Administrator

Administrator

“እድል መሰጠቱ በራሱ በጣም ትልቅ ነገር ነው”ነዋል አቡበክር እባላለሁ። በሙያዬ የሚዲያ ባለሞያ ነኝ። በ“ሠላሳዎቹ“ የአጫጭር ልብወለዶች መድበል ፅሁፎቻቸው ከታተመላቸው 30 ወጣት ፀሀፍት አንዷ ነኝ። ‘’የክራሩ ክር’ የሚል ድርሰቴ በመድበሉ ውስጥ  ታትሞልኛል፡፡
ድርሰትሽ በ“ሠላሳዎቹ “ የአጫጭር ልብወለዶች መድብል ውስጥ በመካተቱ ምን ዓይነት ስሜት ፈጠረብሽ? ከዚህ በፊት ተመሳሳይ ዕድል ገጥሞሽ ያውቃል? የራስሽን መጽሐፍስ አሳትመሻል?
ለመጀመሪያ ጊዜ ስሜ በመጽሐፍ ላይ ሰፍሮ ሳየው እጅግ ነበር ደስ ያለኝ። ሥነ ፅሁፍን ለሚወድና ፅሁፍ ለሚሞክር ሰው ለመጀመሪያ ጊዜ ‘የሱ’ የሚባል ፅሁፍ ኖሮት ለመነበብ ሲበቃ ያለው ስሜት ይሄ ነው የሚባል አይደለም። የፃፍከውን ነገር የምታከብራቸው ባለሞያዎች አንብበውት፣ አምነውበትና ወደውት ወደ ህትመት መላኩን ስታውቅ፣ የሚያስፈራና በራስ መተማመን የሚጨምር ስሜት ነው የሚሰማህ፡፡ መፅሐፉ ከተነበበ በኋላም ሰዎች የሚያበረታታ አስተያየት ሲሰጡህ ውስጥህ የሚፈጥረው ትልቅ ተስፋ አለ። ከዚህ በፊት ተመሳሳይ ውድድር ላይ ተሳትፌም ሆነ የራሴን መጽሐፍ አሳትሜ አላውቅም።
. የአጫጭር ልብወለዶች ስብስቡን እንዴት አገኘሽው ?
የ“ሰላሳዎቹ“ አጫጭር ልብወለዶች ስብስብ’፣ ድንቅ ወጣት ፀሀፊያንን ለማንበብ እድል ያገኘሁበት፣ ብዙ አይነት ቀለም የተመለከትኩበት፣ ታሪክ በመንገር አቅማቸው በአተራረካቸውና በሀሳባቸው የተገረምኩባቸውን ፅሁፎች ያገኘሁበት መጽሐፍ ነው።
የወጣት ጸሃፍት ሥራዎች እንዲህ ተሰባስበው በጋራ መታተማቸው ምን ፋይዳ አለው ብለሽ ታስቢያለሽ?
በጣም ትልቁ ነገር እድል መስጠቱ ነው ብዬ አስባለሁ። ወጣቶች በራሳቸው አምነው የሚሉት ነገር ኖሯቸው ለመፃፍ እንዲነሱ የሚያደርግ እድል መሰጠቱ በራሱ በጣም ትልቅ ነገር ነው።  ከዚያ በተጨማሪ እንደ አንባቢ ይሄ መጽሐፍ የዘመናችንን መልክ የምናይበት አንዱ መንገድ ነው። በተቀራራቢ እድሜ የሚገኙ ነገር ግን የተለያየ ህይወትና አመለካከት ያላቸው ፀሀፍት ሃሳብና ስሜት፣ ህመምና ተስፋ ወዘተ-- በአንድ መጽሐፍ ተሰድረው ማንበብ ችለናል። እንደ ጀማሪ ፀሀፊ፣ ፅሁፍን የማሳተምና የመነበብ እድል ማግኘት የሚሰጠው ሞራልና ተስፋ በምንም የሚሰፈር አይደለም።
 ወጣት ጸሀፍት ከሥነ ፅሁፍ ጋር ስለሚኖረን ግንኙነት ለመወሰን እራስን መመልከቻ ነውም ብዬ አስባለሁ።
ከራስም  ከታላላቆቻችንም  ለመማር እድል ይሰጣል።
ከዚህም ባለፈ በጣም ያስደነቁንና የት ነበሩ ያስባሉንን አዲስ ፀሀፍትም  አፍርቷል፤ አበርክቷል ብዬ አስባለሁ።
 በጀርመን የባህል ማዕከል ድጋፍ ከተሰጣችሁ አጭር ሥልጠና ምን አዲስ ትምህርት ቀሰምሽ?
በርግጥ በስራ አጋጣሚ ከተማ ውስጥ ስላልነበርኩ በሥልጠናውን መሳተፍ አልቻልኩም ነበር። ነገር ግን ፅሁፉን ለመፃፍ ከማሰብ ጀምሮ እስከ መጨረሻው የአርትኦት ስራ ድረስ በጣም ብዙ እውቀትን አግኝቻለሁ። እኔ በአፃፃፍ ብዙ የምሳብበትን የአፃፃፍ አይነት ከማወቅና ከመረዳት ጀምሮ ስለ አማርኛ ሰዋሰው ፤ ቃላት መረጣ ፤ ሀሳብ አሰፋፈር ብዙ ነገር አስተምሮኛል።
ብዙ ጊዜ  ጀማሪ ፀሀፊ ስትሆን ልትፅፍ የፈለከውና አእምሮህ የሰጠህን ሀሳብና ቃል ነው ወረቀት ላይ የምታሰፍረው። በዚህ በኩል መንገድ የሚያሳይህ፣ ስህተትህን የሚያርምህና እራስህ እንድታስተካክል እድል የሚሰጥህ ስታገኝ ብዙ ታተርፋለህ፡፡ ለዚህ ደግሞ የጀርመን የባህል ማዕከልን ፣ አርታኢዎቻችንን፣ አስልጣኞቻችንንና አዘጋጆቹን ከልብ እናመሰግናለን።
 ከአገራችን ወይም ከውጭ አገራት የአጭር ልብወለድ ጸሐፍት ማንን ታደንቂያለሽ ?
ከሀገር ውስጥ ተመስገን ገብሬ፣ ከውጭ የፍራንዝ ካፍካ ፅሁፍ ይስበኛል።

