Saturday, 10 January 2015 09:35

የህንድ የአይን ህክምና ማዕከል ከመንግሥት በቂ ድጋፍ አላገኘሁም አለ

Written by  ናፍቆት ዮሴፍ
Rate this item
(2 votes)

በህንድ አገር የሚገኘው ኦቨርሲስ ኢንፍራስትራክቸር አሊያንስ (OIA) የተባለው ኩባንያ በዘውዲቱ ሆስፒታል ግቢ ውስጥ ለሚሰጠው የበጐ ፈቃድ የአይን ህክምና አገልግሎት ከመንግሥት በቂ ድጋፍ እንደማይደረግለት ገለፀ፡፡
ኩባንያው በህንድ ከኢትዮጵያ ኤምባሲ ጋር በመተባበር በሶስት ከተሞች በኢትዮጵያ ያለውን ምቹ የኢንቨስትመንት አማራጮች ለህንድ ኢንቨስተሮች የሚያስተዋውቅ የጐዳና ላይ ትእይንት ማድረጉን አስታውቋል፡፡ ትናንት ረፋድ ላይ በሰጠው ጋዜጣዊ መግለጫ በዘውዲቱ ሆስፒታል ውስጥ የአይን ህክምና ማዕከል ከፍቶ አገልግሎት እየሰጠ መሆኑን አስታውሶ፤ መንግሥት አስፈላጊውን ድጋፍ ሳያደርግ፣ የተለያዩ አካላት ማዕከሉ ችግር እንዳለበት በማስመሰል መልካም ስራውን ለማጉደፍ የሚያደርጉት ሙከራ ተገቢ አለመሆኑን ገልጿል፡፡
ከዲሴምበር 15 ጀምሮ ኩባንያው ለአምስት ቀናት በህንድ ከተሞች ባደረገው የጐዳና ላይ ትእይንት ኢትዮጵያ ውስጥ ሰፊና ምቹ የኢንቨስትመንት አማራጮች እንዳሉ ለህንዳዊያን ባለሀብቶች ማስተዋወቁን ተከትሎ በህንድ የኢትዮጵያ አምባሳደር ገነት ዘውዴ የምስጋናና የአድናቆት ደብዳቤ መፃፋቸውን ጠቁሟል፡፡ አምባሳደሯ፤ OIA የኢትዮጵያን የኢንቨስትመንት ምቹነት ለማስተዋወቅ ያደረገውን እንቅስቃሴ አድንቀው፣  የህንድ ባለሀብቶች የተነገራቸውን የኢንቨስትመንት ምቹነት አይተው እንዲያረጋግጡ የጉብኝት ጉዞ እንደሚያዘጋጁ በደብዳቤው ላይ ቃል መግባታቸው በመግለጫው ላይ ተናግሯል፡፡
OIA የአይን ህክምና ማዕከል በህክምና ስህተት በታካሚዎች ላይ ጉዳት እያደረሰ መሆኑን የአይን ብርሃናቸውን ያጡ ታካሚዎችን በማነጋገርና በአዲስ አበባ ጤና ቢሮ የተደረገ የዳሰሳ ጥናት በመጥቀስ መዘገባችን የሚታወስ ነው፡፡
በትላንትናው እለት በሂልተን ሆቴል በተሰጠው ጋዜጣዊ መግለጫ፤ በህንድ የሚገኘው OIA ኩባንያ ዋና ስራ አስኪያጅና የOIA የአይን ህክምና ማዕከል የቦርድ አባል ሚስተር ቪኖድ ዲዮካር፤ የባለሙያዎቹ የጥናት ሪፖርት የማዕከሉን መጠነ ሰፊ አገልግሎት ግምት ውስጥ ያላስገባ ነው ብለዋል፡፡ ማዕከሉ ተገንብቶ የህክምና አገልግሎት መስጠት ከጀመረ ከ15 ወራት በላይ ማስቆጠሩን የጠቆሙት ሚስተር ቪኖድ፤ እስካሁን በማዕከሉ ከ22 ሺህ በላይ ህሙማን መታከማቸውንና ከሶስት ሺህ በላይ ህሙማን የቀዶ ህክምና አገልግሎት ማግኘታቸውን ገልፀዋል፡፡
“እስካሁን የቀዶ ህክምና ለማድረግ ካቀድነው አምስት ሺህ ሰው የሶስት ሺውን አሳክተናል” ያሉት ዋና ሥራ አስኪያጁ፤ አገልግሎቱን ካገኙት ከሶስት ሺህ ሰዎች 10 እና 15 ሰዎች እይታቸውን ሊያጡ የቻሉት እድሜያቸው ከ65 አመት በላይ በመሆኑ፣ የስኳር፣ የልብ፣ የደም ግፊትና እድሜን ተከትለው በሚመጡ በሽታዎች እንጂ በህክምና ስህተት እንዳልሆነ ተናግረዋል፡፡
