Administrator

Administrator


   የአድዋ ድልና ኢትዮጵያዊነት፣ ታሪክና ብሔራዊ መግባባት፣ የዘርና የብሔር ፖለቲካ በሚሉና ተያያዥ ጉዳዮች ላይ የታሪክ ምሁሩ ዶ/ር ቴዎድሮስ ኃ/ማርያም ሰፊ ትንታኔ ሰጥተውናል፡፡ የክፍፍልና ብሄር ፖለቲካ ምንጩን ይነግሩናል፡፡ ምሁሩ ከአዲስ አድማስ ጋዜጠኛ አለማየሁ አንበሴ ጋር ያደረጉት ቃለ ምልልስ እነሆ፡-

አድዋና ኢትዮጵያዊነት ምንና ምን ናቸው?
ኢትዮጵያ፤ ከአድዋ በፊት 3ሺህ ዓመታት ነፃነቷን ጠብቃ የኖረች ሃገር ናት፡፡ ነገር ግን አድዋን ልዩ የሚያደርገው፣ በ19ኛው መቶ ክፍለ ዘመን መጨረሻ ላይ አፍሪካን ለመቀራመት፣ የአውሮፓ ኢምፔሪያሊዝም አፍሪካን በእጁ ያስገባበት ወቅት ነው፡፡ ትንሽ ወደ ኋላ መለስ ብለን ብናይ ደግሞ ከአፄ ቴዎድሮስ ጀምሮ ከግብፅ፣ ከእንግሊዝ፣ ከጣሊያን ጋር በርካታ ሉአላዊነትን ያለማስደፈር ጦርነቶች የተደረጉበት ወቅት ነበር፡፡ አደዋ የእነዚህ ሁሉ ሙከራዎች መደምደሚያ ነው፡፡ ወቅቱ ኢትዮጵያ ሙሉ ለሙሉ በአውሮፓ ኢምፔሪያሊስት የተከበበችበት ነበር፡፡ አድዋ ይሄን የከበባትን ስጋት ሁሉ የናደ ነው፡፡ በአፍሪካ ውስጥ እስካሁንም የአድዋ ጦርነት ብቸኛ የነፃነት ተጋድሎ ታሪክ ነው፡፡ አድዋ የኢትዮጵያ የነፃነት አክሊል ነው፡፡ በኢትዮጵያ ህልውና እና ሉአላዊነት ውስጥ አድዋ ያለው ትርጉም ከፍተኛ ነው፡፡ ከኢትዮጵያ አልፎም በጥቁር ህዝቦችና በዓለም ላይ ለተጨቆኑ ህዝቦች ያለው ትርጉም ልዩ ነው፡፡ አድዋና ኢትዮጵያዊነት የአንድ ሳንቲም ሁለት ገፅታዎች ናቸው፡፡ አድዋ ባይኖር ዛሬ ያለው ኢትዮጵያዊነት አይኖርም ነበር፡፡
በአድዋ ድል ታሪክ ላይ የሚነሱ ውዝግቦች መነሻቸው ምንድን ነው?
የአደዋ ድል የማን ነው የሚሉ ክርክሮች ናቸው አሁን ችግር የሚፈጥሩት፡፡ እንዲህ ያሉ ክርክሮች የመጡት ደግሞ ከሁለተኛው የጣሊያን ወረራ በኋላ ነው፡፡ በተለይ የተጠናከሩት ከአብዮቱ ዘመን በኋላ፣ ያውም በኢህአዴግ ዘመነ መንግስት ነው እንጂ ስለ አድዋ ከዚያ በፊት ክርክርም ብዥታም አልነበረም። የመጡት አስተሳሰቦች ሁለት ናቸው። አንደኛው ዘውጋዊ የሆነው አስተሳሰብ ነው፡፡ ይሄ ኢትዮጵያን በአጠቃላይ የሚተረጉመው በዘውጋዊ መልክ ብቻ ነው፡፡ ሁለተኛው ደግሞ ኢትዮጵያን የሚተረጎመው ስር ነቀል አብዮታዊ በሆነ መልክ ነው፡፡ እነዚህ ሁለት ትርጓሜዎች የመጡት በአብዮቱ ጊዜ ከማርክስና ሌኒን አስተሳሰብ ጋር ተያይዘው ነው። እነዚህ ናቸው የአድዋን ትርጉም ያዛባ አስተሳሰብ ያመጡት፡፡ ደርግን ጨምሮ በሶሻሊስት አስተሳሰብ ስር የነበሩ ኃይሎች በሙሉ፣ አድዋን አስመልክቶ ያስቀምጡት የነበረው ትንታኔ፤ ከድሉ ጋር ተያይዞ መነገር ያለበት የነገስታቱ ገድል ሳይሆን የሰፊው ጭቁን ህዝብ የነፃነት ተጋድሎ ነው የሚል ነበር፡፡ የተዋጉት ነገስታቱ መኳንንቱ ብቻ ሳይሆን ሰፊው የኢትዮጵያ ህዝብ ነው፤ ስለዚህ አድዋ ይበልጥ የኢትዮጵያን ህዝብ የሚወክል እናድርገው የሚል ሀሳብ ነበር የተራመደው፡፡
በእርግጥ ይህ የመጀመሪያው አስተሳሰብ አዎንታዊ መልክ ያለው ነበር፡፡ ሌላው ቀርቶ በጣሊያን ድጋሚ ወረራ ወቅት እንኳ በጦርነቱ ኢትዮጵያውያን ይጠቀሙ የነበረው ባንዲራ ሁለት ዓይነት መልክ ያለው እንደሆነ ተደርጎ በደርግ በኩል ይቀርብ ነበር፡፡ በዋናነት በወቅቱ የነበረው ክርክር፤ ነገስታት ብቻ ለምን ይወደሳሉ፤ ሰፊው ጭቁን ህዝብስ ለምን በጉልህ ስሙ አይነሳም የሚል አዎንታዊ መልክ ያለው ሃሳብ ነው፡፡ ነገር ግን ይሄን ሃሳብ በታሪክ ሚዛን ስናስቀምጠው፣ ብዙም አያስኬድም፡፡ ምክንያቱም በየትኛውም የዓለም የጦርነት ታሪክ የሚዘገበው ጦርነቱን የመሩ የጦር አዛዦች፤ የጦርነቱ ወኪል ተደርገው ነው፡፡ የሰው ልጅ መረዳቱም በውክልና በመሆኑ፣ የጦር አዛዦችና መሪዎች ናቸው በውክልና በጉልህ የሚነሱት፡፡ ይሄ በኛ ሃገር ብቻ አይደለም፤ በሁሉም የዓለም የጦርነት ታሪክ ውስጥ ያለ ሃቅ ነው፡፡ እያንዳንዱን ተዋጊ ስም ጠርቶ የሚዘለቅ አይደለም፡፡ ሁለተኛው ለአድዋ አረዳድ ውዝግብ መነሻ የሆነው ደግሞ የዘውገኝነት መግነን ነው፡፡ የዘውገኝነት መግነን አፄ ምኒሊክን ከአማራው ጋር፣ አፄ ቴዎድሮስን ከአማራው ጋር አድርጎ በአጠቃላይ ስራቸውን የመቃወም ነገር ነው የተፈጠረው፡፡ ይሄ ከየት መጣ? ከተባለ፣ የቅኝ ገዥዎች የተከሉትን ርዕዮተ ዓለም መለስ ብሎ ማየቱ ምላሽ ይሰጠናል፡፡ በአመዛኙ ይሄ ዘውገኝነት ዝም ብሎ የመጣ ወይም በልሂቃን ምርምር የተፈጠረ አይደለም፡፡ ቅኝ ገዥዎች የተከተሉት አደገኛ አስተሳሰብ ነው፡፡ ጣሊያንና ሌሎች ቅኝ ገዥዎች የተከሉት አደገኛ ርዕዮተ ዓለም ነው፡፡ ለምሳሌ ጣሊያን የምስራቅ አፍሪካ ኮሎኒ (ቅኝ ግዛቱን) ሲያደላድል፡- ታላቋ ሶማሊያ፣ ታላቋ ትግራይ፣ ታላቋ ኦሮሚያ… እያለ ነው፡፡ እንግሊዞችም ይሄን ስልት ይከተሉ ነበር፡፡ በተወሰነ መልኩ ግብፆችም፤ ኢትዮጵያ ውስጥ ካላቸው ጥቅም በመነሳት፣ ዘውገኝነትን እንደ ርዕዮተ አለም አስፋፍተዋል፡፡ ለምሳሌ፡- ግብፆች አማራውን ከኢትዮጵያዊነት ጋር ፈርጀው ለመምታት ፍላጎት ነበራቸው፡፡ ጣሊያንም ተመሳሳይ አቋም ነበረው፡፡ ኢትዮጵያዊነትን ለመምታት የሚፈልጉ በሙሉ ጉዳዩን ከአማራው ጋር አጣብቀው ነው የሚተረጉሙት፡፡ ጎሰኛ ልሂቃን የመጡት በዚህ መንገድ ነው፡፡ ቅኝ ተገዥነት የሚናፍቃቸው፣ ተገዝተናል የሚሉ ኃይሎች፤ የአውሮፓ ቅኝ ተገዥነትን የማያውቁ ሰዎች የተፈጠሩት በዚህ መንገድ ነው፡፡ ፀረ ኢትዮጵያዊነትና የተገዥነት ስሜት በጎሰኛ ልሂቃን መቀንቀን የጀመረው፣ በጣሊያን የከፋፍለህ ግዛ አስተምህሮ ነው፡፡ በተለይ አፄ ምኒሊክን ማዕከል አድርጎ፣ አፄው ራሳቸው ቅኝ ገዥ እንደነበሩ አድርጎ ማቅረብ፣ እስከዛሬ ያሉትን ቁስሎች በሙሉ አፄ ምኒልክ ላይ ማላከክ የመጣው፣ ቅኝ ተገዥነትን በተግባር ካለማወቅ ነው፡፡ የራሳቸው ልሂቅ ላጠፋው እንኳ አፄ ምኒልክን ተጠያቂ የሚያደርጉ ልሂቃን ናቸው በዚህ መንፈስ የተፈጠሩት፡፡ አፄ ምኒልክ ካለፉ ከ100 ዓመታት በላይ ቢሆናቸውም አራት ትውልድ ያህል ዛሬም እየተወቀሱ ነው፡፡ አራት ትወልድ በሙሉ አፄ ምኒልክን እየወቀሰ፣ ኢትዮጵያዊነትን ለአማራው ሰጥቶ፣ ከኢትዮጵያዊነት በተቃራኒው እየቆመ ነው ዛሬ ላይ የደረስነው፡፡ አድዋንም ከዚህ ጋር አስተሳስረው የማጠልሸትን መንገድ ነው ሲከተሉ የኖሩት፡፡ ኢትዮጵያን የሚያስከብረውን፣ ኢትዮጵያን ከፍ የሚያደርገውን በሙሉ እግር በእግር እየተከታተሉ የሚፃረሩ ርዕዮተ ዓለሞች በመንገሳቸው የተነሳ ነው እንጂ አድዋ ለሰከንድ እንኳ ጥያቄ ውስጥ የሚገባ አልነበረም፡፡ ለምን ወራሪን ወግተን አሸነፍን? ለምን ነፃነታችንን አስከበርን? ብሎ ማልቀስ ከበታችነት ስሜት የሚመጣ ነው። ታሪክ እየተዛባ፣ ትውልድም የበታችነት ስሜት ውስጥ እንዲገባ እየተደረገ የሚቀረፁ አስተሳሰቦች በተለይ ባለፉት 27 ዓመታት የገነኑ ስለሆኑ በቀላሉ የሚስተካከሉ አይሆኑም፡፡
ዛሬ ትልቁ የልዩነት ምንጭ የሆነው የዘር፣ የጎሳ፣ የብሔር… ጉዳይ ነው፡፡ በአድዋ ጦርነት የብሄር ጉዳይ ምን ቦታ ነበረው? ከዚያ በኋላስ ባሉት አመታት…?
በአድዋ ጦርነት ጊዜ ሃገሪቱ አንድነቷ የተጠናከረ ነው፡፡ ህዝብ በወንዝ ነው እንጂ የሚለየው ጎጃሜው በጎጃሜነቱ፣ ሸዋው በሸዋነቱ፣ ሃማሴኑ በሃማሴንነቱ የሚኖረው እንጂ ብሔሩ ርዕዮተ ዓለሙ አልነበረም። በወቅቱ የሃገሬው ርዕዮተ ዓለም ሃይማኖቱ ነበር፡፡ አፄ ምኒልክ “ማርያምን አልምርህም” ነው ያሉት። ብሔርተኝነቱም ያለው ሃይማኖቱ ውስጥ ነው። “እናት ሃገሩ ሚስቱ፣ እናቱ ናት” የሚል ርዕዮተ ዓለም ነው ህዝቡ የነበረው፡፡ ምኒልክ በዚህ ርዕዮተ ዓለም ውስጥ ያለን ሃገር እየመሩ ስለነበር፣ ህዝቡን በአንድ ቃል አስተባብሮ፣ ጦርነቱን ለማሸነፍ አልከበዳቸውም፡፡ አድዋ የኢትዮጵያ አንድነት ፅኑ ማሳያ የሆነውም ለዚህ ነው፡፡
ዘርና ብሄር የልዩነት መነሻ መሆን የጀመረበት ትክክለኛ ወቅት መቼ ነው?
ችግር መፈጠር የጀመረው ከአድዋ በኋላ ነው። በተለይ የአደዋን ድል ተከትሎ፣ ወደ ሃገሪቱ የሚመላለሱ አውሮፓውያን ዘጋቢዎች ነበሩ። በተለይ በሃገሪቱ የነበረውን የአንድነት መንፈስ በወቅቱ ይታዘቡ ነበር፡፡ ከመቼውም ጊዜ በላይ ኢትዮጵያ የብሔራዊ ፍፁም አንድነቷን ያፀናችበት ወቅት ነበር፡፡ በዚህ ጉዳይ እና ጣሊያን ወይም ነጭ በመሸነፉ መላ አውሮፓ በእጅጉ ተናደው ነበር፡፡ የሃገሪቱ አንድነትም ያበሳጫቸው ነበር። በዚህ የተነሳ ኢትዮጵያን ለመከፋፈል ስልቶችን ነድፈው ይንቀሳቀሱ ነበር፡፡ ኢትዮጵያን የማያዳግም ቅጣት ለመቅጣት ያልሙ ነበር፡፡ ለዚህ ቀላል ሆኖ ያገኙት ደግሞ ሃገሪቱን በዘውግ - በጎሳ መከፋፈል ነው፡፡ ከአድዋ በኋላ ጣሊያኖች በሃገሪቱ የተለያዩ አካባቢዎች የቆንፅላ ፅ/ቤቶችን አቋቁመው ነበር፡፡ ያቋቋሙትም ለዚህ ተግባር ነበር፡፡ በቆንፅላዎቻቸው አማካይነት የህዝቡን ስነ ልቦናና አንድነት እያጠኑ፣ እየሰለሉ፣ ባላባቶቹን በድለላ እየከፋፈሉ፣ የኢትዮጵያውያንን ማህበራዊ ክፍተቶች - ሃይማኖትን ጨምሮ ጎሳ፣ ዘርን፣ መደብን ያጠኑ ነበር፡፡ ደቡብ፣ ሰሜን የሚባለውን፣ ኩሸቲክ ሰሜቲክ፤ አቢሲኒያ ኢትዮጵያ የሚባለውን ክፍፍሎች በሙሉ እያጠኑ፣ እየከፋፈሉ፣ ለ40 ዓመት መርዛቸውን ሲረጩ ነው የኖሩት፡፡ አንድ ትውልድ መርዝ ሲረጩ ኖረዋል፡፡
እንደሚታወቀው፤ በማይጨው ጦርነት ዋዜማ ላይ ትላልቆቹ ደጃዝማች፣ ራሶች ናቸው ሸፍተው ከጣሊያን ጎን የተሰለፉት፡፡ በአንድ ጊዜ ተንደው ነው ባንዳ የሆኑት፡፡ ጦርነቱ ማይጨው ላይ ሳይደረግ ነው ኢትዮጵያ የተሸነፈችው፡፡ ይሄን ያመጣው ትልቁ ነገር የጣሊያኖች የ40 ዓመት የመከፋፈል ስራ ነው፡፡ አፄ ኃይለሥላሴ ዘመናዊነትን አፋጥናለሁ በሚል ስልጣንን በከፍተኛ ሁኔታ ወደ ራሳቸው ማሰባሰባቸውና ሌሎችን የየአውራጃ ገዥዎች መብቶችን መሸርሸራቸው እንዲሁም ዘውዱን አንድ ቤተሰብ ብቻ የሚይዘው አድርገው በአዋጅ ማውጣታቸው፤ ነገ ዘውዱን አግኝቼ ሃገር እመራለሁ የሚለውን የየአካባቢው ገዥ ቅሬታ ውስጥ መክተቱ ደግሞ ታማኝ ለማጣታቸው ሌላኛው ምክንያት ነበር፡፡ አፄ ኃይለሥላሴ ዓለም ያወቃቸው ጥበበኛ ዲፕሎማት ቢሆኑም ኢትዮጵያን በወታደር ኃይል ባለማጎልበታቸው የተነሳ ሽንፈቱ እንዳጋጠመም መረዳት ይቻላል፡፡ እሳቸው የተማመኑበት ዲፕሎማሲ ሲከሽፍ፣ አስቀድመው በዲፕሎማሲ የሰሩትን ያህል ወታደራዊ አቅም በመገንባት ላይ አለመስራታቸው ዋጋ ካስከፈሉ ምክንያቶች አንዱ ነው፡፡ እሳቸው የተማመኑበት የዓለም መንግስታት ድርጅት፣ ተስማምቶ ነው ኢትዮጵያን ለጣሊያን የሸጣት፡፡ ከምንም በላይ ግን ጣሊያን በ40 ዓመት ጊዜ ውስጥ የሰራው የመከፋፈል ሴራ፤ የአፄ ኃይለ ሥላሴ ስልጣንን ወደ ራሳቸው ከማሰባሰብ ጋር ተደማምሮ፣ በሁለተኛው ጦርነት እንድንሸነፍ አድርጎናል፡፡
ወያኔም የአናሳዎች መንግስት ስለነበረ፣ ለከፋፍለህ ግዛው መርህ እንዲጠቅመው የኮረጀው የአስተዳደር መዋቅር ነው፡፡ ጣሊያን ያቀደውንና በ5 ዓመቱ ወረራ በተግባር ያዋለውን ወያኔ አጠናክሮ፣ ላለፉት 27 ዓመታት በተግባር አውሎታል፡፡ አሁን የምንከተለው የፌደራል ስርአት፤ ጣሊያን ለቅኝ ግዛት ስልት ሲጠቀምበት የነበረው አይነት ነው፡፡
የአደዋ ድል በኢትዮጵያዊያንና በሌላው ዓለም ባሉ አፍቃሬ ኢትዮጵያ ህዝቦች መካከል ያለው አተያይ እንዴት ይገለፃል?
