Administrator

Administrator

 ከዕለታት አንድ ቀን፤ አንዲት አሮጊት ዐይናቸውን በጣም ይታመማሉ፡፡ አንድ ሐኪም ስለህመማቸው ያማክራሉ፡፡ በእማኞች ፊት ውል ይገባሉ፡፡
አሮጊቷ -  እንግዲህ ውላችን ዐይኔን ካዳንክልኝና በደንብ እንዲያይ ካደረግህልኝ ከፍተኛ ገንዘብ እከፍልሃለሁ፡፡ ታድነኝካልቻልክግንበነፃትሰናበታለህ፡፡
ሐኪሙ - ባሉት ሙሉ በሙሉ ተስማምቻለሁ፤ ይሄንኑም በፊርማዬ አረጋግጣለሁ፡፡
ይፈራረማሉ፡፡
ሐኪሙ በውሉ መሠረት መድኃኒት ያዝላቸውና ህክምናቸውን ይጀምርላቸዋል፡፡ በየጊዜው እየመጣም ይጎበኛቸዋል፡፡
ሆኖም መጥቶ በሄደ ቁጥር አንዳንድ የቤት ዕቃ ይዞባቸው ይሄዳል፡፡ ይሄን ዕቃ ይዞ መሄድ በጣም ይደጋግመዋል፡፡
በዚሁ ቀጠለና ልክ መድኃኒቱ ሲያልቅ የቤት ዕቃው ተወስዶ አለቀ፡፡ አሮጊቷ ቤቱ ባዶ እንደቀረ አዩና፤
“አምሥት ሳንቲም አልከፍልህም” አሉት፡፡
 “ሠርቻለሁ፡፡ የሠራሁትን መከፈል አለብኝ” አለ በቁጣ፡፡ ደጋግሞ እንዲከፍሉት ጠየቃቸው፡፡ ደጋግመው፤ “ንብረቴን ዘርፈሃል ስለዚህ ድምቡሎ አልከፍልህም!” አሉት፡፡
“ፍርድ ቤት ወስጄ እገትርዎታለሁ!”
“እሱን እናያለን፡፡ ማን ልብ እንዳለው አሳይሃለሁ”
ከሰሳቸው፡፡
ፍርድ ቤት ቀርበው ተጠየቁ፡፡
ዳኛው  - “ከሳሽ የሚለውን ይቀበላሉ?” ሲሉ ይጠይቋቸዋል፡፡
አሮጊቷ - “ክቡር ፍርድ ቤት! ከሳሼ ያለው ትክክል ነው፡፡”
ዳኛው  -  “ታዲያ ምን ይላሉ? ምንድን ነው መከላከያዎ?”
አሮጊቷ -  “እርግጥ ነው፡፡ እሱ ዐይኔን ሊያክመኝ፤ ካዳነኝ ደህና ገንዘብ ልከፍለው ተስማምተናል፡፡ እሱም በበኩሉ ካላዳነኝ ምንም ላይከፈለውና በነፃ ወደቤቱ ሊሄድ ተስማምተናል፡፡”
ዳኛው  - “እሱም ያለው ይሄንኑ ነው፡፡ ታዲያ ምንድን ነው ችግሩ?”
አሮጊቷ - “አሁን እሱ አድኜሻለሁ ይላል”
ዳኛው  -  “እርስዎስ?”
አሮጊቷ -  “እኔማ፤ አላዳነኝም ጭራሽ የበለጠ አሳውሮኛል ነው የምለው፡፡”
ዳኛው  -  “ለዚህ ኮ ማስረጃ ማቅረብ ያስፈልጋል”
አሮጊቷ -  “አሳምሬ አቀርባለሁ ጌታዬ”
ዳኛው  -  “ጥሩ፡፡ ያቅርቡ”
አሮጊቷ -  “ክቡር ፍርድ ቤት፤ ዐይኔን ባመመኝ ሰዓትና እሱ እንዲያክመኝ በጠራሁት ጊዜ የተወሰነ የማየት ችሎታ ነበረኝ፡፡ ያኔ በማይበት አቅም በቤቴ ውስጥ የተወሰነ የቤት ዕቃና ሌላም ንብረት እንደነበረ እገነዘባለሁ፡፡ አሁን፤ እሱ አድኛታለሁ በሚልበት ጊዜ ግን፤ ምንም ነገር በቤቱ ውስጥ እንደሌለ እስከማላይበት ደረጃ አድርሶኛል፡፡”
 *   *   *
ከሁሉም በላይ ከዐይን ህመምተኛነት ይሰውረን! ዐይንህን እገልጥልሃለሁ ብሎ የበለጠ ከሚያውር ያድነን፡፡ ያ ሳያንስ ቤታችንን ባዶ ከሚያደርግ ያውጣን፡፡ የሚታዘዝልን መድኃኒት በሙሉ ሁሌም ላያድነን እንደሚችል እንገምታለን፡፡ አንዳንዱ ያድናል፤ አንዳንዱ አያድንም፡፡ መድኃኒት ሰጥቼሃለሁ በሚል የቤት ንብረታችንን ሳይቀር የሚያራቁተን ሀገር - አቀፋዊም ሆነ ዓለም- አቀፋዊ መዝባሪ እንዳይመጣብን ግን ይጠብቀን፡፡ ይሄንኑም የሚያይ ያልታመመ ዐይን ያለው ዳኛ አያሳጣን፡፡
ደህና ዐይን ካለን ታሪካችንን በኩራት እናያለን፡፡ የታሪክ አሻራ አይፋቅም - ከልደት እስከሞት አይለወጥም፤ እንዲሉ፡፡ From the Cradle to the grave
I, grieve, yet I achieve!
(“ከአንቀልባ እስከ መቃብር
ባዝንም ማሸነፌ አይቀር” እንደ ማለት ነው፡፡ “የታሪክ ዝማሬ” ተብሎ የተፃፈ ነው፡፡) ሚኒልክን በአድዋ፣ ኃ/ሥላሴን በአፍሪካ አንድነት (ህብረት)፣ መንግሥቱ ኃ/ማርያምን በመሠረተ ትምህርት ማሰብ የበጎ አዕምሮ ሀቅ ነው፡፡ ዛሬ በኢትዮጵያ መሬት፣ በቻይና ገንዘብ፤ የተመረቀው የአፍሪካ ህብረት ህንፃ ፊት የክዋሜ ንኩሩማ ሐውልት ሲቆም የአገራችን መሪዎች ቅር አይላቸውም ለማለት ባያስደፍርም፣ ከሞኝ ደጅ ሞፈር መቆረጡን እንዴት አጡት ማሰኘቱና በማን ተፅዕኖ ተፈፀመ? የሚል ጥያቄ ማስነሳቱ ግድ ነው፡፡ ብዙ እጅ በዙሪያው ለመኖሩ መጠርጠር አያቅትም፡፡ ግን ለምን፤ በዋናነት ኃይለ-ሥላሴን ያካተተ ቢያንስ ዋና ዋና የሚባሉ ሌሎች መሪዎችን የጨመረ ምስል እንኳ መቅረፅ አይቻልም?
“ልትዋጉን ስትፈልጉ ዕድል አንሰጣችሁም - ልታገኙን አትችሉም፡፡ እኛ ልንዋጋችሁ ስንፈልግ ግን እንደማታመልጡ እናረጋግጣለን፡፡ ስንመታችሁ ድርግም ነው፡፡ … ከዚያ ድምጥማጣችሁን ነው የምናጠፋው፡፡ … ጠላት ሲገፋ እናፈገፍጋለን፡፡ ጠላት ካምፑ ውስጥ ሲሰፍር፤ እንልቅፍ እንነሳዋለን፡፡ ሲደክም እናጠቃዋለን፡፡ ሲያፈገፍግ ደግሞ እኛ እንገፋለን!”
ምናልባት ዘመኑ የጃፓኖችን ዝነኛ አባባል ያስታውሰን ይሆናል፡፡ Tada yori takai mono wa nai በነፃ ከተሰጠ ስጦታ በላይ፤ ዋጋ የሚያወጣ ምንም ነገር የለም፤ እንደማለት ነው፡፡ ያንን ዋጋ እኛ እየከፈልን ይሆን?
በእርግጥ ትልቅ ዋጋ ነው፡፡ በነፃ ለተገኘ ስጦታ የምንከፍለው የክብር ዋጋ - የክብር መስዋዕትነት! ስምንም ቅስምንም የሚያም መስዋዕትነት! ምናልባትም ለማያባራው የአፍሪካ ችግር ጭምር ተጨማሪ አበሳ የሚያስመረቅዝ መስዋዕትነት፡፡ ሐውልት የማፍረስ ባህል ቢያንስ ከዓመታት ወዲህ አልምተናልና፤ጊዜ ሲፈቅድ፣ ሁኔታዎች ሲከለሱ፤
“ከተመታህ በኋላ መቆጣት፣ ጅብ ከሄደ አጥር ማጠር” ከሚለው ተረት ይገላግለን ይሆናል፡፡ የህንፃው መቆም “ፍየል-ፈጁን አውሬ፣ ፍየል አርደህ ያዘው” ዓይነት እንዳልሆነ ተስፋ እናረጋለን፡፡ “የስጦታ ፈረስ ጥርሱ አይታይም፡፡” ቢባልም ከፈረሱ ጋር  የመጣውን ጣጣ ሁሉ ቻል አይባልም፡፡ በእርግጥ ለዘመናት “የመተሳሰር አገልግሎት” ሲሰጥ በቆየው የአገር ወህኒ ቤት ላይ የቆመ ህንፃ መሆኑ፣ የወቅቱ ስብሰባ ተናጋሪ Farewell To Prison (ዓለም በቃኝ ደህና ሰንብት) እንዳሉት ብቻ ነው ባይባልም፤ የአፍሪካን ህንፃ በእሥር ቤቱ ላይ መሥራት ትልቅ ፍሬ ያለው እርምጃ የሚሆነው የህዝቦች ሥቃይ ሲያከትም ነው! የመከራውን ሥር መንቀል እንጂ በላዩ ላይ ረጅም ጣራ ያለው ህንፃ ማቆም፤ የመከራውን አጀንዳ የማያነሳ የመሰብሰቢያ ቦታ ከመፍጠር የበለጠ ፋይዳ አይኖረውም፡፡ በስብሰባው በአፅንዖት እንደተነገረው፤ አጋሮቻችን የተባሉት  ቻይና፣ ህንድ፣ ደቡብ ኮርያ እና አሜሪካ ለአፍሪካ ህብረትም ሆነ ለየአገሩ በነብስ-ወከፍ ምኑ ናቸው? ሲባል፤ “ከረጅም ጋር ሲሄድ የዋለ አጭር፣ ሲያቃስት አደረ!“ እንዳያሰኝ ያሰጋል፡፡ ከዚህም ይሰውረን!!

