Administrator

Administrator


           በቀልደኝነታቸውና በዋዘኝነታቸው ስለሚታወቁት ስለ አለቃ ገብረሃና ብዙ ተወስቷል፡፡
አንዳንዴ እሳቸው ያላሉትም የእሳቸው ተደርጐ ይተረካል፡፡ ለማንኛውም የሳቸው ከተባሉት ጥቂቶቹን እንጥቀስ፡፡
አንድ ቀን አለቃ ወደ ገበያ ይሄዳሉ፤ አሉ፡፡
ገበያው ደርቷል፡፡ የአለቃን ተረበኛነት የሚያውቅና የሚወድ አንድ ተጨዋች ሰው ይመጣል፡፡
ሰውዬው እግሩ ገደድ ያለ ነው፡፡
አለቃን እንዳገኛቸው፤
“አለቃ እንደምን ዋሉ?” አላቸው፡፡
“ደህና ውለሃል ወዳጄ?” አሉ አለቃ፡፡
“ከየት እየመጡ ነው?”
“ሰው ሳስታርቅ ውዬ፣ የፍንጥር ምሣ በልተን ገና አሁን ተለያየን፡፡”
እግረ-ጠማማው ሰውዬ፣ አለቃ አፍ ላይ የተልባ ፍሬ ያያል፡፡ አለቃ ምሣ የበሉት በተልባ ወጥ መሆኑን በመገመት፤ ጥቂት ሊተርባቸው ፈልጐ፤
“ለመሆኑ ተልባ ስንት ስንት ዋለ፤ አለቃ?” አለ፡፡
አለቃም ወደ ሰውዬው እግር መልከት ብለው፤
“በጠማማ ጣሣ ሰባት ሰባት ነው” አሉት፡፡
*   *   *
አንድ ቀን ደግሞ፤ ጐጃም ውስጥ፣ አንድ ሰው ከወደ ሞጣ ሲመጣ አለቃ ያገኙታል፤ በእጁ በትር ይዟል፤
አለቃ - “እንደምን ዋልክ ወዳጄ?”
ሰውዬው - “ደህና እግዚሃር ይመስገን፡፡ ደህና ውለዋል አለቃ?”
አለቃ - “ደህና ነኝ፡፡ ከወዴት ትመጣለህ ወዳጄ?”
ሰውዬው - “ከምፃ” አላቸው…(“ጣ” የሚባለው “ፃ” አለው ማለት ነው)
አለቃ - “ምን ይዘሃል?”
ሰውዬው - “ድግፃ”…(ድግ “ጣ” የዛፍ ዓይነት ነው)
አለቃ - “በል መንገድ መትቶሃል፤ ምሣ እንብላ” አሉትና ተያይዘው ወደ አለቃ ቤት ሄዱ፡፡
ምሣ ቀርቦ እየበሉ ሳሉ፣ ሰውዬው ወጡ ጨው እንደሌለው ልብ ብሏል፡፡
ወደ አለቃ ቀና ብሎ፤
“ትንሽ ፀው ያስፈልጋል - ፀው አምጡ; አለ፡፡
ይሄኔ አለቃ፤
“አይ እንግዲህ! “ፀ”ን ምን ብንወዳት እወጥ ውስጥ አንጨምራትም?” አሉት፡፡
*   *   *
አንድ ቀን አለቃ ከሚስታቸው ከወይዘሮ ማዘንጊያ ጋር እየተጨዋወቱ ሳሉ፤ አንድ የጐረቤት ህፃን ልጅ ወደእነ አለቃ ቤት ይመጣል፡፡
ልጁ ረባሽ ነው፡፡
በአንፃሩ የእነ አለቃ ገ/ሃና ልጅ ደግሞ ወደ ጐረቤት ቤት ሄዷል፡፡
ረባሹ የጐረቤት ልጅ የወይዘሮ ማዘንጊያን ብርጭቆዎች ሲነካካ ሁለቱን ሰበረባቸው፡፡
ወይዘሮ ማዘንጊያ በጣም ተናደዱና፤
“አሁንስ ይሄን ልጅ ምን ባደርገው ይሻላል አለቃ! እጁን በእሳት ላቃጥለው እንዴ?” አሉ፡፡
አለቃ ገ/ሃናም፤
“ማዘንጊያ፣ እዛም ቤት እሳት አለኮ!” አሉ፡፡
*   *   *
ጥፋት ለማንም አይበጅም፡፡ ለጥፋት መቆም መጨራረስንና ውድመትን እንጂ የሚያመጣው ረብ - ያለው ነገር አይኖርም፡፡ ለረዥም ዘመን የኖረ ጐረቤትን ማጥቃትም ሆነ ማጥፋት ምላሹን መርሳትና የእርስ በርስ እልቂትን መደገስ ነው!
“የማ ቤት ጠፍቶ፣ የማ ሊለማ
የማ ቤት ጠፍቶ፣ የማ ሊበጅ
የአውሬ መፈንጫ፣ ይሆናል እንጅ”
የተባለው ለተራ ፉከራና ቀረርቶ እንዳልሆነ ትክክለኛ አዕምሮ ያለው ሚዛናዊ ሰው ልብ ይላል፡፡
ወትሮውንም ቢሆን፤
ለጥፋት የቆመ፤ ዐይኑ ያለጥፋት አያይም፡፡
የጐረቤቱ ዕድገትና ልማት አይጥመውም፡፡
“እኔ ዶሮ ሳረባ አይቶ፣ ጐረቤቴ ሸለ-ምጥማጥ ያረባል!” ይላል አበሻ፤ ምቀኛን ሲገልፀው፡፡
ልማትን ልፋት ለማድረግ፣ ለውጥን ነውጥ ለማድረግ መሻት ከንቱና እኩይ ተግባር መሆኑን ልብ ያለው፣ ልብ የሚለው፣ ማንም ጅል የማይስተው፣ ጉዳይ ነው፡፡
ሉዓላዊነቱንና ህልውናውን ቸል ብሎ ሲነካ ዝም የሚል፣
“ባለቤቱን ካልናቁ
አጥሩን አይነቀንቁ!” የሚለውን ምሣሌያዊ አነጋገር የማያውቅ ብቻ ነው!
አያሌ መንግሥታት ሁለት ዋና ነገሮችን ሲስቱ ለውድቀት ይዳረጋሉ፡- አንድም የዕብሪትና የንቀት፤ አንድም የድንቁርናና የአጓጉል ዕውቀት ሰለባ ሲሆኑ፡፡ የሁሉም ውጤት ድቀት ነው!
“ዐባይ ሞልቶ፣ ጣና ሞልቶ፣
ላጨኝ በደረቁ
          እራሴን ሳያመኝ፣
          ነደደኝ መናቁ!”…
(“መ” እና “ና” ይጠብቃል) የሚልን ህዝብ እሳቤ የማያውቅ የውጪ ኃይል ታሪክንም፣ ጂኦግራፊንም፣ ባህልንም የዘነጋ ነው፡፡
የውስጥን ችግር ለማስታገስ፣ ወደ ውጪ መተንፈስ የአብዛኛዎቹ የአፍሪካ መንግሥታት የፖለቲካ መላ ነው፡፡ ሆኖም የዘመነ - ብሉይ እንጂ የዘመነ - ሐዲስ ፖለቲካ አይሆንም፡፡ “አሮጌ ወይን በአዲስ ጋን” ነው፡፡ በሁሉም ረገድ ክፉና ደግ ያየች እንደኛ ያለች አገር፤ ከእነ ህዝቦቿ ህልውናዋን ለማስጠበቅ፣ ብልህነትን ከትዕግሥት፣ ዕውቀትን ከድፍረት አቅፋ የምትራመድ ታሪካዊ አገር ናትና፣ ዋና ማዕቀፏን ዲፕሎማሲያዊነቷን አድርጋ የምትጓዝ የጀግኖች ምድር ናት:: ባንድ ፊት ድህነትን፣ ባንድ ፊት ኮሮናን እየተዋጋች በጥኑ ልብ የምትቀጥል፤ አንድ አራሽ፣ አንድ ተኳሽ፣ አንድ ቀዳሽ ያሏት አገር ናትና ያሻችውን ሳትቀዳጅ፣ የጀመረችውን ዳር ሳታደርስ ከቶም ወደ ኋላ አትልም!

Saturday, 18 July 2020 16:37

የግጥም ጥግ

    ይድረስ ለኛ

ይድረስ ለእኛ ለኔና ላንተ
ዘመን በትውልድ ክር ባንድ ስቦ ላቋጠረን
የዚያ ሰፈር ኤሊቶች፣ የዚህ ሰፈር ኤሊቶች እየተባባልን
በህዝብ ስም እየማልን፣ በወገን ስም እየማልን
አገር አቃጥለን ለምንሞቅ
በእናቶች ሃዘን ሰቆቃ፣ በአባቶች እንባ ለምንስቅ
ይድረስ ለእኛ ለኔና ላንተ
 ለነቃነው ለበቃነው
ክፉ ዘመን ክፉ ሥርአት፣ በጥፋት ላስተሳሰረን
በጥላቻ የተሰራ፣ በቂም በቀል የበቀለ ሴራና ሸፍጥ ለወረረን
ክህደት- ቅጥፈት- መሰሪነት፣ የህሊና አይናችንን ልባችንን ለሰወረን
ከሰው ተራ ወርደን ከፈጣሪ ተገዳድረን
ሃገር ሽቅብ የምትረጨው እንባ የማይገደን
ይድረስ ለእኛ ለኔና ላንተ
አክቲቪስት በሚባል ማዕረግና ካባ ተጠቅልለን
ከአገር በላይ … ከህግ በላይ…  ተቆልለን
ሰዎችን ከኑሮ  ነቅለን፣ ፍትህን ጫማችን ስር ጥለን
በአገር ላይ ፍቅርን መግደል ፤ ተስፋን መግደል፤ ደስታን መግደል፤ ሰላምን መግደል
እንደ ውሃ ጥም ለቀቀለን….ይመስለኛል ለኔና ላንተ
ድንቁርና፣ ዕብሪት፣ ትዕቢት፣ ክፋት ላስታጠቀን
ነገ ታሪክ በእውነት ችሎት በደም ቃል ለሚጠይቀን
ወንድምዬ፤ ምን መልስ አለህ ?--
(ከገጣሚና ጸሃፌ ተውኔት ጌትነት እንየው ;ይድረስ ለኛ; ዘለግ ያለ ግጥም የተቀነጨበ)

 አዜብ ወርቁ ፀሐፌ ተውኔት፣ ተርጓሚ፣ ተዋናይት፣ መምህርት፣ ጋዜጠኛና  መድረክ መሪ ናት፡፡ በአሁኑ ወቅት የአርትስ ቴሌቪዥን ዋና ሥራ አስፈፃሚ ሆናም በመስራት ላይ ትገኛለች፡፡ በቅርቡ ‹‹እረኛው ሐኪም›› የተሰኘ መፅሐፍ ከፈረንሳይኛ ወደ አማርኛ መልሳ ለንባብ አብቅታለች፡፡ ስምንቱ ሴቶች የተሰኘ ቴያትርን ከፈረንሳይኛ ወደ አማርኛ ተርጉማ በዳይሬክተርነት ለዕይታ አብቅታለች፡፡ የ#ዳና; እና  "ገመና 2" ተከታታይ የቴሌቪዥን ድራማ ደራሲም ናት፡፡ የአዲስ አድማስ አምደኛ ደረጀ በላይነህ በመጽሐፏ፣ በሕይወቷ፣ በጥበብ ፍልስፍናዋና በሙያዋ ዙሪያ አነጋግሯታል፡፡ እነሆ፡-