ከኢትዮጵያ ውስጥ ለኢትዮጵያዊነት ግምት የማይሰጥ የተወሰነ አካል ለዚህ ድል ብዙም ግምት አይሰጠውም፡፡ ኢትዮጵያዊ ነን ለምንል ግን አደዋ አሁንም የአልማዝ አክሊላችን ነው፡፡ የነፃነታችን አክሊል ነው፤ እንኮራበታለን፣ ለወደፊትም ልጆቻችን እንዲኮሩበት የሚቻለውን ሁሉ እናደርጋለን፡፡ በአክራሪ ዘውገኞችና በኢትዮጵያዊነት አስተሳሰብ አራማጆችና መካከል ያለው አተያይ ነው የተራራቀው እንጂ በኢትዮጵያዊነት አስተሳሰብ አራማጆች በሌሎች ሃገራት በሚገኙ አፍቃሬ ኢትዮጵያ ህዝቦች መካከል ለአድዋ ያለው ስሜት ተመሳሳይ ነው። አትዮጵያውያን አድዋን አልካድንም፤ የካዱት በኢትዮጵያ ውስጥ ኢትዮጵያዊነት የማይሰማቸው ናቸው፡፡ አሁንም አደዋ በዓለም ላይ ለጥቁር ህዝቦችና ጭቁኖች አንፀባራቂ ድል ነው፡፡ ለየትኛውም የጭቁን ህዝቦች አደዋ የተስፋ አርማ ነው፡፡ ለኢትዮጵያዊያን ደግሞ ከምንም በላይ የህልውናችን መሰረት ነው። ማንኛውም ኢትዮጵያዊ ርዕዮተ ዓለሙ አድዋን ማዕከል ሳያደርግ ሊመሰረት አይችልም፡፡
አባቶቻችን አጥንታቸውን የከሰከሱበት፣ ደማቸውን ያፈሰሱበት፣ ለ3 ሺህ ዓመታት ጠብቀው ያቆዩትን ሃገር፤ ለአንዴና ለመጨረሻ ጊዜ ሊገድላት የመጣን ቅኝ ገዥ ኃይል ድል የመቱበት ነው፡፡ ይሄ ልንኮራበት ይገባል፡፡ ለሃገራችን ማንኛውንም መስዋዕትነት እንደምንከፍል ቋሚ ማስረጃችን ነው - አድዋ፡፡ ነገር ግን ስልጣን ይዘው፣ የኢትዮጵያን ሚዲያዎች ተቆጣጥረው የነበሩ ኃይሎች፣ አድዋን በማጥላላት ዘመቻ ላይ በግልፅ ተሰማርተው ነበር፤ እነዚህ ሰዎች ናቸው፣ በአድዋ ላይ መርዝ የረጩት፡፡ ዛሬ የኢትዮጵያን ባንዲራ ይዞ እንኳ አድዋ ድረስ ያለ ስጋት መሄድ ያልተቻለው ለዚህ ነው፡፡ ይሄ ለወደፊት ልጆቻቸው የሚሸማቀቁበት አሳፋሪ ታሪክ ነው፡፡
በታሪክ የሚያግባባን ብሔራዊ ጀግና ማጣታችን፣ ለብሔዊና አለመግባባቱ ትልቅ አስተዋፅኦ እንዳለው የሚሞግቱ አሉ፡፡ በዚህ ጉዳይ የእርስዎ አተያይ ምንድን ነው?
እኔ በተገላቢጦሽ ነው የማየው፡፡ ብሔራዊ መግባባት አለመቻላችን ነው ብሔራዊ ጀግና ለማጣታችን መሰረት የሆነው፡፡ ያለመግባባታችን ነው ጀግኖቻችንን እንድንቆጥራቸው ያስገደደን፡፡ ዛሬ ለኢትዮጵያዊነት የተዋደቁ ጀግኖቻችንን ባልዋሉበት፣ ባልሰሙበት፣ በሌሉበት አጥንት ቆጥረን፣ ዘር ሰጥተናቸው ነው ወደ የራሳችን የምንጎትተው። እገሌ የአማራ ጀግና ነው፣ እገሌ የትግሬ ጀግና ነው፣ እገሌ የኦሮሞ ጀግና ነው እያልን፣ ሰዎቹ በነበሩበት ጊዜ ያላሰቡትን ነገር ነው የምንሰጣቸው፡፡ ደጃዝማች ባልቻ አባነፍሶ አድዋ ላይ የተዋጉት የኦሮሞ ጀግና ነኝ ብለው አይደለም፤ የኢትዮጵያ ጀግና ነኝ ብለው ነው፡፡ ራስ አሉላ አባነጋ አደዋም ዶጋሊም ሲዋጉ ሃገሬ ኢትዮጵያ ወራሪ አይደፍራትም ብለው ነው፡፡ የኢትዮጵያን አፈር አትነካም ብለው ነው የተዋደቁት እንጂ የትግሬ ጀግና ነኝ ብለው አይደለም፡፡ እኛ ነን አጥንትና ደም እየቆጠርንላቸው ይሄ ትግሬ፣ ያኛው አማራ፣ ሌላው የኦሮሞ ጀግና ነው እያልን የከፋፈልናቸው፡፡ ስለዚህ በብሔራዊ ጉዳይ አለመግባባታችን ነው ሁላችንም የምንቀበለው ጀግና  ያሳጣን፡፡ በእርግጥ በየትኛውም አለም መቶ በመቶ ሃገርን ሙሉ ለሙሉ ያስማሙ ጀግኖች አይገኙም። ለምሳሌ የአሜሪካ መስራች አባቶች የሚባሉት እነ ጆርጅ ዋሽንግተን፣ ጀፈርሰን ዛሬ ጥቁሮች ቅሬታ የሚያቀርቡባቸው ናቸው፤ ይሁን እንጂ በኛ ሃገር እንዳለው ዘመንን ባልዋጀ ጥላቻ አይታወሩም፡፡ ባርነትን ይደግፋሉ ብለው ይቃወሟቸዋል፡፡ የጋራ ብሔራዊ ጀግና ማለት፣ መቶ በመቶ የሚያስማማ ነው ብሎ መጠበቅ አይቻልም፤ ነገር ግን መሰረታዊ በሆኑት ጉዳዮች፣ የታሪክ አንጓዎች ከተግባባን በቂ ነው፡፡
በታሪክ ወደኋላ እየተጓዝን ከመናቆርና ከጥላቻ እንድንወጣ መፍትሄው ምንድን ነው?
