Wednesday, 21 February 2024 12:09

ጠ/ሚኒስትር ዐቢይ ከታጣቂዎች ጋር ለመወያየትና ሰላም ለማምጣት እንደሚፈልጉ ተናገሩ

Written by 
Rate this item
(4 votes)


• በአማራ ክልል ትራክተር እንጂ ጥይት አያስፈልግም

• ይቅርታም ብለን ካሣም ከፍለን ቢሆን፣ እንታረቅ እንስማማ

• በምርጫ የሰጣችሁንን ሥልጣን በምርጫ ውሰዱት

-ሪፖርታዥ-

በትላንትናው ዕለት ከአማራ ክልል ተወካዮች ጋር በጽ/ቤታቸው የተወያዩት ጠ/ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ፤ በአማራና በኦሮምያ ክልል ነፍጥ አንግበው ከሚንቀሳቀሱ ወገኖች ጋር በጠረጴዛ ዙሪያ በመወያየት ሰላም ለማምጣት እንደሚፈልጉ ተናገሩ፡፡

አዲሱ ምክትል ጠ/ሚኒስትር ተመስገን ጥሩነህና የአማራ ክልል ርዕሰ መስተዳደር አረጋ ከበደ በተገኙበት በተካሄደው በዚህ ውይይት ላይ ጠ/ሚኒስትር ዐቢይ፣ ለሃይማኖት መሪዎችና ለአገር ሽማግሌዎች ባስተላለፉት ጥሪ፤ ”እባካችሁ በሰላማዊ መንገድ ገብቶ መነጋገር የሚፈልግ ሰው ካለ --ከየሰፈሩ አምጡ አወያዩና ይቅርታም ብለን ካሳም ካስፈለገ ካሳ ከፍለን እንታረቅ፤ እንስማማ፡፡” ብለዋል፡፡

“ሰው መግደልና መዝረፍ የትም አያደርስም፤ መክራችሁ የሚመለስ ሰው ካለ በመመለስ እርዱን፤እኛ የምንፈልገው ሰላም ነው” ሲሉ ጠ/ሚኒስትሩ ለአማራ ክልል ተወካዮች መልዕክት አስተላልፈዋል፡፡

ከአማራ ክልል የተለያዩ ዞኖች ተወክለው በውይይቱ ላይ የታደሙ ተሳታፊዎች በክልሉ የሰላምና ጸጥታ ጉዳይ፣ በመሰረተ ልማቶች ችግር፣ በግብርና ግብአቶች አለመሟላት፣ በመልካም አስተዳደር እጦትና በሌሎችም ዙሪያ ጥያቄዎችና አስተያየቶችን ሰንዝረዋል፡፡

ከተወካዮቹ ለተሰነዘሩት ጥያቄዎችና አስተያየቶች ምላሽና ማብራሪያ የሰጡት ጠ/ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ፤ ስለ ታጣቂዎች፣ ስለ አማራ ተወላጆች የሥልጣን ድርሻ፣ ስለ ሃይማኖትና መንግስት ሚና፣ ስለ አንድነት ቤተ መንግሥት ፒኮክ ጉዳይ፣ ስለ ልማትና ሌሎች ሰፊ ጉዳዮች ተናግረዋል፡፡

የአማራ ተወላጆች ባለፉት 5 ዓመታት በአዲስ አበባ ላይ ያገኙት የሥልጣን ድርሻ ባለፉት 30 ዓመታት ኖሯቸው እንደማያውቅ የገለጹት ጠ/ሚኒስትሩ፤ ከለውጡ በኋላ የትኛውም ሥልጣን ለሁሉም ክፍት መሆኑን ተናግረዋል፡፡

“ድሮ የአዲስ አበባ የሥልጣን ድርሻን በተመለከተ 25 ፐርሰንት ለኦህዴድ፣ 25 ፐርሰንት ለብአዴን፣ 25 ፐርሰንት ለህወኃት እና 25 ፐርሰንት ለደህዴን ነበር” ያሉት ጠ/ሚኒስትሩ፤ የፈለገ ቢያብጥ በአዲስ አበባ ላይ የአማራ የሥልጣን ድርሻ 25 ፐርሰንት ብቻ እንደነበር አስታውሰዋል፡፡

“ዛሬ ግን ካላጋነንኩት አማራ በአዲስ አበባ ላይ ከ33–35 ፐርሰንት የሥልጣን ድርሻ አለው” ብለዋል፡፡

ከምክትል ጠ/ሚኒስትር ጀምሮ ደህንነት፣ መከላከያ፣ ውጭ ጉዳይ፣ አየር መንገድና ብዙ ተቋማት በአማራ ተወላጆች ሥልጣን ሥር መሆናቸውንም ጠ/ሚኒስትሩ አብራርተዋል፡፡

የመንግሥት ሥልጣንን አስመልክቶ ያብራሩት ጠ/ሚኒስትሩ፤ “ሥልጣን በምርጫ ነው የሰጣችሁን፤ ስትፈልጉ በምርጫ ውሰዱት፤ ከኛ የተሻለ ካገኛችሁ ምረጡ፤ደሞ ታዩታላችሁ በምርጫ ህዝብ ሲወስን እንዴት እንደምናከብር፤ ጊዜው ሲመጣ ታዩታላችሁ” ብለዋል፡፡

ሥልጣን በአፈሙዝ ግን በፍጹም አይሞከርም ያሉት ጠ/ሚኒስትሩ ፤ “እኛ ወታደሮች ነን፤ የአድዋ አርበኞች ልጆች ነን፤ ማንም በጉልበት ሊያሸማቅቀን አይችልም” ሲሉ ተናግረዋል፡፡



በአማራና ኦሮምያ ክልል ነፍጥ አንግበው የሚንቀሳቀሱ ወገኖችን በተመለከተ ጠ/ሚኒስትሩ ሲናገሩ፤ “የኛ ፍላጎት በአማራ ክልል ያለውም ሸኔ በኦሮምያ ያለውም ሸኔ ህዝብ ከማገድ፣ ከማገት፣ ከመግደል፣ ከመጥለፍና ከመዝረፍ ወጥቶ በሰላማዊ መንገድ ተነጋግሮ፣ ትጥቁን አስቀምጦ፣ ምርጫ ተወዳድሮ በሃሳብ አሸንፎ፣ እነሱ እዚህ መጥተው (ሥልጣን ላይ) እኛ እዚያ ብንቀመጥ ምንም ችግር የለብንም፡፡” ብለዋል፡፡

በአማራ ክልል ጥይት አያስፈልግም፤ ትራክተር ነው የሚያስፈልገው ያሉት ጠ/ሚኒስትር ዐቢይ፤ እኛ ከናንተ ጋር በፍቅር ብቻ ነው መኖር የምንፈልገው፤ ከዚህ የተለየ አጀንዳ የለንም ብለዋል፡፡

ጠ/ሚኒስትሩ ከአማራ ክልል የተለያዩ ዞኖች ከተወከሉ ተሳታፊዎች ጋር ያደረጉትን ውይይት ሲቋጩ፤ “በትብብር እንሥራ፤ በምክክር እንስራ፤ አንናናቅ፤ እንተባበር፤ የሚሻለው እሱ ነው፤ከዚያ ውጭ ያለው ሃሳብ ጥፋት ነው፡፡” የሚል መልዕክት አስተላልፈዋል፡፡

የቴሌግራም ቻናልችንን በመቀላቀል የአዲስ አድማስን መረጃ ይከታተሉ…
https://t.me/AdissAdmas

Read 1167 times