             በተመሳሳይ እድሜ ላይ ብንገኝ ወይም የአንድ ቤተሰብ አካል ብንሆንም፤ በቁመታችን በመልካችን፣ በጉልበታችን፣ በእምነታችን፣ በመንፈሳችንና በአስተሳሰባችን እንለያያለን፡፡ በልዩነታችን ውስጥ ግን ታላቅ የአንድነት ሃይል አለ፡፡ ሃይላችን ሁላችንም እግዜርን መምሰላችን ነው፡፡ “በመልኬ ፈጥሬአችኋአለሁ” ብሏልና:: እግዜር ማለት ሁለንተናዊ ተፈጥሮ ማለት ነው…ምዕሉ በኩልከ!!
ወዳጄ፡- አንድ አጭር ሰው በረዣዥሞች ወይም ረዥም ሰው በአጫጭሮች መሃል ሲገኝ ምቾት ካልተሰማው ተፈጥሮን አልተረዳትም፡፡ አጭሩ እንደ ለንቋሳ ማሽላ ፍሬ ለወፍ ወይም ለወንጭፍ ቀድሞ ሲሳይ አይሆንም፡፡ ረዥሙ ደግሞ የሞላ ኩሬን ተዘናክቶ ሊያቋርጥ ወይም ከበለሷ ጫፍ ላይ የተንጠለጠሉትን በለስ ፍሬዎች በቀላሉ ሊያወርዳቸው ይችላል፡፡ ሁለቱም የየራሳቸው ፀጋ አላቸው፡፡የቁመት ነገርን ካነሳን፣ አንድ የድሮ አማርኛ ተረት መጽሐፍ ላይ “ፍርደ ገምድል ዳኛ“ የሚል ታሪክ አለ፡-
ተምትም የተባለው ሰው ባጠፋው ጥፋት በስቅላት እንዲሞት ይፈረድበታል:: አስፈፃሚዎቹ ፍርዱን ለመተግበር ወደ መግደያው ቦታ ሲወስዱት የሰውየው ቁመት ከመስቀያው እኩል ሆነና ተቸገሩ:: ወደ ንጉሱ ተመልሰው ያጋጠማቸውን ሲነግሩት፤ “ከዘመዶቹ መሃል አጭር የሆነውን መርጣችሁ ስቀሉ“ አላቸው:: ቁመት ዠርጋጋው ተምትምን ሲያድን፣ ምንም ያላጠፋውን ዘመዱን ደግሞ ሞት አስፈረደበት፡፡ እንደ ንጉስ ዳዊት ብልህ የሆኑ አጫጭር ታሪኮችም ሞልተዋል፡፡
ወዳጄ፡- ሰዎች በአካልም ሆነ በአእምሮ የተባረኩበት ግለሰብአዊ ፀጋ አላቸው:: ችሎታ ወይም ብቃት የምንለው ሃይል ከዚህ ፀጋ ይመነጫል፡፡ ከትንኝ ጀምሮ እስከ ትልቁ እንስሳ ድረስ በዚህ “መክሊት“ ተክህኖ አለው፡፡ የታንኳ ቀዛፊው ብላቴናና በታንኳ ላይ ተሳፍረው የነበሩትን ፕሮፌሰር  ጨዋታ ቀንጭበን እናስታውሳለን፡-
“ወዳጄ ተምረሃል?“
“አረ በጭራሽ“
“እንደው ምንም?“
“ምንም“
“አዝናለሁ“ አሉ ፕሮፌሰሩ ከልባቸው:: …ሁለቱ ሰዎች እየተንሸራሸሩ ሲጫወቱ አያድርስ እንደሚባለው ሆነና ሃይቁ በማእበል ተመታ፤ታንኳቸው ራደች፡፡ ምስኪኑ ቀዛፊ ተደናግጦ ፕሮፌሰሩን፡-
“ዋና ይችላሉ?" በማለት ጠየቃቸው።
“አረ በጭራሽ!"
“እንደው ምንም"  
“ምንም"
“አዝናለሁ" አለ በልቡ፤ የማዕበሉን መክፋት አይቶ፡፡ ከዛ በኋላ የሆነውን አስቡት፡፡ ዲተርሚኒስቶች ሁለቱም ተረቶች በህይወት መዝገብ ላይ እንደተጻፈው የተከናወኑ ናቸው ይሉናል፡፡ አንተ ምን ትላለህ?
ወዳጄ፡- ተረግሞ ወይም ተመርቆ የተፈጠረ ማንም የለም፡፡ ዕርግማንና ምርቃት የራስን ፀጋ የመረዳት፤ የራስን ማንነት የመቀበል ወይም በተቃራኒው የማሰብ ጉዳይ ነው፡፡ የራስን ጸጋ አለማወቅ በሌላው ላይ የመቅናት ስሜት ያሳድራል:: ቅናት የተፈጥሯችን አካል ነው፡፡ ፈጣሪ እንኳን “እኔ ቀናተኛ አምላክ ነኝ" ማለቱ ተፅፏል፡፡ ቅናት እርግማን የሚሆነው ወይም ጥፋት የሚያስከትለው እራሳችንን ስናሳንስ ወይም የበታችነት ስሜት በውስጣችን ሲያቆጠቁጥ ነው፡፡ ቃየል በወንድሙ ላይ የተነሳሳው እራሱን ዝቅ አድርጎ ስለገመተ ነበር፡፡
ወዳጄ፡- የዝቅተኝነት መንፈስ አጉል ቅናት ይወልዳል ያልነው ያለ ምክንያት አይደለም:: አጉል ቅናት ጥላቻን፤ ጥላቻ ደግሞ ጥፋትን ያስከትላል፡፡ በራሱ የሚተማመን ሰው አይቀናም፡፡ በራሱ የሚተማመን ሰው እሱ የሌለውን ወይም ያጣውን፤ ሌሎች የተቀበሉትን ወይም ያላቸውን እየመረመረ፤ እየመዘነ ይማርበታል፡፡ ተበለጥኩኝ በሚል ቅዠት ሌላውን ማጥላላት አላዋቂነት ነው፡፡
ህውሃት በተሰነጠቀበት “ገማን፣ በሰበስን፣ ቦናፓርቲዝም ምናምን" በተባለበት ሰሞን የታዘብነው የቅናት ፖለቲካ ቦታውን ቀይሮ ዛሬ ላይ የተቀናባቸው ሲቀኑ፣ ታሪክ እራሱን ሲደግም ማየት ያስገርማል፡፡ የቅናት ፖለቲካ የወጡበትን የወረዱበትን ትግልና ጓዳዊነት፣ ጎን ለጐን ሆነው የተዋጉለትን ዓላማና አንድነት በአንድ አረፍተ ነገር ዜሮ ድምር ያደርገዋል፡፡ ይህ ጉዳይ በህወሃት ብቻ ሳይሆን በኢህአፓ፣ በመኢሶን፣ በቅንጅት፣ በኦነግ፣ በመኢአድ፣ በአንድነት፣ በኢዴፓ፣ በኦብኮ፣ በኢህአዴግና በሌሎች የፖለቲካ ፓርታዎችና እንደ መምህራን ማህበር በመሳሰሉት የሙያ ማህበራት ውስጥ ተከስቷል፡፡
መለስ ዜናዊ ላይ የቀረበው ክስ ሃሳብን በተሻለ ሃሳብ መሞገትን መሰረት ያደረገ አልነበረም። በዘርና በቅናት የተቃኘ የቅናት ፖለቲካ እንደነበር የወቅቱ ምክትል ጠ/ሚኒስትር አቶ አዲሱ ለገሰ ሲናገሩ አድምጠናል። መለስም በብሔራዊ ቴሌቪዥን ቀርበው በዋልታ ኢንፎርሜሽን ድርጅት ስራ አስኪያጅ በነበሩት አቶ ሴኩ ቱሬ ጠያቂነት፡-
’’´ተቀናቃኞች ኤርትራዊ ነዎት እያሉ ነው፤ ምን ይላሉ?’’ ሲባሉ
’’ጥያቄው ማን ምንድን ነው ሳይሆን ማን ምን ሰራ ነው? መሆን ያለበት’’ በማለት  ነበር  የመለሱት፡፡ እንደ  ምሳሌም ጠያቂያቸውን ራሱን፡-
"’አንተ አማራ ነህ፤ ነገር ግን የህወሐት አባል ነህ’’ በማለት ሰዎችን የሚያጸናቸው የዘርና የጎሳ ትስስር ሳይሆን የአላማ አንድነት እንደሆነ ለማስረዳት ሞክረዋል። ይኽውም የጎሳ ፖለቲካ ፉርሽ እንደሆነ በአንደበታቸው የመሰከሩበት አጋጣሚ ነበር። በተግባር አላየነውም እንጂ። በነገራችን ላይ ጥራት በሌለው ትምህርትና አጓጉል ሰርተፍኬቶች አገራችን በታጠነችው ቅናት የወለደው ፖለቲካ ሰበብ አላማችንን እስተቀበለ ድረስ ዘበኛም ቢሆን ሚኒስትር ሊሆን ይችላል ያሉትን ለማካካስ ታስቦ የተደረገ በመሆኑ ነው።
ወዳጄ፡-
ኢትዮጵያውያንን የሚያስጨንቃቸው መሪዎቻቸው የወጡበት ጎሳ ወይም ክልል ወይም ቤተሰብ አይደለም። ኢትዮጵያውያን የሚፈልጉት አድሎ የሌለበት አስተዳደር ነው። የፍትህ ስርአቱን በብቃት የሚያስፈፅሙለትን ሰዎች ነው። መሪዎች እንደ ፖለቲከኛ ለሀገራቸው ሰላም፤ አንድነትና ብልፅግና፣ ጥቅም የሚያስገኝ ዲፕሎማሲያዊ ትግል ካደረጉ፣ እንደ ምሁር ለሳይንስና ለጥበብ ዕድገት መሰረት የሚጥል የትምህርት ስርዓት በማደራጀት የስልጣኔ ፋና ወጊዎችን ካፈሩ፤ እንደ ግለሰብ እርህሩህና የተፈጥሮ ወዳጅ ከሆኑ በቂ ነው።
ወዳጄ፡- አንድ ነገር ልብ በል። “ግለሰቦች ራሳቸውን ይሰራሉ፤ መሪዎችን ግን ህዝብ ይሰራቸዋል ይባላል። ከመልካም ህዝብ ውስጥ መልካም፣ ከሰራተኛ ህዝብ ውስጥ ሠራተኛ፣ ከጀግና ህዝብ ውስጥ ጀግና፣ ከሰለጠነ ህዝብ ውስጥ የሰለጠነ መሪ ይወጣል። ነገር ግን ሁሉም ሕዝብ በአንድ ጊዜ መልካም፣ ሰራተኛ፣ ጀግና፣ የሰለጠነ ሊሆን አይችልም። መሪ ግን ሁሉንም በመሆን ያስተባብራል። ይህን ችሎታና ታጋሽነት ነው የቃለ አብነት ፀጋ (wisdom) የምንለው።
ወዳጄ፡- እያንዳንዱ ሰው የራሱ ብርሃን፣ የራሱ ጨለማ እና ንጋት አለው። መስታወት ፊት የቆመች ድመት የነብር ፊት ከታያት ወይም የተገላቢጦሽ ከሆነ ቅዠት ነው። እራስን ያለ ቦታ ማስበለጥም ሆነ ማሳነስ ተፈጥሯዊ ፀጋን አለመረዳት ይሆናል። ሰዎች ታሪካቸውን የሚሰሩት እራሳቸው በመረጡት መስመር አይደለም። እንደውም ተከታታይነት ያላቸው ሁኔታዎችና የመጡበት ኮሮኮንች መንገድ ነው ሰዎቹን የሚሰራቸው ይባላል። “Men could make their own history, but not under circumstances chosen by themselves, but under the circumstances encountered, given and transmitted from the past” ይላል ካርል ማርክስ፤ The 18th brumier of laos Bonaparte በሚለው መፅሐፉ፡፡
ወቅታዊ ጉዳዮች ስናተኩር የአባይ ግድብ ከትላንት ወዲያ ጀምሮ ውሃ ለመሙላት እንደጀመረ የሳተላይት ምስሎች እንደሚያሳየው ከአሜሪካን ድምፅ ሬድዮ ሰምተናል። እንደዚሁም በሚቀጥሉት ዓመታት ሀገራችን ከፍተኛ ኢኮኖሚያዊና ማህበራዊ እድገት እንደምታስመዘግብ የሚያረጋግጡ ጥናቶች እየወጡ መሆናቸው ተነግሯል። ወዳጄ፡- ኢትዮጵያ አትቆምም!!
እንዲሁም በዓለም ላይ አለ ብዙ ነገር
በዚህ ቢሉት በዚያ መሆኑ የማይቀር --- ይሉናል ከበደ ሚካኤል። በዚህም ቢሉን በዚያ ወደ ኋላ አንመለስም።
“ኑ! መስቀሉን የተሸከመውን እናግዝ" የሚለን ደግሞ ዶስቶቪይስኪ ነው… እንደ ቤን ኸር!!


          "በስንቱ እንቃጠል እናንተ?! የሕይወታችንንና የንብረታችንን ደህንነት ለምን አይነት ሰዎች ውሳኔና አመራር እንደሰጠን ማሰቡ እንዴት ያስፈራል? እንዴት ተስፋ ያስቆርጣል? ከሞትን፣ ከተቃጠልንና ንብረታችን እንዳይሆን ከሆነ በኋላ ሟች ሊቆጥሩ፣ አመድና ፍርስራሽ ሊመለከቱ የሚተጉ ሃላፊዎች ምን ያደርጉልናል?;