ሊድያ ተስፋዬ እባላለሁ። ትውልድና እድገቴ አዲስ አበባ ነው። ከአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ በመጀመሪያ በኢኮኖሚክስ ቀጥሎም በእንግሊዝኛ ሥነ ጽሑፍ ተመርቄአለሁ። በሕትመት ሚድያው ላይ ከጀማሪ ዘጋቢነት ጀምሮ በተለያዩ ድርሻዎች ሠርቻለሁ፣ አሁንም እየሠራሁ ነው። ድርሰቴ በመጽሐፍ ላይ ሲታተም የአሁኑ የመጀመሪያዬ ነው፡፡ ከዚህ ቀደም በመደበኛነት እሠራ በነበረበት “አዲስ ዘመን“ ጋዜጣ እንዲሁም በኋላ ላይ “አዲስ ማለዳ“ ጋዜጣ ላይ የተለያዩ ጽሑፎችን ለአንባቢያን የማድረስ እድልን አግኝቻለሁ። “ሠላሳዎቹ“ በተሰኘው መድበል ውስጥ ‘’ስለምን ታለቅሺያለሽ?’’ የሚለው ድርሰቴ ተካትቶልኛል፡፡
ድርሰትሽ በ“ሠላሳዎቹ“ የአጫጭር ልብወለዶች መድብል ውስጥ በመካተቱ ምን ዓይነት ስሜት ፈጠረብሽ? ከዚህ በፊት ተመሳሳይ ዕድል ገጥሞሽ ያውቃል? የራስሽን መጽሐፍስ አሳትመሻል?
በቅድሚያ አዲስ አድማስ ጋዜጣ ይህን እድል ስለሰጠን በጣም አመሰግናለሁ። ከዚህ ቀደም የራሴን መጽሐፍ አላሳተምኩም። በተለያዩ ደራሲዎች በኀብረት ተዘጋጅተው የታተሙ የአጫጭር ልብወለድ እንዲሁም የግጥም ስብስብ ሥራዎች መኖራቸውን አውቃለሁ እንጂ እንዲህ ያለ እድል ገጥሞኝ አያውቅም። ደራሲ የመሆን ምኞት  አለኝ፡፡ ድርሰቴ በዚህ “ሠላሳዎቹ“ የተሰኘ መድበል ውስጥ መግባቱን ሳውቅ በጣም ነበር ደስ ያለኝ። በአንድ በኩል መመረጡ ራሱ ለወደፊት በተስፋ እንድበረታ የሚያግዘኝ ነው። አንድ ብሎ መጀመር ከባድ ነው፣ አንዳንዴ እንዲህ ያለ እድልን ይፈልጋል። በሌላ በኩል፤ ለሕትመት ወጪ እንድንጨነቅ አልተደረግንም። ከዚያም ባልተናነሰ በሥነ ጽሑፉ ዘርፍ  የተመሰገኑ፣ የተደነቁ ሰዎች ናቸው አርትዖቱን የሠሩት። ድርብርብ እድል ማለት ነው። በእነዚህ ሁሉ ምክንያቶች የተነሳ እድሉን ማግኘቴም፣ ቀድሞ ነገር እድሉ ራሱ መፈጠሩ ደስ አሰኝቶኛል። በዚህ አጋጣሚ ለዚህ ምክንያት የሆነውን የጀርመን ባሕል ማዕከል ወይም ጎተ’ን፣ እንዲሁም በዋናነት ሐሳቡን ከመጸነስ ጀምሮ ልብወለዶቹ እንዲህ መጽሐፍ ሆነው እንዲወጡ ለማድረግ፣ ባየነውም ባላየነውም ሂደት ውስጥ ሲደክም የነበረውን ዮናስ ታረቀኝን  በጣም አመሰግናለሁ።
የአጫጭር ልብወለዶች ስብስቡን እንዴት አገኘሽው?
በጣም ወድጄዋለሁ። የተለያዩና ጥልቅ ሐሳቦችን፣ ዕይታዎችን፣ ስሜቶችን የተሸከሙ ሥራዎች ናቸው። በወጣቶች ዐይን ሀገር፣ ዓለም፣ ማኅበረሰብና ራሱ ሕይወት የተሳሉበትን መንገድ አሳይቶኛል። ወደፊት በአዳዲስ ሥራዎች  ላያቸው የምናፍቃቸው ደራሲዎችን አስተዋውቆኛል።  
የወጣት ጸሐፍት ሥራዎች እንዲህ ተሰባስበው በጋራ መታተማቸው ምን ፋይዳ አለው ብለሽ ታስቢያለሽ?
ይህን ከኹለት አንጻር ነው የማየው፣ ከደራሲዎችና ከተደራሲዎች አንጻር። ከደራሲዎች አንጻር መተባበርን፣ አንድነትን፣ መተዋወቅን የሚፈጥርና እንደ ሃምሳው ሎሚ የቤት ሥራን አከፋፍሎ ድካምን የሚቀንስ ነው። ይህን የእኛን ሥራ እንኳ ብንመለከት፣ ሠላሳዎቻችንም በመጽሐፉ ላይ በተካተተ አንድ ሥራችን ብቻ የተነሳ አፋችንን ሞልተን መጽሐፉን ‘የእኔ መጽሐፍ’ እንላለን። ልክ እንደዛ ሁሉ፣ አብሮ መሥራቱ አንድነትን ይፈጥራል፣ ያበረታል፣ ያተጋል። ከተደራሲዎች አንጻር ደግሞ የተለያየ ጣዕምን ይሰጣል። አንባቢዎች የአንድ ደራሲን ወይም የአንዲት ደራሲትን ሥራ አይደለም የሚያነብቡት፣ የተለያዩ ደራሲዎችን ሥራ በአንድ ላይ ነው የሚያገኙት። ማኅበራዊ ሚድያው ተወዳጅ ያደረገው አንድ ጠባዩ ይህ ይመስለኛል፣ የተለያዩ ሰዎች ዕይታዎችና ሐሳቦች በአንድ አውድ የሚቀርብበት መሆኑ። በዚያ ልክ ባይሆንም እንኳ፣ መጽሐፍም በራሱ ሜዳ በተለያዩ ጸሐፍት በጋራ የተዘጋጁ ሥራዎችን ሲይዝ፣ ለአንባቢ ምርጫን ያሰፋል ብዬ አምናለሁ። ከዚያ ባሻገር ለሥነ ጽሑፍ አጥኚዎችም  የጥናት ግብዓትና መነሻ ሊሆን ይችላል።
በጀርመን የባህል ማዕከል ድጋፍ ከተሰጣችሁ አጭር ሥልጠና ምን አዲስ ትምህርት ቀሰምሽ?
ድርሰቶቻችን ከተመረጡ በኋላና ለሕትመት ከመዘጋጀታቸው በፊት የሁለት ቀናት ሥልጠና ወስደን ነበር። በዚህ አጋጣሚ እርስ በእርስ ከመተዋወቃችን ጎን ለጎን፣ ስለሥራዎቻችን ጥንካሬና ደካማ ጎን ተነግሮናል። በበኩሌም አስቀድሞ በአስተውሎት የማላያቸው የነበሩ ጉዳዮችን በትኩረት እንዳይ አንቅቶኛል። በዚያው ሥልጠና መሠረታዊ የሚባሉ ከሥነ ጽሑፍ ጋር የተገናኙ ጉዳዮችንም በተመለከተ ሐሳቦችን አግኝተናል። በሥልጠናው የሰማናቸው ልምዶችም ጽሑፎቻችንን ብቻ ሳይሆን እንደ ጸሐፊ ራሳችንም ላይ እንድንሠራ የሚጋብዝ ሆኖ ነው የተሰማኝ።
ከአገራችን ወይም ከውጭ አገራት የአጭር ልብወለድ ጸሐፍት ማንን ታደንቂያለሽ?
ጥቂት ከሚባሉ ሴት ደራሲያት መካከል ሕይወት እምሻውን ብጠቅስ እወዳለሁ። በብዛት በግጥም፣ በጥቂቱ ደግሞ በረጅም ልብወለድ ሥራዎች የሚጠቀሱ ደራሲያት አሉ። በአጫጭር ልብወለድ ግን ጎልተው የሚጠቀሱ ሴት ደራሲያት መኖራቸውን እርግጠኛ አይደለሁም። ከእኔ የንባብ እጥረት ከሆነ ይቅርታ እጠይቃለሁ። ካሉትና ከማውቃቸው ግን ሕይወት እምሻውን አደንቃለሁ።

· ወልዲያ--የህዝቡ ፍቅር ለማዘንና ለመተከዝ ፋታ የሚሰጥ አይደለም
· የባህል ሙዚቃ በሜጀር ደረጀ በያሬድ ሙዚቃ ት/ቤት አይሰጥም
· ምርጫ ሲመጣ---ከማንም በላይ የሚጎዳው አርሶ አደሩ ነው
· እናቴ ወይፈን ሸጣ ጊታር ገዝታልኛለች