የዶክተሮችን የተጋነነ የደሞዝ ክፍያ በተመለከተም፤ ቀድሞ የተፈራረሙበትና አሁን የሚከፈላቸው በጋዜጣው ላይ እንደተገለፀው መሆኑን አምነው ስራውን ለመጀመር በተስማሙበት 2008 እና 2009 ዓ.ም የነበረው የውጭ ምንዛሪና አሁን ያለው የተለያየ በመሆኑ በ2000 ዶላር ደሞዝ በሚሰሩ ዶክተሮች ማዕከሉን ማንቀሳቀስ ባለመቻሉ የደሞዝ ማሻሻያው መደረጉን ተናግረዋል፡፡ ብቃት በሌላቸው ሃኪሞች ህክምና ይሰጣል የተባለው ሁለቱ ዶክተሮችና ሶስቱ ረዳቶቻቸው የትምህርት ዝግጅታቸው፣ የስራ ልምዳቸው ታይቶና ብቃታቸው ተረጋግጦ ፈቃድ ያገኙ መሆናቸውን የገለፁት ሥራ አስኪያጁ፤ ማዕከሉ ብዙ ችግሮችን ተቋቁሞ እንደሚሰራም ጠቅሰዋል፡፡ ከመንግሥት በቂ ባለሙያ አለመመደቡ፣ ያሉትም ባለሙያዎች በኢትዮጵያ ህግና የስራ ሰዓት መጠቀማቸው፣ ለስልጠናና ለመሰል ጉዳዮች እየተጠሩ ስራ አቁመው 10 እና 15 ቀን እየቆዩ መምጣታቸውና በየጊዜው መቀያየራቸው ለስራው እንቅፋት እንደሆነም ገልፀዋል፡፡
ዘውዲቱ የመደባቸው ባለሙያዎች ለምሳ 5፡30 ወጥተው 8፡00 ሰዓት ይመለሳሉ፤ ህንዳዊያኑ ሙሉ ሰዓታቸውን ይሰራሉ፣ ቅዳሜ ኢትዮጵያዊያኑ ግማሽ ቀን ሲሰሩ ህንዳዊያኑ ሙሉ ቀን ይሰራሉ፤ ከዚህም ሌላ ለስልጠና ለረጅም ቀናት መሄዳቸውና መቀያየራቸው የእውቀት ሽግግሩና የአቅም ግንባታ ስራው በአግባቡ እንዳይከናወን ችግር ፈጥሯል ብለዋል ሚስተር ቪኖድ፡፡
ማዕከሉ በአምስት የቦርድ አባላት የሚመራ ሲሆን ከዘውዲቱ ሆስፒታል፣ ከOIA፣ ከቀበሌ፣ ከገንዘብ ሚኒስቴርና ከአዲስ አበባ የምግብ የመድሃኒትና ጤና ክብካቤ ቁጥጥር ባለስልጣን የተውጣጡ እንደሆኑም ተናግረዋል፡፡ በየጊዜው የቦርድ ስብሰባ ሲኖር አባላቱ ተሟልተው እንደማይገኙ የተናገሩት ሥራ አስኪያጁ፤ ባለፈው ሰኞ በነበረው የቦርድ ስብሰባ እንኳን ከአምስት አባላት ሶስቱ ብቻ እንደተገኙና ቀሪዎቹ በተደጋጋሚ ቢደወልላቸው ምላሽ እንዳልሰጡ ገልፀው መንግስት በቀጣይ በቂ ባለሙያ በመመደብ፣ የስራ ፈቃዳችንን በማደስና በሁሉም በኩል አስፈላጊውን ድጋፍ በማድረግ እንዲያግዘን እንጠይቃለን ብለዋል፡፡
ማዕከሉ በኢትዮጵያ መንግስትና በቦርድ የሚመራ በመሆኑ ሁሉም ኃላፊነቱን ሳይወጣ የሚከሰቱ ችግሮችን በማዕከሉ ላይ ማላከክ አግባብ እንዳልሆነ የገለፁት ሥራ አስኪያጁ፤ የጠየቅናቸው ነገሮች እስከተሟሉ ድረስ በበጐ ፈቃደኝነትን አገልግሎት መስጠታችንን እንቀጥላለን፤ መንግስት በራሱ ባለሞያዎች ማዕከሉን ማንቀሳቀስ ሲችል አስረክበን የመውጣት ፍላጐትም አለን ሲሉ አብራርተዋል፡፡ ማዕከሉ እስካሁን 70 በመቶ ለሆኑ ታካሚዎች ከክፍያ ነፃ ህክምና የሚሰጥ መሆኑን ገልፀው፤ 30 በመቶውን የመክፈል አቅም ላላቸው የግል ታካሚዎች አገልግሎት እንደሚሰጥ እስካሁንም 550 ወላጅ አልባ ህፃናትን በነፃ ማከሙን፣ ከ751 በላይ የቀበሌ የነፃ ህክምና ወረቀት ላመጡ ታካሚዎችም አገልግሎት መስጠቱን እንዲሁም ከ10 ጊዜ በላይ በዶ/ር ጋንዲ የሚመራ ስልጠናና ወርክሾፖችን ማካሄዱንና ሌሎችንም ስኬቶች እንዳስመዘገበ ሚስተር ቪኖድ ለጋዜጠኞች ተናግረዋል፡፡

Read 1753 times