Saturday, 05 December 2015 08:46

አዋሽ ኢንተርናሽናል ባንክ ከ645 ሚ.ብር በላይ ትርፍ ማግኘቱን አስታወቀ

Written by  መንግሥቱ አበበ
Rate this item
(0 votes)

በድርቅ ለተጎዱና ለበጎ አድራጎት ማኅበራት 2.5 ሚ. ብር ለገሰ

   አዋሽ ኢንተርናሽናል ባንክ የዛሬ ሳምንት በሂልተን ሆቴል ባካሄደው 20ኛው የባለአክሲዮኖች ጠቅላላ ጉባኤ፣ ጁን 30, 2015 በተጠናቀቀው በጀት ዓመት ባደረገው እንቅስቃሴ ከታክስ በፊት 861.2 ሚሊዮን ብር፣ ከታክስ በኋላ 645.3 ሚሊዮን ብር የተጣራ ትርፍ ማግኘቱን አስታወቀ፡፡
ጁን 30, 2015 የተጠናቀቀው በጀት ዓመት በአጠቃላይ ለባንክ ኢንዱስትሪው፤ በተለይ ደግሞ ለአዋሽ ኢንተርናሽናል ባንክ ጥሩ አጋጣሚዎችና ፈታኝ ሁኔታዎች ነበሩት ያሉት የባንኩ የቦርድ ሊቀመንበር አቶ ታቦር ዋሚ፤የዓለም ኢኮኖሚ መሻሻል፣ በማደግ ላይ ወደአሉ አፍሪካ አገራት የውጭ ቀጥተኛ ኢንቨስትመንት ፍሰት፣አንፃራዊ የማክሮኢኮኖሚክና የአገራችን የፖለቲካ መረጋጋት የባንክ ቢዝነስ ለመስራት አመቺ እንደነበሩና በመላው ዓለም የኤክስፖርት ምርቶች ዋጋ መቀነስ (በተለይም የቡናና የሰሊጥ) በባንኮች የውጭ ምንዛሬ ግኝት ላይ ተፅዕኖ ነበረው በማለት ገልጸዋል፡፡
በዓመቱ የባንኩ እንቅስቃሴ አጠቃላይ ገቢ 2.3 ቢሊዮን ብር የተገኘ ሲሆን ካለፈው ዓመት ተመሳሳይ ወቅት ጋር ሲነፃፀር 19.8 በመቶ ብልጫ እንዳለውና በባንኩ ታሪክ ተመዝግቦ እንደማያውቅ ተናግረዋል፡፡ ከብድርና አድቫንስ 12.5 ቢሊዮን የደረሰ ሲሆን ይህም ከአምናው ተመሳሳይ ወቅት ጋር ሲተያይ የ36 በመቶ (3.3 ቢሊዮን ብር) ዕድገት ማሳየቱን፣ የባንኩ አጠቃላይ ተቀማጭ በ3.4 ቢሊዮን ብር  ወይም 21 በመቶ አድጎ 19.5 ቢሊዮን ብር፣ በዚህም የተነሳ የባንኩ አጠቃላይ ሀብት 25.2 ቢሊዮን ብር መድረሱን አስታውቀዋል፡፡
ባንኩ፣ ከታክስ በፊት ያገኘው አጠቃላይ ትርፍ ከ861.2 ሚሊዮን ብር የዘለለ፣ በ32.4 ሚሊዮን ብር ብልጫ እንዳለውና ከአምናው ተመሳሳይ ወቅት ጋር ሲተያይ በ3.4 በመቶ እንደሚበልጥ የጠቀሱት የባንኩ ፕሬዚዳንት አቶ ፀሐይ ሺፈራው፣ አንድ ዕጣ የሚያስገኘው የትርፍ ክፍያ ከአምናው ጥቂት ዝቅ ብሎ 445 ብር ሲሆን የአምናው 475 ብር ነበር ብለዋል፡፡
የባንኩ አጠቃላይ ወጪ 1.4 ቢሊዮን ብር የደረሰ ሲሆን ካለፈው ዓመት ጋር ሲነፃፀር የ31.8 በመቶ ብልጫ አለው፡፡ የወለድ ወጪ ከአምናው 34 በመቶ ጨምሮ 163.3 ሚሊዮን ብር የደረሰ ሲሆን ከባንኩ አጠቃላይ ወጪ ግማሽ ያህል እንደሚሆን የጠቀሱት አቶ ፀሐይ፣ ለተመረጡ ደረጃዎች የተደረገው የደሞዝና የጥቅማ ጥቅም ማስተካከያ፣ አዲስ የተከፈቱ ቅርንጫፍ ሰራተኞች ደሞዝ፣ የቢሮ ኪራይ ከፍተኛ መሆን፣ የአስተዳደራዊ ወጪዎች መናርና የአጠቃላይ እንቅስቃሴዎች ስፋት መጨመር አጠቃላዩን ወጪ አሳድገውታል ሲሉ ገልፀዋል፡፡
ለኅብረተሰቡ የምንሰጠውን አገልግሎት ተደራሽነት ለማስፋት በዓመቱ ባደረግነው እንቅስቃሴ 52 አዳዲስ ቅርንጫፎች ከፍተን የቅርንጫፎቻችንን ብዛት 202 አድርሰናል ያሉት ፕሬዚዳንቱ፣ ይህም ባንካችንን ከግል ባንኮች ቀዳሚ ያደርገዋል ብለዋል፡፡ አዋሽ ባንክ የግሉ የሆኑ 100 ኤቲኤሞችና 500 የግብይት መፈጸሚያ  ፖስ (POS) መሳሪያዎች፣ ከሌሎች የግል ባንኮች ጋር በጋራ የሚጠቀምባቸው 60 ኤቲኤሞችና 300 ፖስ ማሽኖች እንዳሉትና እነዚህን መሳሪያዎች በመጨመር ተደራሽነቱን ለማስፋት አስፈላጊ ሂደቶች ማጠናቀቁን ተናግረዋል፡፡
ባንኩ የራሱን ንብረት ለማፍራት ባደረገው እንቅስቃሴ፣ ልደታ አካባቢ እያሰራ ያለው ባልቻ አባነፍሶ ሕንፃ ግንባታ በቅርቡ እንደሚጠናቀቅ፣ በሀዋሳ ከተማ እየተሰራ ያለው ባለ ብዙ ፎቅ ግንባታ በጥሩ ሁኔታ እየሄደ መሆኑን አቶ ፀሐይ ገልጸዋል፡፡
በሌላ በኩል ባንኩ፣ ባለአክሲዮኖቹ በወሰኑት መሰረት፣ 2.5 ሚሊዮን ብር በዕርዳታ የለገሰ ሲሆን ለሙዳይ በጎ አድራጎት ማህበር 350ሺ ብር፣ ለክብረ አረጋውያን ምግባረ ሰናይ ድርጅት  500ሺ ብር፣ ለጥቁር አንበሳ ስፔሻላይዝድ ሆስፒታል 650ሺ ብር እና በድርቅ ለተጎዱ ወገኖቻችን የ1ሚ. ብር ዕርዳታ አበርክቷል፡፡ 

Read 3259 times