እንዲህ አብዮቱ ሁሉን ነገር ካፈነዳው በኋላ እስካሁን የሰከነ ነገር የለም፡፡ የሰከነ ትውልድ አልተፈጠረም፡፡ በደርግም በኢህአዴግም የታፈነ ትውልድ ነው የተፈጠረው፡፡ ሁለት ተከታታይ ትውልድ የታፈነና ለአንድ ቦይ ፕሮፓጋንዳ የተጋለጠ ነው፡፡ የኛ ቀጣይ ልጆች ከዚህ አፈና ይላቀቁ ይሆን የሚለውን በቀጣይ የምናይ ነው፡፡ እስከዚያው ግን ኢትዮጵያውያን ለታሪካችን ለመግባባት በመጀመሪያ አሁን ባለው የፖለቲካ ስርአታችን ልንግባባ ይገባል። ሁሉንም በእኩልነት የሚያያይዘው ከአክራሪነት የወጣ ፍትሃዊ የፖለቲካ ስርአት ሊገነባ ይገባዋል። ያ እስካልተገነባ ድረስ ስለታሪካችን ሰከን ብለን የምንነጋገርበት እድል ሊመጣ አይችልም፡፡ ስለዚህ መጀመሪያ ማስተካከል ያለብን የፖለቲካ ስርአታችንን ነው፡፡ የፖለቲካ ስርአቱን ስናስተካክል ነው በታሪክ ጉዳይ ሰከን ብለን ተነጋግረን መግባባት የምንችለው። ሁላችንንም በእኩልነት የሚያይ ስርአት ሲፈጠር፣ ምንድን ነው ብለን የጋራ ብሔራዊ ኢትዮጵያዊነትን ማስፋፋት እንችላለን፡፡ ይሄን ማድረግ አይቸግረንም። ትልቁ የፖለቲካ ነቀርሳ ከተስተካከለ፡፡ ስለዚህ የፖለቲካ ስርአቱን ከተራ የውረፋ ስርአት ማላቀቅ ወሳኝ ነው፡፡ የትግሬ ተራ ነው፣ የአማራ ተራ ነው፣ የኦሮሞ ተራ ነው፣ የሶማሌ ተራ ነው … እየተባለ መቀለጃ የማይሆን ስርአት መመስረት ግዴታችን ነው፡፡ አሁን የሰሜን ተራ አብቅቷል፤ አሁን የደቡብ ተራ ነው የሚል ልሂቅ ባለበት ሃገር ግን እንዴት አድርገን ነው በታሪክ የምንግባባው? ሃገርን የከፋፈለው የዘውግ አስተሳሰብ ነው በመጀመሪያ መፍትሄ ማግኘት ያለበት፡፡   
የፖለቲካ ሳይንስ ተመራማሪ የሆኑት ሮበርት ኢ.ላኔ፤ “መንግሥትና ሕዝብ ከሚነጣጠሉባቸው ምክንያቶች አንዱ፤ መንግሥት ለሕዝብ ጥቅም ሳይቆም ሲቀር፣ ህዝቡ መንግሥት ስለ እኔ ጉዳይ ደንታ የለውም ብሎ ሲያስብ ነው” ይላሉ፡፡
መንግሥትን ህዝብ የሚከተለው፣ የሚያጅበውና ከጐኑ የሚቆመው፣ ለኔ ጥቅም የቆመ፣ ደህንነቴን የሚጠብቅና እኔን አሳታፊ ያደርጋል ብሎ ካሰበ ብቻ ነው፡፡ አለበለዚያ በቸልተኝነት ቆሞ ያያል፤ አደጋ የተጋረጠበት መስሎ ከታየው፣ ያንን አደጋ ለማስወገድ፣ አደጋ ፈጣሪው መንግሥት የሚወድቅበትን መንገድ ያሰላስላል፡፡ መንግሥት ወዳጁ ካልሆነና በጠላት ዐይን ካየው፣ የጠላቱን ጠላት ለመወዳጀት ቀዳዳና ዕድል እስከ መፈለግ ይደርሳል፡፡
ኢትዮጵያ ውስጥ የነበሩ መንግሥታት ሁሉ ህዝብን ከጐናቸው ያሰለፉ ሳይሆን በጐናቸው ጠመንጃና ሽጉጥ የታጠቁ ስለነበሩ፣ መጨረሻቸው በክብር አልተደመደመም፡፡ አሁን በቅርቡ እንኳ የመንግሥት ቁንጮ የነበረው የወያኔ ቡድን፣ ሥልጣኑን እንደ ቀልድ የተነጠቀው፣ ለሕዝብ ዕድል ባለመስጠቱና ለሌሎች ሃሳቦች ጆሮውን ደፍኖ፣ የራሱን ዘፈን በመስማቱ ነው፡፡ “ያለ እኔ ጀግናና ብልህ የለም” ብሎ በማሰቡ፣ ዛሬ ያ ሁሉ ትዕቢት አልፎ የተነፈሰ ፊኛ ሆኗል፡፡ ታዲያ ይህ ጉዳይ ያለ ጦርነትና ዕልቂት እንዲህ ይሆናል ብሎ ማሰብ ለልቡና በእጅጉ የራቀ ነበር፡፡ እውነት ለመናገር በወያኔ የሚመራው መንግሥት፣ ስግብግብነቱን ትቶ ለጋራ ጥቅማችን ቢሰራ ኖሮ፣ ከየትኛውም ጊዜ ይልቅ የተመቻቸ አጋጣሚና ዕድል ነበረው፡፡
አሁን በወያኔ ቁንጮነት ቦታ የተተካው “ኦዴፓ” የተባለው የኦሮሞ ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ፣ ለዚህ ለውጥ ግንባር ቀደም መሪ ሆኖ፣ አፈትልኮ ሲወጣ፣ በሟቹ አቶ ተስፋዬ ጌታቸው የሚመራው የ”ኦዴፓ” (አማራ ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ) ቡድንም አብሮት ነበር፡፡ ይሁንና የአማራው ፓርቲ በብዙ የሕወሓት ሰዎች ተጠፍንጐ ስለነበር፣ በቀላሉ ጠርቶ መውጣት አልቻለም፡፡ ስለዚህም ቀደም ሲል በኦነግ ሰበብ ሲታሠርና ሲገደል የነበረውን የኦሮሞ ወጣት በማደራጀት፣ የኦሮሞ ዲሞክራሲያዊ ፓርቲ ትግሉን አጧጡፎ ከሄደ በኋላ፣ በሁለቱ ትልልቅ ብሔሮች መካከል በተፈጠረው አንድነት፤ አሮጌውን የጭቆና ቀንበር ሰብረው መውጣት ችለዋል፡፡
ታዲያ በዚህ ጊዜ ግንባር ቀደም መሪው የያኔው ኦህዴድ፣ ያሁኑ ኦዴፓ - ነው፡፡ ይህ ፓርቲ በተለይ በሁለቱ ትንታግ መሪዎች፣ ሁሉን አቀፍ ሃሳብና ንግግር፣ ከዳር እስከ ዳር ህዝቡን ነቅንቆ ከጐኑ ማሳለፍ ችሏል፡፡ ኢትዮጵያዊ የሆነ ሁሉ ዘርና ሃይማኖት ሳይለይ፣ የትኛውንም መሪ ከተቀበለበት ፍቅርና አድናቆት በተለየ ሁኔታ፣ በጊዜው የለውጡን ሃሳብ ይዘው አደባባይ የታዩትን አቶ ለማ መገርሳን በታላቅ ጭብጨባና ሆታ አጀባቸው፡፡ ህዝቡ የራሱን ብሔር ትቶ እንደ ብሔራቸው ሆነ፡፡ ሀገራችንን ወደ ቀድሞ ክብር የሚመልሱ፣ ህልም ያላቸው፣ ምናልባትም ከመለኮት የተላኩ ሰዎች መጡልን ብሎ አጨበጨበ፡፡ እስከ ዛሬ ድረስ የምንደነቅበት የአቶ አዲሱ አረጋ ድፍረት የተሞላና በጥበብ ያጌጠ ንግግር፣ የወያኔ ሥልጣን ሳይላላ፣ በየመገናኛ ብዙኃኑ ሲነበነብ ተዓምር ተባለ፡፡ በርግጥም የኢትዮጵያ ህዝብ ንግሥት እንዳገኘ ንብ፤ ወደ አንድ አቅጣጫ ተመመ፡፡ ሁላችንም ያለንን ይዘን ከኦዴፓ ጐን ተሠለፍን፡፡ የደስታ እንባ ጉንጮቻችንን አጠባቸው፡፡ ሳቃችን ከከንፈሮቻችን እንደ አዲስ ተወለዱ፤ የተስፋ እሸቶች ታቅፈን፣ ዳር እስከ ዳር እልልል አልን፡፡ በብሔር ቁርኝነት ሳይሆን በኢትዮጵያዊነት ደም ተቀላቀልን ብለን በመሪዎቻችን ኮራን፡፡
በተለይ በየአደባባዩ ላይ ያደርጓቸው የነበሩ ንግግሮችና ሃሳቦች በእጅጉ ቀልብ ሳቢ እንጂ ከፋፋይና አግላይ ስላልነበሩ፣ አንድም ሰው ስለ ብሔር አላሰበም፡፡
ስለዚህም መሠለኝ … ገጣሚ መንገሻ ክንፉ፤ “እምባም ይናገራል” በሚል መጽሐፉ ውስጥ በአንዱ ግጥም እንዲህ ያለው፡-
ነቢዩ ቢወለድ ከትግራይ ኦሮሞ
ከጉራጌ አማራ አለዚያም ከጋሞ
በጭንቃችን ጊዜ ከኛ ጋር ታድሞ
ስናለቅስ አልቅሶ፤ ስንታመም ታሞ
