Monday, 03 April 2017 00:00

ተቃዋሚዎች የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ መራዘሙ አሳዝኖናል አሉ

Written by  አለማየሁ አንበሴ
Rate this item
(3 votes)

“አዋጁ በሁሉም ክልል መሆኑ ህገ መንግሥታዊ ጥያቄ ያስነሳል” (የህግ ባለሙያ)
  የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ለቀጣይ 4 ወራት መራዘሙ በእጅጉ እንዳሳዘናቸውና እንዳስደነገጣቸው ተቃዋሚ ፓርቲዎች የገለፁ ሲሆን ኮማንድ ፖስቱ በበኩሉ፤ያላጠናቀቃቸው የቤት ስራዎች ስላሉት አዋጁ እንዲራዘም ማስፈለጉን አስታውቋል፡፡
ከ6 ወራት በፊት የታወጀው አስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ሊጠናቀቅ የአንድ ሳምንት ጊዜ የቀረው መሆኑን ተከትሎ የኮማንድ ፖስቱ ሴክሬታሪያትና የመከላከያ ሚኒስትር ሲራጅ ፈርጌሣ ከትናንት በስቲያ ለፓርላማው ምክንያታቸውን አቅርበው አዋጁ እንዲራዘም የጠየቁ ሲሆን ፓርላውም ለሚቀጥሉት 4 ወራት እንዲራዘም በሙሉ ድምፅ ወስኗል፡፡
የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ ከታወጀ በኋላ ባሉት ወራት በሀገሪቱ ላይ ተጋርጦ የነበረውን አደጋ ለመቀልበስ መቻሉን ያስረዱት ሚኒስትሩ፤ይሁን እንጂ ክልሎች በሚዋሰኑባቸው አካባቢዎች የሚነሱ ችግሮችን ለመጠቀም የሚፈልጉ “ፀረ ሰላም” ኃይሎች እየተንቀሳቀሱ መሆናቸውንና  “የሁከት” እና “ብጥብጡ” አብዛኞቹ ቀንደኛ መሪዎች ቢያዙም ቀሪዎች መኖራቸውን ጠቁመው፣  ወረቀት በመበተን ሰላምና መረጋጋቱን ለማደፍረስ የሚንቀሳቀሱ ኃይሎች በመኖራቸው አዋጁን ማራዘም ማስፈለጉን አስታውቀዋል፡፡
በአዋጁ መራዘም ላይ አስተያየታቸውን የሰጡት የኢዴፓ ፕሬዚዳንት ዶ/ር ጫኔ ከበደ፤ የአዋጁ መራዘም እንዳሳዘናቸው ገልጸው፣እርምጃው ኢኮኖሚያዊ፣ ፖለቲካዊና ማህበራዊ ውድቀትን የሚያባብስ ነው ብለዋል፡፡ “ለ4 ወር ብቻ ሳይሆን ለቀጣይ አንድ ዓመት ቢራዘምም ምንም መፍትሄ አያመጣም” ያሉት ዶ/ር ጫኔ፤አሁንም ቢሆን የሚያስፈልገው የፖለቲካ መፍትሄ ነው ብለዋል፡፡
“የአዋጁ መራዘም ለኔ አስደንጋጭ ነው” ያሉት የመድረክ ሊቀመንበር ፕ/ር በየነ ጴጥሮስ በበኩላቸው፤አዋጁ በመራዘሙ እነሱ ተሃድሶአችንን እያጠለቅን ነው እንደሚሉት ሁሉ የኛ ስጋትም እየጠለቀ ነው” ሲሉ አስተያየታቸውን ሰጥተዋል፡፡  
የአዋጁ መራዘም በእጅጉ እንዳሳዘናቸው የገለፁት የሰማያዊ ፓርቲ የውጭ ግንኙነት ኃላፊ አቶ አበበ አካሉ፤"ሁሉም ነገር ተረጋግቷል፣ሰላም ሰፍኗል እየተባለ አዋጁን ማራዘም ተገቢ አይደለም፤ ለሀገሪቱ አይጠቅምም፣ የፖለቲካ ምህዳሩንም ያጠባል” ብለዋል፡፡
"የአዋጁ መራዘም በፓርቲያችን እንቅስቃሴ ላይ እንቅፋትና ስጋት ይፈጥርብናል፡፡ በየክልሉ ተንቀሳቅሰን የፓርቲውን ስራ መስራት አለብን፣ ከህዝብ ዘንድ መድረስ አለብን፡፡ ይሄ በጣም ያሳስበናል፡፡" ሲሉ ስጋታቸውን ገልጸዋል- አቶ አበበ፡፡  
የመኢአድ ፕሬዚዳንት ዶ/ር በዛብህ ደምሴ በበኩላቸው፤የአዋጁ መራዘም መፍትሄ እንደማይሆን በመግለፅ መንግስት አዋጁን ከማራዘም ይልቅ ለህዝቡ ጥያቄ ቀጥተኛ ምላሽ ለመስጠት ቢሞክር እንደሚሻለው ተናግረዋል፡፡   
ጠ/ሚኒስትር ኃይለማርያም ደሳለኝ "ከ80 በመቶ በላይ የሚሆነው ህዝብ አዋጁ እንዲራዘም ይፈልጋል" ሲሉ መናገራቸውን ተከትሎ ተቃዋሚዎች መረጃው ሃሰተኛ ነው ሲሉ አጣጥለውታል፡፡ "የህዝቡን ፍላጎት ማን ነው የጠየቀው? መቼስ ነው የተጠናው?" በማለት ይጠይቃሉ - ተቃዋሚዎች፡፡   
የአስቸኳይ ጊዜ መርማሪ ቦርድ ባለፈው ማክሰኞ ለፓርላማው ባቀረበው ሪፖርቱ፤ባለፉት 6 ወራት ከ25 ሺህ በላይ ዜጎች በቁጥጥር ስር ውለው ከ20 ሺህ በላይ የሚሆኑት ስልጠናና ትምህርት ተሰጥቷቸው መለቀቃቸውንና ከ5 ሺህ በላይ የሚሆኑት ጉዳያቸው ወደ ፍ/ቤት ማምራቱን መግለፁ አይዘነጋም፡፡

Read 3472 times