የአገው ምድር ቻግኒ ናት ያበቀለችው፡፡ ከክራር ጋር የተዋወቀው ገና የ11 ዓመት ለጋ ታዳጊ ሳለ መሆኑን ይናገራል፡፡ የበዓል እንግዳችን የባህል ሙዚቀኛና ድምጻዊ አስቻለው ፈጠነ፤ “እናትዋ ጎንደር” እና “ካሲናው ጎጃም” የተሰኙትን ከቱባው ባህል የተቀዱና ለ“ኮራ አዋርድ” እጩ እስከመሆን ያደረሱትን ዘፈኖች እስኪያወጣ ድረስ እምብዛም አይታወቅም ነበር፡፡ ዝምታና ጥሞናን ገንዘቡ ያደረገው ድምፃዊው፤ ሁለቱን ነጠላ ዘፈኖቹን ባወጣ ማግስት በሀገር ውስጥና በውጪ ለሙዚቃ ኮንሰርት ቢጋበዝም፣ ”በሁለት ዘፈን ህዝብ ላይ መፈንጨት ተገቢ አይደለም” በሚል ሚሊዮን ብሮችን ወደ ጎን ትቶ፣ ለተጨማሪ ሥራዎች ውሎና አዳሩን ስቱዲዮ ማድረጉን ይገልጻል፡፡ ከሁለት ዓመት ከስምንት ወራት የስቱዲዮ ምናኔ በኋላም ከሰሞኑ “አስቻለ” የተሰኘውን አዲስ የሙዚቃ አልበሙን እነሆ በረከት ብሏል፡፡ የአዲስ አድማስ ጋዜጠኛ ናፍቆት ዮሴፍ፣ ድምጻዊ አስቻለው ፈጠነን ቦሌ መድሃኒያለም ቤተክርስቲያን  ጀርባ  በሚገኘው የሙዚቃ ስቱዲዮው ተገኝታ በስፋትና በጥልቀት ስለ ሙዚቃ ህይወቱ አነጋግረዋለች፡፡ በዚህ ቃለ መጠይቅ ስለ ሙዚቃ ብቻ ግን አይደለም ያወጉት፡፡ ስለ ትምህርቱና ፍቅር ህይወቱ፣ ስለ ግብርና ሙያው እንዲሁም በፖለቲካ ምክንያት ስለደረሰበት ውጣ ውረድም ተጨዋውተዋል፡፡ አንብቡት - ትወዱታላችሁ፡፡አስቻለው፤ ስለ አዲሱ አልበምህ እንኳን ደስ አለህ---
እንኳን አብሮ ደስ አለን፤ በጣም አመሰግናለሁ!
ከ“እናትዋ ጎንደር” እና “ካሲናው ጎጃም” ነጠላ ዘፈኖችህ በፊት ብዙ ልብ ያላልናቸውና ስላንተ ልናውቃቸው የሚገቡ ነገሮች ያሉ ይመስለኛል፡፡ እስኪ በደንብ እንተዋወቅህ?
ከሙዚቃ ጋር የተዋወቅሁት ገና በ11 ዓመቴ አካባቢ ነው፡፡ አባቴ ነፍሱን ይማርና የተከበረች ማንም የማይነካት ቆንጆ ክራር ነበረችው፡፡ በር ላይ ቁጭ ይልና “ፋኖ ፋኖ”ን በደንብ ነበር የሚጫወተው፡፡ እኔ አሁንም የማስታውሳቸው ከግጥሞቹ ሁለት ጊዜ የሚደጋግማቸው ነበሩ፡፡
እስኪ ንገረን?  
“ሰው ሁሉ ይዋሻል እኔ አላውቅም ውሸት፤
 እንሂድ አገራችን እንብላ መስኖ እሸት
 ብቻዬን ነኝ ብዬ ዞሬ ዞሬ ሳይ
 ለካስ ዳሞቶቹ አሉ ከኋላዬ” ይላል፡፡
 ሁልጊዜም በጥር መድሃኒያለም የአባቴ ዘመዶች እኛ ቤት ይመጣሉ፡፡ መጥተው ይሰበሰቡና ታዲያ፤
”እቴ መላ ዘውዴ ዘውዴ
እቴ መላ ዘውዴ ዘውዴ--እቴ መላ ዘውዴ ዘውዴ” ይላሉ (በድምጹ እየዘፈነ)፡፡ ያንን ነው እኔ ”ካሲናው ጎጃም” ላይ ግጥሙን ቀይሬ የሰራሁት እንጂ የአባቴና የዘመዶቼ የጥንት ዘፈን ነው፡፡ ያኔ ፉከራ ሽለላም አለ፤ በደንብ አስታውሳሁ፡፡ አባቴም ዘመዶቹን በቅጥያ ስም ነው የሚጠራቸው፡- “ጋርጣው” ይለዋል አንዱን፡፡ “አፈንዳው ጎርድም” ይለዋል ሌላውን፡፡ ለምሳሌ አባቴ እኔን “የእኔ እንግዳ” ብሎ ይጠራኛል፡፡ ስሜ አስቻለው ሆኖ ሳለ በራሱ ልዩ ምክንያት ነው ”የእኔ እንግዳ” የሚለኝ፡፡ ታዲያ ዘመዶቻችን ሲመጡ የማንኩሳና የቡሬ አገዳ ይዘው ስለሚመጡ እሱን እንጠብቃለን፡፡ ደሞ የእናቴ ዘመዶች በፈረስ ከግምጃ ቤት ይመጣሉ፡፡ እነ አባ ጓንጉልና አባ ገዳሙ የተባሉ ዘመዶቻችን ይመጣሉ፡፡ በዚያን ጊዜ የአገው ፈረስ አለ፤ ቻግኒ ውስጥ ጥቅምት መድሃኒያለም በደንብ ይከበራል፡፡ እኛ አገዳ ከዘመዶቻችን እንቀበላለን፡፡ በጣም የሚኮሰኩስ ጢማቸው ውስጥ እያሹ ይስሙናል፤ ፍቅር ይሰጡናል፤ ያ ድባብ በጣም ነው ደስ የሚለው፡፡ ከልጅነቴ ጀምሮ ቱባው ባህል ውስጥ ነው ያደግሁት ለማለት ነው፡፡
በትምህርትህ ጎበዝ እንደነበርክ ሰምቻለሁ --?
አዎ! በጣም ጎበዝ ተማሪ ነበርኩኝ፤ 12ኛ ክፍል ማትሪክ ሒሳብ “F” መጣብኝ፤ እንደገና ተፈትኜ ግን 3 ነጥብ 8 አመጣሁ፡፡ ከዚያ በኋላ ዩኒቨርሲቲ ለመግባት ለአማራ ክልል  ስትሬት A ብቻ ተባለ፡፡ እኔ ደግሞ ማምቡግ ነበር የተማርኩት፤ ክልል 6 ማለት ነው፡፡ ከእኔ ጋር ተምረው 3 ነጥብ 2 ያመጡት ተጠሩ፡፡ ያኔ እኔ በጣም ተሰማኝ፡፡ እኔ ከአማራ ክልል ሄጄ ነበር የተፈተንኩት፤ ይሄ በክልል የሚባል ነገር ነው ችግሩን ያመጣውና በጣም አዘንኩ፡፡ ቀጠልኩና ባህርዳር ሄጄ ደግሞ በሰባት ወርና በ1 ዓመት ህግ ለመማር ተወዳድሬ አለፍኩ፤ ግን ያ ኮታ ደግሞ ለከተማዋ ሰዎች ነበር የወጣውና እዛ ተወላጅ ነኝ ብላ 3.2 ያመጣች ልጅ ገባች፡፡ በዚያም ማሰልጠኛ ልገባ የነበረበት ዕድል ቀረ፡፡ በኋላ የማታ ተማር ስባል እናቴን ብር አላስወጣም ብዬ ተውኩት፡፡
ትውት ትውት--?
አዎ ሁሉም ነገር አስጠላኝ፡፡ ያን ጊዜ እናቴ ወይፈን ሽጣ ጊታር ገዛችልኝ፡፡ በነገራችን ላይ እናቴ በጣም አራዳ ናት፡፡ አሁን የጊታሩን ሳይንሳዊ አፈጣጠር አታውቀውም፤ ለኔ እንደሚያስፈልገኝ ግን አውቃ ነበር፡፡ ያን ጊዜ እንደዛ ጎበዝ ተማሪ የነበርኩት ልጅ  ከትምህርት ስቀር እናቴ ብቻ ሳትሆን፣ ሁሉም ነበር ያዘነው፡፡ ከዚያ የግብርና የ3 ዓመት ስልጠና እንድማር እኔ ባህርዳር ሆኜ ቻግኒ አስመዘገቡኝ፤ መርጡ ለማሪያም ሄድኩኝ፡፡ እዚያ ስሄድ ክራሬንም ጊታሬንም ይዤ ነበር፡፡ ያንን ትምህርት የጀመርኩት በትምህርቴ ሁኔታ እናቴ አዝና ስለነበር፣ እሷን ለማስደሰት ነው፡፡ ያኔ መርጡ ለማሪያም አካባቢውን ስዞር ስጎበኝ ብዙ አዳዲስ ልምዶችንም አካበትኩ፡፡ መርጡ ለማሪያም በዲፕሎማ ተመርቄ የግብርና ባለሙያ ሆኜ ቻግኒ ተመደብኩ፡፡ የጉምዞች አካባቢ ሳስ ዱባክቻ የሚባል ጉደር ጃቢ ቀጠና ውስጥ አኩሪ አተር እዘራ ነበር፤ ሰሊጥ በርበሬና ሌሎችንም እያዘራሁ ሚንጊ ላይ ሁለት ዓመት ያህል ኖርኩ፡፡ የጉምዞች አኗኗራቸውም አካባቢውም ተመቸኝ፤ እነሱ የኢትዮጵያ መሪ ማን ይሁን፣ ፖለቲካው ምን ይምሰል የሚያውቁልሽ ነገር የለም፡፡ በጋ ላይ ከእነሱ ጋር ቁጭ ብለሽ ቦርዴሽን ትጠጫለሽ፤ ቦያ የሚባል ምግብ አለ፤ ዱባ አለ፡፡ እኔ የግብርና ባለሙያ ነኝ፤ አስፈቅደው አደን ያድናሉ፡፡ አድነው ከተሳካ የሚዳቋዋን አንድ እግር ያመጣሉ፤ ያንን እየበላን ዙምባራ ይነፋል፣ ሁሌ ማታ ማታ ጨዋታ ነው፡፡ በጣም ከማልረሳው የህይወቴ ክፍል፣ ከጉምዞች ጋር የኖርኩት አንዱ ነው፡፡ ከሁለት ዓመት በኋላ “ዳንጉላ” የሚባል ቀበሌ ገበሬ ማህበር ገባሁ፡፡ ይህ ደግሞ በአብዛኛው አገውዎች በብዛት የሚኖሩበት ነው፡፡ እዚህ ደግሞ ሌላ ባህል፣ ሌላ ህይወት አወቅሁኝ፡፡ እስከዚህ ጊዜ ድረስ ህይወቴ ጥሩ ነበር፡፡ በ2002 ዓ.ም ምርጫ ሲመጣ ነገሮች መበላሸት ጀመሩ፡፡
እንዴት ማለት?
ያው ምርጫ ሲመጣ በነገራችን ላይ ከማንም በላይ የሚጎዳው አርሶ አደሩ ነው፡፡ ምክንያቱም የእከሌ ፓርቲ ነህ፣ እንዲህ ነህ እያሉ ካድሬዎች ምንም የማያውቀውን ህዝብ እያስፈራሩ ሙስና ይቀበላሉ፡፡ ምንም የለሁበትም ብሎ ቢያንገራግር ወስደው ያስሩታል፡፡ እናም በዚያ ጊዜ በሃያዎቹ ዕድሜዬ መጀመሪያ ላይ ነኝ፤ እናንተ “ፍንዳታ” እንደምትሉት አይነት ነኝ፤ ምንም አልፈራም ስራዬን እሰራለሁ፤ መንግሥት የማያቀርበውን ዘር እኔ በኮሙኒኬሽኔ እየገዛሁ አቀርብላቸዋለሁ፡፡ በዚህ በዚህ ህዝቡ ወደደኝ፡፡ አርሶ አደሩ አፈር እንዳይሸረሸር ክትር (እርከን) እንስራ ስላቸው ተንጋግተው ይወጣሉ፡፡ የመንግስት ካድሬዎች ሲጠሯቸው አንዳቸውም አይወጡም፡፡ “ይሄማ ነገር ልጁ ሌላ ተልእኮ ቢኖረው ነው” አሉና አንድ ስብሰባ ላይ አባል ሁን አሉኝ፡፡ እምቢ አልሆንም አልኩኝ፡፡ ስብሰባ ላይ ገመገሙኝና የአመለካከት ችግር አለበት ተባልኩ፡፡ ስራም አይሰራም ብለው ሀጢያቴን ሊያበዙ ሞከሩ፡፡ በአጋጣሚ እዚያ ቀጠና ላይ በምሰራው ውጤታማ ስራ የኢትዮጵያ ቴሌቪዥን መጥቶ ቀርፆኝ ነበር፡፡ በግምገማው ላይ “እርግጠኛ ናችሁ ሥራ አልሰራም?“ ብዬ ጠየኳቸው፡፡ ሀላፊው ተነስቶ “ስራ ላይ ጠንካራና ጎበዝ ሰራተኛ ነው” ብሎ መሰከረ፡፡ ”እንኳንም ስራ መስራት አትችልም ያልተባልኩ፤ የእኛ አባል ሁን ካላችሁኝ ግን የእናንተን የአመለካከት ኮርቻ ለመፈናጠጥ በጣም ትጠቡኛላችሁ“ አልኳቸው፡፡ ተመልከቺ አዳራሹ ውስጥ ወደ አምስት መቶ የሚጠጋ ሰው አለ፡፡ ኧረረረ--- አሉ፡፡ ”የአመለካከት ችግር አለበት፤ አርሶ አደሩን በህቡዕ ያደራጅብናል“  አሉና ከስብሰባው ሁለት ሦስት ቀን በኋላ የእስር ትእዛዝ እንደወጣብኝ ወዳጆች ደውለው ሲነግሩኝ፣ ከዚያ ጠፍቼ ወልዲያ ገባሁ፡፡
