Saturday, 22 April 2023 19:14

በሱዳኑ ጦርነት በርካታ ኢትዮጵያውያን መገደላቸው ተሰማ

Written by  መታሰቢያ ካሳዬ
Rate this item
(4 votes)

የአንድ ቤተሰብ አባላት የሆኑ አራት ሰዎች ተገድለዋል
ኢትዮጵያ ወታደሮቿን ሱዳን ውስጥ አስገብታለች መባሉን ጠቅላይ ሚኒስትሩ አስተባበሉ


ሰባተኛ ቀኑን በያዘው በጀነራል መሃመድ ሐምዶን ዳጋሎ በሚመራው የፈጥኖ ደራሽ ልዩ ሀይል እና በጀነራል አብደል ፈታህ አልቡርሃን በሚመራው የአገሪቱ ጦር ሰራዊት መካከል እየተካሄደ ባለው ጦርነት የሞቱ ኢትዮጵያውያን ቁጥር እየጨመረ ነው፡፡ እስከ ትናንት ምሽት ድረስ በውጊያው ከ15 በላይ ኢትዮጵያውያን መገደላቸውን ምንጮች ጠቁመዋል፡፡
በሱዳን የኢትዮጵያ ኤምባሲ በበኩሉ፤ በጦርነቱ የሞቱ ኢትዮጵያውያን መኖራቸውን ጠቁሞ፣ በቁጥር ምን ያህል እንደሆነ ለማወቅ አለመቻሉን ገልጿል፡፡
ኤምባሲው በማህበራዊ ድረገፅ ከትናንት በስቲያ ባወጣው አጭር መግለጫ፤ በሱዳን እየተካሄደ ባለው ጦርነት የበርካታ ሲቪሎች በኢትዮጵያውያን ህይወት በአሳዛኝ ሁኔታ እየተቀጠፈ ነው ብሏል፡፡ ኤምባሲው ኢትዮጵያውያኑ ሞትና ጉዳት የተሰማውን ጥልቅ ሃዘንም ገልጿል፡፡
በሱዳን አምዱርማን ከተማ ውስጥ በሁለቱ ተፋላሚዎች መካከል በተፈጸመ ውጊያና በጦር ጀት ጥቃት የአንድ ቤተሰብ አባል የሆኑ አራት ኢትዮጵያውያን መገደላቸውን ምንጮች ገልፀዋል፡፡ በካርቱም (ጅሬፍ) ኢትዮጵያውያን ባልና ሚስት ከሶስት አመት ህፃን ልጃቸው ጋር በሚኖሩበት ቤት ላይ በተፈጸመ ሌላ ጥቃት ባልና ሚስቱ  ሲገደሉ፣ የ3 ዓመት ህፃን ልጃቸው በህይወት መትረፏን ምንጮች ጠቁመዋል፡፡
ካርቱም በሚገኘው የኢትዮጵያውያን ኤምባሲ ላይም ጥቃት መፈጸሙን ያመለከቱት ምንጮች፤ ጥቃት ፈፃሚዎቹ የኤምባሲውን ቅጥር ግቢ ጥሰው በመግባት፣ በግቢው ኢትዮጵያውያን ማህበረሰብ ባለቤት በሆኑበት የመጠለያ ማዕከል ውስጥ በነበሩ ኢትዮጵያውያን ላይ አስፀያፊ ድርጊት እንደፈፀሙባቸው ለአዲስ አድማስ ተናግረዋል፡፡ካርቱም ከተማ ኢልማሞራ እየተባለ በሚጠራው አካባቢ ነዋሪ የሆነችው ወ/ሮ ትዕግስት እንደምትናገው በአካባቢው ቀንና ሌሊት የአየር ድብደባ እየተካሄደ እንደሆነ ጠቁማ በሱዳን የሚገኘው የኢትዮጵያ ኤምባሲ በአየር ድብደባ ከፍተኛ ጉዳት እንደደረሰበትና እስከ አሁን የኤምባሲው ሰራተኞች የሆኑ ኢትዮጵያውያን መገደላቸውን ለአዲስ አድማስ ተናግራለች፡፡በከተማው