤት ይህን አማራጭ በመጠቀም አገሪቱን ከጥፋት እንዲታደግ ጥሪ አቅርቧል፡፡
ኡመር አልበሽር ከስልጣን ከወረዱ በኋላ እጅግ አስከፊው የተባለው የተቃውሞ ሰልፍ ባለፈው ሰኞ በካርቱም መካሄዱንና የወታደራዊ የሽግግር ምክር ቤት ወታደሮች ባለፉት ቀናት በድምሩ 100 ያህል ተቃዋሚዎችን መግደላቸውን የዘገበው አሶሼትድ ፕሬስ፤ ይህን ተከትሎም ተቃውሞው ወደ ሌሎች የሱዳን ከተሞች መስፋፋቱንና ውጥረቱ መባባሱን አመልክቷል፡፡
ከትናንት በስቲያ የተወሰኑ ሰራተኞቹን ከሱዳን ያስወጣውን የተባበሩት መንግስታት ድርጅት ጨምሮ የተለያዩ የአለማችን አገራት መንግስታት ወታደሩ በሱዳን ተቃዋሚዎች ላይ የሚወስደውን የሃይል እርምጃ እያወገዙት እንደሚገኙ የጠቆመው ዘገባው፤ ሩስያ በበኩሏ በሱዳን ላይ የሚደረግን የውጭ ሃይሎች ጣልቃ ገብነት እንደምታወግዝና ችግሩ በብሄራዊ መግባባት መፈታት እንዳለበት ያላትን አቋም አስታውቃለች፡፡ አለማቀፉ ተቋም አምነስቲ ኢንተርናሽናል በበኩሉ፤ ወታደራዊው መንግስት ከሃይል እርምጃዎች እንዲታቀብ አለማቀፍ ጫና ሊደረግ ይገባል ሲል መግለጫ አውጥቷል፡፡
የሱዳን ዶክተሮች ማዕከላዊ ኮሚቴ ከትናንት በስቲያ ባወጣው መግለጫ፤ በሳምንቱ በወታደሮች በተፈጸመባቸው ጥቃት ከ108 በላይ ተቃዋሚዎች መገደላቸውንና ከ500 በላይ የሚሆኑትም መቁሰላቸውን ቢያስታውቅም፣ የሱዳን የጤና ሚኒስቴር ግን “ቁጥሩ ተጋኗል፤ የሞቱት 61 ብቻ ናቸው” ሲል ማስተባበሉን አልጀዚራ ዘግቧል፡፡
በሱዳን ህዝባዊ ተቃውሞው ተባብሶ መቀጠሉን ተከትሎ፣ የቱርክ አየርመንገድን (ተርኪሽ ኤርላይንስን) ጨምሮ ወደ አገሪቱ ይጓዙ የነበሩት የግብጽና የተባበሩት አረብ ኤሜሬትስ አየር መንገዶች በጸጥታ ስጋት ሳቢያ በረራቸውን መሰረዛቸውን አናዶሉ ኤጀንሲ ዘግቧል፡፡

 የህንዷ ከተማ ሙምባይ ባለፈው የፈረንጆች አመት 2018 ከአለማችን አገራት ከተሞች መካከል እጅግ አስከፊው የትራፊክ መጨናነቅ ችግር የነበረባት ቀዳሚዋ ከተማ መሆኗን አንድ አለማቀፍ ጥናት አመለከተ፡፡
ቶምቶም የተባለው የሆላንድ የጥናት ተቋም በ56 የአለማችን አገራት ውስጥ በሚገኙ 403 ከተሞች ላይ የሰራውን ጥናት ጠቅሶ ሲኤንኤን እንደዘገበው፣ በሙምባይ ጎዳናዎች ላይ የሚያሽከረክር አንድ ሾፌር በትራፊክ መጨናነቅ ሳቢያ ጉዞው ከሚፈጅበት ጊዜ 65 በመቶ ያህል ተጨማሪ ጊዜ ለማባከን ተገድዷል፡፡
