Saturday, 09 December 2023 11:48

መንግስት ለሰላም ድርድር ፍላጎት የለውም›› ተባለ

Written by 
Rate this item
(6 votes)

በመንግስትና በኦሮሞ ነፃነት ሰራዊት መካከል በዳሬ ሰላም ሲካሄድ የነበረው ድርድር እንዳይሳካ የተደረገው በመንግስት ነው ሲሉ የሰላም ሚኒስቴር ሚኒስትር ዴኤታ አቶ ታዬ ደንደኦ ገለፁ፡፡ መንግስት በሁለቱ ወገኖች መካከል የተፈጠረውን ችግር በውይይት ለመፍታት ፍላጎት የለውም
ሲሉም ለቢቢሲ በሰጡት ቃለ ምልልስ ላይ ተናግረዋል፡፡


የሰላም ሚኒስትር ዴኤታና የኦሮሚያ ክልል ምክር ቤት (ጨፌ) አባል የሆኑት አቶ ታዬ ደንደአ ከትናንት በስቲያ ከቢቢሲ አፋን
ኦሮሞ ጋር ባደረጉት ቆይታ እንደገለፁት፤ በሁለቱ ወገኖች መካከል ያለው ችግር በሰላም እንዲፈታ ከተወሰነ በኋላ በመንግስት በኩል ድርድሩ እንዳይሳካ ተደርጓል ብለዋል፡፡ በሁለቱ ዙር ውይይቶች ተስፋ ሰጪ ሁኔታዎች ታይተው እንደነበር ያመለከቱት አቶ ታዬ፤ “የኦሮሞ ነፃነትሰራዊትን የሚመራው ድሪባ ኩምሳ (ጃልመሮ) ለሰላም ካለው ቁርጠኝነት የተነሳ መንግስት ከፈለገ እርምጃ ይውሰድብኝ ብሎ
በመንግስት ቁጥጥር ስር በሆነው የአየር ክልል ውስጥ አልፎ ወደ ታንዛኒያ የሄደ ቢሆንም በመንግስት በኩል ግን ለሰላምና ችግሮችን በውይይት ለመፍታት ፍላጎት አልታየም” ብለዋል፡፡ የሰላም ድርድር ጉዳይ በሰላም ሚኒስቴር በኩል የሚከናወን መሆኑ በህግ የተሰጠ የስራ ሃላፊነት መሆኑን 
ያመለከቱት አቶ ታዬ፤ እኛ በማናውቀው ሁኔታ በሰላም ድርድሩ ከሰላም ሚኒስቴር ይልቅ የፍትህ ሚኒቴር ተሳታፊ እንዲሆን ተደርጓል ብለዋል፡፡

ከህውሃት ጋርም ሆነ ከኦሮሞ ነፃነት ሰራዊት ጋር በሁለት ዙር በተደረገው የሰላም ድርድር መስሪያ ቤታቸው የሰላም ሚኒስቴር አለመሳተፉንም

አመልክተዋል፡፡
በመንግስትና በኦሮሞ ነፃነት ሰራዊት መካከል የመጀመሪያው ዙር ድርድር ሲካሄድ ገብረጉራቻ ከተማ ውስጥ ህዝቡን በማወያየት ላይ እንደነበሩ

ያመለከቱት አቶታዬ፤ ህዝቡ የሰላም ድርድሩ በሰላም ተጠናቆ እፎይታን እናገኛለን የሚል ትልቅ ተስፋን ሰንቆ እንደነበር ገልፀው፤ በመንግስት በኩል
የሰላም ድርድሩ እንዲደናቀፍ ተደርጓል ብለዋል፡፡“እኔ ያለሀብት መንግስት ችግር ውስጥ ነን፣ ተወያይተን መፍትሄ እናመጣለን ብዬ ስጠይቅ ቤቱ ለውይይት ክፍት አይደለም፡፡ በማምታታትና በማደናገር ማለፍ ነው የሚፈልገው፡፡
የእኔ መንግሰት እንዲህ አይነት ፀባይ ነው ያለው” ሲሉ በቃለምልልሱ ወቅት ተናግረዋል፡፡ በአሁኑ ወቅት በመንግስት ውስጥ ሙስና እና ብልሹ አሰራር በከፍተኛ ሁኔታ መንሰራፋቱን የገለፁት የሰላም ሚኒስትር ዴኤታው አቶ ታዬ፤ ድሮ መሬት ይዘረፋል ከሚባለው በላይ አሁን ህጋዊ ሆኖ በቃላት መግለፅ በሚከብድ መልኩ እየተዘረፈ ከፍተኛ የአስተዳደር ቀውስ ፈጥሯል ብለዋል፡፡በአገሪቱ አሁን ለተፈጠረው ችግር መንግስት ትልቅ ተጠያቂነት አለበት ያሉት አቶ ታዬ፤ ራሳቸውም ቢሆኑ ለተጠያቂነት ዝግጁ መሆናቸውን ተናግረዋል፡፡የሰላም ሚኒስትር ዴኤታው በዚህ ቃለ ምልልሳቸው ማጠቃለያም፤ ታጥቆ የሚታገለውም ሆነ አገር እያስተዳደረ ያለው መንግስት ችግሮቻቸውን በውይይት ለመፍታት ጥረት ማድረግ እንደሚገባቸው ጠቁመው፤ “ህዝቡ ከሚፈለገው በላይ ዋጋ ከፍሏል፤ ከዚህ በላይ ዋጋ እንዲከፍል መደረግ የለበትም፤ ለህዝቡ
ስትሉ ችግሮቻችሁን በውይይት ብትፈቱ መልካም ነው” ሲሉ መልእክታቸውን አስተላልፈዋል፡፡

Read 1810 times