Monday, 05 January 2015 07:34

የቅ/ማርያም ገዳም አስተዳደር የገንዘብ ምዝበራውን አስተባበለ

Written by  መታሰቢያ ካሳዬ
Rate this item
(3 votes)

         በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን የመንበረ ፓትሪያሪክ ቅ/ማርያም ገዳም አስተዳደር የሥራ ኃላፊዎች፤ በገዳሟ ውስጥ በሚሊዮኖች ብር የሚገመት የገንዘብ ምዝበራ ተፈፅሟል መባሉን አስተባበሉ፡፡
የገዳሟ አስተዳደር አባ ገብረትንሳኤ አብርሃን ጨምሮ የገዳሟ ዋና ፀሐፊ መ/ሥ/ ኃ/ጊዮርጊስ እዝራ፣ ገንዘብ ያዥ መ/ታ ይትባረክ ወልደስላሴና ተቆጣጣሪው መ/ር ምሥራቅ ዘውዴ፤ ባለፈው ሳምንት በአዲስ አድማስ ጋዜጣ “በመንበረ ፓትርያርኩ ቅ/ማርያም ገዳም በሚሊዮኖች የሚገመት ገንዘብ መመዝበሩ ተገለፀ” በሚል የወጣው ዘገባ ከእውነት የራቀ ነው ብለዋል፡፡ የአስተዳደር ኃላፊዎቹ እንደጠቆሙት፤ በገዳሟ በየሁለት ወሩ የሙዳይ ምፅዋት ቆጠራም የሚደረግ ሲሆን ባለፈው ህዳር ወር ቆጠራው አገረ ስብከቱ ባስመረጣቸውና 6 አባላት ባሉት ኮሚቴ እንዲካሄድ ተወስኖአል፡፡ ህዳር 19 እና ህዳር 22 ለሁለት ቀናት በተካሄደ ቆጠራ በድምሩ 626.078 ብር የተገኘ ሲሆን በዘገባው ላይ ከ826 ሺ ብር በላይ ተብሎ የተገለፀው ስህተት ነው ብለዋል፡፡
ከንብረት ሽያጭና በሞዴል 30 ከተሰበሰቡ ገቢዎች በአጠቃላይ በህዳር ወር ለገዳሟ ገቢ የሆነው ገንዘብ 831.589.50 ሣንቲም ብቻ ነው ያሉት ኃላፊዎቹ፤ ከ1.2 ሚሊዮን ብር በላይ ገቢ እንደተገኘ ተደርጐ መዘገቡም ከእውነት የራቀ ነው ብለዋል፡፡ ባለፈው ሳምንት በወጣው ዜና፤ ለሀገረ ስብከቱ መከፈል የሚገባው የ20 በመቶ ውዝፍ ዕዳ ሳይፈፀም አሁን በካዝና ያለው ብር 129 ሺ ብር ብቻ እንደሆነ የጠቀሱት ማህበረ ካህናቱ፤ በህዳሩ ቆጠራ የተገኘው ገንዘብ ገዳሟ በየዓመቱ በሚሊዮኖች የሚቆጠር ብር ስትመዘበር እንደኖረች ያሳያል ማለታቸው መዘገቡ ይታወሳል፡፡ኃላፊዎቹ በበኩላቸው፤የገዳሟ ገቢና ወጪ በህጋዊ አሠራርና በሰነዶች በተደገፈ መንገድ እየተሠራ ባለበት ሁኔታ ግልፅነትና ተጠያቂነት በጐደለው አሠራር ገዳሟ በአስተዳደር ኃላፊዎችና ሰራተኞች በሚሊዮኖች የሚቆጠር ገንዘብ እየተመዘበረች ነው መባሉም እንዳሣዘናቸው ገልፀዋል፡፡ የገዳሟ ሰበካ ጉባዔ ኃላፊነቱን በአግባቡ መወጣት ባለመቻሉና የሥራ ጊዜው በማለፉ እንዲቀየር መጠየቁን በተመለከተ የአስተዳደር ኃላፊዎቹ ሲናገሩም፤ “በእርግጥ የሰበካ ጉባዔው የሥራ ዘመን ተጠናቋል፤ ይሁን እንጂ አሁን በልማት ሥራ ላይ በመሆኑና የተጀመረውን የህንፃ ግንባታ ሥራ ከዳር ማድረስ ስለሚገባው፣ ለሥራ እንቅፋት የሚሆኑ ችግሮች እንዳይፈጠሩና ልማቱ እንዲቀጥል ታስቦ የሥራ ዘመኑ ላልተወሰነ ጊዜ እንዲራዘም ተደርጓል ብለዋል፡፡ በዚህ ሰበካ ጉባዔ ያለ አግባብ ወጪ ሆኗል ተብሎ የተገለፀው 440ሺ ብር ለሠራተኛ ደመወዝ፣ ለአገረ ስብከቱና ለልዩ ልዩ ጉዳዮች የወጣና ህጋዊ ደረሰኞችና ሰነዶች የሚቀርቡበት በመሆኑ ውንጀላው ያለአግባብ የቀረበ ነው ሲሉም አስተባብለዋል፡፡ “ጥቅማቸው የተነካባቸው የገዳሚቱ አስተዳደር ሠራተኞች የቆጠራ ኮሚቴውን ለማፍረስ ‹ማህበረ ቅዱሣንና ግንቦት ሰባት ናችሁ፤ ምርጫውን ለማወክ ትንቀሳቀሳላችሁ እያሉ ያስፈራራሉ› በሚል የተዘገበውን አስመልክተው በሰጡት ምላሽ፤ “እኛ የፖለቲካ ድርጅት አይደለንም፤ እንዲህ የምንልበት አንዳችም ምክንያት አይኖረንም፡፡ ሠራተኞችን የማዛወር ሥልጣን ያለው አገረ ስብከቱ በመሆኑ እኛ እናዛውራችኋለን በማለት ልናስፈራራ የምንችልበት ሁኔታም አይኖርም” ብለዋል፡፡ የማህበር ካህናቱንና የልማት ኮሚቴውን ጥያቄ ተከትሎ ፓትሪያርኩ በሰጡት መመሪያ፤ ሰበካ ጉባዔው የሥራ ክንውን ሪፖርቱን እንዲያቀርብ፣ የአዲስ ሰበካ ጉባዔ ምርጫ እንዲካሄድ፣ የገዳሚቱ ገቢና ወጪ ሂሣብ በአስቸኳይ በውጪ ኦዲተር እንዲጣራ፣ የተጓተተው ህንፃ ግንባታ እንዲቀጥል መመሪያ ተሰጠ በተባለው ጉዳይም የአስተዳደር ኃላፊዎቹ በጽሑፍ የደረሳቸው ነገር እንደሌለ ጠቁመው በቃል ግን እንዲህ ብታደርጉ ጥሩ ነው፤ ተብሎ እንደ የተነገራቸው ገልፀዋል፡፡

Read 2309 times