የኮሎምቢያዋ መዲና ቦጎታ በትራፊክ መጨናነቅ ከአለማችን ከተሞች በሁለተኛ ደረጃ ላይ እንደምትገኝ የጠቆመው ዘገባው፣ በከተማዋ ጎዳናዎች የሚመላለሱ መኪኖች ካሰቡበት ለመድረስ 57 በመቶ ተጨማሪ ጊዜ እንደሚፈጅባቸውም አመልክቷል:: በትራፊክ መጨናነቅ የፔሩዋ ሊማ በሶስተኛ፣ የህንዷ ርዕሰ መዲና ኒው ደልሂ በአራተኛ ደረጃ ላይ መቀመጣቸውን የጠቀሰው ተቋሙ፤ ባለፉት አስር አመታት 75 በመቶ በሚሆኑት የአለማችን ከተሞች የትራፊክ መጨናነቅ ችግር ተባብሶ ቀጥሏል ብሏል፡፡

  ሳኒ አባቻ በእንግሊዝ ባንክ ያስቀመጡት 267 ሚሊዮን ዶላር ተወረሰ

              በአፍሪካ በነዳጅ ሃብቷ ቀዳሚውን ስፍራ በምትይዘው ናይጀሪያ፣ በየቀኑ በአማካይ 100 ሺህ በርሜል ያህል ድፍድፍ ነዳጅ በህገ ወጦች እንደሚዘረፍ ብሉምበርግ ዘግቧል፡፡
በመላው ናይጀሪያ የነዳጅ መተላለፊያ ቱቦዎችን እየሰረሰሩ ከፍተኛ መጠን ያለው ነዳጅ የሚዘርፉ ሰዎች ቁጥር ግማሽ ሚሊዮን ያህል እንደሚደርስ የጠቆመው ዘገባው፤ ይህም አገሪቱ ከነዳጅ ኤክስፖርት የምታገኘው ገቢ በከፍተኛ ሁኔታ እንዲቀንስ ማድረጉንም አመልክቷል፡፡
በናይጀሪያ ነጋ ጠባ የሚዘረፈውና በመቶዎች በሚቆጠሩ ትናንሽ የነዳጅ ማጣሪያዎች እየተጣራ በህገ ወጥ መንገድ ለሽያጭ የሚቀርበው ነዳጅ በገንዘብ ሲተመን የአገሪቱን የበጀት ጉድለት ሙሉ ለሙሉ የመሸፈን አቅም እንዳለው የጠቆመው ዘገባው፤ በአገሪቱ የሚገኙ የነዳጅ ኩባንያዎችም የዝርፊያው ሰለባ መሆናቸውን ገልጧል፡፡
ታዋቂው ሼል ኩባንያ በናይጀሪያ ባለፈው የፈረንጆች አመት (2018)፣ በየቀኑ 11 ሺህ በርሜል ድፍድፍ ነዳጅ በወንጀለኞች መዘረፉንም ዘገባው አስታውሷል፡፡
በተያያዘ ዜና ደግሞ፣ የቀድሞው የናይጀሪያ ፕሬዚዳንት ሳኒ ኣባቻ፣ በስልጣን ዘመናቸው በሙስና ያፈሩትና በእንግሊዝ ውስጥ በሚገኝ ባንክ ከዝነውት የነበረ 267 ሚሊዮን ዶላር እንዲወረስ መወሰኑ ተዘግቧል፡፡
እ.ኤ.አ ከ1993 አንስቶ በሞት እስከተለዩበት 1998 ድረስ አገሪቱን የመሩትና በአምባገነንነታቸው የሚታወቁት ሳኒ ኣባቻ፤ በህገ ወጥ መንገድ ከአገር አስወጥተውታል የተባለውና ላለፉት 5 አመታት እንዳይንቀሳቀስ ታግዶ የነበረው ይህ ገንዘብ፣ ለናይጀሪያ ለአሜሪካና ለእንግሊዝ እንደሚከፋፈል ተነግሯል፡፡


 አጠቃላይ የሀብቷ መጠን 600 ሚሊዮን ዶላር እንደደረሰ የሚነገርላት አሜሪካዊቷ ድምጻዊት ሪሃና፣ በታዋቂው የፎርብስ መጽሄት፣ የአለማችን ሴት ሙዚቀኞች የሀብት ደረጃ በመሪነት መቀመጧ ተነግሯል፡፡
ሪሃና ከሙዚቃ ስራዎቿ፣ ከኮንሰርት በተጨማሪ ታዋቂውን ፌንቲ ቢዩቲ ኩባንያ ጨምሮ ባቋቋመቻቸው የፋሽንና የውበት ኩባንያዎች ከፍተኛ ገቢ እንደምታገኝ የጠቆመው ፎርብስ፤ ከፍተኛውን የ570 ሚሊዮን ዶላር ገቢ ያገኘችውም ከፌንቲ መሆኑን አስታውቋል፡፡
