Friday, 26 May 2023 06:01

ዘመን ባንክ፤ አዲሱን የዋና መሥሪያ ቤቱን ህንጻ ቅዳሜ ያስመርቃል

Written by 
Rate this item
(0 votes)

 የዛሬ 15 ዓመት፣ በ87.2 ሚሊዮን ብር የተከፈለ ካፒታል፣ የባንክ ኢንዱስትሪውን  የተቀላቀለው ዘመን ባንክ፣ አዲሱንና ዘመናዊውን ባለ 36 ወለሎች የዋና መሥሪያ ቤቱን ህንጻ የፊታችን ቅዳሜ ያስመርቃል፡፡

የዘመን ባንክ ማናጅመንት በዛሬው ዕለት ከሰዓት በኋላ በአዲሱ የዋና መሥሪያ ቤት ህንጻ  መግለጫ የሰጠ ሲሆን፣ የባንኩን ያለፉ ዓመታት የሥራ አፈጻጸምና የአዲሱን ህንጻ መጠናቀቅ አስመልክቶ ማብራሪያ ሰጥቷል፡፡

በአዲስ አበባ የፋይናንስ ማዕከል ተብሎ በሚታወቀው ሰንጋ ተራ አካባቢ የተገነባው የዘመን ባንክ አዲስ የዋና መሥሪያ ቤት ህንጻ አምስት ዓመታትን የፈጀ ሲሆን፤ግንባታው በ1.2 ቢሊዮን ብር ቋሚ ክፍያ የተጀመረ ቢሆንም፣በተለያዩ ምክንያቶች በተፈጠረ መዘግየትና የዲዛይን ለውጥ አሁን ላይ አጠቃላይ ወጪው ወደ 1.5 ቢሊዮን ብር እንደሚደርስ ተገምቷል፡፡

የዋና መ/ቤቱ ህንጻ መጠናቀቅ ተበታትነው የቆዩትን የባንኩን የተለያዩ የሥራ ክፍሎች ወደ አንድ ህንጻ በመሰብሰብ ለደንበኞቹም ሆነ ለራሱ ወጪ ቆጣቢ፣ ቀልጣፋና ምቹ አገልግሎት ለመስጠት እንደሚያስችለው ተገልጧል፡፡

አዲሱ ህንፃ ባንኩ በየዓመቱ ለህንጻ ኪራይ ሲያወጣው የነበረውን ከ40 ሚ. ብር በላይ እንደሚያስቀርለት የተናገሩት የዘመን ባንክ ዋና ሥራ አስፈጻሚ አቶ ደረጀ ዘበነ ፤”አዲሱ ህንጻ ለባለአክሲዮኖቻችን ሃብት፣ ለደንበኞቻችን ደግሞ ዋስትና ነው” ብለዋል፡፡

የባንኩ ዘመናዊ ህንጻ ሁሉንም የግንኙነት አማራጮችን በቴክኖሎጂ ያቀፈ፣ የመረጃ መሰብሰቢያና ማደራጃ እንዲሁም መተንተኛ ማዕከላት ያሉት ነው ተብሏል፡፡

በ2300 ካሬ ሜትር ስፋት ላይ ያረፈው ህንጻው፤ እስከ 200 ተሳታፊዎችን የመያዝ አቅም ያላቸው የስብሰባ አዳራሾች፣ እያንዳንዳቸው 13 ተሳፋሪዎችን የሚያጓጉዙ አሳንሰሮች፣ 200 ተሽከርካሪዎችን ማቆየት  የሚያስችሉ የምድር ቤትና ፎቅ የተሽከርካሪ ማቆሚያዎችን ይዟል፡፡

ግንባታውን ያከናወነው China Wu Yi CO. LTD የተሰኘ የቻይና መንግሥት ተቋራጭ ኩባንያ መሆኑ ታውቋል፡፡

ባለፈው 2021/22 በጀት ዓመት የባንኩ ትርፍ ከታክስ በፊት 2.1 ቢሊዮን ብር እንደነበር ያስታወሱት የባንኩ አመራሮች፤ ይህም ባንኩ ከተመሰረተ ጀምሮ ካስመዘገበው ትርፍ ከፍተኛው መሆኑን አስታውቀዋል፡፡ ያለፉት አምስት ዓመታት የትርፍ ድርሻ በአማካይ 40 በመቶ መድረሱንም አክለው ጠቁመዋል፡፡

የባንኩ ተቀማጭ ገንዘብ በአሁኑ ሰዓት ከ35 ቢሊዮን ብር በላይ መድረሱ የተገለጸ ሲሆን፤የባንኩ አጠቃላይ ካፒታል ከ6 ቢሊዮን ብር በላይ መድረሱና የተከፈለው ካፒታል መጠን 4.7 ቢሊዮን ብር መሆኑ ተመልክቷል፡፡ 100 የሚደርሱ ቅርንጫፎች ያሉት ዘመን ባንክ፤ ከ40 ቢሊዮን ብር በላይ ጠቅላላ ሃብት እንዳለው  ታውቋል፡፡

Read 2471 times