Saturday, 11 July 2015 11:33

አዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ዛሬ 10 ሺህ የሚደርሱ ተማሪዎች ያስመርቃል

Written by  መንግሥቱ አበበ
Rate this item
(5 votes)

- ለስዊድኑ “ሲዳ” የላቀ አገልግሎት ሽልማት ይሰጣል
- ዩኒቨርሲቲው ከአፍሪካ ዩኒቨርሲቲዎች በ9ኛ ደረጃ ላይ ይገኛል
- ጅማ ዩኒቨርሲቲ 97 ተማሪዎችን በድህረ ምረቃ ፕሮግራም አስመርቋል
               
 
    የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ዛሬ 9851 ተማሪዎችን በመጀመሪያ፣ በሁለተኛና በሦስተኛ ዲግሪ በሚሌኒየም አዳራሽ ከ2፡00 ጀምሮ እንደሚያስመርቅ የዩኒቨርሲቲው የህዝብ ግንኙነት ጽ/ቤት አስታወቀ፡፡
የጽ/ቤቱ ዳይሬክተር አቶ አሰማኸኝ አስረስ በተለይ ለአዲስ አድማስ በሰጡት መግለጫ፤ ዩኒቨርሲቲው ዘንድሮ በ10 ኮሌጆችና በ12 ኢንስቲትዩቶች ያስተማራቸውን 9851 ተማሪዎች እንደሚያስመርቅ ጠቅሰው፤ እነዚህ ተመራቂዎች ዓመቱን ሙሉ በመስከረም፣ በታኅሣሥ፣ በየካቲትና በሐምሌ ወር ትምህርት ያጠናቀቁትን እንደሚያካትት ገልጸዋል፡፡
የዛሬ ተመራቂዎች በመደበኛ ፕሮግራም 5920፣ በመደበኛ የዶክትሬት (PHD) ትምህርት 228 (ከዚህ ውስጥ 8 በመቶ ሴቶች ናቸው)፣ በዩኒቨርሲቲው የሚያስተምሩ መምህራን ሁሉ በሚያስተምሩት ትምህርት መሰልጠን አለባቸው በሚለው አዲስ ፕሮግራም የሠለጠኑ 233 መምህራን፣ 1930 በማታው ክፍለ ጊዜና 1540 በክረምት ትምህርታቸውን ተከታትለው ያጠናቀቁ ናቸው ብለዋል፡፡
ከዘንድሮ ተመራቂዎች ውስጥ 6469 ተማሪዎች በመጀመሪያ ዲግሪ (ሴት 1774፣ ወንድ 4695) በሁለተኛና በሦስተኛ ዲግሪ (ፖስት ግራጁየት) 2658 ወንዶችና 724 ሴቶች እንደሆኑ ዳይሬክተሩ ጠቅሰው፣ ከዚህ ውስጥ 228ቱ ዶክተሮች እንደሆኑ ተናግረዋል፡፡ ይህን ያህል ቁጥር ያላቸው ዶክተሮች በማስመረቅ አአዩ ከአፍሪካ ቀዳሚ መሆኑንና አንዳንድ ድረ ገፆች በሚያወጡት መረጃ መሰረት፤ ከአፍሪካ ዩኒቨርሲቲዎች በ9ኛ ደረጃ ላይ እንደሚገኝ እንደሆነ አመልክተዋል፡፡
በየጊዜው የምናከናውነውን ሥራ ስለማናስተዋውቅ ነው እንጂ ደረጃችን ከዚህም ከፍ እንደሚል እናምናለን ያሉት አቶ አሰማኸኝ፣ በቅርብ ካሉ አገሮች የሚበልጡን የግብፅ፣ የኬንያ የታንዛኒያና የደቡብ አፍሪካ ዩኒቨርሲቲዎች ናቸው፡፡ እየሰራንባቸው ያሉትን ፕሮግራሞች በመፈተሸ (በመከለስ) የሚቀሩትን አስወግደን የሚጨመሩ አዳዲስ ፕሮግራሞች ለማካተት አቅደናል፡፡ አዳዲሶቹን ፕሮግራሞች ስንጀምርና ሥራዎቻችንን ስናስተዋውቅ ደረጃችን ከፍ ይላል፡፡ በአሁኑ ወቅት ከአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ በስተቀር ከ100 የአፍሪካ ዩኒቨርሲቲዎች ስም ዝርዝር ውስጥ የተጠቀሰ አንድም ኢትዮጵያዊ ዩኒቨርሲቲ የለም በማለት አስረድተዋል፡፡
