Saturday, 18 March 2023 19:47

የከንቲባዋ ንግግር ከፍተኛ ተቃውሞ ገጥሞታል

Written by  መታሰቢያ ካሳዬ
Rate this item
(2 votes)

 - አብን፣ እናት ፓርቲ፣ መኢአድ እና ኢህአፓ ንግግሩን ተቃውመዋል
      - ከንቲባዋ ፓርላማ ቀርበው በጉዳዩ ላይ ማብራሪያ እንዲሰጡ መጠየቅ ነበረባቸው
           
      የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ከንቲባ አዳነች አቤቤ፣ ባለፈው ማክሰኞ ለከተማዋ ምክር ቤት አባላት ባቀረቡት የስራ አፈጻጸም ሪፖርት ላይ፤ “የመንግስት ስልጣን በሃይል ለመቆጣጠር ከአንዳንድ ክልሎች ወደ አዲስ አበባ ከፍተኛ ፍልሰት እየተደረገ ነው” ሲሉ መናገራቸው ከተለያዩ አቅጣጫዎች ከፍተኛ ተቃውሞም ገጥሞታል።
“የከንቲባዋ ንግግር ህዝብን ከህዝብ የሚያጋጭ፤ አደገኛ የዘር ማጥፋት ወንጀል ቅስቀሳ ነው” ሲል አብን በመግለጫው ነቅፎታል።
ከንቲባዋ የከተማ አስተዳደሩን የስድስት ወር የስራ አፈጻጸም ሪፖርት ለምክር ቤቱ አባላት ባቀረቡበት ወቅት፣ የከተማዋ ጸጥታና ደህንነት በተመለከተ በሰጡት ማብራሪያ፤ “ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በህዝብ የተመረጠን መንግስት በመጣል፣ ስልጣንን በሃይል ለመቆጣጠር፣ ከተማዋን ወደ አለመረጋጋት ለማስገባት የሚደረጉ እንቅስቃሴዎች” መኖራቸውን ጠቁመው፤ “በተለይም “ከአንዳንድ ክልሎች ወደ አዲስ አበባ በከፍተኛ መጠን የሚደረገው ፍልሰት መንግስትን በመጣል በሃይል ስልጣንን ለመቆጣጠር ያለመ ነው” ብለዋል።
ይህንኑ የከንቲባዋን ንግግር ተከትሎ የተለያዩ ወገኖች ከፍተኛ ተቃውሞ እያሰሙ ሲሆን አብን፣ እናት ፓርቲ፣ መኢአድና ኢህአፓ በጉዳዩ ላይ የተቃውሞ መግለጫ አውጥተዋል።
የአማራ ብሔራዊ ንቅናቄ (አብን) በመግለጫው፤ “ከንቲባዋ በሪፖርታቸው ይህን መሰል አደገኛ ከፋፋይና የዘር ማጥፋት ወንጀል ቅስቀሳ፣ አገርና መንግስቱን አደጋ ላይ የሚጥልና በማናቸውም መመዘኛ ተቀባይነት የሌለው የዓለም አቀፍ ወንጀል ጥሪ ነው” ሲል ተቃውሞታል። አብን በዚሁ መግለጫው፤ “የከንቲባዋ ጥሪ “የኦሮሚያ ሚዲያ ኔትወርክ” በሚባለው ጽንፈኛና በአንድ ወቅት መንግስት ራሱ “የሽብርተኞች መጠቀሚያ ነው” ሲል በፈረጀው ሚዲያ፣ በተከታታይ የሚወጡ ቅስቀሳዎች ቅጣይ የሆነ አደገኛ የወንጀል ቅስቀሳ ነው ሲል አስታውቋል።
የፌደራል መንግስቱም ሆነ ገዥው የብልጽግና ፓርቲ፤ አደገኛ የዘር ማጥፋት ወንጀል ቅስቀሳ ያደረጉትን ግለሰብ ከስልጣን እንዲያነሳና ለፍርድ እንዲያቀርብም አብን ጥሪ አቅርቧል።
