Friday, 11 September 2015 09:18

ኢህአዴግና ተቃዋሚዎች በስኬታቸው ላይ ማተኮርን መርጠዋል

Written by  አለማየሁ አንበሴ
Rate this item
(15 votes)

       ከወትሮው በተለየ ሁኔታ ገዢው ፓርቲ ኢህአዴግም ሆነ ዋነኞቹ ተቃዋሚ ፓርቲዎች ባለፈው ዓመት ቀላል የማይባሉ ችግሮችና ፈተናዎችን ቢጋፈጡም ስኬታቸው ላይ ማተኮርን የመረጡ ይመስላል፡፡ ሁለቱም ጐራዎች ዓመቱ በስኬት ማለፉን ገልፀዋል፡፡ የኢትዮጵያ ፌደራላዊ አንድነት መድረክ፤ የዓመቱ ዋነኛ እቅዱ በምርጫው መሳተፍ እንደነበር የጠቆሙት ሊቀመንበሩ ፕ/ር በየነ ጴጥሮስ፤ ፓርቲያቸው በተወዳደረባቸው የተለያዩ የአገሪቱ አካባቢዎች በሰላማዊ ሰልፍና ስብሰባዎች በ100ሺ ከሚቆጠሩ ሰዎች ጋር መገናኘት መቻላቸውን እንደ ከፍተኛ ስኬት እንደሚቆጥሩት ተናግረዋል፡፡ ለምርጫው ወደ 1ሺ ገደማ እጩዎች ማቅረባችንም ሌላው ስኬታችን ነው ይላሉ - ሊቀመንበሩ፡፡ የምርጫው ውጤት ግን በፖለቲካ ምህዳሩ መጥበብ ምክንያት ሙሉ ለሙሉ ስኬታማ አልነበረም - ብለዋል፡፡ መድረክ ከምርጫው በፊት ከገዢው ፓርቲ ጋር ለመደራደር አቅዶ እንደነበር የጠቆሙት ሊቀመንበሩ፤ ከገዥው ፓርቲ በኩል ፍላጎት ባለመኖሩ ግን ጥረቱ ሣይሳካ መቅረቱን ጠቁመዋል፡፡ “በዓመቱ ከያዝናቸው እቅዶች አብዛኛውን አሳክተናል፤ አመቱም የተሳካ ነበር ያሉት ደግሞ የኢትዮጵያ ዲሞክራሲያዊ ፓርቲ (ኢዴፓ) ፕሬዚዳንት ዶ/ር ጫኔ ከበደ ናቸው፡፡ በ5ኛው አገራዊ ምርጫ እጩ ለማስመዝገብ ያደረግነው ጥረት በእጅጉ የተሳካ ነበር የሚሉት ፕሬዚዳንቱ፤ “በገዥው ፓርቲ ተፅዕኖ ምክንያት በምርጫው ውጤት ማጣታችን ግን አሳዝኖናል” ብለዋል፡፡ በአዲስ ዓመት ፓርቲው አደረጃጀቱን በማስፋትና በንቃት በመንቀሳቀስ ለቀጣይ ምርጫ ዝግጅት እንደሚያደርግ ፕሬዚዳንቱ ጠቅሰው፤ ከሌሎች ፓርቲዎች ጋር በህብረት ለመስራት  እንደሚጥሩም ገልፀዋል፡፡
ባለፈው የግንቦት ምርጫ በአዲስ አበባ ከኢህአዴግ ቀጥሎ ከፍተኛ ውጤት ያስመዘገበው ሰማያዊ ፓርቲ በበኩሉ፤ መዋቅሩን በመዘርጋት ረገድ ስኬታማ እንደነበር ጠቁሟል፡፡ የፓርቲው ብሄራዊ ም/ቤት ሰብሳቢ አቶ ይድነቃቸው ከበደ፤ በምርጫው የስርአት ለውጥ ለማምጣት ቢያቅዱም እንዳልተሳካላቸው ተናግረዋል፡፡ “እቅዳችን የስርአት ለውጥ ማምጣት በመሆኑ ባለፈው ምርጫ ያገኘነው ውጤት ለቀጣይ ጉዞአችን ያግዘዋል” ብለዋል ሰብሳቢው፡፡ ኢህአዴግ በበኩሉ፤ ዓመቱ የ1ኛው እድገትና ትራንስፎርሜሽን እቅድ በስኬት የተጠናቀቀበትና ሃገሪቱን ወደ ተሻለ ምዕራፍ ያሸጋግራታል ተብሎ የታሰበው ሁለተኛው እቅድ ይፋ የሆነበት አመት በመሆኑ እንዲሁም 5ኛው አገራዊ ምርጫን በውጤታማነት በማጠናቀቁ 2007 ስኬታማ አመት ነበር ብሏል፡፡
ፓርቲው የመጀመሪያውን እቅድ አፈፃፀም ገምግሞ፣ ሁለተኛውን በተጠና መልኩ አዘጋጅቶ ለህዝብ ውይይት ማቅረቡን የጠቀሙት የኢህአዴግ ፅ/ቤት የህዝብና የውጪ ግንኙነት ዘርፍ ኃላፊ አቶ ደስታ ተስፋው፤ በዓመቱ የተከናወነው ምርጫም በሰፊ የህዝብ ተሳትፎ በስኬት ተጠናቋል  ብለዋል፡፡በህዝብ ውይይት ወቅትም ሆነ በ10ኛው የኢህአዴግ ጉባኤ ላይ የመልካም አስተዳደርና የልማት ተደራሽነት ጉድለቶች እንዳሉ መገለፁን የተናገሩት ኃላፊው፤ በቀጣይ በነዚህ ጉዳዮች ላይ በተለየ ትኩረት እንሰራለን ብለዋል፡፡ የድርጅቱ ቀጣይ እቅድ በጉባኤው የተላለፉትን የለውጥ ሃሳቦችና የእድገት እቅዱን ማሳካት ነው ያሉት ኃላፊው፤ የህዝቡን ተጠቃሚነት የሚያረጋግጡ ስራዎች እንሰራለን ብለዋል፡፡ ኢህአዴግና ተቃዋሚዎች፤ አዲሱ ዓመት ለመላው የኢትዮጵያ ህዝብ የለውጥና የብልፅግና እንዲሆን ተመኝተዋል፡፡  

Read 2485 times