              ነዳጅና ማቀጣጠያ ጎማ ተሸክሞ ቤትና ንብረትህ ላይ እሳት ሊለቅ በመንጋ የመጣን አካል እንዲከላከሉልህ፣ ከጥቃትና ከጥፋት እንዲጠብቁህ ለሚመለከታቸው የመንግስት ሰዎች “ድረሱልን፣ አትርፉን” ስትል “ስብሰባ ላይ ነን” ተብሎ ስልክ ሲዘጋብህ…..እና ቤት ንብረትህ ያለ ሃይ ባይ እየተዘረፈና በእሳት እየጋየ፣ መንግስት ባለበት ሀገር፣ የሚደርስልህ መጥፋቱን ስታውቅ እንዲህ ያለው ጥያቄ እየደጋገመ ያቃጭልብሃል፡- ስብሰባ ምንድነው? የመሰብሰብ ፋይዳውስ?
የእኛ ሃገር ሃላፊዎች ዋና ስራቸው የሚመስላቸው ስብሰባ ሳይሆን አይቀርም፡፡ እኔ እንደሚገባኝ ሌላውም ሰው እንደሚረዳው፤ የምንሰበሰበው የሚጠበቀውን ግብ በተሻለና በተቀናጀ መንገድ ለመድረስ ወይም ለማሳካት ነው፡፡ ሃሳብ ተለዋውጦ፣ የስራ ድርሻ ተከፋፍሎና ተናብቦ የተፋጠነ ውጤት ለማስገኘት ነው:: እንጂ ልንጠብቀውና ልናድነው የሚገባ ንብረትና የሰው ሕይወት ከወደመና ከጠፋ በኋላ አመድና ፍርስራሽ ላይ ለመድረስ አይደለም፡፡
በመንጋ የመጣ የጥፋት ኃይል ‘ቆይ ስብሰባ ላይ ነን ስላሉ እስኪጨርሱ ጠብቁ’ ተብሎ እንደማይቆም ማገናዘብ የማይችሉ አመራሮች ያሉን ጉደኛ ህዝቦች እኮ ነን፤ እኛ፡፡ የማወራው በቅርቡ የአርቲስት ሃጫሉን ግድያ ተከትሎ በጂማ ከተማ የተከሰተውን ሁኔታ ተንተርሼ ነው፡፡ ሰሚ ካለ ግን የኡኡታዬ ጉዳይ ከአንድ ከተማ በላይ የሚሻገር ወሰነ ሰፊ ችግር ነው፡፡ በጂማ ከተማ ከፍተኛ የሚባለው ውድመት የደረሰበት የዶሎሎ ሆቴል ባለቤት አቶ ፀሐይ አበበ በሚዲያም እንደገለፁት፤ አገልግሎት መስጠት ከጀመረ ገና አራት አመት ገደማ የሆነው ይህ ሆቴል፤ ለከተማዋ አይን የሚባል ነበር፡፡ የዶላሩ ዋጋ ዛሬ ካለበት በግማሽ ያህል የወረደ በነበረበት ወቅት ከመቶ ሚሊዮን በላይ ገንዘብ የፈሰሰበት ሆቴል፤ የረባ ሲኒማ ቤት እንኳን ለሌላት ከተማ አራት መቶ ወንበሮች ያሉት እጅግ ዘመናዊ ሲኒማ ቤትን ጨምሮ ከሰባ በላይ አልጋዎችንና ስፓን አካትቶ የተገነባ ባለ ሦስት ኮከብ ሆቴል ነበር፡፡ የዚያ ሆቴል መኖር ለባለቤቱ ካለው ጥቅም በላይ ለከተማዋ ስምና መነቃቃት ያለው ፋይዳ የላቀ እንደሆነ ከተማዋን የሚያውቅ ሁሉ ይመሰክራል፡፡ በእርጅናና በመዘንጋት ውስጥ ስትዋልል ለኖረች ከተማ፤ ንቃትና መታወሻ እንደሆናትም አለመመስከር አይቻልም፡፡
ሆኖም ጂማ እንደነ አቶ ፀሐይ ያሉ ንብረታቸው እየወደመና በስጋት እየሸሹም “ጂማን እወዳታለሁ”፣ “ጂማ ከተማዬ ናት የተቃጠለችው” የሚሉ በአዚማም ፍቅሯ የናወዙ ሰዎች (ነዋሪዎች) ቢኖሯትም፤ በሚያስቡላትና በሚጨነቁላት  የመንግስት ሃላፊዎች በኩል ግን የታደለች አይደለችም:: አዋራ ከለበሱ፣ ዝገት ካጠቆራቸው ቆርቆሮዎች፣ በላስቲክና በድንጋይ ክምር ከተደጋገፉና ከተወታተፉ የመንገድ ዳር ጎስቋላ ቤቶችና ሱቆች ሳትላቀቅ ለዘመናት የምናያት "የእኔ" ብሎ ከራሱ ከፍታና የኪስ ሙላት ባሻገር ከፍ ሊያደርጋት የሚተጋ መሪ በማጣቷ ነው፡፡ ዛሬም የሆነው ከዚህ የተለየ አይመስለኝም፡፡ አንድ የሚመለከተው አካል "ሆቴሌን ሊያቃጥሉት ነውና ድረሱልኝ" ሲባል "ስብሰባ ላይ ነን" የሚል ምላሽ የሚሰጠው ከምን በመነጨ ነው? የስብሰባው መዳረሻ ውድመቱ ነው ወይንስ ውድመቱን መከላከል? ማንም ባለ ጤነኛ አእምሮ የሆነ ሰው እንደሚገምተው፤ በዚያን እለት የሚደረግ ስብሰባ፤ ስለ መከላከሉ ወይንም ስለ ወቅቱ ሁኔታ ነው ሊሆን የሚገባው:: እንዲያ ከሆነ ደግሞ ከበር ለደረሰ አጥፊ ለጊዜው የመመለስ፣ የመከላከል ትዕዛዝና ስምሪት እያደረጉ ስብሰባው መካሄድ የማይችለው በምን የተነሳ ነው? የነገሮችን አዝማሚያ ተከትለን መልሱን እንገምት ካልን፣ መድረሻችን ሌላ ነውና የሚሆነው ግዴለም መልሱን እንተወው፡፡ ግን ዝም ብለን እንጠይቅ፡፡ የስብሰባው ስፍራ የትም ይሁን የት እንደው ከከተማው ምክር ቤትና ከዋናው ፖሊስ ማዘዣ (ጣቢያ) እንኳን ብንነሳ እስከ ዶሎሎ ሆቴል ያለው ርቀት ከአስራ አምስትና ሃያ ደቂቃ በላይ የሚወስድ ሆኖ ነው አመድ ላይ የደረሱት? ወይንስ ጉዳዩ በስብሰባው ላይ አጀንዳ ሆኖ ቀርቦ በድምፅ ብልጫ ተወስኖ ነው?
በስንቱ እንቃጠል እናንተ?! የሕይወታችንንና የንብረታችንን ደህንነት ለምን አይነት ሰዎች ውሳኔና አመራር እንደሰጠን ማሰቡ እንዴት ያስፈራል? እንዴት ተስፋ ያስቆርጣል? ከሞትን፣ ከተቃጠልንና ንብረታችን እንዳይሆን ከሆነ በኋላ ሟች ሊቆጥሩ፣ አመድና ፍርስራሽ ሊመለከቱ የሚተጉ ሃላፊዎች ምን ያደርጉልናል? መቅደም ያለበትን ማስቀደም የማይችሉ፣ ያለ ስብሰባና የበላይ አካል ቀጭን ትዕዛዝ ባላቸው የሃላፊነት ደረጃ ይበልጡንም ሰዋዊ ስሜት ሕዝብን ሊጠብቁና ሊከላከሉ የማይንቀሳቀሱ አመራሮች ለምን ያስፈልጉናል? ሰዎቹ ከዚህ የለቅሶ ደራሽነትና የሃዘን መግለጫ አውጪ ኤክስፐርትነት የሚላቀቁት መቼ ነው? ኧረ ሰው ጠማን! ሰው ራበን! አንዳንዴ እንኳን ከአዛዥና ታዛዥ ተዋረዳዊ ትብታብ ወጥቶ ስለ ሰብአዊነትና ስለ ሰው ደህንነት ሲል በራሱ ውሳኔም ቢሆን እርምጃ የሚወስድ ሰው! በገዛ ህሊናዊ መመሪያና ትዕዛዝ ጭምር የሚመራ ሰው!
እኔ የምለው ከስብሰባ በፊት የሚወሰድ ህይወትና ንብረትን ከጥፋት የመከላከል እርምጃ ወንጀል ሆኖ ያስጠይቅ ይሆን እንዴ? ግን ማን ሊመልስልኝ ነው ይህን ሁሉ የምጠይቀው? እንደው ሁኔታዎችን ያገናዘበ መሆን ቢችል እንኳን የሚለውን ለመጨመር እንጂ ያለ ስብሰባ የመወሰን፣ ያለ መመሪያ እርምጃ የመውሰድ አቅሙም ድፍረቱም በሌላቸው  እንደተሞላንማ ግልፅ ነው፡፡ ያ ባይሆን ኖሮ በየቦታው የምንሰማና የምናያቸው ጥፋቶችና ወንጀሎች ተደላድለው ባልነገሱብን ነበር፡፡ ሁሉም በየደረጃው ለህዝብ ንብረትና ህይወት ያለ አድልዎ፣ ያለ ልዩነት የመወሰን ብሎም የመጠየቅ ግዴታና ሃላፊነት ቢኖርበት ኖሮ እንዲህ ባልሆንን ነበር፡፡ በዘር፣ በፓርቲ በገለመሌ ተሰብስቦ ከመተሻሸትና ከመወሻሸቅ ይልቅ እንደ ግለሰብ ራስን ችሎ በመቆም ብቃታቸው፣ ሃላፊነት በመውሰድ ብሎም በመጠየቅ ወኔና ድፍረታቸው ወደ ስልጣን የወጡ የመንግስት አመራሮች ቢሆኑ ኖሮ ለዚህ ባልበቃን ነበር፡፡
ማንም እንደ ግለሰብ መቆም፣ ማሰብ የማይችል፣ ፈሪና አቅመ ቢስ ሁሉ ነው ሀገር ለማመስ በቡድን፣ በዘር፣ በፓርቲ የሚወሸቀው:: የእንደዚህ አይነት ፈሪዎች ሴራና ዱላ ደግሞ ለነጥሎ መጠየቅ፣ ለለይቶ መምታት ስለማይመች ጥፋቱ ሁሌም አደገኛ ነው:: ልፋትና ተስፋን፣ እምነትና ፍቅርን ሳይቀር ያሳጣል፡፡ የጂማው ባለሃብት ላይ የደረሰው ይሄው ነው፡፡ ሌላው የረሳትን፣ የሸሻትን፣ ሰርቶ ያገኘውን ገንዘብ ሰብስቦ ወደ ሌላ የሚሄድባትን ከተማ፣ ከተማዬ ብሎ የምትነሳ የምትወሳበትን ከፍ ያለ ነገር ቢያቆም፣ የማይገባ ነገር እንዳደረገ ተቆጥሮ ንብረቱን ማውደም፣ ልፋትና ተስፋውን መና ማድረግ፣ እምነትና ፍቅሩን ገደል መክተት ተፈረደበት፡፡ ከዚህ ጥፋት ምንድነው የሚገኘው?
ከድርጊቱ ፈፃሚዎች መልሱ እንደማይገኝ ብዙዎቻችን እናምናለን፤ እነሱም አያውቁትምና:: በነጂዎች የሚመራው የወጣት መንጋ እንደ ሰው፣ ህሊናና ማሰብያ አእምሮ እንዳለው ፍጥረት ሳይሆን እንደ መገልገያ ቁስ (መሳሪያ) ሆኖ የተቀረፀና የተሰራ በመሆኑ እንዲያ አድርገው በሰሩት አካላት አብዝተን እናዝናለን:: የሰው ወግ ማዕረግ (ምክንያታዊ ሆኖ ማሰብና ማገናዘብ) ስለ ማጣቱ እንብሰለሰላለን፡፡ ወደ ሰብአዊነት ያልፈጠረበት አውሬነት ተራ ስላወረዱት እንቆጫለን፡፡ በሰሩ፣ በተለወጡና በበለፀጉ ሰዎች እንዲነቃቃና እንዲተጋ ከመሆን ይልቅ እንዲቀናና ለጥፋት እንዲነሳሳ በመደረጉ እንከፋለን፡፡ መሆን እንደሚገባው ሳይሆን እንዲሆን እንደሚፈልጉት አድርገው በሰሩትና እንዳሻቸው በሚነዱት ጨካኞች ገና ወደፊትም እናፍራለን፡፡
ይሄ ሆኖ ነው እንጂ ጤነኛ አእምሮና ንፁህ ልቡና የያዘ ማንም ሰው፣ ለሚኖርበት ከተማና ሃገር ጌጥና ከፍታ የሆነን ነገር ለማጥፋት አይታዘዝም ነበር፡፡ ያንን ሆቴልም ሆነ ሌላውን ማንም ይስራው ማን፣ ለምንኖርበት አካባቢ ተጨማሪ ነገር በመሆኑ ብቻ ሊጠበቅ ነበር የሚገባው:: ለባለቤቱ ኪስ ከሚገባው ጥሬ ገንዘብ በላይ ከተማዋ ተጠቃሚ እንደሆነች ማሰብ አለመቻል ድንቁርና ነው፡፡ እዚያ አካባቢ ላይ በመሰራቱ ብቻ ለአካባቢው ነዋሪ የሚኖረው ፋይዳ ነበር የሚልቀው:: አስፍቶ ለማሰብ፣ አዙሮ ለማየት እድልና አቅም እንዳይኖረን ያደረጉን የፖለቲካ ቁማርተኞቻችን ግን ለሚነዱት ወጣት ይህን አይነግሩትም፡፡ ለራሳቸው አላማ በጭፍን መንዳትን እንጂ ምን እያሳጡት እንደሆነ እንዲያገናዝብ ቀዳዳ እንኳን አይተዉለትም:: የምኞትና የህልም ግንብ እንጂ መሬት የወረደች አንዲት የመንደር ድልድይ ስለ መገንባት አስበው አያውቁምና የተገነባን እንደ ማፍረስ የሚቀላቸው ነገር የለም:: እያፈረሱና እያጠፉ ያሉትን ተቋማት እንኳንና በተግባር በሃሳብ የመገንባት አቅም የሌላቸው ስለመሆናቸው ከጭፍን ተግባራቸው በላይ ማሳያ አያስፈልገንም:: ቀላሉን (ማፍረስን) መምረጥ የቀላሎች መገለጫ ነው፡፡ ወትሮም ለመስራት የማይሞክሩትን ለማፍረስ ይሽቀዳደማሉና:: ከባዱን (መገንባትና ማልማትን) መምረጥ ግን ከፍ ያሉት መታያ ነው:: እነሱ ከ‘እኔ’ አጥር አልፈው ከ‘እኛ’፣ ከብሔርና ሃይማኖት ቆጠራ ርቀው ከሃገር (ከከተማ) ማማ ላይ የቆሙ ናቸውና የድርጅታቸውን መቃጠል ሲገልፁ እንኳን “ከተማዬ፣ ጂማዬ ተቃጠለች” ይላሉ፡፡ “ከእንግዲህ ይህን አይቶ ማን ነው ጂማ ላይ መጥቶ ኢንቨስት የሚያደርገው?” የሚለው ያሳስባቸዋል፡፡ በዚህ ሁሉ ጉዳት ውስጥ ሆነው ስለ ጂማ ፍቅር በእንባ ጭምር ይናገራሉ:: ወይ የሰው ከፍታ! በዚህ የመንጋ ዘመን ግራ ተጋብተን ተስፋ እየቆረጥን ላለን፣ እንዲህ ያሉ ሰዎች መኖራቸውን ማወቁ በራሱ ተስፋ ነውና ይኑሩልን፡፡ ፈጣሪ ያቆይልን፡፡ የእንባቸውን መታበሻ ጊዜም ያቅርብልን፡፡
የዶሎሎ ሆቴልን ባለቤት ንግግርና እንባ ስመለከት “ጂማ እንደ ድመት ልጆቿን ትበላለች” ይል የነበረ አንድ ቀደም ባለው ጊዜ የነበረ የከተማዋ አርቲስት አባባል ነው ወደ አእምሮዬ የመጣው፡፡ እኔ ደግሞ ዛሬ እላለሁ፤ “ጂማ ተስፋና እድገቷን በማይፈልጉና በሚያጓትቱ ድመቶች እጅ ላይ ወድቃለች”፡፡ ከከተማው ፖሊስ ሌላ የምዕራብ እዝ ጦር ማዘዣ (ስሙን ካልተሳሳትኩ) ባለበት ከተማ፤ ያን የሚያህል ሆቴል እንደ ደመራ ነዶ ማለቁ የሚያፀናልኝ ይህንን እንጂ ሌላ አይደለም፡፡
ያልተመለሰ ጥያቄ፣ የጎደለብን ነገር አለ የምትሉ እስቲ በስልጡን ወግ፣ በ21ኛው ክፍለ ዘመን የአስተሳሰብ ልኬት፤ በግልፅ በአደባባይ ቁሙና በሃሳብ ስትሞግቱ፣ በጥያቄ ስትፈትኑ እንያችሁ፡፡ የሚነግራችሁ ሳታገኙ ቀርታችሁ ከሆነ እንንገራችሁ፡- እየተደበቃችሁና እየተሽሎከሎካችሁ ንብረት ላይ እሳት መልቀቅ፣ ምንም የማያውቀውን ማህበረሰብ መግደል፣ ማስጨነቅና ማሸበር ከተራ ውንብድና ያለፈ የጀግንነት ወግ የለውም፡፡ ሃገር መገንባት፣ ከተማ ማልማት ከፖለቲከኞችና አክቲቪስቶች ፕሮፓጋንዳና ቅዠት በላይ የሆነ ከባድ ሃሳብ፣ ከፍ ያለ ተግባር ነው፡፡ ሰርቶ የማሰራት አቅም ባይኖራችሁ እንኳን የተሰራውን የመጠበቅ አቅም ያጣችሁ እናንተስ አስተዳዳሪዎች ትባላላችሁ? ቀድሞ ‘አይሆንም! ተመለስ!’ ከማለት ይልቅ ከሆነ በኋላ ሺዎችን ሰብስቦ ማሰር የቀለላችሁ እናንተ፣ እንዴት ነው የሕዝብ መሪ የምትባሉት? የአርቲስት ሃጫሉ መገደልን ተከትሎ ሁከትና ግርግር እንደሚፈጠር ገምታችሁ ያልተሰናዳችሁ እናንተ፣ እውነት የህዝብ አስተዳዳሪ ናችሁን? ወይንስ የበግ ለምድ የለበሳችሁ ተኩላዎች?
ከጥያቄዎቼ ጎን ለጎን እንዲህ እላለሁ፡- ክቡር ጠቅላይ ሚኒስትራችንና ሌሎች የበላይ አመራሮች ሆይ፤ የሹሞቻችሁን ጉያ አራግፋችሁ ፈትሹልን፡፡ እጅ ወደ ላይ አስደርጋችሁ የሸጎጡትን ሁሉ አራግፉልን፡፡ እንደ መሪ ሳይሆን እንደ ግለሰብ ቢደርስባችሁ የማትታገሱትን ነገር እንድንታገስና እንድንሸከም መወትወታችሁን ተዉን:: ይልቅስ ጫካ ከገባው በላይ በሹመት ወንበሮቻችሁ ላይ ተቀምጠው በስብሰባ እያመካኙ፣ ድንገት ሳንዘጋጅ ሆኖብን ነው እያሉ እንዳልሰማ እንዳላየ መስለው በእሳት የሚያስበሉንን፣ በካራ የሚያሰይፉንን የራሳችሁን ጉዶች አፅዱልን፡፡
(የሆነውና እየሆነ ያለው ካንገበገባቸው የጂማ ከተማ ነዋሪዎች አንዱ ነኝ)


