Wednesday, 03 April 2024 10:33

ጠ/ሚኒስትሩ ተፎካካሪ ፓርቲዎች ሰብሰብ ብለው እንዲታገሉ ጥሪ አቀረቡ

Written by 
Rate this item
(1 Vote)

ጠ/ሚኒስትሩ ተፎካካሪ ፓርቲዎች ሰብሰብ ብለው እንዲታገሉ ጥሪ አቀረቡ

”60 ፓርቲዎች ሆናችሁ ልንደግፋችሁ ይቸግረናል“

ለሁለት ወር ግድም ከተለያዩ የማህበረሰብ ክፍሎች ጋር ውይይት ያደረጉት ጠ/ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ፤ ባለፈው ሰኞ መጋቢት 23 ቀን 2016 ዓ.ም በመቶዎች ከሚቆጠሩ የተፎካካሪ ፓርቲዎች አመራሮች  ጋር በተለያዩ አገራዊ ጉዳዮች ዙሪያ ተወያይተዋል፡፡

የፓርቲ አመራሮቹ በውይይቱ ላይ ለጠ/ሚኒስትሩ የተለያዩ ጥያቄዎችን ያቀረቡ ሲሆን፤ ከእነዚህም መካከል የሰላምና ጸጥታ ችግር፣ የህግ የበላይነት አለመኖር፣ የፖለቲካ  ምህዳር መጥበብ፣ የሜጋ ፕሮጀክቶች ተጠያቂነትና  የዜጎች መፈናቀል ጉዳዮች ይጠቀሳሉ፡፡

የፖለቲካ ፓርቲዎች የጋራ ም/ቤት ሃላፊን ጨምሮ አንዳንድ የፓርቲ አመራሮች የቢሮ፣ የአዳራሽና የፋይናንስ ችግር  እንዳለባቸው ጠቅሰው ላነሱት ጥያቄ፣ ጠ/ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ  ምላሽ ሰጥተዋል፡፡

እኛ እንደ ፓርቲ ማድረግ የምንችላቸውን ነገሮች እናያለን ያሉት ጠ/ሚኒስትሩ፤ ያንን ለማድረግ ግን ለፓርቲዎቹ ቅድመ ሁኔታ አስቀምጠዋል - አሁን ያሉት 70 የሚደርሱ ፓርቲዎች 4 ወይም 5 ሆነው ሰብሰብ እንዲሉ፡፡

“አሁን ኢትዮጵያ ውስጥ 66 ወይም 68 ገደማ ፓርቲዎች አሉ፡፡ ለ68 ሊቀ መንበር ቦታ የለንም፤ ለ68 ሊቀ መንበር ቢሮ የለንም፤ 2-3-4-5 ሆናችሁ ብትሰባሰቡ --- ከብልጽግና ጋር 5 ወይም 6 ፓርቲ ብንሆን አንቸገርም ነበር፡፡”  ያሉት ዐቢይ፤ ”ለምሳሌ ዛሬ በውይይቱ ላይ ከእያንዳንዱ ፓርቲ አምስት አምስት ሰው ቢወከል፣ 25ቱም ሰዎች መናገር ይችሉ ነበር” በማለት አስረድተዋል፡፡

 “ስንበዛ መበተን ብቻ ሳይሆን በዚያው መጠን አቅማችንም ውስን ይሆናል፤” ሲሉም አክለዋል፡፡



ጠ/ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ፤ ውይይቱን የቋጩትም  የፖለቲካ ፓርቲዎቹ ሰብሰብ እንዲሉ በመማጸን ነበር፡፡

“እባካችሁ ወደ 4 ወይም 5 ፓርቲ ሰብሰብ በሉ፡፡ ግዴለም ይጠቅማችኋል፡፡ እንደዚያ ከሆናችሁ ፓርላማውም ይከፈታል፤ የምታስቡትም ሥልጣን ይመጣል፡፡ በዋና ዋና ጉዳይ ከተግባባችሁ በጋራ ሆናችሁ ብትታገሉ---አትጠራጠሩ ፓርላማውንም እንከፋፈለዋለን፡፡” ብለዋል፡፡

“እናንተ ግን አሁን 60 ናችሁ፤ ይሄ ለህዝብም ያስቸግራል” ያሉት ጠ/ሚኒስትሩ፤ ”እኔ እንኳን ስማችሁን አላውቀውም፤እንኳን የኢትዮጵያ ህዝብ--” ሲሉም ፓርቲዎቹ ሰብሰብ ብለው እንዲታገሉ መክረዋል፡፡

ጠ/ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ፣ ከዚህ ቀደምም የኢትዮጵያ ተቃዋሚ ፓርቲዎች ሰብሰብ ብለው በጋራ እንዲታገሉ ጥሪ አቅርበው እንደነበር አይዘነጋም፡፡

Read 703 times