Saturday, 30 March 2024 20:41

ንብ ባንክ የተከፈለ ካፒታሉን ወደ 20 ቢሊዮን ብር ለማሳደግ ወሰነ

Written by 
Rate this item
(3 votes)

ሃያኛው የባለአክሲዮኖች አስቸኳይ ጠቅላላ ጉባኤውን መጋቢት 14 ቀን 2014 ዓ.ም በሚሊኒየም አዳራሽ ያካሄደው ንብ ኢንተርናሽናል ባንክ፣ የተከፈለ ካፒታሉን ወደ 20 ቢሊዮን ብር ለማሳደግ ውሳኔ አሳለፈ፡፡    
የባንኩ አዲሱ የዲሬክተሮች ቦርድ ሊቀመንበር አቶ ሺሰማ ሸዋነካ በጉባኤው ላይ ባደረጉት ንግግር፣ ንብ ኢንተርናሽናል ባንክን ወደ ቀድሞ ከፍታው ለመመለስና ላቅ ወዳለ ደረጃ ለማድረስ በሚያስችል ጉዞ ላይ መሆናቸውን ገልጸዋል።
“ንብ ኢንተርናሽናል ባንክ በበርካታ ደንበኞች በተለይም በንግዱ ማኅበረሰብ ዘንድ ተወዳጅ ባንክ ነው’’ ያሉት ሊቀመንበሩ፤ ባለአክሲዮኖች ከምንጊዜውም በበለጠ ድጋፋቸውን እንዲያረጋግጡለት ጠይቀዋል።
ቀደም ሲል እንደ አገርም ሆነ በዘርፉ እንዳሉ ሌሎች ተቋማት ሁሉ ያጋጠሙ የገንዘብ አከል ችግሮች በንብ ባንክ ደረጃ በባሰ መልኩ መስተዋላቸውን በመጥቀስ፣ አሁን ግን አዲስ የተመረጠው የዲሬክተሮች ቦርድ ችግሮችን እያቃለለ መምጣቱን ጠቁመዋል፡፡
ባንኩ፣ “በአዲስ መንፈስ፣ ለላቀ ከፍታ!” በሚል መሪ ቃል ያስጀመረውን የማርኬቲንግ ንቅናቄ ተከትሎም፣ በሂደት የባንኩ ቅርንጫፎች ምንም አይነት የስንቅ ችግር እንዳያጋጥማቸው መሠራቱን ተናግረዋል፡፡ ደንበኞች ከቼክ ምንዛሪ ጋር በተገናኘም ስጋት እንዳይገባቸው መልዕክት አስተላልፈዋል።
ባንኩ በምንጊዜም ባለውለታነት ሊጠቀሱ የሚችሉ የረጅም አመታት ባለአክሲዮኖችና ደንበኞች ያሉት መሆኑን የጠቀሱት ሊቀመንበሩ፤ አሁን ላይ ሁሉም ገንዘባቸውን ሲያስወጡም ሆነ ሲያስገቡ በንብ ኢንተርናሽናል ባንክ እንዲሆን ጠይቀዋል፡፡
የደንበኞቹን እምነት መልሶ ለመገንባት የተለያዩ ሥራዎችን እያከናወነ የሚገኘው ንብ ኢንተርናሽናል ባንክ፤ አስቸጋሪ ባለው የሥራ ወቅት የተከፉ ደንበኞቹን በይፋ ይቅርታ በመጠየቅ በጀመረው አገራዊ የማርኬቲንግ ንቅናቄ መልካም ለውጦችን እያመጣ መሆኑን የቦርድ ሊቀመንበሩ አቶ ሺሰማ አስታውቀዋል።
በቀጣይም ወደ ትግበራ በገባው የዘጠና ቀናት ፍኖተ ካርታ ዕቅድ መሠረት በሁሉም የባንክ አገልግሎቶች ፈጣን ለውጦችን በማምጣት ንብ ባንክን ወደነበረበትና ከዚያም ላቅ ወዳለ ደረጃ ለማሸጋገር ትልቅ ቁርጠኝነት መኖሩን በአስቸኳይ ጠቅላላ ጉባኤው ለተገኙ ባለአክሲዮኖች ገልጸዋል፡፡
አዲሱ ቦርድ ወደ ሥራ ከገባበት አጭር ጊዜ አኳያ ጥሩ ውጤት ለማስመዝገብ የሚያስችሉ እንቅስቃሴዎችን እያደረገ መሆኑን መገንዘባቸውን የገለጹት የጉባኤው ተሳታፊ ባለአክሲዮኖችም፤ ቦርዱ ባንኩን ከግል ባንኮች ዘርፍ ከፊት ለማሰለፍ የሚያደርገውን ጥረት በመደገፍ ከጎኑ እንደሚቆሙ በሰጡት ቃል አረጋግጠዋል።
በጉባኤው ከተነሱ አጀንዳዎች መካከል አንዱ፣ እ.ኤ.አ በ2022 የተገኘውና ያልተወሰነበት የትርፍ ድርሻ ክፍፍል ላይ ውይይት በማድረግ ገንዘቡ ለባንኩ ካፒታል ማሳደጊያነት እንዲውል የባለአክሲዮኖች ጉባኤ በአብላጫ ድምፅ ወስኗል።
በባንኩ በ18ኛ አስቸኳይ ጠቅላላ ጉባኤ የተወሰነውን የካፒታል ማሳደጊያ ጊዜ እንዲሻሻል በተደረገው ውይይትም፣ እስከ ሰኔ 30 ቀን 2016 ዓ.ም ተጠናቅቆ እንዲከፈል መወሰኑን ከባንኩ የተገኘው መረጃ ያመለክታል።

Read 617 times