Tuesday, 09 April 2024 20:23

ሙሉቀን መለሰ በ70 ዓመቱ ከዚህ ዓለም በሞት ተለየ

Written by 
Rate this item
(5 votes)
የቀድሞ ድምፃዊ ሙሉቀን መለሰ ባደረበት ህመም በህክምና ሲረዳ ቆይቶ በተወለደ በ70 ዓመቱ ከዚህ ዓለም በሞት ተለይቷል፡፡
ከሦስት አስርት ዓመታት በላይ በሀገረ አሜሪካ ኑሮውን ያደረገው ሙሉቀን መለሰ፤ የሙዚቃውን ዓለም በመተው በመንፈሳዊ የሙዝሙር ስራዎች ውስጥ ያሳልፍ እንደነበር ይታወሳል።
 
ሙሉቀን መለሰ በጎጃም ክፍለ ሀገር አነደድ ወረዳ ውስጥ ዳማ ኪዳነ ምሕረት በምትባል መንደር በ1946 ዓ.ም እንደተወለደ ግለታሪኩ ያወሳል። አሥር ዓመት ሲሆነው እናቱ ስለሞቱ፤ አዲስ አበባ ይኖሩ ከነበሩ አጐቱ ጋር እንዲማር ብለው ያመጡት ሙሉቀን መለሰ፤ ኮልፌ ሰፈር ጳውሎስ ትምህርት ቤት ሊገባ ችሏል።
 
ለሙዚቃ ልዩ ፍቅር የነበረው ድምፃዊው፤ እርሱ በነበረበት አካባቢ በተከፈተው የሙዚቃ ትምህርት ቤት ገብቶ በአቶ ተፈራ አቡነ ወልድ አማካይነት ለስድስት ወራት የዘለቀ የትምህርት እገዛ አግኝቷል።
ገና የ13 ዕድሜ ታዳጊ ሳለ ሙዚቃን የጀመረው ድምፃዊው፤ በ1958 ዓ.ም በፈጣን ኦርኬስትራ ውስጥ ተቀላቅሎ በመግባት ለሁለት ዓመታት ያህል መስራት ችሏል። ከእዚያ በማስከተል በ1960 ዓ.ም ወደ ፖሊስ ኦርኬስትራ ክፍል በመግባት ይበልጥ በሙዚቃ ስራው ዝናን ማትረፍ ችሎ ነበር።
በ1972 ዓ.ም ላይ ደግሞ ከዳህላክ ባንድ ጋር ተቀላቅሎ ሰርቷል፡፡ እስከ 1980ዎቹ ድረስ በነበሩት ዓመታት እጅግ ተወዳጅ የሙዚቃ ስራዎችንም መስራት ችሏል።
ድምጻዊው፤ የአንጋፋዋ ሁለገብ ከያኒት የአለምፀሐይ ወዳጆ እና የተስፋዬ ለሜሳን ግጥምና ዜማዎች አቀንቅኗል።
ሙዚቃ በቃኝ ብሎ ራሱን ከሙዚቃው ዓለም እስካገለለበት ጊዜ ድረስ በርካታ የሙዚቃ ስራዎችን ለትውልድ አበርክቷል።
ከ1980ዎቹ በኋላ ፊቱን ወደ መንፈሳዊ ስራዎች በማዞር የመዝሙር ስራዎችን ሲሰራ ቆይቷል።
እስከ ህልፈተ ሕይወቱ ድረስ በሀገረ አሜሪካ ኑሮውን አድርጎ በእዚያው ቆይቷል።
የዝግጅት ክፍላችን በአንጋፋው ድምጻዊ ሙሉቀን መለሰ ህልፈት የተሰማውን ሀዘን እየገለጸ፤ ለቤተሰቦቹና ለአድናቂዎቹ መጽናናትን ይመኛል።
 
Read 1137 times