Sunday, 30 October 2016 00:00

ዓይነ ስውራን ለመጀመሪያ ጊዜ በዳኝነት እንዲሰሩ ተወሰነ

Written by  አለማየሁ አንበሴ
Rate this item
(3 votes)

   በአገሪቱ ታሪክ ለመጀመሪያ ጊዜ አይነ ስውራን በመደበኛ ፍ/ቤቶች በዳኝነት ተሹመው እንዲሰሩ የፌደሬሽን ም/ቤት ውሳኔ ማሳለፉ ተገለፀ፡፡ “እስካሁን በልማድ ዓይነ ስውራን በዳኝነት ሥራ  ላይ እንዳይሰማሩ ተከልክሎ መቆየቱ አግባብ አይደለም” ያለው የፌዴሬሽን ም/ቤት፣ “ከዚህ በኋላ ዓይነ ሥውራን በመደበኛ ፍ/ቤት በዳኝነት ተሾመው መስራት እንደሚችሉ አስታውቋል፡፡
የራሳቸውን መብት ለማስከበር ለረጅም ጊዜያት ለተለያዩ የመንግስት አካላት አቤቱታ ሲያቀርቡ መቆየታቸውን የገለፁት አቶ ወሰን አለሙና አቶ ዳዊት ኦትቾ የተባሉት አይነ ስውራን የህግ ባለሙያዎች፤ ከብዙ ውጣ ውረድ በኋላ የፌዴሬሽን ም/ቤት ጥቅምት 2 ቀን 2009 ዓ.ም “አይነ ስውራን ዳኛ ሆነው መስራት ይችላሉ” የሚል ውሳኔ ማሳለፉን ተናግረዋል፡፡
ከአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲና ከዲላ ዩኒቨርሲቲ በ2005 ዓ.ም በህግ ሙያ ከተመረቁ በኋላ ወደ አማራ ክልል የፍትህ ባለሙያዎች ማሰልጠኛና የህግ ምርምር ኢንስቲትዩት መግባታቸውን የጠቆሙት ሁለቱ የህግ ባለሙያዎች፤ ጥያቄውን የጀመሩት ሥልጠናውን እየወሰዱ ባሉበት ወቅት እንደነበር ያስታውሳሉ፡፡
‹‹አይነ ስውራን ተመርጠው አቃቤ ህግ ብቻ ነው የሚሆኑት፤ ይሄ ለምን ይሆናል ብለን በስልጠናው ወቅት ቀድመን ጠየቅን›› የሚሉት አቶ ወሰን፤ ማሰልጠኛ ተቋሙ የሰጠን መልስ “ጉዳዩ እኔን አይመለከተኝም” የሚል ነበር ብለዋል፡፡ ወደ ጠቅላይ ፍ/ቤት ስንሄድም ጠ/ፍ/ቤቱ እንደማይመለከተው ገለፀልን፤ ከዚያም ወደ ኢንስቲትዩቱ ቦርድ በማምራት ጉዳዩን ያመለከቱ ሲሆን፤ ጉዳዩ በቦርዱ እየታየ ጎን ለጎ ደግሞ ለዳኞች አስተዳደር ጉባኤ ማመልከታቸውን ይናገራሉ፡፡ ነገር ግን የዳኞች አስተዳደር ጉባኤው “እኔን አይመለከተኝም›› የሚል ምላሽ ሰጣቸው፡፡ እንዲያም ሆኖ ተስፋ አልቆረጡም፡፡
“ለክልሉ ም/ቤት አመለከትን፤ አሁንም ምላሽ አላገኘንም፡፡ በክልሉ ያሉ ሁሉንም የሚመለከታቸውን አካላት ካነጋገርን በኋላ በድጋሚ የኢንስቲቲዩቱ ቦርድ ጋ በመሄድ የመጨረሻ ውሳኔያችሁን አሳውቁን አልናቸው፡፡ ቦርዱም በመጨረሻ ውሳኔው፤ “አዎ! ትክክል ነው አይነ ስውራን ዳኛ እንዳይሆኑ የሚከለክል ህግ የለም፤ ነገር ግን በልምድ ተከልክለዋል፡፡ ስለዚህ ይህ ልምድ ትክክለኛ ነው አይደለም የሚለውን አጥንተን ለወደፊት ዳኛ መሆን ይችላሉ አይችሉም የሚለውን እንወስናለን የሚል ምላሽ ሰጠን›› የሚሉት አቶ ወሰን፤ “እኛ በዚህ ስላልረካን መብትን ለመንፈግ እንጂ መብትን ለመፍቀድ ጥናት አያስፈልግም ብለን ክርክራችንን ቀጠልን ብለዋል፡፡
ክርክራቸው ከመቋጨቱ በፊት ግን ከባህር ዳር ርቀው ባሉ የክልሉ ወረዳዎች በአቃቤ ህግነት መመደባቸውን የሚገልፁት የህግ ባለሙያዎቹ፤ “የህገ መንግስቱ አንቀፅ 42(1) ላይ የተደነገገውን ሙያን የመምረጥ መብት በመጥቀስ፣ የክልሉ መንግስት ይህን ህገ መንግስታዊ መብት ጥሶብናል ሲሉ ለፌዴሬሽን ም/ቤት አቤቱታ ማቅረባቸውን ይገልፃሉ፡፡
በፌዴሬሽን ም/ቤት የህገ መንግስት ጉዳዮች አጣሪ ጉባኤም፤ ጉዳዩን ከመረመረ በኋላ ስራን የመምረጥ ህገ መንግስታዊ መብት ገደብ ሊኖረው እንደሚችል፣ ነገር ግን አይነ ስውራን ዳኛ መሆን ይችላሉ የሚል ውሳኔ ማሳለፉን ጠቁመው፣ ውሳኔውንም የፌዴሬሽን ም/ቤቱ ተቀብሎ ማፅደቁን አቶ ወሰን ለአዲስ አድማስ አስረድተዋል፡፡
ረጅም ጊዜያት የፈጀው ይህ የመብት ክርክር፣ በዚህ መልኩ መቋጨቱን የገለፁት የህግ ባለሙያዎቹ፤ ከዚህ በኋላ በአማራ ክልል ብቻ ሳይሆን በመላ አገሪቱ አይነ ስውራን የህግ ባለሙያዎች በመደበኛ ፍ/ቤት ዳኛ ሆነው መሾም ይችላሉ ብለዋል፡፡
የፌዴሬሽን ም/ቤት የኢንፎርሜሽን ኮሚኒኬሽን ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር አቶ ገብሩ ገብረስላሴ፤ ጉዳዩ ለህገ መንግስት አጣሪ ጉባኤ ቀርቦ፣ ዓይነስውራን በዳኝነት መስራት ይችላሉ የሚል ውሳኔ መስጠቱን ለአዲስ አድማስ አረጋግጠዋል፡፡




Read 3176 times