  የእውቁ ፖለቲከኛና ሃኪም ፕ/ር አስራት ወልደስ 20ኛ የሙት አመት፣ ፓርቲዎች፣ የአዲስ አበባ ነዋሪዎችና ጥሪ የተደረገላቸው እንግዶች በተገኙበት ነገ ከ8 ሰአት ጀምሮ በመኢአድ ጽ/ቤት  ይዘከራል፡፡
ባለፈው ማክሰኞ በፕ/ር አስራት የመቃብር ስፍራ ማለትም በአዲስ አበባ መንበረ ፀባኦት ቅድስት ስላሴ ካቴድራል በሶስት የፖለቲካ ድርጅቶች የጉንጉን አበባ የማስቀመጥ የመታሰቢያ መርሃ ግብር የተከናወነ ሲሆን በመርሃ ግብሩ ላይ የአማራ ብሔራዊ ንቅናቄ (አብን)፣ የመላ ኢትዮጵያውያን አንድነት ድርጅት (መኢአድ) እና የመላ አማራ ህዝብ ድርጅት (መዐህድ) አመራሮችና አባላት መገኘታቸውም ታውቋል፡፡
በነገው እለትም የዚሁ መርሃ ግብር ቀጣይ የሆነና መላው የአዲስ አበባ ህዝብ የተጋበዘበት የመታሰቢያ መርሃ ግብር የሚካሄድ ሲሆን ፕ/ር አስራትን የሚያወሱ የኪነጥበብ ስራዎች ለታዳሚያን እንደሚቀርቡና የሻማ ማብራት ስነስርአት እንደሚደረግ  የመኢአድ  ም/ፕሬዚዳንት አቶ ሙሉጌታ አማረ ለአዲስ አድማስ ገልጸዋል፡፡ ፕ/ር አስራት ወልደየስ በአማራ ህዝብ ላይ የሚደርስበትን ግፍና በደል ለመታገል የመላ አማራ ህዝብ ድርጅትን መመሥረታቸው አይዘነጋም፡፡ በወቅቱ በፖለቲካ ልዩነት ምክንያት በእስር ላይ ሳሉ ባደረባቸው ህመም ህይወታቸው ማለፉም ይታወሳል፡፡


                 አዲስ አድማስ ጋዜጣ ቅዳሜ ግንቦት 3 ቀን 2011 ዓ.ም ባወጣው ዕትሙ፣ “የልብ ማዕከሉ ይፈተሽ” በሚል ርዕስ ስር ያቀረበው ፅሑፍ፤ ለአገርና ለወገን ከፍተኛ አስተዋፅኦ እያደረገ የሚገኘውን የልብ ህክምና ማዕከሉን ስራና ተግባር የሚያጎድፍ፣ እውነታን የማይገልጽና ማስረጃ የሌለው ተራ ወቀሳ ነው፡፡ በጋዜጣው ላይ በዶ/ር በላይ አበጋዝ ተተክተው የተቀመጡት ከሙያው ጋር ግንኙነት የሌላቸው “…የሂሳብ ሰራተኛ፣ የቦርድ ዋና ሰብሳቢ፣ የማዕከሉ ዋና አስተዳደርና የሰው ኃይል ኃላፊ እንዲሁም የፋይናንስ ኃላፊ ሆነው እየሰሩ ይገኛሉ፡፡
ይህን ሁሉ ኃላፊነት ጠቅልለው መያዛቸው የልብ ማዕከሉ ከእርሳቸው ውጪ ኃላፊና ለምን ብሎ ጠያቁ እንዳይኖረው እያደረገ ሲሆን ማዕከሉን ለዝርፊያና ለብክነት አጋልጦታል” በማለት የተጠቀሰው ሐሰት ነው፡፡ ማዕከሉ በፅሁፍ እንደተገለፀው ሳይሆን የራሱ ሜዲካል ዳይሬክተር፣ የሂሳብ ባለሙያ፣ የፋይናንስ ኃላፊና ሥራ አስኪያጅ ያለው ነው፡፡ አወቃቀሩም ቢሆን ህግንና ደንብን የተከተለ፣ ግልፅ አሰራር ያለው ነው፡፡ ይሁን እንጂ ጋዜጣው የፀሐፊውን የአንድ ወገን መሰረተ ቢስ ፅሑፍ ተቀብሎ፣ ከማዕከሉ በኩል ያለውን እውነታ ሳያካትት፣ ከፍተኛ የስም ማጥፋት ዘመቻ ከፍቶብናል፡፡
ያለ በቂ ምክንያት ልምድ ያላቸው ሰራተኞች በኃላፊው ተሰናብተዋል የተባለውም፣ ማን እንደተሰናበተና ለምን እንደተሰናበተ ሳይገልጽ፣ በደፈናው የቀረበ መሰረተ ቢስ ውንጀላ ነው፡፡
ሰላሃዲን ከሊፋ
የበኢ.ል.ሕ.ሕ.መ ቦርድ ሰብሳቢ
ማህተምና ፊርማ አለው