   ደራሲ ከበደ ሚካኤል በታሪክና ምሳሌ ተረቶቻቸውና ግጥሞቻቸው ውስጥ የሚከተለው ወቅታዊና ዘላለማዊ ሆኖ ሲጠቀስ የኖረ ነው (Timely and timeless እንዲሉ)፡፡ ዛሬም ያንኑ ባህሪውን   ጠብቆ ጉልህ ሆኖ ይታያል፡-
አዝማሪና ውሃ ሙላት፣
አንድ ቀን አንድ ሰው፣
ሲሄድ በመንገድ፣
የወንዝ ውሀ  ሞልቶ፣
ደፍርሶ ሲወርድ
እዚያው እወንዙ ዳር፣
እያለ ጎርደድ
አንድ አዝማሪ አገኘ፣
ሲዘፍን አምርሮ
በሚያሳዝን ዜማ ፣
ድምጹን አሳምሮ፤
"ምንነው አቶ አዝማሪ፣
ምን ትሰራለህ…………"
ብሎ ቢጠይቀው፣
"ምን ሁን  ትላለህ ..
አላሻግር ብሎኝ የውሃ ሙላት
እያሞጋገስኩት በግጥም ብዛት፤
ሆዱን አራርቶልኝ
ቢያሻግረኝ ብዬ …"
"አሁን ገና ሞኝ ሆንክ
ምነዋ ሰውዬ!
ነገሩስ ባልከፋ፣
ውሃውን ማወደስ
ግን እንደዚ ፈጥኖ
በችኮላ ሲፈስ
ምን ይሰማኝ ብለህ፣
ትደክማለህ ከቶ
ድምፁን እያሽካካ፣
መገስገሱን ትቶ?!
እስቲ ተመልከተው፣
ይህ አወራረድ
ያልሰማው ሲመጣ፣
የሰማው ሲሄድ?!
ምክር፡- ተግሳጽም ለጠባይ፣
ካልሆነው አራሚ
መናገር ከንቱ ነው፣
ካልተገኘ ሰሚ!
*   *   *
የሚሰማ ካልተገኘ ሲያወሩ ቢውሉ "ነገር ቢያበዙት በአህያ አይጫንም" እንደሚሆን ግለጽ ነው፡፡ ስለ ምንድን ነው የሚወራው? ማለት ብቻ ሳይሆን ለማን ነው የማወራው? ማለት ምንግዜም ተገቢ ነው" በሀገራችን "ያልሰማው መምጣቱ የሰማው መሄዱ" የተለመደ መሆኑ ብቻ ሳይሆን ምንግዜም እንቅስቃሴ መኖሩን አመላካች ነው፡፡ ያልተገላበጠ ያራል የምንለው ያለ ነገር አይደለም፡፡ ጥበብ አስካለን ድረስ ጎርፉን ለማስቆምም  ይቻላል የሚለው ዕሳቤ፤ አንድም የጥበብን መኖር አስፈላጊነት፣ አንድም ደግሞ የጥበብ ሃይል የት ድረስ ሊያድግ እንደሚችል ያስገነዝበናል፡፡
ሃገራችን ክፉውንም ደጉንም፣ ሀገር ወዳዱንም ሀገር ጠሉንም እያስተናገደች እዚህ ደርሳለች፡፡ ዞሮ ዞሮ ከችግር ቋት አልወጣችም፡፡ የፖለቲካ ክስረት፣ የኢኮኖሚ ድቀት፣ ማህበራዊ ውዥንብር  ሁሌም ቀይዶ አንደያዘን ነው፡፡ ከሰራነው ያልሰራነው መብዛቱ መቼም፤ አገር ያወቀው ጸኃይ የሞቀው ጉዳይ ነው! የቤት ስራችን የበዛው ለዚህ ነው፡፡ የተዛባው ሲበዛ በትክክል የማቀድን ሁኔታ ያውከዋል፡፡ ይሄ ደግሞ በፈንታው አፈጻፀሙን መላቅጡን ያሳጣዋል፡፡ ይህንን የመሰለ ምስቅልቅል ሂደት ውስጥ እያለን ኮሮና የመሰለ ተውሳክ፣ ሰላምን የሚያናጋ ነውጥ፣ ልክ የለሽ የስራ አጥነት መብዛት እያለ በኮሮና ሳቢያ የሚሰራውም ሰው አንዳይሰራ መገደዱ በእንቅርት ላይ ጆሮ ደግፍ መሆኑ ወዘተ--- በሃገር ኢኮኖሚ ላይ የሚያመጣው ጣጣ የምበላው ሳጣ ልጄ ጥርስ አወጣ መሆኑን ለማየት 110 ሚሊዮን ህዝብ ባላት አገር አንፃር ማስላትና በችግሩ ማባዛት በቂ ነው፡፡
ከላይ ያነሳነው ችግር ላይ ሌብነት ስንጨምርበት "በደንባራ በቅሎ ቃጭል ተጨምሮ" ከማለት በቀር የምስቅልቅሉን ውል ለማግኘት እንኳ እንቅልፍ የሚያሳጣ ነገር ነው፡፡ መንግስትና የግሉ ሴክተር አይናበቡም ይባላል እንጂ ዋናው አባዜ ያለው የየራስን ንባብ በቅጡ አለማንበብ ላይ ነው! ለዚህ ደግሞ "ለተገቢው ቦታ ተገቢ ሰው ማስቀመጥ" ትክክለኛ መርህ ነው! ያ ካልሆነ ዕቅዱ ሁሉ የግድግዳ ጌጥ ነው የሚሆነው! ማን ሊሰራው ይታቀዳል? እንኳንስ የኢኮኖሚ ዕቅዱማቀፊያ ነው የሚባለው የፖለቲካ ስርዓት የጠራ ዲሞክራሲም ያልተሟሸበት ነው፡፡ ይህን ያህል ዘመን ስለ ዲሞክራሲ ዳዴ ስለ አለመጎልበቱ፣ ህዝቡ መረዳት ስለማቃቱ ስናወጋ ለባህላችን፣ ለአስተሳሰባችን፣ ለአኗኗራችን አግባብ ያለው ዲሞክራሲ ሳይሆን የምዕራቡን ዓለም ዓይነት እያሰላሰልን ነው የኖርነው፡፡
በውጪው ቀመር የተለካው ስፌት ይጠበናል  ይሰፋናል? ሳንል አንድ ቀን ልብስ እንለብሳለን በሚል ተምኔታዊ ህልም ውስጥ ብዙ ባዝነናል፡፡ ለኛ የሚመጥነውን ልብስ የሚሸምን የሌላ አገር ባለሙያ ሳይሆን የኛው ሸማኔ ቢሆን ይመረጣል፡፡ በምዕራቡ ዓለም የተጠመቀ ወይን ጠጅ ቢያንስ እኛ ዘንድ ሲመጣ ጣዕሙ ሊቀየር እንደሚችል ማስተዋል ደግ ነው፡፡
ሌላው የወቅቱ ቁልፍ ጥያቄ፡- "የዘገየ ፍርድ ከሌለ አንድ ነው ነው፡፡" የሚባለው ነው፡፡ ለአንድ ሰሞን የምንጮሃቸው ጩኸቶች ሲውሉ ሲያድሩ እየቆዩ ይላዘዛሉ፡፡ የቡና ስብሃቱ መፋጀቱ መሆናቸው ይቀራል (decaffeinated ይሆናል እንደ እንግሊዞቹ አባባል!) ከነጭራሹ የሚረሱበትም ሁኔታ አለ፡፡ ይልቁንም ጉዳዮቹን ሁሉ በትኩስነታቸው መቋጨት ለአገርም ለህዝብም ለመንግስትም ይበጃል፡፡ ብረትን እንደጋለ ቀጥቅጠው (hit the iron while it is hot) ነው ጉዳዩ!
"ጅራፍ እራሱ ገርፎ እራሱ ይጮህ›› ዓይነት ሁኔታ ተለይቶ አያውቀም፡፡ በፈረንጅኛ አፍ ስንገልፀው፡- "They shout at most against the vices they themselves are guilty of" እንደሚባለው ነው፡፡ አንቺ ታመጪው አንቺው ታሮጪው እንደ ማለትም ነው፡፡
ፍትህ፣ ዲሞክራሲ፣ እኩልነት፣ ግልፅነት፣ ተጠያቂነት፣ ሰላም፣ ሰብዓዊነት፣ ዲሞክራሲ መብት፣ ስነምግባራዊነት፣ ሙያዊነት፣ …..ከቃልነት አልፈው ወደ ተግባራዊነት ተሸጋግረው ልማትና ዕድገት የሚሆኑት፣ እጁን የታጠበና ልቡ የፀዳ ሰው ሲኖር ነው! የሁሉ ነገራችን ማሰሪያው ሰው ነው፡፡ አለበለዚያ "ባሉ ሳይገኝ ሚዜ ታማርጣለች" ይሆንብናል!

