Saturday, 13 August 2022 00:00

ኢትዮጵያ የተፈተነችበት ግዙፉ የሕዳሴ ግድብ ፕሮጀክት

Written by  መታሰቢያ ካሳዬ
Rate this item
(2 votes)

የግድቡ 3ኛ ዙር የውሃ ሙሌት በስኬት ተጠናቋል
    ሁለተኛው ተርባይን ሃይል ማመንጨቱን ጀምሯል
                    
        ግንባታው ሲጠናቀቅ በአፍሪካ ግዙፍ የኤሌክትሪክ ኃይል ማመንጫ  እንደሚሆን የሚጠበቀውና ኢትዮጵያ በብዙ የተፈተነችብት ግዙፍ የህዳሴ ግድብ ፕሮጀክት፣ 3ኛውን ዙር የውሃ ሙሌት በስኬት ተጠናቋል፡፡ የግድቡ 2ኛው የሀይል ማመንጫ ተርባይን ከትናንት በስቲያ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶ/ር አብይ አህመድ፣ ፕሬዚዳንት ሳህለ ወርቅ  ምክትል ጠ/ሚኒስትርና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አቶ ደመቀ መኮንን በተገኙበት ሥራ ጀምሯል፡፡
270 ሜጋ ዋት የኤሌክትሪክ ኃይል የማመንጨት አቅም አለው የተባለው ሁለተኛው ተርባይን ስራ መጀመሩ በይፋ የተገለፀ ሲሆን ባለፈው የካቲት 13 ቀን 2014 ዓ.ም የግድቡ አንደኛው ተርባይን የኤሌክትሪክ ሃይል ማመንጨት መጀመሩ ይታወቃል፡፡
ኢትዮጵያ የህዳሴ ግድቡን 3ኛ ዙር የውሃ ሙሌት በተያዘው ነሀሴ ወር እንደምታከናውን ካሳወቀች ጊዜ ጀምሮ ግብፅ እንደተለመደው ኢትዮጵያ ስምምነት ባልተደረሰበት ሁኔታ 3ኛ ዙር የውሃ ሙሌት ማከናወን አትችልም የሚል ተቃውሞዋን ስታሰማ ቆይታለች፡፡ ባለፈው ሳምንት በውጭ ጉዳይ ሚኒስትሯ ሳሜህ ሽኩሪ በኩል፣ ለመንግስታቱ ድርጅት የፀጥታው ምክር ቤት አቤቱታዋን አቅርባለች፡፡ የአፍሪካ ህብረት፣ የአረብ ሊግ፣ የተባበሩት መንግስታት ድርጅትና ምዕራባውያን አገራት ድጋፋቸውን እንዲሰጧትም  ስትማጸን ሰንብታለች፡፡
ግብጽ ባለፉት 3 ዓመታት በኢትዮጵያ ከባዱ የክረምት ወቅት ሲጀምር እየጠበቀች ተፅህኖ ማሳደር ይችላሉ  በምትላቸው አገራትና ተቋማት በኩል በውሃ አጠቃቀሙ ዙሪያ አሳሪ ስምምት እንዲደረግ ግፊት ስታደርግ ቆይታለች። ግብጽና ሱዳን፣ ስምምነት ላይ ሳይደርሱ ኢትዮጵያ ግድቡን መሙላት አትችልም የሚል ተቃውሞና ማስፈራሪያቸውን ቢገፉበትም  ኢትዮጵያ 3ኛውን ዙር የውሃ ሙሌት በስኬት ማጠናቀቋን ትላንትና ይፋ  አድርጋለች፡፡ በግድቡ የተወዛገቡት ኢትዮጵያ ግብጽና ሱዳን ተከታታይ ድርድርና ውይይት ሲካሂዱ ቢቆዩም እስከአሁን ይህ  ነው ከሚባል ስምነት ላይ አልደረሱም፡፡
ሱዳንና ግብፅ ሶስቱ አገራት በሕዳሴው ግድብ ዙሪያ በሚያደርጉት ድርድር ከአፍሪካ ህብረት ውጪ ሌሎች  አገራትና አለማቀፋዊ ተቋማት እንዲሳተፉ በተደጋጋሚ ሲወተውቱ የቆዩ ሲሆን ኢትዮጵያ ግን በአደራዳሪነት ከአፍሪካ ህብረት ውጪ ማንንም እንደማትቀበል እና ሌሎች አለም አቀፍ ታዛቢዎች ግን ሊኖሩ እንደሚችሉ ስትገልጽ ቆይታለች በዚህም በአፍሪካ ህብረት አደራዳሪነትና በዓለም አቀፍ ማህበረሰብ ታዛቢነት ሲካሄድ የከረመው ድርድር ተጨባጭ ስምምነት ላይ  መድረስ ሳይችል ቀርቷል፡፡ ኢትዮጵያ በሕዳሴው ግድብ ድርድር ስበብ  የአባይን ወንዝ ተጠቃሚነቷን የሚገድብ ስምምነት እንደማትቀበል በተደጋጋሚ ገልጻለች፡፡
ኢትዮጵያ በመስከረም ወር 2013 ዓ.ም የመጀመሪያ የግድቡን ሙሌት በማካሄዷ  ሳቢያም፣ የትራምፕ አስተዳደር፣ ለአገሪቱ ከሚሰጠው እርዳታ ላይ ቅነሳ እንደሚያደርግ በማስታወቅ አገሪቱ ከአሜሪካ ታገኝ የነበረውን የገንዘብ ድጋፍ አስቀርቶባታል፡፡