Saturday, 11 May 2019 14:58

የሙሴ ጭንቀቱ

የሙሴ ጭንቀቱ


             ህዝበ እስራኤልን ነፃ እንዲያወጣ እግዜር ሲመርጠው
የፈርኦን ክንድ አይደለም ሙሴን ያስጨነቀው፤
እንቢ ይላል ብሎ ህዝቡን ነው የፈራው፡፡
በጨለማ ሰርቶ በቀን ለሚተኛ
ብርሃን ፅልመት ነው የፍርሃት መገኛ፤
በመጨቆን ህይወት መብቱን ለማያውቀው
ምዕራብ ተቀምጦ ምስራቅ ለሚመስለው
ወደ ምስራቅ መሄድ፣ ወደ ምዕራብ ነው፤
ውሸት እንጂ እውነት፣ እውነቱ ውሸት ነው፡፡
ይህ ነው እውነታቸው፣ ይህ ነው የነሱ እምነት፤
ስለዚህ ከፈርኦን ዛቻ ከፈርኦን ጉልበት
ያለ እምነት ተስፋ፣ ያለ እውነት ድፍረት
ትጥቅን ያስፈታል
ጉልበትን ያዝላል፤
ይህ ነው ምክንያቱ የሙሴ ፍርሃቱ፡፡
ዛሬም በዚች ምድር እስራኤል ተማርኳል
ነፃነትን ረስቶ ባርነትን ለምዷል፤
ከነዓን ሳይደርሱ ብዙዎች ሞተዋል
በጀግንነት ወኔ ፍርሃት ተወልዷል፤
በማጣት ተፋቅሮ፣ በማግኘት ተጋድሏል፡፡
ሙሴም፤
በእምነቱ ተስፋ አጥቶ፣ እውነትን ፈርቷታል
በበትሩ እራሱን አሻግሮ አሮንን ይለካል፡፡
ህዝቡም፤
እሺ ብሎ ባይከተለው
የህይወት ሐቅ አለው
ምክንያቱም፤
ዘመንን ላላየ ለፈርኦን አምላክ ለነበረ ሲምል
ታፍኖ ለቆየ ንፁህ አየር መተንፈስ እጅጉን ይጨንቃል፡፡
(ባንተ ደሳለኝ)

 የኢትዮጵያ መጽሐፍ ቅዱስ ማህበር፤ ኢትዮጵያ አሁን ያለችበትን ተጨባጭ ሁኔታ ግምት ውስጥ በማስገባት “ሠላምና እርቅን በማስፈን የአብያተ ክርስቲያናት ሚና” በሚል ርዕስ የምክክር ጉባኤ ማዘጋጀቱን አስታወቀ፡፡
ግንቦት 10 ቀን 2011 ዓ.ም ከጠዋቱ 2፡30 ጀምሮ በአፍሪካ ህብረት ዋና ጽ/ቤት የመሰብሰቢያ አዳራሽ በሚከናወነው በዚህ ጉባኤ ላይ የመንግስት ባለስልጣናት፣ የሃይማኖት መሪዎችና ከመላው ኢትዮጵያ የተውጣጡ የማህበረሰብ ክፍሎች፣ እንዲሁም መንግስታዊ ያልሆኑ ተቋማት መሪዎች የሚሳተፉ ሲሆን ጥናታዊ ጽሑፎች ቀርበው ውይይት ይደረግባቸዋል ተብሏል፡፡
በዚህ መሰረት፤ “በሠላምና እርቅ ተግባር ላይ የሀይማኖት ተቋማት ሚና” በሚል ዶ/ር በድሉ ዋቅጅራ፣ “ትውልድን በሰላምና በእርቅ የማሳተፍ ተግባር” በሚል ወ/ሮ ሰላማዊት ቸርነት እንዲሁም “የዘረኝነት ገጽታ በማህበረሰብ ዕድገትና በሀገር ሰላም ላይ ያስከተለው ተፅዕኖ” በሚል አቡነጴጥሮስ ጥናታዊ ጽሑፎች የሚያቀርቡ ሲሆን የመፍትሔ አቅጣጫዎችና እቅዶችን በመንደፍ ጉባኤው እንደሚጠናቀቅ ለማወቅ ተችሏል፡፡


         የትራፊክ አደጋ በመላው አለም እያደረሰ ያለው ጥፋት እየከፋ መሆኑንና በአለማችን በየአመቱ 1.35 ሚሊዮን ሰዎች በመኪና አደጋ ሰበብ ለሞት እንደሚዳረጉ ተመድ አስታውቋል፡፡
ካለፈው ሰኞ ጀምሮ በመከበር ላይ የሚገኘውን አለማቀፍ የመንገድ ደህንነት ሳምንት አስመልክቶ ተመድ ባወጣው መግለጫ እንዳለው፣ በመኪና የሚከሰት የመቁሰል አደጋ በአለም አቀፍ ደረጃ ከ5 እስከ 29 አመት የእድሜ ክልል ውስጥ የሚኖሩ ሰዎችን ለሞት በመዳረግ ቀዳሚነቱን ይዟል፡፡
አነስተኛ ገቢ ባላቸው አገራት ለትራፊክ አደጋ የመጋለጥ እድል ከፍተኛ ገቢ ካላቸው አገራት ጋር ሲነጻጸር በሶስት እጥፍ እንደሚበልጥ የጠቆመው መግለጫው፣ በአለማችን ከፍተኛው የትራፊክ አደጋ ስጋት ያለው በአፍሪካ መሆኑንና አውሮፓ አነስተኛ የትራፊክ አደጋ ስጋት እንዳለባት አመልክቷል፡፡
በመላው አለም በትራፊክ አደጋ በየአመቱ ለሞት ከሚዳረጉት መካከል እግረኞችና የብስክሌት አሽከርካሪዎች 26 በመቶውን ሲይዙ፣ የሞተር ብስክሌት አሽከርካሪዎችና የመኪና ተሳፋሪዎች ደግሞ 28 በመቶ ድርሻ እንዳላቸው መግለጫው አስታውቋል፡፡

የአልኮል ተጠቃሚነት በ27 አመታት 70 በመቶ ጨምሯል

            የአልኮል ተጠቃሚነት በአለማቀፍ ደረጃ ከፍተኛ ጭማሪ እያሳየ እንደሚገኝና ባለፉት 27 አመታት ጊዜ ውስጥ የአልኮል ተጠቃሚነት በ70 በመቶ ያህል መጨመሩን አንድ አለማቀፍ ጥናት አመለከተ፡፡
አንድ የጀርመን ተቋም በአለማችን 189 አገራት ላይ የሰራውን ጥናት ጠቅሶ ዘ ጋርዲያን እንደዘገበው፣ በፈረንጆች አመት 2017 ብቻ በመላው አለም 35 ሺህ 676 ቢሊዮን ሊትር አልኮል ተጠጥቷል፡፡ ባለፉት 27 አመታት የአልኮል ተጠቃሚነት በከፍተኛ ሁኔታ የጨመረው በእስያ አገራት እንደሆነ የጠቆመው ጥናቱ፤ አነስተኛ አልኮል የሚጠቀሙት ደግሞ አውሮፓውያን መሆናቸውን አመልክቷል፡፡
የአልኮል መጠጥ ተጠቃሚነት በመላው አለም በርካታ ሰዎችን ለተለያዩ የጤና ችግሮች በመዳረግ በቀዳሚነት ከሚጠቀሱ ምክንያቶች አንዱ መሆኑንና ከ200 በላይ በሽታዎችን ሊያስከትል እንደሚችል ያመለከተው ዘገባው፤  የአለም የጤና ድርጅት በበኩሉ በፈረንጆች አመት 2016 ብቻ ከ3 ሚሊዮን በላይ ሰዎች አልኮል አብዝተው በመጠጣታቸው ሳቢያ ለሞት እንደተዳረጉ ማስታወቁን አስታውሷል፡፡
የአልኮል ተጠቃሚነት በተለይ በወጣቶች ዘንድ እየተስፋፋ እንደሚገኝና በመጪዎቹ አስር አመታት ጊዜ ውስጥ ከአለማችን ወጣቶች መካከል ግማሹ አልኮል ጠጪዎች ይሆናሉ ተብሎ እንደሚገመትም ጥናቱ አክሎ ገልጧል፡፡