በዘንድሮው የፎርብስ መጽሄት የአለማችን ሴት ባለጸጋ ሙዚቀኞች ዝርዝር ውስጥ የሁለተኛነት ደረጃን የያዘቺው ሌላኛዋ ታዋቂ ድምጻዊት ማዶና ስትሆን፣ ድምጻዊቷ 570 ሚሊዮን ዶላር ሃብት እንዳላት ፎርብስ አስታውቋል፡፡
ሴሊን ዲዮን በ450 ሚሊዮን ዶላር፣ ቢዮንሴ ኖውልስና ባርባራ ስቴሪሳንድ በ400 ሚሊዮን ዶላር፣ ቴለር ስዊፍት በ360 ሚሊዮን ዶላር እንደ ቅደም ተከተላቸው ከሶስተኛ እስከ እስከ አምስተኛ ያለውን ደረጃ የያዙ ሌሎቹ የአለማችን ዝነኛ ድምጻውያን መሆናቸውንም ፎርብስ መጽሄት ሰሞኑን ባወጣው መረጃ አመልክቷል፡፡


                  ሰሞኑን በአክሱም ዩኒቨርስቲ በተማሪዎች መካከል በተፈጠረ ግጭት አንድ ተማሪ ህይወቱ ማለፉ የሚታወቅ ሲሆን፤ ከተማሪው ግድያ ጋር በተያያዘ 10 ተጠርጣሪዎች በቁጥጥር ሥር ውለው በፖሊስ ምርመራ እየተደረገባቸው ነው::
በደብረ ማርቆስ ዩኒቨርስቲ በተከሰተ ግጭት አንድ ተማሪ መሞቱን ተከትሎ ከግንቦት 19 ቀን 2011 ዓ.ም ጀምሮ በአክሱም ዩኒቨርስቲ የብሔር መልክ ያለው ውጥረት ተከስቶ እንደነበር ያስረዱት የአክሱም ዩኒቨርስቲ ፕሬዚዳንት፤ ተማሪዎች ድንጋይ መወራወር ሲጀምሩ የፀጥታ ኃይሎች ወደ ግቢው ገብተው ለማረጋጋት መሞከራቸውን ተናግረዋል፡፡
ሆኖም የብሔር መልክ ያላቸው ትንኮሳዎች አይለው ማክሰኞ ግንቦት 27 ቀን 2011 ዓ.ም፣ የኢድ አልፈጥር በዓል ቀን ሁሉም ተማሪዎች ዕረፍት ላይ በነበሩበት አጋጣሚ፣ ከረፋዱ 4፡30 ላይ በተወሰኑ ተማሪዎች የድንጋይ ውርወራ ግጭት ማገርሸቱንና በግጭቱም ዮሐንስ ማስረሻ የተባለ የመካኒካል ኢንጅነሪንግ የ2ኛ ዓመት ተማሪ ህይወቱ ማለፉን ፕሬዚዳንቱ ያስረዳሉ፡፡
በዚህ ግጭት ሶስት ተማሪዎች ከባድ ጉዳት ደርሶባቸው በህክምና ላይ እንደሚገኙም የተገለፀ ሲሆን በርካቶች ደግሞ ቀላል ጉዳት አጋጥሟቸው መታከማቸውን ለማወቅ ተችሏል::
ረቡዕ እለት አምስት ያህል ተማሪዎች በግጭቱ ተሣትፎና ወንጀል ፈፃሚነት ተጠርጥረው መታሰራቸውን ዩኒቨርስቲው ያስታወቀ ሲሆን ድርጊቱን በጽኑ ያወገዙት የትግራይ ም/ርዕሰ መስተዳድር ዶ/ር ደብረ ፂዮን ገ/ሚካኤል በበኩላቸው፤ በዩኒቨርስቲው ለተፈጠረው ብሔር ተኮር ግጭትና ለተማሪው ሞት ተጠያቂ የሆኑ አካላት ለህግ ይቀርባሉ ብለዋል፡፡
“ድርጊቱ አስነዋሪ ነው” ያሉት ዶ/ር ደብረጽዮን፤ “ትግራይ የብሔሮችና ብሔረሰቦች መኖሪያ መሆኗን አምኖ ለመጣ ተማሪ፣ እንዲህ አይነት ተግባር መፈፀም፣ ሰላም ወዳዱን የክልሉን ህዝብ ባህልና ታሪክ የማይገልጽ ነው” ብለዋል፡፡
