Saturday, 16 September 2023 00:00

ኢሰመኮ ለመጀመሪያ ጊዜ ያዘጋጀውን የማኅበራዊና ኢኮኖሚያዊ መብቶች ሁኔታ ዓመታዊ ሪፖርት ይፋ አደረገ

Written by 
Rate this item
(0 votes)

 የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብቶች ኮሚሽን (ኢሰመኮ) ጋዜጣዊ መግለጫ መስከረም 4 ቀን 2016ዓ.ም.

         የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብቶች ኮሚሽን (ኢሰመኮ)፤ የማኅበራዊና ኢኮኖሚያዊ መብቶችን ሁኔታ የተመለከተ ዓመታዊ ባለ 29 ገጽ ሪፖርት ዛሬ ይፋ አድርጓል፡፡ ይህ ለመጀመሪያ ጊዜ የተዘጋጀው የዘርፍ ሪፖርት፣ ኢሰመኮ ሐምሌ 5 ቀን 2015 ዓ.ም. ይፋ ካደረገው የኢትዮጵያ ዓመታዊ የሰብአዊ መብቶች ሁኔታ ሪፖርት ላይ በተጨማሪነት ማኅበራዊና ኢኮኖሚያዊ መብቶች ላይ በማተኮር የታዩ መልካም እመርታዎች፣ ትኩረት ሊሰጣቸው የሚገቡ አሳሳቢ ጉዳዮችና ምክረ ሐሳቦችን አካቷል።
ሪፖርቱ ከሰኔ ወር 2014 ዓ.ም. እስከ ሰኔ ወር 2015 ዓ.ም. ያለውን ጊዜ የሚሸፍን ሲሆን፤ ኮሚሽኑ በማኅበራዊና ኢኮኖሚያዊ መብቶች ዘርፍ በበጀት ዓመቱ ካከናወናቸው የሰብአዊ መብቶች ክትትልና ምርመራዎች፣ጥናቶች፣ የውትወታ ሥራዎች፣ በግለሰቦች ከቀረቡ አቤቱታዎች፣ ከልዩ ልዩ የምክክር መድረኮች ላይ የተገኙ ግብአቶችንና ሌሎች የመረጃ ምንጮችን በማጠናቀር የተዘጋጀ ነው።
በሪፖርት ዘመኑ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የትራንስፖርት ቢሮ፣ በባለሦስትና አራት እግር አነስተኛ የሕዝብ ማመላለሻ አገልግሎት ተሽከርካሪዎች (ባጃጅ) ላይ ያሳለፈውን የእገዳ ውሳኔ ተከትሎ፣ የኢሰመኮን ምክረ-ሐሳቦች በመቀበል ለጉዳዩ እልባት መሰጠቱ፣ በኦሮሚያና በሶማሌ ክልሎች በሚገኙ የተለያዩ ዞኖች የተከሰተውን ድርቅ አስመልክቶ በተደረገው የሰብአዊ መብቶች ክትትል ሪፖርት፣ በኮሚሽኑ የተሰጡ ምክረ ሐሳቦች አፈጻጸም ላይ በተለይም የዘላቂ መፍትሔ ፕሮጀክቶች አፈጻጸምን በተመለከተ አበረታች ሥራዎች መከናወናቸውና የግል ሥራና ሠራተኛ አገናኝ ኤጀንሲ ሠራተኞች መብቶች አተገባበር እየተሻሻለ መምጣቱ በመልካም እመርታነት በሪፖርቱ ተካተዋል።
በተጨማሪም በሰሜኑ የሀገሪቱ ክፍል በተካሄደው ጦርነት ሳቢያ ጉዳት የደረሰባቸውን መሠረተ-ልማቶች መልሶ ለማቋቋም በፌዴራል መንግሥት ይፋ የተደረገው “የመልሶ ማቋቋምና ግንባታ ፕሮግራም” እና እነዚህን ተቋማት ወደነበሩበት ለመመለስ እየተደረጉ ያሉ እንቅስቃሴዎችም ተጠቃሽ ናቸው።
