Saturday, 15 April 2023 20:14

ሸማቹን ተስፋ ያስቆረጠው የፋሲካ ገበያ

Written by  መታሰቢያ ካሳዬ
Rate this item
(2 votes)

“ዘንድሮ ገበያውን እንደ ጦር ሜዳ ፈራነው......”
የበግ፣ የፍየልና የበሬ ዋጋ ታይቶ በማይታወቅ ሁኔታ አሻቅቧል

 በአብዛኛዎቹ የከተማችን የእርድ እንስሳት መሸጫ ቦታዎች ላይ ከዚህ ቀደም የተለመደው አይነት የሻጭና ገዥ ክርክርና ግብይት አይታይም። ለዚህም ምክንያቱ የእርድ እንስሳቱ ዋጋ ከዚህ በፊት ባልታየ ሁኔታ በከፍተኛ መጠን መጨመሩ እንደሆነም ነጋዴዎች ይናገራሉ።
በተዘዋወርንባቸው የሾላ እና የመርካቶ የዶሮ ገበያ ውስጥ ዶሮ በአንጻራዊነት የተሻለ በሚባል ዋጋ ለሽያጭ ቀርበው ተመልክተናል። ከ900-1300 ብር በሚደርስ ዋጋ እየተሸጡ ነው። በመሪ ገበያ  አንድ ዶሮ በ1500 ብር ሲሸጥም ታዝበናል።
በዘንድሮው ፋሲካ በዓል ግብይት በከፍተኛ መጠን የዋጋ ጭማሪ የታየበት የእርድ እንስሳት ዋጋ ሲሆን (በግ፣ፍየልና በሬ) ሲግናል የበግ ገበያ ላይ በ22ሺ ብር ለሽያጭ የቀረበ በግና 24ሺ ብር ዋጋ የተቆረጠለት ፍየልም አይተናል። በኮተቤው የበሬ መሸጫ ስፍራ ደግሞ ከ52 ሺ ብር እስከ 110 ሺ ብር ድረስ ዋጋ የወጣላቸው  ሰንጋዎች ለሽያጭ ቀርበው ተመልክናል።                                                                                                                                           አዲሱ ገበያ ላይ ከ38 ሺ እስከ 98 ሺ ብር ዋጋ የተቆረጠላቸውን ሰንጋዎች የተመለከትን ሲሆን በግና ፍየል ከ7 ሺ እስከ 16 ሺ ብር ሲሸጡ አስተውለናል።በሾላ ገበያ የአንድ ኪሎ ቅቤ ዋጋ ከ750-850 ዋጋ የወጣለት ሲሆን የሽንኩርት ዋጋ ከቀናት በፊት ከነበረበት በኪሎ 25 ብር ዋጋ ከእጥፍ በላይ ጨምሮ ከ55-60 ብር፤ እንቁላል ደግሞ አንዱ ከ12-14 ብር እየተሸጠ ይገኛል።የዘንድሮው የፋሲካ በዓል ገበያ ከፍተኛ የዋጋ ጭማሪ የታየበትና የሸማቹን አቅም የፈተነ እንደሆነ ነጋዴዎች ሸማቾች ይናገራሉ። በሾላ ገበያ በዶሮ ግብይት ላይ ያገኘናቸው አቶ ሰለሞን ታመነ፤ “ዘንድሮ ገበያውን እንደ ጦር ሜዳ ፈራነው። ዛሬ ያየነውና የሰማነው ዋጋ ነገ ተቀይሮ ሌላ ሆኖ ይጠብቀናል፤ እንዴት ነው መኖር የሚቻለው” ሲሉ ጠይቀዋል።
