Saturday, 26 March 2016 10:50

450 ሺህ ሜ. ቶን የእርዳታ ስንዴ በወደብ መጨናነቅ ዘግይቷል ተባለ

Written by 
Rate this item
(23 votes)

     የርሃብ ተጎጂ ለሆኑ ዜጎች ከውጭ አገራት የተገዛ 450 ሺህ ሜትሪክ ቶን የእርዳታ ስንዴ በጅቡቲ ወደብ በተፈጠረ የመርከቦች መጨናነቅና ወረፋ ሳቢያ በወቅቱ ወደ አገር ውስጥ ገብቶ ለተረጂዎች ሊከፋፈል አለመቻሉን ብሉምበርግ ዘገበ፡፡
ኢትዮጵያ ከውጭ አገራት የምትገዛው ስንዴ መጠን እያደገ መምጣቱን ተከትሎ በጅቡቲ ወደብ ከፍተኛ መጨናነቅ ተፈጥሯል ያለው ዘገባው፣ የእርዳታ እህሉን የጫኑ አስር ያህል መርከቦች ጭነታቸውን ለማራገፍ ወረፋ እየጠበቁ እንደሚገኙ ከጅቡቲ ወደብ አስተዳደር ያገኘውን መረጃ ጠቅሶ ገልጧል፡፡
“ሴቭ ዘ ችልድረን” የእርዳታ እህሉን ከመርከቦቹ ለማራገፍ 40 ቀናት ያህል ጊዜ ይፈጃል ማለቱን የጠቆመው ዘገባው፣ በኢትዮጵያ የ“ሴቭ ዘ ችልድረን” ዳይሬክተር ጆን ግርሃምም፣ የእርዳታ እህል የጫኑ በርካታ መርከቦች በጅቡቲ ወደብ ወረፋ እየጠበቁ እንደሚገኙና እህሉን ለማራገፍ በቂ ሁኔታዎች አለመመቻቸታቸውን እንደተናገሩ አስረድቷል፡፡
የኢትዮጵያ መንግስትም በጅቡቲ ወደብ መጨናነቅ መኖሩን አምኖ፣ ለማዳበሪያና ለስንዴ ቅድሚያ ተሰጥቶ የማራገፍ ስራው እየተከናወነ እንደሚገኝ መግለፁን ዘገባው አመልክቷል፡፡

Read 6341 times