 በኮሮና ሳቢያ የከፉ ጥፋቶችን ብታስተናግድም የሚበጃትን መላ ከመምታት ይልቅ አጉል አጉሉን መንገድ መከተሏን የያዘችው አለማችን፣ ቆም ብላ ማሰብና የሚበጀውን መንገድ መከተል ካልጀመረች፣ ከዚህም በላይ የከፋ ነገር ማስተናገዷ አይቀሬ መሆኑ እየተነገረ ነው፡፡
“እጅግ በርካታ የአለማችን አገራት በተሳሳተ መንገድ መጓዛቸውን ገፍተውበታል፤ ኮሮና ቫይረስም የአለማችን ቁጥር አንድ የሰው ልጆች ጠላት ሆኖ ጥፋቱን እያስፋፋ ቀጥሏል!... መደባበቅ አያስፈልግም፤ የማይጠቅመውን ነገር ትተን የኮሮናን ጉዳይ ሙያዊ በሆነ መንገድ በቁጥጥር ስር ለማዋል በአፋጣኝ ርብርብ ካላደረግን በቀር፣ ጉዳዩ የበለጠ አስከፊ እየሆነ መሄዱ አይቀሬ ነው!” በማለት ነበር የአለም የጤና ድርጅት ዋና ዳይሬክተር ዶ/ር ቴዎድሮስ አድሃኖም እቅጩን የተናገሩት፤ የአለማችን የኮሮና ቫይረስ ተጠቂዎች ቁጥር 13 ሚሊዮን መድረሱ በተነገረባት የሳምንቱ የመጀመሪያዋ ዕለተ ሰኞ፡፡
ሰውዬው ሰኞ ዕለት ይህን ካሉም በኋላ፣ ቀናት በተፈራረቁ ቁጥር ቫይረሱ በመላው አለም በፍጥነት እየተሰራጨና ብዙዎችን ለህልፈተ ህይወት እየዳረገ ነው ሳምንቱን ያገባደደው፡፡
የዎርልዶ ሜትር ድረገጽ ዘገባ እንደሚለው፤ ኮሮና ቫይረስ እስካለፈው ሃሙስ አመሻሽ ድረስ በመላው አለም ከ13 ሚሊዮን 780 ሺህ በላይ ሰዎችን ሲያጠቃ፣ በቫይረሱ ለሞት የተዳረጉ ሰዎች ቁጥር ደግሞ ከ559 ሺህ አልፏል:: እስከተጠቀሰው ጊዜ ድረስ አሜሪካ 3,639,653፣ ብራዚል 1,972,072፣ ህንድ 992,746፣ ሩስያ 752,797፣ ፔሩ 337,724 ሰዎች በቫይረሱ የተጠቁባቸው ቀዳሚዎቹ አምስት የአለማችን አገራት ሲሆኑ፣ ከአለማችን አገራት ከፍተኛ ቁጥር ያላቸው ሰዎች ለሞት በተዳረጉባት አሜሪካ የሟቾች ቁጥር ከ140 ሺህ በላይ ማለፉ ተነግሯል፡፡
የኮሮና ቫይረስ ሟቾች ቁጥር በብራዚል ወደ 76 ሺህ የተጠጋ ሲሆን፣ በእንግሊዝ ከ45 ሺህ በላይ፣ በሜክሲኮ ከ37 ሺህ በላይ ሲደርስ፣ ከ28 ሺህ 400 በላይ ሰዎች ለሞት የተዳረጉባት ስፔን በሞት ያጣቻቸው ዜጎቿን ለማሰብ ባለፈው ሃሙስ ባካሄደችው የመታሰቢያ ሥርዓት ወረርሽኙ በአገሪቷ ላይ ያደረሰው ጉዳት ምን ያህል አሳዛኝ እንደሆነ ዘክራለች፡፡
አፍሪካ እና መሰንበቻው
በግንቦት ወር መጨረሻ 100 ሺህ የነበረው የአፍሪካ አህጉር የኮሮና ቫይረስ ተጠቂዎች ቁጥር፣ በሃምሌ መጀመሪያ ላይ ወደ ግማሽ ሚሊዮን ማደጉን ያስታወሰው የአለም የጤና ድርጅት፤ከ35 በመቶ በላይ በሚሆኑት የአፍሪካ አገራት የኮሮና ቫይረስ ተጠቂዎች ቁጥር ባለፈው ወር ብቻ በእጥፍ ያህል ማደጉን ይጠቁማል፡፡
እስካሁን ድረስ በአህጉሪቱ በኮሮና ቫይረስ ከተጠቁት ሰዎች መካከል ከ70 በመቶ በላይ የሚሆኑት በአምስት አገራት ውስጥ እንደሚገኙ የጠቆመው ድርጅቱ፣ በሃምሌ ወር አጋማሽ በመላው አፍሪካ በቫይረሱ ከተያዙት ሰዎች መካከል 75 በመቶ ያህሉ በደቡብ አፍሪካና ግብጽ እንደሚገኙም አመልክቷል፡፡ ቫይረሱ እስካለፈው ሀሙስ አመሻሽ ድረስ በመላው አፍሪካ ያጠቃቸው ሰዎች ቁጥር ከ645 ሺህ ያለፈ ሲሆን፣ ለሞት የተዳረጉት ሰዎችም 15 ሺህ ያህል መድረሱን መረጃዎች ይጠቁማሉ፡፡
የአፍሪካ ልማት ባንክ በበኩሉ፤ በአፍሪካ የኮሮና ቫይረስ በአሁኑ ፍጥነት መሰራጨቱን ከቀጠለና ከመጪው 2020 ግማሽ አመት ካለፈ አህጉሪቱ በ2020/21 የፈረንጆች አመት በቫይረሱ ሳቢያ 236.7 ቢሊዮን ዶላር ያህል ኪሳራ ሊያጋጥማት እንደሚችልና የአህጉሪቱ አጠቃላይ የአገር ውስጥ ምርት በአመቱ በ1.7 በመቶ ያህል ይቀንሳል ተብሎ እንደሚጠበቅ ባለፈው ረቡዕ ባወጣው መግለጫ አስጠንቅቋል፡፡
በቅርቡ ስልጣን የያዙት የማላዊ ፕሬዚዳንት ላዘሬስ ቻክዌራ በአገሪቱ እየተስፋፋ የመጣውን የኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝ ለመግታት ስኬታማ ይሆን ዘንድ ህዝባቸው ለሶስት ቀናት በሚቆይ ብሔራዊ ጾምና ጸሎት ከጎናቸው እንዲቆም ጥሪ ማቅረባቸው ተነግሯል፡፡
በዴንማርክ የደቡብ አፍሪካ አምባሳደር ሆነው ሲያገለግሉ የቆዩትና ባለፈው ሰኞ በ59 አመታቸው ከዚህ አለም በሞት የተለዩት የቀድሞው የደቡብ አፍሪካ ፕሬዝዳንት ኔልሰን ማንዴላ ልጅ፣ ዚንዲዚ ማንዴላ በአስከሬናቸው ላይ በተደረገው ምርመራ በኮሮና ቫይረስ ተይዘው እንደነበር መረጋገጡን ሮይተርስ ዘግቧል፡፡
ቀጣይ የአለማችን ስጋትና ፈተናዎች
የአለም የኢኮኖሚ ፎረም ከሰሞኑ ይፋ ባደረገው መረጃ፤ አለማችን በመጪዎቹ 18 ወራት ከኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝ ጋር በተያያዘ ከኢኮኖሚ እስከ ጂኦፖለቲክስ ዘርፈ ብዙ ፈተናዎችና ስጋቶች እንደሚያጋጥሟት ያስታወቀ ሲሆን፣ ከሁሉም በላይ የአለም ህዝቦችን የሚያሰጋቸው ፈተና ኢኮኖሚያዊ እንደሚሆን አመልክቷል፡፡
አለማችን በተጠቀሰው ጊዜ ያጋጥማታል ተብለው ከተጠቆሙት 31 ያህል ስጋትና ፈተናዎች መካከል አስሩ ኢኮኖሚያዊ፣ ዘጠኙ ማህበራዊ፣ ስድስቱ ጂኦፖለቲካዊ፣ አራቱ ቴክኖሎጂያዊ፣ ሁለቱ አካባቢያዊ መሆናቸውንም መረጃው ጠቁሟል፡፡
ከቀዳሚዎቹ የአለማችን ቀጣይ ፈተናና ስጋቶች መካከል የተራዘመ አለማቀፍ የኢኮኖሚ ቀውስ፣ ከፍተኛ ስራ አጥነት፣ ሌላ የበሽታ ወረርሽኝ ክስተት፣ የኢንዱስትሪዎች ማገገም አለመቻል፣ ተጨማሪ የጉዞ እገዳዎችና የንግድ እንቅስቃሴ ገደቦች፣ የማህበራዊ ዋስትና መዳከም፣ የከፋ ሰብዓዊ ቀውስ፣ ከፍተኛ የዋጋ ንረት ጭማሪ፣ የጤና አገልግሎቶች የዋጋ ውድነትና የከፋ የአእምሮ ጤና ችግር መስፋፋት እንደሚገኙበትም መረጃው አመልክቷል፡፡
በሌላ በኩል ደግሞ ቻይና የኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝ ከተቀሰቀሰበት ጊዜ አንስቶ የኢኮኖሚ እድገት ያስመዘገበች የመጀመሪያዋ ሃያል አገር መሆኗን የዘገበው ብሉምበርግ፤ አገሪቱ የእንቅስቃሴ ገደቦችን ካነሳችና ፋብሪካዎችን መክፈት ከጀመረች በኋላ ባለፈው ሩብ አመት ያልተጠበቀ የ3.2 በመቶ የኢኮኖሚ ዕድገት ማስመዝገብ መቻሏን አመልክቷል፡፡
ቻይና እስከ ሃምሌ በነበሩት 3 ወራት ያስመዘገበችው የኢኮኖሚ ዕድገት ያልተጠበቀና ከፍተኛ መሆኑን የጠቆመው ዘገባው፣ ከዚያ በፊት በነበረው ሩብ አመት ኢኮኖሚዋ በ6.8 በመቶ ቀንሶ እንደነበርም አስታውሷል፡፡
ክትባት እና መድሃኒት
አለም ለመጣባት የጥፋት ማዕበል መላ የሚሆናትን ክትባት ወይም መድሃኒት ለማግኘት ደፋ ቀና ማለቷን አሁንም አጠናክራ የቀጠለች ሲሆን፣ ከሰሞኑም ከሌሎች በተለየ ተስፋን የሚሰጥ ወሬ ከወደ አሜሪካ ተሰምቷል፡፡
ለኮሮና ክትባት ለማግኘት ሰፊ ምርምር ሲያደርግ የቆየው የአሜሪካው የባዮቴክኖሎጂ ኩባንያ ሞደርና፣ ከሁለት ሳምንታት በኋላ ክትባቱን በሰዎች ላይ ለመሞከር ወደሚያስችለው የመጨረሻ ደረጃ የሙከራ ሂደት እንደሚገባ ያስታወቀ ሲሆን፣ በሙከራው 30 ሺህ ሰዎችን ለማሳተፍ ማቀዱንም ገልጧል፡፡
ስምንት የአለማችን አገራት መሪዎች በቀጣይ በምርምር ይገኛሉ ተብለው የሚጠበቁ የኮሮና ክትባቶችን በፍትሃዊነት ለአለም ህዝቦችና አገራት ለማዳረስ ትኩረት እንዲሰጥ ለአለማቀፉ ማህበረሰብ ጥሪ ማቅረባቸውን የዘገበው ሮይተርስ፣ ፕሬዚዳንት ሳህለ ወርቅ ዘውዴና የካናዳ፣ የደቡብ ኮርያ፣ የኒውዚላንድ፣ የደቡብ አፍሪካና የስፔን መሪዎች እንደሚገኙበትም አመልክቷል፡፡
በተያያዘ ዜናም፣ ከ150 በላይ የሚሆኑ የአለማችን አገራት የኮሮና ክትባትን በመላው አለም ለሚገኙ አገራት በፍትሃዊነት ለማዳረስ እየሰራ የሚገኘው ኮቫክስ የተሰኘ ስብስብ አባል ሆነው ዜጎቻቸውን የክትባቱ ተጠቃሚ ለማድረግ እየሰሩ እንደሚገኙ ሮይተርስ ዘግቧል፡፡ ከእነዚህ አገራት መካከል 75 የሚሆኑት የራሳቸውን ፋይናንስ በመመደብ ክትባቱን ለማስገባት የፈቀዱ መሆናቸውንም ዘገባው አመልክቷል፡፡
የአፍሪካ የበሽታ መከላከልና ቁጥጥር ማዕከል በበኩሉ፤ ውጤታማነታቸው የሚረጋገጡ የኮሮና ክትባቶችን በአፍሪካውያን ኩባንያዎች ማምረት የሚቻልበትን ሁኔታ ለመፍጠር የክትባቱ ፈጣሪዎች ለኩባንያዎቹ የአእምሮአዊ ንብረት መብት ፍቃድ እንዲሰጡ ማድረግ እንደሚገባ ገልጧል፡፡
ኖቫርቲስ የተባለው የስዊዘርላንድ ኩባንያ ምንም አይነት የገንዘብ ትርፍ የማይገኝባቸውን ከኮሮና ጋር በተያያዘ ለህክምና የሚውሉ 15 አይነት መድሃኒቶች ለ79 ያላደጉ አገራት እንደሚለግስ ማስታወቁን የዘገበው አልጀዚራ፣ ሩስያ በበኩሏ ለ30 ሚሊዮን ሰዎች የሚሆን በሙከራ ላይ የሚገኝ የኮሮና ክትባት በአገር ውስጥ ለማምረት ማሰቧን አስነብቧል፡፡
በተያያዘ ዜና ደግሞ፣ በፈረንጆች አመት 2019 በመላው ዓለም 14 ሚሊዮን ያህል ህፃናት መሰረታዊ የሚባሉና በቀላሉ መከላከል የሚቻሉ ህመሞችን ክትባቶች  አለመከተባቸውን የዓለም ጤና ድርጅትና ዩኒሴፍ ከሰሞኑ ያስታወቁ ሲሆን፣ በዚህ ዓመትም በኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝ ምክንያት ክትባቶች በመቋረጣቸው ቁጥሩ በእጥፍ ያህል ይጨምራል ተብሎ እንደሚጠበቅ ጠቁመዋል፡፡
ባለፉት 30 አመታት ታሪክ እጅግ በርካታ ቁጥር ያላቸው ህጻናት በኮሮና ቫይረስ ምክንያት የተለያዩ ህይወት አድን የሆኑ ክትባቶች አለመከተባቸውን የጠቆሙት ተቋማቱ፣ በ2020 የፈረንጆች አመት የመጀመሪያዎቹ አራት ወራት ብቻ የፖሊዮ፣ ኩፍኝ፣ ማጅራት ገትር፣ ቲታኖስና የማያቋርጥ ሳል መከላከያ ክትባቶችን የወሰዱ ህጻናት ቁጥርም በከፍተኛ መጠን መቀነሱን ገልጸዋል፡፡
ህጻናት እና ትምህርት
ከኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝ ጋር በተያያዘ በመላው አለም በርካታ ቁጥር ያላቸው ትምህርት ቤቶች አገልግሎታቸውን አቋርጠው መዘጋታቸውን ያስታወሰው ሴቭ ዘ ችልድረን፣ 9.7 ሚሊዮን ያህል የአለማችን ህጻናት ዳግም ወደ ትምህርት ቤት ላይመለሱ እንደሚችሉ ከሰሞኑ አስታውቋል፡፡
ባለፈው ሚያዝያ ወር በመላው አለም ወረርሽኙን ለመግታት ታስቦ ትምህርት ቤቶችና ዩኒቨርሲቲዎች በመዘጋታቸው ከአለማችን ተማሪዎች 90 በመቶ ያህሉ ወይም 1.6 ቢሊዮን ያህል ወጣቶች ትምህርት ማቆማቸውን ያስታወሰው ድርጅቱ፣ በቀጣይም 9.7 ሚሊዮን ያህል ህጻናት የቤት ውስጥ ስራ እንዲሰሩ፣ ተገድደው እንዲዳሩ በመደረጋቸው እስከ ወዲያኛው ወደ ትምህርት ቤት ላይመለሱ እንደሚችሉ አስጠንቅቋል፡፡
የኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝ ያስከተለው ተጽዕኖ፣ አነስተኛና መካከለኛ ገቢ ባላቸው አገራት የ2021 የፈረንጆች አመት የትምህርት ዘርፍ በጀት ላይ የ77 ቢሊዮን ዶላር እጥረት ሊያስከትል እንደሚችልም ባለፈው ሰኞ ባወጣው መረጃ አመልክቷል፡፡
አንዳንድ ነገሮች - በኮሮና ዙሪያ
ኮሮናን እንደ ቀላል ጉንፋን በመቁጠር የራሳቸው መዘናጋት ሳያንሳቸው ህዝባቸውንም ለከፍተኛ ጥፋት የዳረጉትና በቅርቡ በኮሮና ቫይረስ ተይዘው ያገገሙት የብራዚሉ ፕሬዚዳንት ጄር ቦልሶናሮ፣ ባለፈው ረቡዕ በድጋሚ በቫይረሱ መያዛቸው መረጋገጡን የዘገበው አልጀዚራ፣ ሰውዬው ግን አሁንም ፈዋሽነቱ ያልተረጋገጠውን ክሎሮኪን የተባለ የወባ መድሃኒት ኮሮናን ለማዳን ተጠቀሙ ሲሉ መደመጣቸውን ገልጧል፡፡ የደቡብ አፍሪካው የማዕድንና ኢነርጂ ሚኒስትር እና ባለቤታቸውም በኮሮና ቫይረስ መያዛቸው ተነግሯል፡፡
የቺሊ መንግስት በኮሮና ቫይረስ የተጠቁ ሰዎችን አነፍንፈው መለየት የሚችሉ ውሻዎችን ማሰልጠን መጀመሩ የተነገረ ሲሆን፣ በኮሮና የተያዙ ሰዎች ከፍተኛ መጠን ያለው ላብ ከሰውነታቸው ስለሚወጣና የተለየ መዓዛ ስለሚያመነጩ ውሾቹ ይህንን መዓዛ በማነፍነፍ የቫይረሱ ተጠቂዎችን እንዲለዩ ለማድረግ መታሰቡን አጃንስ ፍራንስ ፕሬስ ዘግቧል፡፡
የእንግሊዝ ጤና ሚኒስትር ማት ሃንኮክ፤የአገሪቱ ዜጎች በቢሮ ውስጥና በሥራ ቦታዎች ላይ የአፍና የፊት መሸፈኛ ጭንብል ወይም ማስክ እንዲያደርጉ የሚያስገድድ መመሪያ ማስተላለፋቸውን የዘገበው ቢቢሲ፤ በአገሪቱ በህዝብ መጓጓዣዎችና በሱቆች አካባቢ ማስክ ማድረግ ግዴታ ከሆነ ወራት መቆጠራቸውን አስታውሷል፡፡
ቫይረሱ ከ30 ሺህ በላይ ዜጎችን የቀጠፈባትና ከሰሞኑ ደግሞ በፍጥነት መሰራጨት የጀመረባት ፈረንሳይ ፕሬዚዳንት ኢማኑኤል ማክሮን በበኩላቸው፤ በዝግ ህዝባዊ ስፍራዎች ውስጥ የአፍና የፊት ጭምብል ማድረግ ከመጪው ነሃሴ ወር መጀመሪያ አንስቶ ግድ እንደሚሆን ከትናንት በስቲያ ለህዝባቸው አስታውቀዋል፡፡
በአገሪቱ ፖሊስ ስልጠና እየተሰጣቸው የሚገኙት እነዚሁ አነፍናፊ ውሾች እስከ መጪው ወር ስልጠናቸውን ጨርሰው በአገሪቱ የተለያዩ አካባቢዎች በሚገኙ ባቡር ጣቢያዎችና የአየር ማረፊያ ጣቢያዎች ይሰማራሉ ተብሎ እንደሚጠበቅም ዘገባው አመልክቷል።