“እየኖርን ያለነው በእግዚአብሔር ቸርነት እንጂ በደመወዝና በገበያው አይደለም። ድሮ አመት በዓል ሲደርስ ደስታ ነበር የሚሰማን፤ ዛሬ ጭንቀት ሆኗል። ከሰው ላለማነስ ብንፍጨረጨርም አልሆነልንም። ከዚህ ሁሉ ጭንቀትና ሰቀቀን ሞቶ መገላገል ምንኛ ጥሩ ነበር”  ሲሉም በቆረጠ ስሜት ተናግረዋል።በመርካቶ ዶሮ ተራ ግብይት ላይ ያገኘኋቸው እነ ወ/ሮ ደስታ ተካልኝም፣ ኑሮው ከቀን ወደ ቀን እየከፋ፤ የዋጋ ንረቱ እያሻቀበ መሄዱ ግራ ቢያጋባቸውም፣ የትንሳኤ በዓልን በደስታ ለመቀበል አቅማቸው የፈቀደውን ሊሸምቱ ገበያ መጥተዋል። በገበያው የጠበቃቸው የዋጋ ጭማሪ ግን ያልጠበቁትና አስደንጋጭ ሆኖባቸዋል። “ምን ማድረግ እችላለሁ ትንሳኤ ነው። ጾሙ በምን ይገደፋል። አነስተኛ ዶሮና አንድ ኪሎ ቅቤ ገዝቼ እየወጣሁ ነው። ገበያው ግን ምን እንዲህ አደረገው? ድሃ እኮ መኖር አልቻለም።” ሲሉ ምሬታቸውን ተንፍሰዋል። በተዘዋወርንባቸው ሁሉም ገበያዎች ለዋጋ ጭማሪው መንስኤው ምን እንደሆነ የጠየቅናቸው ነጋዴዎች የሰጡትን ምላሽ ይመሳሰላል። “በአሁኑ ወቅት በአገሪቱ ባለው የጸጥታ ችግር ሳቢያ በአራቱም አቅጣጫዎች መንገድ በመዘጋቱና እንደልብ ምርት ወደ መሃል ገበያ ባለመግባቱ ሳቢያ ነው” የሚል ነው። በእርግጥ በበአላት ወቅት በሁሉም የምግብ ሸቀጦችና ለበዓሉ አስፈላጊ በሆኑ ነገሮች ላይ የዋጋ ጭማሪ መታየቱ የተለመደ ጉዳይ ቢሆንም፤ የዘንድሮው የፋሲካ በዓል ገበያ ጭማሪ ግን ከወትሮው የተለየና ሸማቹን የሚፈትን ሆኗል ብለዋል።
የኢትዮጵያ ስታቲስቲክስ አገልግሎት ሰሞኑን ያወጣው መረጃ እንደሚያመለክተው፤ በአገሪቱ የታየው የጤፍ ዋጋ  ጭማሪ ወርሃዊውን ምግብ ዋጋ ግሽበት እንዲያሻቅብ ያደረገው ሲሆን በተለይ በአዲስ አበባ ከተማ ከበዓል መምጣት ጋር ተያያዞ ጭማሪ ከፍተኛ ሆኗል-ብሏል።
 በከተማው እንደ ጤፍ፣ ስንዴ፣ በቆሎና ገብስ ያሉ መሰረታዊ እህሎች ዋጋ ላይ ከፍተኛ ጭማሪ መታየቱን ያመለከተው የድርጅቱ ሪፖርት፤ የጭማሪው ባለፈው አመት ተመሳሳይ ወቅት ላይ ከነበረው ዋጋ የ32.8 በመቶ ጭማሪ ማሳየቱንና አጠቃላይ የዋጋ ግሽበቱ ካለፈው አመት መጋቢት ወር ጋር ሲነጻጸር 34.2 በመቶ ጭማሪ ማሳየቱን ጠቁሟል።
የዋጋ ጭማሪው በከፍተኛ መጠን እንዲጨምር ሌላ ምክንያት ነው ተብሎ በሪፖርቱ የተጠቀሰው የሁለቱ ታላላቅ ሃይማኖቶች ዋንኛ በአላት በተመሳሳይ ወቅት ላይ መድረሳቸውና አቅርቦቱና ፍላጎቱ የተመጣጠነ አለመሆኑ ነው።

Read 2411 times