Saturday, 02 July 2016 11:54

የአዲስ አበባ መስተዳድር ለታክሲ እጥረት መፍትሄ አገኘ - 300 ብስክሌቶችን ገዛ

Written by 
Rate this item
(17 votes)

የአንድ ብስክሌት ዋጋ - 35 ሺ ብር!
    የአዲስ አበባ ነዋሪዎች፣ በታክሲ እጥረት መንገላታታቸውና መማረራቸውን እንርሳው - ሁሉንም ችለውና ተሸክመው ኑሯቸውን ይገፋሉ እንበል፡፡ ግን፣ ከአገሪቱ ኢኮኖሚ ውስጥ ሩብ ያህሉን የምታመነጭ ከተማ፣ በትራንስፖርት እጥረት ስትጨናነቅ ጉዳቱ ቀላል ይሆናል?
የከተማዋ ትራንስፖርት ባለስልጣናት፣ “ነዋሪዎችን ከታክሲ ተፅእኖ ነፃ ለማውጣት ነው አላማችን” ብለው ሲናገሩ፤ ምን ለማለት ፈልገው እንደሆነ ግራ ያገባል፡፡ ከትራንስፖርት እጥረት ነጻ የማውጣት አላማ ሳይሆን “ከታክሲ ነፃ የማውጣት” አላማ መያዝ ምን ማለት ነው?
ጉዳዩ፣ ቀልድና ጨዋታ እንዳልሆነ በቅጡ ባይገባቸው ይሆናል፡፡ ነዋሪዎች በተለያዩ እውነተኛ የኑሮ ችግሮች በቤት እጦት፣ በትራንስፖርት እጥረት፣ በኑሮ ፈተናዎች ተወጥረዋል፡፡ ባለስልጣናት ደግሞ በመግለጫና በፕሮፓጋንዳ፣ ሁሉንም ችግሮች ብን አድርገው ማጥፋት የሚችሉ ይመስላቸዋል፡፡ የምናብ ዓለም ይፈጥራሉ፡፡ ህገ ወጥ ቤቶችን የማፍረስ ዘመቻዎች ላይ እየተፈጠሩ ያሉ ችግሮችን ተመልከቱ፡፡ በአንድ ክፍለ ከተማ ብቻ 20 ሺህ ቤቶችን ለማፍረስ ነው የታቀደው፡፡ በሌሎች ክፍለ ከተማዎችም እንዲሁ፡፡
ቤቶችን ማፍረስ ከመቶ በላይ ሰዎችን እንደሚያፈናቅልና ህይወታቸውን እንደሚያናጋ ለመገንዘብ ይከብዳል? አብዛኞቹ ከአካባቢው ገበሬ ትንንሽ መሬት በመግዛት፣ የአቅማቸውን ያህል አንድ ሁለት ክፍል የጭቃ ቤት የሰሩ ነዋሪዎች ናቸው፡፡
የመንግሥት ባለስልጣናት ግን፣ በደፈናው የመሬት ወረራ በማለት ነገሩን ያጋንኑታል፡፡ መሃል ከተማ ውስጥ ቤት ተከራይተው ለመኖር እንኳ አቅም የሌላቸው ናቸው - ብዙዎቹ፡፡ ለዚህም ነው ከከተማ ዳር ላይ ለመኖር የሚሞክሩት፡፡ እነዚህ ነዋሪዎች፣ በማናለብኝነት፣ በየቦታው ሰፋፊ መሬት እየያዙ አራት አምስት ቦታ፣ የተንጣለለ ቪላና ፎቅ የሚሰሩ እብሪተኞች እንደሆኑ አድርጐ ፕሮፓጋንዳ መንዛት፤… እውነተኛ ያልሆነ ምናባዊ አቋም ለመፍጠር ይጠቅም ይሆናል፡፡ “መንግሥት ደና አደረገ፤ የማፍረስ ዘመቻው መቀጠል አለበት” የሚል ድጋፍ ለማግኘትም ይረዳ ይሆናል፡፡ ነገር ግን፤ በፕሮፓጋንዳ በተፈጠረ ”ምናባዊ አለም” እውነተኛው የነዋሪዎች ችግር ብን ብሎ አይጠፋም፡፡