በዚያው ዓመት ሰኔ ወር ላይ የተካሄደውን 2ኛውን ዙር የውሃ ሙሌት ተከትሎ ግብጽና ሱዳን  በህዳሴው ግድብ ዙሪያ ለተከሰተው አለመግባባት በተመሳሳይ ጉዳይ ቀደም ሲል ባልታየ ሁኔታ ለተባበሩት መንግስታት የፀጥታው ምክር ቤት አቤቱታ አቅርበው፣ ምክር ቤቱ ሐምሌ 2013 ዓ.ም በጉዳዩ ላይ ለመምክር ተሰበስቦ ነበር፡፡ ኢትዮጵያም በሕዳሴው ግድብ ጉዳይ የፀጥታው ምክር ቤት መወያየቱን እንደማትቀበለው በማስታወቅ ጉዳዩ ቀድም ሲል በተያዘበት የአፍሪካ ህብረት በኩል መቋጫ እንዲያገኝ ጠይቃለች፡፡ ይህ ጥያቄዋ ተቀባይነትን አግኝቶ ምክር ቤቱ  ጉዳዩ በአፍሪካ ህብረት በኩል ሊታይ ይገባል የሚል ውሳኔ አሳልፏል፡፡
ጠ/ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ የሁለተኛውን ተርባይን ሃይል የማመንጨት ስራ ያስጀመሩትና ለኢትዮጵያውያን ያበሰሩት፣ በቀጥታ በሚተላለፍ የቴሌቪዥን ሥርጭት ነበር-ግድቡ ከሚገኝበት ከትላንት በስቲያ፡፡
በዚህ ስነ-ስርዓት ላይም ጠ/ሚኒስትር ዶ/ር  ዐቢይ አህመድ፤ በግድቡ የውሃ ሙሌትና አጠቃላይ ስራ ላይ ተቃውሞ ከሚያስተጋቡት ግብፅና ሱዳን ጋር ኢትዮጵያ ድርድር ለመቀጠል እንደምትሻ ገልፀዋል።
 ጠ/ሚኒስትሩ ላለፉት አራት ዓመት ግድቡን በተመለከተ ለግብጽና ሱዳን ሲያስተላልፉ የነበረው መልዕክት ወጥና ተመሳሳይ ነው ኢትዮጵያ ራሷን ከማልማት ውጭ የታችኛው የአባይ ተፋሰስ አገራትን የመጉዳት ፍላጎት እንደሌላት በመጠቆም፣ “ከድርድር ውጭ ያሉ አማራጮች የግድቡን ግንባታ አያስቆሙትም” ብለዋል፤ ጠ/ሚኒስትሩ በንግግራቸው።
ጠ/ሚኒስትሩ የ3ኛው ዙር የውሀ ሙሌት  በስኬት መጠናቀቁን አስመልክቶ ባስተላለፉት መልዕክት፤
“እነሆ 3ኛውን ዙር ውሃ ሙሌት  በታሰበው ጊዜ ማጠናቀቅ ስለቻልን የዓባይ ልጆች ሁሉ እንኳን ደስ ያለን!! የዓባይ ወንዝ ለሺ ዘመናት ሦስቱን አገራት
አስተሳስሮ እንዳኖራቸው ሁሉ፤ በእሱ ላይ የተገነባው ግድብ ከሌሎች ጎረቤቶቻችንም ጋር በትብብር እንድንኖር ያስችለናል” ብለዋል።
አክለውም፤ በሦስቱ አገራት መካከል ሲካሄድ የነበረውና የተቋረጠው ድርድር እንዲቀጥል ጥሪ አቅርበዋል ለአገራቱ፡፡
የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ መለስ አለም ከሰሞኑ በጉዳዩ ላይ በሰጡት መግለጫ፤ “የግብጽና ሱዳን ከተሞች በጎርፍ ተጥለቅልቀው እንደነበር ተሰምቷል። ይህም የታላቁ ህዳሴ ግድብ ግንባታ የግብፅና የሱዳን ህዝቦችን እንደማይጎዳ ያሳያል። የግድቡን ውሃ ሙሌት በተመለከተ፣ ግንባታው እየተካሄደ ሙሌቱም ይቀጥላል” ብለዋል።
ግድቡ በአጠቃላይ 13 ተርባይኖች ያሉት ሲሆን ሁለቱ በአሁኑ ወቅት  ሃይል ማመንጨት ጀምረዋል፡፡ 750 ሜጋ ዋት የኤሌክትሪክ ሃይል የማያመንጨት አቅም እንዳላቸውም ተነግሯል።
 የዛሬ 10 ዓመት ግድም በቀድሞው ጠ/ሚኒስትሩ አቶ መለስ ዜናዊ የመሰረተ ድንጋይ የተቀመጠለት ታላቁ የህዳሴ ግድብ ኢትዮጵያ ክፉኛ የተፈተነችበት የ5ቢ. ዶላር (200 ቢ. ብር)  ግዙፍ ፕሮጀክት ነው። ፕሮጀክቱን በግላጭ የሚቃወሙት ግብፅና ሱዳን ብቻ አይደሉም። የበርካታ ክንደ ፈርጣማ የግብፅ ወዳጆች እጅም አለበት።
 ታላቁ የህዳሴ ግድብ በ2 ዓመት ተኩል ጊዜ ውስጥ ሙሉ በሙሉ ይጠናቀቃል ተብሎ የሚጠበቅ ሲሆን  ሁሉም ተርባይኖች ስራ ሲጀምሩ ግድቡ ሃይል የማመንጨት አቅም ከ5 ሺ 150  ሜጋ ዋት  ይደርሳል ተብሏል።  ትሩፋም ለኢትዮጵያ ብቻ ሳይሆን ለመላው አፍሪካ እንደሚተርፍ ይጠበቃል፡፡