Saturday, 11 July 2020 00:00

ማራኪ አንቀፆች

  እንባቆም፡- ጉዳት ወይም ችግር አግጦ በራሳችሁ ላይ ሲደርስ ይነዝራችኋል፤ የሌላ ሌላ ግን የገለባ ያህል አይከብዳችሁም…ያም ሆነ ይህ ጦርነት እጅግ አክሳሪና ውድ ዋጋ የሚያስከፍል መሆኑን ማጤን አለባችሁ… የቀደመ ታሪክ ማስታወስም ይበጃል፡፡
አባ ዘዮሐንስ፡- ለመሆኑ ለግብጽ አጀንዳ መንግሥታችን ምን መለሰ?
አዱኛው፡- በመስታወት ቤት ውስጥ የሚኖር ቀዳሚ ጠጠር ወርዋሪ አይሆንም፤ ግብጽም ግድቦች አሏት፤ ጦር ስታወናጭፍ ለነሱ ምን ዋስትና ሰጥታ ነው? ሌላው ግብጾች ካላበዱ በስተቀር ወደ ጦርነት አይሄዱም ነው የተባለው… ውጤቱን ያውቁታላ!
በኃይሉ፡- ከባዱም ዓለም አቀፍ ህክምና ይቀርብላቸዋል፡፡
እንባቆም፡- አባይ የለም ግብጽ የለም የሚለውን ፈሊጥ ገልጠን ብናየው፣ ለማስፈራራትና የግብጽን ህዝብ በኢትዮጵያ ላይ ለማነሳሳት ብቻ ነው… ሌላው አስቂኝ ጩኽታቸው ግብጾች እውን ላንዲት ጠብታ ውሃ ከዓለም ላይ ይጠፋሉ? የግብጽን ያህል ውሃ ሳያገኙ የሚኖሩ ምድረ በዳነት የበዛባቸው ሀገሮች የሉም… አሉ /ጭብጨባ/
ደሌቦ፡- ከአባይ ላይ ጠብታ ውሃ አይቀነስም ይበሉ እንጂ እዚያው ሀገራቸው ውስጥ ከአስዋን ግድብ በትነት የሚጠፋ ውሃ መጠን በሚሊዮናት ኪዩቢክ ሜትር የሚለካ በየዓመቱ ይባክናል፤ ገልጠን ብናየው አባይን ደግሞ አድራቂዋ ሌላ ሳይሆን እራሷ ግብጽ ነች፡፡
እንባቆም፡- በሌላ በኩል፤ የህዳሴው ግደብ ከተሰራ በኋላ ወደ ግብጽ አልፎ የሚያጥለቀልቃትን ውሃ መጠንና ደለሉን በመቀነስ የጠራ ውሃ እንድታገኝ ለመከላከያው የምታወጣውንም ከፍተኛ የገንዘብ ወጪ ኪሳራ ይቀንስላታል፡፡
ደሌቦ፡- እናም ከኢትዮጵያ ያልተናነሰ ጥቅም ታገኛለች ማለት ነው እኮ… ሀቁ!
እንባቆም፡- (ፋታ) ውድ ተሰብሳቢዎች፤ ዳውድ እስካሁን ሲያወጋን የነበረው ፖለቲከኞቻቸው የሚያላዝኑትን የውሸት ጩኸት ነበር፡፡ የሱ ሙግትም የነሱ የመከነ ፖሊሲ ዜሮ ሳም ሜንታሊቲ ወይም አልቦ ድምር አስተሳሰብ ነጻብራቅ ነበር /ጭብጨባ/ እና ዳውድ ዋሽቼ ከሆነ አጋልጠኝ፡፡
ዳውድ፡- /ከሊፋ ጋር ተነጋግሮ ቀድሞ መልስ ይሰጣል/ ወንድሜ ሆይ እንዲሁም አባቶቻችን… ወደ ሃቁ እንምጣ፤ ሃቅ ያንቃል ይባላል /ፋታ/ እስካሁን በናንተ በኩል የተወረወረውና የኔም ልብ የሚያስበው  የግብጽ አዲሱ ትውልድ  በሆሆታና በጋጋታ… በኡኡታ ጠብ ያለሽ በዳቦ የሚነዳ አይደለንም /ጭብጨባ/ ከእንግዲህ ወደፊት የሚያራምደን ሳይንስና አመክንዮ፣ ነባራዊ እውነታ እንጂ የምናብ ከንቱ ፈጠራና ስጋት አይሰራም፤ከአዲሱ ትውልድ መፈጠሬ እድለኛ ነኝ /ፋታ/ ሌላው ነጥብ፣ ለኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ይቀነሳል ተብሎ የሚታሰበው የአባይ ውሃ መጠን እጅግ የሚገርም ነው፡፡ የአባይ ውሃ ጠቅላላ መጠኑ ከ80 ኪዩቢክ ሜትር በላይ ሲሆን ከዚህ ውስጥ ለህዳሴው ይቀነሳል የሚባለው ከ3-4 ቢሊዮን ኪዩቢክ ነው፤ የጠብታ ያህል! ተመልከት እንግዲህ… እዚህ ግባ ለማይባልና ከቁጥር ለማትገባ መጠን… ለዚያውም ጥቅሙ የጋራ የሆነ ፕሮጀክት… ግብጽን ከቶም የሚያሰጋት ሊሆን አይችልም፣ ታዲያ ጉዳዩን ጠልቀን ሳንረዳ በርግገን ማስበርገግ ባልተገባ… አሁንም ሌላ ነጥብ የማነሳው ኢትዮጵያ በጣም በጣም ታጋሽ እናት ሀገር ነች /ጭብጨባ/ እኛ ብንሆን… የምሬን ነው የምናገረው ከስኩዊዝ ካናል ያልተናነሰ የአባይ ፈሰስ ወይም ቀረጥ እናስከፍላችሁ ነበር … በውነቱ የኔ ትውልድ ነቅቷል፤ ኋላ ቀር ፖሊሲ በሚያራምዱ አንድ አንድ ወግ አጥባቂ ብዥታም ባለስልጣናት ፈር የሳተ አመለካከት ብለን እሳት አንጭርም፤ አቃጥለን አንቃጠልም ! /ጭብጨባ/ ከእንግዲህ እኛ የአባይን ሸለቆ  ለልማት ማረስ እንጂ  በአንጡራነት የመያዝ እሳቤ እንደማያዛልቅ፣ ኢትዮጵያም በወንዟ  እንዳትጠቀም የሚያደርግ አንዳችም ምድራዊ ሀይል እንደሌለ በግልጽ የሚታይ ነው/ሞቅ ያለ ጭብጨባ/፡፡
ከሊፋ፡- እኔም የዳውድ ሃሳብ ደጋፊ ነኝ /ፋታ/ የኛ ትውልድ ለራሱ የሚኖር እንጂ ሙት ታሪክ  እየቆፈረ በጫጫታና ወዳልተፈለገ አቅጣጫ በልጓም የሚነዳ የጋሪ ፈረስ አንሆንም፤ እኛ እስካሁን ያቀረብንላችሁ  ክርክር የየግላችን ሀሳብ ወይም አቋም ሳይሆን የአንዳንድ ፖለቲከኞቻችን ከንቱ ሙግት ነው፤ ማዕዳችን አንድ ነው፤ ላንዱ እሬት ላንዱ ማር አይደለም … ለምን ማሩን ወደ እሬት ለመለወጥ እንደምንተጋ አይገባኝም /ጭብጨባ/ ለማንኛውም የመንግስቶቻችን ውይይቱ ይቀጥላል፤ ለወደፊቱ ምን ላይ ሊደርስ እንደሚችል በንድፈ ሀሳብ ከወዲሁ አውቀነዋል፤ የግርጌ የራስጌ የአባይ ተፋሰስ ሀገራት ተብሎ ቅራኔ ማክረር ይቀራል፤ በአዲስ መንፈስና በአዲስ አመለካከት ተነሳስተንም ጠላት በዘመኑ መካከላችን ሰንቅሮ ያኖረውን ጊዜ ጠብቆ የሚፈነዳ የቅራኔ ፈንጂ አምክነን፣ እንደ ጥንት አንጋፋነታችን የስልጣኔ እርካብ ላይ ተቆናጥጠን እጅ ለእጅ ተያይዘን፣ አባይን በጋራ እያለማን፣ ትውልዱን በአንድ ቤተሰብነት መንፈስ ይዘን በስራና በፍቅር እየመራን መራመድ እንድንችል፣ ከእኛም ሆነ ከምሁሮቻችን ትጋት በጥብቅ ይጠበቅብናል /የጋለ ጭብጨባ/
ዳውድ፡- እኛም ግብጾች ከሚያስማማን ከውይይቱ መድረክ መሸሽ ወይ በራስ አለመተማመን ወይም ራስ ወዳድነት እንጂ ጥበብ አይሆንም /ጭብጨባ/ ስለዚህ ሀገሬ ግብጽ አወዛጋቢ ነጥብ ፈትታ ከተፋሰሱ ሀገራት ጋር ሰምና ክር ሆና የመሪነት ሚናዋን ማጉላት ይጠበቅባታል የሚል የጸና ተስፋ አለኝ /ጭብጨባ/ ለዚህም በጋራ እንታገላለን፡፡
አባ ዘዮሐንስ፡- ጨው ለራስህ ስትል ጣፍጥ፤ አለዚያ ድንጋይ ነው ብለው ይጥሉሃል እንዲሉ፡፡
ዳውድ፡- አዎን ከእንግዲህ ለአባይ አሉታዊ መፈክር ሳይሆን አዎንታዊ መፈክር እያሰማን፣ በተስፋ ወደፊት እንተማለን /ተሰብሳቢው እያጨበጨበ ከመቀመጫው ይነሳል/ መፈክሩን አብረን እንበል /ኖ ናይል ሳይሆን የስ ናይል እንበል -  አባይ ለግል ሳይሆን ለጋራ ይሆናል ! /ሆታና ጭብጨባ፤ መተቃቀፍ ይከተላል/
እንባቆም፡- ክቡራትና ክቡራን -ስብሰባች ንን ልንቋጭ ነው፤ መንፈስ እንደ አረቄ የሚያሞቁ ሀሳቦችን ሰምተናል፤ ያረጁ ያፈጁ ውሎች የሙዝየም እድል እንኳን አይሰጣቸውም፤ ይቃጠላሉ! /ሆታ/ በአሲሲው ካህን ፍራንሲስ አባባል ውይይቱን ብናጠናቅቅ ደስ ይለኛል፡- አምላኬ ማድረግ የምችለውን እንድፈጽመው ድፍረት ስጠኝ፤ የማልችለውን ደግሞ እንድቀበለው ትዕግስቱን ስጠኝ ይላል/ ሆታ/
አባ ዘዮሐንስ፡-  ልክ ነህ ልጄ፤ እሱ አንድዬ ልቦናችንን ወደ ቀና ጎዳና ይመልስልን /ሆታ፤ ክራርና መሰንቆ ያጅባል/
ጦቢያ፡- /ጦቢያ ያማጽናሉ/ ውይይቱ ቢጠናቀቅም ባህላዊ ቡና እየተዘጋጀ ስለሆነ እባካችሁን ለጥቂት ደቂቃ ባላችሁበት እየተጨዋወታችሁ ቆዩልን/ ከወንበራቸው ሄደው ይቀመጣሉ /ፋታ/
ሄንሪ፡- /ወደ እነ ዳውድ ጠጋ ብሎ ሹክ ይልና ይቆማል/ ክቡራትና ክቡራን፤ ቡናው እስኪመጣ ድረስ ለጥቂት ደቂቃ እንለያችኋለንና ፍቀዱልን… እንመለሳለን…/ይወጣሉ/ ሌሎች ጭውውታቸውን በቡድን በቡድን ይቀጥላሉ… ይጠጣሉ ይስቃሉ /መብራት ይጠፋል/
(ከግርማ እንቻለው የህዳሴ ግድብ እና "ፈርኦኑ ቀለበት" ተውኔት መጽሐፍ የተወሰደ፤ 2012)

Saturday, 11 July 2020 00:00

ከፌስቡክ ገጾች በጨረፍታ

   የሰው ልጅ ቁጥር ሆነ!
የመጀመሪያዋ ሴትዮ በኮቪድ ሲሞቱ ለሁላችንም ሰው ነበሩ፡፡ እናት ነበሩ:: ለሁላችንም ሃዘን ነበሩ፡፡ ለሁላችንም ድንጋጤ ነበሩ፡፡
ከሁለተኛው ሰው በኋላ ግን፣ ሰው ቁጥር ሆነ፡፡
ስንት ሰው ሞተ? ብለን እንጠይቅና ፣ ወደ ዕለት ጉዳያችን እንሄዳለን፡፡ የሞተው ሰው ቁጥር ሲነገረን እንሰማና፣ ወደ ጉዳያችን እንገባለን፡፡ ያ ቁጥር ነገ እኛ ልንሆን እንደምንችል ማሰብ ከተውን ቆየን፡፡
ስድስት ሰው ሞተ… አስር ሰው ሞተ… አስራ… ይቀጥላል፡፡ ባለአንድ፣ ባለሁለት፣ ባለሶስት፣ ባለአራት ዲጂት እስኪደርስ ድረስ ሰው ቁጥር ሆኗል፡፡
ወደፊት ቁጥሮች ከፍ ይላሉ፡፡ እያንዳንዳችን ቤት እስኪደርሱ ድረስ ሰዎች ቁጥር መሆናቸው ይቀጥላል፡፡
ቤታችን ሲገባ ግን፣ አንድ ቁጥር ሺህ ነው፤ ከሺህም በላይ ነው፤ ከሚሊዮንም በላይ ነው…  ያ ቁጥር አባት ነው፤ እናት ናት፤ ወንድም ነው፤ ሚስት ናት፤ ባል ነው፤ ሚስት ናት፤ ልጅ ነው፤ ዘመድ አዝማድ ነው:: ያ ስም ሌላው ሰው ጋ ሲሄድ ቁጥር ነው፤ እኛ ጋ ግን ከስጋችን ቦጭቆ የሚወጣ… ትልቅ ቁስል የሚሆን ህመም ነው፡፡
አስበነው እናውቅ ይሆን?
ከቁጥር አንጉደል!
ቁጥር እንዳንሆን እንጠንቀቅ!
እንጠበቅ!
እንጠብቅ!
(ከመላኩ ብርሃኑ የፌስቡክ ገጽ የተወሰደ)
*   *   *
እንዴት ዝም ልበል?!
(የአንድ አጥፊ ኑዛዜ)
ፍቅር በሚሉት ቃል
የጨለፍኩላችሁ፣ መርዜን ስታረክሱት
ሳቆመው የባጀሁ
የዘር ድንበር ኬላ፣ አጥሬን ስታፈርሱት
የተንኮል ጎጆዬን
ወጋግራ ነቅላችሁ፣ ስታደርጉት ዘመም
እያየሁ ልታመም?...
ትተራረዱበት
የሳልኩት ቢላዋ፣ በእጃችሁ ሲመከት
በዋይታችሁ ፋንታ
ጆሮዬን ስትነድሉት፣ በፍቅር መለከት
ዝም ብዬ ልመልከት?...

ዘመናት ፈጅቶብኝ
የተከልኩትን ቂም፣ ነቅላችሁ ስትጥሉት
የጥላቻ እሾሄን
ከየጀርባችሁ ላይ፣ በድንገት ስትነቅሉት
የማናከስ ልክፍት
ስንት የደከምኩበት፣ ከንቱ ሲቀር ህልሜ
ልያችሁ ዳር ቆሜ?...