“ህገ ወጥ ቤቶች” መነካት የለባቸው እያልኩ አይደለም፡፡ ውለው አድረው ችግር ያስከትላሉ፡፡ ነገር ግን፣ እንደዘበት በመቻ ማፍረስ፣ የመቶ ሺ ነዋሪዎችን ኑሮ እንደዘበት ማናጋት ማለት ነው፡፡ ይህ ደግሞ፣ ለነውጠኞችና ለዱርዬዎች እድል ይከፍታል፡፡ የድብድብና የግድያ ሰበብ ይሆንላቸዋል፡፡ የአብዛኛው ሰው ፍላጐት ግን ይሄ አይደለም፡፡ ብጥብጥ፣ ችግርን ያባብሳል እንጂ መፍትሄ አይሆንም፡፡ ጥያቄ ምንድነው? ቤታቸው ፈረሰ፤ ከዚያስ የት ይጠለሉ? የት ይሂዱ? የት ይኑሩ? አብዛኞቹ አማራጭ የላቸውም፡፡ ይህንን እውነተኛ ችግር ለመገንዘብ አለመፈለግ፣ ነገሩን እንደ ቀልድና እንደ ጨዋታ ከመቁጠር አይለይም፡፡ መዘዙም ብዙ ነው፡፡ ራስን በራስ ጠልፎ ለመጣል እንደመሞከር ነው፡፡ ይልቅ፣ በአስተዋይነትና በጥንቃቄ የብዙ ሰዎችን ኑሮ በማያናጋና አማራጭ በማያሳጣ መንገድ መፍትሄ ለማበጀት መትጋት ይሻላል፡፡ የትራንስፖርት እጥረት ላይም ነገሩ እንደ ቀላል ጉዳይ በማየት “ከታክሲ ነፃ ማውጣት” የሚል ቀልድና ጨዋታ ላይ ጊዜ ማጥፋት አያዋጣም፡፡ ይህም ብቻ አይደለም፤ የአየር ብክለትን ለመከላከል የካርቦን ልቀትን ለመቀነስ፣ ታክሲዎችን ማዳከም… የሚባል ጨዋታ አለ፡፡
ወደ ቀልድ!
የአውሮፓ ፖለቲከኞችና ወገኞች “የአየር ብክለት፣ የካርቦን ልቀት” .. እያሉ ይቀናጡ፡፡ እዚህ አዲስ አበባ ሰዎች በኑሮ፣ በትራንስፖርት፣ በቤት ችግር መከራ በሚያዩበት ከተማ ግን፣ እንዲህ አይነት … የመቀናጣት ወገኛ ሙከራ … መጨረሻው አያምርም፡፡ የኑሮ ችግር ተጠራቅሞ ተደራርቦ መቼ እንደሚያፈተልክና እንደሚፈነዳኮ አይታወቅም፡፡ ስለዚህ፣ ከጥፋት በስተቀር ሌላ ትርጉም የሌለውን ወገኛነት በመተው፣ ኢኮኖሚና ተጨባጭ የኑሮ ችግሮች ላይ ማተኮር ይበጃል፡፡
የትራንስፖርት እጥረትን ለመፍታት ከመትጋት ይልቅ፤ የካርቦን ልቀትን የሚቀንሱ ብስክሌቶችን በታክሲ ምትክ እናከፋፍላለን በሚል ወገኛነት መቀናጣት፤ … 300 ብስክሌት ለመግዛት፣ ለብስክሌት ልዩ መንገድ ለመከለል … 21 ሚሊዮን ብር ማባከን … የራስን መቃብር የመቆፈር ሙከራ ከመሆን ያለፈ ትርጉም አይኖረውም፡፡ በርካታ ደርዘን አገራት በቀውስና በነውጥ ውስጥ ተዘፍቀው፣ መውጣት እንዳቃታቸው እያየን … አንዴ ከተንሸራተቱ በኋላ ማጠፊያው እንደሚያጥር እያየን … በራሳችን እጅ ቀውስ እንጠራለን እንዴ?

Read 7143 times