Saturday, 06 May 2023 18:16

“ሁለቱም ወገኖች ለቀጣይ ውይይት ፈቃደኛ መሆናቸው የሰላም ተስፋው እንዳይጨልም ያደርገዋል”

Written by  መታሰቢያ ካሳዬ
Rate this item
(2 votes)

በመንግስትና በኦሮሞ ነፃነት ሰራዊት (ኦነግ ሸኔ) መካከል ላለፉት ዘጠኝ ቀናት በዛንዚባር ሲካሄድ የሰነበተው የሰላም ድርድር ያለስምምነት ተጠናቅቋል። ሁለቱን ወገኖች ካላስማሟቸው ጉዳዮች መካከል አንዱና ዋንኛው የጋራ የሽግግር መንግስት እንዲቋቋም በኦሮሞ ነፃነት ሰራዊት በኩል ጥያቄ በመቅረቡ እንደሆነም ታውቋል።
የኦሮሞ ነፃነት ሰራዊት፤ በዚሁ የሰላም ድርድር ላይ ካቀረባቸው ጥቄዎች መካከል በኦሮሚያ ክልል ውስጥ የሚንቀሳቀሱትን የኦሮሞ ነፃነት ግንባር፣ የኦሮሞ ፌደራሊስት ኮንግረስና ብልፅግናን ጨምሮ ሌሎች የፖለቲካ ፓርቲዎችን ያካተተ የጋራ የሽግግር መንግስት ሊቋቋም ይገባል የሚለው ይገኝበታል። የሽግግር መንግስቱ የሚቋቋመው በሁሉም የፖለቲካ ፓርቲዎች መካከል መተማመን እንዲኖርና አገሪቱ ነፃና ፍትሃዊ ምርጫ ማካሄድ እንድትችል የማሻገር ኃላፊነቱን እንዲወጣ ለማድረግ ነውም ተብሏል።
ሌላው በኦሮሞ ነፃነት ሰራዊት በኩል የተነሳው ጉዳይ፣ በመንግስትና በኦሮሞ ነፃነት ሰራዊት መካከል ሊደረስ የሚገባው ስምምነት፣ በዘላቂነት ጦርነትን በሚያከትም መልኩ እንዲሁም  ሁሉንም የሰራዊቱን ፖለቲካዊና የጦር ክንፉን ማካተት አለበት የሚለው ሃሳብ ነው።
እነዚህ ሃሳቦች በፌደራል መንግስቱ ተደራዳሪዎች በኩል ተቀባይነት አለማግኘታው ታውቋል።
ድርድሩን አስመልክቶ መንግስት ባወጣው መግለጫ፤ ከአማጺው ቡድን ጋር ሲደረግ የሰነበተው የመጀመሪያው ዙር ንግግር በአንዳንድ ጉዳዮች ላይ ስምምነት ላይ ሳይደረስ መጠናቀቁን ገልጾ፤ ውይይቱ በአብዛኛው በአዎንታዊ መልኩ ተከናወኗል ብሏል።
ግጭቱን በሰላማዊ መንገድ ለማስቆም እንዲቻል ሁለቱም አካላት የሰላም ውይይቱ የመቀጠሉ አስፈላጊነት ላይ ተግባብተዋል ያለው የመንግስት መግለጫ፤ በኢትጵያ ህገ-መንግስትና እስከ አሁን ሲመራባቸው በነበሩ መሰረታዊ መርሆዎች መሰረት ግጭቱን በሰላማዊ መልኩ ለመፍታት የመንግስት አቋም ፅኑ ነው ብሏል። የውይይቱ ሌላኛውን ምዕራፍ ለመቀጠል በሁለቱም ወገኖች በኩል ስምምነት ላይ መደረሱን በመግለጫው አመልክቷል፡፤
የኦሮሞ ነፃነት ሰራዊት በበኩሉ፤ ከሰላም ድርድሩ መጠናቀቅ በኋላ ባወጣው መግለጫ፤ በሁለቱ ወገኖች መካከል ለቀናት ሲካሄድ የሰነበተው የሰላም ድርድር በዋና ዋና ፖለቲካዊ ጉዳዮች ላይ ስምምነት ላይ ሳይደረስ መጠናቀቁን አመልክቷል።