ውሃና የኤሌክትሪክ አገልግሎ ከተቋረጠ ቀናት መቆጠራቸውን ያመለከተችው ወ/ሮ ትእግስት በሱዳን ሙቀትና የበርሃ ንዳድ ከነልጆቿ ማለቃችን ነው ብላለች፡፡ በቤት ውስጥ የሚበላም ሆነ የሚጠጣ ምንም ነገር አለመኖሩንና ክጅግ በከፋ ሁኔታ ውስጥ እንደሚገኙም ገልፃለች፡፡ መንግስት እንደሌሎቹ አገራት ለዜጎቹ ግድ እንዲሰጠውና በነፍሳችን እንዲደርስልን ስትልም ተማፅኖዋን አቅርባለች፡፡የኢትዮጵያ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ከትናንት በስቲያ ስለጉዳዩ በሰጠው ጋዜጣዊ መግለጫ መንግስት በሱዳን ባለው ወቅታዊ የፀጥታ ሁኔታ ምክንያት በአገሪቱ የሚኖሩ ኢትዮጵያውያንን ሁኔታ በቅርበት እየተከታተለ መሆኑን አስታውቋል፡፡ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር በዋናው መስሪያ ቤትና ካርቱም በሚገኘው ኤምባሲ አማካኝነት የኢትዮጵያውያንን ደህንነት ለመጠበቅ እንደሚሰራም በመግለጫው አመልክቷል፡፡ሱዳን ውስጥ በመቶ ሺዎች የሚቆጠሩ ኢትዮጵያውያን እንደሚኖሩና በአሁን ወቅትም እጅግ በአስከፊ ሁኔታ ውስጥ እንደሚገኙ እነዚሁ ምንጮች ለአዲስ አድማስ ጠቁመዋል፡፡
በሌላ በኩል ኢትዮጵያ ወታደሮቿን ሱዳን ውስጥ አስገብታለች እየተባለ የሚሰራጨው መረጃ ሀሰተኛ ነው ሲሉ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶ/ር አቢይ አህመድ ተናገሩ። በኢትዮጵያና በሱዳን መካከል ግጭት መቀስቀስ የሚፈልጉ አካላት ከድርጊታቸው እንዲታቀቡም ጠይቀዋል።
በኢትዮሱዳን ድንበር ላይ ቀደም ሲል የሱዳን ወታደሮች ኢትዮጵያ በሰሜኑ ጦርነት ላይ በነበረችበት ወቅት ድንበር ጥሰው በመግባት በወረራ የያዙትን መሬት ለማስለቀቅ ኢትዮጵያ ወታደሮቿን አሰማርታለች እየተባለ የሚነዛው መረጃ ሀሰተኛ ነው ያሉት ጠ/ሚኒስትሩ በኢትዮጵያና በሱዳን መካከል ያለው የድንበር ውዝግብ በንግግር ይፈታል ብለዋል።
ኢትዮጵያ አሁን ሱዳን ያለችበትን ነባራዊ ሁኔታ ለድንበር ውዝግቡ መጠቀሚያ አታደርገውም ያሉት ጠ/ሚሩ ሱዳን ኢትዮጵያ በአስቸጋሪ ሁኔታ ውስጥ በነበረችበት ወቅት ሉአላዊነቷን በመጣስና መሬቷን በሃይል በመቆጣጠር የፈጸመችውን ድርጊት ኢትዮጵያ በሱዳን ላይ አትፈጽምም ብለዋል።
ወንድም የሆነው የሱዳን ህዝብ ለዚህ ዓይነቱ ሃሰተኛ ወሬ ጆሮዋ እደማትሰጥ እምነታቸው መሆኑንም ገልጸዋል።

Read 2366 times