Sunday, 28 May 2017 00:00

ዳኛ ልኡል ገ/ማርያም፤ በጡረታ እንዲገለሉ የቀረበው ሃሳብ በም/ቤት አባላት ከፍተኛ ተቃውሞና ውዝግብ አስነስቷል

Written by  መታሰቢያ ካሳዬ
Rate this item
(4 votes)

• በመጨረሻ በሁለት ድምጸ ተዐቅቦና በሙሉ ድምጽ ጸድቋል
• በጀርመን አገር ከፍተኛ ህክምና እየተከታተሉ ነው ተብሏል
   በፌደራል ከፍተኛ ፍ/ቤት ለበርካታ ዓመታት ያገለገሉት ዳኛ ልዑል ገ/ማርያም፣ በከባድ ህመም ምክንያት ለ8 ወራት በሥራ ገበታቸው ላይ ያለመገኘታቸውን ተከትሎ፣ ከግንቦት 1 ቀን 2009 ዓ.ም ጀምሮ  ከሥራ እንዲሰናበቱና የጡረታና ሌሎች ጥቅማጥቅሞቻቸው እንዲከበሩላቸው የፌደራል ዳኞች አስተዳደር ጉባዔ ለህዝብ ተወካዮች ም/ቤት ያቀረበው ሃሳብ ከፍተኛ  ተቃውሞ ገጠመው፡፡
ዳኛው በምን ሁኔታ ውስጥ እንደሚገኙና ስለ ቤተሰቦቻቸው በህግ አግባብ ሳይታወቅ የጡረታ መብት ማስከበርም ሆነ የስምንት ወራት ደመወዝ እንዲከፈላቸው መፍቀድ ተገቢ አለመሆኑን በመግለፅ ነው የምክር ቤቱ አባላት ተቃውሟቸውን የገለጹት፡፡ ዳኛ ልዑል ገ/ማርያም ከሥራ እንዲሰናበቱ እንዲፈቀድ ለምክር ቤቱ ሃሳብ ያቀረቡት የፌደራል ዳኞች አስተዳደር ጉባዔ አባል አቶ ተስፋዬ ዳባ እንደገለፁት፤ ዳኛ ልዑል ገ/ማርያም በከባድ ህመም ተይዘው ላለፉት ስምንት ወራት በሥራ ገበታቸው ላይ ሊገኙ አልቻሉም፤ የዳኞች ጉባዔም በዳኝነት ሥራቸው መቀጠል እንደማይችሉ አምኖበታል፡፡ በዚህም ምክንያት የስምንት ወራት ደሞዛቸው እንዲከፈላቸውና የጡረታ መብታቸው ተከብሮ፣ከዳኝነት ሥራቸው እንዲሰናበቱ ውሳኔ እንዲሰጥ ም/ቤቱን ጠይቀዋል፡፡
ዳኛ ልዑል ቀደም ሲል በባንኮክ፣ በአሁኑ ወቅት ደግሞ በጀርመን በከፍተኛ ሕክምና ላይ እንደሚገኙ ለም/ቤቱ አባላት የተገለጸላቸው ሲሆን አባላቱም፤”ላለፉት ስምንት ወራት ዳኛው በሥራ ገበታቸው ላይ ባለመገኘታቸው ምክንያት የተወሰዱ እርምጃዎች ለም/ቤቱ መገለፅ ይገባቸው ነበር፤ አሁን ምንም ዓይነት መረጃ ባልቀረበበትና የግለሰቡን የጤና ሁኔታ የሚያረጋግጥ ማስረጃ በሌለበት ስንብት መጠየቁ ተገቢ አይደለም” ሲሉ ተቃውሞአቸውን አስረግጠው ተናግረዋል፡፡
የውሳኔ ሃሳቡን ለም/ቤቱ ያቀረቡት አቶ ተስፋዬ በበኩላቸው፤ የጡረታ መብትንና የስምንት ወራት ያልተከፈለ ደመወዝን በተመለከተ ውሣኔ የሚሰጠው የሚመለከተው አካል መሆኑን በመጠቆም፤ ከም/ቤቱ አባላት የሚጠበቀው ዳኛ ልዑል፤ በዳኝነት ሥራቸው መቀጠል የማይችሉ በመሆኑ ከዳኝነት ሥራቸው ላይ እንዲነሱ ማድረግ ብቻ ነው ሲሉ አስረድተዋል፡፡ በጉዳዩ ላይ የምክር ቤቱ አባላት የተለያዩ አስተያየቶችን የሰነዘሩ ሲሆን በመጨረሻም የዳኛ ልዑል ገ/ማርያም የዳኝነት ሥራ ስንብት፣በሁለት ድምፀ ተአቅቦና በሙሉ ድምፅ ጸድቋል፡፡  
ዳኛ ልዑል ገ/ማርያም፤ላለፉት 27 ዓመታት በፌደራል ከፍተኛ ፍ/ቤት በዳኝነት ሲያገለግሉ የቆዩ ሲሆን በ98 ዓ.ም የ”ቅንጅት” ችሎትና በድምፃዊ ቴዎድሮስ ካሣሁን (ቴዲ አፍሮ) ላይ ቀርቦ የነበረውን ሰው በመኪና ገጭቶ የማምለጥ ክስ መዳኘታቸው ይታወሳል፡፡

Read 5664 times