Saturday, 17 June 2023 00:00

የፖለቲካ ፓርቲዎች የጋራ ምክር ቤት ያወጣው መግለጫ እያወዛገበ ነው

Written by  መታሰቢያ ካሳዬ
Rate this item
(0 votes)

32 የፖለቲካ ፓርቲዎች መግለጫው አይወክለንም ብለዋል
    -በ”5 ቀናት ውስጥ ምክር ቤቱ ይቅርታ ካልጠየቀን፣ የራሳችንን ምክር ቤት እናቋቁማለን”
                           
         ሰሞኑን የኢትዮጵያ የፖለቲካ ፓርቲዎች የጋራ ምክር ቤት በወቅታዊ ሀገራዊ ጉዳዮች ዙሪያ ያወጣው መግለጫ እንደማይወክላቸውና ምክር ቤቱ በአምስት ቀናት ውስጥ በይፋ ይቅርታ የማይጠይቅ ከሆነ፣ የራሳቸውን ምክር ቤት እንደሚያቋቁሙ የ32 ፖለቲካ ፓርቲዎች ተወካዮች ገልጸዋል።
ግንቦት 24 ቀን 2015 ዓ.ም የብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ታዛቢዎች በተገኙበት በተደረገው የአባል ፓርቲዎች ጠቅላላ ጉባዔ ላይ በተነሱትና ሰፊ ውይይት ተደርጎባቸው ገና በስምምነት ላይ ባልተደረሰባቸው ጉዳዮች ላይ ም/ቤቱ የአቋም መግለጫ ማውጣት አይገባውም ያሉ ተቃዋሚዎች፤ የጋራ ም/ቤቱ መግለጫ በስምምነት ላይ ያልተደረሰባቸው ጉዳዮችን ያካተተና በአመዛኙ በጉባዔው የተነሱ ሃሳቦችን ያላካተተ በመሆኑ የ32 ተቃዋሚ ፓርቲዎችን አቋም የሚያንፀባርቅ አይደለም ብለዋል።
የጋራ ምክር ቤቱ በአምስት ቀናት ውስጥ ከምክር ቤቱ አባል ፓርቲዎች ፊት ቀርቦ ይቅርታ የሚጠይቅ ይፋዊ መግለጫ ካላወጣ ለብሔራዊ ምርጫ ቦርድ በማሳወቅ፣ ሌላ የ32 ፖለቲካ ፓርቲዎች የጋራ ምክር ቤት እንደሚያቋቁሙ ገልጿል። የጋራ ምክር ቤቱ ያወጣውን መግለጫ የሚቃወሙት ፓርቲዎች፤ ጊዜያዊ ኮሚቴ በማቋቋም ተቃውሟቸውን እያሰሙ ሲሆን የምክር ቤቱን መግለጫ ተቃውመው መግለጫ የሰጡት ከተቃዋሚ ፓርቲዎቹ ውክልና ተሰጥቷቸው መሆኑን ተናግረዋል። እነዚህም ፓርቲዎች የኦሮሞ ነፃነት ግንባር፣ የአገው ብሔራዊ ሸንጎ ፓርቲና ህዳሴ ዲሞክራሲያዊ ፓርቲ ናቸው። በዚሁ ጊዜያዊ ኮሚቴ ተብሎ በተቋቋመውና መግለጫውን በሰጠው አካል በኩል ተቃውሞአቸውን ካሰሙት ፓርቲዎች መካከል የኦሮሞ ፌደራላዊ ኮንግረስ (ኦፌኮ) የገዳ ሰርዓት አራማጅ ፓርቲ፣ አማራ ዲሞክራሲያዊ ፓርቲ (አዴፓ) የኢትዮጵያ ብሔራዊ ፓርቲና አረና ትግራይ ይኙበታል።
 እነዚህ ቅሬታ አቅራቢ ፓርቲዎቹ የጋራ ምክር ቤቱ  በአምስት ቀናት ውስጥ በምክር ቤቱ አባል ፓርቲዎች ፊት ቀርቦ ይቅርታ የሚጠይቅ መግለጫ ማውጣት ካልቻለ፣ ጉዳዩን ለብሔራዊ ምርጫ ቦርድ በማቅረብ የራሳቸውን የጋራ ምክር ቤት እንደሚያቋቁሙ አስጠንቅቀዋል።
የኢትዮጵያ ፖለቲካ ፓርቲዎች የጋራ ምክር ቤት፤ “ሀገርን ከከፋ ቀውስና ብጥብጥ መታደግ፣ በከፍተኛ ደረጃ እየተሸረሸረ የመጣውን የፖለቲካ ምህዳር ማስፋት፣ የዜጎችን ህይወትና መብት መጠበቅ የመንግሥት ተቀዳሚ ግዴታ ነው” የሚል መግለጫ ሰኔ 2 ቀን 21015 ዓ.ም አውጥቶ እንደነበር ይታወሳል።


Read 1348 times