Monday, 10 April 2017 10:31

በኦስትርያ ታቦታቱንና ንዋያተ ቅድሳቱን መዝብረው የኮበለሉት አስተዳዳሪ እያወዛገቡ ነው

Written by 
Rate this item
(4 votes)

• ለመንበረ ፓትርያርኩ ሪፖርት እንዲያደርጉ ቢጠሩም ለመታዘዝ ፈቃደኛ አልኾኑም
                           • ለ19 ዓመታት የተከማቸውን የደብሩን ገንዘብ፣ የማኅበር ሀብት ነው፤ በሚል ክደዋል

       በኦስትርያ - ቪየና፣ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ምእመናንን በመክፈልና የቤተ ክርስቲያኒቱን ሁለት ታቦታት ከንዋያተ ቅድሳታቸው ጋራ በማውጣት፣ የኢትዮጵያን ቅዱስ ሲኖዶስ አላውቅም፤ በማለት ኮብልለዋል የተባሉት የቀድሞው አስተዳዳሪ፣ መጋቤ ስብሐት አባ ብርሃኑ ደበበ ጉዳይ እያነጋገረ ነው፡፡
አስተዳዳሪው የኮበለሉት፣ ከቅዱስ ሲኖዶስ ለተላለፈላቸው  መመሪያ ባለመታዘዝ ከሓላፊነታቸው ከተነሡና በሌላ አስተዳዳሪ መተካታቸውን ተከትሎ እንደኾነ ተገልጿል፡፡
በኦስትርያ - ቪየና በምትገኘው የደብረ ሲና ቅድስት ኪዳነ ምሕረት ቤተ ክርስቲያን፣ ላለፉት 12 ዓመታት በአስተዳዳሪነት የቆዩት መጋቤ ስብሐት አባ ብርሃኑ፣ ከአስተዳደር ሥራዎች ጋራ በተያያዘ፣ ባለፈው ዓመት ጥቅምትና ኅዳር ወራት፣ በደብሩ ሰበካ ጉባኤና በምእመናን ተደጋጋሚ አቤቱታ የቀረቡባቸው ሲኾን፤ ችግሩን ለመፍታትና የተጓደለውን አገልግሎት ለማሟላት እንዲቻል፣ ንብረቱን ለሰበካ ጉባኤው አስረክበው ወደ አዲስ አበባ እንዲመለሱና ለመንበረ ፓትርያርክ የውጭ ግንኙነት መመሪያ ሪፖርት እንዲያደርጉ አስቸኳይ ትእዛዝ ተላልፎላቸው እንደነበር ተጠቅሷል፡፡
ይኹንና፣ “ለጠቅላይ ቤተ ክህነቱ የተላከው ደብዳቤ ለእኔም ይላክልኝ” የሚል ተገቢ ያልኾነ ጥያቄ በመጠየቅ በትእዛዙ መሠረት ወደ ሀገር ቤት ባለመመለሳቸው፣ ካለፈው ዓመት መጋቢት ጀምሮ ከአስተዳዳሪነታቸው ተነሥተው፣ መጋቤ ብሉይ አባ ዘተክለ ሃይማኖት ገብረ መስቀል በተባሉ ሌላ ሓላፊ መተካታቸው ታውቋል፡፡
በቅዱስ ሲኖዶስ የተመደቡት አዲሱ አስተዳዳሪ ወደ ስፍራው ቢጓዙም፣ መጋቤ ስብሐት አባ ብርሃኑ፣ የደብሩን ንዋያተ ቅድሳትና ንብረት ለማስረከብ ፈቃደኛ ባለመኾናቸውም በተፈጠረው ውዝግብ፣ ቤተ ክርስቲያኗን አዘግተው፣ ቍልፉን እስከማስወሰድ ደርሰው እንደነበር ተነግሯል፡፡
ብፁዕ ወቅዱስ ፓትርያርክ አቡነ ማትያስ፣ በኦስትርያ ለካቶሊካዊት ቤተ ክርስቲያን ካርዲናልና የጳጳሳት ጉባኤ ሰብሳቢ በጻፉት የትብብር ጥያቄ፤ ቤተ ክርስቲያኑን ለመክፈት ቢቻልም፣ የቀድሞው አስተዳዳሪ፣ የደብሩን የቅድስት ኪዳነ ምሕረትና የቅዱስ ገብርኤል ታቦታት ከንዋያተ ቅድሳታቸው ጋራ በማውጣትና ምእመናኑን በመክፈል ከቤተ ክርስቲያን ማዕከላዊ አስተዳደር ኮብልለዋል፤ ተብሏል፡፡ ላለፉት 19 ዓመታት ከተለያዩ የገቢ ምንጮች አስተዋፅኦ እየተደረገ የተቀመጠውን፣ ከ75ሺሕ ዩሮ በላይ የቤተ ክርስቲያኒቱን የባንክ ሒሳብ፣ ‹‹የማኅበር  ሀብት ነው፤›› በሚል ፍጹም ክሕደትን ፈጽመዋል፤ ይላል፣ የምእመናኑ አቤቱታ፡፡
ቀደም ሲል የሚመደቡት ሓላፊዎች፣ ከአስተዳደር ሥራቸው ጋራ በካቶሊክ ቤተ ክርስቲያን የሚሰጠውን ስኮላርሽፕ የመከታተል ዕድል እንደነበራቸውና ለመንበረ ፓትርያርኩ ጥሪም ታዛዥ እንደነበሩ የገለጹት ምእመናኑ፣ በውዝግቡ ሳቢያ ዕድሉ ሊሰረዝ እንደሚችል ጠቁመዋል፡፡
ጉዳዩም በሕግ ሒደት ላይ የሚገኝ ሲኾን፣ አስተዳዳሪው በችሎት ቀርበው፣ ‹‹የኢትዮጵያን ቅዱስ ሲኖዶስ አላውቅም›› በማለት ክሡን መካዳቸውን ለማወቅ ተችሏል፡፡

Read 3942 times