Saturday, 09 December 2023 11:31

በዜጎች ላይ የሚፈፀሙ አሰቃቂ የሰብአዊ መብት ጥሰቶች መባባሳቸውን ኢሰመኮ ገለፀ

Written by  መታሠቢያ ካሣዬ
Rate this item
(2 votes)

መንግስት ለዜጎች ደህንነት ጥበቃ እንዲያደርግ ጠይቋል

በአማራ፣ በኦሮሚያና በቤንሻንጉል ጉሙዝ ክልሎች በዜጎች ላይ የሚፈጸሙ አሰቃቂ የሰብአዊ መብት ጥሰቶች ተባብሰው መቀጠላቸውንና መንግስት ለሰብአዊ መብቶች ጥሰትና ለጥቃት ተጋላጭ ለሆኑ አካባቢዎችና ነዋሪዎች የተሟላ ጥበቃ እንዲያደርግ የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብት ኮሚሽን (ኢሰመኮ) አሳሰበ። ኮሚሽኑ በሶስቱ ክልሎች በሲቪል ሰዎች ላይ የሚፈፀሙ ግድያዎች፣ መፈናቀሎች፣ እስሮችና የሰብአዊ መብት ጥሰቶች እጅግ አሳሳቢ ደረጃ ላይ መድረሳቸውንም አመልክቷል። ኮሚሽኑ በሶስቱ ክልሎች እየተፈፀሙ ያሉ የሰብአዊ መብት ጥሰቶችን መመርመሩን ገልፆ፤ ባወጣው
ሪፖርት እንዳመለከተው፤ በሶስቱ ክልል በተለይም በአማራ ክልል እጅግ ዘግናኝ የተባሉ የሰብአዊ መብት ጥሰቶች በዜጎች ላይ ተፈጽሟል። እንደ ኢሰመኮ ሪፖርት ከሆነ፤ በአማራ ክልል በአዊ ብሔረሰብ ዞን በአያሁ ጓጉሳ ወረዳ እና በምዕራብ ጎጃም ዞን ቡሬ ዙሪያ ወረዳ እንዲሁም በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል አሶሳ ዞን አዳብድግሉ ወረዳ በተጨማሪም በኦሮሚያ ክልል አርሲ ዞን ሸርካ ወረዳና በቄለም ወለጋ ዞን ጊዳሚ ወረዳ በሲቪል ሰዎች ላይ ጥቃቶች ተፈጽመዋል ብሏል። በሶስቱ ክልሎች ከጥቅምት ወር ጀምሮ በተለያዩ ጊዜያት የተፈጸሙ የሰብአዊ መብት ጥሰቶችን አስመልክቶ ኮሚሽኑ ባወጣው በዚሁ ሪፖርት ላይ እንደገለፀው፤ በአማራ ክልል በአዊ ብሔረሰብ ዞን አስዳደር በአያሁ ጓጉሳ ወረዳ እምቢላ ቀበሌና በዚጊሞ ወረዳ ሶሪት ቀበሌ ከጥቅምት 29 ቀን 2016 ዓ.ም ጀምሮ በተለያዩ ቀናት በተፈጠረው ብሔር ተኮር ግጭት ሞትና የአካል ጉዳት ደርሷል። በኦሮሚያ ክልል አርሲ ዞን ሸርካ ወረዳ ህዳር 13 ቀን 2016 ዓ.ም ታጣቂዎች በፈፀሙት ብሔር ተኮር ጥቃት 7 የአንድ
ቤተሰብ አባላት መገደላቸውንም ገልጿል።
ከዚህ በተጨማም፣ በዚያው ዕለት ታጣቂዎች በስሌ ዲጊሉ ቀበሌ በፈፀሙት ጥቃት የአንድ ቤተሰብ አባላት የሆኑ 11 ሰዎችን ጨምሮ 12 ንፁሃን ዜጎችን መግደላቸውን ሪፖርቱ አመልክቷል።
ጥቃት አድራሾቹ ሟቾቹን ከቤታቸው እየጠሩ አሰልፈው እንደገደሏቸው ከቤታቸው ሳይወጡም የተገደሉ ንፁሃን መኖራቸውን ኢሰመኮ የአይን እማኞችን
ዋቢ አድርጎ ገልጿል። በጥቃቱ ከሞቱት ሰዎች መካከል ከጨቅላ ህፃን እስከ 80 ዓመት የዕድሜ ባለፀጋ አዛውንትና ነፍሰጡሮች ድረስ ጥቃት እንደተፈፀመባቸው የኢሰመኮ ሪፖርት ይፋ አድርጓል። በጥቃቱ ከተገደሉት ሰዎች በተጨማሪ ቁጥራቸው በውል የማይታወቅ ዜጎች ከፍተኛ ጉዳት ደርሶባቸው በህክምና ላይ እንደሚገኙና በተፈጠረው ግጭት የተፈናቀሉ በርካታ ዜጎች መኖራቸውን ኢሰመኮ በመግለጫው ይፋ አድርጓል።
በግጭቶቹ እየደረሰ ያለው እጅግ አሰቃቂ ጉዳት ከዚህ የበለጠ ከመባባሉና የበለጠ ጉዳት ከመድረሱ በፊት መንግስት ተገቢውን ሰላማዊና ፖለቲካዊ መፍትሔ ተግባራዊ እንዲያደርግ የጠየቁት የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብቶች ኮሚሽን ኮሚሽነር ዶ/ር ዳንኤል በቀለ፤ ሁሉም ታጣቂ ቡድኖችና መንግስት
የተኩስ አቁም አድርገው ችግሮቻውን በውይይት እንዲፈቱ፣ በተለይ መንግስት ለሰብአዊ መብቶች ጥሰትና ለጥቃት ተጋላጭ ለሆኑ አካባቢዎች ነዋሪዎች ሁሉ የተሟላ ጥበቃ እንዲሰጥና ደህንነታቸው የሚረጋገጥበትን መንገድ እንዲፈልግ ኮሚሽነሩ አሳስበዋል።በክልሎቹ በዜጎች ላይ የሚፈፀሙት የሰብአዊ መብት ጥሰቶች ከሪፖርቱም በኋላ መቀጠላቸውን የገለፀው የኢሰመኮ መግለጫ፤ በእነዚህ አካባቢዎች ላይ የደረሱ ተጨማሪ ጥቃቶችን በተመለከተ
አሁንም ለኮሚሽኑ መረጃዎች እያደረሱት መሆኑንና የማጣራትና የማረጋገጥ ስራው የቀጠለ እንደሆነም አመልክቷል።

Read 1238 times