Monday, 08 December 2014 14:04

ጋዜጠኞችና ጦማሪያን ተለዋጭ ቀጠሮ ተሰጣቸው

Written by  ናፍቆት ዮሴፍ
Rate this item
(2 votes)

“አቃቤ ህግ አሻሽል የተባለው ክስ የተሻሻለ ነገር የለውም” ጠበቆች

   ከሰባት ወራት በፊት በአገሪቱ ላይ ሽብር ለማስነሳትና የሽብር ሴራውን ለመተግበር ሲንቀሳቀሱ ተደርሶባቸዋል በሚል በአሸባሪነት ወንጀል ክስ ተመስርቶባቸው በእስር ላይ በሚገኙት ሶስት ጋዜጠኞችና ስድስቱ ጦማሪያን ጉዳይ ላይ ብይን ለመስጠት ለባለፈው ረቡዕ ተቀጥሮ የነበረ ፍ/ቤት ለታህሳስ 7 ተለዋጭ ቀጠሮ ሰጥቷል፡፡ የተከሳሾቹ ጠበቆች፤ አቃቤ ህግ ያቀረበው ክስ የተሻሻለ ነገር እንደሌለው ለፍ/ቤት ገልፀዋል፡፡
ባለፈው ችሎት ተከሳሾቹ አቃቤ ህግ የከሰሰበትን የወንጀል ድርጊት ለመፈፀማቸው የሚያረጋግጥ መረጃ ባለመገኘቱ፣ ፍ/ቤቱ ተከሳሾችን ከወንጀል ክስ ነጻ አድርጐ ክሳቸው በአሸባሪነት ብቻ እንዲታይ መወሰኑ የሚታወስ ሲሆን አቃቤ ህግ በሽብርተኝነት ያቀረበባቸው ክስ ላይ ብይን ለመስጠት ላለፈው ረቡዕ ቀጠሮ ይዞ ነበር፡፡ የተከሳሽ ጠበቆች “የብይኑ ግልባጭ ከጽ/ቤት ስላልደረሰን፣ ከደረሰን በኋላ አይተንና ተወያይተን መቃወሚያችንን በፅሁፍ እንድናቀርብ ተለዋጭ ቀጠሮ ይሰጠን” ብለው ቢያመለክቱም ፍ/ቤቱ “ግልባጭ አለመስጠት የአስተዳደር ጉዳይ በመሆኑ ከአስተዳደሩ ጋር ጨርሱ፤ እኛ ግን ክሱን በንባብ እናሰማለን” በማለት አቃቤ ህግ አሻሽዬዋለሁ ያለውን 10 ገፅ የክስ መዝገብ ለተከሳሾች በፅሁፍ አሰምቷል፡፡
አቃቤ ህግ ባቀረበው ክስ፤ ተከሳሾች በአገሪቱ ላይ ሽብር ለመንዛት ከግንቦት ሰባት አሸባሪ ቡድን ጋር በህቡዕ በመገናኘት፣ ሽብሩን የሚያስፈፅሙበትን ስልጠና በአገር ውስጥና በውጭ በመውሰድ፣ ከአሸባሪ ቡድኑ ገንዘብ በመቀበል፣ የሴኩዩሪቲ ኢንቦክስ ስልጠና በመውሰድና የስራ ድርሻ በመከፋፈል፤ ህገ-መንግስቱንና ህገ-መንግስታዊ ስርዓቱን በህገ ወጥ መንገድ ለመጣል ሲንቀሳቀሱ ተደርሶባቸዋል ብሏል፡፡ በዚህም በፀረ ሽብር አዋጁ አንቀፅ ሶስት ንዑስ አንቀፅ ሁለት እና ንዑስ አንቀፅ ሰባት ላይ የተጠቀሱትን በመተላለፍ የሃገሪቱን ሰላም ለማናጋት፣ ህዝቡንና አገሪቱን ለማሸበር ተንቀሳቅሰዋል ሲል በክስ መዝገቡ ላይ ጠቅሷል፡፡  ከተከሳሽ ጠበቆች አንዱ የሆኑት አቶ አመሃ መኮንን በበኩላቸው፤ በፅሁፍ የቀረበው ክስ ላይ ከቀድሞው የተለየና የተሻሻለ  አንድም አዲስ ነገር እንደሌለና ፍ/ቤቱ ለአቃቤ ህግ ክሱን አሻሽሎ እንዲያመጣ የሰጠው ትዕዛዝ እንዳልተተገበረ ተናግረዋል፡፡ “ፍ/ቤቱ የሽብር ሴራ ሲጠነስሱና ሲንቀሳቀሱ የተገኙበት ቦታና ሰዓት እንዲገለፅ ትዕዛዝ ቢሰጥም አቃቤ ህግ ይህን አላደረገም” ብለዋል - አቶ አመሃ፡፡
አቃቤ ህግ ባቀረበው የክስ ፅሁፍ ላይ በርካታ የፊደል ግድፈት የታየ በመሆኑ ተስተካክሎ እንዲቀርብ የታዘዘ ሲሆን ጠበቆች ይህን የክስ ፅሁፍ በጽ/ቤት በኩል ለመውሰድ ጠይቀው  ማግኘት ባለመቻላቸው ፍ/ቤቱ ትዕዛዝ እንዲሰጥላቸው ጠይቀዋል፡፡ ፍ/ቤቱም መልሳችሁን ከአስተዳደሩ ጠይቁና እምቢ ካሏችሁ አመልክቱ የሚል ምላሽ ለጠበቆች ሰጥቷል፡፡
ብይኑና የአቃቤ ህግ የክስ ቻርጅ የታይፕ ግድፈት ተስተካክሎ ሲደርሰን የክሰ መቃወሚያችንን በፅሁፍ ለማቅረብ ተለዋጭ ቀጠሮ ይሰጠን ሲሉ የተከሳሽ ጠበቆች ፍ/ቤቱን በጠየቁት መሰረት፣ የክስ መቃወሚያውን ለማድመጥ ለታህሳስ 7 ተቀጥሯል፡፡
ይህ በእንዲህ እንዳለ የሴት ተከሳሾችን የመብት ጥሰት በተመለከተ ጠበቆቻቸው አቤቱታ ሲያቀርቡ የቆዩ መሆኑ የሚታወስ ሲሆን የወዳጅ ዘመድ የመጠየቂያ ሰዓት ከ10 ደቂቃ ወደ አንድ ሰዓት እንዲራዘም መደረጉንና ይህም እንዲተገበር ከማረሚያ ቤቱ ጋር መነጋገራቸውን ጠበቃው አቶ አመሃ መኮንን ለጋዜጠኞችና ለተከሳሽ ቤተሰቦች ከችሎት በኋላ ገልፀዋል፡፡  

Read 1366 times Last modified on Monday, 08 December 2014 14:19