ግንቦት 16 ቀን 2011 ዓ.ም በደብረ ማርቆስ ዩኒቨርስቲ በተመሳሳይ ሁኔታ በተማሪዎች በተቀሠቀሰ ግጭት፤ የሦስተኛ አመት የኢኮኖሚክስ ተማሪ የነበረው ወጣት ሰአረ አብርሃ ህይወቱ ማለፉ አይዘነጋም፡፡ በዚሁ ግጭት 3 ተማሪዎችም ከፍተኛ ጉዳት ደርሶባቸው ሆስፒታል ገብተው እንደነበር ይታወቃል፡፡ ተማሪዎቹ የተገደሉት በድንጋይና በዱላ ተደብድበው እንደሆነም ተነግሯል፡፡
በሌላ በኩል፤ ባለፈው ሐሙስ በነቀምቴ ከተማ “ፋክት” በተባለ ሆቴል ላይ በተፈፀመ የቦንብ ጥቃት፣ የነቀምት ከተማ እግር ኳስ ቡድን ተጫዋች የሆነው ወንድወሰን ዮሐንስ የተገደለ ሲሆን፤ ሶስት ሰዎች ላይም ከባድ ጉዳት መድረሱ ተገልጿል፡፡ ጥቃት አድርሰዋል የተባሉ ተጠርጣሪዎች በፖሊስ ቁጥጥር ስር ውለው ምርመራ እየተደረገባቸው መሆኑም ታውቋል፡፡

በመላው አፍሪካ 60 ሚሊዮን ያህል ህጻናት የምግብ አቅርቦት እንደማያገኙና በአህጉሪቱ በየአመቱ ለሞት ከሚዳረጉ ህጻናት መካከል ግማሽ ያህሉ በርሃብ ምክንያት እንደሚሞቱ አንድ ጥናት አመለከተ፡፡
አፍሪካን ቻይልድ ፖሊሲ የተባለው ተቋም ከሰሞኑ ይፋ ያደረገው ጥናት እንደሚለው፤ ምንም እንኳን የአፍሪካ አገራት በቀርብ አመታት ኢኮኖሚያዊ ዕድገት ቢያስመዘግቡም፣ ከሶስት አፍሪካውያን ህጻናት አንዱ የመቀንጨር ችግር ተጠቂ ነው፡፡
በመላው አለም በምግብ እጥረት ምክንያት በየቀኑ 10 ሺህ ያህል ህጻናት ለሞት እንደሚዳረጉ የዘገበው ዘ ጋርዲያን፤ የህጻናት ረሃብ በአለማቀፍ ደረጃ መሻሻል ቢያሳይም በአንዳንድ የአፍሪካ አገራት ግን ችግሩ በእጅጉ እየተባባሰ እንደሚገኝ አመልክቷል፡፡
90 በመቶ አፍሪካውያን ህጻናት የአለም የጤና ድርጅት ያስቀመጠውን ዝቅተኛ የምግብ ንጥረነገር ቅንብር ደረጃ ያላሟሉ መሆናቸውን የጠቆመው ዘገባው፤ ከአምስት አፍሪካውያን ህጻናት መካከል ሁለቱ በቋሚነት ምግብ እንደማይመገቡ ገልጧል፡፡


               ከዕለታት አንድ ቀን በአንድ ቤት ውስጥ አንድ አህያና አንድ የቤት ውሻ ይኖሩ ነበረ፡፡
አህያው እግርግም ውስጥ ይታሰራል፡፡ ብዙ መኖ በዙሪያው ይቀመጥለታል፡፡ በጣም ጠግቦ ይበላል። ጌታው ደግ በመሆኑ እንደ ልቡ እንዲያናፋም ይፈቀድለታል፡፡
የቤት ውሻው ደግሞ ጌታው ከውጪ ሲመጣ በር ድረስ ሄዶ ይቀበለዋል፡፡ ጌታውም ያመጣለትን ቅንጣቢ ሥጋ ይሰጠዋል፡፡
ወደ  ቤት አስገብቶም እጭኑ ላይ አስቀምጦ፣ እያሻሸ፣ እራት ሲበላ እንደገና ጉርሻ ይሰጠዋል፡፡ አህያ ከደጅ ሆኖ ለውሻው የሚደረግለትን እንክብካቤ በማየት በጣም ይቀናል፡፡
አንድ ቀን አህያ፤
“ውሻ ሆይ?” ይላል፡፡
“አቤት” አለ ውሻ፡፡
“እኔ ባንተ ህይወት በጣም እቀናለሁ”
“ለምን?”