ብዙ ውጣ ውረድ ገጥሞሀል ማለት ነው?
እጅግ በጣም፡፡ ከዚያ ወልዲያ ሄጄ አሁን ካናዳ የሚኖር ሀይለየሱስ የሚባል ወንድሜ ጋር መኖር ጀመርኩ፡፡ መታወቂያም አወጣልኝ፡፡ ከዚያ በኋላ በየገጠሩ ታቦት ወጣ ከተባለ አርሴማ ብትይ ሌላው ቦታ በእግሬ እስከ 8 ሰዓት እየተጓዝኩ በዚያው አድሬ እመለሳለሁ፡፡ አዳጎ የሚባለውን የወልዲያ ተራራማ ቦታ፣ መቻሬ ሜዳ፣ ጎንደር በር ፒያሳ፣ መድሃኒያለም ሰፈር--- ሁሉንም በእግሬ እየዞርኩ ተዋወቅኋቸው፡፡ እንዳልኩሽ የገጠር ታቦት ሲወጣ ሁለት ሦስት ቀን እዚያ ብቀመጪ የወሎን ሰው ታውቂዋለሽ፤ ቸር ሩህሩህና ፍቅር ነው፤ ብቻ አለመዱኝ፡፡
አስቼ ቻግኒ እያለህ በፍቅር ያንገላታችህ ወሎዬ ልጅ እንደነበረች ሰምቻለሁና፣ እስኪ ለጨዎታው ድምቀት ስለዚያች ውብ ወሎዬ አጫውተኝ----
አሃ ይሄንንም ጋዜጣው ላይ ታስገቢዋለሽ?
ምን አለበት?
ካልሽ እሺ! ቻግኒ በጣም ቆንጆ ወሎዬ አፍቅሬ ነበር፡፡ በዚያ ሁሉ የህይወት ምስቅልቅል ውስጥ ሳለሁ፡፡ ብቻ ተለያየን፤ ብዙ ታሪክ አለው፡፡ እዚያ ከደረሰብኝ ውጣ ውረድ ጋር እንደዚያ የምወዳትን ልጅ ማጣቴ በጣም ጎድቶኝ ነበር፡፡ ወሎ ገባሁ፤ ወሎየዎቹ መከፋቴን ቁስሌን ቶሎ አሻሩት፡፡ ከችግሬ ከሀዘኔ እንድወጣ አደረጉኝ፡፡ ህዝቡ ቁንጅናው ደግነቱ ልዩ ነው፡፡ መደብ ላይ ቁጭ ብለሽ ትበያለሽ ትጠጫለሽ፤ ያንቺ ገንዘብ መኖር አለመኖር ለወሎ ህዝብ ጉዳዩም አይደል፡፡
ብቻ ወሎ፣ ነውር የሌለበት ፍቅርና ደግነት ብቻ ነፍስያውን ያረሰረሰው ህዝብ ነውና ህይወቴን ቀየረው፡፡
ያቺን ቻግኒ ያፈቀርካትን ቆንጆ አስረሱኝ ነው የምትለኝ?  
መርሳት ሲባል እንዴት መሰለሽ---በፊት ብቻዬን ስሆን እያሰብኳት አዝን እተክዝ ነበር፡፡ ወልዲያ ስመጣ የህዝቡ ፍቅር ለማዘንና ለመተከዝ ፋታ የሚሰጥ አይደለም፡፡ ልጅቷን መቶ በመቶ ባልረሳትም ግን በቃ በብዛት ረሳኋት፤ ከጭንቅ ወጣሁ፡፡ በዚህ ፍቅር ህዝብ መሃል ሁለት ዓመት ቆየሁና እንደገና እንዴት ልውጣ? ህዝቡን ወደድኩት፡፡
ድጋሚ ወልዲያ ከአንዷ ጉብል ፍቅር ያዘህ ይሆን?
እንዲያው ፍቅር የሚባል ነገር እንኳን አይደለም፤ ብቻ ከእነ ገምሻሪት ጋር ተገማሽረናል ተይውማ…. (ተያይዘን በሳቅ….)
ከሁለት ዓመት የወልዲያ ቆይታ በኋላ ነው አዲስ አበባ የመጣኸው? እስኪ ወደ አዲስ አበባ ስለመጣህበት አጋጣሚ አውራኝ?
አዎ፤ ከወልዲያ ነው የመጣሁት፤ ብቻ መጣሁ፤ ግን ከክፍለ ሀገር አዲስ አበባ ሰው ሲመጣ ውጣ ውረዱ ከባድ ነው፡፡ ፍሬ የምትባል እህት አለችኝ፤ እሷ ጋ መጥቼ ፈረንሳይ ጉራራ የሚባል ሰፈር ገባሁ፡፡ እዚያ እህቴ ጋር እየኖርኩ ቻግኒ ደግሞ ትንሽ ቪዲዮ ቤት  ያላት ፊልምና ሙዚቃ የምታከፋፍል ታናሽ እህቴ ነበረችና (አሁን ለንደን ነው ያለችው)፣ ለሷ የፊልም ሲዲ በአውቶቡስ ለመላክ ሌሊት 11 ሰዓት እነሳና በ12 ቁጥር አውቶቢስ ተሳፍሬ መርካቶ እገባለሁ፡፡ ከዚያ ሳንቲም ለመቆጠብ ከመርካቶ በእግሬ ፈረንሳይ ለጋሲዮን እሄዳለሁ፡፡ ይህ ሁኔታ ከአንድ አመት በላይ ነበር የቆየው፡፡ ይህን ሁሉ የምለፋው እሷ ገንዘብ አጠራቅማና እቁብ ጥላ የኔን የሙዚቃ አልበም ለማሳተም ነበር፡፡
ወቸጉድ! ብዙ ውጣ ውረድ ነዋ ያለፍከው?
ውጣ ውረድ ብቻ!? በጣም ተፈትኛለሁ፡፡ አልፎ ሲወራ ቀላል ነው የሚመስል፡፡ ብቻ ይህንን እየሰራሁ አዲስ አበባ ቴአትርና ባህል አዳራሽ (ማዘጋጃ ቤት) ማስታወቂያ ወጣ፡፡
የምን ማስታወቂያ?
የድምጻዊነት ማስታወቂያ ነበር የወጣው፡፡ እኔ በአገውኛና በጉምዝኛ ተወዳድሬ አለፍኩ፡፡
በእኔ እምነት፣ ወደ ህዝብ አፍና ጆሮ መግባት የጀመርከው ክራርህን ይዘህ ግጥም በጃዝ ላይ ብቅ ስትል ነው----
አመሰግናለሁ! ምን መሰለሽ---አንድ ቀን የአድዋ በዓል ሲሰራ ማዘጋጃ ቤት ክራር መጫወቴን ማንም አያውቅም፡፡ ከዚያ እዚያው ማዘጋጃ ቤት የዘመናዊ ዳንሱ ቡድን ሀላፊ የሆነው ከድር የሚባል ልጅ አየኝ፡፡ እንግዲህ ከተቀጠርኩ ከሁለት ከሦስት ዓመት በኋላ እኮ ነው፡፡ “እንዴ አስቼ ክራር ትችላለህ እንዴ!” አለኝና “ቆይ ቆይ ከእኛ ጋር ተዋህደህ ትሰራለህ“ ብሎኝ ሰራን፡፡ ሰው ሥራዬን በጣም ወደደው፡፡ እዚያች መድረክ ላይ ደግሞ የፖየቲክ ጃዝ አዘጋጇ ምስራቅ ተረፈ ነበረች፡፡ “እኛ ጋ ግጥም በጃዝ የሚባል ፕሮግራም አለ፤ እዚያ ስራ“ አለችኝ፡፡ እዚያ ገብቼ ስሰራ ደግሞ ሥራዬ በጣም ተወደደ፡፡ በዚሁ ቀጥል ተባልኩ፡፡ ኧረ ቆይ እስኪ ብዬ ግጥም በጃዝ ላይ ሦስት ወይም አራት መድረክ ከሰራሁ በኋላ ተወት አደረግሁት፡፡
ሌላው የዛሬ አራት ዓመት አካባቢ ስለ ህዳሴው ግድብ በተዘጋጀ ፕሮግራም ላይ በሸራተን አዲስ “አባይ” የሚል ሙዚቃ ተጫወትኩ፡፡ አዘጋጁ ሰራተኛና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴር ነበር፡፡ በእለቱ በርካታ ሚኒስትሮችና ሌሎች የስራ ሃላፊዎችም ነበሩ፡፡ በዚያ መድረክ ላይ አባይን ስጫወት በጣም ወደዱት፡፡ በዚህ መርሃ ግብር ላይ በዚያን ወቅት ባህልና ቱሪዝም በሚባለው ሚኒስቴር መስሪያ ቤት፣ በአሁኑ ባህል ሚኒስቴር የሚሰራ አበበ (የሀብከ) የሚባል ልጅ “ይህን ነገር ለሚኒስትሯ ላሰማት” ብሎ ለዶ/ር ሂሩት ካሳው አሰማ፡፡ በእርግጥ ሚኒስትሯ በመድረኩም ላይ ነበረች፡፡ ይህንን ደግማ ከሰማች በኋላ ፕሮጀክት ንደፉና በደንብ ይስራ ተባለ፡፡ ይሄ ነገር እውነት ሆኖ ከተሰራማ ሰው መሆን ይሰማው (ሶሚክ) ነው የሚሰራው ብዬ ደወልኩለት፤ አላነሳም፡፡ እኔ ደግሞ ስለ አባይ በክራር የተጫወትኩትን ላኩለት፤ በሌሊት ደወለ፡፡ “ፈጣሪ ያክብርልኝ፤ እንኳን ላክልኝ” አለና እንገናኝ አለኝ ተገናኝተን አወራንና ወደ ቀረፃ እንግባ ተባለ፡፡ ቀረፃው ግን ቆየ፡፡
ለምን ቆየ?
ሶሚክ አስቦበት አሰላስሎ አውጥቶ አውርዶ ነው የሚሰራው በፈጣሪ የሚመራ ልጅ ነው፡፡ በየክረምቱ ለአባይ ብዙ ይባል ነበር- ለግድቡ፡፡ ክረምቱ አለፈ አልደረሰም፡፡ አራት አምስት ወር ሆነው፡፡ ከዚያ ተነስቶ አልበም እንስራ አለ፡፡ አንድ ሁለት ብለን “እናትዋ ጎንደር” አሰራ ምናምንኛ ነው የተቀረፀው፡፡
ተው እንጂ?
የምሬን ነው፡፡ ሁሉም ሰው በዚህ ዘፈን ስለሆነ በደንብ ያወቀኝ የመጀመሪያዬ ይመስለዋል፤ ግን አይደለም፡፡ “ፍየሌን ነብር በላት”፣ “ትዝታ”፣ ሌሎቹ የሰማሻቸው ናቸው የቀደሙት፡፡ በአልበሙ ያልተካተቱ በቁጥር ሁለት አልበም የሚወጡ ያለቀላቸው ብዙ ስራዎች አሉ፡፡ አይነታቸውም ሁሉ ነገር በዚህ አልበም ከተካተቱት ይለያል፡፡ በአጠቃላይ ኮሶሚክ ጋርም የተገናኘነውና እዚህ የደረስነው በህዳሴው ግድብ ስራ ነው ማለቴ ነው፡፡
ከህዝብ ጋር በጣም የተዋወቅህባቸውን “እናትዋ ጎንደር” እና “ካሲናው ጎጃም”ን ያቀናበረልህ እስራኤል ማረፉን ሰምተናል ብዙ ሰውም ሲያዝን ነበር፡፡ እስራኤልን ምን ገጠመው? በህይወት ቢኖርስ አልበሙን በሙሉ ያቀናብር ነበር ወይ? እሱ ካረፈስ በኋላ ከማን ጋር ሰራህ?