 90 በመቶ የጋና የዩኒቨርሲቲ ተማሪዎች ፈተና አላለፉም

              በአገረ ጀርመን ከ6 ሚሊዮን በላይ የሚሆኑ ሰዎች በአገሪቱ ብሄራዊ ቋንቋ ማንበብና መጻፍ እንደማይችሉ ዴች ዌሌ ዘግቧል፡፡
ባለፈው ማክሰኞ ይፋ የተደረገውን አገር አቀፍ የትምህርት ሁኔታ ጥናት ጠቅሶ ዘገባው እንዳለው፣ በአገሪቱ የሚኖሩ 6.2 ሚሊዮን ሰዎች ጀርመንኛን በአግባቡ ማንበብና መጻፍ እንደማይችሉ፣ አንድ አረፍተ ነገር ለመመስረት በእጅጉ እንደሚቸገሩ ለማረጋገጥ ተችሏል፡፡ በጀርመንኛ ቋንቋ ማንበብና መጻፍ ከማይችሉት ከእነዚህ ሰዎች መካከል 47.4 በመቶ የሚሆኑት ስደተኞችና የሌሎች አገራት ዜጎች መሆናቸውን የጠቆመው ዘገባው፤ በጀርመንኛ አፋቸውን ከፈቱት መካከልም 7.3 በመቶ ያህሉ የማንበብና የመጻፍ ችግር እንዳለባቸው አመልክቷል፡፡
በተያያዘ ዜና ደግሞ፣ በጋና የዩኒቨርሲቲ የሚማሩ 90 በመቶ የህግ ተማሪዎች በፈተና መውደቃቸው አነጋጋሪ ሆኖ መሰንበቱን ቢቢሲ ዘግቧል፡፡ የአገሪቱ የከፍተኛ ትምህርት ፈተና ኮሚቴ ያወጣውን መረጃ ጠቅሶ ዘገባው እንዳለው፤ ይህን ያህል መጠን ያለው ተማሪ መውደቁ ያበሳጫቸው አንዳንድ የዩኒቨርሲቲ መምህራን ስራቸውን ለማቋረጥ እንደወሰኑ ማስታወቃቸውን አመልክቷል፡፡


             ፕሬዚዳንት አልበሽርን ከስልጣን አውርዶ መንበሩን የተቆናጠጠው ጊዜያዊ ወታደራዊ መንግስት ስልጣኑን ለሲቪል መንግስት የሚያስረክብበትን ጊዜ ካላፋጠነ በመላው ሱዳን አዲስ የተቃውሞ ሰልፍ እንደሚጠሩ የአገሪቱ የተቃውሞ መሪዎች ማስጠንቀቃቸው ተዘግቧል፡፡
አጃንስ ፍራንስ ፕሬስ እንደዘገበው፤ ወታደራዊ መንግስቱ በአፋጣኝ ስልጣኑን የማያስረክብ ከሆነ አገሪቱን ወደ ከፋ እልቂት ሊያስገባ የሚችል ቀውስ እንደሚፈጠር ከተቃውሞው መሪዎች አንዱ የሆነው ካሊድ ኦማር ዮሴፍ ባለፈው ረቡዕ አስታውቋል፡፡
ተቃውሞውን ያስተባበረው ዲክላሬሽን ኦፍ ፍሪደም ኤንድ ቼንጅ ፎርስስ የተባለው ቡድን መሪ የሆኑት ማዳኒ አባስ ማዳኒ በበኩላቸው ካርቱም ውስጥ በሰጡት ጋዜጣዊ መግለጫ፤ በመላ ሱዳን ወታደራዊውን መንግስት የሚቃወም እጅግ ከፍተኛ ተቃውሞ ለማድረግ ዝግጅታቸውን ማጠናቀቃቸውን በመግለጽ፣ ወታደሩ በአፋጣኝ ምላሽ እንዲሰጥ አስጠንቅቀዋል፡፡  
ስልጣኑን የያዘው የሱዳን ወታደራዊ የሽግግር ምክር ቤት፣ ምርጫ ከመደረጉ በፊት የሲቪል ወታደራዊ ጥምረት ምክር ቤት ለማቋቋም ከተቃዋሚዎች ጋር ስምምነት ላይ በደረሰው መሰረት፣ አዲስ ህገ መንግስት በማርቀቅ ላይ እንደሚገኝ የጠቆመው ዘገባው፤ ያም ሆኖ ግን ወታደሩ ስልጣኑን ለማራዘም እየተጋ ነው በሚል ተቃውሞው ተባብሶ መቀጠሉን አመልክቷል፡፡
ለሶስት አስርት አመታት ያህል አገሪቱን የገዙትን ኦማር አልበሽርን በአደባባይ ተቃውሞ ከስልጣን ያወረዱት የሱዳን ተቃዋሚዎች፣ ወታደራዊው መንግስት ስልጣኑን ለሲቪሉ እስካላስረከበ ድረስ እረፍት የለንም በሚል ጽኑ አቋም፣ የአገሪቱን ጎዳናዎች በተቃውሞ ማጥለቅለቃቸውን እንደቀጠሉ ዘገባው ጠቁሟል፡፡ የአገሪቱን መንገዶችና የባቡር መስመሮች በመዝጋት የትራንስፖርት እንቅስቃሴውን ገድበው የሚገኙት የሱዳን ተቃዋሚዎች፣ በወታደራዊው መንግስት ላይ ሊከፍቱት ያሰቡት አዲስ የተጠናከረ ተቃውሞ ምን አይነት እንቅስቃሴዎችን እንደሚያካትትና መቼ እንደሚጀመር በግልጽ አለማስታወቃቸውንም ዘገባው አክሎ ገልጧል፡፡

 • ፕሬዚዳንታዊ ሥርአት አገርን አንድ ለማድረግ ይጠቅማል የሚል እምነት አለን
            • ትልቁ ዓላማችን፣ ህዝቡ የሚተማመንበት አገር አድን ፓርቲ መፍጠር ነው
            • ቀዳሚ ትኩረታችን ምርጫ ሳይሆን የአገሪቱ ሠላምና አንድነት ነው


