Saturday, 25 November 2023 19:46

የነዋሪውን ተስፋ ያጨለመው ያልተሣካው የሠላም ድርድር

Written by  መታሰቢያ ካሳዬ
Rate this item
(2 votes)

ድርድሩ ያለ ስምምነት መጠናቀቁ የአካባቢውን ሰላም ይበልጥ ያደፈርሰዋል ተብሏል


በመንግሥትና  ራሱን የኦሮሞ ነጻነት ሠራዊት  (ኦነስ ) ብሎ በሚጠራው ታጣቂ ቡድን መካከል በታንዛኒያ ዳሬሰላም ከተማ ለቀናት ሲካሄድ የሰነበተው የሠላም ድርድር፤ ያለ ሥምምነት መቋጨቱ  በእጅጉ እንዳሳዘናቸውና ተስፋ እንዳስቆረጣቸው
የአምቦ ከተማና የምስራቅ ወለጋ ዞን የተለያዩ አካባቢ   ነዋሪዎች ለአዲስ አድማስ ገለፁ።  የድርድሩ ያለውጤት መጠናቀቅ የክልሉን ሰላም ወደከፋ ደረጃ የሚያደርስና  ነዋሪውን ለአስከፊ  የፀጥታ ችግር የሚዳርግ እንደሆነም ተናግረዋል ።
በምዕራብ ሸዋ ዞን አምቦ ወረዳ አምቦ ከተማ ውስጥ ነዋሪ የሆኑት አቶ ለገሠ ጉደታ ለአዲስ አድማስ እንደገለፁት፤ በመንግስትና በሸኔ መካከል ሰሞኑን ሲካሄድ የሠነበተው  የሠላም ድርድር  በክልሉ ላለፉት አራትና አምስት አመታት የቀጠለውን  የነዋሪዎች ሞትና ከመኖሪያ ቀዬ መፈናቀል ያስቀራል የሚል ትልቅ ተስፋ በህዝቡ ላይ አድሮ ነበር ። በክልሉ በተለይም በምዕራብ እና ደቡብ ኦሮሚያ ውስጥ  ቢያንስ አራት ዓመታትን ያስቆጠረው  የፀጥታ ችግርና አለመረጋጋት፣ በሁለቱ ወገኖች የሠላም ድርድር መፍትሄ ያገኛል የሚል ትልቅ ተስፋ አሣድሮ እንደነበር የገለጹት  አቶ ለገሠ፤ የሠላም ድርድሩ ያለውጤት መጠናቀቅ የነዋሪውን ተስፋ ያጨለመና ለከፋ  የፀጥታ ችግር ስጋት የዳረገ ነው ብለዋል ።
“ እኔ በምኖርበትና  ከዞኑ የተለያዩ አካባቢዎች የተፈናቀሉ በርካታ ነዋሪዎች በሚገኙበት  ኦቦራ  ከተማ ውስጥ በመንግስትና በሸኔ መካከል ከተደረገው የመጀመሪያ ዙር የሠላም ድርድር ጀምሮ አካባቢው አንፃራዊ ሰላም ሠፍኖበት ነበር ያሉት ሌላው አስተያየታቸውን የሠጡን  የአካባቢው ነዋሪ  አቶ  ገለታ ደጀኔ፤ አሁን የድርድሩ አለመሣካት የአካባቢውን ሰላም በማደፍረስ የከፋ ችግር ማስከተሉ አይቀሬ ጉዳይ ነው ብለዋል ። “በሁለቱ ወገኖች መካከል ሲደረግ ቆይቶ ያለውጤት መጠናቀቁ የተገለጸው የሠላም ድርድር፤  በበርካቶች ዘንድ በትልቅ ተስፋ ሲጠበቅ የነበረ ነው “  ያሉትና ስማቸው እንዲገለጽ ያልፈለጉ አንድ የፖለቲካ ምዑር፤  “ተደራዳሪዎቹ ከተመሳሳይ ማህበራዊ አካባቢ የወጡ የፖለቲካ ምሁራን በመሆናቸው እነዚህን ወገኖች አስማምቶ ወደ ሠላምና እርቅ ማምጣቱ ፈታኝ ይሆናል ብዬ አስባለሁ”  ብለዋል ።  ሁለተኛው ዙር የሠላም ውይይትና ድርድር ያለውጤት መጠናቀቁ ለጊዜው ተስፋ አስቆራጭ ቢመስልም   ሁለቱ ወገኖች በጠረጴዛ ዙሪያ ለመነጋገር መቀመጣቸው  አበረታችና  ተስፋ ሰጭ ጉዳይ ነውም ብለዋል ።
ራሱን የኦሮሞ ነጻነት ሰራዊት ብሎ በሚጠራውና  መንግሥት “ሸኔ” የሚል ስያሜ ሰጥቶ  በአሸባሪነት በፈረጀው ታጣቂ ቡድንና በመንግስት መካከል ታንዛንያ-ዳሬሰላም ሲካሄድ የቆየው የሠላም ውይይት  ያለስምምነት መጠናቀቁን ሁለቱም ተደራዳሪ አካላት በተናጥል ባወጡት መግለጫ አሳውቀዋል። ይህ በሁለቱ ተፋላሚዎች መካከል ለሁለት ሳምንታት ገደማ ምሥጢራዊ ሆኖ የዘለቀው ድርድር በስኬት ባለመጠናቀቁም አንዱ አካል ሌላኛውን እየወቀሰ ነው ።