በውይይቱ በአንዳንድ አንኳር ጉዳዮች ላይ ከስምምነት ላይ መደረሱን ያመለከተው የአማጺ ቡድኑ መግለጫ ቁልፍ በሆኑ ፖለቲካዊ ጉዳዮች መግባባት ላይ ለመድረስ አለመቻሉን ጠቁሟል። ግጭቱን በሰላማዊ መንገድ ለመፍታት የሰላም ውይይቱ መቀጠል አስፈላጊ መሆኑ ታምኖበታል ያለው የአማፂው መግለጫ፤ የኦሮሞ ነጻነት ሰራዊት በኦሮሚያ ክልል ያለው ግጭት በሰላማዊ መንገድ እንዲፈታ ቁርጠኛ መሆኑን ገልጿል።
ላለፉት ዘጠኝ ቀናት በታንዛኒያዋ ደሴት ዛንዚባር በፌደራል መንግስቱና በኦሮሞ ነፃነት ሰራዊት መካከል ሲካሄድ ሰነበተው የሰላም ድርድር ያለስምምነት መጠናቀቁ በብዙ ወገኖች በጉጉት ሲጠበቅ የቆየውን የሰላም ተስፋ ያደበዘዘ ቢሆንም፣ ሁለቱም ወገኖች ለቀጣይ ዙር ውይይት ፍቃደኝነታቸውን መግለጻቸው የሰላሙ ተስፋ ጨርሶ የጨለመ እንዳልሆነ የሚያመለክት ነው ተብሏል።የህግ ባለሙያውና ፖለቲካ ምሁሩ ዶ/ር አንተነህ ተስፋዬ፣ ያለስምምነት የተበተነውን የሁለቱ ወገኖች የሰላም ድርድር አስመልክተው ለአዲስ አድማስ እንደተናገሩት፤ ሁለቱ ወገኖች ከተመሳሳይ ማህበራዊ አካባቢዎች የተገኙ እንደመሆናቸው እርስ-በርሳቸው ሊያግባባቸውና ችግሮቻቸውን በሰላማዊ መንገድ ለመፍታት የሚያስችላቸው ዕድሎችን ይሰጣቸዋል የሚል ግምት ቢኖርም ሁኔታው እንደሚታሰበው ቀላል አይደለም።
በቀላሉም ከስምምነት ላይ ይደርሳሉ ብሎ መጠበቁ የዋህነት ነው፤ ተቀራርበው መነጋገራቸው በራሱ አበረታችና ተስፋ ሰጪ ጉዳይ ነው ብለዋል። በአንድ ጊዜ የሚመጣ ለውጥ እንደማይኖርም ተናግረዋል። በሁለቱም ወገኖች በኩል ለቀጣይ ዙር ውይይት ዝግጁ መሆናቸውን መግለፃቸው ሌላው ተስፋቸውን ከፍ ያደረገ ጉዳይ መሆኑን የሚገልጹት ዶ/ር አንተነህ፤ ተደራዳሪዎቹ በቀጣይ ዙር የድርድር ምዕራፍ ከማያግባቧቸው ጉዳዮች ይልቅ በሚግባባቸው ጉዳዮች ላይ ጠንከር ብለው እንደሚሰሩና የህዝብን ጥቅም በማስቀደም ኃላፊነታቸውን እንደሚወጡ ተስፋ አደርጋለሁ ብለዋል።ያለስምምነት በተጠናቀቀውና ለዘጠኝ ቀናት በተካሄደው ውይይት ላይ ከመንግስት በኩል የጠቅላይ ሚኒስትሩ የብሔራዊ ደህንነት አማካሪው አምባሳደር ሬድዋን ሁሴን፣ የፍትህ ሚኒስትሩ ዶ/ር ጌዲዮን ጢሞቴዎስ፣ የኦሮሚያ ክልል የፍትህና ደህንነት ክላስተር ምክትል ሃላፊ ከፍያለው ተፈራ፣ የወታደራዊ መረጃ ምክትል ሃላፊ ሜጀር ጀነራል ደምሰው አመኑ እና በታንዛኒያ የኢትዮጵያ አምባሳደር ሽብሩ ማሞ ተሳታፊ ሆነዋል። በኦሮሞ ነፃነት ሰራዊት በኩል ደግሞ የታሪክ ምሁሩና በጆርጂያ ስቴት ዩንቨርሲቲ መምህር የሆኑት ፕሮፌሰር መሐመድ ሐሰን፣ ከኦነግ መስራቾች አንዱና ለበርካታ አመታት አመራር የነበሩት ጣሃ አብዲ እንዲሁም የጦሩ አዛዥ ዋና አማካሪ ጄሬኛ ጉደታ ናቸው። ሁለቱ ወገኖች ለቀጣይ ዙር ውይይት ፍቃደኝነታቸውን የገለፁ ቢሆንም፣ ቀጣዩ ዙር ውይይት የትና መቼ እንደሚደረግ የተገለጸ ነገር የለም።


Read 1547 times