              ከስምንት ወራት ያህል ምክክር እና ውይይት ሲደረግበት የነበረውና ዜግነትን የፖለቲካ መሠባሰቢያው እንዲሁም ማህበራዊ ፍትህን ርዕዮተ አለሙ አድርጐ የተመሠረተው አዲሱ ፓርቲ እነማን ተካተቱበት? ምን የምስረታ ሂደት አሳለፉ? አደረጃጀቱ ምን ይመስላል? ለሀገሪቱ ፖለቲካ ምን አዲስ ባህል ይዞ መጣ? የፓርቲው ራዕይና ዓላማው ምንድን ነው? በሚሉና ተያያዥ ጉዳዮች ዙሪያ የፓርቲው አደራጅ አባል የሆኑት የቀድሞው የሠማያዊ ፓርቲ ሊቀመንበር አቶ የሺዋስ አሰፋ ከአዲስ አድማስ ጋዜጠኛ አለማየሁ አንበሴ ጋር ተከታዩን ቃለ ምልልስ አድርገዋል፡፡
ይህን ሀገር አቀፍ ውህድ ፓርቲ ለማደራጀት የታለፈበት መንገድ ምን ይመስላል?
አዲሱን ሀገራዊ ሃይል ለመፍጠር በርካታ ውጣ ውረዶች አልፈናል፡፡ በጣም ከባድ ፈተና ነው ያሳለፍነው፡፡ የለውጥ ጭላንጭሉ ከመጣ በኋላ ትግሉ የሚቀጥልበትን አዲስ መንገድ መፈለግ ነበረብን፡፡ ቀደም ሲል መግለጫ ማውጣት፣ መጋፈጥ፣ መታገል፣ መታሰርና መሞትም የሚጠይቅ የነፃነት ትግል ነበር የሚካሄደው፡፡ አሁን  በዚህ የለውጥ ጭላንጭል ውስጥ ግን፣ የጥያቄዎች ሁሉ ቁንጮ የሆነው የኢትዮጵያ ህዝብ በመረጠው ይተዳደር የሚለው ነው፡፡ ይሄን ተግባራዊ ለማድረግ ደግሞ በሰው ሃይል፣ በሃሳብ፣ በፋይናንስ --- በሁሉ ነገር የተደራጀና በትክክልም የኢትዮጵያን ችግር ሊሸከም የሚችል፤ ህዝብ ተስፋ የሚጥልበትና እንደ አማራጭ የሚታይ የፖለቲካ ድርጅት ማቋቋም፣ ወቅቱ የሚጠይቀው ወሳኝ ጉዳይ መሆኑን በማመን ነበር የተንቀሳቀስነው፡፡ ከዚህ የደረስነው ሁላችንም የራሳችንን ህጋዊ ህልውና አፍርሰን፣ ሌሎችም ወደ ስብስቡ እንዲመጡ አግባብተን ነው፡፡ በርካታ ፓርቲዎች ወደ ውህደቱ እንዲመጡ  አነጋግረናል፡፡ ጥሩ ምላሽ የተገኘውና ራስን ወደ ማክሰም የገቡት ስምንት ያህል የፖለቲካ ፓርቲዎችና ንቅናቄዎች ናቸው፡፡
እስካሁን ባለፍንበት ሂደት በዋናነት፣ ማህበራዊ ፍትህን መሠረት ያደረጉ ፖሊሲዎችን የማዘጋጀት ስራ ሠርተናል፡፡ የትምህርት፣ የጤና፣ የኢኮኖሚ የመሳሰሉት ፖሊሲዎች ተዘጋጅተዋል፡፡ በፕ/ር በፍቃዱ ደግፌ የሚመራ የምሁራን ቡድን ተቋቁሞ ጥሩ ፖሊሲ አዘጋጅቶልናል፡፡
የዚህ ፓርቲ ትልቁ አካል ወረዳ ላይ ያለው አደረጃጀት ነው፡፡ ስለዚህ ውህደቱን የጀመርነው ከወረዳዎች ነው፡፡ የሁሉም ፓርቲዎች አባላትና ሌሎች በፓርቲ ያልታቀፉ ግለሰቦች በወረዳዎች ደረጃ እንዲዋሃዱ የማድረግ ስራ ሠርተናል፡፡
የወረዳ አደረጃጀቱ ምን አይነት ቅርፅ ነው ያለው?
በሂደቱ የተሳተፍን ፓርቲዎች አባላት፣ የፓርቲው አባል መሆን የፈለጉ ግለሰቦች በሙሉ በአንድ ጉባኤ ተሰበሰብን፤ የሁለታችንም ጉባኤ ሆኖ አንድ የወረዳ አደረጃጀት ፈጠርን ማለት ነው፡፡ ለምሣሌ ግንቦት 7 ብቻ አባላት ባሉት ወረዳ፣ የሁላችንም የአዲስ የተመሰረተው እንዲሆኑ ተደርጓል ማለት ነው፡፡ በሙሉ አቅማችን ተንቀሳቅሰን የወረዳ ጉባኤ ያደረግነው በመላ ሀገሪቱ በሚገኙ 312 ያህል ወረዳዎች ይሁን እንጂ በሌሎች ወረዳዎችም መደበኛ አባላትን አደራጅተናል፡፡ ቀጥሎ ያደረግነው ነገር ከእነዚህ ወረዳዎች 350 ያህል የፓርቲ ካድሬዎችን መልምለን፣ በአዲስ አበባ ሰሜን ሆቴል፣ በፓርቲው አላማና ግብ እንዲሁም ደንብና ፕሮግራም ላይ ስልጠና ሰጥተናል:: እነዚህ ምልምል ሠልጣኞች ደግሞ በመላ ሀገሪቱ ተንቀሳቅሰው፣ የሠለጠኑትን ለአባላት አሰልጥነዋል፡፡ በዚህ መሠረትም፣ በየወረዳዎቹ ጉባኤ ተዘርግቶ፣ ጉባኤው የመረጣቸው ናቸው፣ አሁን በዚህኛው የፓርቲው መስራች ጉባኤ፣ አባል ሆነው የተሳተፉ ግለሰቦች የተገኙት፡፡
እኔ በበኩሌ፣ እስካሁን ካለፍኩበት የፖለቲካ ሕይወት (ከቅንጅትም አንድነትም ሠማያዊም) በእጅጉ የተለየ ልምድ ያገኘሁበት ሂደት ነው፡፡ አሁን እንዳለፍንበት የመሰለ የፓርቲ አመሠራረት ተከናውኖ አያውቅም፡፡ በዚያው ልክ እንደዚህ ተስማምተን የተዋሃድንበት ጊዜም የለም፡፡ በሙሉ ቁርጠኝነትና በንፁህ ልብ፣ ከሁሉም ጋር በመግባባት ነው የሠራነው፡፡ ጥሩ አማራጭ ሆነን እንወጣለን ብለን እናስባለን፡፡
በዚህ ውህደት ውስጥ ከግለሰቦች በተጨማሪ የትኞቹ ፓርቲዎች ናቸው የተሳተፉት?
ግንባር ቀደም ሆኖ የመክሰም እርምጃ የወሰደው ሰማያዊ ፓርቲ ነው፡፡ በዚህ እኔም ሆንኩ የፓርቲው አባላት በእጅጉ እንኮራለን:: ትልቅ ውሣኔ ነው አባላቱ የወሰኑት:: የሚገርመው ይሄን ፓርቲ አደራጅተው፣ በአመራር ውስጥ የነበሩ፣ ነገር ግን በወረዳ በተካሄደው ምርጫ ሳይመረጡ የቀሩ በርካታ የቀድሞ አመራሮቻችን፣ ሁኔታውን በደስታ ነው የተቀበሉት፡፡ ሌላው አርበኞች ግንቦት 7፣ የጋምቤላ ህዝባዊ ንቅናቄ፣ ኢዴፓ፣ መኢዴፓ፣ አትፓ (አዲስ ትውልድ ፓርቲ)፣ የቀድሞ አንድነት አባላትና አቶ ግርማ ሰይፉ፣ አንዷለም አራጌ ያሉበት ጠንካራ ስብስብም አለ:: የመኢአድ የቀድሞ አመራሮች ያሉበት ወደ 40 ወረዳ ያህል አደራጅተው፣ የዚህ ውህድ ፓርቲ አካል ሆነዋል፡፡