በመጀመሪያ የሰራኋቸው “እቅፍ አርጊኝ በናትሽ”፣ “በላይ ዘለቀ” እና የአገውኛው “እርግብ ዳባኔ” የተሰኙ ዘፈኖች አሉ፡፡ እነዚህ ዘፈኖች መጀመሪያ ቀበሌሽ፣ ከዚያ ከተማሽ፣ ከዚያ ክልልሽ እየሰማቸው ይመጣና ከዚያ ነው አገር አቀፍ የምትሆኚው፡፡ ከላይ የገለፅኩልሽ ዘፈኖች እዚያው አባይ ማዶ ነበሩ፤ በነገራችን ላይ፡፡ “በላይ ዘለቀ”ን አሻሽዬ ሰርቼ ነው በአልበሙ ያካተትኩት፡፡ ከዚያ “እናትዋ ጎንደር” እና “ካሲናው ጎጃም” በጣም ምርጥ ሆነ፡፡ ወደ እስራኤል ስመጣ ህልፈቱ በጣም የሚያሳዝነኝ ነው፡፡ ሳስታምመው ነበር አልሆነም አንድ ልጅ አለችው፡፡ እሱን የምክሰው ልጁን በማሳደግ ነው፡፡ ከአልበሙም ዘጠኙን ዘፈኖች አቀናብሮ ነው ያለፈው፡፡ “ትዝታውን”፣ “እናትዋ ጎንደርን”፣ “ካሲናው ጎጃምን”፣ “አባይን እስኪ ስሚው” እነዚህን ሁሉ ሰርቶ ነው ያረፈው፡፡ ሌሎቹን ሶስቱን ቢን አንዴ የተባለ ልጅ ሰራ ሰለሞን ሀይለማሪያም  ሁለቱን ሰራ፡፡ እስራኤል ምን አገኘው ላልሽኝ ታሞ ነበር፡፡ ህንድ ለህክምና ተልኮ ነበር ተለፋ ተለፋ አልተቻለም፡፡ “እናትዋ ጎንደር” ሲለቀቅ እኔ እሱን እያስታመምኩት ነበር፡፡ “ካሲናው ጎጃም”ን ከለቀቅን በኋላ ሌላውን አዘጋጅቶ በዳታ አድርጎ ነው ያረፈው፡፡ እንዳልኩሽ በወለዳት ልጅ እንካሰው በሚለው ነው እንጂ የምፅናናው ስለ እስራኤል ሳስብ በጣም አዝናለሁ፡፡ ምክንያቱም ብዙ መስራት የሚችል የተለየ ተሰጥኦ ያለው ጀግና ልጅ ነበር፡፡ ተደማምጠን መልካም አመለካከትን ተጋርተን ያለ ኢጎ ተናበን ነበር የምንሰራው፡፡ ነፍሱን ይማረውና፡፡ በእርግጥ የአሁኑም ቢን አንዴ የወሎውንና “አስቻለ” የተሰኘውን የሠራ ጀግና ልጅ ነው መቼም። የስራውን ከፍታ ሳውንዱን ሰምተሽዋል፡፡ በጣም ተናበን እየሰራን ነው፡፡ እድለኛ ነኝ መሰለኝ ሰለሞን ሀይለማሪያም ደግሞ ከቴአትር ቤት ጀምሮ ያሰለጠነኝ ሰው ነው፡፡ ሪትም አያያዝ ብትይ… ምን በደንብ አሰልጥኖኛል፡፡ አሁንም እኛ የመሰረትነው “ቡር ቧክስ” ባንድ አስተባባሪ ነው፡፡ ሦስቱም አብረውኝ የሰሩት ምርጥ የምትያቸው ናቸው፡፡ ማሲንቆውን የተጫወተው እንድሪስ ሀሰንም ቢሆን አለ የተባለ ልጅ ነው፡፡ እነ አቡ ገብሬ፣ ብርሃኑ ሞላና እነመሰለ እምቢልታ ተጫዋች፣ እነ ዘሪሁን ሁሉንም ብጠቅስ ጊዜውም አይበቃ። በደንብ ተቀናጅተን ስለሰራነው መሰለኝ ተዋጥቶልናል። እግዜር ያሳይሽ አሁን እምቢልታ እዚህ የለም፣ ትግራይ ብቻ ነው ያለው፡፡ እምቢልታ የሚነፋ አጥተን እደምንም ነው ያካተትነው፡፡
በእኔ መረዳት በአልበሙ የኢትዮጵያ የባህል ሙዚቃ መሳሪያ ሰፊውን ድርሻ ይዟል፡፡ ዘመናዊ መሳሪያ በአልበሙ ውስጥ ብዙ ቦታ ያገኘ አልመሰለኝም። ልክ ነኝ?
በጣም ልክ ነሽ!
ታዲያ በዚህ ልክ ሙዚቃን የሚያነግስ የሙዚቃ መሳሪያ እያለን ለምን የውጪው ሙዚቃ ላይ ሙጭጭ ማለት አስፈለገን ትላለህ?
በአልበሙ ላይ ትዝታው ላይና የበርታው ሙዚቃ ላይ ሳክስ አስገብተናል። እና ፒያኖ ላይቭ አለው። ከዚያ በተረፈ 95 በመቶው በአልበሙ የተካተቱ ዘፈኖች ህይወት በባህላዊ መሳሪያ ላይ የተመሰረተ ነው፡፡ የእኔን ቁጭት ልንገርሽ፡- ሰፈሬ ስድስት ኪሎ ነው አሁን፡፡ አንዳንዴ እህቴ ጋር ወደ ቦሌ ጎራ ካላልኩ በስተቀር ያው አላገባሁም፤ ወ/ሮ ተሰሩን ስሚው፡፡ ታዲያ የምኖርበት ሰፈር የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲው በታላቁ የዜማ ሊቅ ስም የተሰየመው “ያሬድ ሙዚቃ ት/ቤት” አለ። ቅዱስ ያሬድን በደንብ ፕሮሞት ስላላደረግነው የዓለም ቲፎዞ ወደእነ ሞዛርት አዳላ እንጂ ከእነሞዛርት የቀደመ የዜማ ሊቅ ያለን እኛ ነን፡፡ እነሞዛርት ፕሮሞት ስለተደረጉ ገነኑ፡፡ ታዲያ ያሬድ ሙዚቃ ትምህርት ቤት የቅዱሱን የሊቁን ስም ይዞ አንድም ቀን ተማሪዎቹን በባህላዊ ሙዚቃ አስመርቆ አያውቅም፡፡
አሃ ታዲያ እነ ጋሽ ዓለማየሁ ፋንታን የመሰሉ አንጋፋ የባህል ሙዚቃ መምህራን ያሬድ ውስጥ ምንድን ነው የሚሰሩት?
እየውልሽማ… እነጋሽ ዓለማየሁ ፋንታ ማይነር ነው የሚያስተምሩት፡፡ ለምሳሌ ፒያኖ ሜጀር ትማሪና ማይነር ማሲንቆ ወይም ሌላ ነገር ትወስጃለሽ። የባህል ሙዚቃ በሜጀር ደረጃ በያሬድ ሙዚቃ ት/ቤት አይሰጥም፡፡ እኔ ባህል ዘመናዊ በሚባለው አባባልም አላምንም፡፡ የኢትዮጵያና የውጪ የሙዚቃ መሳሪያ ብዬ ነው የምጠራውም። የምቀበለውም። አንድም የኢትዮጵያ ሙዚቃ ተጫዋች መድረክ ላይ ከሚታዩት  ከያሬድ የወጣ የለም፡፡ በልምድ ነው የሚጫወቱት፡፡ ኢትዮጵያዊ የሙዚቃ ት/ቤት ሆኖ፣ የያሬድን የዜማ ሊቁን ስም ይዞ የኢትዮጵን የሙዚቃ መሳሪያ የማያስተምር መሆኑን ሳስብ፣ የሰማይ ስባሪ የሚያህል ሳቅ ነው የሚፈጥርብኝ፡፡ ምርጥ ምርጥ የኢትዮጵያ የሙዚቃ መሳሪያ ባለሙያዎች እያሉ ከዚያ የወጣ ተማሪ ስታነጋግሪ በትሪምፔት ዲግሪዬን ይዣለሁ ይልሻል፡፡ ብቻ አገሩ ሰው እንደሌለው መደረጉ ይቆጨኛል፡፡
ስለዚህ ቁጭትህን ለመወጣት ነው “አስቻለ”ን በኢትዮጵያ ሙዚቃ የሞሸርከው?
በትክክል! እኔ ለምሳሌ የተለያየ ድምጽ ያላቸው ከቅል የተሰሩ ስድስት ክራሮች አሉኝ፡፡ እና ክራሮችን ሳያቸው ያሳዝኑኛል፡፡
ታዲያ ይሄ ሁሉ ቁጭት ካደረብህ ዘንዳ፣ የኢትዮጵያ ሙዚቃ ት/ቤት የመክፈት ንሸጣስ የለህም?
የረጅም ጊዜ እቅድ አቅጄ አላውቅም። በእጄና በጊዜዬ ላይ ያለውን ነገር በደንብ እሰራለሁ፤ እየሰራሁ መሄድ ነው ደስ የሚለኝ፡፡ እንጂ ብከፍት ደስ ይለኛል፡፡
አሁን ለመክፈት ምን ያግድሃል?
አሃ ገና  አሁን ቁጥር አንድ ላይ ነኝ፡፡ ማለቴ ገና ጅማሪ ላይ ነኝ፤ የብቃት የተወዳጅነትና ሌሎች ነገሮችን አሳድጌ 40 እና 50 ቁጥር ላይ ፈጣሪ ካደረሰኝ ያኔ ይሆናል እንጂ፤ አሁን ላይ ሆኜ እከፍታለሁ፤ እንዲህ አደርጋለሁ ማለት ግብዝነት ነው፡፡ አሁን ላይ ከት/ቤቱ በፊት የኢትዮጵያ የሙዚቃ መሳሪያን ባንድ እንዴት አስተባብረን መድረክ ላይ እናብቃው የሚለውን ባስቀድም ነው ደስ የሚለኝ፡፡ አሁን ያ አልበሙ ላይ ያማረውና የተቀናጀው የሀገራችን የሙዚቃ መሳሪያ በባንድ ደረጃ ተዋህዶ እንዴት ጣዕም ይፍጠር የሚለው ነው የሚያሳስበኝ፡፡
ወደ ሙዚቃዎችህ እንምጣ፣ “እንገር ወሎ”፣  “እመት ሸዋ”፣ “አድዋ”፣ “ወ/ሮ ተሰሩ እንደምን አደሩ”ን “በላይ ዘለቀ”ን፣ “ትዝታው”ን ሌሎችንም በደንብ ሳዳምጥ ነበር። ከ”እንገር ወሎ” እንጀምር?
ይቻላል።
እኔ እንገር የማውቀው ላሞች ሲወልዱ የመጀመሪያ ወፍራሙ ቢጫ መልክ ያለው ቅድመ ወተቱን ነው፡፡ ሴትም ስትወልድ የመጀመሪያው ልጁ የሚጠባው እንገር እንደክትባት እንደሚቆጠር ሳይንስ ይናገራል፡፡ እንገር ለጤና እንደክትባት ነው፣ ይጣፍጣል፤ መልኩም ያምራል። እንዴት ነው ወሎን “እንገር” ያልከው?
እየውልሽ በጣም ትክክል ነሽ፤ “እንገር” ወተቱ ነው ያ ወተት የሚሰጠው ከአምላክ ነው፡፡ በትክክል ተናግረሽዋል እንደክትባት ይቆጠራል፤ ልጁ እንዲጠነክር ጤናው እንዲስተካከል አምላክ ቀምሞ የስራው ነው እንገር፡፡ ወሎን እንዴት “እንገር” አልከው፤ ላልሽኝ ቃል አጣሁ ወሎን የምገልፅበት እንደገና ደግሞ አዳምጥ አዳምጥና አዳምጥ የሆነ ሀሳብ ብልጭ ይልልኛል፡፡
“ቁኒ ተቀባብታ የኔ ስለውላዋ
የተነደፈ ጥጥ እንገር ነው ገላዋ”፡፡ ይላል። የተነደፈ ባዘቶ ጥጥ አይተሸ ታውቂያለሽ? ጥራቱ ንጣቱ። እንደገና እንገር ጣፋጭም መድሃኒትም ነው። እንገር ብዙ ትርጉም አለው፡፡ የለፋንበት ግጥም ነው። ወሎ የአራቱ ቅኝት መፍለቂያ፣ የውበት፣ የጀግንነት፣ የደግነት የፍቅር፣ የመንዙማ የቅዳሴው ሁሉ መገኛ ነው። ይህንን ሁሉ የቦረና፣ የከሚሴ፣ የራያ፣ የሰቆጣ፣ የመሃል ወሎን ሁሉ… በስድስት ደቂቃ ለመግለፅ መሞከር ምጥ ነው መቼም።
“ፈረንጅ ደሴ ገባ ቁንጅናሽን ሰምቶ
ላብሽን አንቆርቁሮ ሊያሰራው ነው ሽቶ” ነው‘ኮ ያልከው…
ይሄ ግጥም መጀመሪያ ሌላ ነበር አላረካ ሲለኝ ነው እንደገና ይሄን የፃፍኩት። እንዳልኩሽ ለወሎ ቃል አጥሮኝ ነው እንጂ ብዙ ሊባልለት ይገባ ነበር።
…. ይቀጥላል።

