Saturday, 30 December 2023 19:50

የከተማው አስተዳደሩ የመንግስት ሰራተኞች የብቃት ምዘና ፈተና ዛሬ ይሰጣል

Written by  ናፍቆት ዮሴፍ
Rate this item
(3 votes)

ፈተና መቅረብ ያለበት አንድ ሰው ከመቀጠሩ በፊት ነው (አቶ ከፈለኝ ሀይሉ)
           ሙስናና ብልሹ አሰራር ከእውቀትና ክህሎት ማነስ ይመጣሉ ብዬ አላምንም (ጌቱ ከበደ (ኢ/ር)
                              
          ባለፈው ሳምንት ቅዳሜ ለአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የመንግስት ሰራተኞች ሊሰጥ ታቅዶ የነበረውና ድንገት የተሰረዘው የብቃት ምዘና ፈተና በዛሬው እለት እንደሚሰጥ ተገለፀ፡፡
በአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲና በኮተቤ የትምህርት ዩኒቨርስቲ ከ16ሺ በላይ ለሚሆኑ የከተማው አስተዳደር የመንግስት ሰራተኞች የተዘጋጀው የብቃት መመዘኛ ፈተና፣ በቴክኒክ ችግር ምክንያት መሰረዙን በመግለፅ፤ አዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ ይቅርታ መጠየቁ ይታወሳል፡፡
የመጀመሪያው ዙር የከተማው አስተዳደር የመንግስት ሰራተኞች የብቃት መመዘኛ ፈተና የህዝብ ቅሬታ የሚነሳባቸው፤ ለሙስናና ብልሹ አሰራር የተጋለጡና የአገልግሎት ጥራታቸው የተጓደለ 16 የአስተዳደሩ ተቋማትን የሚመለከት ነው ተብሏል፡፡ ፈተናው የስነምግባርና የክህሎት ክፍተቶችን ለመለየት የሚካሄድ የምዘና አካል እንደሆነና ከዳይሬክተር እስከ ፈፃሚ ሰራተኞች ያሉትን እንደሚያካትት ተጠቁሟል፡፡ ከከተማው አስተዳደር የተገኘው መረጃ እንደሚያመለክተው፤ ከ30-35 በመቶ ነጥብ ከመመዘኛ ፈተናው የሚያዝ ሲሆን ቀሪው ደግሞ የስራ አፈፃፀም፣ የስራ ልምድ፣ ስነምግባርና መሰል ጉዳዮችን ታሳቢ ያደረገ ነው፡፡ በክህሎትና በስነምግባር አንፃር ክፍተት የተገኘባቸው ሰራተኞች በሚመጥኗቸው ቦታዎች ተመድበው ተገቢው የክህሎትና የሥነምግባር አቅም ግንባታ ማሻሻያ ሥልጠና እንደሚሰጣቸው ነው የተገለፀው፡፡ “በተለያየ መልኩ ውዥንብር በመፍጠር ሪፎርሙ እንዳይሳካ የሚፈልጉ ሃይሎች አሉ” ያለው የከተማ አስተዳደሩ፤ “የሪፎርሙ ዓላማ በዘመናዊ ቴክኖሎጂ የታገዘ፤ የተገልጋዩን እርካታ ከፍ የሚያደርግ የከተማዋን ቀጣይ እድገት ታሳቢ ያደረገ ሲቪል ሰርቫንትና ተቋማትን መገንባት ብቻ ነው” ብሏል፡፡ የብቃት ምዘና ፈተናው በሚመለከታቸው ተቋማት የሚሰሩ አንዳንድ የመንግሰት ሰራተኞች  የፈተናውን አላማ በትክክል አለመረዳታቸውንና በእንደዚህ አይነት ፈተና የተጠቀሱትን ችግሮች መቅረፍ እንደማይቻል ተናግረዋል፡፡
አንድ ስማቸው እንዳይጠቀስ የፈለጉ የመንግሥት ሰራተኛ ፈተናውን በተመለከተ በሰጡት አስተያየት፤ “ከተማ አስተዳደሩ ያዘጋጀው ፈተና ችግሩን ከመቅረፍ ይልቅ እንደሚያባብሰው ይሰማኛል፤ በተለያየ ሙያና ደረጃ ለሚገኝ ሰራተኛ አንድ አይነት ፈተና አዘጋጅቶ መስጠት ማህበራዊ ቀውስን ያስከትላል እንጂ መፍትሄ አያመጣም” ሲሉ ስጋታቸውን ገልፀዋል፡፡