በጣም ግዙፍ አደረጃጀት ነው የተፈጠረው፤ በእያንዳንዱ ወረዳ በአማካይ ከ1ሺህ በላይ አባላት አሉን፡፡ ከ312 ወረዳዎች ሶስት ሶስት ሴቶች ማሳተፍ አለባቸው፡፡ ተጨማሪ አንድ እንዲሁም አምስት የጉባኤ ተወካይ ማድረግ ከፈለጉ አካል ጉዳተኞችን ማሳተፍ አለባቸው፡፡ ስለዚህ ፓርቲው ለሴቶችና በተለይ በኢትዮጵያ ፖለቲካ ውስጥ እምብዛም ቦታ ሳይሰጣቸው የምናያቸውን አካል ጉዳተኞችን በእጅጉ ታሳቢ ያደረገ ነው፡፡ ከትግራይ እስከ ሶማሌ፣ ከጋምቤላ እስከ ምስራቅ የሀገሪቱ ጫፍ ተወካዮች ያሉት ፓርቲ ነው፡፡
ለኛ አሁን ከምንም በላይ የምትቀድመው ኢትዮጵያ ነች፤ ምርጫ ማሸነፍ ቀጥሎ የሚመጣ ነው፡፡ አረና ትግራይ በዚህ ውህደት ውስጥ እንዲካተቱ እየተነጋገርን ነው፡፡ ትልቁ አላማችን፣ ህዝቡ፣ ሀገር አድን ፓርቲ አግኝቻለሁ ብሎ የሚተማመንበትን ምህዳር መፍጠር ነው፡፡ ለዚህም በቅርቡ ከአፋር፣ ከሶማሌና ከሌሎች አካባቢ ፓርቲዎችም ጋር እየተነጋገርን ነው:: እስከዚህ አመት ማጠናቀቂያ ድረስ ፓርቲው በ547 የምርጫ ወረዳዎች የራሱ አባላትና አደረጃጀት እንዲኖረው ይደረጋል፡፡ አሁንም በዚህ ፓርቲ ውስጥ ለመግባት የተዘጋ በር የለም::
የኛ ዋናው መሠረታዊ አላማ አንደኛ፤ አደረጃጀቱ ህዝባዊ መሆን አለበት፣ ሁለተኛ፤ ማህበራዊ ፍትህን ማስፈን አለበት የሚል ነው:: ይህን አላማ ይዘን አሁን በየወረዳዎቹ ጽ/ቤቶች ከፍተናል፡፡ 312 ተብሎ የተጠቀሰው የወረዳ ቁጥር በቀጣይ እየጨመረ ይሄዳል፡፡ በእነዚህ ወረዳዎች ላይ ሙሉ ጉባኤ አለ፡፡ ሁሉም ወረዳዎች የራሳቸው 15 የስራ አስፈፃሚ፣ 5 ወይም 3 የጠቅላላ ጉባኤ ተወካይ  ምክር ቤት ያላቸው ናቸው፡፡ ጠንካራ ስራ የሠራንባቸውን ነው አሁን 312 ብለን በመግለጫ የጠቀስነው እንጂ ሌሎች ወረዳዎች ላይም ይሄው አደረጃጀት ነው የተፈጠረው፡፡
ፓርቲያችሁ በምርጫ ቢያሸንፍ፣ የፓርቲው ሊቀ መንበር፣ ጠ/ሚኒስትር የመሆን እድል አለው?
በሀገሪቱ የፓርቲ ፖለቲካ ባህል ውስጥ ለውጥ አድርገንበታል የምንለው አንዱ በሊቀ መንበርነት ጉዳይ ነወ፡፡ በዚህ ፓርቲ ውስጥ ሁለት አደረጃጀቶች ናቸው ያሉት፡፡ አንዱ በቀጥታ ለመንግስት ስልጣን የሚዘጋጅ አካል ነው፡፡ ሌላኛው የፓርቲ ስራን የሚሠራ አካል ነው፡፡ ሥራ አስፈፃሚ፣ የጉባኤ ተወካይ ሆነው የተመረጡ በሙሉ የተለያዩ ሰዎች ናቸው፡፡ አሁን የወረዳ ሥራ አስፈፃሚ ኮሚቴ የሚሠራው፣ በዋናነት የፓርቲውን የፖለቲካ ስራ ነው፡፡ ለምሣሌ ለምርጫ ተወዳዳሪ የሆነን ሰው በመምረጥ ሂደት ምናልባት የፋይናንስ፣ የተቀባይነትና የተጽእኖ ፈጣሪነት ያላቸውን፣ ነገር ግን የፓርቲው አባል ያልሆኑ ሰዎችን ሊመለምል ይችላል፡፡ ለምሣሌ ዶ/ር በድሉ ዋቅጅራ ባሉበት ወረዳ ያለው የሥራ አስፈፃሚ አካል፣ እሣቸው የዚህ ፓርቲ አባል ባይሆኑ እንኳን ለፓርላማ ተወዳዳሪ አድርጐ ሊያቀርባቸው ይችላል፤ የእርሳቸው ፍቃድ ከተገኘ፡፡ በዚህ አይነት መንገድ ነው የተደራጀው፡፡ ይሄን ስራ ከአሁኑ ነው መስራት የሚጀምረው፡፡ 547 (በፓርላማው ወንበር ቁጥር) ሰዎች ተመልምለው፣ ለቀጣዩ ምርጫ ከወዲሁ ይዘጋጃሉ ማለት ነው፡፡ የፓርቲው መሪና ምክትል መሪ በዋናነት ይሄን ስራ ነው የሚሰሩት፡፡  
ሊቀ መንበርና ም/ሊቀመንበር ሌላ ነው የሚሆነው፡፡ የፓርቲው መሪና ምክትል መሪ (የማደራጀት ስራ የሚሠሩ) እንዲሁም ሊቀ መንበርና ም/ሊቀመንበር (የዕለት ተዕለት የፓርቲውን እንቅስቃሴ የሚያሳልጡ) ይመረጣሉ ማለት ነው:: ስለዚህ ፓርቲው በአንድ በኩል፣ መንግስት ለመሆን የተዘጋጀ ኃይል፣ በሌላ በኩል፣ የፓርቲ ተግባር ብቻ የሚከውን ኃይል ይኖረዋል ማለት ነው:: ፓርቲው የራሱ ተሽከርካሪ፣ ንብረት ይኖረዋል:: ይህም በቀጣይ፣ መንግስት ሲሆን በራሱ ንብረት እንዲጠቀም ያግዘዋል፡፡
የፓርቲው ሊቀ መንበር ጠ/ሚኒስትር መሆን አይችልም ማለት ነው?
አዎ! ምክንያቱም አስቀድሜ እንዳልኩት፣ ከሁሉም የምርጫ ወረዳዎች ለመንግስትነት (ለምርጫ ውድድር) የተመረጡ 547 ሰዎች ተሰብስበው መሪያቸውን ይመርጣሉ፡፡ ያ መሪ ነው የሃገሪቱ ጠ/ሚኒስትር ሊሆን የሚችለው:: ስለዚህ የፓርቲው ሊቀ መንበር፤ ጠ/ሚኒስትር አይሆንም ማለት ነው፡፡ ሊቀ መንበሩ የፓርቲውን ስራ ነው የሚሰራው፡፡ በ547 ሰዎች በመሪነት የተመረጠውን፣ ህዝብ በምርጫ ካልመረጠው ደግሞ በሌላ ይተካል ማለት ነው፡፡
የዜግነት ፖለቲካ ስትሉ ምን ማለታችሁ ነው?
የዜግነት ፖለቲካ ማለት ማንም ዜጋ፣ በዜጋነቱ ብቻ የሃገሩ ጉዳይ ይመለከተዋል ማለት ነው፡፡ አሁን ባለው ለምሳሌ አፋር ላይ ተሰብስበው በሌላ ቋንቋ የሚወሰነው ውሳኔ፣ በአፋር የሚኖረውን ዜጋ አይመለከተውም፤ ይሄ ዜግነትን የሚሽር ነው:: ቢያንስ ከሌላ ቦታ ሄዶ እዚያ የሚኖር ዜጋ፣ የማወቅ መብቱ (ውሳኔው ምን እንደሆነ) የለውም፤ ብሄሮች ናቸው በሱ ጉዳይ የሚወስኑት፡፡ ህውሓት የሚወስነውን፣ የሶማሌ ድርጅት የሚወስነውን ውሳኔ እኩል አውቀን እየተቸን ነው ወይ? ብለን ከጠየቅን፣ የዜግነት ፖለቲካ ማለት ምን እንደሆነ ይገባናል:: አሁን በኛ አደረጃጀት፣ ማንኛውም ሰው የኛን አላማ፣ አርማና የትግል ስልት የተቀበለ፣ የፈለገው ቦታ ሆኖ አባል ሊሆን ይችላል፡፡ ስለዚህ ከየትኛውም አካባቢ የዚህ ፓርቲ አባል የሆነ ሰው፣ የሃገር መሪ የመሆን እድሉ ሰፊ ነው ማለት ነው፡፡ ዋናው መስፈርቱ ዜግነት ነውና፡፡