በይቅር ባይነት ከፈታው ህልማችን
ዘመን ካሻገረው ካደሰው ተስፋችን
በሰላም በፍቅር በአንድ ከደመረን
በአረንጊዴ ቢጫ በቀይ ካሰመረን፡፡
እኛ ከግብሩ እንጂ ከዘሩ ምን አለን፡፡
አሥር ወራት ያህል ያስቆጠረው በዶክተር ዐቢይ የሚመራው መንግሥት፤ በህዝቡ ውስጥ ያሳደረው እምነትና ፍቅር ቀላል አልነበረም፡፡ በተለይ ጠቅላይ ሚኒስትሩ በተከታታይ የወሰዷቸው ፖለቲካዊና ኢኮኖሚያዊ እርምጃዎች፣ የለውጡን ተዓማኒነት ከፍ አድርጎታል፡፡ ለውጡም የሁሉም ኢትዮጵያዊ እንደሆነ እንዲሠማን በማድረጋቸው፣ ሁላችንም ለውጡን ለማገዝ የምንችለውን ሁሉ ያደረግን ይመስለኛል፡፡ ይህ ሲሆን የለውጡ መሪዎች፣ የተሳሳቱትና ዋጋ የከፈልንበት ነገር አልነበረም ብለን አንክድም፡፡ በተለይ ከውጭ ሀገር የሚገቡ ፓርቲዎችን አቀባበል አስመልክቶና ያልተጠናና በዘፈቀደ የተሠራ የሚመስለው ልቅ አካሄድ፤ እኛንና መንግሥትን ዋጋ አስከፍሎናል፡፡ ምናልባትም ብዙ የለውጡ ደጋፊ የሚመስሉ ሰዎች፤ ለውጡን እንደ ሁለተኛ አማራጭ እንደቆጠሩት የሚያሳዩ ፍንጮችን አጢነናል፡፡ ይህንን ለማወቅ በማህበራዊ ሚዲያ የ“ቲም ለማ” ደጋፊዎች የሚመስሉ ሰዎች፣ አፈሙዛቸውን ወደ ለውጡ ደጋፊዎች አዙረው እንደነበር ልብ ማለት ብቻ ይበቃል፡፡ ከዚያ ቀጥሎ በሀገር ደረጃ ያመጣውን መሳከር ሁላችንም እናውቀዋለን፡፡ ብቻ ልብ ብለን ስናየው፣ በለውጡ ሂደት መንግሥት ላይ አንዳች ቸልተኝነትና የበዛ ትዕግስት አይተናል፡፡ ለምን እንደሆን ባይገባኝም ፖለቲካ ባለፈበት ያላለፍነው እኛ የምንጠርጥረውን ነገር፤ መንግሥትን የሚመሩ ሰዎች ለዚያውም በሀገር ደህንነት ላይ ልምድ እንዳላቸው የሚነገርላቸው መሪዎቻችን ሲሳሳቱ እናያለን፡፡ ይሁን እንጂ የዚህ ውስብስብ ሀገር ጣጣ፣ ልክ የለሽ ስለሆነ ሥራ በዝቶባቸው ይሆናል ብለን ስናልፍ ቆይተናል፡፡ ይህ ብቻ አይደለም፡፡ “ኦዴፓ” ሸክሙ ብዙ፣ ጣጣው እልፍ ነው፡፡ ሲጀምር ኦዴፓ የለውጡ ተወርዋሪ አልፎ፣ ዛሬ ግን የተከበበ ነብር ነው፡፡ ግራና ቀኙ በብዙ ችግሮች የተሞላ ነው፡፡
በተለይ ከሌሎቹ የኦሮሞ ብሔር ተኮር ፓርቲዎች ጋር ሲነፃፀር፣ በኦሮሞ ሕዝብ ዘንድ ያለው ተቀባይነት በጥርጣሬ የተሞላ ነው፡፡ ፓርቲው ሁላችንም እንደምናውቀው፤ የዛሬው በጡረታ የተሰናበተው የሕወሓት አክራሪ ቡድን ተለጣፊና መሣሪያ ስለነበር፣ በሕዝቡ ዘንድ የዛሬ የለውጥ ፊቱ ብቻ ሳይሆን የትናንት የግፍ ጠባሳው ይነበባል፡፡ “ዛሬ ተለውጠናል” ቢሉም፣ ትናንት ካድሬዎቹ ያደረሱበትን እሥራት፣ ግድያና እንግልት እያሰበ ህዝቡ ልቡን አልሰጣቸውም፡፡ አብዛኛውን የቀድሞ ካድሬዎቹን ነቅሎ ያባረረው የአቶ ለማ መገርሳ ቡድን፤ ዛሬም በተለይ ወደ ታቹ ብዙ አሰስ ገሠሥ እንዳለው፣ ወደ ገጠር ወጣ ያለ ሰው ሁሉ የሚያውቀው ነው፡፡
ኦዴፓን፤ የቀድሞ ጠባሳው ያመጣበት ጣጣ ያለመታመን ብቻ አይደለም፡፡ በሀገራዊ አመራር ላይ መቀመጡ ወዲያና ወዲህ እንዲሳቀልና ባተሌ እንዲሆን አድርጎታል፡፡ በተለይ በቀጣዩ ምርጫ ላይ ለሚኖረው ውድድር ለመዘጋጀት፣ በእጁ ላይ ከወደቀው የሰማንያ ብሔር ብሔረሰቦች ዕድልና አደራ ጋር ሥራውን አከብዶታል፡፡
እውነት ለመናገር የዶክተር ዐቢይ መንግሥት፤ ህዝባዊ ድጋፍ፣ ከኦሮሚያ ክልል ባለፈ መላው ኢትዮጵያን የሞላ ነበር፡፡ በተለይ የአማራ ብሔራዊ ንቅናቄ ህዝቡን ሳይገምሰው በፊት! ታዲያ - በዚህ መከበብ ምክንያት ትናንት ለውጡን በእጁ በማስገባት በወኔ ይወረወር የነበረው ነብር (ኦዴፓ)፤ ዛሬ ብዥታ የገጠመው ይመስላል፡፡
ለዚህ ብዥታ ደግሞ ከላይ ከጠቀስኳቸው ችግሮች ናቸው፡፡ ሌላው የቀደመውን ታሪኩን ስስነት ያዩ አክቲቪስቶችና ፓርቲዎች መሀል እየገቡ፣ ከህዝብ ጋር ያለውን ህብረት ሊነጥቁ መሞከራቸው ነው፡፡ በተለይ ቁጥራቸው የበዛ ሚዲያዎች ባሉበት ዘመን፣ የብሔር ግጭትን የሚፈጥሩ ንግግሮችንና የጥላቻ ታሪኮችን እየመዘዙ፣ ያጠበውን ልብ የሚያቆሽሹበት ስለበረከቱ ጉዞው እንቀፋት በዝቶበታል፡፡ አንዳንዴም ነገ ሊመርጠው የሚችለው የኦሮሞን ህዝብ ድጋፍ እንዳያጣ ሲል በሚወስዳቸው ወጣ ያሉ እርምጃዎች፣ የሌላውን ወገን አጋርነት እየተነጠቀ እንደሆነ እያየን ነው፡፡
ይህ ትግልና ፍልሚያ ደግሞ የአማራው ብሔራዊ ንቅናቄ (አብን) ከተመሠረተ በኋላ ይበልጥ እያሰጋና እያስፈራ መጥቷል፡፡ ትግራይ መሽገው ፍላፃቸውን የሚልኩት ሰዎች፣ የሚሠሩት ሴራ እንዳለ ሆኖ “ለኦሮሞ ህዝብና ለእኛ ብቻ” የሚል ስግብግብ ቅዠት ያላቸው ሰዎች ቅብጠት ኦዴፓን አጣብቂኝ ውስጥ እየከተተው ነው፡፡
“ለውጡ የሁላችንም የትግል ውጤት ነው” የሚለውን የለማ መገርሳን ቡድን ሃሳብ ትተው፣ “እኛ ብቻ ነን” የሚል የተንሻፈፈና መረጃ የሌለው ወሬ የሚያወሩ ጽንፈኞች፣ ለውጡን ብቻ ሳይሆን ሀገሪቱን ወደለየለት ጥፋት እንደሚመሩ ባለማወቃቸው ተስፋችንን እያጨለሙና ታሪካችንን እያጠለሹ ነው። እነዚህ “የለውጡ ጌቶች” ነን የሚሉ ሠካራሞች፤ ለውጡ በብዙ ተግዳሮትና ፈተና እንደተከበበ እንኳ ማስተዋል የተሳናቸው ናቸው፡፡ ሌላው ቀርቶ በብዙ ቢሊዮን ብሮች ኪሱ ያበጠውና ዛሬም የትግራይን ህዝብ በር ዘግቶ በሃሰት ፕሮፓጋንዳ የጠላትነት መንፈስ እየጫረ፣ ለጦርነት የሚያዘጋጀው ቡድን ጠመንጃ ታጣቂ መሆኑን ማሰብ የዘነጉ ይመስላሉ፡፡
እንግዲህ - “ኦዴፓ” የተከበበ የመሠለኝ በነዚህና መሰል ጉዳዮች ነው፡፡ ከሁሉ ይልቅ ይህንን እንድቀበል ያደረገኝ የሰሞኑ የለገጣፎ ቤት የማፍረስ ጉዳይ ነው፡፡
የሕዝብ ጥቅምንና መብት እንተወውና ለራሱ ለመንግሥትስ ቢሆን ቀደም ሲል የጠቀስኳቸው፣ ባላንጣዎችና ፈተናዎች እያሉበት የፀብና ሽንቁሮችን እድል መድፈን እንጂ ሌላ ቀዳዳ መክፈት ያስፈልገዋል? ደግሞስ በየጊዜው በገንዘብ እየተገዙ ሕዝብ መግደልና ማፈናቀል ሥራዬ ብለው የሚሠሩ ሰዎች እያሉ ሌላ በፍቃደኝነት ቦንብ የሚጥል ሠራዊት ማዘጋጀት ከአንድ ሀገር የሚመራ መንግሥት ይጠበቃል?