 እናት ፓርቲ፣ መኢአድና ኢህአፓም በጉዳዩ ላይ ባወጡት የጋራ መግለጫ፤ “በአስተዳደራዊ ድክመትና በንግግር ለከት ማጣት ሀገር የከፋ ቀውስ ውስጥ እየገባች መሆኑን” ጠቁመው፤ “ዜጎች ከቦታ ቦታ የመንቀሳቀስና በመረጡት ቦታ የመኖር መብት በህገ-መንግስቱ ለዜጎች የተሰጣቸው መብት እንጂ አንዳንድ ባለስልጣናት የሚቸሩትና የሚነፍጉት ጉዳይ አይደለም” ብለዋል።
“ከንቲባዋ ለምክር ቤቱ ያቀረቡት ይህ ንግግር ለበለጠ ዘር ፍጅት የሚያመቻችና ዜጎችን የማሸማቀቅ አካል ነው ያለው የፓርቲዎቹ መግለጫ፤ “የንግግር ለከት ማጣቱና በጽንፈኛ ሃይሎች የተጻፈን ስክርፒት በመንግስት መዋቅር፣ በተከበረ ምክር ቤት ፊት አምጥቶ ማነብነብ በእጅጉ ያስቆጣል” ብሏል።
በሌላው ዓለም ቢሆን እንዲህ ያለ እጅግ መርዘኛ ፍጅት ቀስቃሽ ንግግሮችና ተናጋሪዎች ተገቢው እርምት በቶሎ በተሰጣቸው ነበር ያለው መግለጫው፤ ህግና ስርዓት ሰፍኖ አጥፊዎቹ በፍትህ አደባባይ እንዲቀርቡ ጥሪ አቅርቧል፡፡
“በከተማዋ ክንቲባ የተደረገው ንግግር፣ ግልፅ የሆነ ግጭት ቀስቃሽና ለስራና ግላዊ ጉዳይ ወደ አዲስ አበባ በሚጓዙ ዜጎች ላይ ጥቃትና አደጋን የሚያስከትል አደገኛ ንግግር ነው” በማለት ለአዲስ አድማስ አስተያየታቸውን የሰጡት የፖለቲካ ምሁር ዶ/ር አንተነህ ተስፋዬ በበኩላቸው፤ “የከንቲባዋ ንግግር ቅዠትና ፍርሃት የተሞላበት፣ ጥልቅና ውስብስብ የፖለቲካ ሴራ የወለደው ስጋት ጭምር ነው” ብለዋል፡፡ የከንቲባዋ ንግግር እጅግ አደገኛ፣ ህዝብን በከፍተኛ ደረጃ የሚለያይና በጥርጣሬ መንፈስ ውስጥ የሚከት እንደሆነምአመልክተዋል፡፡ “ከዚሁ ከከንቲባዋ ንግግር ጋር ተመሳሳይነት ያለው ቅስቀሳ ኦኤምኤን በተባለው በመንግስት “የአሸባሪዎች መጠቀሚያ” ነው ሲባል በቆየ ሚድያ ላይ ሲተላለፍ ሰንብቷል ያሉት ምሁሩ፣ “ይህ የአሁኑ የከንቲባዋ ንግግር የዚያ ቅስቀሳ ቀጣይ አካል ነው” ብለዋል፡፡
 በከንቲባዋ የተነገረው ይኸው አደገኛ የጥላቻ ንግግር፣ በሀገሪቱ የህግ የበላይነት ቢኖር ኖሮ በህግ የሚያስጠይቅ ጉዳይ ነው ያሉት ዶ/ር አንተነህ ከእንቅልፉ የነቃ ፓርላማ ቢኖረን ኖሮ፤ ከንቲባዋ ፓርላማ ቀርበው በጉዳዩ ላይ ማብራርያ እንዲሰጡበት ሊጠይቃቸው ይገባ ነበር ብለዋል፡፡ ፓርላማው ከንቲባዋን በምክር ቤት ጠርቶ “ይህን ሲሉ ምን ማለትዎ ነው?” “ይህን ለማለት ያበቃዎት ማስረጃ ምንድን ነው?” ብሎ ሊጠይቃቸው ይገባ እንደነበርም አመልክተዋል፡፡ ይህ አይነቱ ማንነትንና የመጡበትን አካባቢ ትኩረት ያደረገ ጅምላ መድልዎና ማዋከብ ሃይ ሊባልና ገደብ ሊበጅለት እንደሚገባ የተናገሩት የፖለቲካ ምሁሩ፤ የከንቲባዋ ንግግር አሁን በአገሪቱ ላይ ላለው ውጥረት ተጨማሪ ቤንዚን የማርከፍከፍ ያህል እንደሆነም ጠቁመዋል፡፡

Read 2830 times