Sunday, 22 January 2017 00:00

በኦሮሚያና በሶማሌ ክልል አዋሳኝ በተቀሰቀሰ ግጭት የበርካቶች ህይወት ቀጥፏል ተባለ

Written by  አለማየሁ አንበሴ
Rate this item
(18 votes)

    በኦሮሚያ እና በኢትዮጵያ ሶማሌ ክልል አዋሳኝ ድንበሮች በተቀሰቀሰ ግጭት የበርካቶች ህይወት ያለፈ ሲሆን ግጭቱን ለማብረድ መከላከያ ሰራዊት ጣልቃ መግባቱ ተገልጿል፡፡
የኦሮሚያና የኢትዮጵያ ሶማሌ ክልል በምስራቅ ሀረርጌ፣ በምዕራብ ሀረርጌ፣ በባሌ፣ ጉጂና ቦረና በኩል የሚዋሰኑ ሲሆን በሁሉም ተዋሳኝ አካባቢዎች የተቀሰቀሰው ግጭት እየቀነሰ ቢሆንም እስከ ትናንት ድረስ ሙሉ ለሙሉ አለመብረዱን ምንጮች ጠቁመዋል፡፡  ግጭቱ ከሶስት ሳምንት በፊት ታህሳስ 20 በምስራቅ ሀረርጌ ጭራቅሰን ወረዳ ላይ መቀስቀሱን የገለፁት የኦሮሚያ ክልል የመንግስት ኮሚኒኬሽን ጉዳዮች ኃላፊ አቶ አዲሱ አረጋ በምስራቅ ሀረርጌ በሜዩም ሙሉቤ፣ በቁምቢ ወረዳዎች፣ በምዕራብ ሀረርጌ ሜኤሶ አካባቢ፣ በባሌ፣ ዳዋ ሄረር እንዲሁም በጉጂና በቦረና አዋሳኝ አካባቢዎች በተፈጠሩት ግጭቶች የበርካታ ሰዎች ህይወት ማለፉንና በንብረት ላይም ውድመት መድረሱን አስታውቀዋል፡፡
ግጭቱ እስከ ትናንት በስቲያ መቀጠሉን የጠቆሙት ኃላፊው፤ በግጭቱ የደረሰው የጉዳት መጠንና የግጭቱ መነሻ ተጣርቶ በቅርቡ ይገለጻል ብለዋል፡፡
በግጭቶቹ በሰው ህይወት ላይ የሚደርሰው ጉዳት እንዳይጨምር የመከላከያ ሰራዊት በመሃል ገብቶ እያረጋጋ መሆኑን ለአዲስ አድማስ የጠቆሙት አቶ አዲሱ፤ ከፌደራል መንግስትና ከሱማሌ ክልላዊ መንግስት አመራሮች ጋር ዘላቂ መፍትሄ ለማምጣት ውይይት እየተደረገ ነው ብለዋል፡፡
ከዚህ ቀደም በሁለቱ ክልሎች መሃከል በነበረ የድንበር ይገባኛል ጥያቄ ላይ ሪፈረንደም ተደርጎ አሁን ግጭት የተቀሰቀሰባቸው አካባቢ የሚገኙ በርካታ ወረዳዎች ወደ ኦሮሚያ መካለላቸውን የጠቆሙት ኃላፊው የአሁኑ የከፋ ይሁን እንጂ በፊትም አልፎ አልፎ ግጭቶች ይፈጠሩ እንደነበር አውስተዋል፡፡
አዋሳኝ ድንበሮች በምልክት አለመከለላቸው እና የድርቁን ወቅት ተከትሎ በአርብቶ አደሮች የሚፈጠር የውሃ ፍላጎት የግጭት መንስኤ ሳይሆን እንደማይቀር የጠቆሙት አቶ አዲሱ፤ ነገር ግን ይህ በሚደረገው ምርመራ የሚረጋገጥ መሆኑን አስረድተዋል፡፡  

Read 5716 times