Monday, 11 January 2016 12:00

አቃቂ የተያዘው 800 ኪ.ግ የአሳማ ሥጋ የገባበት አልታወቀም

Written by  ማህሌት ኪዳነወልድ
Rate this item
(6 votes)

      በህገ ወጥ መንገድ ወደ አዲስ አበባ ሊገባ የነበረ 800 ኪ.ግ የአሳማ ሥጋ አቃቂ ኬላ ላይ መያዙን የጠቆሙ ምንጮች፤ በአዲስ አበባ ቄራዎች ድርጅት እንዲወገድ ከተላከ በኋላ ሥጋው የገባበት መጥፋቱን ገልፀዋል፡፡
ድርጅታቸው የአሳማ ስጋውን መረከቡን የተናገሩት የአዲስ አበባ ቄራዎች ድርጅት ተወካይ ማኔጂንግ ዳይሬክተር አቶ ሸዋለፉ ይትባረክ፤ በነጋታው ግን ሥጋውን ከተጫነበት ፒክ አፕ መኪና ላይ ምን እንደወሰደው አልታወቀም ብለዋል፡፡
ድርጅቱ ጉዳዩን ከመረመረ በኋላም ለወቅቱ ማኔጂንግ ዳይሬክተርና ለሌሎች ሁለት የሥራ ክፍል ኃላፊዎች የማስጠንቀቂያ ደብዳቤ መስጠቱን የጠቆሙት አቶ ሸዋለፍ፣ የተሽከርካሪ ስምሪት ሰራተኞችም የምርት ሱፐርቫይዘርና ሌሎች ሰራተኞችም ጉዳያቸው ተመርምሮ ሲሆን እስከ 10 ቀን በሚደርስ የደሞዝ መቆረጥ ተቀጥተዋል ይላሉ፡፡
እንዲያም ሆኖ ግን ጉዳዩ አልተዘጋም፡፡ በአሁኑ ወቅት ፀረ ሙስና ኮሚሽን እየመረመረው ይገኛል ያሉት ማኔጂንግ ዳይሬክሩ፤ ድርጅቱም አስፈላጊውን ሰነዶች ለፀረ ሙስና ኮሚሽን ማስረከቡን ተናግረዋል፡፡ የሥጋው መጥፋት በህብረተሰቡ ላይ ጉዳት አያደርስም ወይ ብለን የጠየቅናቸው አቶ ሸዋለፍ፤ “ጉዳት ማድረሱ አያጠያይቅም፤ እንዲወገድ የተወሰነው ጎጂ ስለሆነ ነው፤ አንድም መቃጠል አሊያም ወደ ተረፈ ምርት መቀየር ነበረበት፡፡ ጠፍቷል ማለት ወደ ህብረተሰቡ ሄዷል ማለት ነው፡፡ ወደ ህብረተሰቡ ከሄደ ለምግብነት ውሏል ማለት ነው፡፡ ይህ ደግሞ በህብረተሰቡ ላይ ከባድ ጉዳት ያደርሳል፡፡” ሲሉ አስረድተዋል፡፡ በቅርቡ የድርጅቱ ማኔጂንግ ዳይሬክተርን ጨምሮ 4 ከፍተኛ የሥራ አመራሮች በሙስና ተጠርጥረው በቁጥጥር ስር እንደዋሉ መዘገባችን ይታወሳል፡፡

Read 4143 times