Wednesday, 08 November 2023 00:00

የኢንፎርሜሽን መረብ ደህንነት አስተዳደር እና ኢትዮ ቴሌኮም በጋራ መሥራት በሚችሉባቸው ጉዳዮች ላይ ተወያዩ

Written by 
Rate this item
(0 votes)
ኢንፎርሜሽን መረብ ደህንነት አስተዳደር (ኢመደአ) እና የኢትዮ ቴሌኮም በጋራ ለመሥራት በሚያስችላቸው ጉዳዮች ላይ ሰፊ ውይይት አደረጉ።
በውይይቱ ወቀት የኢመደአ ዋና ዳይሬክተር አቶ ሰለሞን ሶካ በኢመደአ የእድገት ጉዞ ውስጥ የቴሌኮም አሻራ ከፍተኛ መሆኑን ገልጸው ሁለቱ ተቋማት ትብብራቸዉን ወደ ላቀ ደረጃ በማሳደግ በቅንጅት መስራት መቻላቸዉ ለሀገራዊ እድገት ያለዉ አስተዋጽዎ ከፍተኛ መሆኑን አንስተዋል።
ሁለቱ ተቋማት በጋራ የሚሰሩባቸዉ ብዙ ጉዳዮች እንዳሉ የጠቆሙት ዋና ዳይሬከተሩ አቶ ሰለሞን ዲጂታል 2025ን እንደ መነሻ በመዉሰድ ለሃገራዊ የዲጂታል ሽግግር የብኩላችንን ሚና መጫወት ይገባናል ብለዋል።
በትብብር መስራት ከቻልን ከሀገር አልፈን በመካከለኛው ምስራቅ እና በአፍሪካ በቢሊየን የሚቆጠር ትርፍ ሊያስገኝ የሚችል ምርትና አገልግሎቶች በሁለቱም ተቋማት ዉስጥ መኖሩን የገለጹት ዋና ዳይሬክተሩ እነዚህን ምርትና አገልግሎቶች ለገበያ በማቅረብ በዘርፉ የሃገርን ኢኮኖሚ መደገፍ እንችላለን ብለዋል።
ዘመኑ የመደመር በመሆኑ በተናጠል መሮጥ ብዙም አዋጭ አለመሆኑን የጠቆሙት አቶ ሰለሞን ሶካ ኢመደአ እና ኢትዮ-ቴሌኮም ተባብሮ በመስራት፤ የሃብት ብክነትን በመቀነስ፤ ሀገር በቀል ቴክኖሎጂዎችን በማልማትና ደረጃቸዉን ከፍ አደርጎ ወደ ገበያ በማቅረብ፤ ሀገራዊ ሀብት መፍጠር እንደሚገባ ጠቁመዋል።
የኢትዮ-ቴሌኮም ዋና ሥራ አሥፈጻሚ ፍሬህይወት ታምሩ በበኩላቸው ይህ ውይትት ቢዘገይም ያልረፈደ በመሆኑ በቀጣይ በትብብር የምንሰራቸዉ ስራዎችን በመለየት ለሀገር የሚጠቅሙ ስራዎችን መስራት እንችላለን ብለዋል።
ኢመደአ ለሀገር ሰፊ ሀብት የሚሆኑ ምርትና አገልግሎት እንዳለዉ ተረድቻለሁ ያሉት ዋና ስራ አስፈጻሚዋ በሂደት ምርትና አገልግሎቶቹ በአለም አቀፍ ስታንዳርድ መሰረት ከፍ በማድረግና በጋራ በመስራት ትርፋማ መሆን እንደሚቻል ጠቁመዋል።
በኢንፎርሜሽን መረብ ደህንነት አስተዳደር በነበረዉ ቆይታ የኢትዮ ቴሌኮም ዋና ስራ አስፈጻሚ ፍሬህይወት ታምሩን ጨምሮ ሌሎች የኢትዮ-ቴሌኮም ከፍተኛ አመራሮች በኢመደአ ዋና መስሪያ ቤት እየተሰሩ ያሉ ስራዎችን ጎብኝተዋል።
Read 668 times