የጎሳ ፖለቲካ በህግ ይታገድ የሚል እንቅስቃሴ እየተካሄደ ነው፡፡ በዚህ ላይ ምን አስተያየት አለዎት?
እኔ በብሄር ድርጅት ውስጥ ያሉ ሰዎችን አልፈርድባቸውም፡፡ ተገደው ነው የገቡበት፡፡ እንደ ገዥ ሃሳብ ስለሆነ ነው ዛሬ “አብን”ም ሆነ  ሌላው በዚህ አደረጃጀት የተሰለፉት፡፡ ስለዚህ ህውሓት እያለ አብን፣ ኦነግ እያለ ህውሓት፣ ህውሓት እያለ ኦነግ ሊጠፋ አይችልም:: ምክንያቱም አንዱ በአንደኛው ፍርሃት ላይ የቆመ ነው፡፡
ስለዚህ እንደ ሃገር፣ የትኛው ላይ ብንቆም ነው የሚያዋጣው ብለን ከተመካከርን፣ የብሔር ፖለቲካን መስመር ማስያዝ ይቻላል:: የትኛውም የብሔር ፖለቲካ ውስጥ ያሉ ስለ ኢትዮጵያ አይጨነቁም ማለት ተገቢ አይደለም:: ሁላችንም እንተዋወቃለን፡፡ የኢትዮጵያ ጥላቻ የላቸውም፡፡ ስለዚህ እነዚህን አካላት ገፍተን ገደል መክተት ተገቢ አይደለም፡፡ ከሁሉም ጋር መነጋገር፣ መወያየት ነው የሚያስፈልገው፡፡
የጎሳ፣ የብሔር ወይም የዘር ፖለቲካን ይቁም የሚለው እንግዲህ የማህበረሰቡ ጉዳይ ነው የሚሆነው፡፡ የትኛውም ሃገር በዚህ የፖለቲካ መስመር ያለፈለት የለም፡፡ የተባላ የተጫረሰ ተሞክሮ ነው የምናገኘው እንጂ መልካም ነገር የለውም:: ስለዚህ ይሄን ማህበረሰቡ የሚወስነው ነው የሚሆነው፡፡ እኛ ግን ብዙ ሰው ወደዚህ ነገር ባይገባ ብለን ነው የምንመክረው፡፡ ጉድጓድ ውስጥ ያለን አካል ለማውጣት እንዴት ጉድጓድ ውስጥ ይገባል፡፡ ጫፍ ላይ ቸክለህ ቆመህ ነው በገመድ መሳብ ያለብህ እንጂ አንተም ከገባህ ማን ያወጣሃል፡፡ ነገርየው ዛፍ ከሆነ በኋላ በቀላሉ መስበር ማለት ሀገር ማፍረስ ነው፡፡ ስለዚህ ቀስ በቀስ በሂደት ነው መውጫ መንገዶች መፈጠር ያለበት፡፡ ለምሳሌ የሶማሌ ክልል ገዥ ፓርቲ በቅርቡ ያሳለፈው፣ ማንኛውም ሶማሊኛ የሚችል ኢትዮጵያዊ ሊቀላቀለኝ ይችላል ያለው አንድ እርምጃ ነው፡፡ ሌሎችም በዚህ መልኩ አንድ እርምጃ ከተራመዱ፣ ወደ ሌላኛው እርምጃ በሂደት መሻገር ይቻላል፡፡ በአንድ ጊዜ ይቁም ይታገድ  ማለት ግን ግዙፍ ዛፍን መስበር ማለት ነው፡፡ ዘረኝነት በኔ እምነት ጥልቅ ጉድጓድ ነው፡፡ ስለዚህ ከዚህ ጥልቅ ጉድጓድ መውጣት የሚቻለው በጥበብ እንጂ በኃይል አይደለም፡፡ መውጫው መንገድ ልክ እንደ መወጣጫ ደረጃ ነው መሆን ያለበት፡፡  
አዲስ የመሰረታችሁት ፓርቲ በፌደራሊዝም ጉዳይ ያለው አቋም ምንድን ነው?
በፌደራል ስርአቱ ላይ ግልፅ አቋም ነው ያለን፡፡ ለኢትዮጵያ የሚያስፈልጋት ያልተማከለ አስተዳደር ነው፡፡ ፌደራላዊ ስርአት ነው የሚያስፈልጋት:: በዚህን ያህል ብዝኃነትና የህዝብ ብዛት ውስጥ አሃዳዊነት በፍፁም አያዋጣም የሚል ድምዳሜ ነው ያለን፡፡ ግን ፌደራላዊ አወቃቀሩ በመጀመሪያ የሚመልሰው አስተዳደራዊ አመቺነትን መሆን አለበት:: በቁጥር አንድ ያስቀመጥነው አስተዳደራዊ አመቺነትን ነው፤ ቀጥሎ ጂኦግራፊያዊ አቀማመጥ ነው፤ ከዚያም ባህል፣ ቋንቋ፣ የህዝብ አሰፋፈር፣ የህዝብ ስነ ልቦና የመሳሰሉ መስፈርቶችን አካትቶ መዋቀር አለበት የሚል ነው ፕሮግራማችን፡፡ ይሄን ስናስብ፣ በዋናነት ምሁራን ብዙ የደከሙበትን ጥናት መነሻ አድርገናል:: የአስተዳደር ወሰንና የማንነት ኮሚሽን ውስጥ አለሁበትና በዚያ አጋጣሚ የተጠኑ ጥናቶችን ለመመልከት እድሉ ገጥሞኛል፡፡ በብሔረሰብ ጥናት ኢንስቲትዩት እነ ዶ/ር አስፋው፣ እነ ዶ/ር ኃይሉ አርአያ የመሳሰሉ ምሁራን ለሃገራችን ምን ይበጃል ብለው በንፁህ ልቦና የለፉበትን ጥናት ለመመልከት ሞክሬያለሁ፡፡ የእያንዳንዱን ማህበረሰብ ማንነት፣ ቋንቋ፣ ባህል፣ ሃይማኖት የሚያከብር አወቃቀር መከተል የሚለው ፕሮግራማችን ነው፤ ካሸነፍንም ይሄን ተግባራዊ እናደርጋለን፡፡
ህገ መንግስቱን በተመለከተ ሃሳባችሁ ምንድነው? ምን ዓይነት መንግስታዊ ሥርዓት ነው የምትከተሉት?
ህገ መንግስቱን እያፈረሱ ከዜሮ መጀመር አስፈላጊ አይደለም፡፡ ሰብአዊ መብትን የሚመለከቱና ሌሎች ጠቃሚ ያልናቸውን እንዳሉ እንወስዳቸዋለን፤ ነገር ግን ለዚህች ሃገር የማያስፈልጉ በክፋት የተሰነቀሩ አንቀፆች የምንላቸው አሉ፣ እነሱ እንዲቀየሩ እንታገላለን:: ሥርአቱን ፕሬዚዳንታዊ ማድረግ ሌላው አላማችን ነው፡፡ ፕሬዚዳንታዊ ሥርአት ሃገርን አንድ ለማድረግ ይጠቅማል የሚል እምነት አለን:: አንድ ሰው ለፕሬዚዳንትነት ሲወዳደር ቢያንስ ሦስትና አራት ክልል ማሸነፍ አለበት፡፡ ስለዚህ ሁሉንም ያሳተፈ መንግስት ለማቆም ፕሬዚዳንታዊ ሥርአት በእጅጉ ጠቃሚ ነው፡፡ በነገራችን ላይ እነ ዶ/ር ዐቢይ፣ ለማ፣ ገዱ፣ ደመቀ ሲመጡ፤ አንድም ሰው ሃይማኖታቸውንና ብሔራቸውን ለማየት አልፈለገም፡፡ ለኢትዮጵያና ህዝቦቿ ምን ሃሳብ አላቸው? የሚለውን ነው ያየው፡፡ ይሄ ሥርአቱ ፕሬዚዳንታዊ ቢሆን ጠቃሚ እንደሆነ ያሳየናል:: ጠቅላይ ሚኒስትር ግን የፓርቲ መስመርን ተከትሎ የሚመጣ ነው፡፡ ይሄ በቂ ውክልናና ቅቡልነት አለው ለማለት ማረጋገጫ አናገኝም፡፡
