Saturday, 13 February 2016 10:46

“የማንነት ጥያቄ በማንሳታችን ስቃይና በደል እየደረሰብን ነው”

Written by  ናፍቆት ዮሴፍ
Rate this item
(8 votes)

      በደቡብ ክልል በጎሙ ጎፋ ዞን ውስጥ የሚገኙ የቁጫ ህዝቦች፤ በሚያነሱት የማንነት ጥያቄ ምክንያት እስራት፣ ድብደባና እንግልት እየደረሰባቸው መሆኑን በምሬት ገለፁ፡፡
የቁጫ ህዝብ ከ1987 ዓ.ም ጀምሮ ባልተደራጀ መልኩም ቢሆን የማንነት ጥያቄ ሲያቀርብ መቆየቱን የገለፁት ቅሬታ አቅራቢዎቹ፤ በ2005 ዓ.ም ህዝብ እንደ አንድ ብሔረሰብ ማንነቱን የሚያረጋግጥ በጥናት የተደገፈ ሙሉ ማስረጃ ለክልሉ ብሔረሰቦች ምክር ቤት አቅርቦ ምላሽ ባለማግኘቱ፣ ጉዳዩን ወደ ፌደሬሽን ምክር ቤት ለማቅረብ መገደዳቸውን ተናግረዋል፡፡
የደቡብ ክልል የብሔረሰቦች ም/ቤት፤ አንድ ብሔረሰብ የማንነት ጥያቄ ሲያቀርብለት ለሁለት ዓመት ጉዳዩን በጥናት ተከታትሎ ውሳኔ እንዲሰጥ ይፈቀድለታል ያሉት ቅሬታ አቅራቢዎቹ፤ ሆኖም ም/ቤቱ ላለፉት ሦስት ዓመታት ለጥያቄያችን ምላሽ ስላልሰጠን ጉዳዩን ለፌዴሬሽን ምክር ቤት አመልክተናል ብለዋል፡፡ ብሔረሰቡ የማንነት ጥያቄ በማንሳቱ እስራት፣ ድብደባና እንግልት እየደረሰበት መሆኑን የጠቆሙት ቅሬታ አቅራቢዎቹ፤ የሰብአዊ መብት ጥሰቱ ስለተባባሰ አካባቢውንና ቤተሰቡን ጥሎ ለመሰደድ እየተገደደ ነው ብለዋል፡፡
ስማቸው እንዳይጠቀስ የፈለጉ የቁጫ አርሶ አደር እንደገለፁት፤ “ማንነቴን ለማረጋገጥ ባደረግሁት እንቅስቃሴ ከጥቂት ወራት በፊት በወረዳው ፖሊስ በደረሰብኝ ድብደባ፣ ብልቴ ደም እስከማፍሰስ ደርሶ ራሴን ስቼ ነበር” ብለዋል፡፡
የወረዳው ባለስልጣናት፤ የማንነት ጥያቄ ህዝቡ እንዲያቀርብ አስተባብረዋል ያሏቸውን በርካታ ሰዎች የሀሰት ክስ መስርተው በአርባ ምንጭ ማረሚያ ቤት ከሁለት ዓመታት ላይ በእስር እንዳቆያቸውም ቅሬታ አቅራቢዎቹ ተናግረዋል፡፡
ዘንድሮ በአዲስ በተዋቀረው የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት፣ ቁጫን ወክለው ወ/ሪት ወይንሸት ገሰሰ የተባሉ የአካባቢው ፓርላማ መግባታቸውን የተናገሩት የቁጫ ህዝብ ተወካዮች፤ እሳቸው ጉዳያችንን ለመንግስት እንዲያሳውቁልን እንማፀናለን ብለዋል፡፡

Read 2018 times