Saturday, 23 November 2019 11:47

የኦሮሚያ ክልል ከፍተኛ ባለሥልጣን በታጣቂዎች ተገደሉ

Written by  አለማየሁ አንበሴ
Rate this item
(1 Vote)

  የኦሮሚያ መንገዶች ባለሥልጣን አማካሪ የነበሩት አቶ ቶላ ገዳ ለመስክ ስራ ወደ ምዕራብ ወለጋ በተሰማሩበት አጋጣሚ በታጣቂዎች መገደላቸውን የኦዴፓ የሕዝብ ግንኙነት ኃላፊ አቶ ታዬ ደንደአ አስታውቀዋል፡፡ ባለሥልጣኑ ባለፈው ረቡዕ ሕዳር 10 ቀን 2012 ዓ.ም በመስክ ስራ ላይ እያሉ ‹‹በሸኔ›› ታጣቂዎች መገደላቸውን ኃላፊው ጠቁመዋል፡፡
በተለይ በምዕራብ ወለጋ አካባቢዎች የሚንቀሳቀሰው ታጣቂ ቡድኑ፤ ከዚህ ቀደምም ከወረዳ አስተዳዳሪዎችና ከበርካታ ግለሰቦች ግድያ ጋር በተያያዘ ስሙ የሚነሳ ሲሆን ከሦስት ሳምንት በፊትም በአካባቢው በመንግሥት ሃይሎችና በታጣቂ ቡድኑ መካከል ጠንካራ ውጊያ ሲካሄድ እንደነበር ምንጮች አስታውሰዋል፡፡
ረቡዕ እለት የተገደሉት ጎልማሳው ባለሥልጣን ለረጅም ጊዜ በኦሮሚያ ክልል በተለያዩ ሃላፊነቶች የሰሩ፣ እውቀቱና ብቃቱ ያላቸው አመራር እንደነበሩ አቶ ታዬ ገልጸዋል፡፡
‹‹ኦዴፓ አንድ ጠንካራ አመራሩን አጥቷል›› ያሉት ኃላፊው፤ የጓዳችንንና የሌሎችን ነፍስ በየጊዜው እየነጠቁ ያሉ አካላትን መንግሥት ለሕግ የማቅረብ ተግባሩን አጠናክሮ ይቀጥላል ብለዋል፡፡ጥቃት አድራሾቹ በሕዝብ ስም የሚነግዱ ቁማርተኞች ናቸው ያሉት አቶ ታዬ፤ እንዲህ ያሉ ግድያዎች ኦዴፓ የጀመረውን የለውጥ ጉዞ አያደናቅፈውም ብለዋል፡፡ መንግሥት ታጣቂዎች ላይ ጠንካራ እርምጃ በመውሰድ የህግ የበላይነትንና የአገሪቱን ሰላም እንደሚያረጋግጥ ጠ/ሚኒስትሩ በፓርላማ መናገራቸው አይዘነጋም፡፡



Read 1282 times