በኅብረተሰቡ ዘንድ ሰላምን ያመጣል በሚል ትልቅ ተስፋ የተጣለበትና ለሁለት ሳምንታት ገደማ የዘለቀው የሰላም ድርድር  ያለ ውጤት  መቋጨቱን መንግስት  በይፋ አስታውቋል። ለ15 ቀናት ገደማ በታንዛኒያ ዳሬሰላም ከተማ ሲካሄድ የነበረው የሁለቱ ተፋላሚ ቡድኖች የሰላም ስምምነት ድርድሩ አለመሳካቱን አስቀድሞ የገለጹት የጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ የደህንነት ጉዳዮች አማካሪና የሰላም ድርድሩ የመንግስት ተወካይ አምባሳደር ሬድዋን ሁሴን ናቸው፡፡ «በሁለት ዙር ከሸኔ ጋር ስናደርግ የነበረው ውይይት ያለ ስምምነት ተጠናቋል» በሚል በይፋዊ የማኅበራዊ ገጻቸው የገለጹት አምባሳደር ሬድዋን፤ የፌዴራል መንግስት በኦሮሚያ በተለያዩ አከባቢዎች ሲካሄድ በነበረው ጦርነት ሲደርስ የነበረውን ቀውስና እንግልት ለማብቃት ቁርጠኛ ነበር ብለዋል፡፡ ይሁንና «በሌላኛው ወገን ግትርነት» ውይይቱ ያለ ስምምነት መጠናቀቁን ነው ያስረዱት።
አምባሳደር ሬድዋን ድርድር ያለውጤት መጠናቀቁን ተከትሎ በጽሑፍ ባወጡት መግለጫ፤ «ሌላኛው ወገን (ኦነግ -ኦነሰ) በፈጠረው እንቅፋት እና በሚያራምደው እውን ሊሆን በማይችል ፍላጎት ምክንያት ስምምነቱ አልሰመረም» ነው ያሉት፡፡
አክለውም መንግስት ያሉትን ፍላጎቶች በማገናዘብ በሁለቱም ወገኖች ተቀባይነት ሊኖራቸው የሚችለውን የመፍትሄ አካል ሲፈልግ ነበርም ብለዋል፡፡ አምባሳደር ሬድዋን በዚሁ  መግለጫቸው፤  በስምምነቱ ያለስኬት መጠናቀቅ መጸጸታቸውን ገልጸው ውይይቱ እንዲደረግ ላስተባበሩ አካላት ምስጋና አቅርበዋል፡፡
የመንግስት ኮሚዩኒኬሽን አገልግሎት ሚኒስቴር  ከትናንት በስቲያ ባወጣው ይፋዊ መግለጫ፤ «መንግስት በአገሪቱ ሰላም ሰፍኖ ኢትዮጵያ ያሏትን ጸጋዎች ወደ ተጨባጭ ሀብትና አቅም ቀይራ ብልጽግናዋን ታረጋግጣለች የሚል ተስፋ ተይዞ ከግማሽ መንገድ በላይ ተሂዶ ለጉዳዩ እልባት ለመስጠት» መሞከሩን በመግለጽ፤ «የሽብር ቡድን» ያለው ሌላኛው ወገን  የሠላም ጥሪውን ባለመቀበሉ ውይይቱ ያለ ውጤት ተበትኗል  ብሏል።  የመንግስት ኮሚዩኒኬሽን አገልግሎት በመግለጫው፤ «መንግስት በሰላማዊ መፍትሄው ላይ ያለው አቋም እንደተጠበቀ ሆኖ ሕግና ሕገመንግስታዊ ስርዓቱን የማስከበር ተልእኮው ይቀጥላልም» ብሏል፡፡
የኦሮሞ ነጻነት ሰራዊት (ሸኔ) በፊናው «በታንዛንያ ዛንዚባር እና ዳሬሰላም ውስጥ ሲካሄድ በነበረው ሁለት ዙር የሰላም ስምምነት በኦሮሚያ ክልላዊ መንግስት ከፍተኛ ለውጥ እንዲመጣ ያቀረብነውን ሐሳብ መንግስት ባለመቀበሉ» ድርድሩ ሳይሳካ ቀርቷል ብሏል፡፡ ኦነግ-ኦነሰ «የኢትዮጵያ መንግስት ፍላጎት የኦነሰ አመራሮችን ከመቀላቀል ባሻገር መሰረታዊውን የአገሪቱን የሠላምና ፖለቲካ ችግሮችን ከመፍታት የራቀ» ነው ሲልም ገልጿል ። ካልተሳካው  የሠላም ድርድር በኋላ የሰላም ሚኒስቴር ሚኒስትር ዴኤታ አቶ ታዬ ደንደአ   በማህበራዊ ትስስር ገጻቸው ላይ  ባሠፈሩት መልዕክት  «ትልቅ ሐዘን

Read 1690 times