Monday, 11 March 2024 14:49

የተመድ የቀድሞ ሰራተኞች ማህበር 25ኛ ዓመቱን አከበረ

Written by 
Rate this item
(0 votes)

በተባበሩት መንግስታት ድርጅት  ሲሰሩ የነበሩ የቀድሞ ባልደረቦች ማህበራቸውን ወይም ‹‹አፊክሰን››  የመሰረቱበትን  25ኛ  ዓመት ክብረ በአል  ቅዳሜ የካቲት 30 ቀን 2016 ዓ.ም  ከጠዋቱ 3 ሰአት ጀምሮ በኢሲኤ አዳራሽ አክብረዋል፡፡

ፕሬዚዳንት  ሳህለወርቅ ዘውዴ  የአፊክስ የክብር አባል ሲሆኑ፤ ሌሎችም በአለም አቀፍ ደረጃ ሀገራቸውን ያስጠሩ ኢትዮጵያውያንም  የዚህ ማህበር አባላት ናቸው፡፡
 
አፊክስ ፣ በዋነኛነት የአባላቱን ጥቅምና መብት  ማስጠበቅን ቀዳሚ አላማው አድርጎ የተመሰረተ  ሲሆን፤ ከ586 በላይ አባላትም አሉት፡፡

 ከልዩ ልዩ አለም አቀፍ ተቋማት ጡረታ በወጡ ባለሙያዎች የተመሰረተው ይህ ማህበር  25ኛ አመቱን በድምቀት ሲያከብር፤ ከፍተኛ የተባበሩት መንግስታት ድርጅት የሥራ ኃላፊዎች ታድመዋል፡፡ የእለቱ የክብር እንግዳ ሚስተር ሪሚዝ አልካባሮቭ፣ የተባበሩት መንግስታት ኤጀንሲዎችን በመወከል ንግግር አድርገዋል ።

ማህበሩን ከመሰረቱት መካከል ለረጅም አመት በፕሬዚዳንት ያገለገሉት  አቶ ተድላ ተሾመ በእለቱ የታደሙ ሲሆን፤ እርሳቸውም በዩኤንዲፒ ከ20 አመት በላይ  በከፍተኛ  ኃላፊነት አገልግለዋል፡፡

በዚህ ክብረ በአል ላይ ዶ/ር አፈወርቅ አየለ የኦፊክስ ፕሬዚዳንት የእለቱን መልእክት አሰምተዋል፡፡   ልዩ ልዩ ኪነጥበባዊ መሰናዶዎችና  የኦፊክስን የ25 አመት ጉዞ የሚያሳይ ዘጋቢ ፊልም በተወዳጅ ሚድያና ኮሚኒኬሽን አማካይነት ቀርቧል፡፡

ኦፊክስ  የአባላቱን ጥቅም ሊነካ የሚችል  የመመሪያ ለውጥ በተባበሩት መንግስታት  ድርጅት ውስጥ ቢከሰት ለውጡን  ለአባላቱ ያሳውቃል፡፡ በስራ ላይ እየተሳተፉ ያሉ አባላት  ልምድና እውቀት በሰፊው ያካበቱ በመሆኑም ይህን የተቀደሰ አላማ ከግብ ለማድረስ ሌት ተቀን የሚታትሩ ባለሙያዎችም  ናቸው፡፡

ማህበሩ ሲመሰረት አንስቶ፣ ከጡረታ መስሪያ ቤት ዘንድ ውሳኔ የሚጠብቅ ጉዳይ ያላቸውን አባላት  በፍጥነት ውሳኔ እንዲገኝላቸው አድርጓል፡፡ በሥራ ላይ የሚገኙት ደግሞ  ጡረታ ከመውጣታቸው አስቀድሞ  ስለጡረታ ክፍያቸው እንዲሁም ስለ ጤና ጥበቃ መድን ቅድመ ዝግጅት  እንዲያደርጉ  አፊክስ እገዛውን በተሟላ መንገድ ሲሰጥ መቆየቱን ለመረዳት ተችሏል፡፡

የተባበሩት መንግስታት የቀድሞ ዓለምአቀፍ  ሠራተኞች ማህበር  ወይም አፊክስ ለጠቅላላ ጉባኤው ተጠሪ የሆኑ የቦርድ አባላት ያሉት ሲሆን፤ የማህበሩም ጽ/ቤት በኢሲኤ ግቢ ውስጥ ነው የሚገኘው፡፡

Read 632 times