የህዳሴ ግድቡ እውነታዎች
አልጀዚራን ጨምሮ በአረብ ቴሌቪዥን ጣቢያዎች  በህዳሴው  ግድብ ዙሪያ ከግብፅና ሱዳን ልሂቃን ጋር በራሳቸው ቋንቋ በመሞገት የሚታወቀው ሞሃመድ አል-አሩሲ ከትላንት በስያ በፌስቡኩ ገፁ ባሰፈረው አስተያየት፤ “በዚህ ልዩ ስኬት ታላቁ የኢትዮጵያ ህዝባችን እንኳን ደስ አላችሁ እያልን፣ የህዳሴው ግድብ ለኢትዮጵያ፣ ለግብፅ፣ ለሱዳንና ለአፍሪካ አህጉር በሙሉ ጠቃሚ መሆኑን አሁንም እናረጋግጣለን። የህዳሴውን ግድብ ጥቅም ሁሉም በዓይኑ ማየት ችሏል። ጉዳቱን እያዩ ያሉት የኢትዮጵያን እድገትና ህዳሴን የተቃወሙና የጠሉ አካላት ብቻ ናቸው” ብሏል።
ግንባታው በዋናነት በጣሊያኑ ሥራ ተቋራጭ ሳሊኒ ኢምፕሬጅሎ  የሚከናወን ሲሆን የግንባታ ሥራው 83.3 በመቶ ደርሷል
ግንባታው ከተጀመረ 10 ዓመታት አስቆጥሯል
ባለፈው የካቲት 13 ቀን 2014 ዓ.ም በአንድ ተርባይን የመጀመሪያውን የሃይል የማመንጨት ስራ ጀምሯል
የሲቪል ሥራዎች ግንባታ 95 በመቶ ተጠናቋል
ከሰሞኑ ሦስተኛው የውሃ ሙሌት በስኬት ተጠናቋል
ግንባታው በ2 ዓመት ተኩል ጊዜ ውስጥ ሙሉ በሙሉ ይጠናቀቃል
ሐሙስ ሥራ የጀመረው 2ኛው ተርባይን፣ 270፣ ሜጋ ዋት ሃይል ያመነጫል
ግንባታው ሙሉ በሙሉ ሲጠናቀቅ ከ5ሺ በላይ ሜጋ ዋት ሃይል ያመነጫል
የታላቁ ህዳሴ ግድቡ አጠቃላይ ወጪ 200 ቢ. ብር ገደማ ነው
የህዳሴ ግድብ ከፍታ 145 ሜትር ሲሀን፤ ርዝመቱ 1.8 ኪሎ ሜትር ነው
ግንባታው ሲጠናቀቅ የሚይዘው የውሃ መጠን 74 ቢሊዮን ኪዩቢክ ሜትር ሲሆን፣ ግድቡ የሚሸፍነው የቦታ ስፋት 1ሺ 680 ስኩዌር ኪ.ሜ ይሆናል
ግድቡ 13 ተርባይኖች ሲኖሩት፤ አንዱ ተርባይን 375 ሜጋ ዋት ሃይል የማመንጨት አቅም አለው
በቅኝ ግዛት ወቅት በእንግሊዝ አደራዳሪነት በተደረገ ስምምነት ከአባይ ወንዝ ግብጽ 66 በመቶ ድርሻ ሲኖራት፣ ሱዳን 22 በመቶ ድርሻ አላት፡፡ ቀሪው 12 በመቶ በትነት የሚባክን ሲሆን ኢትዮጵያ ግን ከአባይ ወንዝ ምንም ድርሻ የላትም፡፡ ይህም ኢ-ፍትሃዊ ድርድር ነው ለዛሬው ውዝግብ መነሻ የሆነው፡፡

Read 5891 times