በዘንድሮው የምረቃ ሥነ-ሥርዓት አዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ለማንም የክብር ዶክትሬት እንዳልሰጠ ዳይሬክተሩ ጠቅሰው፤ ዓለም አቀፉ የስዊድን የልማት ድርጅት (Sewden International Development Association – SIDA ሲዳ) እ.ኤ.አ ከ1980 ዓ.ም አንስቶ በተለያዩ ማህበራዊ ዘርፎች በእርሻ በትምህርት፤ በጤና… ላበረከታቸው ድጋፎች እውቅና ለመስጠት ዩኒቨርሲቲው ሲዳ በአገሪቷ ትምህርት እንዲዳብር የአንደኛ ደረጃ ት/ቤቶች በመገንባት ለተጫወተው ሚና የተለየ የአገልግሎት ሰርቪስ (Special Service Award) ይሰጣል ብለዋል፡፡
ከዘንድሮ ተመራቂዎች ከፍተኛውን ቁጥር (763) በመያዝ ሲቪል ኢንጂነሮች ቀዳሚ ናቸው፡፡ 380 ተማሪዎች ዘንድሮ ስለማይመረቁ ነው እንጂ ቀጥራቸው ከሺህ በላይ ይሆን ነበር ብለዋል፡፡ ምክንያቱ ደግሞ በ70/30 ቅበላ መሰረት ከ70 በላይ የተፈጥሮ ሳይንስ ተማሪዎች በመሆናቸው ነው፡፡
የወርቅ ሜዳሊያ ተሸላሚዎች 12 ሲሆኑ አራቱ ሴቶች ናቸው ያሉት ዳይሬክተሩ፤ ከፍተኛውን 4 ነጥብ ያመጣው አንድ ተማሪ ከተፈጥሮ ሳይንስ ኮሌጅ ነው ብለዋል፡፡ በዛሬው ምረቃ ለየት ያለው ነገር ሁለት ሴት የወርቅ ሜዳሊያ ተሸላሚዎች ለመለየት አለመቻል ነው፡፡ ኤልሳ ኪሮስ ወልዱና ኤልሳቤጥ ደሳለኝ ረጋሳ ያመጡት ነጥብ እኩል 3.64 ሆነ፡፡ በተለያዩ መመዘኛዎች ለመለየት ቢሞከርም አልተቻለም፡፡ ኤግዚቢሽን ወይም ሴሚናር አዘጋጅተው ገለጻ ያድርጉ፣ … የሚሉ ሀሳቦች ቀርበው ነበር፡፡ ግን ጊዜው ስላጠረ ይህም አልተቻለም፡፡ በመጨረሻ ሴኔቱ ሁለቱም ሴቶች የወርቅ ሜዳሊያ ይሸለሙ በማለት መወሰኑን አቶ አሰማኸኝ ገልፀዋል፡፡ ከ10    ኮሌጆችና ከ12 ኢንስቲትዩቶች ሴቶች ብቻ ተወዳድረው የተሻለ ነጥብ ያመጡ (Top Scorers) 12 ሴቶችም የወርቅ ሜዳሊያ ተሸላሚ ናቸው፡፡     
በሌላ በኩል ጅማ ዩኒቨርሲቲ በማስተር ኦፍ ቢዝነስ አድሚኒስትሬሽንና በማስተር ኦፍ ፐብሊክ ሄልዝ ያስተማራቸውን 97 ተማሪዎች ከትናት በስቲያ በሸራተን ሆቴል አስመርቋል፡፡ ዩኒቨርሲቲው በአዲስ አበባ በኤቢኤች ካምፓስ በሁለቱ የድህረ ምረቃ ፕሮግራሞች ካስመረቃቸው 97 ተማሪዎች መካከል 24ቱ ሴቶች ናቸው፡፡

Read 5015 times