Saturday, 02 March 2024 21:00

መንግሥትና የትግራይ ጊዜያዊ አስተዳደር አደራዳሪዎች ባሉበት ዳግም ሊነጋገሩ ነው

Written by 
Rate this item
(1 Vote)

የፌደራል መንግስትና  የትግራይ ክልል ጊዜያዊ አስተዳደር፣ አደራዳሪዎች በተገኙበት   በቀጣይ ሳምንታት  በፕሪቶርያው ስምምነት ዙሪያ ዳግም ለውይይት ሊቀመጡ ነው ተባለ።  የካቲት 18 እና 19 ቀን 2016 ዓ.ም  የትግራይ ክልል ጊዜያዊ አስተዳደር ካቢኔ  መሰብሰቡንና የተለያዩ ውሳኔዎች ማሳለፉን የክልሉ ኮሙዩኒኬሽን ቢሮ ሃላፊ አቶ ረዳኢ ሀለፎም ከትግራይ ቴሊቪዥን ጋር ባደረጉት ቃለምልልስ ገልጸዋል። ካቢኔው ባካሄደው ስብሰባ፣ የአስተዳደሩን ስራዎች ለመስራት አስቸጋሪ የነበሩ መመሪያዎችን ማሻሻሉን ጠቁመዋል። በሁለቱ ወገኖች መካከል በፕሪቶርያ የተደረገው  ስምምነት ባለመተግበሩ ሣቢያ  የክልሉ ህዝብ ላይ የሚደርሰው መከራና ስቃይ ሊቆም አልቻለም ያሉት  የክልሉ ኮሙዩኒኬሽን ቢሮ ሃላፊ አቶ ረዳኢ ሀለፎም፤  የትግራይ ክልል ጊዜያዊ አስተዳደር ከፌደራል መንግስቱና ከሚመለከታቸው አካላት ጋር በስምምነቱ አፈጻጸም ዙሪያ በተደጋጋሚ መምከሩን ገልጸዋል።
በፕሪቶርያው የሰላም ስምምነት አፈጻጸም ዙሪያ አደራዳሪ አካላት በተገኙበት በፌደራል መንግስትና በትግራይ ጊዜያዊ አስተዳደር መካከል በቀጣይ ሳምንታት ውይይት እንደሚካሄድም አስታውቀዋል።
የአፍሪካ ህብረት፣ የመንግስታቱ ድርጅት፣ የአሜሪካንና የደቡብ አፍሪካ መንግስታት ተወካዮች ተሳታፊ የሚሆኑበት የፕሪቶርያውን ውል አፈጻጸም የተመለከተ ውይይት ለማካሄድ ቀጠሮ መያዙን የጊዜያዊ አስተዳደሩ ፕሬዚዳንት አቶ ጌታቸው ረዳ፣ የካቲት 5 ቀን 2016 ዓ.ም ለክልሉ መገናኛ ብዙኃን በሰጡት ጋዜጣዊ መግለጫ መናገራቸው ይታወሳል።

Read 1003 times