Sunday, 25 December 2016 00:00

አንከር ወተት ለ“ስለእናት ህፃናት ማሳደጊያ ማህበር” ድጋፍ አደረገ

Written by  ናፍቆት ዮሴፍ
Rate this item
(3 votes)

“ፋፋም” ለህፃናቱ የፋፋና ሴሪፋም ምርት ለግሷል
                                          
      አንከር ወተት ኢትዮጵያ ውስጥ መመረት የጀመረበትን አንደኛ አመት ምክንያት በማድረግ ለስለእናት ወላጅ አልባ ህፃናት ማህበር” ለ1 አመት የሚዘልቅ የወተት ድጋፍ አደረገ፡፡ በማሳደጊያው የሚገኙ 70 ህፃናት የወተት ድጋፍ ተጠቃሚ ይሆናሉ፡፡
የዛሬ ሳምንት መካኒሳ በሚገኘው “ስለ እናት የህፃናት ማሳደጊያ ማህብር” ውስጥ በተካሄደው በዚህ ስነ-ስርዓት ላይ የተገኙት “የኒውዚላንድ ሚልክ ፕሮዳክትስ ኢትዮጵያ” ዋና ስራ አስኪያጅ አቶ ዜኮ ቃሲም ድጋፉን ካበረከቱ በኋላ ባደረጉት ንግግር፤ አንከር ወተት በዓለም ገበያ ላይ ለ130 ዓመት መዝለቁንና ከ70 በላይ በሆኑ የአለም አገራት በፓውደርና በፈሳሽ መልክ ጥራት ያለው ወተት በማቅረብ ዝና ማትረፉን አስረድተዋል፡፡
አንከር ኢትዮጵያ ውስጥ በቆየበት አንድ አመት 40 ቢሊዮን ሚሊ ሊትር ብርጭቆ ወተት ለገበያ ማቅረቡን የገለፁት አቶ ዜኮ፤ ወተቱ የያዛቸው 33 ንጥረ ነገሮች በተለይ ለኢትዮጵያውያን ህፃናት እጅግ አስፈላጊ መሆናቸውን ተናግረዋል፡፡
ኒውዚላንድ ሚልክ ፕሮዳክትስ፤ ከወተት አቅርቦት በተጨማሪ ማህበራዊ ሀላፊነቱን ለመወጣት በርካታ ፕሮጀክቶች እንዳሉት የጠቆሙት ኃላፊው፤ ከነዚህም መካከል ላለፉት 14 ዓመታት ወላጅ አልባ ህፃናትን ሲታደግ የቆየውን “ስለ እናት ማህበር” መደገፉ የፕሮጀክቱ አንዱ አካል ነው ብለዋል፡፡ በቅርቡም ለኢትዮጵያ ወተት አቅራቢ ማህበር የማቀዝቀዣ ማዕከላትን በማቋቋም ለመደገፍ ከማህበሩ ጋር መፈራረማቸውን ኃላፊው ተናግረዋል፡፡
ከአንከር ጋር የስራ ግንኙነት የፈጠረው ፋፋ ፋብሪካም ለህፃናቱ ለአንድ አመት የሚያገለግል የፋፋና የሴሪፋም ምርት ለህፃናት ማሳደጊያው ለግሷል፡፡ ከተቋቋመ 14 ዓመት ያስቆረው “ስለ እናት ወላጅ አልባ ህፃናት ማሳደጊያ ማዕከል”፤ በስሩ 202 ያህል ህፃናትን እየደገፈ እንደሚኝ ተገልጿል፡፡

Read 2386 times