Tuesday, 21 November 2023 16:39

ራክሲዮ፤ በኢትዮጵያ የዳታ ማዕከሉ በይፋ ሥራ መጀመሩን አበሰረ

Written by 
Rate this item
(0 votes)

*ኩባንያው በቅርቡ በ3 የአፍሪካ አገራት የዳታ ማዕከሎቹን ይከፍታል

በሰባት የአፍሪካ አገራት የሚንቀሳቀሰው  ራክሲዮ የዳታ ማዕከል ኩባንያ፣ በአዲስ አበባ አይሲቲ ፓርክ የገነባው ዓለም አቀፍ ደረጃውን የጠበቀ የዳታ ማዕከሉ  በይፋ ሥራ መጀመሩን አበሰረ፡፡

በዓይነቱ ልዩ መሆኑ የተነገረለት የራክሲዮ ኢትዮጵያ የዳታ ማዕከል፣ በይፋ ሥራ መጀመሩን የማብሰሪያ ሥነስርዓት ዛሬ ጠዋት ረፋዱ ላይ በአይሲቲ ፓርክ የተከናወነ ሲሆን፤ በሥነሥርዓቱ ላይ ከፍተኛ የመንግሥት ባለሥልጣናት፣ አምባሳደሮች፣ የፋይናንስ ተቋማት ሃላፊዎች፣ የቴክኖሎጂ ዘርፉ መሪዎችና ጥሪ የተደረገላቸው እንግዶች ተገኝተዋል፡፡

ራክሲዮ ኢትዮጵያ በይፋ ሥራ መጀመሩን አስመልክቶ ባወጣው ጋዜጣዊ መግለጫ፤ “በኢትዮጵያ ዋና ከተማና የአገሪቱ የኢኮኖሚ ማዕከል በሆነችው አዲስ አበባ የሚገኘው አዲሱ የራክሲዮ ደረጃ III ዕውቅና የተሰጠው ዘመናዊ የዳታ ማዕከል፣ ከምንጊዜውም በላይ እያደገ ለመጣው የመንግሥትና የግል ተቋማት የዳታ ማዕከል አገልግሎት ጥያቄዎች፣ አስተማማኝና የማይቆራረጥ የኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጂ መፍትሄ በማቅረብ መልስ የሚሰጥ ይሆናል፡፡” ብሏል፡፡

ማዕከሉ፤ 800 ራኮችና እስከ 3 MW የአይቲ ሃይል፣ ደህንነቱ በተጠበቀ የዳታ ማዕከል አገልግሎት ለመስጠት፣ ሙሉ በሙሉ ምትክ ያለው ያለማቋረጥ የሚሰራ የአይቲ መሰረተ ልማቶች  ዝግጁ አድርጓል - ሲል አክሏል ኩባንያው በመግለጫው፡፡

በኢትዮጵያ የራክሲዮ ዳታ ማዕከል ዋና ሥራ አስኪያጅ አቶ በዕውቀቱ ታፈረ ባደረጉት ንግግር፤ “ይህ አገልግሎት በአዲስ አበባ መጀመሩ ለራክሲዮና ለአገራችን በዲጂታል መሰረተ ልማት ረገድ መሰረት የሚጥል ነው፡፡ አገልግሎቱ በኢትዮጵያ የምጣኔ ሃብት ዕድገት ውስጥ ከፍተኛ ሚና የሚጫወት ሲሆን፤ በተለያዩ አካባቢዎች የሚከናወኑ የንግድ ሥራዎችንና የመንግሥት ኤጀንሲዎች የሥራ እንቅስቃሴን ከማፋጠንም ባሻገር፣ አህጉራዊና ዓለማቀፍ አገልግሎትና የይዘት አቅራቢዎችን ወደ ኢትዮጵያ ለመሳብ አጋዥ እንደሚሆን እናምናለን፡፡” ብለዋል፡፡

ዋና ሥራ አስኪያጁ በማከልም፤ “የማዕከላችን ደረጃ III ዓለማቀፍ የምስክር ወረቀት፣ እኛ  እየሰጠን ያለው የአገልግሎት ጥራት መጠን ማሳያ ሲሆን፤ ለደንበኞቻችን ደግሞ ለማናቸውም ንብረቶቻቸው ከፍተኛ ደህንነት አስተማማኝ ማረጋገጫ የሚሰጥ ነው፡፡” ሲሉ አስረግጠው ተናግረዋል፡፡

የዳታ ማዕከሉ በይፋ ሥራ መጀመሩን ያበሰሩት የራክሲዮ ግሩፕ ዋና ሥራ አስፈጻሚ ሮበርት ሙሊንስ በበኩላቸው፤ “ይህንን በዓይነቱ ልዩና የመጀመሪያ የሆነ ወሳኝ መሠረተ ልማት በኢትዮጵያ ተግባራዊ በማድረጋችን እጅግ ኩራት ይሰማናል፡፡ የኢትዮጵያን ቀጣይ የዲጂታል ትራንስፎርሜሽንና የዲጂታል አካችነት ጅምር ግቦችን የሚደግፍ እንደሆነ ሙሉ እምነታችን ነው፡፡ ብለዋል፡፡

ሮበርት ሙሊንስ አክለውም ሲናገሩ፤ “ይህ ጊዜ ለእኛ እንደ ኩባንያ እጅግ በጣም ደስተኛ የሆንበት ነው፡፡ ከሁለት ዓመት በፊት በኡጋንዳ እንደዚሁ ተመሳሳይ ማዕከላችንን ከጀመርን በኋላ፣ ራክሲዮ ኢትዮጵያ በአህጉሪቱ ሁለተኛው ማዕከላችን  መሆኑ ነው፡፡ እ.ኤ.አ. እስከ 2024 የመጀመሪያ አጋማሽ ድረስ ተመሳሳይ ማዕከሎችን  በሞዛምቢክ፣ በአይቮሪኮስትና በዲሞክራቲክ ሪፐብሊክ ኮንጎ የምንከፍት ይሆናል፡፡” ብለዋል፡፡

ዛሬ ረፋድ ላይ በአይሲቲ ፓርክ የተገነባው የራክሲዮን ኢትዮጵያ የዳታ ማዕከል በይፋ ሥራ መጀመር ከተበሰረ በኋላ፣ የዕለቱ እንግዶችና ባለድርሻ አካላት እንዲሁም የሚዲያ ባለሙያዎች  የዳታ ማዕከሉን ጎብኝተዋል፡፡

Read 953 times