…ደግነትና ቅንነት ቆመው ቢሄዱ አስፋው ናቸው…”

በአሜሪካ  ዋሽንግተን ዲሲ በሚገኘው የጆርጅ ዋሽንግተን ዩኒቨርስቲ ሆስፒታል ህክምናውን ሲከታተል ቆይቶ ባለፈው ቅዳሜ ጥር 4 ቀን 2016 ዓ.ም ከሌሊቱ 9 ሰዓት ላይ ያረፈው የኢቢኤስ ቴሌቪዥን የመዝናኛ ፕሮግራም አዘጋጁና አቅራቢው አስፋው መሸሻ አስከሬን ነገ ወደ ኢትዮጵያ እንደሚገባ ተነግሯል። እዚህ አዲስ አበባ የቀብር ሥነ-ስርዓቱን የሚያስፈጽም ኮሚቴ ተዋቅሮ ዝግጅት እየተደረገ መሆኑ የተጠቆመ ሲሆን፤ የቀብር ሥነ-ስርዓቱ ከነገ ወዲያ ሰኞ እንደሚከናወን ተገልጿል።
ተወዳጁ የሬዲዮና ቴሌቪዥን ፕሮግራም አዘጋጁና አቅራቢው አስፋው መሸሻ ከኢቢኤስ የቴሌቪዥን ጣቢያ አስቀድሞ በኤፍኤም አዲስ 97.1 “አይሬ”  የሙዚቃ ፕሮግራሙ ዕውቅናና ተወዳጅነትን ማትረፉን ይታወቃል። ከዚያም በኢቢኤስ ይተላለፍ ከነበረው “ኑሮ በአሜሪካ” እስከ “እሁድን በኢቢኤስ” መሰናዶ ድረስ በብዙዎች ዘንድ ተወዳጅነትን አትርፏል።
አስፋው መሸሻን በሥራ ባልደረባነትና በጓደኝነት ለ20 ዓመታት ገደማ የሚያውቀው በአሜሪካ የኢቢኤስ ባልደረባ ጋዜጠኛ አበበ ፈለቀ ለቪኦኤ በሰጠው ምስክርነት፤ “…ደግነትና ቀናነት በእግር ቆመው ቢሄዱ አስፋው ናቸው…” ብሏል።
አስፋው በአሜሪካ  በህክምና ላይ ሳለ ያስተዋልኩት የህዝብ ድጋፍና ፍቅር ከአዕምሮዬ በላይ ነው ሲል የተናገረው ጋዜጠኛ አበበ ፈለቀ፤ “ሆስፒታል መጥቶ ልጠይቅህ ላስታምህ ከሚለው ባሻገር… በፀሎትም በገንዘብም…. በስልክም በመንፈስም… ሁሉም ሰው አብሮት ነው የቆመው” ብሏል። “አስፋው በህዝብ ፍቅር ታጅቦ ነው የኖረውም ያለፈውም” ሲልም ምስክርነቱን ሰጥቷል።
ካለፈው ረቡዕ ጀምሮ በአሜሪካ የስንብትና የሽኝት ፕሮግራም እንደሚደረግለት ለሬዲዮ ጣቢያው የገለፀው አበበ ፈለቀ፤  ጥር 13 ቀን 2016 ዓ.ም የአስፋው መሸሻ አስክሬን ወደ ኢትዮጵያ እንደሚላክ ጠቁሟል።
ከአባቱ አቶ መሸሻ አስፋውና ከእናቱ ወ/ሮ ዘነበወርቅ አሻግሬ ሃምሌ 19 ቀን 1959 ዓ.ም የተወለደው አስፋው መሸሻ፤ የአንድ ልጅ አባት ነበር።የአዲስ አድማስ ጋዜጣ ዝግጅት ክፍል፣ በአንጋፋው የሬዲዮና ቴሌቪዥን ፕሮግራም አዘጋጅና አቅራቢ አስፋው መሸሻ ህልፈት የተሰማውን ጥልቅ ሃዘን እየገለፀ፤ ለቤተሰቦቹ፣ ለስራ  ባልደረቦቹና ለወዳጆቹ ሁሉ መጽናናትን ይመኛል። ፈጣሪ ነፍሱን በአፀደ ገነት ያኑርለት።

