የኢትዮጵያ ፌደራላዊ አንድነት መድረክ፤ ሀገሪቱን ያረጋጋል ተብሎ የወጣው የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁን በተመለከተ ኮማንድ ፖስቱን ማብራሪያ እንደጠየቀ የፓርቲው ሊቀመንበር ፕ/ር በየነ ጴጥሮስ ገለፁ፡፡
የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ ተቃዋሚ ፓርቲዎችን በተመለከተ፤ “ማንኛውም ተቃዋሚ ፓርቲ የሀገርን ደህንነትን አደጋ ላይ የሚጥል መግለጫ መስጠት የለበትም” እንደሚል የጠቀሱት ፕ/ር በየነ፤ ኮማንድ ፖስቱ ዝርዝር ማብራሪያ እንዲሰጣቸው በደብዳቤ መጠየቃቸውን አስታውቀዋል፡፡
አዋጁ በተለይ በመሰረታዊ የፓርቲው ስራ ላይ ስለሚኖረው ተፅዕኖ፣ ለመገናኛ ብዙኃን ቃለ ምልልስና የአቋም መግለጫ ስለሚሰጥበት አግባብ እንዲሁም የፓርቲ ስብሰባዎች፡- ማካሄድ በተመለከተ ግልፅ ማብራሪያ እንዲሰጣቸው ጥያቄ ማቅረባቸውን ፕ/ር በየነ ገልፀዋል፡፡
“ሰላማዊ ሰልፍ ለማድረግ፣ የአዳራሽ ስብሰባ፣ በየክልሉ አዳዲስ ፅ/ቤቶች መክፈት እንዲሁም ተቃዋሚዎች በአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ በምን አግባብ መንቀሳቀስ እንደሚችሉ ማብራሪያ ጠይቀናል›› ብለዋል፡፡
ዝርዝር ጉዳዮችን በግልፅ እስከምንረዳ ድረስ የአቋም መግለጫዎችን ከማውጣት ተቆጥበን ቆይተናል ያሉት ሊ/መንበሩ፤ አዋጁን መተርጎም የሚችለው ኮማንድ ፖስቱ ብቻ መሆኑን ገልፀዋል፡፡
===========
Sunday, 30 October 2016 00:00
“መድረክ” በአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ ላይ የኮማንድ ፖስቱን ማብራሪያ ጠየቀ
Written by አለማየሁ አንበሴ
Published in
ዜና