የቂሜን ጥቅርሻ
ይቅርታ በሚሉት፣ እንዶድ ስታጸዱት
የዘር ስናጾሬን
በአንድ የፍቅር ቋንቋ፣ ከስሩ ስትንዱት
ዘመናት ያለፈ
የጥፋት ድግሴን፣ የደም ጽዋ ጸበል
ድንገት ባደባባይ
ባንድነት ሱባኤ፣ ስታደርጉት ከንበል
እንዴት ዝም ልበል!?...
(ገጣሚ - ፊያሜታ)


   ስለ ሽልማት ስናስብ---ከነበረው አልወጣንም- በአስተሳሰብ ማለቴ ነው:: ሌላስ መኖር አልነበረበትም ወይ የሚል ጥያቄ አንጠይቅም፡፡ የቀዳማዊ ኃይለ ስላሴ ፋውንዴሽን አንዱ ትልቁ የሽልማት ድርጅት ነው፡፡ ይሄን  አሁን --- ብልጭ ድርግም ከሚሉት የሸላሚ ድርጅቶች ልዩ የሚያደርገው በአግሮ ኢኮኖሚ፣ በእርሻ፣ ኢንዱስትሪን ባስፋፉና በጀመሩ ሰዎች፣ በሰዓሊያን፣ በደራሲያን -- እያለ ሁሉን አቀፍ የሆነ የሽልማት ድርጅት ነው……እኛም የሚያስፈልገን የዚህ ዓይነቱ ይመስለኛል:: ብንችል ስፔሻላይዝ ብናደርግ ጥሩ ነው:: ለአርት ብቻ የሚሸልም ሊኖር ይችላል:: አግሪካልቸር ላይ ትልልቅ ስራ ለሰሩ ወይም አዳዲስ ኢኖቬሽን ለፈጠሩ ሰዎች፣ የሥራ ፈጠራ ላመጡ…..ኢንተርፕሩነርስ ለመሳሰሉት የሚሸልም ተቋም መናፈቅ ብቻ አይደለም--ብንችል ልንታገልለት የሚገባ ነገር ነው የሚመስለኝ፡፡ ምክንያቱም It will bring out the excellence…….ዋናው በቃ-- የመጠቀ አእምሮ አለው የሚባለውን ሰው ወደ ላይ እንዲወጣ ያደርገዋል፤ ያስከብረዋል፡፡ ከዚያም እንዲወሳ ያደርገዋል:: ከዚያ እንግዲህ ትልቁ ነገር፣ ትውልድ አርአያ እያገኘ ይሄዳል፡፡ አርአያ እንዲኖረን እኮ ነው ሽልማት የሚያስፈልገው--ትልቁ ነገር እሱ ነው፡፡ አርአያ ስላጣንም ነው--አርአያ ሲታጣ ደግሞ እንዲሁ እንደ ውሃ መፍሰስ ብቻ ነው የምትሆኚውና---እገሌን እሆናለሁ የምትይው ነገር መኖር መቻል አለበት፡፡
ያ አይነቱ ሰው ደግሞ ከአፈርሽ የበቀለ ቢሆን ነው የሚመረጠው--እንጂ አንድ የሳይንስ ተማሪ አንስታይንን መሆን እፈልጋለሁ ሊል ይችላል --- ግን የአገርህ ሰው ለዚህ የሚያበቃ፤ ለዚህ መጠሪያ-- ለአርአያነት የሚበቃ አለ ወይ የሚለውን ጥያቄ መጀመሪያ ቢጠይቅ ነው የሚሻለው:: ለልጅ ልጆች እንደ እገሌ እንድሆን ….በቃ የአበበ ቢቂላ …ጥላሁን ገሰሰ ይድርሻል  እንደምንልበት ዘመን---የሆነ የምናስባቸው ሰዎች አሉ፤ እና እገሌ የምትይው የምትጠሪው---ሩጫ ሮጠሽ እንደ ኃይሌ ገ/ሥላሴ መሆን እፈልጋለሁ….የምትይ ከሆነ…ያንን እሆነዋለሁ ብለሽ ከልጅነትሽ የምታስቢ የሚያደርግሽ መሆን አለበት፡፡
እንግዲህ ከድሮም ዶክተር እሆናለሁ…ፓይለት እሆናለሁ የሚሉት የሚታወቁ፣ የተለመዱ ናቸው፡፡ ግን እንደ እገሌ የሚለው ነገር የሚመጣው---ሽልማት እየሰጠሽ፣ እያበረታታሽ፣ ስሙን እያነሳሳሽ፣ አንዳንድ ነገሮችን እየሰየምሽለት ከሄድሽ ነው፤ከሰው አዕምሮ እንዳይወጣ የምታደርጊው…እንጂ የክፍል ጓደኞችሽን የመሳሰሉ ትላልቅ ቦታ የደረሱ ሰዎችን እናውቃለን፡፡ እነዚህ ሰዎች ግን እዚህ  የሚነሱበት ሁኔታ ይጠፋል፤ ውጭ አገር ወይ ናሳ ገብተዋል ወይ አንድ የአውሮፕላን ድርጅት ውስጥ ናቸው…ትልልቅ ኢንጂነሮች ተብለው የተቀመጡ ሰዎች አሉ:: ታዋቂ ፊዚስቶችም  አሉ::
ግን እነሱን እዚህ የምናመጣበት መንገድ የለም፡፡ ለዚህም እንግዲህ እንዲህ አይነት ፋውንዴሽን ሲኖር፣ መጀመሪያ ኢንዴክስ ይሰራል፤ በዓለም ደረጃ ጭምር ያሉ ኢትዮጵያውያንን--- ታላላቅ ሰዎች የሚባሉትን በሙሉ ይመዘግባል---አሁን እኮ  ቢያንስ ኢንዴክስ የለሽም---ችግሩ እኮ አመልካች የሆነ ተሰብስቦ የሚገኝ ሰነድ አታይም፡፡ አንድ ጊዜ አስታውሳለሁ…ሰዓሊ ከበደች ተክለአብ ከአሜሪካ የኮርኔል ዩኒቨርሲቲ አንድ ፕሮጀክት ሰጥቷት መጥታ ነበር…ምንድን ነበር ፕሮጀክቱ---ኢትዮጵያ ውስጥ ያሉትን ሰዓሊዎች በሙሉ አንደር ሊስት ማድረግና መያዝ ነው…በምን በምን ትምህርት እንደተመረቁ፤ ግን መረጃ  ማግኘት አልተቻለም…አብሬያት ስዞር ነበር፤ አድራሻ ማግኘት ጭራሽ ከባድ ነው፤አሁን ትንሽ ሞባይል አቅልሎት ከሆነ …በሞባይል ደውለሽ አድራሻ ስጡኝ ልትይ ትችያለሽ:: ስልክና ስም ማግኘትም ቢሆን ከባድ ነገር አለው፡፡ የሽልማት ድርጅት መኖር አንዱ አድቫንቴጅ፣ ታዋቂ ሰዎችን አሰባስቦ የሚይዝ ዶክመንት ይኖረዋል ማለት ነው:: ሁለተኛው ለዚህ ሽልማት ለመብቃት ሌላው ወጣት ይተጋልና ነው፤ ይኼ ትልቁ ቁም ነገር ነው፡፡ ሦስተኛው ያንን ሰው ማክበር መጀመራችን ነው፤ምንም ይሁን ምን ያ የተሸለመበት ሙያ የእሱ ተከባሪነት ማረጋገጫ ነው፡፡ ያንን አክብረሽለት…ምንም ዓይነት ህይወት ይኑረው…ምንም ዓይነት ኑሮ ይኑር አንቺም ማድነቅ ያለብሽ ኤክሰለንሱን ነው፤የሰውን ትልቁን ችሎታ ነው መያዝ ያለብሽ፡፡ አሁን ትልቁ ችሎታ ለሌሎች አርአያ ብቻ ሳይሆን ለስራ፣ ለትምህርት፣ ለዕውቀት፣ ለኤክሰለንስ ያለንን አክብሮት ሁሉ መንገድ ይመራናል፤ስለዚህ ሁለገብ የሆነ ሸላሚ ድርጅት ቢኖር የምመኘው…ምናልባትም የምጥረው ለዚህ ነው፡፡ ሌላው በዚህ በሥነቃል፣ በፊደል፣ በቋንቋ ረገድ እያዘቀዘቅን የምንሄድበት---በጣም አርቴፊሻልና ክልስ ዓይነት፣ ዲቃላ ዓይነት ቋንቋችንን ለማጥራት የሚችሉት፣ እንደ ሌክሲኮግራፈርስ ዓይነት ተቋማት የሚያስፈልግ ይመስለኛል፡፡ ባህል ሚኒስቴር ይሄን መስራት የሚያቅተው አይመስለኝም፡፡ አየሽ-- በባህል ቅርሳ ቅርስ፣ ከዚያ ደግሞ ሥነ ቋንቋ ዙሪያ አንድ ጥሩ ተቋም መኖር ያለበት ይመስለኛል፡፡ ብዙ ነገራችን ዝብርቅርቁ የሚወጣው፣ ሴንትራላይዝድ የሆነ አመራር የሚያካሂድ ባለመኖሩ ይመስለኛል፡፡
ቴሌቪዥን ላይ መነገር ያለበት ቋንቋ፣ ሬዲዮ ላይ መነገር ያለበት ቋንቋ--- የጽህፈት ቋንቋ የምትያቸው እንዴት እንደሚለያዩ ሃይ የሚል ተቋም ያስፈልጋል፡፡ ከላይ ሆኖ እስቲ አረፍ በሉ እዚህ ጋ---ይሄን ቋንቋ እያበላሻችሁ ነው፤ እንዲህ ነው መሆን ያለበት የሚል የሚከበር---- ፈረንሳዮቹ ለምሳሌ አላቸው፤ ተቋሙ ነው ሁሉንም የሚወስነው:: በዘፈቀደ እንዳይሰራ እኮ ነው፤ ሁሉ ነገር ዝብርቅርቁ ሲወጣ አናርኪ ነው የሚሆነው መጨረሻ ላይ፡፡ ሁሉም ባለ ጉዳይ ይሆናል፤ ሁሉም ሃላፊ ነኝ ይላል፤እና የፈለገው ሰው የፈለገውን ቃል ፈጥሮ፣ የፈለገው ቦታ ይደነቁረዋል፤ይሄ ልክ አይደለም የሚባልበት መንገድ የለም፤ሁሉም በየቤቱ ብቻ ነው የሚያዝነው፡፡--
(ገጣሚና ተርጓሚ ነቢይ መኮንን፣ በሸገር ኤፍኤም ከጋዜጠኛ  መዓዛ ብሩ ጋር ካደረገው ጣፋጭ ወግ የተወሰደ)  
 • የግብፅ ልጆች ከእናታቸው ጡት ቀጥሎ የህልውናቸው መሠረት ተደርጎ የሚነገራቸው ዐባይ ነው
   • ሁላችንም የየራሳችንን ችቦ ደምረን ካቀጣጠልን፣ የድህነት ጨለማ ከሀገራችን ይወገዳል
   • የዐባይን ጉዳይ ከፖለቲካና ከፓርቲ ጋር ለማገናኘት መሞከር ነውር ነው
   • የዐባይ ግድብ እኛ ታሪክ መሥራት እንድንችል የተፈጠርልን ዕድል ነው


          ቢኒ ምዕራፍ ወይም ወ/ሩፋኤል አለሙ ከ260 በላይ የሙዚቃ ክሊፖችን በዳይሬክርነትና በስክሪፕት ጸሃፊነት አዘጋጅቷል፡፡ በብስራት 101.1 ሬዲዮና በአሀዱ 94.3 ሬዲዮ ለ4 ዓመታት የሰራ ሲሆን የምዕራፍ ፕሮሞሽን ባለቤትም ነው፡፡ ቢኒ በምዕራፍ ፕሮሞሽን ለህዳሴው ግድብ የገቢ ማሰባሰቢያ የተሰሩት የ8100A ማስታወቂያ ቁጥር አንድና ሁለት ላይ በሃሳብ አፍላቂነት፣ በግጥምና ዜማ ደራሲነት አስተዋጽዖ ያደረገ ሲሆን በቅርቡ ደግሞ ለህዝብ የቀረበውን ;የዓባይ ዘመን ልጆች; የሙዚቃ ክሊፕ ግጥምና ዜማን በመድረስ ፕሩዱዩስ አድርጓል፡፡ የአዲስ አድማስ አምደኛ ደረጀ በላይነህ፤ ከቢኒ ምዕራፍ ጋር በሥራዎቹና በህዳሴ ግድብ ዙሪያ ወኔና መንፈስ የሚያነቃቃ ወግ አውግተዋል፡፡ እነሆ፡-