ም/ቤቱ ሁለቱ አገራት አለመግባባታቸውን በንግግር እንዲፈቱ መክሯል
የሶማሊያ ባለሥልጣናት ጦርነት ቀስቃሽ ዛቻዎችን መሰንዘር ቀጥለዋል

የአፍሪካ ህብረት የሰላምና የፀጥታ ምክር ቤት ባለፈው ረቡዕ ጥር 8 ቀን 2016 ዓ.ም በኢትዮጵያና በሶማሊያ መካከል የተፈጠረውን ውጥረት አስመልክቶ ውይይት ያደረገ ሲሆን፤ የውጭ  ሃይሎች በሁለቱ አገራት መካከል ጣልቃ ከመግባት እንዲቆጠቡ አሳስቧል። ምክር ቤቱ የቀድሞው የናይጄሪያ ፕሬዚዳንት ኦሉሴጉን ኦባሳንጆ ውጥረቱን ለማርገብ ጣልቃ ገብተው ውይይት እንዲያስጀምሩ ህብረቱን ጠይቋል።ሶማሊያ፤ በቅርቡ ኢትዮጵያ ከሶማሊላንድ ጋር የደረሰችው ስምምነት ሉአላዊነቷን የሚጥስ መሆኑን በመግለፅ ውድቅ ያደረገችው ሲሆን፤ አሁንም ድረስ በኢትዮጵያ ላይ ዛቻና ማስጠንቀቂያ በይፋ መሰንዘሯን ቀጥላለች።
ኢትዮጵያና ሶማሊላንድ በቅርቡ በተፈራረሙት የመግባቢያ ሰነድ መሰረት፤ ሶማሊላንድ ለኢትዮጵያ የባህር በሯን የምታከራይ ሲሆን፤ ስምምነቱ ወታደራዊ ትብብርንም ያቀፈ ነው ተብሏል። ሶማሊላንድም በምላሹ ከአትራፊው የኢትዮጵያ አየር መንገድ አክስስዮን እንደምታገኝ ተነግሯል። ኢትዮጵያ ወደፊት ለሶማሊላንድ የአገርነት ዕውቅናም ልትሰጥ እንደምትችል ተሰምቷል።የአፍሪካ ህብረት የሰላምና የፀጥታ ምክር ቤት ባለፈው ረቡዕ ባካሄደው ስብሰባው፤ ኢትዮጵያም ሆነች ሶማሊያ በህብረቱና በዓለማቀፉ ህግ መሰረት ውጥረቱን እንዲያረግቡ ጥሪ አቅርቧል።
ምክር ቤቱ በዚህ ስብሰባው በህብረቱ የኢትዮጵያ መንግሥት ተወካይ አምባሳደር አየለ ሊሬና የሶማሊያው አቻቸው አምባሳደር አብዱላሊ ዋርፋ አስተያየትን አድምጧል ተብሏል። ምክር ቤቱ ከስብሰባው በኋላ ባወጣው መግለጫም፤ የውጭ ሃይሎች በሁለቱ የህብረቱ አባል አገራት መካከል ጣልቃ ከመግባት እንዲቆጠቡም አሳስቧል።
ሁለቱ አገራት ያላቸውን የጎረቤትነት መንፈስ ከሚያውክ ተጨማሪ ተግባር አንዲቆጠቡ ያሳሰበው ምክር ቤቱ፤ አለመግባባታቸውን በንግግር እንዲፈቱም መክሯል።ኢትዮጵያ ከሶማላንድ ጋር የደረሰችውን ስምምነት ተከትሎ፣ በኢትዮጵያና በሶማሊያ መካከል የተፈጠረውን ውጥረት ለማብረድ በየአቅጣጫው የተለያዩ ጥረቶች እየተደረጉ ቢሆንም፤ ከሶማሊያ መንግስት ከፍተኛ አመራሮች በኩል ጦርነት ቀስቃሽ የሆኑ ጠንካራ አስተያየቶችና ዛቻዎች እየተሰነዘሩ ይገኛሉ።የሶማሊያ ፕሬዚዳንት ሐሰን ሼክ ሞሃመድ ባለፈው አርብ ጥር 3 ቀን 2016 ዓ.ም በአንድ መስጊድ ውስጥ ከተካሄደ የጸሎት ሥነ-ስርዓት በኋላ ባደረጉት ንግግር፤ “ከዚህ ቀደም የወረራ ሙከራቸውን ተከላክለናል፤ ከዚህ ቀደም አሸንፈናቸዋል፤ አሁንም እናሸንፋቸዋለን” ብለዋል።
የሶማሊያ ጠ/ሚኒስትር ሐምዛ አብዲ በበኩላቸው፤ ከኢትዮጵያ ጋር ጦርነት ውስጥ ለመግባት ዝግጁ መሆናቸውን ባለፈው ቅዳሜ መናገራቸው ተዘግቧል።
“… ወደ ሶማሊያ ግዛት አንድ ኢንች ለመግባት ቢሞክሩ፤ አስከሬኖችን ይዘው ወደ አገራቸው ይመለሳሉ።” ብለዋል፤ ጠ/ሚኒስትሩ።በሁለቱ አገራት መካከል የተፈጠረው ውዝግብና ውጥረት ክፉኛ ያሳሰበው የአፍሪካ ህብረት የሰላምና የጸጥታ ም/ቤት ባለፈው  ረቡዕ ባደረገው ስብሰባ፤ የውጭ ሃይሎች በሁለቱ አገራት መካከል ጣልቃ ከመግባት እንዲቆጠቡ አሳስቦ፣ የቀድሞው የናይጄሪያ ፕሬዚዳንት ኦሉሴጉን ኦባሳንጆ ውጥረቱን ለማርገብ ንግግር እንዲያስጀምሩ ለአፍሪካ ህብረት ኮሚሽን ሊቀ መንበር ጥያቄ አቅርቧል።