የዚህ ፓርቲ ዋነኛ  ፈተናዎች የሚሆኑት ምንድን ናቸው? የለያችኋቸው ጉዳዮች አሉ?
አዎ! ዋነኛ ፈተናዎቹ ሁለት ናቸው፡፡ አንደኛው ብሔረሰብን፣ ዘርን ወይም ጐሣን ማዕከል አድርጐ የተዋቀረውና ታርጋ ላይ የተለጠፈው፣ ባንክ ላይ፣ የቀበሌ መታወቂያ ላይ፣ ሚዲያ ላይ የተለጠፈው የብሔር ታርጋ ነው፡፡ ሁለተኛው ሥራ አጥነት ነው፡፡ ኢትዮጵያ በጣም ሃብታም ናት ስንል፣ ጥሩ የሚሠራ የሰው ሃይል አላት፣ በቂ መሬት፣ ጥሩ አየርና ውሃ አላት:: እነዚህን አገናኝቶ የተትረፈረፈ ምርት ማግኘት ሲቻል፣ አሁን ግን ሰው ሁሉ የሚበላውና የሚያስበው ፖለቲካ ሆኗል፡፡ ይሄን መለወጥ ያስፈልጋል፡፡ በዚህ ሀገር፣ በንጉሡም በደርግም በወያኔም በተሠራው ፖለቲካ  የተነሳ  ህዝቡ ተጠራጣሪ፣ ፈሪና ዘረኛ እንዲሆን ተደርጓል:: ይሄ እንደ ሀገር እየሠበርን ያለ ጉዳይ ነው፡፡ ስለዚህ ሰው ከራሱ ጋር እንዲታረቅ፣ ማንንም እንዳይፈራና እንዳይጠራጠር መደረግ  አለበት፡፡ የብሔር ድርጅት መነሻው ፍርሃት ነው፡፡ እየመጡብህ ነው ከሚል ሥነልቦና ነው የሚነሳው:: ካልተደራጀን እናልቃለን የሚል ፍርሃት በህዝቡ ላይ ይለቀቃል፡፡ ከዚያ ቀጥሎ መደራጀት ብቻውን ምን ይሠራል፣ ተነስ እንታጠቅ ይላል፣ ከታጠቀ በኋላ  ምሽግ ቆፍረን እንጠብቃቸው ይባላል፡፡ ግን ጠላቱ ጭንቅላት ውስጥ ስለሆነ የተባለው ቢጠበቅ ቢጠበቅ አይመጣም፡፡ ሲጠበቅ ካልመጣ ደግሞ እኛ ለምን አንሄድም ይባላል፡፡ የትም ሀገር ብንሄድ፣ የብሔር ፅንፍ አካሄዱ ይሄው አይነት ነው፡፡ ከዚያ መጠፋፋቱ ይከተላል ማለት ነው፡፡
በርዕዮተ አለማችሁ ለእነዚህ ችግሮች መፍትሄው ምንድን ነው?    
እዚህ አገር በአንድ በኩል፤ ሁሉ የሞላላቸው፣ ቁርሣቸውን ቻይና፣ ምሣቸውን አውሮፓ የሚበሉ የናጠጡ ሃብታሞች አሉ፡፡ በሌላ በኩል ደግሞ የእለት ጉርስ አጥተው በየመንገዱ የወደቁ አሉ፡፡ የኛ ሀገር እውነታ ይሄ ነው፡፡ ስለዚህ በምንም የገበያ ሁኔታ መንግስት ከግለሰብ ጋር ገበያ ውስጥ ገብቶ ውድድር አያደርግም፤ ከገበያ ጨዋታ ይወጣል፡፡ ነገር ግን የሚደግፋቸው፣ የሚረዳቸው የማህበረሰብ ክፍሎች አሉ፡፡ መንገድ መሠረተ ልማት ይሠራል:: ዶ/ር መረራ “የሚበላው ያጣ ህዝብ መሪውን ይበላል” ይላል:: ጋሽ አንዳርጋቸው ፅጌ ደግሞ “ነገሩ እንደዚያ ብቻ አይደለም፤ የሚበላው ያጣ ህዝብ ያለውን ይበላል” ይላል፡፡ ስለዚህ ሀብት ያለው ሃብቱን፣ እውቀት ያለው እውቀቱን የማካፈል ኃላፊነት አለበት፡፡ ይሄን እናስተምራለን፤ በፖሊሲም እንሠራበታለን፡፡ የብሔረሰብ ፖለቲካን በተመለከተ ቀስ በቀስ ጉዳቱን እያስረዱ እያስተማሩ፣ ወደ ሃሳብ ፖለቲካ የሚወርድበት ሁኔታ ይኖራል፡፡ ይሄን ፓርቲ በምናደራጅበት ወቅት በሁሉም የሀገሪቱ አካባቢዎች ስንሄድ፣ ሰው የብሔር መካረሩ ስጋትና መሠላቸት እንደፈጠረበት ተረድተናል፡፡ ትክክለኛ የህዝቡ ስሜት ይሄ ነው፡፡ ስለዚህ ወደ አንድ አሰባሳቢ ነገር መሳቡ አይቀርም፡፡
አሁን የኢትዮጵያ ህዝብ ብሔርተኛ ድርጅቶችን “ምን ይዘህልን መጣህ” ብሎ መጠየቅ ጀምሯል፡፡ ትክክለኛ አካሄዱ ይሄ ነው:: እንደው ነፃ በወጣ ሀገር፣ ነፃ አውጪ ነኝ ማለት ህዝቡ ሠልችቶታል፡፡ እኔ የምመኘው፤ እኛ በሃሳብ ስንፋጅና ስንጣላ፣ ህዝቡ እንዲስቅ እንጂ እኛ ህዝቡን እያጋጨን እንድንስቅ አይደለም:: አሁን እየሆነ ያለው ግን እኛ የእነ እንትናና የእነ እንትና ተወካዮች ተጣልተን ስናበቃ፣ በአካል ተገናኝተን ስንሳሳቅ፣ ህዝቡ ይፋጃል፡፡ ይሄ ፍፁም መለወጥ አለበት፡፡ ሂላሪና ትራምፕ ሲወራረፉ የአሜሪካ ህዝብ እንደሚዝናና ሁሉ፣ እኔና ሌላው ስንወራረፍ ህዝብ እንዲባላብን ሳይሆን እንዲስቅብን ነው የምፈልገው፡፡
ቀጣዩን አገራዊ ምርጫ በተመለከተ ዕቅዳችሁ ምንድን ነው?
እኛ ቀዳሚ ትኩረታችን  ምርጫው ሳይሆን የአገሪቱ ሠላምና አንድነት ነው፡፡ ሽግግሩ ላይ ነው ዋነኛ ትኩረታችን፡፡ ሽግግሩ በጥሩ ሁኔታ ከተከናወነ፤ ምርጫ ሁላችንም የምንዝናናበት ጨዋታ ነው የሚሆነው፡፡ የምርጫ ቦርድ፣ የፍትህ ተቋማት መጠናከራቸውን ማረጋገጥ ያስፈልጋል:: የህዝብና ቤት ቆጠራ መካሄድ አለበት፡፡ በአንድ በኩል ህዝብና ቤት ቆጠራ መካሄድ የለበትም የሚሉ ፓርቲዎች፣ በሌላ በኩል ምርጫ መደረግ አለበት ሲሉ ግራ አጋቢ ነው፡፡ አንዳንድ ፓርቲዎች እኮ በራሣቸው ተመርጠው ጨርሰዋል፡፡ እንግዲህ ችግሩ የሚመጣው ፌስቡክ ላይ ያገኙት ላይክና ትክክለኛው መራጭ የሚሰጣቸው ድምጽ ሲለያይ ነው፡፡ ይህ እንዳይሆን ተቋማት በቅድምያ ይጠናከሩ፣ በአገሪቱ ላይ አስተማማኝ ሠላም ይስፈን፣ ከተቻለ ህዝብና ቤት ቆጠራ ይካሄድ፡፡ ይህ ሁሉ ተሟልቶ ምርጫ የሚደረግ ከሆነ፣ አንድ ወንበር እንኳን ብናገኝ፣ ኢትዮጵያ ሠላም ከሆነች፣ ተጨባብጠንና ተመራርቀን ለመለያየት ዝግጁ ነን፡፡  

Page 2 of 428