ያ - ብቻ አይደለም፣ ችግሮች በተፈጠሩ ጊዜ መግለጫ የሚሰጡ ሰዎች የንግግር ሥልጠናና ስልት ሊሰጣቸው አይገባም? ከአቶ አዲሱ አረጋ በቀር ለመገናኛ ብዙሀን መግለጫ የሚሰጡ የ”ኦዴፓ” አባላት ሁሉ የፓርቲውን አቋም መግለጥ የማይችሉና የጽንፈኞችን ድምፀት የሚያስተጋቡ ናቸው፡፡ እንደኔ - እንደኔ በንግግር ጊዜ ከድምፀት ጀምሮ፣ የመንግሥትን ተቀባይነትና ድጋፍ የሚያጠናክሩ እንጂ በጥላቻ እሳት ላይ የሚጥሉ መሆን የለባቸውም፡፡
ይህ በእጅጉ ሊታሰብበት የሚገባ ጉዳይ ነው። መንግሥት ለገጣፎ ላይ ስለፈፀመው ጥፋት ነገር ሺህ ነገር ስለተነገረ ደግሜ ማውራት አልፈልግም፤ ግን፣ የጊዜውን ሁኔታና ዐውድ ያልተከተለ፣ ጥበብ የጐደለውና ሀገርን በቀዳሚነት ከሚመራ ፓርቲ የሚጠበቅ አይደለም፡፡ እንደ ኦቦ ለማ መገርሳ ካለ የሰለጠነ መሪ፤ ሊወጣ የሚገባው ጭካኔም አይመስለኝም፡፡ ምክንያታዊ ቢሆን እንኳ፤ የሚከወንበት መንገድና የሚሰጠው መግለጫ ይህን የመሰለ ቀሽምና ተዐማኒነት የጐደለው መሆን የለበትም፡፡ ስለ ኦሮሞ ገበሬ መሬት ያላግባብ መነጠቅን እንደ ሰበብ እንኳ ብናይ፣ በዚህ ጉዳይ ላይ ለመጮህ ሁሉም ኢትዮጵያዊ፣ ማለትም አማራ፣ ትግሬ፣ ጉራዜና ሌሎችንም ይመለከተናል፡፡ እንደኔ እንደኔ የተፈናቀሉት የኦሮሞ አርሶ አደሮች ጉዳይ ለፕሮፓጋንዳ የምንጠቀምበት ሳይሆን፣ ዛሬም በቀጥታ የሚካሉበት መንገድ መፈጠር አለበት። የጥበቃ ሰራተኛ ሆነው የተጣትና ልጆቸውን ማስተማር የተሳናቸው ሰዎች ህይወታቸው መለወጥ አለበት፡፡ ለዚህ ደግሞ ህዝብን ካስተባበርን ይህ ጉዳይ የማይሰማው ኢትዮጵያዊ አይኖርም፡፡
ስለ ኦዴፓ ሳስብ አንድ አሜሪካዊ ፕሬዚዳንት ትዝ ይሉኛል፡፡ እኒህ ፕሬዚዳንት ዋይት ሀውስ ውስጥ ባሳለፉባቸው ዐመታት ሁሉ ፕሬዚዳንት እንደሆኑ መቀበል ያቃታቸው፣ ወይም ህልም የመሰላቸው ነበሩ፡፡ ስለዚህ ብዙ ጊዜ “ማስታወቂያ ሲያነብቡ፣ “ክቡር ፕሬዚዳንት” ሲባሉ ሌላ ሰው እና መሰላቸው ይደነግጡ እንደነበር ራሳቸው በአንደበታቸው ተናግረዋል፡፡
አሁን ኦዴፓም የዚህን ዓይነት ችግር ውስጥ ያለ ይመስላል፡፡ ምክንያቱም ሲነጋገርና ሲከራከር ወክልሉ ላይ ነው፡፡ እውነቱ ግን ያ አይደለም፡፡ የትናንቱ የሕወሓት ወንበር ዛሬ የ“ኦዴፓ” ነው፡፡ ልዩነቱ ሕወሓት በጦር ግንባር ታግሎ ወደ ሥልጣን መሪነት መጣ፡፡ ኦዴፓ ደግሞ በሰለጠነ መንገድ በፖለቲካ የበላይነት አግኝቶ በህወሓት እግር ተተካ። ስለዚህ ኦዴፓ ዛሬ የኢትዮጰየውያን መሪ ፓርቲም እንጂ የኦሮሞ ህዝብ ፓርቲና መሪ ብቻ እንዳልሆነ ደጋግሞ ሊያስብ ይገባል፡፡
በብዙ ባላንጣዎች የተከበበው ይህ ነብር ራሱን መሬት ላይ አስቀምጦ ወደ ጐን ከማየት ይልቅ ዛፉ ላይ ወጥቶ ወደፊት ማየት አለበት፡፡ ህልሙ እውን የሚሆነው ይሄኔ ነውና!  
በተረፈ ሁላችንም አማራ፣ ትግሬ፣ ኦሮሞ ሳንል፣ በፍቅር በይቅርታና በመቀባል ሀገራችንን በጋራ ለመገንባት መነሳት ይኖርብናል፡፡   


ባለፈው ረቡዕ ይፋ በተደረገው የዘንድሮው የናይጀሪያ ፕሬዚዳንታዊ ምርጫ በስልጣን ላይ ያሉት ሙሀመድ ቡሃሪ ማሸነፋቸው መገለጹን ተከትሎ፣ በተፎካካሪነት የቀረቡት የተቃዋሚ ፓርቲ መሪ አቲኩ አቡበከር፣ የምርጫ ውጤቱን እንደማይቀበሉ በይፋ መግለጻቸው ተዘግቧል፡፡
ረቡዕ ማለዳ ላይ ይፋ በተደረገው የምርጫ ውጤት ሙሃመድ ቡሃሪ 56 በመቶ ድምጽ በማግኘት ማሸነፋቸውን ካስታወቁ ከሰዓታት በኋላ፣ ተሸናፊው አቲኩ አቡበከር በሰጡት መግለጫ፣ ምርጫው በ36 ግዛቶች ተጭበርብሯል፣ ዳግም እንዲካሄድ በፍርድ ቤት ክስ እመሰርታለሁ ማለታቸውን አሶሼትድ ፕሬስ ዘግቧል፡፡
በጤና እክል ሳቢያ አገሪቱን በቅጡ ለመምራት አልቻሉም፤ ሲሾሙ የገቡትን ቃል አክብረው አገሪቱን ከኢኮኖሚ ቀውስና ከሽብርተኞች መናኸሪያነት ማውጣት አልቻሉም በሚል ተቃውሞ በርትቶባቸው የከረሙት የ76 አመቱ ፕሬዚዳንት ሙሀመድ ቡሃሪ፤ ለሁለተኛ የስልጣን ዘመን እንደሚቀጥሉ ያረጋገጠው የምርጫ ውጤት ይፋ መደረጉን ተከትሎ፣ በርካታ የቡሃሪ ደጋፊዎች አደባባይ ወጥተው ደስታቸውን መግለጻቸውን የጠቆመው ዘገባው፤ በሌላ በኩል ደግሞ የተቃዋሚ ደጋፊዎች ተቃውሟቸውን ማሰማታቸውን ገልጧል።
በተለያዩ ምክንያቶች ሲራዘም የቆየው የናይጀሪያ ፕሬዚዳንታዊ ምርጫ፣ ቅስቀሳ ከተጀመረበት ጥቅምት ወር አንስቶ በተነሱ ግጭቶች ከ260 በላይ ሰዎች መገደላቸውን ያስታወሰው ዘገባው፣ ተቃዋሚው ፓርቲ መሪ ውጤቱን አልቀበልም ማለታቸው ተጨማሪ ግጭት ሊያስከትልና አገሪቱን ወደ ከፋ ቀውስ ሊያመራት እንደሚችል መሰጋቱንም አክሎ ገልጧል፡፡
ስራ ፈትተው በየማህበራዊ ድረገጹ የሆነ ያልሆነውን ሲለጥፉ የሚውሉ ዜጎችን ላለማበረታታትና በዚያውም ተጨማሪ ገቢ ለማግኘት በሚል ከወራት በፊት በኢንተርኔት አገልግሎት ተጠቃሚዎች ላይ አዲስ ግብር የጣለቺው ኡጋንዳ፣ በግብሩ የተማረሩ በሚሊዮኖች የሚቆጠሩ ዜጎች፣ ኢንተርኔት መጠቀም ማቆማቸው ኢኮኖሚዋን ስጋት ላይ እንደጣለው ተዘግቧል፡፡
የኡጋንዳ መንግስት ባለፈው ሃምሌ ወር ላይ ተግባራዊ ያደረገውና በአንድ ቀን 4 ፓውንድ ያህል የሚደርሰው የኢንተርኔት ግብር ያማረራቸው 2.5 ሚሊዮን ያህል የአገሪቱ ዜጎች ኢንተርኔት መጠቀም ማቆማቸውን የዘገበው ዘ ጋርዲያን፣ ይህ አዝማሚያ ከቀጠለ መንግስት ከኢንተርኔት ያገኝ የነበረውን ከፍተኛ ገቢ እንደሚያሳጣውና የአገሪቱን ኢኮኖሚ ሊጎዳው እንደሚችል መሰጋቱን አመልክቷል፡፡