ከዕለታት አንድ ቀን በአንድ መንደር በየዕለቱ የሚፈጠር አንድ ችግር ነበር፡፡ የችግሩ መንስዔ በየማታው እየሰከረ የሚመጣ አንድ ወንደላጤ መኖሩ ነበር፡፡
የሚፈጥረው ዋንኛው ችግር ልክ እሱ ሲመጣ የመንደሩ ውሾች መጮህ መጀመራቸውን ሲሆን “በእኔ ላይ በእኔ ላይ ነው የምትጮሁት? ማን መሰልኳችሁ? ሁሌ ስመጣ ቅንጣቢ ስጋ የምሰጣችሁ እኮ ነኝ? በዓመት በዓልማ ማነው አስቦ ስጋ ይዞላችሁ የሚመጣው? ልክ እንደ ዛሬ ማለቴ ነው!?”
ውሾች መጮሃቸውን አላቋረጡም፡፡  ያ ሰካራምም እንደ ወትሮው ድንጋይ ይለቃቅምና መወርወር ይጀምራል፡፡ ይስታቸዋል - በስካር ዐይንና በስካር እጁ በመሆኑ፡፡ በአካባቢው ያለውን የብረትም የቆርቆሮም በር ያናጋዋል፡፡
የብረትና የቆርቆሮውን በር እንዲሁም ውሾቹን ያልፍና መንገዱን ይቀጥላል፡፡ ሌላ ብረት በር ፊት ለፊት ይደርሳል፡፡ ሌሎች ውሾችም ብቅ ብቅ ይሉና ይጮሁበታል፡፡
“ኧረ በፋሲካ ምድር አታሳብዱኝ?” ይልና ድንጋዩን ሰብስቦ መወርወሩን ይቀጥላል፡፡ ይስታል፡፡ የሌሎቹን በር ይመታል፡፡ እንዲህ እንዲያ እየሆነ ለወራት ሰፈር ሲበጠብጥ  ይከርማል፡፡ የሰፈሩ ሰው በዚህ ሰው ጉዳይ ላይ መመካከር ጀመረ፡፡
“እንደው የዚህን ሰካራም ነገር ምን ብናደርግ ይሻላል?”
አንዱ፡-
“በራችን የተሰበረብን ሰዎች እንሰብሰብ”
ሁለተኛው፡-
“ምን ልንሆን?!”
ሦስተኛው፡-
“እንመካከርና መፍትሄ እንድናመጣ ነዋ?!”
አራተኛው፡-
“ይሄ በጣም መልካም ሀሳብ ነው! የሰፈሩ ሰው ይንቀሳቀስ፡፡ ይምከርና መላ ያብጅ እንጂ እስከመቼ አንድ ሰው ተሸክመን እንዘልቃለን? ላንዴም ለሁሌም ዘላቂ ዘዴ እንዘይድ!”
ሁሉም በሀሳቡ ተስማሙ፡፡
አንድ እሁድ ማለዳ የመንደሩ አዛውንቶች እንዲያገኙት ቀጠሮ ተያዘ፡፡
ተገኘላቸው፡፡
የፋሲካ እለት  ጠዋት፡፡
እንዲህ አሉ የአዛውንቶቹ ተወካይ፡-
“አየህ አንተ የመንደራችን ህዝብ ውድ ወንድም ነህ፤ ስለዚህ ቀረብ ብለን ልናወያይህ ነው አመጣጣችን”
እሱም፡-
“ስለምን ጉዳይ ልታማክሩኝ አሰባችሁ?”
ሽማግሌዎቹ፡-
“ወንድማችን መቼም መጠጥ ጎጂ መሆኑን ማንም አያጣውም፡፡ አንተም ጎጂነቱን አትስተውም!”
እሱም፡-
“እንዴታ! እንዴት እስተዋለሁ?”
ሽማግሌዎቹ፡-  “አየህ አምሽተህ ስትመጣ ከውሾች ጋር ትጣላለህ፤ ድንጋይ ትወረውራለህ፡፡ የሰው በር ትመታለህ፡፡ ይሄ ሁሉ የመነጨው አምሽተህ በመምጣትህ ምክንያት ነው፡፡ ስለዚህ ወንድማችን ሆይ እባክህ አታምሽ!”
እሱም፡-
“ውይ አባቶቼ እንዲያው በከንቱ አደከምኳችሁ! አሁንማ ማምሸት ትቼ! አሁንማ ተመስገን ነው፡፡ እያነጋሁ ነው የምገባው!”
***
ኢትዮጵያ ትንሳኤ ያስፈልጋታል፡፡ የዲሞክራሲ መስዋዕትነቷ አብቅቶ የተባ ትንሳኤ ያሻታል፡፡ የወገናዊነት በደሏ ይሻር ዘንድ ትንሳኤ ያስፈልጋታል፡፡ የፍትህ እጦት መከራዋ ይወገድ ዘንድ ትንሳኤን ትሻለች፡፡ በእድሜዋ ያልገጠማትን ዓይነት የመፈናቀል አደጋዋ ለአንዴም ለሁሌም ይታገድ ዘንድ “ኢትዮጵያ ታበፅዕ እደዊሃ ሀበ እግዚአብሄር” መባሉ ዛሬም መኖር አለበት (ኢትዮጵያ እጆቿን ወደ እግዚአብሄር ትዘረጋለች እንደማለት ነው)፡፡ ፍትህ ርትህ ያልተጓደለባት፣ ለአንዱ እናት ለአንዱ እንጀራ እናት እንዳትሆን፣ ልጆቿ እንዲታገሉላት ትፀልያለች፡፡ የትምህርት ስርዓቷ ደክሞ ከሚያንቀላፋበት ቀና ብሎ ወደ ጥንቱ ጠንካራ ንቃቱ ይመለስ ዘንድ አማልከቱን ትማለዳለች፡፡ የህዝብ ጤነኝነት የአገር ጤና ነውና የጤናም ትንሳኤ ያሻታል፡፡ ከለማበት የተጋባበት እንዲሉ፣ የጎረቤት አገሮች በሽታ እንዳይተላለፍባትና ድንበሯ ይከበር ዘንድ ህዝቧ አንድነቱን እንዲጠብቅ፣ የውስጥ ጥንካሬው በይዘትም በቅርፅም እንዲታነፅ አራሽ፣ ቀዳሽ፣ ተኳሽ ልጆቿ እንዲበረቱ አምላኳን ትማጠናለች፡፡  የህዝቦቿ ልቦና በቅንነትና በፍቅር እንዲከፈት ፀሎቷን ማሰማት አለባት፡፡ ከሚያወሩ አፎች ይልቅ የሚሰሩ እጆች መድህኖቿ መሆናቸውን ልጆቿ  ማወቅ አለባቸው፡፡
ኢትዮጵያ በመታገል እንጂ በእድል እንደማትለማ መገንዘብ ግዷ ነው፡፡
ዛሬም ከገሞራው ጋር
“..ነገሩ አልሆን ብሎ ሁኔታው ሲጠጥር
ጠጣሩ እንዲላላ የላላውን ወጥር”
…ማለት አለባት፡፡
መሪዎች የህዝብ የልብ ትርታ  ማዳመጥ አለባቸው፡፡ ፖለቲካዊ ቅሬታውንና ኢኮኖሚያዊ ብሶቱን ከልብ ማዳመጥ ዋና ነገራቸው ነው፡፡ ህዝብም ጉዳዩን ሁሉ ለመሪዎች ጥሎ እጆቹን አጣጥፎ መቀመጥ የለበትም፡፡ አገር “ቀኗ ሲደርስ ትቀናለች” የምትባል የምኞት አስኳል አይደለችም፡፡ “መንገዶች ሁሉ ወደ ልማት ያመራሉ” ብሎ መመኘት በስራ ካልታገዘ ምኞት ብቻ ነው፡፡ ዱሮ ስለ ትግል ሲወራ “ጉዟችን ረዥም ትግላችን መራራ ነው” ይባል ነበር፡፡ ይሄን ሲሰብክ የቆየ ካድሬ ቀና ጎድሎበት ታሰረ፡፡ መፈክሩን ፈተሸና፤
“ይሄ አግባብ አይደለም፡፡ መራራ ከሆነ አጠር ይበል፣ ረዥም ከሆነ ደግሞ ጣፈጥ ይበል እንጂ መራራም ረዥምም ማድረግ በጭራሽ በጎ አካሄድ አይደለም!” አለ አሉ፡፡
ጊዜ የማይለውጠው ነገር የለም፡፡ ለጊዜ ጊዜ መስጠት ብቻ ነው የሚጠበቅብን፡፡ ምናልባት ከደራሲ ከበደ ሚካኤል ጋር
“ለሁሉም ጊዜ አለው ብሏል ሰለሞን
እጠይቀው ነበር በተገናኘን
ሞት ራሱ እሚሞት ምን ጊዜ እንደሆነ”
…ማለትም ያባት ነው፡፡
 ከዚህ ቀደም፤
“እናትና አባቴን በጊዜ ቀብሬ
መንግሥት እጦራለሁ አንጀቴን አሥሬ”
…. እንል የነበረውን ቀይረን ለውጡን እንዴት እናግዝ? የሚለውን አቅጣጫ ማሰብ አንድ መላ ነው፡፡
መልካም የጥምቀት በዓል ይሁንልን!!

“TX Cargo Chassis” ዘመናዊ  የጭነት መኪና ለመጀመሪያ ጊዜ ለኢትዮጵያ ገበያ ቀረበ

በተሽከርካሪው ኢንዱስትሪ የሚታወቁት ሲኖትራክ ኢንተርናሽናልና ሃንሰም ግሩፕ፣ እጅግ ዘመናዊና የላቀ አቅም ያለው ነው ያሉትን “TX Cargo Chassis” የተሰኘ አዲስ የጭነት መኪና ለመጀመሪያ ጊዜ ለኢትዮጵያ ገበያ ማቅረባቸውን አስታወቁ፡፡

ሲኖትራክ ኢንተርናሽናልና ሃንሰም ግሩፕ፣ ይህን ያስታወቁት በዛሬው ዕለት ከቀኑ 8 ሰዓት ጀምሮ በሂልተን ሆቴል በተዘጋጀ ሥነሥርዓት ላይ ነው፡፡

ኩባንያዎቹ ለአገሪቱም ሆነ በተለያየ ንግድ ላይ ለተሰማሩ ዜጎች ይበጃል ያሉት ይኸው አዲስ የጭነት ተሽከርካሪ፤ ፍጹም አዲስ ግብአቶችን አካትቶ፣ ነገር ግን ለተጠቃሚው በቀላሉ እንዲመች ተደርጎ የተመረተ መሆኑን አረጋግጠዋል፡፡

“TX Cargo Chassis የተነደፈው ልዩና የተቀላጠፈ አሰራርን የሚያግዙ ግብአቶችን በማካተት፣ ብቃትን በማሳደግ እንዲሁም ጊዜንና የጥገና ወጪን በሚቀንስ መልኩ ነው” ብለዋል፤ ኩባንያዎቹ በሰጡት መግለጫ፡፡

ተሽከርካሪው ባለሦስት ድርብ፣ ሙሉ ለሙሉ ብረት የሆነ ጠንካራ መከላከያ የተገጠመለት ሲሆን፤ ይህም መኪናው በማንኛውም ጊዜና በአስቸጋሪ ሁኔታዎች ለሚደረጉ እንቅስቃሴዎች እንዳይበገር ከማድረጉም በላይ የጥገና ወጪን የሚቀንስና የአገልግሎት ዘመኑን የሚያረዝም ነው ተብሏል፡፡

ከ2001 እስከ 2015 ዓ.ም ባሉት ጊዜያት ሲኖትራክ ኢንተርናሽናልና አጋሩ ሃንሰም ግሩፕ በጋራ ከ80ሺ በላይ ተሽከርካሪዎችን ከመሸጣቸውም በላይ ከ400 ሺ በላይ ተዛማጅ  የሥራ ዕድሎችን በሃገር ውስጥ  መፍጠራቸውን በመግለጫቸው ጠቁመዋል፡፡

የደራሲ ቴዎድሮስ መብራቱ "ንሥር እና ምስር"ሁለተኛ ዕትም መጽሐፍ ከሰሞኑ ለአንባቢያን ደርሷል።ደራሲው ሁለተኛው ዕትም መጽሐፉ ተሻሽሎ እንደቀረበም ገልጿል።መጽሐፉን በተለያዩ የመጻሕፍት መደብሮች ታገኛላችሁ።

"ትዝታሽን ለእኔ ትዝታዬን ለአንቺ" መጽሐፍ
ደራሲ እሱባለው አበራ "ፀሐይ ከጨለማዬ ምን አለሽ?" የተሰኘ ሁለተኛ መጽሐፉን ትላንት ረቡዕ ጥር 8 2016 ዓ.ም ለአንባቢያን አቅርቧል።
መጽሐፉን ጃፍርን ጨምሮ በተለያዩ የመጻሕፍት መደብሮች ታገኛላችሁ ተብላችኋል።

መጽሐፉ በዋናነት የኢትዮጵያ ችግሮች፣ መንሥዔዎች እና የመፍትሔ ሀሳቦች ላይ ትኩረቱን ያደርጋል ተብሏል። በአምስት መቶ ብር  ለአንባቢያን ቀርቧል።

Page 7 of 690