Saturday, 03 January 2015 10:34

በሽብር በተከሰሱት የተቃዋሚ አመራሮች መቃወሚያ ላይ አቃቤ ህግ ምላሽ ሰጠ

Written by  አለማየሁ አንበሴ
Rate this item
(5 votes)

   በተለያዩ የሽብር ድርጊቶች ተሣትፈዋል በሚል የተከሰሱት የተቃዋሚ ፓርቲ አመራሮችና ግለሰቦች ባቀረቡት የክስ መቃወሚያ ላይ አቃቤ ህግ በጽሑፍ ምላሽ የሰጠ ሲሆን ፍ/ቤቱም መቃወሚያው መርምሮ ብይን ለመስጠት ቀጥሯል፡፡ አቃቤ ህግ በ5 ነጥቦች ከፋፍሎ በሰጠው ምላሽ፤ “ሁሉም መቃወሚያዎች ህጋዊ ምክንያቶች ስለሌላቸው ውድቅ ይደረጉልኝ” ሲል ፍ/ቤቱን ጠይቋል፡፡“ግንቦት 7” ነኝ እያለ  ራሱን የሚጠራው ድርጅት ሽብርተኛ ድርጅት የተባለበት አግባብ በክሱ በግልጽ አልተቀመጠም፣ በፍትህ አካል ሽብርተኛ ስለመሰኘቱ የተሰጠ ውሣኔ በማስረጃ ይቅረብ ሲሉ የተከሳሽ ጠበቆች ለቀረቡት መቃወሚያ አቃቤ ህግ በሰጠው ምላሽ፤ “ግንቦት 7 በይፋ በፓርላማ ሽብርተኛ ድርጅት ተብሎ ተሰይሟል፣ ይህም በይፋ ይታወቃል” ብሏል፡፡
የሽብርተኛ ቡድኑን አላማና ተግባር የሚያሳይ የማስረጃ ሰነድ ተያይዞ መቅረብ ነበረበት በሚል ከጠበቆች ለቀረበው አቤቱታም አቃቤ ህግ “በመቃወሚያ ደረጃ ሊነሳ የማይችል ነው፤ አስፈላጊ ያልናቸውን ማስረጃዎች
አቅርበናል” ብሏል፡፡ የተከሳሽ ጠበቆች፤ በክሱ ዝርዝር የተገለፁትን አመራር አባላትና ግለሰቦች ሽብርተኝነት የተፈረደባቸው ወይም የተላለፈባቸው ውሳኔ መቼ፣ የት እና ምን ተብሎ እንደተወሰነባቸው በማስረጃ ተያይዞ እንዲጠቀስ ይታዘዝልን ሲሉ ላቀረቡት መቃወሚያ አቃቢ ህግ፤ ግለሰቦቹ የሽብር ድርጅት አባላትና አመራር መሆናቸውን በማስረጃ የምናረጋግጥ ይሆናል ብሏል፡፡ ተከሳሾቹ በሽብር ድርጅቱ ያላቸው ቦታ፣ የሚሰሩት ስራ በዝርዝር መገለፁን አቃቤ ህግ ጠቅሶ ተግባራቸው አልተገለጸም ለሚለው መቃወሚያ ምላሽ ሰጥቷል፡፡ ፍ/ቤቱም በተከሳሾች የቀረበውን መቃወሚያና የአቃቤ ህግን ምላሽ ጨምሮ ብይን ለመስጠት መዝገቡን ለጥር
26 ቀን 2009 ዓ.ም ቀጥሯል በሌላ በኩል ተከሣሾቹ፤ በማረሚያ ቤት ሌሊት በተደረገ ድንገተኛ ፍተሻ ንብረታችን ተወስዶብናል ሲሉ ላቀረቡት አቤቱታ ምላሹን በትናንትናው እለት እንዲያቀርብ ታዞ የነበረው የማረሚያ ቤቱ አስተዳደር፤ የተከሳሾች አቤቱታ ከመቅረፀ ድምጽ ወደ ጽሑፍ ተገልብጦ ስላልተሰጠው ማቅረብ እንዳልቻለ ለማወቅ ተችሏል፡፡ ፍ/ቤቱም የተከሳሾች አቤቱታ በጽሑፉ እንዲቀርብለትና ማረሚያ ቤቱ ምላሹን ይዞ እንዲቀርብ በድጋሚ ለጥር 7 ቀን 2007 ዓ.ም ቀጥሯል፡፡ የአንድነት ፓርቲ የህዝብ ግንኙነት ኃላፊ አቶ ሃብታሙ አያሉው እና የድርጅት ጉዳይ ም/ኃላፊው አቶ ዳንኤል ሺበሺ፣ የሰማያዊ ፓርቲ የብሄራዊ ም/ቤት ምክትል ሰብሳቢ አቶ የሽዋስ አሰፋ እና የአረና  ፓርቲ አመራር አባል አቶ አብርሃ ደስታን ጨምሮ 10 ግለሰቦች በኢትዮጵያ መንግስት አሸባሪ ተብሎ በተሰየመው ግንቦት 7 ድርጅት ውስጥ አባል በመሆን የተለያዩ የሽብር ድርጅቶችን ለመፈጸም ሲንቀሳቀሱ ነበር በሚል ክስ እንደተመሰረተባቸው
ይታወሳል፡፡

Read 2310 times