Thursday, 02 May 2024 00:00

ሕብረት ባንክና ማስተር ካርድ “ህብር ማስተር ካርድን” አስተዋወቁ

Written by 
Rate this item
(0 votes)

ሕብረት ባንክና ማስተር ካርድ የቅድመ ክፍያ ህብር ማስተር ካርድ አገልግሎትን አስተዋወቁ።
ሁለቱ ተቋማት ከትላንት በስቲያ ሀሙስ በህብረት ባንክ ዋና መስሪያ ቤት አዳራሽ ነው አገልግሎቱን በጋራ ያስተዋወቁት፡፡
ህብረት ባንክ ከማስተር ካርድ ጋር በመተባበር እውን ያደረገው ህብር የቅድመ ክፍያ ሕብር ማስተር ካርድ አገልግሎት ደህንነቱ የተጠበቀ፣ ኢትዮጵያዊያን በሌሎች የዓለም ሀገራት የሚኖራቸውን ግብይት ምቹ በሆነ ከባቢ እንዲያከናውኑ የሚያስችል፣ የፋይናንስ አካታችነትንና ዲጂታል ትራንስፎርሜሽንን ለማምጣት ትልቅ ሚና ያለው ዘመናዊ የባንክ አገልግሎት መሆኑን የህብረት ባንክ ዋና ስራ አስፈፃሚ አቶ መላኩ ከበደ ተናግረዋል፡፡
ሥራ አስፈፃሚው አክለውም የቅድመ ክፍያ ሕብር ማስተር ካርድ አገልግሎት “ዱዋል ኢንተርፌስ” (Dual Interface) ያለው በመሆኑ ካርዱን ወደ ክፍያ ማሽኑ በማስገባት ወይም በማስጠጋት አገልግሎት በቀላሉ እንዲያገኙ ያደርጋል ያሉት ዋና ስራ አስፈፃሚው፤ ሕብረት ባንክ ለቴክኖሎጂና ለትብብር ሥራዎች ትኩረት እንደሚሰጥም አብራርተዋል። ዋና ሥራ አስፈፃሚው አክለውም፤ “በህብረት ባንክ ውስጥ አጋርነትና ቴክኖሎጂ የዕለት ተእለት ተግባራችን ብቻ ሳይሆኑ የባንካችንን ስኬት የሚያግዙ ናቸው፤ ይህ ይፋ የተደረገው የቅድመ ክፍያ ህብር ማስተር ካርድ አገልግሎትም የዚህ ማሳያና ባንኩ ለያዘው የዲጂታል ፋይናንሽያል አካታችነት ወሳኝ ምዕራፍ ነው” ሲሉ በአፅንኦት ገልፀዋል። የማስተር ካርድ የምስራቅ አፍሪካና የህንድ ውቅያኖስ ደሴቶች ሲኒየር ምክትል ፕሬዚዳንትና  ካንትሪ ማናጀር ሻህሪያር አሊ በበኩላቸው በአጋርነት መስራት እጅጉን አስፈላጊ መሆኑን ገልፀው፣ ከህብረት ባንክ ጋር በህብረት ማስተር ካርድ አገልግሎት የተደረገው ትብብር፣ በኢትዮጵያ ብቻ ሳይሆን በመላው አፍሪካ የፋይናንስ አካታችነትንና ዲጂታላይዜሽንን ዕውን ለማድረግ ያለንን ቁርጠኝነት ያሳያል ብለዋል፡፡ የካርድ አገልግሎቱ ከክፍያ አማራጭነት ባሻገርም፣ ኢትዮጵያዊያን በዓለም አቀፍ ገበያ በቀላሉና ደህንነቱ በተጠበቀ ሁኔታ መሳተፍ የሚያስችላቸው መሆኑንም ተናግረዋል፡፡
በማስተር ካርድ የአፍሪካ ፕሬዚደንት ማርክ ኤሊያት ደግሞ ትብብሩ በአህጉር ደረጃ በሚኖረው በጎ ተፅእኖ ላይ ተመርኩዘው እንደተናገሩት ከህብረት ባንክ ጋር በመተባበር ይፋ የተደረገው የቅድመ ክፍያ ህብር ማስተር ካርድ አገልግሎት፣ ማስተር ካርድ በአፍሪካ የሚያካሂደውን የኢኮኖሚ ትራንስፎርሜሽን ለማሳካት የሚያደርገውን ጥረት ማሳያ ነው ብለዋል፡፡  
ህብረት ባንክ በኢትዮጵያ ከሚገኙ ቀደምት የግል ባንኮች አንዱ ሲሆን ለደንበኞች ምቹና ቀልጣፋ የሆነ ዘመናዊ የባንክ አገልግሎት በመስጠትና ቴክኖሎጂዎችን በማስተዋወቅ የተመሰከረለት ባንክ መሆኑም ተነግሯል። በይፋ የተዋወቀው የቅድመ ክፍያ ህብር ማስተር ካርድ አገልግሎት፣ የባንኩ ደንበኞች ወደ ውጪ ሲሄዱ በቀላሉ የሚገበያዩበት በካርድ ላይ የሚሞላ የውጪ ገንዘብ ያለበት ዲጂታል ካርድ ሲሆን፤ በዋናነት ሶስት ጠቀሜታዎች አሉትም ተብሏል፡፡
አንደኛው በውጪ ሀገር ያሉ ሆቴሎችና ድርጅቶች ገንዘብ በካሽ መቀበል እያቆሙ መሆኑን ተከትሎ፣ ደንበኞች በውጪ ቆይታቸው በካርዱ ዲጂታል ግብይት እንዲፈፅሙ የሚያስችል ሲሆን፤ ሁለተኛው ጠቀሜታው በካሽ ለማግኘት የሚያስቸግረውን ዶላር በካርዳቸው ሞልተው በመያዝ ካሽ ከመያዝ ይድናሉ ተብሏል። ሶስተኛው ጠቀሜታም በካርዳቸው የሞሉት ገንዘብ በመጀመሪያው ጉዟቸው ባያልቅ የተረፈውን ለሌላ ጉዞ በማቆየት መገልገል ይችላሉም ተብሏል፡፡


Read 409 times