“ጌታችን ከበራፉ ጀምሮ እየመገበህ፣ እያሻሸህ፣ አብሮ ገበታ እያቀረበህ፣ አብረህ ቴሌቪዥን እንድታይ እየፈቀደልህ፣ ሳሎን እያሳደረህ እንደ ሰው ያኖርሃል፡፡ እኔ ግን ብርድ እየፈደፈደኝ አድራለሁ፡፡ ጠዋት ተነስቼ እህል ተጭኜ  ወፍጮ ቤት እሄዳለሁ፡፡ ስመለስ ቀርበታ ተጭኜ ወንዝ እላካለሁ፡፡ ከዛ ሸቀጣ ሸቀጥ ተጭኜ ገበያ እሄዳለሁ፡፡ እንዲሁ ስሸከም ውዬ ስሸከም ይመሻል፡፡ የኔን ኑሮ ካንተ ሳወዳድረው ንድድ ይለኛል” አለው በምሬት፡፡
ውሻም፤
“ምን ታደርገዋለህ፡፡ ይሄ የተፈጥሮ ጉዳይ ነው፡፡
ምንም ብናደርግ ልናሻሽለው የምንችለው ጉዳይ አይደለም፡፡”
አህያም፤
“የለም ይሄንን የምንለውጥበት ጊዜ መምጣቱ አይቀርም፡፡ እኔ የማደርገውን ታያለህ” አለ፡፡
ውሻም፤
“ተው አይሆንም፡፡ ይህንኑ ኑሮህን ታበላሸዋለህ፡፡ አርፈህ ብትቀመጥ ይሻላል” አለውና ተለያዩ፡፡
አንድ ቀን አህያ የታሰረበትን ገመድ በጠሰና እየፈነጨ ሳሎን ገባ፡፡ እንደ ውሻው ጭራውን እየቆላ ፣ጌታው ጭን ላይ ሊቀመጥ ሲሞክር፣ አገሩን አተራመሰው፡፡
ሳህኑ መሬት ላይ ወደቀ፡፡ ጌታው ተፈነገለና ከነወንበሩ ወለሉ ላይ ተንጋለለ!
ይሄኔ የቤቱ አሽከሮች ትላልቅ ቆመጥ ይዘው መጡ፡፡ አህያውን እንዳይሞት እንዳይድን አድርገው እየቀጠቀጡ ፣ከቤቱም፤ ከግቢውም አስወጥተው በሩን ዘጉበት፡፡ አህያ ደም በደም ሆኖ፣ባቡር መንገድ ላይ ተኝቶ ቀረ፡፡
* * *
ቦታን አለማወቅ እርግማን የመሆኑን ያህል፣ አቅምን አለማወቅ ደግሞ ከመርገምት የከፋ መርገምት ነው፡፡ መንገድ ስላለና እግር ስላለን ብቻ አንሄድበትም፡፡ አቅጣጫውን ማወቅ አለብን፡፡ ወቅትንም መጠበቅ ይጠበቅብናል!