ሌላው ስማቸው እንዳይጠቀስ የፈለጉ ዛሬ ለፈተና የሚቀመጡ የመንግስት ሰራተኛ በበኩላቸው፤ “ተፈትኜ ባልፍም ብወድቅም ፈተናው የኔ መመዘኛ ነው ብዬ ለመቀበል እቸገራለሁ” ያሉ ሲሆን “በመጀመሪያ ደረጃ የፈተናው አላማ ምን እንደሆነ አልገባኝም፤ ሙስና፣ ተገልጋይን ማማረርና ብልሹ አሰራር ከእውቀትና ከክህሎት ማነስ የሚመጣ ነው ብዬ አላምንም ነገር ግን ፈተናውን ተፈትኜ የሚሆነውን እንደማንኛውም የመንግስት ሰራተኛ እጠባበቃለሁ” ብለዋል፡፡
ለመንግስት ሰራተኞች የሚሰጠውን የብቃት ምዘና ፈተና በተመለከተ አስተያየት የጠየቅናቸው የቢዝነስና ኢንቨስትመንት አማካሪ ጌቱ ከበደ (ኢ/ር) ፤ ሙስና ብልሹ አሰራርና መሰል ችግሮች በኢትዮጵያ ብቻ ሳይሆን በስለጠነውም ዓለም የሚከሰትና ይህንንም የሚፈፅሙት ከፍተኛ የመንግስት ባለስልጣናትና ሃላፊዎች እንደሆኑ ጠቅሰው፤ ችግሩ ከእውቀትና ክህሎት ማነስ የመጣ ነው ብሎ እንዲህ አይነት ፈተና ማዘጋጀት ችግሩን ሊቀርፈው አይችሉም ብለዋል፡፡
ከዚህ ይልቅ ማህበረሰቡ የሚማረርበትን ጉዳይ  እንዲጠቁም ሁኔታዎችን ማመቻቸትና ያንን ጥቆማ ተከትሎ ምርመራ አድርጎ በአጥፊዎች ላይ እርምጃ መውሰድ ውጤት እንደሚያመጣ ተናግረዋል፡፡ የመንግስት ሰራተኛው መስፈርቱ ታይቶ መቁጠር ነው ያለበት አሁን መፈተን አያስኬድም ብለዋል፡፡  አሁን ሁሉንም በጅምላ እንደጀማሪ መፈተን ከጥቅሙ ጉዳቱ እንደሚያመዝንና ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ቀውስ ሊያስከትል እንደሚችልም ጠቁመዋል፡፡
ሌላው በጉዳዩ ላይ አስተያየት የሰጡን የቢዝነስና ኢንቨስትመንት አማካሪ እንዲሁም አሰልጣኝ አቶ ከፈለኝ ሀይሉ በበኩላቸው፤ የአሁኑ የከተማ አስተዳደሩ ያዘጋጀው የመንግስት ሰራተኞች ፈተና ጠቅላላ አላማው መታወቅ አለበት ብለዋል፡፡ “በመጀመሪያ ሙስና ብልሹ አሰራርና ተገልጋዮችን ማማረር ከእውቀትና ከክህሎት ክፍተት ስለ መምጣቱ ከተማ አስተዳደሩ ጥናትና ግኝት አለው ወይ?” ሲሉም ይጠይቃሉ፡፡
“ፈተና የሚዘጋጀው አንድ ሰራተኛ ከመቀጠሩ በፊት ነው” የሚሉት አቶ ከፈለኝ፤  ያለብቃቱ የተቀጠረ ካለ ከፈረሱ ጋሪው የቀደመበትና የከተማ አስተዳደሩ ችግር ነው” ብለዋል፡፡ እንደ አማካሪው አስተያየት ከሆነ፤ “አሁን የተዘጋጀው ፈተና ለእድገት (Promotion) ከሆነ ጥሩ፤ ካልሆነ ግን ኤክስፐርቱንም ድጋፍ ሰጪ ሰራተኛውንም በጅምላ ፈተና ላይ ማስቀመጥ ችግር ከማስከተሉ ውጪ መፍትሄ አያመጣም ምክንያቱም የአበበ ክፍተት ሌላ ነው የከበደ ክፍተት ሌላ ነው”
 ከዚህ ሁሉ ግን በየመስሪያ ቤት ያሉ ችግሮች ተለይተው ማህበረሰቡን ከወያይቶ ችግሩን ያመጡትን ክፍተቶች ላይ ጥናት ተሰርቶ ክትትልና ቁጥጥር በማድረግ፣ አጥፊዎችን መለየት የተሻለ ይሆናል ሲሉም ባለሙያው  አስተያየት ሰጥተዋል፡፡
“ለመሆኑ ፈተናውን ተፈትኖ ያለፈው በብቃቴ ነው የቀጠልኩት ብሎ ያምናል ወይ? ብቃት አለው ተብሎ ካለፈ በኋላ የተፈለገውን ያህል በብቃት ይሰራል ወይ?” የሚሉት አቶ ከፈለኝ፤ “ተፈትኖ የወደቀውስ ብቃት ስለሌለኝ ነው የወደቅኩት ብሎ ይቀበላል ወይ? ብልሹ አሰራር ሙስናና የህዝብ ቅሬታ የሚያቀርብባቸው የአገልግሎት ቦታዎች በእርግጥስ በብቃትና በክህሎት ማነስ የሚፈፀሙ ስለመሀናቸው የሚያሳይ ጥናት ተገኝቷል ወይ?” በማለት በርካታ ጥያቄዎችን ያነሳሉ፡፡
በአሁኑ ወቅት የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ከ163 ሺ በላይ ሠራተኞችን በስሩ እንደሚያስተዳድር ይታወቃል፡፡

Read 1850 times