                  ለህዳሴው ግድብ በሰራሃቸው ሥራዎች  ያገኘኸው ምንድን ነው?
የሠራሁት የሀገሬ ጉዳዩ ስለሚመለክተኝ ነው፡፡ ከዚህ በተረፈ የታላቁ ህዳሴ ግድብ አስተባባሪ ብሔራዊ ምክር ቤት ፕሬዚዳንት ከሆኑት አቶ ደመቀ መኮንን የምስክር ወረቀት ተቀብያለሁ፤ ክፍያን በተመለከተ ድርጅቴም እኔም ያገኘነው ነገር የለም፤ የሰራነው በነፃ ነው፡፡ ለህዳሴው ግድብ ምዕራፍ ፕሮሞሽንና እኔ የሠራነው ይህ ብቻ አይደለም፤ አፋር ሉሲ የተገኘችበት ሥፍራ ድረስ ከደምፃዊው ሀሴን ዓሊ ጋር በመሄድ የአፋርኛ ዘፈን ክሊፕ ሠርተን፣ ለታላቁ ህዳሴ ግድብ አስተባባሪ ጽ/ቤት አስረክበናል:: ይህ ሁሉ ግን በገንዘብ ለማይተመነው ለሀገሬ ልማት የሠራሁት ሥራ ነው፡፡ ብዙ ጊዜ  ሀገራዊ ጉዳዮች ይኮሮኩሩኛል፤ ስሜት ይሰጡኛል፡፡ ለሦስተኛ ዙር የ8100A ልሠራ የተነሳሁት ክብርት ፕሬዝዳንቷ በቤተ መንግሰት ውስጥ ተዘጋጅቶ በነበረው የኪነ ጥበብ ሰዎችን ያሣተፈ ፕሮግራም ላይ ያደረጉት ንግግር ልቤን ስለነካው ነው:: ፕሬዚዳንቷ ግብፆች ስለ ናይል እየሠሩ ስላለው ነገር አንስተው ከእኛ ጋር በማነፃፀር ሲናገሩ፣ ወዲያው ሀሳብ በውስጤ ተፀንሶ፣ ግጥምና ዜማውን እዚያው ጀመርኩት፡፡
“የዐባይ ዘመን ልጆች” የሚለው የሙዚቃ ክሊፕ ምን ያህል ወደ ህዝቡ ገብቷል?
በተለያዩ ሚዲያዎች ላይ እየቀረበ ነው:: ህዝቡም እንደተደሰተና እንደተቀበለው ልዩ ልዩ ግብረ መልሶችን እያገኘን ነው:: ገንቢ አስተያየቶች ደርሰውናል፡፡ ክሊፑን የሠራነው ቀድሞ “የኛ” የሚል ስያሜ ከነበራቸውንና አሁን “እንደኛ” እየተባሉ ከሚጠሩት ወጣቶች ጋር ነው፡፡ የእነርሱ ቡድን በተለመደው አካሄድ ከራሳቸው ቡድን ውጭ ሌላ ሰው አያሰሩም፡፡ ይህ ግን የሀገር ጉዳይ ስለሆነ ያለምንም ማቅማማት በሙሉ ልብ አብረውን ሠርተዋል፡፡  በክሊፑ ላይ መሀል የሚጫወተውን መላኩ መስፍን የሚባል ወጣት አሳትፈዋል፡፡ ለሀገር ያላቸው ፍቅር የሚገርምና የሚደንቅ ነው:: በዚሁ አጋጣሚ ላመሰግናቸው እወዳለሁ:: የመዝሙሩ ሀሳብ ሲመጣም እንዴት ልሥራው የሚለው ነገር ከብዶኝ ነበር፡፡ ስለ ዐባይ ለመሥራት “ወዴት መሄድ አለብኝ” ብዬ የሄድኩት ወደ አድዋ ድል ነበር፡፡ ዐድዋ ግዙፍ የጀግንነት ተጋድሎ ታሪክ፣ የአብሮነታችን መቀነት ነው፡፡ ወደዚያ ሀሳብ ደርሼ ስመለስ የሚያሥፈልገን ነገር አንድነት ነው፡፡ ወደ ቀጣዩ ዘመን ስመለከት ደግሞ ከፊት ለፊት ያለውን ትውልድ አሰብኩኝ፤ እሱ ደግሞ ዕዳ ያለብን ሰዎች እንደሆንን አሣየኝ፡፡ እናም አሁን ያለነው “የዐባይ ዘመን ሰዎች” ይህንን አደራ መወጣት እንደሚገባን ተሰማኝ፡፡ ይህን ባናደርግ  መጪው ትውልድ “ድህነትና ኋላቀርነት አወረሳችሁን!” ብሎ ይወቅሰናል፡፡ ስለዚህ የሦስቱን ትውልድ ሠንሠለት አቆራኝቼ ለመስራት ሞክሬያለሁ::
አባቶቻችን በደም መስዋትዕነት ነፃ ሀገር እንዳስረከቡን እኛ ደግሞ በላባችን በዕውቀታችንና ትጋታችን ከድህነት የተላቀቀች ሀገር ማስረከብ አለብን ማለትህ መሰለኝ?
ይህን ለማድረግ መጀመሪያ መግባባት መቻል አለብን፡፡ ዐባይ መጀመሪያ ለእኛ ምንድነው? ይህን መፈተሽ ያስፈልጋል:: እንደሚታወቀው የቱም ሰው ቢሆን የሚከተለውና ዋጋ የሚሰጠው ለሚወድደው ነገር ነው፡፡ አሁን ባለው ተጨባጭ ሁኔታ ዐባይን እንድንወድድ ተደርጎ የተሠራብን ነገር አይታየኝም፡፡ ለዚህ ነው ቢያንስ “ሰዎች ዐባይ የኛ ነው” የሚለው ስሜት እንዲሰማቸው አድርገን ለመስራት የሞከርነው፡፡ ዐባይ ለኛ ምን ጥቅም ይሰጣል? መገደቡ ያስፈለገው ለምንድነው? ዐባይ ውሃ ብቻ ነው? ጥቅም ካለው ጥቅሙ እስከ የት ድረስ ነው? የሚለውን ነገር፣ ሰዎች አዕምሮ ውስጥ መፍጠር ያስፈልጋል:: ስለዚህ እኛ እንደሞተር ማስነሻ የሆነን ነገር፣ ክብሪት መጫር ነው የሞከርነው:: ሕዝቡን አነሳስተህ ጆሮውን ሲከፍትና ልቡን ሲያዘጋጅ፣ ስለ ዐባይ መናገር የሚችሉ ሰዎች  በዕውቀትና በታሪክ ላይ የተመሠረተ  ነገር መናገር ይችላሉ፡፡ ባለሙያዎች መናገር ቢችሉ ጥሩ ውጤት ይገኛል የሚል እምነት አለኝ፡፡ ሁሉም ሰው በየፈርጁና በየሙያው የሚቻለውን ሁሉ ቢያዋጣ፣ ወደ ግባችን ለመድረስ በሁሉም ላይ የእኔነት ስሜት እንዲፈጠር ያደርጋል፡፡
የግብፅ ልጆች ከእናታቸው ጡት ቀጥለው የታሪክ ጉዳይ ሲያነሱ የህልውናቸው መሠረት ተደርጎ የሚነገራቸው ዐባይ ነው:: ስለዚህም የዐባይ ጉዳይ ሲነሳ፣ ዐባይን የራሳቸው አድርገው እንዲያስቡት ተደርጓል:: አንዳንዶቹ የዐባይ ምንጭ ሀገራቸው ውስጥ እስኪመለስላቸው ድረስነው የተሰራው:: እኛ ግን ከምንጩ ተፈጥረን፣ ምንጩን ያለ ማወቃችን ሁኔታ ያሳዝናል፡፡ ሕዝቡም የማወቅ ጉጉት ሊኖረው ይገባል፡፡ መቼም ቢሆን ዛሬ የምትዘራው ዘር ነገ አዝመራ ይሆናል፤ ፍሬ ይሰጣል፡፡ ስለዚህ ስለ ዐባይ የምንሠራው በሙሉ እንድትወደው እንድትተጋለትና እንድታስፈፅመው የሚያደርግ መሆን አለበት የሚል እምነት አለኝ፡፡ እኛም በዚህ መነሻ ትንሽ የራሳችንንን ለማዋጣት ብለን የሠራነው ነው፡፡
እንደ ዐድዋ በአብሮነት ሆነን፤
ዐባይን እንጨርሳለን!
ሆ! ብለን ተምመን በፍቅር ዜማ
ይገደብ ዐባይ ከሀገር ይስማማ!! --- ያልነው ለዚህ ነው፡፡
ዐድዋን ስታስብ ትልቅ አቅም ይሰጥሃል:: ኢትዮጵያውያን የውስጥ ልዩነቶች እንኳ ቢኖራቸው በጋራና በአንድነት ሆነው፤ ቦታው ድረስ ሄደው በመዋጋት ሀገር አስረክበውናል፡፡ እኛም ለልጆቻችንን የምንነግረው ምንድን ነው  ለሚለው ጥያቄ፤ የሚዳሰስ ሀውልት፤ የሚሻገር ታሪክ ሊኖረን ይገባል፡፡ እኔ እንደሚመስለኝ፤ የዐባይ ግድብ እኛ ታሪክ እንድንሠራ የተመቻቸ ዕድል ነው፡፡ ነገሩን ከፖለቲካና ከፓርቲ ጋር ለማገናኘት መሞከር ነውር ነው፡፡ “ዐባይ የእኔ ነው፤ ግድቡ የእኔ ነው” ካልክ አንተ መጀመሪያ እዚያ ውስጥ መግባት አለብህ፤ ከዚያ የእኛ ይሆናል፡፡ “የእኛ ነው” ብለህ የቡድን መጠሪያ ሰጥተኸው፣ ሁሉም ሰው ሳያምንበት ከምትቆሰቁሰው “የእኔ ነው” ብዬ እኔ ራሴ ማመን አለብኝ፡፡ ባለቤትነት ሊሰማኝ ይገባል፡፡ እኛም በዚህ ስሜት ለመስራት ሞክረናል፡፡ በዚህ አጋጣሚ የኢትዮጵያ ወጣቶች ለፈጠራና ለስራ የተዘጋጁ መሆናቸውን ማሰብ ያስፈልጋል:: ግን የሚያነሳሳቸው መሪ ያስፈልጋል፡፡ ይህ የሚሆነው ደግሞ ለልማት ብቻ ሳይሆን ለጥፋትም ነው፡፡ መስመር ካሳትካቸው በዚያው ስለሚፈሱ ችግር ይፈጠራል::  መልካም ዘር ከዘራህ ደግሞ፤ ወጣቱን ከያዝከውና “ያንተ ነው” ካልከው፣ ስለ ጦርነት ሳይሆን ቴክኖሎጂን በመጠቀም ሀገሩን ለማልማት እስከ መጨረሻው ግብ ድረስ ሊሄድ ይችላል፡፡
ስለ ዐባይ የምትነግረውም ነገር ሲገባው ስሜት ይሰጠዋል፡፡ ካልገባው ደግሞ ምኑም አይደለም፡፡ በተለይ ሚዲያዎች በዚህ ነገር ላይ ማርሻቸውን ቀይረው ቢሰሩ ብዙ ትርፍ እናገኛለን ብዬ አስባለሁ፡፡
ግብፅ በከፍተኛ ደረጃ የውሃ ሙሌታችንን ለማዘግየት የማትረግጠው ደጅ፣ የማትቀጥፈው ቅጠል የለም፤ እኛ ጋ ደግሞ ክፍተት አለ፡፡ በዚህ ጉዳይ ላይ ምን ታስባለህ?
አንድ ጉዳይ ላይ የተለያዩ ሰዎች በየራሳቸው የሚሠሩት ቢኖርም ግን ሁሌም እንደ አቅሙና በሚመለከተው ጉዳይ ላይ መሥራት አለበት፡፡ ለምሳሌ በውሃ ጉዳይ ላይ ያጠና ሰው፣ ስለ ውሃና ውሃ ይናገር፤ በዲፕሎማሲ የተሻለ ጥበብና ዕውቀት ያለው ሰው፣ የዲፕሎማሲ ሥራ ይስራ፡፡ ተወዳጅ የሆኑ የኪነጥበብ ሰዎች ደግሞ ሕዝቡን በማነሳሳትና በማነቃቃት ይስሩ! ሚዲያውም የራሴ ጉዳይ ነው በሚል በሀገር ውስጥና በውጭ ሀገር ቋንቋዎች የአለምን ሕዝብ የማሳመን ሥራ ሊሠራ ይገባል፡፡ ግብፆች የበለጡን በዚህ ይመስለኛል፡፡ በእንግሊዝኛ፣ በአረብኛና በሌሎችም ቋንቋዎች የዓለምን አመለካከት ለመቀየር እየሠሩ ነው፡፡ ይሔን ደግሞ ሌሎችም እያስተጋቡላቸው ነው:: በዚህም የተነሳ ዕርዳታ የምናገኝባቸውን መንገዶችና ብድሮች ለመዝጋት ይሞከራሉ:: ይሁንና የኛ ግድብ የተጀመረው ምንም የሌላት ኢትዮጵያዊ እናት ከመቀነቷ ፈትታ ባዋጣችው፣ ወታደሩ ከደሞዙ ቆርጦ በሰጠው ገንዘብ ነው፡፡ ገበሬው ከብቶቹን በጎቹንና ጥጃዎቹን ሳይቀር ሰጥቶ፣ ህፃናት ከትምህርት ቤት ምሳቸው ቀንሰው፣ መገደብ የጀመርነው ግድብ ነው፡፡ ይህን ነገር ለሕዝቡ መንገርና ሕዝቡንና ዓለም አቀፉን ማህበረሰብ ማሳመን ያስፈልጋል፡፡ ጉዳዩ የጥበብ እንጂ የጦር መሳሪያ አይደለም:: ስለዚህ የመገናኛ ብዙሀን (ሚዲያዎች) ሚናቸው ትልቅ የሚሆነውም ለዚህ ነው:: ዐባይ ደግሞ ለኢትዮጵያ የህልውና ጉዳይ ነው፡፡ በዚህ አጋጣሚ የአሀዱ ሬድዮ ዋና ስራ አስኪያጅ ሊዲያ አበበ፣ ሬድዮ ጣቢያው ሥራ ከጀመረ አንስቶ ለዓመታት ያለማቋረጥ “የኢትዮጵያ ወንዞች” በሚል በተለይ በዐባይ ላይ ትኩረት አድርጋ የምትሰራውን ስራ ማድነቅ እፈልጋለሁ፡፡ እንዲህ አይነት ግለሰቦች ሚዲያ ላይ ሲኖሩ ለውጥ ያመጣሉ፡፡ አሁንም እንዲህ አይነት ሰዎች ያስፈልጉናል፡፡ ሚዲያ ራሱን የቻለ የጦር መሳሪያ ነው፡፡
በአብዛኛው ግን ሚዲያ ላይ የሚታየው ነገር በግል ጉዳያችን ላይ ያተኮረ ነው፡፡ ቢበዛ እግር ኳስ አካባቢ ነው የሚያተኩረው:: የጋራ የሆኑ ሀገራዊ ጉዳዮች ላይ ማተኮር ያነሰን ይመስለኛል፡፡ ኢትዮጵያ ደግሞ ብዙ የጋራ የሆኑ አስተሳሳሪ ነገሮች ያሏት ሀገር ነች፡፡ በጋራ የሳቅናቸው ሳቆች፣ በጋራ ያለቀስናቸው ለቅሶዎች አሉ፡፡ አብረን ተርበናል፣ አብረን ተሰድበናል፣ ከልዩነቶቻችን አንድ የሚያደርጉን ነገሮች ይበዛሉ፡፡ እነርሱ ላይ መስራት አለብን፡፡
ነገሮችን ከፖለቲካ ጋር ማያያዝ ያለብንም አይመስለኝም፡፡ ለሀገር የሚሰራውን ልማት ዛሬ ስልጣን ላይ ያሉ ሰዎች፤ ነገ ከስልጣን ሲነሱ ይዘውት አይሄዱም፡፡ የህዳሴው ግድብ ፕሮጀክትም የህዝብ ነው፡፡ ስለዚህ ሁሉም ሰው ባለው ችሎታና አቅም፣ ዕውቀትና ክህሎት ተረባርቦ ይህንን ፕሮጀክት ከግብ ማድረስ አለብን፡፡ “የእኔ ነው!” የሚል የፀና አቋምም ያስፈልገናል፡፡ በተለይ የህዳሴው ግድብ ህዝባዊ ማስተባባሪያ ጽ/ቤት ያሉ ሰዎች፤ ከእኛ በተለየ በተሻሉ፣ በአራት ዓይኖች ማየት፣ በአራት ጆሮዎች መስማት ይጠበቅባቸዋል፡፡ ግብፆች ከሚሰሩት ስራ በተመጣጠነ አቅም ውስጥ መገኘት ይጠበቅብናል፡፡ ከጎናችን የሚቆሙ ሀገራት የመኖራቸው ያህል በባላንጣነት የሚገዳደሩን እንዳሉም መዘንጋት የለብንም፡፡ ስለዚህ ብዙ መስራት አለብን፡፡ እኔና ድርጅቴ ምዕራፍ ፕሮሞሽን ያደረግነውም ይህንኑ ነው፡፡
የዐባይ ጉዳይ የሀገራችን ዐብይ ጉዳይ ነው፤ ይህንን ስራ በጊዜና በአግባቡ ካልሠራን በትውልድ ተወቃሽ ከመሆን አናመልጥም:: ለመጪው ትውልድ ዕዳ ጥለን መሄድም የለብንም፤ አሳፋሪና አስወቃሽ ከሆነ የስንፍና ስራ ወጥተን፣ እጅ ለእጅ ተያይዘን ይህን ፕሮጀክት ከግብ ማድረስ አለብን የሚል እምነት አለኝ፡፡ በተረፈ ከግብፅ ህዝብ ጋር የሚያገናኘን ምንም ዓይነት ክፉ መንገድ የለም፡፡ እኛ በልተን እነርሱ ጦም ይደሩ ማለት የኢትዮጵያውያን የሕይወት ዘይቤ አይደለም፡፡ ነገር ግን እኛ በልተን እናንተ ጦም እደሩ! የሚለውን መቀበል ልማዳችን አይደለም፡፡ የሚያከብሩንን እናከብራለን! ከእጃችን ማስነጠቅ ግን በታሪካችን ውስጥ የሌለ ነው፡፡
በኩበት ጢስ ዓይናቸው እየተጨናበሰ፣ ዳቦ የሚጋግሩልን የዐባይ ልጆች ታሪክ መቀየር አለበት፡፡ “ደህነትን እንደውርስ መቀባበል የሚቆመው በእኛ ዘመን መሆን አለበት” ብለን በጽናት መቆም አለብን:: “የዐባይ ዘመን ልጆች” ቁርጠኛ ሆነን ድህነትን ካልቀረፍን፣ የእናቶቻችንን ህይወት ከእንግልት ካላወጣን ኖረን ማለፋችን ፋይዳ ቢስ ነው፡፡ እንግዲህ እኛም በዚሁ የዕድገትና የልማት ደመራ ውስጥ አንድ ችቦ መወርወር አለብን ብለን ያለንን ሰጥተናል፡፡ ሁላችንም የየራሳችንን ችቦ ደምረን ካቀጣጠልን፣ የድህነት ጨለማ ከሀገራችን ይወገዳል፡፡ የብርሃን ዘመን ይመጣል፡፡ ስለዚህ ከሁሉም በላይ አንድ ሆነን፣ ለአንድ ዓላማ መቆም ያለብን ጊዜ አሁን ነው፡፡ ዐባይን የስላቅና የወቀሳ መዝሙር ተቀባይ ከመሆን ወደ ብልፅግና መሸጋገሪያ ድልድይ መለወጥ ያስፈልጋል፡፡Page 11 of 493