ስለዚህ እንግዲህ፣ ቦታ፣ አቅም፣ መንገድና አቅጣጫን ማወቅ የመጪው ዘመን ትምህርታችን ይሁን።
“በደጉ ጊዜ ሆያ ሆዬ ሲጨፈር፤
ብትሰጠኝ ስጠኝ ባትሰጥ እንዳሻህ
ከጐረቤትህ ከነሱ ጋሻህ” ይባል ነበር፡፡
ዛሬ ጋሻ ቀርቶ ሁዳይም የለምና ዘፈኑ ተቀይሯል፡፡
“እዚያ ማዶ አንድ ሻማ እዚህ ማዶ አንድ ሻማ፤
የኛ መብራት ኃይል ባለመቶ አርማ” በሚል ምፀት ተለወጠ፡፡
“ክፈት በለው በሩን የጌታዬን” ብለናል በቡሄ፡፡
የ”ሀሁ በስድስት ወሩዋ”
ሙሾ አውራጅ፣ እቴሜት ጌኔ አምበርብር ደግሞ
“ዋይ ዋይ
ህመም ለህመም ሳንወያይ
አንተ ከመሬት እኛ ከላይ” ያለችውን ገልብጠን “እኛ ከመሬት አንተ ከላይ” ተባብለናል፡፡
 ለውጥ በአንድ ጀንበር ይምጣ አይባልም፡፡ “ዓይንህነገ ይበራልሃል”
ሲባል፤ ዛሬን እንዴት አድሬ” አለ እንደሚባለው አንሆንም፡፡
ምኞታችንና ጥያቄያችን ብዙ፤ መልሳችን ግን ጥቂት ነው፡፡ ሚዛን ይሸቀባል ወይ? የኑሮ ውድነት የት ደረሰ? ዲሞክራሲያችን ፋፋ ወይ? ፍትሕ አበበ ወይ? ኢኮኖሚው አደገ ወይ? ትምህርት ተስፋፋ ወይ? እስፖርት በለፀገ ወይ? ቤት ኪራይ ረከሰ ወይ? ሙስና ቀነሰ ወይ? ወንጀል መነመነ ወይ? ሹም - ሽር ቀነሰ ወይ? መንገድ በዛልን ወይ? ህንፃዎች በዙ ወይ? መኖሪያ ቤት ሞላን ወይ? ሻጭና ሸማች ተስማምተው ከረሙ ወይ? መልካም አስተዳደር ሰፈነ ወይ? መብራት ይጠፋል ወይ? ውሃ ይደርቃል ወይ? ኔትዎርክ ይበጣጠሳል ወይ? በመጨረሻም ገቢ ጨመረ ወይ? ወጪ ቀነሰ ወይ? ወይስ የተገላቢጦሽ ሆነ?
ጥያቄያችን እጅግ ረዥም፣ መልሳችን በጣም አጭር ነው፡፡
በአጠቃላይ ግን ኑሮ ተመቸን ወይ? ሰፊው ህዝብ “የባሰ አታምጣ” አለ? ወይስ “ነገ በተስፋ የተሞላ ሆነልኝ” አለ፡፡ መቼም፤ ወቅቱ የትራንስፎርሜሽን ነው ብለን ለማጽናናት አንችልም፡፡ አዝመራ እሚደርሰው በሰኔ፣ እኔን የራበኝ አሁን” ይለናላ! በክፉ ዘመን የሰው ሁሉ ስሙ “አበስኩ ገበርኩ ነው” እንዳለው ይሆን?
የዱሮ ዘመን ሊቀመንበር፤ ኤክስፐርቶች ግራፍና ስታቲስቲክስ ደርድረው፤ “ሀገራችን ለመለመች፣ አደገች፣ ዘንድሮ እህል በሽበሽ እንደሚሆን ነው ስታቲስቲክሱ የሚያሳየው” ሲሉ፤ የሀገሪቱ መሪ “የግድግዳውን ስታቲክስ አይተናል፡፡ የመሬቱን ንገሩኝ፡፡
ገበያው ጋ ሄደን እህሉ መኖሩን አሳዩኝ!” አሉ ይባላል፡፡
በልተን ለማደር ችለናል ወይ? እንደ ማለት ነው፡፡
የኑሮ ውድነትን መባባስ ለማየት አውዳመቶቹን መመርመር ነው፡፡ የጉራጌው ተረት ሁሉንም ይቋጨዋል:-
“ጅቡን የወጋኸው ምኑን ነው? ቢሉት፤ አፉን አለ፡፡ አፉን ከወጋኸውማ አሰፋኸው!”

Page 6 of 435