የኢንተርኔት ግብሩ በተለይም የሞባይል ኢንተርኔት ተጠቃሚዎችን ቁጥር በእጅጉ እንዲቀንስ ማድረጉን የጠቆመው ዘገባው፣ አገሪቱ ከሞባይል የገንዘብ ዝውውር አገልግሎቶች ታገኘው የነበረው ገቢ ብቻ በቴክኖሎጂው ይዘዋወር የነበረው የገንዘብ መጠን ከሰኔ እስከ መስከረም በነበሩት ወራት በሩብ ያህል በመቀነስ፣ 3.4 ቢሊዮን ፓውንድ መድረሱንም አስታውሷል፡፡


የወቅቱ የአለማችን ቁጥር አንድ ባለጸጋ የሆኑት አሜሪካዊው ቢሊየነር ጄፍ ቤዞስ በአመቱ ከፍተኛ ገንዘብ ለበጎ አድራጎት ተግባራት በመለገስ በአለማችን በአንደኛ ደረጃ ላይ መቀመጣቸው ተዘግቧል፡፡
የአማዞን ኩባንያ መስራቹ ጄፍ ቤዞስ ባለፈው የፈረንጆች አመት 2018 ብቻ ከባለቤታቸው ጋር ባቋቋሙት ቤዞስ ዴይ ዋን ፈንድ በተባለው ድርጅት በኩል ለተለያዩ የበጎ አድራጎት ስራዎች 2 ቢሊዮን ዶላር መለገሳቸውንና በክሮኒክል ኦፍ ፌላንትሮፒ ተቋም የአመቱ ምርጥ 50 ለጋሾች ዝርዝር ውስጥ በቀዳሚነት መቀመጣቸው ተነግሯል፡፡
ለኪነጥበብ፣ ትምህርት፣ ጤናና ሌሎች ዘርፎች 767 ሚሊዮን ዶላር የለገሱትና በሚዲያና መዝናኛው መስክ ስኬታማ ለመሆን የቻሉት ማይክል ብሉምበርግ፣ በአመቱ ምርጥ 50 ለጋሾች ዝርዝር ውስጥ የሁለተኛነት ደረጃን የያዙ ሲሆን፣ የኢቤይ ኩባንያ መስራቾቹ ጥንዶቹ ፔሪ እና ፓም ኦሚዲያር 392 ሚሊዮን ዶላር በመለገስ በሶስተኛነት ደረጃ ላይ ተቀምጠዋል፡፡
በምርጥ ለጋሾች ዝርዝር ውስጥ ከተካተቱት ሌሎች ታዋቂ ሰዎች መካከል 213.56 ሚሊዮን ዶላር በመለገስ በሰባተኛ ደረጃ ላይ የተቀመጡት የፌስቡኩ መስራች ማርክ ዙከርበርግና ባለቤቱ ፕሪሲሊካ ቻን ይገኙበታል፡፡
ትራምፕንና ኪም ጆንግ ኡንን በመምሰል ያታለሉም ተይዘዋል

ከአነጋገርና አካሄዱ እስከ አለባበሱ መላ ሁኔታውን በመቀየር ራሱን ልክ እንደ ኬንያው ፕሬዚዳንት ኡሁሩ ኬንያታ በማስመሰል፣ ከአንድ ባለሃብት 100 ሺህ ዶላር ያጭበረበረው ጄሴፍ ዋሳዋ የተባለ ኬንያዊ፣ ከሰባት ግብረ አበሮቹ ጋር ተይዞ ክስ እንደተመሰረተበት ተነግሯል፡፡
አጭበርባሪው ጆሴፍ ዋሳዋ ከግብረ አበሮቹ ጋር በመተባበር ራሱን ልክ እንደ ፕሬዚዳንቱ በማስመሰል በናይጀሪያ ስመ ጥር ለሆነ አንድ የመኪና ጎማ ኩባንያ ባለቤት በመደወል፣ መሬት ልሽጥልዎት የሚል ጥያቄ ማቅረቡን የጠቆመው ዘገባው፣ ድርድሩ በስልክ መጨረሱን አመልክቷል፡፡ የኩባንያው ባለቤት የደወለላቸው ፕሬዚዳንት ቡሃሪ ስለመሆኑ ቅንጣት ታህል ሳይጠራጠሩ ዋጋ መደራደራቸውንና የፋይናንስ ዳይሬክተራቸው ግዢውን እንዲጨርስና ክፍያውን እንዲፈጽም ማዘዛቸውን፣ ይህን ተከትሎም ሌሎች ተባባሪዎች፣ የፕሬዚዳንቱን የሚመስሉ ልዩ መኪኖችን ተከራይተው፣ ወደ ኩባንያው በመሄድ በተጭበረበረ ሰነድ ገንዘቡን መቀበላቸውን ገልጧል፡፡
በተያያዘ ዜና ደግሞ፣ መላ ነገሩ ቁርጥ የሰሜን ኮርያውን ኪም ጆንግ ኡንን የሚመስለው አውስትራሊያዊው ኮሜዲያን ሆዋርድ ኤክስ እና በሚገርም ሁኔታ ከትራምፕ ጋር የሚመሳሰለው ግብረ አበሩ፣ ባለፈው አርብ በቬትናም መዲና ሃኖኢ፣ ሁለቱን ፕሬዚዳንቶች መስለው፣ ለመገናኛ ብዙሃን መግለጫ ሲሰጡ በቁጥጥር ስር መዋላቸው ተነግሯል፡፡
አጭበርባሪዎቹ ፕሬዚዳንቶች ትክክለኛዎቹ ኪምና ትራምፕ፣ በቬትናም ለመገናኘት የያዙትን ቀጠሮ እንደ መልካም አጋጣሚ በመጠቀም እነሱን መስለው፣ ህዝቡን ለመሸወድ ሲሞክሩ፣ እንደተነቃባቸውና ባለፈው ሰኞ ከአገር መባረራቸውን ሮይተርስ ዘግቧል፡፡
ባልተለመደ ሁኔታ እጅግና ከፍተኛ ሃይል ያለው ግዙፍ ባትሪ የተገጠመለትና ለ2 ተከታታይ ሰዓት ያህል ያለ ማቋረጥ ቪዲዮ ማጫወት የሚችል አዲስ ሞባይል ለእይታ መብቃቱ ተነግሯል፡፡ከሰሞኑ በባርሴሎና በተጀመረው አለማቀፍ የሞባይል አውደርዕይ ላይ ለእይታ የበቃውና በፈረንሳዩ የስልክ አምራች ኩባንያ አቬኒር ቴሌኮም የተመረተው ይህ የሞባይል ስልክ ፣ ከጎኑ ትልቅ ባትሪ የሚገጠምለትና 18 ሚሊሜትር ውፍረት ያለው ነው።
ፒ18ኬ ፖፕ የተባለው ይህ ሞባይል ስልክ የሚጠቀመው ባትሪ በግዝፈቱና በሃይሉ በአለማችን አቻ የሌለውና በአጭር ጊዜ ውስጥ ሙሉ ለሙሉ ቻርጅ መደረግ የሚችል ሲሆን፣ የሞባይል ስልኩ ለረጅም ሰዓታት ከማገልገሉ ውጭ ከሌሎች ስማርት ስልኮች የተለየ ነገር እንደሌለው ተነግሯል፡፡
ታዋቂው ብሉምበርግ መጽሄት የ2019 የአለማችን አገራት የጤናማነት ደረጃን ዝርዝር ከሰሞኑ ይፋ ያደረገ ሲሆን፣ ስፔን የአንደኛነቱን ደረጃ ከጣሊያን በመረከብ በቀዳሚነት መቀመጧ ታውቋል፡፡
በአለማችን 169 አገራት ውስጥ ለአጠቃላይ የዜጎች ጤናማነት መሰረት የሆኑ ጉዳዮችን ይዞታ በመገምገም የአገራቱን የጤናማነት ደረጃ ይፋ ያደረገው ብሉምበርግ፣ ጣሊያንን በሁለተኛነት አይስላንድን በሶስተኛነት ደረጃ ላይ አስቀምጧቸዋል። ጃፓን አራተኛ፣ ስዊዘርላንድ አምስተኛ፣ ስዊድን ስድስተኛ፣ አውስትራሊያ ሰባተኛ፣ ሲንጋፖር ስምንተኛ፣ ኖርዌይ ዘጠነኛ፣ እስራኤል አስረኛ ደረጃ ላይ ተቀምጠዋል፡፡
እጅግ አነስተኛ የጤናማነት ደረጃ ያላቸው ተብለው ከተዘረዘሩት 30 አገራት መካከል 27ቱ በአፍሪካና በመካከለኛው ምስራቅ ውስጥ እንደሚገኙ የጠቆመው ብሉምበርግ፣ የአገራቱን የጤናማነት ይዞታ ከገመገመባቸው መስፈርቶች መካከል የጤና አገልግሎቶች መስፋፋትና ጥራት፣ የንጹህ ውሃ አቅርቦት፣ ንጽህና፣ አማካይ እድሜ፣ የሲጋራና የአደንዛዥ ዕጾች ተጠቃሚነት፣ ከፍተኛ የሰውነት ክብደት ይገኙበታል፡፡

ከዕለታት አንድ ቀን አንድ ንጉሥ ሶስት ወንጀለኞች ላይ ሞት ፈረዱ፡፡ ከተፈረደባቸው አንዱ፤
“ንጉሥ ሆይ! አንድ ዕድል ቢሰጡኝ ፈረስዎትን ቋንቋ አስተምሬው እሞት ነበር፡፡” አላቸው፡፡
“በምን ያህል ጊዜ ልታስተምርልኝ ትችላለህ?”
