Monday, 22 April 2024 17:47

አፍሮ-ኤዥያ ዓለማቀፍ የጤና ኤክስፖ በቅርቡ በመዲናዋ ይካሄዳል

Written by 
Rate this item
(0 votes)


*በኤክስፖው ከ30ሺ በላይ ለሚሆኑ ጎብኚዎች  ነጻ የህክምና  ምርመራ ይሰጣል

አፍሮ-ኤዥያ ዓለማቀፍ የጤና ኤክስፖ፣ እዚህ አዲስ አበባ በኤግዚቢሽን ማዕከል፣ ከግንቦት 9-11 ቀን 2016 ዓ.ም ለሦስት ቀናት  ሊካሄድ መሆኑ ተገለጸ፡፡

በኤክስፖው ላይ ከ400 በላይ የአገር ውስጥና የውጭ ድርጅቶች፣ ከ30ሺ በላይ ጎብኚዎችና  ከ2ሺ በላይ የጤና አጠባበቅ ባለሙያዎች  ይሳተፉበታል ተብሏል፡፡

የጤና ኤክስፖውን አስመልክቶ አዘጋጆቹና አጋር ተቋማት  ዛሬ ከሰዓት በኋላ 8 ሰዓት ላይ በራማዳ  ሆቴል የሚዲያ ባለሙያዎችና ጥሪ የተደረገላቸው እንግዶች በተገኙበት  ሰፊ ጋዜጣዊ መግለጫ ሰጥተዋል፡፡



በጋዜጣዊ መግለጫው ላይ እንደተመለከተው፣ በጤና ኤክስፖው  ላይ የፓናል ውይይቶች፣ ዎርክሾፖችና ኤግዚቢሽኖችን ጨምሮ በርካታ ኹነቶች ይቀርባሉ፡፡ የጤና ባለሙያዎች የልምድ ልውውጥ የሚያደርጉበትና የቴክኖሎጂና የዕውቀት ሽግግር የሚካሄድበት እንዲሁም የትስስርና የትብብር ዕድሎች የሚፈጠርበት  መድረክ እንደሚኖርም ተጠቁሟል፡፡

ኤክስፖው በጤና አጠባበቅ ኢንዱስትሪ ውስጥ የህዝብ ጤናን፣ ፋርማሲዩቲካልስን፣ የህክምና ቴክኖሎጂንና ሌሎች በርካታ ርዕሰ ጉዳዮችንና ዘርፎችን እንደሚሸፍን የተገለጸ ሲሆን፤ ይህ ሁሉን አቀፍ አቀራረብም ተሳታፊ ድርጅቶችና ጎብኚዎች በተለያዩ መስኮች ከአዳዲስ ዕድገቶችና ፈጠራዎች ጋር እንዲተዋወቁ ዕድል ይፈጥራል ተብሏል፡፡

“ድልድዮችን እንገንባ፣ ህይወትን እናድን” በሚል መሪ ቃል በሚካሄደው በዚህ ዓለማቀፍ የጤና ኤክስፖ፤ ከ30ሺ በላይ ለሚሆኑ ጎብኚዎች ነጻ የጤና ምርመራ የሚከናወን ሲሆን፤ ለጤና አጠባበቅ  ባለሙያዎችም ነጻ ሥልጠና እንደሚሰጥ ታውቋል፡፡

ለሦስት ቀናት በሚቆየው የአፍሮ- ኤዥያ ዓለማቀፍ የጤና ኤክስፖ ላይ ከህንድ፣ ዱባይ፣ ታይላንድ፣ ቱርክ፣ ኢንዶኔዥያ፣ ማላይዥያና ሌሎችም አገራት የተውጣጡ በጤና ላይ የሚሰሩ ተቋማትና ባለሙያዎች እንደሚሳተፉበት ተጠቁሟል፡፡

ኤክስፖው ከወትሮው በተለየ በቢዝነስ ላይ ብቻ የሚያተኩር ሳይሆን፣ ተቋማት ማህበራዊ ሃላፊነታቸውን ለመወጣት ልዩ ዕድል የሚያገኙበት እንደሆነም ተነግሯል፡፡

ይህን ዓለማቀፍ የጤና ኤክስፖ ኤፍዚ ማርኬቲንግና ኮምዩኒኬሽን ኃ.የተ.የግ. ማህበር ከሰላም ኸልዝ ኮንሰልታንሲ ጋር በመተባበር ያዘጋጀው ሲሆን፤ ሳልማር ኮንሰልታንሲ፣ የኢትዮጵያ ጤና ሚኒስቴር፣ የኢፌዲሪ የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች ባለሥልጣን፣ የኢትዮጵያ ምግብና መድሃኒት ባለሥልጣን፣ የአዲስ አበባ ጤና ቢሮ፣ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የምግብና መድሃኒት ባለሥልጣን እንዲሁም የአዲስ አበባ ንግድና ዘርፍ ማህበራት ምክር ቤት በአጋርነት እንደሚሳተፉበት ታውቋል፡፡

Read 590 times