በሌላ በኩል፣ በሀገሪቱ ከጊዜ ወደ ጊዜ እየተባባሰ የመጣው የጸጥታ ችግርና እየናረ የመጣው የኑሮ ውድነትና የዋጋ ግሽበት፣ ሊደረስበት የሚችል ከፍተኛ አካላዊና አእምሯዊ ጤና የማግኘት፣ ትምህርትና መጠለያ የማግኘት፣የመሥራት፣ከሚኖሩበት ቦታ ያላግባብ በኃይል ያለመፈናቀልና ንብረት የማፍራት መብቶችን ጨምሮ ሌሎች የሰብአዊ መብቶች ላይ አሉታዊ ተጽዕኖ ማሳደራቸው በአሳሳቢነት ከተለዩ ጉዳዮች መካከል ናቸው።
በአማራ ክልል በተለያዩ አካባቢዎች ከሚያዝያ ወር 2015 ዓ.ም. ጀምሮ የተከሰቱ ግጭቶችና አለመረጋጋቶች፣ በሰው ሕይወትና ንብረት ላይ ጉዳት ከማድረሳቸውም በላይ ወቅቱ የግብርና ሥራ ቅድመ ዝግጅት የሚደረግበት የነበረ በመሆኑ አርሶ አደሩ ተረጋግቶ የግብርና ሥራውን እንዳይሠራና መደበኛ ሕይወቱን እንዳይመራ አድርጎታል። ግጭቱ ይህ ሪፖርት ይፋ በተደረገበት ወቅትም የቀጠለና እልባት ያልተበጀለት በመሆኑ ኢኮኖሚያዊና ማኅበራዊ ቀውሱ መባባሱ በሪፖርቱ ተመላክቷል።
በኦሮሚያ ክልል በተደጋጋሚ በታጣቂዎች በሚፈጸሙ ጥቃቶች፤የቤት እንስሳትና የንብረት ዝርፊያዎች፣ ቤቶችን የማቃጠልና ነዋሪዎችን በኃይል ማፈናቀልና ቤተ-እምነቶችን ማቃጠል ምክንያት ኅብረተሰቡ በአካባቢው ተረጋግቶ የዕለት ተዕለት ኢኮኖሚያዊና ማኅበራዊ ሕይወቱን እንዳይመራ ማድረጉንና በርካታ ሰዎች ያለ መጠለያ እንዲኖሩ፤ የሕክምና አገልግሎት እንዳያገኙና ሕፃናት ከትምህርት ገበታ ውጭ እንዲሆኑ ምክንያት እንደሆነ በሪፖርቱ ተብራርቷል።
በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የጸጥታና ደኅንነት ሥጋት በሚልና በሌሎች ምክንያቶች የንግድና የመኖሪያ ቤቶች በማፍረስ ሂደት ልዩ ድጋፍ የሚያስፈልጋቸው አካል ጉዳተኞች ሳይቀር የንግድ ቤቶቻቸው ያላግባብ እንዲፈርሱ መደረጉና ንብረታቸው መወሰዱ በገቢያቸውና በኑሯቸው ላይ ተጽዕኖ አሳድሯል።
በኦሮሚያ፣ በሶማሊና በተለያዩ የደቡብና ደቡብ ምዕራብ ክልሎች አካባቢዎች ባለፉት ሦስት ዓመታት ከፍተኛ ድርቅ በመከሰቱ የሕብረተሰቡ መተዳደሪያ የሆኑ በርካታ ቁጥር ያላቸው የቤት እንስሳት ሞተዋል፤ ነዋሪዎችም ከመኖሪያ ቀያቸው ተፈናቅለዋል።በመንግሥት በኩል ለችግሮቹ መፍትሔ ለማፈላለግ የተለያዩ ሙከራዎች ቢደረጉም የቅድመ መከላከል ሥራ በበቂ ሁኔታ ባለመተግበሩ ችግሩን የከፋ እንዲሆን እንዳደረገው በሪፖርቱ ተጠቁሟል።
የኢሰመኮ የሲቪል፣ የፖለቲካና ማኅበራዊ-ኢኮኖሚያዊ መብቶች ኮሚሽነር ዶ/ር አብዲ ጅብሪል፣ በ2015 ዓ.ም. በኮሚሽኑ የቀረቡ ምክረ ሐሳቦችን ከመተግበር ረገድ አበረታች ተግባራት መስተዋላቸውን ገልጸው፤ የትምህርት፣ የጤና፣ ንብረት የማፍራት፣ በቂ በሆነ የኑሮ ደረጃ የመኖር፣ የሥራና ተያያዥ ማኅበራዊና ኢኮኖሚያዊ መብቶች እንዲከበሩ የፖሊሲና የሕግ ማሻሻያ ማድረግ እንዲሁምጠንካራ የክትትልና የድጋፍ ሥርዓት መዘርጋት ያስፈልጋል ብለዋል።


Read 1738 times