“በአንድ ዓመት ጊዜ ውስጥ” ሲል መለሰ፡፡
“ጥሩ፣ አንድ ዓመት እሰጥሃለሁ”
“እኔም በአንድ ዓመት ተዓምር አሳይዎታለሁ!” አላቸው፡፡
አብሮት የታሰረው ሰው፤
“እንዲህ ያለ ቃል ለምን ገባህ? ለምንስ ይጠቅምሃል? በትክክል ምክንያታዊስ ነህ ወይ?”
“አዎን”
“እንዴት?”
“ምክንያቱ ምን መሰለህ?”
አየህ 1ኛ ወይ ንጉሡ ይሞታሉ
     2ኛ ወይ እኛ ማምለጫ እናገኛለን
     3ኛ ወይ ፈረሱ ይማራል
ማን ያውቃል?”
“ለካ ይሄ ሁሉ ዕድል አለ”?!
*   *   *
ብዙ ዕድል እያለን የማንጠቀም እኛ ኢትዮጵያውያን ብቻ ነን፡፡ ምክንያቱን በአጭሩ መንቆጥ ይቻላል፡፡
አንሄድም፣ አንንቀሳቀስም!
ከሄድንበት አንማርም!
የተማርነውን አናሻሽልም!
የተሻሻልነውን ለማንም አናካፍልም! አናስተላልፍም፡፡ መቼም እንዴትም እኒህን ነጥቦች ውል እንደምናስይዛቸው አይታወቅም፡፡ ከጥንቱ ከጠዋቱ የተማሪዎች እንቅስቃሴ ጀምሮ ጥያቄዎች አሉን፡-
“መቼ ነው ዲሞክራሲ ኢትዮጵያ የሚገባው?”
“መቼ ነው ፍትህ የሚሰፍነው?”
“መቼ ነው ነገን የምናምነው?”
ሳይመለሱ የቆዩ ጥያቄዎቻችን ዕጣ ፈንታቸው ምንድን ነው? የት ይደርሳሉ? ዛሬስ ምን ያህል ዕድሜ አላቸው?
መሪዎቻችን ህዝባቸውን አያስቡም፡፡ ህዝቦች መሪዎቻቸውን ያለምክንያት ይጠምዷቸዋል፡፡ ጊዜ አይሰጡም፡፡ ቦታ አይሰጡም፡፡ ተስፋ አይሰጡም፡፡ ሀሳባቸውን አይገልጡም! ሀሳባቸውን አያገናኙም!
አንድ አሳቢ፤
“The whole theory of development is knowing what change is all about” የዕድገት ምስጢሩ ለውጥ ምንድን ነው ማለት ላይ ነው እንደማለት ነው፡፡
ገጣሚና ፀሐፌ ተውኔት መንግሥቱ ለማ፣ “በባለካባና ባለዳባ” ቴያትር፣
“አንድ ዓለም ተሰጠ ለአዳም ለሄዋን
ለሁለቱ፣ ተረቱ፣ እንደሚነግረን
ምንስ ልጆቻቸው ቢረቡስ ቢራቡ
ጥቂቶቹ ጠግበው ብዙዎች ይራቡ?
ጥቂቶች ሲያምራቸው ያንሱ ጦርነት
ብዙዎችም ይሂዱ ለመሞት ለእልቂት፣”
የአገራችን ዕውነት ይሄው ነው! ጥቂቶች ይኖራሉ፤ ብዙዎች ይሞታሉ! ማንም ምንም ሳይጠይቅ መንገዳችንን እንቀጥላለን፡፡ የሞኞቹን አገር ምሳሌ ሆነን መጓዛችን መሆኑ ነው!
“ሞኙን ላኩትና ሞኞች ሞኞች አገር
ሞኙም አልጠየቃት
ሞኟም አትናገር!”  
የሚለው ተረት የሚመለከተን እዚህ ጋ ነው፡፡ እንጠይቅ! እንጠይቅ! እንጠይቅ!

“የምከተለው የኢኮኖሚ ሞዴል
ካፒታሊዝም ነው” ጠ/ሚ ዶ/ር ዐቢይ አህመድ

የቴሌ ኮሚኒኬሽን 49 በመቶ ድርሻ ወደ ግል ለማዘዋወር አስፈላጊ ዝግጅቶች መጠናቀቃቸውንና በዚህ ዓመት መጨረሻ የከፊል ሽያጩ እንደሚከናወን ጠ/ሚኒስትር ዶ/ር ዐቢይ አህመድ ማስታወቃቸውን ጠቅሶ ፋይናንሻል ታይምስ ዘግቧል፡፡
በሳምንቱ አጋማሽ ከፋይናንሻል ታይምስ ጋዜጣ ጋር ቃለ ምልልስ ያደረጉት ጠቅላይ ሚኒስትር ዶ/ር ዐቢይ አህመድ የሚከተሉት የኢኮኖሚ ሞዴል ካፒታሊዝም መሆኑን አስታውቀው በዚህም ባለፉት 28 ዓመታት በመንግስት ቁጥጥር ስር ቆዩ ግዙፍ ተቋማትን ወደ ግል ማዘዋወር ኢኮኖሚውን ለማነቃቃት የሚወስዱት የመጀመሪያ እርምጃ መሆኑን አስታውቀዋል፡፡
በሚከተሉት የካፒታሊዝም የኢኮኖሚ ሞዴል እና ተቋማትን ወደ ግል የማዘዋወር ፖሊሲ ከራሳቸው ፓርቲ (ኢህአዴግ) ከፍተኛ ተቃውሞ ገጥሟቸው እንደነበር የጠቀሰው ፋይናንሻል ታይምስ ጠ/ሚኒስትሩ በውሳኔያቸው ገፍተውበት ኢትዮ ቴሌኮምን በከፊል ወደ ግል ለማዘዋወር ዝግጅቶችን ማጠናቀቃቸውን አስታውቋል፡፡
መንግስት የኢትዮ ቴሌኮምን 49 በመቶ ድርሻ ወደ ግል እንደሚያዘዋውር ቀሪውን 51 በመቶ በራሱ እያስተዳደረ እንደሚቀጥል ጠ/ሚኒስትሩ ከፋይናንሻል ታይምስ ጋር በነበራቸው ቆይታ አስረድተዋል፡፡
ኢትዮ ቴሌኮም በአሁኑ ወቅት በአጠቃላይ 60 ሚሊዮን ደንበኞች ያሉት ግዙፍ የቴሌኮም ኩባንያ ሲሆን ይህ አመት ከመጠናቀቁ በፊት በከፊል ወደ ግል ይዘዋወራል ተብሏል፡፡
ወደ ግል መዘዋወሩም ለሃገሪቱ በቢሊዮን ዶላር ገቢ እንደሚያስገኝም ጠ/ሚኒስትሩ በቃለ ምልልሳቸው ያስገነዘቡ ሲሆን የአገልግሎት ቅልጥፍና እና ተወዳዳሪነትም ይጨምራል ደንበኞች ጥራት ያለው አገልግሎት ለማግኘት ያስችላቸዋል ተብሏል፡፡   Page 10 of 428